መክብብ 7:13-18
መክብብ 7:13-18 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
የእግዚአብሔርን ሥራ ተመልከት፤ እግዚአብሔር ጠማማ ያደረገውን ማን ሊያቀናው ይችላል? በመልካም ቀን ደስ ይበልህ ፤ በክፉም ቀን ተመልከት፤ ሰው ከእርሱ በኋላ መርምሮ ምንም እንዳያገኝ እግዚአብሔር ይህንም ያንም እንደዚያ ሠራ። ጻድቅ በጽድቁ ሲጠፋ፥ ኃጥእም በክፋቱ ሲኖር፥ ይህን ሁሉ በከንቱ ዘመኔ አየሁ። እጅግ ጻድቅ አትሁን፥ እጅግም ጠቢብ አትሁን፥ እንዳትበድል። እጅግ ክፉ አትሁን፥ እልከኛም አትሁን፥ ያለ ጊዜህ እንዳትሞት። ይህን ብትይዝ ለአንተ መልካም ነው፤ በዚህም እጅህን አታርክስ፥ እግዚአብሔርን የሚፈራ ከሁሉ ይወጣልና።
መክብብ 7:13-18 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
አምላክ ያደረገውን ተመልከት፤ እርሱ ያጣመመውን፣ ማን ሊያቃናው ይችላል? ጊዜው መልካም ሲሆን፣ ደስ ይበልህ፤ ጊዜው ክፉ ሲሆን ግን ይህን ዐስብ፤ አምላክ አንዱን እንዳደረገ፣ ሌላውንም አድርጓል፤ ስለዚህ ሰው ስለ ወደ ፊት ሁኔታው፣ ምንም ሊያውቅ አይችልም። በዚህ ከንቱ በሆነው ሕይወቴ እነዚህን ሁለቱን ነገሮች አይቻለሁ፤ ጻድቅ በጽድቁ ሲጠፋ፣ ኀጥእም በክፋቱ ዕድሜው ሲረዝም። እጅግ ጻድቅ፣ እጅግም ጠቢብ አትሁን፤ ራስህን ለምን ታጠፋለህ? እጅግ ክፉ አትሁን፤ ሞኝም አትሁን፤ ለምንስ ያለ ቀንህ ትሞታለህ? አንዱን ይዞ ሌላውንም አለመልቀቅ መልካም ነው፤ አምላክን የሚፈራ ሰው ጽንፈኛነትን ያስወግዳል።
መክብብ 7:13-18 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
የእግዚአብሔርን ሥራ ተመልከት፥ እርሱ ጠማማ ያደረገውን ማን ሊያቀናው ይችላል? በመልካም ቀን ደስ ይበልህ፥ በክፉም ቀን ተመልከት፥ ሰው ከእርሱ በኋላ መርምሮ ምንም እንዳያገኝ እግዚአብሔር ይህንም ያንም እንደዚያ ሠርቶአል። ጻድቅ በጽድቁ ሲጠፋ ኀጥእም በክፋቱ እጅግ ዘመን ሲኖር፥ ይህን ሁሉ ከንቱ በሆነ ዘመኔ አየሁ። እጅግ ጻድቅ አትሁን፥ እጅግ ጠቢብም አትሁን፥ እንዳትጠፋ። እጅግ ክፉ አትሁን፥ እልከኛም አትሁን፥ ጊዜህ ሳይደርስ እንዳትሞት። እግዚአብሔርን የሚፈራ ከሁሉ ይወጣልና ይህን ብትይዝ ከዚያም ደግሞ እጅህን ባታርቅ መልካም ነው።
መክብብ 7:13-18 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እስቲ የእግዚአብሔርን አሠራር አስተውል፤ እግዚአብሔር ያላቃናውን ማን ሊያቃናው ይችላል? ጊዜው መልካም ሲሆን ደስ ይበልህ፤ ጊዜውም ክፉ ሲሆን አስተውል፤ ይህንንም ያንንም ያደረገ እግዚአብሔር ነው፤ ስለዚህ ሰው ማንኛውንም የወደፊት ሁናቴውን ሊያውቅ አይችልም። ከንቱ በሆነው ዘመኔ ክፉ ሰው በሚሠራው በደል እስከ ረጅም ዕድሜ ሲኖር፥ ደግ ሰው ግን በደግነቱ ሲጠፋ ብዙ ነገር አይቼበታለሁ፤ ስለዚህ እንዳትጠፋ እጅግም ጠቢብ፥ እጅግም ደግ አትሁን። ያለ ጊዜህም በሞት እንዳትቀጭ እጅግ ክፉ ወይም ሞኝ አትሁን። ወደ ክፋት ወይም ወደ ደግነት ከመጠን በላይ ርቀህ አትሂድ፤ እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው ግን በሁሉም ነገር ይሳካለታል።
መክብብ 7:13-18 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
የእግዚአብሔርን ሥራ ተመልከት፥ እርሱ ጠማማ ያደረገውን ማን ሊያቀናው ይችላል? በመልካም ቀን ደስ ይበልህ፥ በክፉም ቀን ተመልከት፥ ሰው ከእርሱ በኋላ መርምሮ ምንም እንዳያገኝ እግዚአብሔር ይህንንም ያንንም እንዲሁ ሠርቶአል። ጻድቅ በጽድቁ ሲጠፋ ክፉም በክፋቱ ረጅም ዘመን ሲኖር፥ ይህን ሁሉ ከንቱ በሆነ ዘመኔ አየሁ። እጅግ ጻድቅ አትሁን፥ እጅግ ጠቢብም አትሁን፥ ለምን ራስህን ታጠፋለህ? እጅግ ክፉ አትሁን፥ አላዋቂም አትሁን፥ ጊዜህ ሳይደርስ ለምን ትሞታለህ? እግዚአብሔርን የሚፈራ በሁሉም ይዋጣለታልና ይህን ብትይዝ፥ ከዚያም ደግሞ እጅህን ባታርቅ መልካም ነው።