መክብብ 8:1-17
መክብብ 8:1-17 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ዐዋቂዎችን ማን ያውቃቸዋል? ቃላቸውንስ መተርጐም የሚያውቅ ማን ነው? የሰው ጥበቡ ፊቱን ታበራለች፥ በፊቱም ኀፍረት የሌለው ሰው ይጠላል። ልጄ ሆይ፥ የንጉሥን አፍ ጠብቅ፤ ለመሐላ ቃልም አትቸኩል። የወደደውን ሁሉ ያደርጋልና ከፊቱ ሂድ፥ በክፉ ነገርም አትቁም፥ ንጉሥ እንደ መሆኑ ኀይል አለውና፤ ይህንስ ለምን ታደርጋለህ? ማን ይለዋል? ትእዛዝን የሚጠብቅ ክፉን ነገር አያውቅም፤ የጠቢብም ልብ የፍርድን ጊዜ ያውቃል። የሰው ዕውቀት በእርሱ ላይ ታላቅ ስለ ሆነ ለነገር ሁሉ ጊዜና ፍርድ አለውና። የሚሆነውንም ምንም የሚያውቅ የለም፤ እንዴትስ እንደሚሆን የሚነግረው ማን ነው? መንፈስን ለማስቀረት በመንፈሱ ላይ ሥልጣን ያለው ሰው የለም፤ በሞትም ቀን ሥልጣን የለውም፤ በጦርነትም ጊዜ ስንብት የለም፥ ኀጢአትም ሠሪውን አያድነውም። ይህን ሁሉ በአንድነት አየሁ፥ ከፀሓይም በታች ወደ ተደረገው ሥራ ሁሉ ልቤን ሰጠሁ፤ ሰውም ሰውን ለመጕዳት ገዥ የሚሆንበት ጊዜ አለ። እንዲሁም ያንጊዜ ኃጥኣን ወደ ጽኑ መቃብር ሲገቡ አየሁ፥ ከቅድስት ስፍራም ወጥተው ተለዩ፤ እነርሱም በከተማዋ ተመሰገኑ፥ እንዲህ ሠርተዋልና፤ ይህም ደግሞ ከንቱ ነው። ክፉን ከሚያደርጉ ወገን ፈጥኖ ክርክርን የሚያደርግ የለምና፤ ስለዚህ የሰው ልጆች ልብ በእነርሱ ክፉን ለመሥራት ጠነከረ። የበደለ ከጥንት ጀምሮ ከዚያም በፊት ኀጢአትን አድርጓል፥ እግዚአብሔርን ለሚፈሩት በፊቱም ለሚፈሩት ደኅንነት እንዲሆን አውቃለሁና፤ ለኃጥእ ግን ደኅንነት የለውም፥ በእግዚአብሔርም ፊት አይፈራምና ዘመኑ እንደ ጥላ አትረዝምም። ከፀሓይ በታች በምድር የሚደረግ ከንቱ ነገር አለ፥ በኃጥኣን የሚደረገው ሥራ የሚደርስባቸው ጻድቃን አሉ፥ ለጻድቃንም የሚደረገው ሥራ የሚደርስላቸው ኃጥኣን አሉ፤ ይህም ደግሞ ከንቱ ነው አልሁ። ከሚበላውና ከሚጠጣው፥ ደስም ከሚለው በቀር ለሰው ከፀሓይ በታች ሌላ መልካም ነገር የለውምና እኔ ደስታን አመሰገንሁ፤ ይህም ከፀሓይ በታች ከድካሙ እግዚአብሔር በሕይወቱ ዘመን ለእርሱ የሰጠው ነው። ጥበብን አውቅ ዘንድ በምድር የሚሆነውንም ድካም አይ ዘንድ ልቤን ሰጠሁ፥ በቀንና በሌሊት እንቅልፍን በዐይኑ የሚያይ የለምና። ከፀሓይም በታች የተደረገውን ሥራ መርምሮ ያገኝ ዘንድ ለሰው እንዳይቻለው የእግዚአብሔርን ሥራ ሁሉ አየሁ። ሰውም ሊፈልግ እጅግ ቢደክም መርምሮ አያገኘውም፤ ደግሞም ጠቢብ ሰው፥ “ይህን ዐወቅሁ” ቢል እርሱ ያገኘው ዘንድ አይችልም።
መክብብ 8:1-17 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ነገሮችን መግለጽ የሚችል፣ እንደ ጠቢብ ያለ ሰው ማን ነው? ጥበብ የሰውን ፊት ታበራለች፤ የከበደ ገጽታውንም ትለውጣለች። በአምላክ ፊት መሐላ ስለ ፈጸምህ፣ የንጉሥን ትእዛዝ አክብር እልሃለሁ። ከንጉሥ ፊት ተጣድፈህ አትውጣ፤ የወደደውንም ማድረግ ስለሚችል ለጥፋት አትሰለፍ። የንጉሥ ቃል የበላይ ስለ ሆነ እርሱን፣ “ምን ታደርጋለህ?” ማን ሊለው ይችላል? እርሱን የሚታዘዝ ሁሉ አይጐዳም፤ ጥበበኛም ልብ ትክክለኛውን ጊዜና ተገቢውን አሠራር ያውቃል። የሰው መከራ እጅግ ቢጫነውም፣ ለሁሉም ነገር ትክክለኛ ጊዜና ተገቢ አሠራር አለው። ሰው የወደ ፊቱን ስለማያውቅ፣ ሊመጣ ያለውን ማን ሊነግረው ይችላል? ሰው ነፋስን መቈጣጠር አይችልም፤ በዕለተ ሞቱም ላይ ሥልጣን ያለው ማንም የለም፤ በጦርነት ጊዜ ማንም ከግዴታ ነጻ እንደማይሆን፣ ክፋትም የሚለማመዷትን አትለቃቸውም። ከፀሓይ በታች የተሠራውን ሁሉ በአእምሮዬ መርምሬ፣ ይህን ሁሉ አየሁ። ሰው ሰውን ለመጕዳት ገዥ የሚሆንበት ጊዜ አለ። እንዲሁም ወደ ቅዱሱ ስፍራ ይመጡና ይሄዱ የነበሩት ክፉዎች ተቀብረው አየሁ፤ ይህን ባደረጉበት ከተማም ይመሰገኑ ነበር፤ ይህም ደግሞ ከንቱ ነው። በወንጀል ላይ ባፋጣኝ ፍርድ ካልተሰጠ፣ የሰዎች ልብ ክፉን በማድረግ ዕቅድ ይሞላል። ኀጥእ መቶ ወንጀል ሠርቶ ዕድሜው ቢረዝምም፣ አምላክን የሚያከብሩ፣ ፈሪሀ እግዚአብሔር ያላቸው ሰዎች መልካም እንደሚሆንላቸው ዐውቃለሁ። ነገር ግን ክፉዎች አምላክን ስለማይፈሩ መልካም አይሆንላቸውም፤ ዕድሜያቸው እንደ ጥላ አይረዝምም። በምድር ላይ የሚከሠት ሌላም ከንቱ ነገር አለ፤ ጻድቃን ለክፉዎች የሚገባውን፣ ክፉ ሰዎችም ለጻድቃን የሚገባውን ይቀበላሉ፤ ይህም ደግሞ ከንቱ ነገር ነው አልሁ። ለሰው፣ ከፀሓይ በታች ከመብላት፣ ከመጠጣትና ከመደሰት ሌላ የተሻለ ነገር ስለሌለ፣ በሕይወት ደስ መሠኘት መልካም ነው አልሁ፤ ስለዚህ አምላክ ከፀሓይ በታች በሰጠው የሕይወት ዘመኑ ሁሉ በሥራው ደስታ ይኖረዋል። ጥበብን ለማወቅና ሌት ተቀን እንቅልፍ የማያውቀውን በምድር ያለውን የሰውን ድካም ለመገንዘብ በአእምሮዬ ስመረምር፣ አምላክ ያደረገውን ሁሉ አየሁ። ከፀሓይ በታች የሚደረገውን ማንም ሊያውቅ አይችልም፤ ሰው ለመመርመር ብዙ ቢጥርም፣ ትርጕሙን ማግኘት አይችልም፤ ጠቢብም እንኳ ዐውቀዋለሁ ቢል፣ ፈጽሞ ሊገነዘበው አይችልም።
መክብብ 8:1-17 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እንደ ጠቢብ የሆነ ሰው ማን ነው? ነገርንስ መተርጐም የሚያውቅ ማን ነው? የሰው ጥበብ ፊቱን ታበራለች፥ የፊቱንም ድፍረት ትለውጣለች። እኔ፦ በእግዚአብሔር መሐላ ምክንያት የንጉሥን ትእዛዝ ጠብቅ እልሃለሁ። የወደደውን ሁሉ ያደርጋልና ከፊቱ ትወገድ ዘንድ አትቸኵል፥ ክፉንም በማድረግ አትጽና። የንጉሥ ቃል ኃይለኛ ነውና፥ ይህንስ ለምን ታደርጋለህ? ማን ይለዋል? ትእዛዝን የሚጠብቅ ክፉን ነገር አያውቅም፥ የጠቢብም ልብ ጊዜንና ፍርድን ያውቃል። የሰው መከራ በእርሱ ላይ እጅግ ስለ ሆነ ለነገር ሁሉ ጊዜና ፍርድ አለውና። የሚሆነውንም አያውቅም፥ እንዴትስ እንደሚሆን የሚነግረው ማን ነው? መንፈስን ለማስቀረት በመንፈስ ላይ ሥልጣን ያለው ሰው የለም፥ በሞቱም ቀን ሥልጣን የለውም፥ በሰልፍም ስንብቻ የለም፥ ኃጢአትም ሠሪውን አያድነውም። ይህን ሁሉ አየሁ፥ ከፀሐይም በታች ወደ ተደረገው ሥራ ሁሉ ልቤን ሰጠሁ፥ ሰው ሰውን ለመጕዳት ገዢ የሚሆንበት ጊዜ አለ። እንዲሁም ኀጥኣን ተቀብረው አየሁ፥ ወደ ዕረፍትም ገቡ፥ ነገር ግን ቅን አድራጊዎች ከቅድስት ስፍራ ወጡ፥ በከተማይቱም ውስጥ ተረሱ፥ ይህም ደግሞ ከንቱ ነው። በክፉ ሥራ ላይ ፈጥኖ ፍርድ አይፈረድምና ስለዚህ በሰው ልጆች ውስጥ ልባቸው ክፉን ለመሥራት ጠነከረ። ኃጢአተኛ መቶ ጊዜ ክፉን ቢሠራ ዘመኑም ረጅም ቢሆን፥ እግዚአብሔርን ለሚፈሩት በፊቱም ለሚፈሩት ደኅንነት እንዲሆን አውቃለሁ፥ ለኀጥእ ግን ደኅንነት የለውም፥ በእግዚአብሔርም ፊት አይፈራምና ዘመኑ እንደ ጥላ አትረዝምም። በምድር የሚደረግ ከንቱ ነገር አለ፥ በኀጥኣን የሚደረገው ሥራ የሚደርስባቸው ጻድቃን አሉ፥ ለጻድቃንም የሚደረገው ሥራ የሚደርስላቸው ኀጥኣን አሉ፥ ይህም ደግሞ ከንቱ ነው አልሁ። ከሚበላውና ከሚጠጣው ደስም ከሚለው በቀር ለሰው ከፀሐይ በታች ሌላ መልካም ነገር የለውምና እኔ ደስታን አመሰገንሁ፥ ከፀሐይም በታች ከድካሙ እግዚአብሔር በሰጠው በሕይወቱ ዘመን ይህ ደስታው ከእርሱ ጋር ይኖራል። ጥበብን አውቅ ዘንድ በምድር የሚሆነውንም ድካም አይ ዘንድ ልቤን ሰጠሁ፥ በቀንና በሌሊት እንቅልፍን በዓይኑ የማያይ አለና፥ ከፀሐይም በታች የተደረገውን ሥራ መርምሮ ያገኝ ዘንድ ለሰው እንዳይቻለው የእግዚአብሔርን ሥራ ሁሉ አየሁ። ሰውም ሊፈልግ እጅግ ቢደክም መርምሮ አያገኘውም፥ ደግሞ ጠቢብ ሰው፦ ይህን አወቅሁ ቢል እርሱ ያገኘው ዘንድ አይችልም።
መክብብ 8:1-17 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ጥበበኛን የሚመስለው ማነው? የነገሮችን ፍቺ የሚያውቅ ማነው? ጥበብ የሰውን ፊት ታበራለች፤ ኰስታራነትንም ትለውጣለች። ለንጉሡ እታዘዛለሁ ብለህ በመሐላ ለእግዚአብሔር ቃል ስለ ገባህ ለንጉሥ ታማኝ ሁን። ንጉሥ የፈለገውን ማድረግ ስለሚችል ክፉ ዓላማን በመደገፍ አትጽና፤ ከንጉሡም ፊት ለመራቅ አትቸኲል። ንጉሥ ሁሉን ነገር ለማድረግ ሥልጣን አለው፤ “ለምን ይህን ሠራህ?” ብሎ የሚጠይቀውስ ማን አለ? ትእዛዙን ብትፈጽም ጒዳት አይደርስብህም፤ ይህ ሁሉ የሚፈጸምበትን ጊዜና ሁኔታ ለይቶ የሚያውቅ ጥበበኛ ብቻ ነው። ሕይወት አስቸጋሪ ቢሆንም ለሁሉም ነገር ጊዜና ቦታ አለው። ወደፊት የሚሆነውን ነገር ለይቶ የሚያውቅ ሰው የለም፤ “ይህ ይሆናል” ብሎ የሚነግረውስ ማነው? የሕይወትን እስትንፋስ ለማስቀረትና የሞትን ቀን ለመለወጥ የሚችል ማንም የለም፤ ማንም ሰው ከጦር ሜዳ መሰናበት እንደማይችል ክፋትም ክፉ ሠሪዎችን አይለቃቸውም። በዚህ ዓለም የሚካሄደውን ሁናቴ በጥሞና ስመለከት ይህን ሁሉ አስተዋልኩ፤ አንድ ሰው ሌላውን ሰው ለመጒዳት ሥልጣን የሚኖረው ለምንድን ነው? ክፉዎች በክብር ሲቀበሩ አየሁ፤ የእግዚአብሔር ሰዎች ግን ከቅድስቲቱ ከተማ ወጥተው በመሄድ ተረሱ፤ ይህ ሁሉ ከንቱ ነው። ሰዎች ሆን ብለው ወንጀል የሚሠሩት ለምንድን ነው? የዚህ ምክንያት ሌላ ሳይሆን ወንጀል በሚሠሩ ሰዎች ላይ ፈጣን የቅጣት ፍርድ ባለመሰጠቱ ነው። ይኸውም ኃጢአተኞች መቶ ጊዜ ወንጀል ቢሠሩም ለረጅም ዘመን ይኖራሉ፤ ይሁን እንጂ እግዚአብሔርን ለሚፈሩና ለሚያከብሩ ሁሉ ነገር እንደሚሰምርላቸው ዐውቃለሁ። ክፉ ሰዎች ግን ምንም ነገር አይሰምርላቸውም፤ እግዚአብሔርንም ስለማይፈሩ ሕይወታቸው እንደ ጥላ ያልፋል፤ በምድር ላይ የሚደረግ ከንቱ ነገር አለ፤ አንዳንድ ጊዜ ደጋግ ሰዎች ለክፉ ሰዎች የሚገባውን ቅጣት ይቀበላሉ፤ ክፉ ሰዎች ደግሞ ለደጋግ ሰዎች የሚገባውን ዋጋ ያገኛሉ፤ ይህም ሁሉ ከንቱ ነው አልኩ። ስለዚህ ሰው በዚህ ዓለም ሲኖር የተሰጠው ዕድል ፈንታ መብላት፥ መጠጣትና ራሱን ማስደሰት መሆኑን አረጋገጥኩ፤ እግዚአብሔር በዚህ ዓለም በሰጠው ዘመን፥ ሰው ሁሉ ሠርቶ ያገኘውን ሀብት በዚህ ዐይነት ይደሰትበታል። ጥበበኛ ለመሆንና በዚህ ዓለም የሚደረገውንም ነገር ሁሉ መርምሬ ለማወቅ በሞከርኩ መጠን ሰው ሌት ከቀን ዕረፍት አጥቶ እንደሚኖር ተረዳሁ። ሰው በምርምር ብዛትም እግዚአብሔር የሚያደርገውን ነገር ሁሉ ማወቅ እንደማይችል አረጋገጥኩ፤ ሰው ብዙ ነገር መርምሮ ለማወቅ የቱንም ያኽል ቢደክም አንዳች ነገር ማግኘት አይችልም፤ በእርግጥ ጥበበኞች ሰዎች “ይህንን እናውቃለን” ለማለት ይደፍሩ ይሆናል፤ ይሁን እንጂ የሚያውቁት ነገር የለም።
መክብብ 8:1-17 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ጠቢብን የሚመስለው? የነገሮችንስ ትርጒም የሚያውቅ ማን ነው? የሰው ጥበብ ፊቱን ታበራለች፥ የፊቱንም ድንዳኔ ትለውጣለች። እኔ፦ በመለኮታዊ መሐላ መሠረት የንጉሥን ትእዛዝ ጠብቅ እልሃለሁ። የወደደውን ሁሉ ያደርጋልና ከፊቱ ለመራቅ አትቸኩል፥ ክፉንም በማድረግ አትጽና። የንጉሥ ቃል ኃይለኛ ነውና፥ “ይህንስ ለምን ታደርጋለህ?” ማን ይለዋል? ትእዛዝን የሚጠብቅ ክፉ ነገር አይገጥመውም፥ የጠቢብም ልብ ጊዜንና ፍርድን ያውቃል። የሰው መከራ በእርሱ ላይ እጅግ ስለ ሆነ ለነገር ሁሉ ጊዜና ፍርድ አለውና። የሚሆነውንም አያውቅም፥ እንዴትስ እንደሚሆን የሚነግረው ማን ነው? መንፈስን ለማገድ በመንፈስ ላይ ሥልጣን ያለው ሰው የለም፥ በሞቱም ቀን ላይ ሥልጣን የለውም፥ በጦርነትም ውስጥ መሰናበቻ የለም፥ ክፋትም ሠሪውን አያድነውም። ይህን ሁሉ አየሁ፥ ከፀሐይም በታች ወደ ለተደረገው ሥራ ሁሉ ልቤን ሰጠሁ፥ ሰው ሰውን ለመጉዳት ገዢ የሚሆንበት ጊዜ አለ። እንዲሁም ክፉዎች ተቀብረው አየሁ፥ ነገር ግን ቅን አድራጊዎች ከቅድስት ስፍራ ወጡ፥ በከተማይቱም ውስጥ ተረሱ፥ ይህም ደግሞ ከንቱ ነው። በክፉ ሥራ ላይ ፈጥኖ ፍርድ አይበየንምና በሰው ልጆች ልብ ውስጥ ክፉን መሥራት ጠነከረ። ኃጢአተኛ መቶ ጊዜ ክፉን ቢሠራ ዘመኑም ረጅም ቢሆን፥ እግዚአብሔርን ለሚፈሩት በፊቱም ለሚፈሩት መልካም እንደሚሆን አውቃለሁ፥ ለክፉ መልካም አይሆንም፤ በእግዚአብሔርም ፊት አይፈራምና ዘመኑ እንደ ጥላ አትረዝምም። በምድር የሚደረግ ከንቱ ነገር አለ፥ በክፉዎች ላይ የሚደረገው የሚደርስባቸው ጻድቃን አሉ፥ ለጻድቃንም የሚደረገው የሚደርስላቸው ክፉዎችም አሉ፥ ይህም ደግሞ ከንቱ ነው አልሁ። ከመብላትና ከመጠጣት፥ ደስም ከመሰኘት በቀር ለሰው ልጅ ከፀሐይ በታች ሌላ ምንም መልካም ነገር የለውምና እኔ ደስታን አመሰገንሁ፥ ይህም እግዚአብሔር ከፀሐይም በታች በሰጠው በሕይወቱ ዘመን በድካሙ ከእርሱ ጋር ይኖራል። ጥበብን አውቅ ዘንድ፥ በምድር የሚሆነውንም ድካም አይ ዘንድ ልቤን በሰጠሁ ጊዜ፥ በቀንና በሌሊት እንቅልፍን በዓይኑ የማያይ አለና፥ የእግዚአብሔርንም ሥራ ሁሉ አየሁ፤ እርሱም ከፀሐይም በታች የተደረገውን ሥራ መርምሮ ሰው ማግኘት አለመቻሉን፥ ሰውም በመፈለግ እጅግ ቢደክምም መርምሮ አለማግኘቱን ነው፥ ደግሞም ጠቢብ ሰው አውቀዋለሁ ቢልም እንኳን ይህንን ለማግኘት አይችልም።