ቈላስይስ 1:13-20
ቈላስይስ 1:13-20 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ከጨለማ አገዛዝ አዳነን፤ ወደ ተወደደው ልጁ መንግሥትም መለሰን። ድኅነትን ያገኘንበት፥ ኀጢአታችንም የተሠረየበት ነው። ይኸውም የማይታይ እግዚአብሔርን የሚመስለው፥ ከፍጥረቱ ሁሉ በላይ የሆነ በኵር ነው። በእርሱ ቃልነት እግዚአብሔር ሁሉን ፈጥሮአልና በሰማይ ያለውን፥ በምድርም ያለውን፥ የሚታየውንና የማይታየውን፥ መናብርትም ቢሆኑ፥ አጋእዝትም ቢሆኑ፥ መኳንንትም ቢሆኑ፥ ቀደምትም ቢሆኑ፥ ሁሉን በእርሱ ቃልነት ፈጥሮአቸዋልና፤ ሁሉም በእጁ ሆነ፤ ሁሉም በእርሱ ለእርሱ ተፈጠረ፤ እርሱ ከሁሉ አስቀድሞ ነበረ፤ ሁሉም በእርሱ ጸና። እርሱ የቤተ ክርስቲያን ራስ ነው፤ በኵር እርሱ ለሁሉ ራስ ይሆን ዘንድ ከሙታን ሁሉ አስቀድሞ ተነሥቶአልና። ሁሉ በእርሱ ፍጹም ሆኖ ይኖር ዘንድ፥ ወዶአልና። ሁሉንም በእርሱ ይቅር ይለው ዘንድ በመስቀሉ ባፈሰሰው ደም በምድርና በሰማያት ላሉ ሰላምን አደረገ።
ቈላስይስ 1:13-20 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እርሱ ከጨለማ አገዛዝ ታደገን፤ ወደሚወድደው ልጁ መንግሥትም አሻገረን፤ በርሱም ቤዛነትን በደሙ አግኝተናል፤ ይህም የኀጢአት ይቅርታ ነው። እርሱ የማይታየው አምላክ አምሳል ነው፤ ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኵር ነው፤ ሁሉ ነገር በርሱ ተፈጥሯል፤ በሰማይና በምድር ያሉ፣ የሚታዩና የማይታዩ፣ ዙፋናት ቢሆኑ ወይም ኀይላት፣ ገዦች ቢሆኑ ወይም ባለሥልጣናት፣ ሁሉም ነገር በርሱና ለርሱ ተፈጥሯል። እርሱ ከሁሉ በፊት ነው፤ ሁሉም ነገር በአንድ ላይ ተያይዞ የጸናው በርሱ ነው። እርሱ አካሉ የሆነችው የቤተ ክርስቲያን ራስ ነው፤ በሁሉ ነገር የበላይነት ይኖረው ዘንድ እርሱ የመጀመሪያ፣ ከሙታን መካከልም በኵር ነው። እግዚአብሔርም ሙላቱ ሁሉ በርሱ ይሆን ዘንድ ወድዷልና፤ በመስቀሉ ላይ በፈሰሰው ደሙ ሰላምን በማድረግ፣ በምድርም ሆነ በሰማይም ያለውን ነገር ሁሉ በርሱ በኩል ከራሱ ጋራ አስታረቀ።
ቈላስይስ 1:13-20 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እርሱ ከጨለማ ሥልጣን አዳነን፥ ቤዛነቱንም እርሱንም የኃጢአትን ስርየት ወዳገኘንበት ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግሥት አፈለሰን። እርሱም የማይታይ አምላክ ምሳሌ ነው፤ የሚታዩትና የማይታዩትም፥ ዙፋናት ቢሆኑ ወይም ጌትነት ወይም አለቅነት ወይም ሥልጣናት፥ በሰማይና በምድር ያሉት ሁሉ በእርሱ ተፈጥረዋልና ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኵር ነው፤ ሁሉ በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሮአል፤ እርሱም ከሁሉ በፊት ነው ሁሉም በእርሱ ተጋጥሞአል። እርሱም የአካሉ ማለት የቤተ ክርስቲያን ራስ ነው፤ እርሱም በሁሉ ፊተኛ ይሆን ዘንድ፥ መጀመሪያ ከሙታንም በኵር ነው። እግዚአብሔር ሙላቱ ሁሉ በእርሱ እንዲኖር፥ በእርሱም በኩል በመስቀሉ ደም ሰላም አድርጎ በምድር ወይም በሰማያት ያሉትን ሁሉ ለራሱ እንዲያስታርቅ ፈቅዶአልና።
ቈላስይስ 1:13-20 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እርሱ ከጨለማ ኀይል አድኖ ወደ ተወደደው ልጁ መንግሥት እንድንገባ አድርጎናል። በእርሱም ተዋጅተን የኃጢአታችንን ይቅርታ አግኝተናል። ክርስቶስ ለማይታየው እግዚአብሔር እውነተኛ ምሳሌ ነው። እርሱ ከፍጥረት ሁሉ በላይ ታላቅና በኲር ነው። በሰማይና በምድር ያሉት፥ የሚታዩትና የማይታዩት፥ የሰማይ ኀይሎችና ገዢዎች፥ አለቆችና ባለሥልጣኖች ሁሉ የተፈጠሩት በእርሱ ነው። እግዚአብሔር ሁሉን ነገር የፈጠረው በእርሱና ለእርሱ ነው። እርሱ ከሁሉ ነገር በፊት ነበረ፤ ሁሉም ነገር ተያይዞ የቆመው በእርሱ ነው። እርሱ አካሉ የሆነችው የቤተ ክርስቲያን ራስ ነው፤ በሁሉ ነገር ቀዳሚ እንዲሆን፤ ከሞት በመነሣትም ፊተኛና መጀመሪያ ነው። ይህም የሆነው የመለኮት ሙላት በልጁ እንዲኖር የእግዚአብሔር አብ ፈቃድ ስለ ሆነ ነው። በእርሱም አማካይነት በሰማይም ሆነ በምድር ያሉትን ነገሮች ሁሉ ከራሱ ጋር አስታረቀ፤ በመስቀል ላይ በፈሰሰው በልጁ ደምም ሰላምን አደረገ።
ቈላስይስ 1:13-20 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እርሱ ከጨለማ ሥልጣን አዳነን፤ ወደ ተወደደውም ልጁ መንግሥት አፈለሰን፤ በእርሱም ተዋጅተን የኃጢአትን ስርየት አገኘን። እርሱም ለማይታየው አምላክ ምሳሌ ነው፤ የፍጥረት ሁሉ በኩር ነው፤ የሚታዩትና የማይታዩትም፥ ዙፋናት ቢሆኑ ወይም ጌትነት ወይም አለቅነት ወይም ሥልጣናት፥ በሰማይና በምድር ያሉት ሁሉ በእርሱ ተፈጥረዋልና፤ ሁሉ በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሮአል፤ እርሱም ከሁሉ በፊት ነው፤ ሁሉም ነገር በእርሱ አብሮ ተዋቅሮአል። እርሱም አካሉ የሆነችው የቤተ ክርስቲያን ራስ ነው፤ እርሱ በሁሉ ነገር ቀዳሚ በመሆን መጀመሪያ ነው፤ ከሙታንም በኩር ነው። እግዚአብሔር ሙላቱ ሁሉ በእርሱ በማደሩ ተደስቷል፤ በመስቀሉም ደም ሰላምን በማድረግ በሰማይም ሆነ በምድር ያሉትን ነገሮች ሁሉ በእርሱ አማካይነት ከራሱ ጋር አስታርቋል።