ዳንኤል 6:1-13

ዳንኤል 6:1-13 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ዳርዮስ በመንግሥቱ ሁሉ ላይ እንዲገዙ አንድ መቶ ሃያ መሳፍንትን መሾም ፈለገ፤ በእነዚህም ላይ ሦስት የበላይ አስተዳዳሪዎችን አደረገ፤ ከእነርሱም አንዱ ዳንኤል ነበረ። ንጉሡ ጕዳት እንዳይደርስበት፣ መሳፍንቱ ተጠሪነታቸው ለሦስቱ የበላይ አስተዳዳሪዎች እንዲሆን ተደረገ። ከመሳፍንቱና ከበላይ አስተዳዳሪዎቹ ሁሉ ይልቅ ዳንኤል ልዩ የጥበብ መንፈስ የሞላበት ሆኖ በመገኘቱ፣ ንጉሡ በመላው ግዛቱ ላይ ሊሾመው ዐሰበ። በዚህ ምክንያት የበላይ አስተዳዳሪዎቹና መሳፍንቱ ዳንኤል በሚያከናውነው የመንግሥት ሥራ ሊከስሱት ሰበብ ፈለጉ፤ ነገር ግን አላገኙበትም፤ ዳንኤል ታማኝ፣ ጠንቃቃና በሥራው እንከን የሌለበት ስለ ነበር፣ በርሱ ላይ ስሕተት ሊያገኙ አልቻሉም። እነዚህም ሰዎች፣ “ከአምላኩ ሕግ ጋራ በተያያዘ ጕዳይ ካልሆነ በቀር፣ ይህን ዳንኤልን የምንከስበት ምንም ሰበብ አናገኝበትም” አሉ። ከዚያም የበላይ አስተዳዳሪዎቹና መሳፍንቱ በአንድነት ወደ ንጉሡ ሄደው እንዲህ አሉ፤ “ንጉሥ ዳርዮስ ሆይ፤ ለዘላለም ንገሥ! ንጉሥ ሆይ፤ እስከ ሠላሳ ቀን ድረስ ወደ አንተ ካልሆነ በቀር ማንም ሰው ወደ ሌላ ሰውም ሆነ ወደ ሌላ አምላክ መጸለይ እንደሌለበት ንጉሡ ዐዋጅ እንዲያወጣ፣ ትእዛዙም እንዲፈጸም፣ ይህንም የተላለፈ ወደ አንበሶች ጕድጓድ እንዲጣል፣ የመንግሥት የበላይ አስተዳዳሪዎች፣ መኳንንት፣ መሳፍንት፣ አማካሪዎችና አገረ ገዦች ሁሉ በአንድነት ተስማምተዋል። ንጉሥ ሆይ፤ ይህን ዐዋጅ አውጣ፤ እንደማይሻረውና እንደማይለወጠው የሜዶንና የፋርስ ሕግ እንዲሆን ትእዛዙን በጽሑፍ አድርገው።” ስለዚህ ንጉሥ ዳርዮስ ዐዋጁ ተጽፎ እንዲወጣ አደረገ። ዳንኤልም ዐዋጁ እንደ ወጣ ባወቀ ጊዜ ወደ ቤቱ ሄደ፤ መስኮቶቹ በኢየሩሳሌም አንጻር ተከፍተው ባሉበት በሰገነቱ ቀድሞ ያደርግ እንደ ነበረው በቀን ሦስት ጊዜ ተንበርክኮ ጸለየ፤ አምላኩንም አመሰገነ። ሰዎቹም በአንድ ላይ ሄደው፣ ዳንኤልን ሲጸልይና አምላኩን ሲማፀን አገኙት። ወደ ንጉሡም ሄደው፣ “ንጉሥ ሆይ፤ በሚቀጥሉት ሠላሳ ቀናት ማንም ሰው ወደ አንተ ካልሆነ በቀር ወደ ሰውም ሆነ ወደ ማንኛውም አምላክ ቢጸልይ፣ በአንበሶች ጕድጓድ ውስጥ እንደሚጣል ዐዋጅ አውጥተህ አልነበረምን?” ሲሉ እርሱ ስላወጣው ዐዋጅ ጠየቁት። ንጉሡም፣ “ዐዋጁ እንደማይሻረው እንደ ሜዶንና እንደ ፋርስ ሕግ የጸና ነው” ሲል መለሰ። እነርሱም ንጉሡን፣ “ንጉሥ ሆይ፤ ከይሁዳ ምርኮኞች አንዱ የሆነው ዳንኤል፣ አንተንም ሆነ በጽሑፍ ያወጣኸውን ዐዋጅ አያከብርም፤ አሁንም በቀን ሦስት ጊዜ ወደ አምላኩ ይጸልያል” አሉት።

ዳንኤል 6:1-13 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ዳርዮስም በመንግሥቱ ሁሉ ዘንድ እንዲሆኑ መቶ ሀያ መሳፍንት በመንግሥቱ ላይ ይሾም ዘንድ ወደደ። መሳፍንቱም ሒሳቡን ያመጡላቸው ዘንድ፥ ንጉሡም እንዳይጐዳ ሦስት አለቆች በላያቸው አደረገ፥ ከእነርሱም አንደኛው ዳንኤል ነበረ። ዳንኤልም መልካም መንፈስ ስላለው ከአለቆችና ከመሳፍንት በለጠ፥ ንጉሡም በመንግሥቱ ሁሉ ላይ ይሾመው ዘንድ አሰበ። የዚያን ጊዜም አለቆችና መሳፍንቱ ስለ መንግሥቱ በዳንኤል ላይ ሰበብ ይፈልጉ ነበር፥ ነገር ግን የታመነ ነበረና፥ ስሕተትና በደልም አልተኘበትምና በእርሱ ላይ ሰበብና በደል ያገኙበት ዘንድ አልቻሉም። እነዚያም ሰዎች፦ ከአምላኩ ሕግ በቀር በዚህ በዳንኤል ላይ ሌላ ሰበብ አናገኝበትም አሉ። የዚያን ጊዜም አለቆቹና መሳፍንቱ ወደ ንጉሡ ተሰብስበው እንዲህ አሉት፦ ንጉሥ ዳርዮስ ሆይ፥ ሺህ ዓመት ንገሥ። የመንግሥቱ አለቆች ሁሉ ሹማምቶችና መሳፍንት አማካሪዎችና አዛዦች፦ ንጉሥ ሆይ፥ ከአንተ በቀር ማንም እስከ ሠላሳ ቀን ድረስ ልመና ከአምላክ ወይም ከሰው ቢለምን፥ በአንበሶች ጕድጓድ ውስጥ ይጣል የሚል የንጉሥ ሕግና ብርቱ ትእዛዝ ይወጣ ዘንድ ተማከሩ። አሁንም፥ ንጉሥ ሆይ፥ እንደማይለወጠው እንደ ሜዶንና እንደ ፋርስ ሕግ፥ እንዳይለወጥ ትእዛዙን አጽና፥ ጽሕፈቱንም ጻፍ። ንጉሡም ዳርዮስ ጽሕፈቱንና ትእዛዙን ጻፈ። ዳንኤልም ጽሕፈቱ እንደ ተጻፈ ባወቀ ጊዜ ወደ ቤቱ ገባ፥ የእልፍኙም መስኮቶች ወደ ኢየሩሳሌም አንጻር ተከፍተው ነበር፥ ቀድሞም ያደርግ እንደ ነበረ በየዕለቱ ሦስት ጊዜ በጕልበቱ ተንበርክኮ በአምላኩ ፊት ጸለየ አመሰገነም። እነዚያም ሰዎች ተሰብስበው ዳንኤል በአምላኩ ፊት ሲጸልይና ሲለምን አገኙት። ወደ ንጉሡም ቀርበው ስለ ንጉሡ ትእዛዝ፦ ንጉሥ ሆይ፥ ከአንተ በቀር እስከ ሠላሳ ቀን ድረስ ከአምላክ ወይም ከሰው የሚለምን ሰው ሁሉ በአንበሶች ጕድጓድ ውስጥ እንዲጣል ትእዛዝ አልጻፍህምን? አሉት። ንጉሡም መልሶ፦ ነገሩ እንደማይለወጠው እንደ ሜዶንና እንደ ፋርስ ሕግ እውነት ነው አላቸው። የዚያን ጊዜም በንጉሡ ፊት መልሰው፦ ንጉሥ ሆይ፥ ከይሁዳ ምርኮኞች የሆነው ዳንኤል በየዕለቱ ሦስት ጊዜ ልመናውን ይለምናል እንጂ አንተንና የጻፍኸውን ትእዛዝ አይቀበልም አሉት።

ዳንኤል 6:1-13 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ዳርዮስ በመንግሥቱ ግዛት ሁሉ ላይ እንዲያስተዳድሩ መቶ ኻያ አገረ ገዢዎች ለመሾም ፈለገ። በተጨማሪም የንጉሡ ቅርብ ረዳቶች ሆነው ንጉሡ ምንም ነገር እንዳይጐድልበት አገረ ገዢዎቹን እንዲቈጣጠሩ ዳንኤልንና ሌሎችን ሁለት ሰዎች መረጠ። ዳንኤል ባለው ልዩ የሥራ ችሎታ ከሌሎቹ አገረ ገዢዎችና ባለ ሥልጣኖች በልጦ መገኘቱን በተግባር አስመሰከረ፤ ስለዚህ ንጉሡ በመንግሥቱ ሁሉ ላይ ኀላፊ አድርጎ ሊሾመው አሰበ። ከዚህ በኋላ ሌሎቹ አገረ ገዢዎችና ባለ ሥልጣኖች በዳንኤልና በሚያከናውነው የመንግሥት ሥራ ላይ ክስ ለመመሥረት የሚያስችላቸውን ወንጀል ለማግኘት ፈለጉ፤ ነገር ግን ዳንኤል እጅግ ጠንቃቃና ታማኝ ስለ ነበር ምንም ዐይነት ስሕተት ወይም በደል ሊያገኙበት አልቻሉም። ስለዚህም እርስ በርሳቸው “ከአምላኩ ሕግ በቀር ዳንኤልን የምንከስበት ምንም ዐይነት በደል ማግኘት አልቻልንም” ተባባሉ። ከዚህ በኋላ አገረ ገዢዎቹና ባለሥልጣኖቹ በማደም ወደ ንጉሡ ሄደው እንዲህ አሉት፦ “ንጉሥ ዳርዮስ ሆይ! አንተ ለዘለዓለም ኑር! እኛ በመንግሥትህ አስተዳደር ሥራ ላይ የተመደብን የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣኖች፥ ዐቃብያነ ሕግ፥ እንደራሴዎች፥ አማካሪዎችና አገረ ገዢዎች የተስማማንበት አንድ ነገር አለ፤ ይኸውም ከአሁን ጀምሮ እስከ ሠላሳ ቀን ድረስ ወደ አንተ ካልሆነ በቀር ወደማንኛውም አምላክ ወይም ሰው ጸሎት እንዳይደረግ ዐዋጅ እንድታስነግር ነው፤ ይህንንም ዐዋጅ የሚተላለፍ ቢኖር በአንበሶች ጒድጓድ እንዲጣል እዘዝ። እንግዲህ ንጉሥ ሆይ! ይህ ዐዋጅ እንደ ሜዶንና እንደ ፋርስ ሕግ የጠበቀና የማይለወጥ እንዲሆን ፈርምበት።” በዚህም ዐይነት ንጉሥ ዳርዮስ ዐዋጁን በፊርማ አጸና። ዳንኤል ዐዋጁ ተፈርሞበት እንደ ጸና ቢያውቅም እንኳ ወደሚኖርበት ሰገነት ወጣ፤ የሚኖርበትም ሰገነት በኢየሩሳሌም ትይዩ የተከፈቱ መስኮቶች ነበሩት፤ ከዚህ በፊት ያደርገው እንደ ነበረም በጒልበቱ በመንበርከክ አምላኩን እያመሰገነ በቀን ሦስት ጊዜ ይጸልይ ነበር። እነዚህም ዐድመኞች በአንድነት ሄደው፥ ዳንኤል ወደ ፈጣሪው ሲጸልይና ሲለምን አገኙት። ሁሉም በአንድነት ወደ ንጉሡ ሄደው የወጣውን ዐዋጅ በመጣሱ ዳንኤልን እንዲህ ብለው ከሰሱት፦ “ንጉሥ ሆይ፥ እስከ ሠላሳ ቀን ወደ አንተ ካልሆነ በቀር ወደማንኛውም አምላክ ወይም ሰው የሚጸልይ በአንበሶች ጒድጓድ ውስጥ እንደሚጣል ዐዋጅ አውጥተህ ፈርመህበት አልነበረምን?” ንጉሡም “አዎ፥ እንደ ሜዶንና እንደ ፋርስ ሕግ የጠበቀና የማይለወጥ ዐዋጅ ወጥቶአል” አለ። እነርሱም “እንግዲያውስ ንጉሥ ሆይ! ከይሁዳ ምርኮኞች አንዱ የሆነው ዳንኤል አንተን አያከብርህም፤ ፈርመህበት የወጣውንም ዐዋጅ በመጣስ በቀን ሦስት ጊዜ ወደ አምላኩ ይጸልያል” አሉት።