ዳንኤል 6:10-15

ዳንኤል 6:10-15 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ዳንኤልም ዐዋጁ እንደ ወጣ ባወቀ ጊዜ ወደ ቤቱ ሄደ፤ መስኮቶቹ በኢየሩሳሌም አንጻር ተከፍተው ባሉበት በሰገነቱ ቀድሞ ያደርግ እንደ ነበረው በቀን ሦስት ጊዜ ተንበርክኮ ጸለየ፤ አምላኩንም አመሰገነ። ሰዎቹም በአንድ ላይ ሄደው፣ ዳንኤልን ሲጸልይና አምላኩን ሲማፀን አገኙት። ወደ ንጉሡም ሄደው፣ “ንጉሥ ሆይ፤ በሚቀጥሉት ሠላሳ ቀናት ማንም ሰው ወደ አንተ ካልሆነ በቀር ወደ ሰውም ሆነ ወደ ማንኛውም አምላክ ቢጸልይ፣ በአንበሶች ጕድጓድ ውስጥ እንደሚጣል ዐዋጅ አውጥተህ አልነበረምን?” ሲሉ እርሱ ስላወጣው ዐዋጅ ጠየቁት። ንጉሡም፣ “ዐዋጁ እንደማይሻረው እንደ ሜዶንና እንደ ፋርስ ሕግ የጸና ነው” ሲል መለሰ። እነርሱም ንጉሡን፣ “ንጉሥ ሆይ፤ ከይሁዳ ምርኮኞች አንዱ የሆነው ዳንኤል፣ አንተንም ሆነ በጽሑፍ ያወጣኸውን ዐዋጅ አያከብርም፤ አሁንም በቀን ሦስት ጊዜ ወደ አምላኩ ይጸልያል” አሉት። ንጉሡ ይህን በሰማ ጊዜ እጅግ ዐዘነ፤ ዳንኤልን ለማዳን ወሰነ፤ ፀሓይ እስክትጠልቅም ድረስ የተቻለውን ሁሉ አደረገ። ከዚያም ሰዎቹ በአንድ ላይ ወደ ንጉሡ ቀርበው፣ “ንጉሥ ሆይ፤ በሜዶንና በፋርስ ሕግ መሠረት፣ አንድ ንጉሥ ያወጣው ዐዋጅም ሆነ ትእዛዝ ሊለወጥ እንደማይችል ዕወቅ” አሉት።

ዳንኤል 6:10-15 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ዳንኤልም ጽሕፈቱ እንደ ተጻፈ ባወቀ ጊዜ ወደ ቤቱ ገባ፥ የእልፍኙም መስኮቶች ወደ ኢየሩሳሌም አንጻር ተከፍተው ነበር፥ ቀድሞም ያደርግ እንደ ነበረ በየዕለቱ ሦስት ጊዜ በጕልበቱ ተንበርክኮ በአምላኩ ፊት ጸለየ አመሰገነም። እነዚያም ሰዎች ተሰብስበው ዳንኤል በአምላኩ ፊት ሲጸልይና ሲለምን አገኙት። ወደ ንጉሡም ቀርበው ስለ ንጉሡ ትእዛዝ፦ ንጉሥ ሆይ፥ ከአንተ በቀር እስከ ሠላሳ ቀን ድረስ ከአምላክ ወይም ከሰው የሚለምን ሰው ሁሉ በአንበሶች ጕድጓድ ውስጥ እንዲጣል ትእዛዝ አልጻፍህምን? አሉት። ንጉሡም መልሶ፦ ነገሩ እንደማይለወጠው እንደ ሜዶንና እንደ ፋርስ ሕግ እውነት ነው አላቸው። የዚያን ጊዜም በንጉሡ ፊት መልሰው፦ ንጉሥ ሆይ፥ ከይሁዳ ምርኮኞች የሆነው ዳንኤል በየዕለቱ ሦስት ጊዜ ልመናውን ይለምናል እንጂ አንተንና የጻፍኸውን ትእዛዝ አይቀበልም አሉት። ንጉሡም ይህን ቃል በሰማ ጊዜ በጣም አዘነ፥ ያድነውም ዘንድ ልቡን ወደ ዳንኤል አደረገ፥ ሊያድነውም ፀሐይ እስኪገባ ድረስ ደከመ። የዚያን ጊዜም እነዚያ ሰዎች ወደ ንጉሡ ተሰብስበው ንጉሡን፦ ንጉሥ ሆይ፥ ንጉሡ ያጸናው ትእዛዝ ወይም ሥርዓት ይለወጥ ዘንድ እንዳይገባ የሜዶንና የፋርስ ሕግ እንደ ሆነ እወቅ አሉት።

ዳንኤል 6:10-15 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ዳንኤል ዐዋጁ ተፈርሞበት እንደ ጸና ቢያውቅም እንኳ ወደሚኖርበት ሰገነት ወጣ፤ የሚኖርበትም ሰገነት በኢየሩሳሌም ትይዩ የተከፈቱ መስኮቶች ነበሩት፤ ከዚህ በፊት ያደርገው እንደ ነበረም በጒልበቱ በመንበርከክ አምላኩን እያመሰገነ በቀን ሦስት ጊዜ ይጸልይ ነበር። እነዚህም ዐድመኞች በአንድነት ሄደው፥ ዳንኤል ወደ ፈጣሪው ሲጸልይና ሲለምን አገኙት። ሁሉም በአንድነት ወደ ንጉሡ ሄደው የወጣውን ዐዋጅ በመጣሱ ዳንኤልን እንዲህ ብለው ከሰሱት፦ “ንጉሥ ሆይ፥ እስከ ሠላሳ ቀን ወደ አንተ ካልሆነ በቀር ወደማንኛውም አምላክ ወይም ሰው የሚጸልይ በአንበሶች ጒድጓድ ውስጥ እንደሚጣል ዐዋጅ አውጥተህ ፈርመህበት አልነበረምን?” ንጉሡም “አዎ፥ እንደ ሜዶንና እንደ ፋርስ ሕግ የጠበቀና የማይለወጥ ዐዋጅ ወጥቶአል” አለ። እነርሱም “እንግዲያውስ ንጉሥ ሆይ! ከይሁዳ ምርኮኞች አንዱ የሆነው ዳንኤል አንተን አያከብርህም፤ ፈርመህበት የወጣውንም ዐዋጅ በመጣስ በቀን ሦስት ጊዜ ወደ አምላኩ ይጸልያል” አሉት። ንጉሡም ይህን በሰማ ጊዜ እጅግ አዘነ፤ ዳንኤልንም ለማዳን ወሰነ፤ ፀሐይም እስክትጠልቅ ድረስ እርሱን ለማዳን የሚችልበትን ዘዴ ሁሉ ለማግኘት ሞከረ። ሰዎቹም በአንድነት ወደ ንጉሡ መጥተው “ንጉሥ ሆይ! በሜዶንና በፋርስ ሕግ መሠረት አንድ ንጉሥ ያስተላለፈው ዐዋጅ ወይም ትእዛዝ መለወጥ እንደማይችል ዕወቅ!” አሉት።