ዳንኤል 6:19-24

ዳንኤል 6:19-24 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

በነጋውም ንጉሡ ማልዶ ተነሣ፥ ፈጥኖም ወደ አንበሶች ጕድጓድ ሄደ። ወደ ጉድጓዱም ወደ ዳንኤል በቀረበ ጊዜ በኀዘን ቃል ጠራው፥ ንጉሡም ተናገረ ዳንኤልንም፦ የሕያው አምላክ ባሪያ ዳንኤል ሆይ፥ ሁልጊዜ የምታመልከው አምላክህ ከአንበሶች ያድንህ ዘንድ ችሎአልን? አለው። ዳንኤልም ንጉሡን፦ ንጉሥ ሆይ፥ ሺህ ዓመት ንገሥ። በፊቱ ቅንነት ተገኝቶብኛልና፥ በአንተም ፊት ደግሞ፥ ንጉሥ ሆይ፥ አልበደልሁምና አምላኬ መልአኩን ልኮ የአንበሶችን አፍ ዘጋ፥ እነርሱም አልጐዱኝም አለው። የዚያን ጊዜም ንጉሡ እጅግ ደስ አለው፥ ዳንኤልንም ከጕድጓዱ ያወጡት ዘንድ አዘዘ፥ ዳንኤልም ከጕድጓድ ወጣ፥ በአምላኩም ታምኖ ነበርና አንዳች ጉዳት አልተገኘበትም። ንጉሡም አዘዘ፥ ዳንኤልንም የከሰሱ እነዚያን ሰዎች አመጡአቸው፥ እነርሱንና ልጆቻቸውንም ሚስቶቻቸውንም በአንበሶች ጕድጓድ ጣሉአቸው፥ ወደ ጕድጓዱም መጨረሻ ሳይደርሱ አንበሶች ያዙአቸው አጥንታቸውንም ሁሉ ሰባበሩ።

ዳንኤል 6:19-24 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

በማለዳም ገና ጎሕ ሲቀድ ንጉሡ ተነሥቶ በፍጥነት ወደ አንበሶቹ ጒድጓድ ሄደ። እዚያም በደረሰ ጊዜ ሐዘን በተሞላበት ድምፅ “የሕያው አምላክ አገልጋይ ዳንኤል ሆይ! ዘወትር በታማኝነት የምታገለግለው አምላክህ ከአንበሶቹ ሊያድንህ ችሎአልን?” ብሎ ተጣራ። ዳንኤልም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ንጉሥ ሆይ! ለዘለዓለም ኑር! አንበሶቹ እንዳይጐዱኝ እግዚአብሔር መልአኩን ልኮ አፋቸውን ዘጋ፤ ይህንንም ያደረገው እኔ በእርሱ ዘንድ ንጹሕ መሆኔንና አንተንም አለመበደሌን ስላወቀ ነው።” ንጉሡም እጅግ ደስ አለው፤ ዳንኤልንም ከጒድጓዱ ውስጥ እንዲያወጡት ትእዛዝ ሰጠ፤ ባወጡትም ጊዜ በእግዚአብሔር በመታመኑ በሰውነቱ ላይ ምንም ጒዳት እንዳልደረሰበት ታወቀ። ከዚህም በኋላ ዳንኤልን የከሰሱት ሰዎች ተይዘው እንዲመጡ ንጉሡ አዘዘ፤ እነርሱም ተይዘው ከሚስቶቻቸውና ከልጆቻቸው ጋር በአንበሶች ጒድጓድ ውስጥ እንዲጣሉ አደረገ፤ ገና ወደ ጒድጓዱ አዘቅት ሳይደርሱም አንበሶቹ ቦጫጨቋቸው፤ አጥንቶቻቸውንም ሁሉ ሰባበሩ።