ቈላስይስ 3:5-11
ቈላስይስ 3:5-11 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ምድራዊ ሰውነታችሁንም ከዝሙትና ከርኵሰት፥ ከጥፋትና ከክፉ ምኞት፥ ጣዖት ማምለክ ከሆነው ከቅሚያም ግደሉት። በእነርሱም ምክንያት በማይታዘዙ ልጆች ላይ የእግዚአብሔር መቅሠፍት ይመጣል። እናንተም ቀድሞ በዚህ ሥራ በነበራችሁ ጊዜ የሄዳችሁበት ነው። አሁንም ቍጣንና ብስጭትን፥ ክፋትንና ስድብን፥ የሚያሳፍረውንም ነገር ተዉ፤ ከንቱ ነገርም ከአፋችሁ አይውጣ። አሮጌውን ሰው ከሥራው ጋር ተዉት እንጂ፤ ወንድሞቻችሁን አቷሹ። ፈጣሪውን ለመምሰል በዕውቀት የሚታደሰውን አዲሱን ሰው ልበሱት። በእርሱ ዘንድ አይሁዳዊ፥ ግሪካዊም፥ የተገዘረ፥ ያልተገዘረም፥ አረመኔም፥ ባላገርም፥ ቤተ ሰብእና አሳዳሪ ማለት የለም ነገር ግን ክርስቶስ ለሁሉ በሁሉም ዘንድ ነው።
ቈላስይስ 3:5-11 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ስለዚህ ምድራዊ ምኞቶቻችሁን ግደሉ፤ እነዚህም፦ ዝሙት፣ ርኩሰት፣ ፍትወት፣ ክፉ ምኞትና አምልኮተ ጣዖት የሆነው መጐምጀት ናቸው። በእነዚህም ምክንያት የእግዚአብሔር ቍጣ በማይታዘዙት ላይ ይመጣል፤ እናንተም ቀድሞ በኖራችሁበት ሕይወት በእነዚህ ትመላለሱ ነበር፤ አሁን ግን ቍጣን፣ ንዴትን፣ ክፋትን፣ ስድብንና አሳፋሪ ንግግርን የመሳሰሉትንም ሁሉ አስወግዱ፤ አሮጌውን ሰው ከሥራው ጋራ አውልቃችሁ ስለ ጣላችሁ እርስ በርሳችሁ ውሸት አትነጋገሩ። የፈጣሪውን መልክ እንዲመስል በዕውቀት የሚታደሰውን አዲሱን ሰው ለብሳችኋል፤ በዚያ ግሪክ ወይም ይሁዲ፣ የተገረዘ ወይም ያልተገረዘ፣ አረማዊ ወይም እስኩቴስ፣ ባሪያ ወይም ጌታ ብሎ ልዩነት የለም፤ ነገር ግን ክርስቶስ ሁሉም ነው፤ በሁሉም ነው።
ቈላስይስ 3:5-11 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እንግዲህ በምድር ያሉቱን ብልቶቻችሁን ግደሉ፥ እነዚህም ዝሙትና ርኵሰት ፍትወትም ክፉ ምኞትም ጣኦትንም ማምለክ የሆነ መጎምጀት ነው፤ በእነዚህም ጠንቅ የእግዚአብሔር ቍጣ በማይታዘዙ ልጆች ላይ ይመጣል፤ እናንተም ደግሞ ትኖሩባቸው በነበራችሁ ጊዜ፥ በፊት በእነዚህ ተመላለሳችሁ። አሁን ግን እናንተ ደግሞ ቍጣንና ንዴትን ክፋትንም፥ ከአፋችሁም ስድብን የሚያሳፍርንም ንግግር እነዚህን ሁሉ አስወግዱ፤ እርስ በርሳችሁ ውሸት አትነጋገሩ፥ አሮጌውን ሰው ከሥራው ጋር ገፋችሁታልና፥ የፈጠረውንም ምሳሌ እንዲመስል እውቀትን ለማግኘት የሚታደሰውን አዲሱን ሰው ለብሳችሁታል፤ በዚያም የግሪክ ሰው አይሁዳዊም የተገረዘም ያልተገረዘም አረማዊም እስኩቴስም ባሪያም ጨዋ ሰውም መሆን አልተቻለም፥ ነገር ግን ክርስቶስ ሁሉ ነው፥ በሁሉም ነው።
ቈላስይስ 3:5-11 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ስለዚህ በእናንተ የሚገኙትን የምድራዊ ሕይወት ምኞቶች ሁሉ ግደሉ፤ እነርሱም “ዝሙት፥ ርኲሰት፥ ፍትወት፥ ክፉ ምኞት፥ ጣዖት ማምለክ የሆነ መጐምጀት” ናቸው። በእነዚህ ነገሮች ምክንያት በማይታዘዙ ሰዎች ላይ የእግዚአብሔር ቊጣ ይመጣል። እናንተም ራሳችሁ ከዚህ በፊት በማይታዘዙ ሰዎች መካከል ሳላችሁ እነዚህን ነገሮች በማድረግ ትኖሩ ነበር። አሁን ግን ቊጣን፥ ንዴትን፥ ተንኰልን፥ ስም ማጥፋትን ከእናንተ አስወግዱ፤ የሚያሳፍር ንግግርም ከአፋችሁ አይውጣ። አሮጌውን ባሕርይ ከነሥራው አውልቃችሁ ስለ ጣላችሁት እርስ በርሳችሁ ውሸት አትነጋገሩ። በፈጣሪው አምሳል በዕውቀት እየታደሰ የሚሄደውን አዲሱን ባሕርይ ልበሱ። በዚህ ሁኔታ በግሪካዊና በአይሁዳዊ፥ በተገረዘና ባልተገረዘ፥ በሠለጠነ አረመኔና ባልሠለጠነ አረመኔ፥ ነጻነት በሌለውና ነጻነት ባለው ሰው መካከል ልዩነት የለም፤ ክርስቶስ ሁሉም ነው፤ በሁሉም ነው።
ቈላስይስ 3:5-11 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እንግዲህ በእናንተ ያሉትን ምድራዊ ነገሮች ሁሉ ግደሉ፤ እነርሱም፦ “ዝሙትና ርኩሰት ፍትወትም ክፉ ምኞትም ጣዖትንም ማምለክ የሆነ ስግብግብነት” ናቸው፤ በእነዚህም ጠንቅ የእግዚአብሔር ቁጣ በማይታዘዙ ልጆች ላይ ይመጣል፤ እናንተም በቀድሞው ሕይወታችሁ ስትኖሩ እነዚህን ነገሮች በመተግበር ትመላለሱ ነበር። አሁን ግን እናንተ ቁጣንና ንዴትን ክፋትንም፥ ከአፋችሁም ስድብን የሚያሳፍርንም ንግግር እነዚህን ሁሉ አስወግዱ፤ አሮጌውን ሰው ከሥራው ጋር ገፋችሁ አስወግዳችሁታልና እርስ በርሳችሁ ውሸት አትነጋገሩ፤ እንደ ፈጣሪውም መልክ በእውቀት የታደሰውን አዲሱን ሰው ለብሳችሁታል፤ በዚህም መታደስ ግሪካዊና አይሁዳዊ፥ የተገረዘና ያልተገረዘ፥ አረማዊና እስኩቴስ፥ ባርያና ነጻ ሰው የሚባል ነገር አይኖርም፤ ነገር ግን ክርስቶስ ሁሉ ነው፤ በሁሉም ነው።