ዳንኤል 4:2-8
ዳንኤል 4:2-8 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ልዑል አምላክ ያደረገልኝን ታምራዊ ምልክቶችንና ድንቅ ሥራዎች ስነግራችሁ እጅግ ደስ እያለኝ ነው። ምልክቱ እንዴት ታላቅ ነው! ድንቁስ እንዴት ብርቱ ነው! መንግሥቱ የዘላለም መንግሥት ነው፤ ግዛቱም ከትውልድ እስከ ትውልድ ይኖራል። እኔ ናቡከደነፆር በቤቴ ደልቶኝ በቤተ መንግሥቴም ተመችቶኝ እኖር ነበር። አንድ ያስፈራኝ ሕልም አየሁ፤ በዐልጋዬ ላይ ተኝቼ ሳለሁ፣ ወደ አእምሮዬ የመጡት ምስሎችና ራእዮች አስደነገጡኝ። ስለዚህ የባቢሎን ጠቢባን ሁሉ ወደ እኔ መጥተው ሕልሜን እንዲተረጕሙልኝ አዘዝሁ። ጠንቋዮቹ፣ አስማተኞቹ፣ ኮከብ ቈጣሪዎቹና መተተኞቹ በመጡ ጊዜ ሕልሙን ነገርኋቸው፤ ነገር ግን ሊተረጕሙልኝ አልቻሉም። በመጨረሻም በአምላኬ ስም ብልጣሶር ተብሎ የተጠራውና የቅዱሳን አማልክት መንፈስ ያለበት ዳንኤል ገብቶ በፊቴ ቆመ፤ ሕልሜንም ነገርሁት።
ዳንኤል 4:2-8 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ልዑል አምላክ በፊቴ ያደረገውን ተአምራቱንና ድንቁን አሳያችሁ ዘንድ ወድጃለሁ። ተአምራቱ እንዴት ታላቅ ነው! ድንቁም እንዴት ጽኑ ነው! መንግሥቱም የዘላለም መንግሥት ነው፥ ግዛቱም ለልጅ ልጅ ነው። እኔ ናቡከደነፆር በቤቴ ደስ ብሎኝ በአዳራሼም ተመችቶኝ ነበር። ሕልም አለምሁ፥ እርስዋም አስፈራችኝ፥ በአልጋዬም ላይ የነበረው አሳቤና የራሴ ራእይ አስጨነቁኝ፥ ስለዚህ የሕልሙን ፍቺ እንዲያስታውቁኝ የባቢሎን ጠቢባን ሁሉ ወደ እኔ ይገቡ ዘንድ አዘዝሁ። የዚያን ጊዜም የሕልም ተርጓሚዎቹና አስማተኞቹ ከለዳውያኑና ቃላተኞቹ ገቡ፥ ሕልሙንም በፊታቸው ተናገርሁ፥ ፍቺውን ግን አላስታወቁኝም። በመጨረሻም የቅዱሳን አማልክት መንፈስ ያለበት እንደ አምላኬ ስም ብልጣሶር የሚባለው ዳንኤል በፊቴ ገባ፥ እኔም ሕልሙን ነገርሁት እንዲህም አልሁት፦
ዳንኤል 4:2-8 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ልዑል እግዚአብሔር ያደረገልኝን ድንቅ ሥራዎችና ተአምራት ልነግራችሁ እወዳለሁ። “እግዚአብሔር የሚያሳየው ተአምር እንዴት ታላቅ ነው! እርሱ የሚፈጽመው ድንቅ ሥራ እንዴት ብርቱ ነው! እግዚአብሔር ለዘለዓለም ንጉሥ ነው፤ ለመንግሥቱም ፍጻሜ የለውም። “እኔ ናቡከደነፆር በቤተ መንግሥቴ በብልጽግናና በምቾት እኖር ነበር። ከዕለታት አንድ ቀን በአልጋዬ ላይ ተኝቼ ሳለ የሚያስፈራ ሕልምና የሚያስደነግጥ ራእይ አየሁ። ስለዚህ የሕልሙን ትርጒም እንዲነግሩኝ በባቢሎን የሚገኙትን ጠቢባን ሁሉ ወደ እኔ እንዲመጡ አደረግሁ። ጠንቋዮች፥ አስማተኞች፥ ኮከብ ቈጣሪዎችና መተተኞች ሁሉ ወደ እኔ በመጡ ጊዜ ሕልሜን ነገርኳቸው፤ እነርሱ ግን የሕልሜን ትርጒም ሊነግሩኝ አልቻሉም፤ ከዚህ በኋላ በአምላኬ ስም ብልጣሶር ተብሎ የሚጠራው ዳንኤል ገባ፤ ይህ ሰው የቅዱሳን አማልክት መንፈስ ያደረበት ነው፤ እንዲህም ስል ሕልሜን ነገርኩት፤