መክብብ 3:1-15

መክብብ 3:1-15 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ለሁሉ ዘመን አለው፥ ከፀ​ሐይ በታ​ችም ለሆነ ነገር ሁሉ ጊዜ አለው። ለመ​ፅ​ነስ ጊዜ አለው፥ ለመ​ው​ለ​ድም ጊዜ አለው፤ ለመ​ኖር ጊዜ አለው፥ ለመ​ሞ​ትም ጊዜ አለው፤ ለመ​ት​ከል ጊዜ አለው፥ የተ​ተ​ከ​ለ​ው​ንም ለመ​ን​ቀል ጊዜ አለው። ለመ​ግ​ደል ጊዜ አለው፥ ለመ​ፈ​ወ​ስም ጊዜ አለው፤ ለማ​ፍ​ረስ ጊዜ አለው፥ ለመ​ሥ​ራ​ትም ጊዜ አለው፤ ለማ​ል​ቀስ ጊዜ አለው፥ ለመ​ሣ​ቅም ጊዜ አለው፤ ዋይ ለማ​ለት ጊዜ አለው፥ ለመ​ዝ​ፈ​ንም ጊዜ አለው። ድን​ጋ​ይን ለመ​ወ​ር​ወር ጊዜ አለው፥ ድን​ጋ​ይ​ንም ለመ​ሰ​ብ​ሰብ ጊዜ አለው፤ ለመ​ተ​ቃ​ቀፍ ጊዜ አለው፥ ከመ​ተ​ቃ​ቀ​ፍም ለመ​ራቅ ጊዜ አለው፤ ለመ​ፈ​ለግ ጊዜ አለው፥ ለማ​ጥ​ፋ​ትም ጊዜ አለው፤ ለመ​ጠ​በቅ ጊዜ አለው፥ ለመ​ጣ​ልም ጊዜ አለው፤ ለመ​ቅ​ደድ ጊዜ አለው፥ ለመ​ስ​ፋ​ትም ጊዜ አለው፤ ዝም ለማ​ለት ጊዜ አለው፥ ለመ​ና​ገ​ርም ጊዜ አለው፤ ለመ​ው​ደድ ጊዜ አለው፥ ለመ​ጥ​ላ​ትም ጊዜ አለው፤ ለጦ​ር​ነት ጊዜ አለው፥ ለሰ​ላ​ምም ጊዜ አለው። ለሠ​ራ​ተኛ የድ​ካሙ ትርፍ ምን​ድን ነው? እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ለሰው ልጆች ይደ​ክ​ሙ​በት ዘንድ የሰ​ጣ​ቸ​ውን ድካም ሁሉ አይ​ቻ​ለሁ። የሠ​ራው ሥራ ሁሉ በጊ​ዜው መል​ካም ነው፤ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ከጥ​ንት ጀምሮ እስከ ፍጻሜ ድረስ የሠ​ራ​ውን ሥራ ሰው መር​ምሮ እን​ዳ​ያ​ገኝ ዘለ​ዓ​ለ​ም​ነ​ትን በልቡ ሰጠው። ሰው ደስ ከሚ​ለ​ውና በሕ​ይ​ወቱ ሳለ መል​ካ​ምን ነገር ከሚ​ያ​ደ​ርግ በቀር በው​ስ​ጣ​ቸው መል​ካም ነገር እን​ደ​ሌለ ዐወ​ቅሁ። ደግ​ሞም ሰው ሁሉ ይበ​ላና ይጠጣ ዘንድ በድ​ካ​ሙም ሁሉ መል​ካ​ምን ያይ ዘንድ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ስጦታ ነው። እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ያደ​ረ​ገው ሁሉ ለዘ​ለ​ዓ​ለም እን​ዲ​ኖር ዐወ​ቅሁ፤ በእ​ነ​ር​ሱም ላይ መጨ​መር ከእ​ነ​ር​ሱም ማጕ​ደል አይ​ቻ​ልም፤ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም በፊቱ ይፈሩ ዘንድ አደ​ረገ። በፊት የተ​ደ​ረ​ገው አሁን አለ። ይደ​ረግ ዘንድ ያለ​ውም እነሆ ተደ​ር​ጓል፤ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ያለ​ፈ​ውን መልሶ ይሻ​ዋል።

መክብብ 3:1-15 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ለሁሉም ነገር ጊዜ አለው፤ ከሰማይ በታች ለሚከናወነው ለማንኛውም ነገር ወቅት አለው፤ ለመወለድ ጊዜ አለው፤ ለመሞትም ጊዜ አለው፤ ለመትከል ጊዜ አለው፤ ለመንቀልም ጊዜ አለው፤ ለመግደል ጊዜ አለው፤ ለማዳንም ጊዜ አለው፤ ለማፍረስ ጊዜ አለው፤ ለመገንባትም ጊዜ አለው፤ ለማልቀስ ጊዜ አለው፤ ለመሣቅም ጊዜ አለው፤ ለሐዘን ጊዜ አለው፤ ለጭፈራም ጊዜ አለው፤ ድንጋይ ለመጣል ጊዜ አለው፤ ድንጋይ ለመሰብሰብም ጊዜ አለው፤ ለመተቃቀፍ ጊዜ አለው፤ ለመለያየትም ጊዜ አለው፤ ለመፈለግ ጊዜ አለው፤ ለመተው ጊዜ አለው፤ ለማስቀመጥ ጊዜ አለው፤ አውጥቶ ለመጣልም ጊዜ አለው፤ ለመቅደድ ጊዜ አለው፤ ለመስፋትም ጊዜ አለው፤ ለዝምታ ጊዜ አለው፤ ለመናገርም ጊዜ አለው፤ ለመውደድ ጊዜ አለው፤ ለመጥላትም ጊዜ አለው፤ ለጦርነት ጊዜ አለው፤ ለሰላምም ጊዜ አለው። ሠራተኛ ከጥረቱ የሚያገኘው ትርፍ ምንድን ነው? ሰዎች ይደክሙበት ዘንድ አምላክ የሰጣቸውን ከባድ የሥራ ጫና አየሁ። ሁሉንም ነገር በጊዜው ውብ አድርጎ ሠራው፤ በሰዎችም ልብ ዘላለማዊነትን አኖረ፤ ይሁን እንጂ አምላክ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ያደረገውን ማወቅ አይችሉም። ለሰዎች፣ በሕይወት እያሉ ደስ ከመሠኘትና መልካምን ነገር ከማድረግ የተሻለ ነገር እንደሌለ ዐወቅሁ። ሰው ሁሉ ይበላና ይጠጣ ዘንድ፣ በሚደክምበትም ሁሉ ርካታን ያገኝ ዘንድ ይህ የአምላክ ችሮታ ነው። አምላክ ያደረገው ሁሉ ለዘላለም እንደሚኖር ዐውቃለሁ፤ በርሱ ላይ ምንም አይጨመርም፤ ከርሱም ምንም አይቀነስም፤ ሰዎች ይፈሩት ዘንድ ይህን አደረገ። አሁን ያለው ከዚህ በፊት የነበረው ነው፤ ወደ ፊት የሚሆነውም ቀድሞ የነበረ ነው፤ አምላክም ያለፈውን መልሶ ይሻዋል።

መክብብ 3:1-15 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ለሁሉ ዘመን አለው፥ ከሰማይ በታችም ለሆነ ነገር ሁሉ ጊዜ አለው። ለመወለድ ጊዜ አለው፥ ለመሞትም ጊዜ አለው፥ ለመትከል ጊዜ አለው፥ የተተከለውንም ለመንቀል ጊዜ አለው፥ ለመግደል ጊዜ አለው፥ ለመፈወስም ጊዜ አለው፥ ለማፍረስ ጊዜ አለው፥ ለመሥራትም ጊዜ አለው፥ ለማልቀስ ጊዜ አለው፥ ለመሳቅም ጊዜ አለው፥ ዋይ ለማለት ጊዜ አለው፥ ለመዝፈንም ጊዜ አለው፥ ድንጋይን ለመጣል ጊዜ አለው፥ ድንጋይንም ለመሰብሰብ ጊዜ አለው፥ ለመተቃቀፍ ጊዜ አለው፥ ከመተቃቀፍም ለመራቅ ጊዜ አለው፥ ለመፈለግ ጊዜ አለው፥ ለማጥፋትም ጊዜ አለው፥ ለመጠበቅ ጊዜ አለው፥ ለመጣልም ጊዜ አለው፥ ለመቅደድ ጊዜ አለው፥ ለመስፋትም ጊዜ አለው፥ ዝም ለማለት ጊዜ አለው፥ ለመናገርም ጊዜ አለው፥ ለመውደድ ጊዜ አለው፥ ለመጥላትም ጊዜ አለው፥ ለጦርነት ጊዜ አለው፥ ለሰላምም ጊዜ አለው። ለሠራተኛ የድካሙ ትርፍ ምንድር ነው? እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ይደክሙበት ዘንድ የሰጣቸውን ጥረት አይቻለሁ። ነገርን ሁሉ በጊዜው ውብ አድርጎ ሠራው፥ እግዚአብሔርም ከጥንት ጀምሮ እስከ ፍጻሜ ድረስ የሠራውን ሥራ ሰው መርምሮ እንዳያገኝ ዘላለምነትን በልቡ ሰጠው። ሰው ደስ ከሚለውና በሕይወቱ ሳለ መልካምን ነገር ከሚያደርግ በቀር መልካም ነገር እንደሌለ አወቅሁ። ደግሞም ሰው ሁሉ ይበላና ይጠጣ ዘንድ በድካሙም ሁሉ ደስ ይለው ዘንድ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው። እግዚአብሔር ያደረገው ሁሉ ለዘላለም እንዲኖር አወቅሁ፥ ሊጨመርበት ወይም ከእርሱ ሊጐድል አይቻልም፥ እግዚአብሔርም በፊቱ ይፈሩ ዘንድ አደረገ። አሁን ያለው በፊት ነበረ፥ የሚሆነውም በፊት ሆኖ ነበር፥ እግዚአብሔርም ያለፈውን መልሶ ይሻዋል።

መክብብ 3:1-15 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

በዚህ ዓለም ለሚፈጸም ለማናቸውም ነገር ሁሉ እግዚአብሔር የወሰነለት ዘመንና ጊዜ አለው፤ ስለዚህም እግዚአብሔር በወሰነው መሠረት፥ ለመወለድ ጊዜ አለው፤ ለመሞትም ጊዜ አለው፤ ለመትከል ጊዜ አለው፤ ለመንቀል ጊዜ አለው። ለመግደል ጊዜ አለው፤ ለመፈወስም ጊዜ አለው፤ ለመገንባት ጊዜ አለው፤ ለማፍረስም ጊዜ አለው። ለማልቀስ ጊዜ አለው፤ ለመሳቅም ጊዜ አለው፤ ለሐዘን ጊዜ አለው፤ ለመጨፈርም ጊዜ አለው። ድንጋይ ለመበተን ጊዜ አለው፤ ድንጋይ ለመሰብሰብም ጊዜ አለው፤ ለማቀፍ ጊዜ አለው፤ ለመለያየትም ጊዜ አለው። ለመፈለግ ጊዜ አለው፤ የጠፋውን ላለመፈለግ ጊዜ አለው፤ ለመጠበቅ ጊዜ አለው፤ ለመጣልም ጊዜ አለው። ለመቅደድ ጊዜ አለው፤ ለመስፋትም ጊዜ አለው፤ ለዝምታ ጊዜ አለው፤ ለንግግርም ጊዜ አለው። ለመውደድ ጊዜ አለው፤ ለመጥላትም ጊዜ አለው፤ ለጦርነት ጊዜ አለው፤ ለሰላምም ጊዜ አለው። ታዲያ፥ ሠራተኛ ከድካሙ የሚያገኘው ትርፍ ምንድን ነው? የሰው ልጆች እንዲደክሙበት እግዚአብሔር የሰጣቸውን የከባድ ሥራ ጭነት ተመለከትኩ። እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ ነገር ጊዜ በመወሰን ሁሉን ነገር ውብ አድርጎ ሠርቶታል፤ ዘለዓለማዊነትንም በሰው ልቡና አሳድሮአል፤ ነገር ግን እግዚአብሔር የሚሠራውን ሁሉ እስከ መጨረሻ ያውቅ ዘንድ ለሰው የተሰጠው ዕውቀት ሙሉ አይደለም። ስለዚህ ሰው በሕይወቱ ሳለ መልካም ነገር ከማድረግና ደስ ከሚለው በቀር ሌላ የተሻለ ነገር እንደሌለ ተረድቼአለሁ። ሰው ጥሮ ግሮ ባገኘው የድካም ዋጋ በልቶና ጠጥቶ መደሰት የእግዚአብሔር ስጦታ ነው። እግዚአብሔር የሠራው ነገር ሁሉ ዘለዓለማዊነት እንዳለው ዐውቃለሁ፤ በእርሱ ላይ የሚጨመርበት ወይም ከእርሱ የሚቀነስ ነገር የለም፤ እግዚአብሔር ይህን ያደረገው ሰዎች እርሱን እንዲፈሩት ነው። የሚሆነውና መሆን የሚችለው ነገር ሁሉ ያው ቀድሞ ተደርጎ የነበረው ነው፤ እግዚአብሔር ያንኑ ቀድሞ የፈጠረውን ነገር እንዲደጋገም ያደርጋል።

መክብብ 3:1-15 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ለሁሉ ዘመን አለው፥ ከሰማይ በታችም ለሆነ ነገር ሁሉ ጊዜ አለው። ለልደት ጊዜ አለው፥ ለሞትም ጊዜ አለው፥ ለመትከል ጊዜ አለው፥ የተተከለውንም ለመንቀል ጊዜ አለው፥ ለመግደል ጊዜ አለው፥ ለመፈወስም ጊዜ አለው፥ ለማፍረስ ጊዜ አለው፥ ለመገንባትም ጊዜ አለው፥ ለማልቀስ ጊዜ አለው፥ ለመሳቅም ጊዜ አለው፥ ዋይ ለማለት ጊዜ አለው፥ ለመዝፈንም ጊዜ አለው፥ ድንጋይን ለመበተን ጊዜ አለው፥ ድንጋይንም ለመሰብሰብ ጊዜ አለው፥ ለመተቃቀፍ ጊዜ አለው፥ ከመተቃቀፍም ለመራቅ ጊዜ አለው፥ ለመፈለግ ጊዜ አለው፥ ለማጥፋትም ጊዜ አለው፥ ለመጠበቅ ጊዜ አለው፥ ለመጣልም ጊዜ አለው፥ ለመቅደድ ጊዜ አለው፥ ለመስፋትም ጊዜ አለው፥ ዝም ለማለት ጊዜ አለው፥ ለመናገርም ጊዜ አለው፥ ለመውደድ ጊዜ አለው፥ ለመጥላትም ጊዜ አለው፥ ለጦርነት ጊዜ አለው፥ ለሰላምም ጊዜ አለው። ለሠራተኛ የድካሙ ትርፍ ምንድነው? እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ይደክሙበት ዘንድ የሰጣቸውን ጥረት አይቻለሁ። ነገርን ሁሉ በጊዜው ውብ አድርጎ ሠራው፤ እግዚአብሔርም ከጥንት ጀምሮ እስከ ፍጻሜ ድረስ የሠራውን ሥራ ሰው መርምሮ እንዳያገኝ ዘላለማዊነትን በልቡ ሰጠው። ሰው ደስ ከሚሰኝበትና በሕይወቱ ሳለ መልካምን ነገር ከሚፈጽምበት በቀር ሌላ መልካም ነገር እንደሌለ አወቅሁ። ደግሞም የእግዚአብሔር ስጦታ ሰው ሁሉ ይበላና ይጠጣ ዘንድ በድካሙም ሁሉ ደስ ይለው ዘንድ ነው። እግዚአብሔር የሚያደርገው ሁሉ ለዘለዓለም እንደሚኖር አወቅሁ፥ ምንም የሚጨመርበት ወይም የሚቀነስለት የለም፥ እግዚአብሔርም ሰዎች ይፈሩ ዘንድ አደረገ። አሁን ያለው በፊት ነበረ፥ የሚሆነውም በፊት ሆኖ ነበር፥ እግዚአብሔርም ያለፈውን መልሶ ይሻዋል።