መክብብ 9:1-12
መክብብ 9:1-12 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ይህን ሁሉ በአንድነት ለልቤ ሰጠሁ፥ ጻድቃንና ጠቢባን ሥራዎቻቸውም በእግዚአብሔር እጅ እንደ ሆኑ፥ ይህን ሁሉ ልቤ ተመለከተች፤ ፍቅር ወይም ጥል ቢሆን ሰው አያውቅም፥ ሁሉ ወደ ፊታቸው ነው። በሁሉም ከንቱነት አለ፥ የጻድቁና የበደለኛው፥ የመልካሙና የክፉው፥ የንጹሑና የርኩሱ፥ መሥዋዕትን የሚሠዋውና የማይሠዋው፥ የመልካሙና እንዲሁ የኀጢአተኛው፥ የመሐላኛውና እንዲሁ መሐላን የሚፈራው ድርሻ አንድ ነው። ከፀሓይ በታች የተደረገው ክፉ ሁሉ ለሁሉ ነው፤ የሁሉ ድርሻ አንድ ነውና። ደግሞም የሰው ልጆች ልብ ክፋትን ትሞላለች፥ በሕይወታቸው ሳሉ ሁከት በልባቸው አለ፥ ከዚያም በኋላ ወደ ሙታን ይወርዳሉ። ከሕያዋን ጋር አንድነት ያለው ማንም ሰው ተስፋ አለውና ከሞተ አንበሳ ያልሞተ ውሻ ይሻላል። ሕያዋን እንዲሞቱ ያውቃሉና፤ ሙታን ግን አንዳች አያውቁም፤ መታሰቢያቸውም ተረስቶአልና ከዚህ በኋላ ዋጋ የላቸውም። ፍቅራቸውና ጥላቸው ቅንአታቸውም በአንድነት እነሆ፥ ጠፍቶአል፤ ከፀሓይ በታችም በሚሠራው ነገር ሁሉ ለዘለዓለም ዕድል ፈንታ ከእንግዲህ ወዲህ የላቸውም። እግዚአብሔር ሥራህን ተቀብሎታልና፦ ና እንጀራህን በደስታ ብላ፥ በበጎ ልቡናም የወይን ጠጅህን ጠጣ። ሁልጊዜ ልብስህ ነጭ ይሁን፤ ቅባትም ከራስህ ላይ አይታጣ። በሕይወትህ፥ አንተም ከፀሓይ በታች በምትደክምበት ድካም ይህ ዕድል ፈንታህ ነውና ከንቱ በሆነ በሕይወትህ ዘመን ሁሉ፥ ከፀሓይ በታች በሰጠህ፥ በከንቱ ዘመንህ ሁሉ፥ ከምትወድዳት ሚስትህ ጋር ደስ ይበልህ። አንተ በምትሄድበት በሲኦል ሥራና ዐሳብ፥ ዕውቀትና ጥበብ አይገኙምና እጅህ ለማድረግ የምትችለውን ሁሉ እንደ ኀይልህ አድርግ። እኔም ተመለስሁ፥ ከፀሓይ በታችም ሩጫ ለፈጣኖች፥ ጦርነትም ለኀያላን፥ እንጀራም ለጠቢባን፥ ባለጠግነትም ለአስተዋዮች፥ ሞገስም ለዐዋቂዎች እንዳልሆነ አየሁ፤ ጊዜና ዕድል ግን ሁሉን ያገናኛቸዋል። ሰውም ጊዜውን አያውቅም፤ በክፉ መረብ እንደ ተጠመዱ ዓሣዎች ፥ በወጥመድም እንደ ተያዙ ወፎች፥ እንዲሁ የሰው ልጆች በክፉ ጊዜ በድንገት ሲወድቅባቸው ይጠመዳሉ።
መክብብ 9:1-12 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ስለዚህ ይህን ሁሉ በልቤ አስቤ እንዲህ አልሁ፤ ጻድቃንና ጠቢባን የሚሠሩትም ሥራ በአምላክ እጅ ነው፤ ነገር ግን ፍቅር ይሁን ወይም ጥላቻ የሚጠብቀውን ማንም አያውቅም። ጻድቃንና ኃጥኣን፣ ደጎችና ክፉዎች፣ ንጹሓንና ርኩሳን፣ መሥዋዕት የሚያቀርቡና የማያቀርቡ፣ የሁሉም የመጨረሻ ዕጣ ፈንታ አንድ ነው። ለደጉ ሰው እንደ ሆነው ሁሉ፣ ለኀጢአተኛውም እንዲሁ ነው፤ ለሚምሉት እንደ ሆነው ሁሉ፣ መሐላን ለሚፈሩትም እንዲሁ ነው። ከፀሓይ በታች በሁሉም ላይ የሚሆነው ክፋት ይህ ነው፤ የሁሉም የመጨረሻ ዕጣ ፈንታ አንድ ነው። በዚህም ላይ የሰዎች ልብ በክፋት የተሞላ ነው፤ በሕይወት እያሉም በልባቸው ውስጥ እብደት አለ፤ በመጨረሻም ወደ ሙታን ይወርዳሉ። በሕያዋን መካከል ያለ ማንኛውም ሰው ተስፋ አለው፤ በሕይወት ያለ ውሻ ከሞተ አንበሳ ይሻላልና! ሕያዋን እንደሚሞቱ ያውቃሉና፤ ሙታን ግን ምንም አያውቁምና፤ መታሰቢያቸው ይረሳል፤ ምንም ዋጋ የላቸውም። ፍቅራቸው፣ ጥላቻቸው፣ ቅናታቸውም ከጠፋ ቈይቷል፤ ከፀሓይ በታች በሚሆነው ነገር ሁሉ፣ ፈጽሞ ዕጣ ፈንታ አይኖራቸውም። ሂድ፤ ምግብህን በደስታ ብላ፤ ወይንህንም ልብህ ደስ ብሎት ጠጣ፤ ባደረግኸው ነገር አምላክ ደስ ብሎታልና። ዘወትር ልብስህ ነጭ ይሁን፤ ራስህንም ዘወትር በዘይት ቅባ። አምላክ ከፀሓይ በታች በሰጠህ በዚህ ትርጕም የለሽ የሕይወት ዘመን ሁሉ፣ ከንቱ በሆኑትም ቀኖችህ ሁሉ ከምትወድዳት ሚስትህ ጋራ ደስ ይበልህ፤ በሕይወትህና ከፀሓይ በታች በምትደክምበት ነገር ሁሉ ይህ ዕድል ፈንታህ ነውና። እጅህ የሚያገኘውን ሥራ ሁሉ በሙሉ ኀይልህ ሥራው፤ ልትሄድበት ባለው መቃብር ውስጥ መሥራትም ሆነ ማቀድ፣ ዕውቀትም ሆነ ጥበብ የለምና። ሌላም ነገር ከፀሓይ በታች አየሁ፤ ሩጫ ለፈጣኖች፣ ውጊያም ለኀያላን አይደለም፤ እንጀራ ለጥበበኞች፣ ወይም ባለጠግነት ለብልኆች፣ ወይም ሞገስ ለዐዋቂዎች አይሆንም፤ ጊዜና ዕድል ግን ሁሉን ይገናኛቸዋል። ደግሞም የራሱን ጊዜ የሚያውቅ ሰው የለም፤ ዓሦች በክፉ መረብ እንደሚያዙ፣ ወይም ወፎች በወጥመድ እንደሚጠመዱ፣ ሰዎችም ሳያስቡት በሚመጣባቸው፣ በክፉ ጊዜ ይጠመዳሉ።
መክብብ 9:1-12 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ጻድቃንና ጠቢባን ሥራዎቻቸውም በእግዚአብሔር እጅ እንደ ሆኑ፥ ይህን ሁሉ እመረምር ዘንድ በልቤ አኖርሁ፥ ፍቅር ወይም ጥል ቢሆን ሰው አያውቅም ሁሉ ወደ ፊታቸው ነው። የጻድቁና የበደለኛው፥ የመልካሙና የክፉው፥ የንጹሑና የርኩሱ፥ መሥዋዕትን የሚሠዋውና የማይሠዋው፥ የሰው ሁሉ ድርሻው አንድ ነው፥ እንደ መልካሙ ሰው እንዲሁ ኃጢአተኛው፥ እንደ መሐለኛው ሰው እንዲሁ መሐላን የሚፈራው ነው። አንድ ድርሻ ሁሉን እንዲያገኝ ከፀሐይ በታች በተደረገው ሁሉ ይህ ነገር ክፉ ነው፥ ደግሞም የሰው ልጆች ልብ ክፋትን ትሞላለች፥ በሕይወታቸውም ሳሉ እብደት በልባቸው ነው፥ ከዚያም በኋላ ወደ ሙታን ይወርዳሉ። ያልሞተ ውሻ ከሞተ አንበሳ ይሻላልና ሰው ከሕያዋን ሁሉ ጋር በአንድነት ቢኖር ተስፋ አለው። ሕያዋን እንዲሞቱ ያውቃሉና፥ ሙታን ግን አንዳች አያውቁም፥ መታሰቢያቸውም ተረስቶአልና ከዚያ በኋላ ዋጋ የላቸውም። ፍቅራቸውና ጥላቸው ቅንዓታቸውም በአንድነት ጠፍቶአል፥ ከፀሐይ በታችም በሚሠራው ነገር ለዘላለም እድል ፈንታ ከእንግዲህ ወዲህ የላቸውም። እግዚአብሔር ሥራህን ተቀብሎታልና ሂድ፥ እንጀራህን በደስታ ብላ፥ የወይን ጠጅህንም በተድላ ጠጣ። ሁልጊዜ ልብስህ ነጭ ይሁን፥ ቅባትም ከራስህ ላይ አይታጣ። በሕይወትህ፥ አንተም ከፀሐይ በታች በምትደክምበት ድካም ይህ እድል ፈንታህ ነውና ከንቱ በሆነ በሕይወትህ ዘመን ሁሉ፥ ከፀሐይ በታች በሰጠህ፥ በከንቱ ዘመንህ ሁሉ፥ ከምትወድዳት ሚስትህ ጋር ደስ ይበልህ። አንተ በምትሄድበት በሲኦል ሥራና አሳብ እውቀትና ጥበብ አይገኙምና እጅህ ለማድረግ የምታገኘውን ሁሉ እንደ ኃይልህ አድርግ። እኔም ተመለስሁ፥ ከፀሐይ በታችም ሩጫ ለፈጣኖች፥ ሰልፍም ለኃያላን፥ እንጀራም ለጠቢባን፥ ባለጠግነትም ለአስተዋዮች፥ ሞገስም ለአዋቂዎች እንዳልሆነ አየሁ፥ ጊዜና እድል ግን ሁሉን ይገናኛቸዋል። ሰውም ጊዜውን አያውቅም፥ በክፉ መረብ እንደ ተጠመዱ ዓሣዎች፥ በወጥመድም እንደ ተያዙ ወፎች፥ እንዲሁ የሰው ልጆች በክፉ ጊዜ በድንገት ሲወድቅባቸው ይጠመዳሉ።
መክብብ 9:1-12 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ስለ ነዚህ ሁሉ ነገሮች ለረጅም ጊዜ በብርቱ ካሰብኩ በኋላ የደጋግና የጥበበኞች ሰዎችን ሥራ በእግዚአብሔር እጅ እንደ ሆነ ተረዳሁ፤ ስለዚህ ወደፊት የሚገጥመውን ነገር ፍቅርም ሆነ ጥላቻ አስቀድሞ የሚያውቅ ሰው የለም። ምንም ዐይነት ልዩነት ሳይደረግ ለጻድቅና ለኃጢአተኛ ለደግና ለክፉ፥ ለንጹሓንና ንጹሓን ላልሆኑ መሥዋዕት ለሚያቀርቡትና ለማያቀርቡትም የሚገጥማቸው ዕድል አንድ ዐይነት ነው፤ ይኸውም ደጉ ሰው ከኃጢአተኛው የተሻለ ዕድል የለውም፤ መሐላን የሚፈራው መሐላን ከሚደፍረው ሰው ተለይቶ አይታይም። የሁሉም ዕድል ፈንታው አንድ ዐይነት ነው፤ ይህም በዓለም እንደሚደረገው እንደማንኛውም ነገር ሁሉ እጅግ የከፋ ነው፤ ሰዎችም በሚኖሩበት ዘመን ሁሉ አእምሮአቸው በክፋትና በእብደት የተሞላ ሆኖ በመጨረሻ ይሞታሉ። ከሞተ አንበሳ ይልቅ በሕይወት ያለ ውሻ ይሻላል፤ በሕያዋን ምድር የሚኖር ሰው የተሻለ ተስፋ አለው፤ በሕይወት ያሉ ሰዎች አንድ ቀን እንደሚሞቱ ያውቃሉ፤ ሙታን ግን አንዳች ነገር አያውቁም፤ ፈጽሞ የተረሱ በመሆናቸውም ዋጋ የላቸውም። ፍቅራቸው፥ ጥላቻቸውና ቅናታቸው ሁሉ ከእነርሱ ጋር አብሮ ሞቶአል፤ በዚህ ዓለም በሚሆነው ነገር ሁሉ እንደገና እስከ ዘለዓለም ተካፋይነት አይኖራቸውም። እግዚአብሔር ቀድሞ የፈቀደልህ ይህ በመሆኑ ሂድ፤ ምግብህን ተመግበህ፥ የወይን ጠጅህንም ጠጥተህ በመርካትህ ደስ ይበልህ። ሁልጊዜ ነጭ ልብስ ለብሰህ ጠጒርህን ተቀባ። በዚህ ዓለም እግዚአብሔር በሰጠህ ከንቱ በሆነ ኑሮህ ከምትወዳት ሚስትህ ጋር ደስ ይበልህ፤ ስለ መከራህና ስለ ድካምህ ሁሉ ዋጋ ሆኖ የተሰጠህ ዕድል ፈንታ ይኸው ብቻ ስለ ሆነ ከንቱ ዘመንህን፥ እያንዳንዱን ቀን ተደሰትበት። ባለህ ኀይል ሥራህን ሁሉ በትጋት ፈጽም፤ ወደ ሙታን ዓለም ከወረድህ በኋላ በዚያ ሥራና ሐሳብ፥ ዕውቀትና ጥበብ የለም። በዚህ ዓለም የተመለከትኩት ሌላም ነገር አለ፤ ይኸውም ፈጣን ሯጮች በአሸናፊነት አይወጡም፤ ጀግኖችም በጦርነት ድል አያደርጉም፤ ጠቢባን የዕለት እንጀራን፥ ብልኆች ሀብትን አያገኙም፤ ችሎታ ያላቸውም ሰዎች በማዕርግ አያድጉም፤ ነገር ግን ሁሉንም ጊዜና ዕድል ያጋጥማቸዋል፤ ይሁን እንጂ እያንዳንዱ ሰው ይህ መጥፎ ዕድል መቼ እንደሚገጥመው አያውቅም፤ ወፍ በራ በወጥመድ ውስጥ እንደምትገባ፥ ዓሣም በመጥፎ አጋጣሚ በመረብ እንደሚያዝ እንዲሁም የሰው ልጅ ሁሉ ሳያስበው ድንገት በሚደርስበት በክፉ አጋጣሚ ይጠመዳል።
መክብብ 9:1-12 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ጻድቃንና ጠቢባን፥ ሥራዎቻቸውም በእግዚአብሔር እጅ እንደ ሆኑ፥ ይህን ሁሉ እመረምር ዘንድ በልቤ አኖርሁ፥ ፍቅርም ሆነ ጥል ቢሆን ሰው አያውቅም፤ ሁሉም በፊታቸው ነው። የጻድቁና የበደለኛው፥ የመልካሙና የክፉው፥ የንጹሑና የርኩሱ፥ መሥዋዕትን የሚሠዋውና የማይሠዋው፥ የሰው ሁሉ ድርሻው አንድ ነው፤ መልካሙ ሰው እንደ ኃጢአተኛው፥ የሚምለው ሰው መሐላን እንደሚፈራው ነው። ለሁሉም አንድ ዓይነት ዕጣ ክፍል መኖሩ ከፀሐይ በታች በሚደረገው ነገር በሙሉ ይህ ክፉ ነው፥ ደግሞም የሰው ልጆች ልብ በክፋት ተሞልታለች፥ በሕይወታቸውም ሳሉ እብደት በልባቸው ውስጥ ይኖራል፥ ከዚያም በኋላ ወደ ሙታን ይወርዳሉ። ያልሞተ ውሻ ከሞተ አንበሳ ይሻላልና ሰው ከሕያዋን ሁሉ ጋር በአንድነት ቢኖር ተስፋ አለው። ሕያዋን እንደሚሞቱ ያውቃሉና፥ ሙታን ግን አንዳችም ነገር አያውቁም፥ መታሰቢያቸውም ተረስቶአልና ከዚያ በኋላ ዋጋ የላቸውም። ፍቅራቸውና ጥላቸው ቅንዓታቸውም በአንድነት ከወዲሁ ጠፍቶአል፥ ከፀሐይ በታችም በሚሠራው ነገር ለዘለዓለም እድል ፈንታ ከእንግዲህ ወዲህ የላቸውም። እግዚአብሔር ሥራህን ተቀብሎታልና ሂድ፥ እንጀራህን በደስታ ብላ፥ የወይን ጠጅህንም በተድላ ጠጣ። ሁልጊዜ ልብስህ ነጭ ይሁን፥ ቅባትም ከራስህ ላይ አይታጣ። በሕይወትህ፥ አንተም ከፀሐይ በታች በምትደክምበት ድካም ይህ እድል ፈንታህ ነውና ከንቱ በሆነ በሕይወትህ ዘመን ሁሉ፥ ከፀሐይ በታች በሰጠህ፥ በከንቱ ዘመንህ ሁሉ፥ ከምትወድዳት ሚስትህ ጋር ደስ ይበልህ። አንተ በምትሄድበት በሲኦል ሥራና አሳብ እውቀትና ጥበብ አይገኙምና እጅህ ለማድረግ የምታገኘውን ሁሉ እንደ ኃይልህ አድርግ። እኔም ተመለስሁ፥ ከፀሐይ በታችም ሩጫ ለፈጣኖች፥ ፍልምያ ለኃያላን፥ እንጀራም ለጠቢባን፥ ሀብትም ለአስተዋዮች፥ ሞገስም ለአዋቂዎች እንዳልሆነ አየሁ፥ ጊዜና እድል ግን ሁሉን ይገናኛቸዋል። ሰውም ጊዜውን አያውቅም፥ በክፉ መረብ እንደ ተጠመዱ ዓሣዎች፥ በወጥመድም እንደ ተያዙ ወፎች፥ እንዲሁ የሰው ልጆች በክፉ ጊዜ በድንገት ሲወድቅባቸው ይጠመዳሉ።