ዳንኤል 4:24-27
ዳንኤል 4:24-27 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
“ንጉሥ ሆይ፤ ትርጕሙ ይህ ነው፤ ልዑሉ በንጉሡ በጌታዬ ላይ ያወጣው ዐዋጅ ይህ ነው፤ ከሕዝብ ተለይተህ ትሰደዳለህ፤ ዱር አራዊትም ጋራ ትኖራለህ። እንደ ከብት ሣር ትበላለህ፤ በሰማይ ጠልም ትረሰርሳለህ፤ ልዑሉ በሰዎች መንግሥታት ሁሉ ላይ እንደሚገዛና እነዚህንም መንግሥታት ለወደደው እንደሚሰጥ እስክታውቅ ድረስ ሰባት ዓመታት ያልፉብሃል። የዛፉ ጕቶ ከነሥሩ እንዲቀር መታዘዙ፣ ሥልጣን ከሰማይ መሆኑን ስታውቅ መንግሥትህ እንደሚመለስልህ ያመለክታል። ስለዚህ ንጉሥ ሆይ፤ ምክሬን ስማ፤ ኀጢአት መሥራትን ትተህ ትክክለኛ የሆነውን አድርግ፤ ክፋትን ትተህ ለተጨቈኑት ቸርነትን አድርግ፤ ምናልባት በሰላም የምትኖርበት ዘመን ይራዘምልህ ይሆናል።”
ዳንኤል 4:24-27 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በጌታዬ በንጉሥ ላይ የወረደው የልዑሉ ትእዛዝ ነው፥ ልዑሉም በሰዎች መንግሥት ላይ እንዲሠለጥን፥ ለሚወድደውም እንዲሰጠው እስክታውቅ ድረስ ከሰዎች ተለይተህ ትሰደዳለህ፥ መኖሪያህም ከምድር አራዊት ጋር ይሆናል፥ እንደ በሬም ሣር ትበላ ዘንድ ትገደዳለህ፥ በሰማይም ጠል ትረሰርሳለህ፥ ሰባት ዘመናትም ያልፉብሃል። የዛፉንም ጉቶ ይተዉት ዘንድ ማዘዙ፥ ሥልጣን ከሰማያት እንደ ሆነ ካወቅህ በኋላ መንግሥትህ ይቆይልሃል። ንጉሥ ሆይ፥ ስለዚህ ምናልባት የደኅንነትህ ዘመን ይረዝም እንደ ሆነ ምክሬ ደስ ያሰኝህ፥ ኃጢአትህንም በጽድቅ፥ በደልህንም ለድሆች በመመመጽወት አስቀር።
ዳንኤል 4:24-27 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
“ንጉሥ ሆይ! እነሆ፥ ትርጒሙ ይህ ነው፤ ልዑል እግዚአብሔር በአንተ በጌታዬ በንጉሡ ላይ እንዲፈጸም የወሰነው ነገር የሚከተለው ነው፤ ከሕዝብ መካከል ተለይተህ ትሰደዳለህ፤ ኑሮህም ከዱር አራዊት ጋር ይሆናል፤ ሰባት ዓመት እስኪያልፍ እንደ በሬ ሣር ትበላለህ፤ በሰማይ ጠል ትረሰርሳለህ፤ ይህም ሁሉ የሚደርስብህ ልዑል እግዚአብሔር በመንግሥታት ሁሉ ላይ ሥልጣን እንዳለውና መንግሥትንም ሁሉ ለወደደው ሰው እንደሚሰጥ እስከምትረዳ ድረስ ነው። ጉቶው በመሬት ውስጥ እንዲቀር ትእዛዝ መሰጠቱ እግዚአብሔር በዓለም ሁሉ ላይ ሥልጣን እንዳለው ካወቅህ በኋላ እንደገና ተመልሰህ የምትነግሥ መሆንህን ያመለክታል፤ ስለዚህ ንጉሥ ሆይ! በበኩሌ የምመክርህን ስማ፤ ኃጢአት መሥራትን ትተህ መልካም ሥራ መሥራትን አዘወትር፤ ክፋትን ትተህ ለተጨቈኑ ሰዎች ራራላቸው፤ ይህን ብታደርግ በሰላም የመኖር ዕድሜህ ይረዝምልህ ይሆናል።”