ዘዳግም 25:1-19

ዘዳግም 25:1-19 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

“በሰ​ዎች መካ​ከል ጠብ ቢሆን፥ ወደ ፍር​ድም ቢመጡ፥ ቢፋ​ረ​ዱም ለጻ​ድቁ ይፈ​ረ​ድ​ለት፤ በበ​ደ​ለ​ኛ​ውም ይፈ​ረ​ድ​በት። በደ​ለ​ኛ​ውም መገ​ረፍ ቢገ​ባው እን​ዲ​ገ​ረፍ ፈራጁ በፊቱ በም​ድር ላይ ያጋ​ድ​መው፤ የግ​ር​ፋ​ቱም ቍጥር እንደ ኀጢ​አቱ መጠን ይሁን። ግር​ፋ​ቱም አርባ ይሁን፤ ከዚህ በላይ ጨምሮ ብዙ ግር​ፋት ቢገ​ር​ፈው ወን​ድ​ምህ በፊ​ትህ ነው​ረኛ ይሆ​ና​ልና ከዚህ በላይ አይ​ጨ​መ​ር​በት። “እህ​ል​ህን በም​ታ​በ​ራይ ጊዜ በሬ​ዉን አፉን አት​ሰ​ረው። “ወን​ድ​ማ​ማ​ቾች በአ​ን​ድ​ነት ቢቀ​መጡ፥ አን​ዱም ልጅ ሳይ​ኖ​ረው ቢሞት፥ የሞ​ተው ሰው ሚስት ሌላ ሰው ታገባ ዘንድ ወደ ውጭ አት​ሂድ፤ ነገር ግን የባ​ልዋ ወን​ድም ወደ እር​ስዋ ገብቶ እር​ስ​ዋን ያግባ፤ ከእ​ር​ስ​ዋም ጋር ይኑር። የም​ዋቹ ስም ከእ​ስ​ራ​ኤል ዘንድ እን​ዳ​ይ​ጠፋ ከእ​ር​ስዋ የሚ​ወ​ለ​ደው ልጅ በሞ​ተው በወ​ን​ድሙ ስም ይጠራ። ያም ሰው የወ​ን​ድ​ሙን ሚስት ማግ​ባት ባይ​ወ​ድድ፥ ዋር​ሳ​ዪቱ በበሩ አደ​ባ​ባይ ወደ​ሚ​ቀ​መጡ ሽማ​ግ​ሌ​ዎች ሄዳ፦ ‘ዋር​ሳዬ በእ​ስ​ራ​ኤል ዘንድ ለወ​ን​ድሙ ስም ማቆም እንቢ አለ፤ ከእ​ኔም ጋር ሊኖር አል​ወ​ደ​ደም’ ትበ​ላ​ቸው። የከ​ተ​ማ​ውም ሽማ​ግ​ሌ​ዎች ጠር​ተው ይጠ​ይ​ቁት፤ እር​ሱም በዚያ ቆሞ፦ ‘አገ​ባት ዘንድ አል​ወ​ድ​ድም’ ቢል፥ ዋር​ሳ​ዪቱ በሽ​ማ​ግ​ሌ​ዎቹ ፊት ወደ እርሱ ቀርባ፦ ‘የወ​ን​ድ​ሙን ቤት በማ​ይ​ሠራ ሰው ላይ እን​ዲህ ይደ​ረ​ግ​በ​ታል’ ስትል የአ​ንድ እግ​ሩን ጫማ ታውጣ፤ በፊ​ቱም እን​ትፍ ትበ​ል​በት። በእ​ስ​ራ​ኤ​ልም ዘንድ ስሙ ‘የጫማ ፈቱ ቤት’ ተብሎ ይጠራ። “ሁለት ሰዎች እርስ በር​ሳ​ቸው ቢጣሉ፥ የአ​ን​ደ​ኛ​ውም ሰው ሚስት ባል​ዋን ከሚ​መ​ታው ሰው እጅ ታድ​ነው ዘንድ ብት​ቀ​ርብ፥ እጅ​ዋ​ንም ዘር​ግታ ሁለ​ቱን የብ​ል​ቱን ፍሬ​ዎች ብት​ይዝ፥ እጅ​ዋን ቍረጥ፤ ዐይ​ን​ህም አት​ራ​ራ​ላት። “በከ​ረ​ጢ​ትህ ውስጥ ታላ​ቅና ታናሽ ሚዛን አይ​ኑ​ር​ልህ። በቤ​ትህ ውስጥ ታላ​ቅና ታናሽ መስ​ፈ​ሪያ አይ​ኑ​ር​ልህ። አም​ላ​ክህ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ርስት አድ​ርጎ በሚ​ሰ​ጥህ ምድር ላይ ዕድ​ሜህ ይረ​ዝም ዘንድ እው​ነ​ተ​ኛና ፍጹም ሚዛን ይሁ​ን​ልህ፤ እው​ነ​ተ​ኛና ፍጹም መስ​ፈ​ሪ​ያም ይሁ​ን​ልህ። ይህን የሚ​ያ​ደ​ርግ ሁሉ፥ ክፋ​ት​ንም የሚ​ያ​ደ​ርግ ሁሉ በአ​ም​ላ​ክህ በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ዘንድ የተ​ጠላ ነውና። “ከግ​ብፅ በወ​ጣህ ጊዜ ዐማ​ሌቅ በመ​ን​ገድ ላይ ያደ​ረ​ገ​ብ​ህን ዐስብ፤ በመ​ን​ገድ ላይ እንደ ተቃ​ወ​መህ፥ አን​ተም ተር​በ​ህና ደክ​መህ ሳለህ ጓዝ​ህ​ንና ከአ​ንተ በኋላ ደክ​መው የነ​በ​ሩ​ትን ሁሉ እንደ መታ፤ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ር​ንም አል​ፈ​ራ​ውም። ስለ​ዚህ አም​ላ​ክህ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ትወ​ር​ሳት ዘንድ በሚ​ሰ​ጥህ ምድር ከሚ​ከ​ብ​ቡህ ጠላ​ቶ​ችህ ሁሉ አም​ላ​ክህ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ባሳ​ረ​ፈህ ጊዜ፥ የዐ​ማ​ሌ​ቅን ዝክረ ስሙን ከሰ​ማይ በታች አጥ​ፋው፤ ይህ​ንም አት​ርሳ።

ዘዳግም 25:1-19 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

በሰዎች መካከል ጠብ ቢነሣና ወደ ፍርድ አደባባይ ቢሄዱ፣ ዳኞች ተበዳይን ነጻ፣ በዳይን ግን ጥፋተኛ በማድረግ የፍርድ ውሳኔ ይስጡ። በደለኛው ሰው መገረፍ የሚገባው ሆኖ ከተገኘ፣ ዳኛው መሬት ላይ ያጋድመው፤ ለጥፋቱ ተመጣጣኝ የሆነ ግርፋት እርሱ ባለበት ይገረፍ። ሆኖም ግርፋቱ ከአርባ የሚበልጥ አይሁን፤ ከዚህ ካለፈ ግን፣ ወንድምህ በፊትህ የተዋረደ ይሆናል። የሚያበራየውን በሬ አፉን አትሰር። ወንድማማቾች በአንድነት ቢኖሩና ከእነርሱ አንዱ ወንድ ልጅ ሳይወልድ ቢሞት፣ የሟቹ ሚስት ከቤተ ሰቡ ውጭ ባል ማግባት የለባትም። የባሏ ወንድም ይውሰዳትና ያግባት፤ የዋርሳነት ግዴታውንም ይፈጽምላት። በመጀመሪያ የምትወልደውም ልጅ ስሙ ከእስራኤል ፈጽሞ እንዳይጠፋ በሟች ወንድሙ ስም ይጠራ። ሆኖም ግን አንድ ሰው የወንድሙን ሚስት ለማግባት ባይፈልግ፣ ሴትዮዋ በከተማዪቱ በር ወዳሉት ሽማግሌዎች ሄዳ፣ “የባለቤቴ ወንድም የወንድሙን ስም በእስራኤል ለማስጠራት አልፈለገም፤ የዋርሳነት ግዴታውንም አልፈጸመልኝም” ትበላቸው። ከዚያም የከተማው ሽማግሌዎች ያን ሰው ጠርተው ያነጋግሩት፤ እርሱም፣ “እርሷን ላገባት አልፈልግም” ብሎ በሐሳቡ ቢጸና፣ የወንድሙም ሚስት በሽማግሌዎች ፊት ወደ እርሱ ቀርባ፣ የአንድ እግሩን ጫማ በማውለቅ በፊቱ ላይ ትትፋበትና “የወንድሙን ቤት በማይሠራ ሰው ላይ እንዲህ ያለው ድርጊት ይፈጸምበታል” ትበል። የዚያም ሰው የዘር ሐረግ በእስራኤል ዘንድ፣ “ጫማው የወለቀበት ቤት” ተብሎ ይታወቃል። ሁለት ሰዎች ቢደባደቡ፣ የአንደኛው ሚስት ባሏን ከደብዳቢው እጅ ለማስጣል መጥታ፣ እጇን ዘርግታ ብልቱን ብትይዘው፣ እጇን ቍረጠው፤ አትራራላት። በከረጢትህ ውስጥ ከባድና ቀላል የሆኑ ሁለት የተለያዩ ሚዛኖች አይኑሩህ። በቤትህም ውስጥ ትልቅና ትንሽ የሆኑ ሁለት የተለያዩ መስፈሪያዎች አይኑሩህ። አምላክህ እግዚአብሔር በሚሰጥህ ምድር ዕድሜህ እንዲረዝም፣ ጻድቅና የታመነ ሚዛንና መስፈሪያ ይኑርህ። አምላክህ እግዚአብሔር እንዲህ ያሉትን ነገሮች የሚፈጽመውንና የሚያምታታውን ሁሉ ይጸየፈዋልና። ከግብጽ በወጣህ ጊዜ፣ አማሌቅ በመንገድ በአንተ ላይ ያደረገብህን አስታውስ፤ ደክመህና ዝለህ በነበርህበት ጊዜ፣ በጕዞ ላይ አግኝተውህ፣ ከኋላ ያዘግሙ የነበሩትን ሁሉ ገደሉ፤ እግዚአብሔርንም አልፈሩም። አምላክህ እግዚአብሔር ርስት አድርጎ በሚሰጥህ ምድር ዙሪያ ካሉት ጠላቶችህ ሁሉ ባሳረፈህ ጊዜ፣ ከሰማይ በታች ያለውን የአማሌቅን መታሰቢያ ደምስስ፤ ከቶ እንዳትረሳ!

ዘዳግም 25:1-19 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

በሰዎች መካከል ጠብ ቢሆን፥ ወደ ፍርድም ቢመጡ፥ ፈራጆችም ቢፈርዱባቸው፥ ጻድቁን፦ ደኅና ነህ፥ የበደለውንም፦ በደለኛ ነህ ይበሉአቸው። በደለኛውም መገረፍ ቢገባው እንዲገረፍ ፈራጁ በፊቱ በምድር ላይ ያጋድመው፤ የግርፋቱም ቁጥር እንደ ኃጢአቱ መጠን ይሁን። ግርፋቱም አርባ ይሁን፤ ከዚህ በላይ ጨምሮ ብዙ ግርፋት ቢገርፈው ወንድምህ በፊትህ ነውረኛ ይሆናልና ከዚህ በላይ አይጨመርበት። እህል የሚያበራየውን በሬ አፉን አትሰር። ወንድማማቾች በአንድነት ቢቀመጡ፥ አንዱም ልጅ ሳይኖረው ቢሞት፥ የሞተው ሰው ሚስት ሌላ ሰው ታገባ ዘንድ ወደ ውጭ አትሂድ፤ ነገር ግን የባልዋ ወንድም ወደ እርስዋ ገብቶ እርስዋን ያግባ፥ ከእርስዋም ጋር ይኑር። የምዋቹ ስም ከእስራኤል ዘንድ እንዳይጠፋ ከእርስዋ የሚወለደው በኩር ልጅ በሞተው በወንድሙ ስም ይጠራ። ያም ሰው የወንድሙን ሚስት ማግባት ባይወድድ፥ ዋርሳይቱ በበሩ አደባባይ ወደሚቀመጡ ሽማግሌዎች ሄዳ፦ ዋርሳዬ በእስራኤል ዘንድ ለወንድሙ ስም ማቆም እንቢ አለ፤ ከእኔ ጋር ሊኖርም አልወደደም ትበላቸው። የከተማውም ሽማግሌዎች ጠርተው ይጠይቁት፤ እርሱም በዚያ ቆሞ፦ አገባት ዘንድ አልወድድም ቢል፥ ዋርሳይቱ በሽማግሌዎቹ ፊት ወደ እርሱ ቀርባ፦ የወንድሙን ቤት በማይሠራ ሰው ላይ እንዲህ ይደረግበታል ስትል ጭማውን ከእግሩ ታውጣ፥ በፊቱም እንትፍ ትበልበት። በእስራኤልም ዘንድ ስሙ የጫማ ፈቱ ቤት ተብሎ ይጠራ። ሁለት ሰዎች እርስ በርሳቸው ቢጣሉ፥ የአንደኛውም ሚስት ባልዋን ከሚመታው ሰው እጅ ታድነው ዘንድ ብትቀርብ፥ እጅዋንም ዘርግታ ብልቱን ብትይዝ፥ እጅዋን ቁረጥ፥ ዓይንህም አትራራላት። በከረጢትህ ውስጥ ታላቅና ታናሽ የሆነ ሁለት ዓይነት ሚዛን አይኑርልህ። በቤትህ ውስጥ ታላቅና ታናሽ የሆነ ሁለት ዓይነት መስፈሪያ አይኑርልህ። ይህን የሚያደርግ ሁሉ ክፋትንም የሚያደርግ ሁሉ በአምላክህ በእግዚአብሔር ዘንድ የተጣላ ነውና አምላክህ እግዚአብሔር በሚሰጥህ ምድር ላይ ዕድሜህ ይረዝም ዘንድ እውነተኛና ፍጹም ሚዛን ይሁንልህ፤ እውነተኛና ፍጹም መስፈሪያም ይሁንልህ። ከግብፅ በወጣችሁ ጊዜ አማሌቅ በመንገድ ላይ ያደረገብህን አስብ፤ በመንገድ ላይ እንደ ተቃወመህ፥ አንተም ተስኖህ ደክመህም ሳለህ ከአንተ በኋላ ደክመው የነበሩትን ሁሉ እንደ መታ፤ እግዚአብሔርንም አልፈራም። ስለዚህ አምላክህ እግዚአብሔር ትወርሳት ዘንድ በሚሰጥህ ምድር ከሚከብቡህ ጠላቶችህ ሁሉ አምላክህ እግዚአብሔር ባሳረፈህ ጊዜ፥ የአማሌቅን ዝክረ ስሙን ከሰማይ በታች አጥፋው፤ ይህንን አትርሳ።

ዘዳግም 25:1-19 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

“ሁለት ሰዎች ተጣልተው ክርክር በማንሣት ወደ ፍርድ አደባባይ ቢመጡ ተገፊውን ነጻ፥ ገፊውን ግን በደለኛ አድርገው ይፍረዱ፤ በደል የፈጸመው ሰው በግርፋት እንዲቀጣ ቢያስፈልግ፥ በደረቱ መሬት ላይ አስተኝተው ጀርባውን እንዲገርፉት ዳኛው ይዘዝ፤ የሚገረፈውም ዳኛው ባለበትና የግርፋቱም ቊጥር የሚወሰነው ወንጀለኛው በሠራው በደል መጠን ይሆናል። እስከ አርባ ጅራፍ ሊገርፈው ይችላል፤ ከአርባ ግን መብለጥ የለበትም፤ ከዚያ በላይ ቢገረፍ ወገንህ በፊትህ የተዋረደ ይሆናል። “እህል በምታበራይበት ጊዜ የሚያበራየውን በሬ አፉን አትሰር። “ወንድማማቾች በአንድ ርስት ላይ ቢኖሩና አንደኛው ልጅ ሳይወልድ ቢሞት፥ የሟቹ ሚስት ከቤተሰብ ውጪ የሆነ ሌላ ሰው ማግባት አይኖርባትም፤ የባልዋ ወንድም እርስዋን በማግባት የዋርሳነት ግዴታውን ይፈጽምላት። ይህም በሚሆንበት ጊዜ በመጀመሪያ የሚወለደው ወንድ ልጅ በሟቹ ስም ይጠራ፤ በዚህም ዐይነት በእስራኤል የሟቹ የትውልድ ሐረግ ሳይጠፋ መቀጠል ይችላል። ነገር ግን የሟቹ ወንድም እርስዋን ለማግባት ባይፈልግ፥ ወደ ከተማይቱ መሪዎች ዘንድ ሄዳ ‘የባሌ ወንድም ግዴታውን ለመፈጸም ፈቃደኛ አልሆነም፤ ለሟቹ ወንድም በእስራኤል ሕዝብ መካከል ዘር ለመተካት ፈቃደኛ አልሆነም’ በማለት ታስረዳ፤ ከዚህ በኋላ የከተማይቱ መሪዎች ሰውየውን ጠርተው ያነጋግሩት፤ አሁንም እርስዋን ለማግባት ፈቃደኛ ባይሆን የሟቹ ሚስት በከተማይቱ መሪዎች ፊት ወደ እርሱ ትቅረብ፤ ከእግሩ ጫማዎች አንዱን አውልቃ ምራቋን በፊቱ ላይ በመትፋት ‘ለወንድሙ ዘር ለመተካት እምቢ ለሚል ሰው ይህን ዐይነት አሳፋሪ ነገር ሊፈጸምበት ይገባል’ ትበል። የዚያም ሰው ቤተሰብ በእስራኤል ‘ጫማው የወለቀበት ሰው ቤተሰብ’ እየተባለ በመነቀፍ ሲጠራ ይኖራል። “ሁለት ሰዎች ተጣልተው በሚተናነቁበት ጊዜ የአንደኛው ሚስት ባልዋን ለማገዝ የሌላውን ሰው ብልት ብትጨብጥ፥ ምሕረት ሳይደረግላት እጅዋ ይቈረጥ። “ትልቅና ትንሽ ሚዛን ወይም መስፈሪያ በመያዝ ሰውን አታጭበርብር። እግዚአብሔር አምላክህ በሚሰጥህ ምድር ለረጅም ዘመን ትኖር ዘንድ እውነተኛና ታማኝ የሆነ ሚዛንና መስፈሪያ ብቻ ይኑርህ፤ እግዚአብሔር አምላክህ እንደዚህ አድርገው በማጭበርበር ተንኰል የሚሠሩትን ሰዎች ሁሉ ይጠላል። “አንተ ከግብጽ በወጣህበት ጊዜ ዐማሌቃውያን የፈጸሙብህን በደል አትርሳ፤ እነርሱ እግዚአብሔርን የሚፈሩ አይደሉም፤ አንተ በጒዞ ላይ ደክሞህ በነበረ ጊዜ በኋላ በኩል አደጋ ጣሉብህ፤ ደክመው ወደ ኋላ ያዘግሙ የነበሩትንም ሁሉ ገደሉ። ስለዚህም እግዚአብሔር አምላክህ ምድሪቱን አውርሶህ በዙሪያህ ከሚኖሩ ጠላቶችህ ሁሉ በሚያሳርፍህ ጊዜ በምድር ላይ ማንም የሚያስታውሳቸው እስኪጠፋ ድረስ ዐማሌቃውያንን ሁሉ ደምስስ! ይህን ከቶ አትርሳ!

ዘዳግም 25:1-19 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

“በሰዎች መካከል ጠብ ቢነሣና ወደ ፍርድ አደባባይ ቢሄዱ፥ ዳኞች ተበዳይን ነጻ፥ በዳይን ግን ጥፋተኛ በማድረግ የፍርድ ውሳኔ ይስጡ። በደለኛው ሰው መገረፍ የሚገባው ሆኖ ከተገኘ ዳኛው መሬት ላይ ያጋድመው፤ ለጥፋቱ ተመጣጣኝ የሆነ ግርፋት እርሱ ባለበት ይገረፍ። ሆኖም ግርፋቱ ከአርባ የሚበልጥ አይሁን፤ ከዚህ ካለፈ ግን፥ ወንድምህ በፊትህ የተዋረደ ይሆናል። “እህል እያበራየ ያለውን በሬ አፉን አትሰር። “ወንድማማቾች በአንድነት ቢኖሩና ከእነርሱ አንዱ ወንድ ልጅ ሳይወልድ ቢሞት፥ የሟቹ ሚስት ከቤተሰቡ ውጭ ባል ማግባት የለባትም። የባሏ ወንድም ይውሰዳትና ያግባት፤ የዋርሳነት ግዴታውንም ይፈጽምላት። በመጀመሪያ የምትወልደውም ልጅ ስሙ ከእስራኤል ፈጽሞ እንዳይጠፋ በሟች ወንድሙ ስም ይጠራ። ሆኖም ግን አንድ ሰው የወንድሙን ሚስት ለማግባት ባይፈልግ፥ ሴትዮዋ በከተማዋ በር ወዳሉት ሽማግሌዎች ሄዳ፥ ‘የባለቤቴ ወንድም የወንድሙን ስም በእስራኤል ለማስጠራት አልፈለገም፤ የዋርሳነት ግዴታውንም አልፈጸመልኝም’ ትበላቸው። ከዚያም የከተማው ሽማግሌዎች ሰው ጠርተው ያነጋግሩት፤ እርሱም፥ ‘እርሷን ላገባት አልፈልግም’ ብሎ በሐሳቡ ቢጸና፥ የወንድሙም ሚስት በሽማግሌዎች ፊት ወደ እርሱ ቀርባ፥ የአንድ እግሩን ጫማ በማውለቅ በፊቱ ላይ ትትፋበትና ‘የወንድሙን ቤት በማይሠራ ሰው ላይ እንዲህ ያለው ድርጊት ይፈጸምበታል’ ትበል። የዚያም ሰው የዘር ሐረግ በእስራኤል ዘንድ፥ ‘ጫማው የወለቀበት ቤት’ ተብሎ ይታወቃል። “ሁለት ሰዎች ቢደባደቡ፥ የአንደኛው ሚስት ባሏን ከደብዳቢው እጅ ለማስጣል መጥታ፥ እጅዋን ዘርግታ ብልቱን ብትይዘው፥ እጅዋን ቁረጠው፤ አትራራላት። “በከረጢትህ ውስጥ ከባድና ቀላል የሆኑ ሁለት የተለያዩ ሚዛኖች አይኑሩህ። በቤትህም ውስጥ ትልቅና ትንሽ የሆኑ ሁለት የተለያዩ መስፈሪያዎች አይኑሩህ። ጌታ እግዚአብሔር በሚሰጥህ ምድር ዕድሜህ እንዲረዝም፥ ትክክለኛና የታመነ ሚዛንና መስፈሪያ ይኑርህ። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ያሉትን ነገሮች የሚፈጽመውንና የሚያምታታውን ሁሉ ይጸየፈዋልና። “ከግብጽ በወጣህ ጊዜ፥ አማሌቅ በመንገድ በአንተ ላይ ያደረገብህን አስታውስ፤ ደክመህና ዝለህ በነበርህበት ጊዜ፥ በጉዞ ላይ አግኝተውህ፥ ከኋላ ያዘግሙ የነበሩትን ሁሉ ገደሉ፤ እግዚአብሔርንም አልፈሩም። ጌታ እግዚአብሔር ርስት አድርጎ በሚሰጥህ ምድር ዙሪያ ካሉት ጠላቶችህ ሁሉ ባሳረፈህ ጊዜ፥ ከሰማይ በታች ያለውን የአማሌቅን መታሰቢያ መደምሰስን፥ ይህንን አትርሳ።”