ኤፌሶን 1:7-12
ኤፌሶን 1:7-12 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በእርሱም እንደ ቸርነቱ ብዛት በደሙ ድኅነትን አገኘን፤ ኀጢአታችንም ተሰረየልን። ይኸውም በፍጹም ጥበብና ምክር ለእኛ አብዝቶ ያደረገው ነው። እንደ ወደደም በእርሱ የወሰነውን፥ የፈቃዱን ምሥጢር ገለጠልን። የሚደርስበትንም ጊዜውን ወሰነ፤ በሰማይና በምድር ያለውም ሁሉ ይታደስ ዘንድ ክርስቶስን በሁሉ ላይ አላቀው። እንደ ፈቃዱ ምክር ሁሉን የሚሠራ እንደ እርሱ አሳብ አስቀድመን የተወሰን በእርሱ ርስትን ተቀበልን። ይኸውም አስቀድመን በክርስቶስ ኢየሱስ ተስፋ ያደረግን እኛ ለክብሩ ምስጋና እንሆን ዘንድ ነው።
ኤፌሶን 1:7-12 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በርሱም እንደ እግዚአብሔር ጸጋ ባለጠግነት መጠን፣ በደሙ በተደረገ ቤዛነት፣ የኀጢአት ይቅርታ አገኘን፤ ጸጋውንም በጥበብና በማስተዋል ሁሉ አበዛልን። በክርስቶስ ያቀደውንም የፈቃዱን ምስጢር እንደ በጎ ሐሳቡ እንድናውቅ አደረገ። በዘመን ፍጻሜ ይሆን ዘንድ ያለው ሐሳቡ፣ በሰማይም ሆነ በምድር ያሉትን ነገሮች ሁሉ ራስ በሆነው በክርስቶስ ሥር ለመጠቅለል ነው። ሁሉን በፈቃዱ ምክር መሠረት እንደሚሠራው እንደ እርሱ ዕቅድ፣ አስቀድሞ የተወሰንን እኛ ደግሞ በርሱ ተመርጠናል፤ ይኸውም በክርስቶስ ተስፋ በማድረግ የመጀመሪያ የሆንነው እኛ ለክብሩ ምስጋና እንሆን ዘንድ ነው።
ኤፌሶን 1:7-12 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በውድ ልጁም፥ እንደ ጸጋው ባለ ጠግነት መጠን፥ በደሙ የተደረገ ቤዛነታችንን አገኘን እርሱም የበደላችን ስርየት። ጸጋውንም በጥበብና በአእምሮ ሁሉ አበዛልን። በክርስቶስ ለማድረግ እንደ ወደደ እንደ አሳቡ፥ የፈቃዱን ምሥጢር አስታውቆናልና፤ በዘመን ፍጻሜ ይደረግ ዘንድ ያለው አሳቡም በሰማይና በምድር ያለውን ሁሉ በክርስቶስ ለመጠቅለል ነው። እንደ ፈቃዱ ምክር ሁሉን የሚሠራ እንደ እርሱ አሳብ፥ አስቀድመን የተወሰንን በክርስቶስ ደግሞ ርስትን ተቀበልን። ይኸውም፥ በክርስቶስ አስቀድመን ተስፋ ያደረግን እኛ ለክብሩ ምስጋና እንሆን ዘንድ ነው።
ኤፌሶን 1:7-12 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከእግዚአብሔር ጸጋ ሙላት የተነሣ በልጁ ደም ተዋጅተን የኃጢአታችንን ይቅርታ አገኘን። ጸጋውንም በጥበብና በዕውቀት ሁሉ አብዝቶ አፈሰሰልን። እግዚአብሔር በቸርነቱ በክርስቶስ አማካይነት አስቀድሞ ባቀደው መሠረት የፈቃዱን ምሥጢር እንድናውቅ አደረገ። ጊዜው ሲደርስ እግዚአብሔር በሥራ ላይ የሚያውለው ዕቅድ በሰማይና በምድር ያሉት ፍጥረቶች ሁሉ ተጠቃለው በአንዱ በክርስቶስ ሥልጣን ሥር እንዲሆኑ ነው። ሁሉን ነገር በራሱ ፈቃድ የሚሠራ እግዚአብሔር አስቀድሞ በዐቀደልን መሠረት በክርስቶስ አማካይነት የእርሱ ወገኖች እንድንሆን መረጠን። ይህም የሆነው ክርስቶስን ተስፋ በማድረግ መጀመሪያዎች የሆንነው የእግዚአብሔርን ክብር በምስጋና እንድንገልጥ ነው።
ኤፌሶን 1:7-12 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በእርሱም እንደ ጸጋው ባለጠግነት መጠን፥ በደሙ ቤዛነታችንን አገኘን፤ የበደላችንም ይቅርታ ሆነ። ጸጋውንም አበዛልን። በጥበብና በአእምሮ ሁሉ፥ በክርስቶስ ለማድረግ የወደደውን የአሳቡን፥ የፈቃዱን ምሥጢር አስታውቆናል፤ በሰማይና በምድር ያለውን ሁሉ በክርስቶስ ለመጠቅለል፥ በዘመን ፍጻሜ እንዲሆን እንዳቀደው፥ እንደ ፈቃዱና እንደ ምክሩ ሁሉን የሚያከናውን እንደ እርሱ ዓላማ የተወሰንን በክርስቶስ በርስትነት ተቀበልን። ይኸውም በክርስቶስ አስቀድመን ተስፋ ያደረግን እኛ ደግሞ ለክብሩ ምስጋና እንድንሆን ነው።