ቈላስይስ 1:10-17
ቈላስይስ 1:10-17 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ወደ እግዚአብሔር በሚገባችሁ ትሄዱ ዘንድ፥ በበጎ ሥራ ሁሉ ፍሬ እያፈራችሁ፥ እግዚአብሔርንም በማወቅ እያደጋችሁ፥ በሁሉ ደስ ታሰኙት ዘንድ። በፍጹም ኀይል፥ በክብሩ ጽናት፥ በፍጹም ትዕግሥት፥ በተስፋና በደስታም ጸንታችሁ። በብርሃን ቅዱሳን ለሚታደሉት ርስት የበቃን ያደረገንን እግዚአብሔር አብን አመስግኑት። ከጨለማ አገዛዝ አዳነን፤ ወደ ተወደደው ልጁ መንግሥትም መለሰን። ድኅነትን ያገኘንበት፥ ኀጢአታችንም የተሠረየበት ነው። ይኸውም የማይታይ እግዚአብሔርን የሚመስለው፥ ከፍጥረቱ ሁሉ በላይ የሆነ በኵር ነው። በእርሱ ቃልነት እግዚአብሔር ሁሉን ፈጥሮአልና በሰማይ ያለውን፥ በምድርም ያለውን፥ የሚታየውንና የማይታየውን፥ መናብርትም ቢሆኑ፥ አጋእዝትም ቢሆኑ፥ መኳንንትም ቢሆኑ፥ ቀደምትም ቢሆኑ፥ ሁሉን በእርሱ ቃልነት ፈጥሮአቸዋልና፤ ሁሉም በእጁ ሆነ፤ ሁሉም በእርሱ ለእርሱ ተፈጠረ፤ እርሱ ከሁሉ አስቀድሞ ነበረ፤ ሁሉም በእርሱ ጸና።
ቈላስይስ 1:10-17 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
የምንጸልየውም ለጌታ እንደሚገባ እንድትኖሩና በሁሉም ደስ እንድታሰኙት ነው፤ ይኸውም በመልካም ሥራ ሁሉ ፍሬ እያፈራችሁ እግዚአብሔርን በማወቅ እያደጋችሁ፣ ታላቅ ጽናትና ትዕግሥት ይኖራችሁ ዘንድ፣ እንደ ክቡር ጕልበቱ መጠን በኀይል ሁሉ እየበረታችሁ፣ ደስ እየተሰኛችሁ፣ በቅዱሳን ርስት በብርሃን ተካፋዮች ለመሆን ያበቃንን አብን እንድታመሰግኑ ነው። እርሱ ከጨለማ አገዛዝ ታደገን፤ ወደሚወድደው ልጁ መንግሥትም አሻገረን፤ በርሱም ቤዛነትን በደሙ አግኝተናል፤ ይህም የኀጢአት ይቅርታ ነው። እርሱ የማይታየው አምላክ አምሳል ነው፤ ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኵር ነው፤ ሁሉ ነገር በርሱ ተፈጥሯል፤ በሰማይና በምድር ያሉ፣ የሚታዩና የማይታዩ፣ ዙፋናት ቢሆኑ ወይም ኀይላት፣ ገዦች ቢሆኑ ወይም ባለሥልጣናት፣ ሁሉም ነገር በርሱና ለርሱ ተፈጥሯል። እርሱ ከሁሉ በፊት ነው፤ ሁሉም ነገር በአንድ ላይ ተያይዞ የጸናው በርሱ ነው።
ቈላስይስ 1:10-17 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በበጎ ሥራ ሁሉ ፍሬ እያፈራችሁ በእግዚአብሔርም እውቀት እያደጋችሁ፥ ከደስታም ጋር በሁሉ ለመጽናትና ለመታገሥ እንደ ክብሩ ጉልበት መጠን በኃይል ሁሉ እየበረታችሁ፥ በቅዱሳንም ርስት በብርሃን እንድንካፈል ያበቃንን አብን እያመሰገናችሁ፥ በነገር ሁሉ ደስ ልታሰኙ ለጌታ እንደሚገባ ትመላለሱ ዘንድ እንለምናለን። እርሱ ከጨለማ ሥልጣን አዳነን፥ ቤዛነቱንም እርሱንም የኃጢአትን ስርየት ወዳገኘንበት ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግሥት አፈለሰን። እርሱም የማይታይ አምላክ ምሳሌ ነው፤ የሚታዩትና የማይታዩትም፥ ዙፋናት ቢሆኑ ወይም ጌትነት ወይም አለቅነት ወይም ሥልጣናት፥ በሰማይና በምድር ያሉት ሁሉ በእርሱ ተፈጥረዋልና ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኵር ነው፤ ሁሉ በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሮአል፤ እርሱም ከሁሉ በፊት ነው ሁሉም በእርሱ ተጋጥሞአል።
ቈላስይስ 1:10-17 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እንዲሁም ለጌታ ተገቢ በሆነ መንገድ በመኖር እርሱን በፍጹም እንድታስደስቱ ማናቸውንም መልካም ሥራ በመሥራት ፍሬ እንድታፈሩና እግዚአብሔርንም በማወቅ እያደጋችሁ እንድትሄዱ እንጸልያለን። ጌታ በገናናው ኀይሉ ብርታቱን ሁሉ ይስጣችሁ፤ በትዕግሥትም ሁሉን ነገር ለመቻል በደስታ የተዘጋጃችሁ ለመሆን ያብቃችሁ፤ ደግሞም በብርሃን መንግሥት ውስጥ ከቅዱሳን ጋር ርስት እንድትካፈሉ ያበቃችሁን እግዚአብሔር አብን በደስታ አመስግኑት። እርሱ ከጨለማ ኀይል አድኖ ወደ ተወደደው ልጁ መንግሥት እንድንገባ አድርጎናል። በእርሱም ተዋጅተን የኃጢአታችንን ይቅርታ አግኝተናል። ክርስቶስ ለማይታየው እግዚአብሔር እውነተኛ ምሳሌ ነው። እርሱ ከፍጥረት ሁሉ በላይ ታላቅና በኲር ነው። በሰማይና በምድር ያሉት፥ የሚታዩትና የማይታዩት፥ የሰማይ ኀይሎችና ገዢዎች፥ አለቆችና ባለሥልጣኖች ሁሉ የተፈጠሩት በእርሱ ነው። እግዚአብሔር ሁሉን ነገር የፈጠረው በእርሱና ለእርሱ ነው። እርሱ ከሁሉ ነገር በፊት ነበረ፤ ሁሉም ነገር ተያይዞ የቆመው በእርሱ ነው።
ቈላስይስ 1:10-17 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በዚህም በበጎ ሥራ ሁሉ ፍሬ እያፈራችሁና በእግዚአብሔር እውቀት እያደጋችሁ፥ ለጌታ እንደሚገባው ፍጹም ደስ የሚያሰኘውን ሕይወት እንድትኖሩ ነው። እንደ ክብሩ ኃያልነት በሁሉ ኃይል እንድትበረቱና ሁሉንም ነገር በትዕግሥት በጽኑ ለመወጣት እንድትዘጋጁ እንዲሁም ደስ በመሰኘት በብርሃን የቅዱሳንን ርስት እንድንካፈል ያበቃንን አብን እንድታመሰግኑት ነው። እርሱ ከጨለማ ሥልጣን አዳነን፤ ወደ ተወደደውም ልጁ መንግሥት አፈለሰን፤ በእርሱም ተዋጅተን የኃጢአትን ስርየት አገኘን። እርሱም ለማይታየው አምላክ ምሳሌ ነው፤ የፍጥረት ሁሉ በኩር ነው፤ የሚታዩትና የማይታዩትም፥ ዙፋናት ቢሆኑ ወይም ጌትነት ወይም አለቅነት ወይም ሥልጣናት፥ በሰማይና በምድር ያሉት ሁሉ በእርሱ ተፈጥረዋልና፤ ሁሉ በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሮአል፤ እርሱም ከሁሉ በፊት ነው፤ ሁሉም ነገር በእርሱ አብሮ ተዋቅሮአል።