ሐዋርያት ሥራ 9:1-25

ሐዋርያት ሥራ 9:1-25 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ሳውል ግን የጌ​ታን ደቀ መዛ​ሙ​ርት ለመ​ግ​ደል ገና እየ​ዛተ ወደ ሊቀ ካህ​ናቱ ሄደ። ምን​አ​ል​ባት በመ​ን​ገድ የሚ​ያ​ገ​ኘው ሰው ቢኖር ወን​ዶ​ች​ንም ሴቶ​ች​ንም እያ​ሰረ ወደ ኢየ​ሩ​ሳ​ሌም ያመ​ጣ​ቸው ዘንድ በደ​ማ​ስቆ ላሉት ምኵ​ራ​ቦች የሥ​ል​ጣን ደብ​ዳቤ ከሊቀ ካህ​ናቱ ለመነ። ሲሄ​ድም ወደ ደማ​ስቆ ከተማ አቅ​ራ​ቢያ በደ​ረሰ ጊዜ መብ​ረቅ ድን​ገት ከሰ​ማይ ብልጭ አለ​በት። በም​ድር ላይም ወደቀ፤ ወዲ​ያ​ውም፥ “ሳውል፥ ሳውል፥ ለምን ታሳ​ድ​ደ​ኛ​ለህ?” የሚ​ለ​ውን ቃል ሰማ። ሳው​ልም፥ “አቤቱ፥ አንተ ማነህ?” አለው፤ እር​ሱም፥ “አንተ የም​ታ​ሳ​ድ​ደኝ የና​ዝ​ሬቱ ኢየ​ሱስ ነኝ፤ በሾለ ብረት ላይ ብት​ቆም ለአ​ንተ ይብ​ስ​ሃል” አለው። እር​ሱም እየ​ፈ​ራና እየ​ተ​ን​ቀ​ጠ​ቀጠ፥ “አቤቱ፥ ምን እን​ዳ​ደ​ርግ ትሻ​ለህ?” አለው፤ ጌታም፥ “ተነ​ሣና ወደ ከተማ ግባ፤ በዚ​ያም ልታ​ደ​ር​ገው የሚ​ገ​ባ​ህን ይነ​ግ​ሩ​ሃል” አለው። ከእ​ር​ሱም ጋር የነ​በ​ሩት ሰዎች ድምፅ እየ​ሰሙ ማን​ንም ሳያዩ ተደ​ን​ቀው ቆሙ። ሳው​ልም ከም​ድር ተነሣ፤ ነገር ግን ዐይ​ኖቹ ተገ​ል​ጠው ሳሉ የሚ​ያ​የው ነገር አል​ነ​በ​ረም፤ እየ​መ​ሩም ወደ ደማ​ስቆ አገ​ቡት። በዚ​ያም ሳያይ ሳይ​በ​ላና ሳይ​ጠጣ ሦስት ቀን ቈየ። በደ​ማ​ስ​ቆም ስሙን ሐና​ንያ የሚ​ሉት አንድ ደቀ መዝ​ሙር ነበር፤ ጌታም በራ​እይ ተገ​ልጦ፥ “ሐና​ንያ” ብሎ ጠራው፤ እር​ሱም፥ “አቤቱ፥ እነ​ሆኝ” አለ። ጌታም፥ “ተነ​ሣና ቅን በም​ት​ባ​ለው መን​ገድ ሂድ፤ በይ​ሁዳ ቤትም ከጠ​ር​ሴስ ሀገር የመጣ ሳውል የሚ​ባል ሰው ፈልግ፤ እርሱ አሁን ይጸ​ል​ያ​ልና” አለው። ሳው​ልም በራ​እይ ሐና​ንያ የሚ​ባል ሰው ወደ እርሱ ገብቶ ያይ ዘንድ እጁን ሲጭ​ን​በት አየ። ሐና​ንያ ግን መልሶ እን​ዲህ አለ፥ “አቤቱ፥ ስለ​ዚህ ሰው በኢ​የ​ሩ​ሳ​ሌም በቅ​ዱ​ሳ​ኖ​ችህ ላይ የሚ​ያ​ደ​ር​ገ​ውን ክፉ ነገር ሁሉ ከብዙ ሰዎች ሰም​ቻ​ለሁ። ወደ​ዚ​ህም ከካ​ህ​ናቱ አለቃ አስ​ፈ​ቅዶ የመጣ ስም​ህን የሚ​ጠ​ሩ​ትን ሁሉ ሊያ​ስር ነው።” ጌታ​ች​ንም እን​ዲህ አለው፥ “ተነ​ሥና ሂድ፤ በአ​ሕ​ዛ​ብና በነ​ገ​ሥ​ታት፥ በእ​ስ​ራ​ኤል ልጆ​ችም ፊት ስሜን ይሸ​ከም ዘንድ ለእኔ የተ​መ​ረጠ ዕቃ አድ​ር​ጌ​ዋ​ለ​ሁና። እኔም ስለ ስሜ መከ​ራን ይቀ​በል ዘንድ እን​ዳ​ለው አሳ​የ​ዋ​ለሁ።” ያን​ጊ​ዜም ሐና​ንያ ሄደ፤ ወደ ቤትም ገባ፤ እጁ​ንም ጫነ​በ​ትና፥ “ወን​ድሜ ሳውል፥ በመ​ን​ገድ ስት​መጣ የታ​የህ ጌታ​ችን ኢየ​ሱስ ክር​ስ​ቶስ ታይና መን​ፈስ ቅዱስ ይመ​ላ​ብህ ዘንድ ወደ አንተ ልኮ​ኛል” አለው። ያን​ጊ​ዜም ፈጥኖ እንደ ቅር​ፊት ያለ ነገር ከዐ​ይ​ኖቹ ላይ ተገፎ ወደቀ፤ ዐይ​ኖ​ቹም ተገ​ለጡ፤ ወዲ​ያ​ውም አየ፤ ተነ​ሥ​ቶም ተጠ​መቀ። እህ​ልም በላ፤ በረ​ታም፤ ጥቂት ቀንም ከደቀ መዛ​ሙ​ርት ጋር በደ​ማ​ስቆ ሰነ​በተ። ወዲ​ያ​ው​ኑም “የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ልጅ ነው” ብሎ ስለ ኢየ​ሱስ ክር​ስ​ቶስ በየ​ም​ኵ​ራ​ቦቹ ሰበከ፥ አስ​ተ​ማ​ረም። የሰ​ሙ​ትም ሁሉ አደ​ነቁ፤ እን​ዲ​ህም አሉ፥ “በኢ​የ​ሩ​ሳ​ሌም ይህን ስም የሚ​ጠ​ሩ​ትን ሁሉ ይጠ​ላ​ቸው የነ​በ​ረው ይህ አይ​ደ​ለ​ምን? ስለ​ዚህ ወደ​ዚህ የመ​ጣው እያ​ሰረ ወደ ሊቀ ካህ​ናቱ ሊወ​ስ​ዳ​ቸው አይ​ደ​ለ​ምን?” ሳውል ግን እየ​በ​ረታ ሔደ፤ በደ​ማ​ስ​ቆም ለነ​በ​ሩት አይ​ሁድ ይህ ክር​ስ​ቶስ እንደ ሆነ እያ​ስ​ረዳ መልስ አሳ​ጣ​ቸው። ከብዙ ቀንም በኋላ አይ​ሁድ ሳው​ልን ይገ​ድ​ሉት ዘንድ ተማ​ከሩ። ሳውል ግን በእ​ርሱ ላይ ሊያ​ደ​ር​ጉት የሚ​ሹ​ትን ዐወ​ቀ​ባ​ቸው፤ ሊገ​ድ​ሉ​ትም በቀ​ንና በሌ​ሊት የከ​ተ​ማ​ውን በር ይጠ​ብቁ ነበር። ደቀ መዛ​ሙ​ር​ትም በሌ​ሊት ወሰ​ዱት፤ በቅ​ር​ጫ​ትም አድ​ር​ገው በቅ​ጽሩ ድም​ድ​ማት ላይ አወ​ረ​ዱት።

ሐዋርያት ሥራ 9:1-25 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ሳውል ግን የጌታን ደቀ መዛሙርት ለመግደል አሁንም እየዛተ ወደ ሊቀ ካህናቱ ሄደ፤ የጌታን መንገድ የሚከተሉትን ወንዶችንም ሆነ ሴቶችን በዚያ ካገኘ አስሮ ወደ ኢየሩሳሌም ለመውሰድ እንዲችል፣ በደማስቆ ለነበሩት ምኵራቦች ደብዳቤ እንዲሰጠው ሊቀ ካህናቱን ለመነው። ደማስቆ ለመድረስ ጥቂት ሲቀረው፣ ብርሃን ከሰማይ ድንገት በዙሪያው አንጸባረቀበት፤ እርሱም በመሬት ላይ ወደቀ፤ በዚያ ጊዜም “ሳውል፤ ሳውል፤ ለምን ታሳድደኛለህ?” የሚል ድምፅ ሰማ። ሳውልም፣ “ጌታ ሆይ፤ አንተ ማን ነህ?” አለው። እርሱም እንዲህ አለው፤ “እኔማ አንተ የምታሳድደኝ ኢየሱስ ነኝ። ነገር ግን ተነሣና ወደ ከተማዪቱ ግባ፤ ማድረግ የሚገባህም ይነገርሃል።” ከሳውል ጋራ ይጓዙ የነበሩትም ሰዎች ድምፁን እየሰሙ ማንንም ባላዩ ጊዜ፣ አፋቸውን ይዘው ቆሙ። ሳውልም ከመሬት ላይ ተነሥቶ ዐይኑን ሲገልጥ ምንም ማየት አልቻለም፤ ስለዚህ ሰዎቹ እጁን ይዘው እየመሩ ወደ ደማስቆ አስገቡት። ሦስት ቀንም ታወረ፤ እህል ውሃም አልቀመሰም። በደማስቆ ሐናንያ የሚባል አንድ ደቀ መዝሙር ነበር፤ ጌታም በራእይ፣ “ሐናንያ!” ብሎ ጠራው። እርሱም፣ “ጌታ ሆይ፤ እነሆኝ” አለ። ጌታም እንዲህ አለው፤ “ተነሣና ‘ቀጥተኛ ጐዳና’ በተባለው መንገድ ይሁዳ ወደ ተባለ ሰው ቤት ሂድ፤ እዚያም ሳውል የሚባል አንድ የጠርሴስ ሰው እየጸለየ ነውና ፈልገው፤ እርሱም ሐናንያ የሚባል ሰው እርሱ ወዳለበት መጥቶ እጁን እንደሚጭንበትና ዐይኑ እንደሚበራለት በራእይ አይቷል።” ሐናንያም መልሶ እንዲህ አለው፤ “ጌታ ሆይ፤ ይህ ሰው እኮ በኢየሩሳሌም ባሉ ቅዱሳንህ ላይ ምን ያህል ጕዳት እንዳደረሰ ከብዙ ሰው ሰምቻለሁ፤ ወደዚህም የመጣው ስምህን የሚጠሩትን ሁሉ ለማሰር ከካህናት አለቆች ሥልጣን ተቀብሎ ነው።” ጌታም እንዲህ አለው፤ “ሂድ! ይህ ሰው በአሕዛብና በነገሥታት ፊት እንዲሁም በእስራኤል ሕዝብ ፊት ስሜን እንዲሸከም የተመረጠ ዕቃዬ ነው፤ እኔም ስለ ስሜ ምን ያህል መከራ መቀበል እንዳለበት አሳየዋለሁ።” ሐናንያ ሄዶ፣ ወደተባለውም ቤት ገባ፤ በሳውልም ላይ እጁን ጭኖ፣ “ወንድሜ ሳውል ሆይ፤ ወደዚህ ስትመጣ በመንገድ ላይ የተገለጠልህ ጌታ ኢየሱስ፣ ዐይንህ እንዲበራና በመንፈስ ቅዱስም እንድትሞላ እኔን ልኮኛል” አለው። ወዲያውም ከሳውል ዐይን ላይ ቅርፊት የመሰለ ነገር ወደቀ፤ እንደ ገና ማየት ቻለ፤ ተነሥቶም ተጠመቀ፤ ምግብም በልቶ በረታ። ሳውል በደማስቆ ከነበሩት ደቀ መዛሙርት ጋራ አያሌ ቀን ተቀመጠ። ወዲያውም፣ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን በየምኵራቦቹ መስበክ ጀመረ። የሰሙትም ሁሉ በመገረም፣ ይህ ሰው “በኢየሩሳሌም ይህን ስም የሚጠሩትን ሲያጠፋ የነበረ አይደለምን? ደግሞም ወደዚህ የመጣው እነርሱን አስሮ ወደ ካህናት አለቆች ሊወስዳቸው አልነበረምን?” አሉ። ሳውል ግን እየበረታ ሄደ፤ በደማስቆ ለሚኖሩትም አይሁድ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ መሆኑን ማስረጃ እያቀረበ አፋቸውን ያስይዛቸው ነበር። ከብዙ ቀንም በኋላ፣ አይሁድ ሳውልን ለመግደል አሤሩ፤ ሳውል ግን ዕቅዳቸውን ዐውቆ ነበር፤ እነርሱም ሊገድሉት የከተማዋን በር ቀንና ሌሊት ይጠብቁ ነበር፤ የርሱ ደቀ መዛሙርት ግን በሌሊት በከተማዪቱ ቅጥር ቀዳዳ አሹልከው በቅርጫት አወረዱት።

ሐዋርያት ሥራ 9:1-25 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ሳውል ግን የጌታን ደቀ መዛሙርት እንዲገድላቸው ገና እየዛተ ወደ ሊቀ ካህናት ሄደ፥ በዚህ መንገድ ያሉትንም ሰዎች ወንዶችንም ሴቶችንም ቢያገኝ፥ እያሰረ ወደ ኢየሩሳሌም ያመጣቸው ዘንድ በደማስቆ ላሉት ምኵራቦች ደብዳቤ ከእርሱ ለመነ። ሲሄድም ወደ ደማስቆ በቀረበ ጊዜ ድንገት በእርሱ ዙሪያ ከሰማይ ብርሃን አንጸባረቀ፤ በምድርም ላይ ወድቆ ሳለ፦ ሳውል ሳውል፥ ስለ ምን ታሳድደኛለህ? የሚለውን ድምፅ ሰማ። ጌታ ሆይ፥ ማን ነህ? አለው። እርሱም፦ አንተ የምታሳድደኝ እኔ ኢየሱስ ነኝ፤ የመውጊያውን ብረት ብትቃወም ለአንተ ይብስብሃል አለው። እየተንቀጠቀጠና እየተደነቀ፦ “ጌታ ሆይ፥ ምን አደርግ ዘንድ ትወዳለህ?” አለው። ጌታም፦ “ተነሥተህ ወደ ከተማ ግባና ታደርገው ዘንድ የሚያስፈልግህን ይነግሩሃል” አለው። ከእርሱም ጋር በመንገድ የሄዱ ሰዎች ድምፁን እየሰሙ ማንን ግን ሳያዩ እንደ ዲዳዎች ቁሙ። ሳውልም ከምድር ተነሣ፥ አይኖቹም በተከፈቱ ጊዜ ምንም አላየም፤ እጁንም ይዘው እየመሩ ወደ ደማስቆ አገቡት። ሳያይም ሦስት ቀን ኖረ፤ አልበላምም አልጠጣምም። በደማስቆም ሐናንያ የሚሉት አንድ ደቀ መዝሙር ነበረ፥ ጌታም በራእይ፦ “ሐናንያ ሆይ፥” አለው። እርሱም፦ “ጌታ ሆይ፥ እነሆኝ” አለ። ጌታም፦ “ተነሥተህ ቅን ወደ ሚባለው መንገድ ሂድ፥ በይሁዳ ቤትም ሳውል የሚሉትን አንድ የጠርሴስ ሰው ፈልግ፤ እነሆ፥ እርሱ ይጸልያልና፤ ሐናንያ የሚሉትም ሰው ገብቶ ደግሞ እንዲያይ እጁን ሲጭንበት አይቶአል” አለው። ሐናንያም መልሶ፦ “ጌታ ሆይ፥ በኢየሩሳሌም በቅዱሳንህ ላይ ስንት ክፉ እንዳደረገ ስለዚህ ሰው ከብዙዎች ሰምቼአለሁ፤ በዚህም ስምህን የሚጠሩትን ሁሉ ለማሰር ከካህናት አለቆች ሥልጣን አለው” አለ። ጌታም፦ “ይህ በአሕዛብም በነገሥታትም በእስራኤልም ልጆች ፊት ስሜን ይሸከም ዘንድ ለእኔ የተመረጠ ዕቃ ነውና ሂድ፤ ስለ ስሜ ስንት መከራ ሊቀበል እንዲያስፈልገው እኔ አመለክተዋለሁና” አለው። ሐናንያም ሄዶ ወደ ቤቱ ገባ፥ እጁንም ጭኖበት፦ “ወንድሜ ሳውል ሆይ፥ ጌታ፥ እርሱም በመጣህበት መንገድ የታየህ ኢየሱስ ነው፥ ደግሞ ታይ ዘንድና መንፈስ ቅዱስ ይሞላብህ ዘንድ ላከኝ” አለ። ወዲያውም እንደ ቅርፊት ያለ ከዓይኑ ወደቀ፥ ያን ጊዜም ደግሞ አየ፤ ተነሥቶም ተጠመቀ፥ መብልም በልቶ በረታ። በደማስቆም ካሉት ደቀ መዛሙርት ጋር ጥቂት ቀን ኖረ። ወዲያውም ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ በምኵራቦቹ ሰበከ። የሰሙትም ሁሉ ተገረሙና፦ “ይህ በኢየሩሳሌም ይህን ስም የሚጠሩትን ያጠፋ አይደለምን? ስለዚህስ ታስረው ወደ ካህናት አለቆች ይወስዳቸው ዘንድ ወደዚህ አልመጣምን?” አሉ። ሳውል ግን እየበረታ ሄደ፥ በደማስቆም ለተቀመጡት አይሁድ ይህ ክርስቶስ እንደ ሆነ አስረድቶ መልስ ያሳጣቸው ነበር። ብዙ ቀንም ሲሞላ አይሁድ ሊገድሉት ተማከሩ፤ ሳውል ግን አሳባቸውን አወቀ። ይገድሉትም ዘንድ በሌሊትና በቀን የከተማይቱን በር ሁሉ ይጠቀብቁ ነበር፤ ደቀ መዛሙርት ግን በሌሊት ወስደው በቅጥር ላይ አሳልፈው በቅርጫት አወረዱት።

ሐዋርያት ሥራ 9:1-25 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

በዚያን ጊዜ ሳውል የጌታን ደቀ መዛሙርት ለመግደል ገና እየዛተ ወደ ካህናት አለቃው ሄደ። የጌታንም መንገድ የሚከተሉትን ሰዎች ወንዶችንም ሴቶችንም ሲያገኝ እያሰረ ወደ ኢየሩሳሌም ለማምጣት የሚያስችል ደብዳቤ ለደማስቆ ምኵራቦች ተጽፎ እንዲሰጠው ሊቀ ካህናቱን ጠየቀ። ሲሄድም ወደ ደማስቆ በቀረበ ጊዜ በእርሱ ዙሪያ በድንገት ከሰማይ ብርሃን አንጸባረቀ። በዚያን ጊዜ በምድር ላይ ወደቀ፤ “ሳውል፥ ሳውል፥ ለምን ታሳድደኛለህ?” የሚል ድምፅም ሰማ። ሳውልም “ጌታ ሆይ! አንተ ማን ነህ?” አለ፤ እርሱም “እኔ አንተ የምታሳድደኝ ኢየሱስ ነኝ፤ አሁን ግን ተነሥና ወደ ከተማ ግባ፤ ልታደርገው የሚገባህም እዚያ ይነገርሃል” አለው። ከሳውል ጋር ይሄዱ የነበሩ ሰዎች ድምፅ እየሰሙ ማንንም ባለማየታቸው የሚናገሩትን አጥተው፥ ዝም ብለው ቆሙ። ሳውልም ከወደቀበት መሬት ተነሣ፤ ዐይኖቹን በገለጠ ጊዜ ግን ምንም ማየት አልቻለም፤ ስለዚህ ሰዎቹ እጁን ይዘው እየመሩ ወደ ደማስቆ ወሰዱት። ሦስት ቀን ሙሉ ምንም ማየት ሳይችል፥ ሳይበላና ሳይጠጣም ቈየ። በዚያን ጊዜ በደማስቆ ሐናንያ የሚባል አንድ ደቀ መዝሙር ነበር፤ ጌታ በራእይ “ሐናንያ!” ብሎ ጠራው፤ እርሱም “እነሆኝ ጌታ ሆይ!” አለ። ጌታም እንዲህ አለው፦ “ቀጥተኛ ወደምትባለው መንገድ ሂድ፤ እዚያ በይሁዳ ቤት ሳውል የሚባለውን የጠርሴስ ሰው ፈልግ፤ እርሱ አሁን በጸሎት ላይ ነው።” ሳውልም ዐይኖቹ እንደገና ማየት እንዲችሉ ሐናንያ የተባለ ሰው ወደ እርሱ ገብቶ እጁን ሲጭንበት በራእይ አየ። ሐናንያ ግን እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ጌታ ሆይ! ይህ ሰው በኢየሩሳሌም በሚኖሩ ምእመናንህ ላይ ብዙ ክፉ ነገር ማድረጉን ከብዙዎች ሰምቻለሁ። እዚህም ስምህን የሚጠሩትን ሁሉ ለማሰር ከካህናት አለቆች ሥልጣን ተቀብሎአል።” ጌታም ሐናንያን እንዲህ አለው፦ “እርሱ ስሜን ለአረማውያን፥ ለነገሥታትና ለእስራኤል ሰዎች የሚያሳውቅ፥ የእኔ ምርጥ መሣሪያ ስለ ሆነ ወደ እርሱ ሂድ፤ ስለ እኔ ምን ያኽል ብዙ መከራ እንደሚቀበል እገልጥለታለሁ።” ስለዚህ ሐናንያ ወደዚያ ሄዶ እርሱ ወደ ነበረበትም ቤት ገባ፤ እጁንም በሳውል ላይ ጭኖ፥ “ወንድሜ ሳውል ሆይ! ወደዚህ ስትመጣ ሳለ በመንገድ የተገለጠልህ ጌታ ኢየሱስ እንደገና ማየት እንድትችልና መንፈስ ቅዱስም እንዲሞላብህ ወደ አንተ ልኮኛል” አለው። ወዲያውኑ ቅርፊት የሚመስል ነገር ከዐይኑ ወደቀና ማየት ቻለ፤ ተነሥቶም ተጠመቀ። መብልም በላና በረታ፤ በደማስቆ ከነበሩት ደቀ መዛሙርት ጋር ለጥቂት ቀኖች ቈየ። ወዲያውም ሳውል በደማስቆ “ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ ነው” እያለ በየምኲራቡ ማስተማር ጀመረ። የሰሙትም ሁሉ፥ “ይህ ሰው በኢየሩሳሌም ይህን ስም የሚጠሩትን ሁሉ የሚያጠፋ የነበረ አይደለምን? ወደዚህስ የመጣው እነርሱን እያሰረ ወደ ካህናት አለቆች ለመውሰድ አይደለምን?” በማለት ይደነቁ ነበር። ሳውል ግን ይበልጥ እየበረታ ሄደ፤ ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን በማስረዳት በደማስቆ ይኖሩ የነበሩትን አይሁድ መልስ ያሳጣቸው ነበር። ከብዙ ቀን በኋላ አይሁድ ሳውልን ለመግደል ተማከሩ፤ እርሱ ግን የተንኰል ዐድማቸውን ዐወቀ፤ እነርሱም እርሱን ለመግደል ሌት ተቀን እርሱ የሚወጣባቸውን በሮች ይጠብቁ ነበር። ነገር ግን በሌሊት የራሱ ደቀ መዛሙርት ሳውልን በቅርጫት አድርገው በግንቡ አጥር መስኮት ወደታች አወረዱት።

ሐዋርያት ሥራ 9:1-25 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ሳውል ግን የጌታን ደቀ መዛሙርት እንዲገድላቸው ገና እየዛተ ወደ ሊቀ ካህናት ሄደ፤ በዚህ መንገድ ያሉትንም ሰዎች ወንዶችንም ሴቶችንም ቢያገኝ፥ እያሰረ ወደ ኢየሩሳሌም ያመጣቸው ዘንድ በደማስቆ ላሉት ምኵራቦች ደብዳቤ ከእርሱ ለመነ። ሲሄድም ወደ ደማስቆ በቀረበ ጊዜ ድንገት በእርሱ ዙሪያ ከሰማይ ብርሃን አንጸባረቀ፤ በምድርም ላይ ወድቆ ሳለ “ሳውል! ሳውል! ስለምን ታሳድደኛለህ?” የሚለውን ድምፅ ሰማ። “ጌታ ሆይ! ማን ነህ?” አለው። እርሱም “አንተ የምታሳድደኝ እኔ ኢየሱስ ነኝ፤ የመውጊያውን ብረት ብትረግጥ ለአንተ ይብስብሃል፤” አለው። እየተንቀጠቀጠና እየተደነቀ “ጌታ ሆይ! ምን አደርግ ዘንድ ትወዳለህ?” አለው። ጌታም “ተነሥተህ ወደ ከተማ ግባና ታደርገው ዘንድ የሚያስፈልግህን ይነግሩሃል፤” አለው። ከእርሱም ጋር በመንገድ የሄዱ ሰዎች ድምፁን እየሰሙ ማንን ግን ሳያዩ እንደ ዲዳዎች ቁሙ። ሳውልም ከምድር ተነሣ፤ ዐይኖቹም በተከፈቱ ጊዜ ምንም አላየም፤ እጁንም ይዘው እየመሩ ወደ ደማስቆ አገቡት። ሳያይም ሦስት ቀን ኖረ፤ አልበላምም፤ አልጠጣምም። በደማስቆም ሐናንያ የሚሉት አንድ ደቀመዝሙር ነበረ፤ ጌታም በራእይ “ሐናንያ ሆይ!” አለው። እርሱም “ጌታ ሆይ! እነሆኝ፤” አለ። ጌታም “ተነሥተህ ቅን ወደ ሚባለው መንገድ ሂድ፤ በይሁዳ ቤትም ሳውል የሚሉትን አንድ የጠርሴስ ሰው ፈልግ፤ እነሆ፥ እርሱ ይጸልያልና፤ ሐናንያ የሚሉትም ሰው ገብቶ ደግሞ እንዲያይ እጁን ሲጭንበት አይቶአል፤” አለው። ሐናንያም መልሶ “ጌታ ሆይ! በኢየሩሳሌም በቅዱሳንህ ላይ ስንት ክፉ እንዳደረገ ስለዚህ ሰው ከብዙዎች ሰምቼአለሁ፤ በዚህም ስምህን የሚጠሩትን ሁሉ ለማሰር ከካህናት አለቆች ሥልጣን አለው፤” አለ። ጌታም “ይህ በአሕዛብም በነገሥታትም በእስራኤልም ልጆች ፊት ስሜን ይሸከም ዘንድ ለእኔ የተመረጠ ዕቃ ነውና ሂድ፤ ስለ ስሜ ስንት መከራ ሊቀበል እንዲያስፈልገው እኔ አመለክተዋለሁና” አለው። ሐናንያም ሄዶ ወደ ቤቱ ገባ፤ እጁንም ጭኖበት “ወንድሜ ሳውል ሆይ! ጌታ፥ እርሱም በመጣህበት መንገድ የታየህ ኢየሱስ ነው፤ ደግሞ ታይ ዘንድና መንፈስ ቅዱስ ይሞላብህ ዘንድ ላከኝ፤” አለ። ወዲያውም እንደ ቅርፊት ያለ ከዐይኑ ወደቀ፤ ያን ጊዜም ደግሞ አየ፤ ተነሥቶም ተጠመቀ፤ መብልም በልቶ በረታ። ወዲያውም ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ በምኵራቦቹ ሰበከ። የሰሙትም ሁሉ ተገረሙና “ይህ በኢየሩሳሌም ይህን ስም የሚጠሩትን ያጠፋ አይደለምን? ስለዚህስ ታስረው ወደ ካህናት አለቆች ይወስዳቸው ዘንድ ወደዚህ አልመጣምን?” አሉ። ሳውል ግን እየበረታ ሄደ፤ በደማስቆም ለተቀመጡት አይሁድ ይህ ክርስቶስ እንደሆነ አስረድቶ መልስ ያሳጣቸው ነበር። ብዙ ቀንም ሲሞላ አይሁድ ሊገድሉት ተማከሩ፤ ሳውል ግን አሳባቸውን አወቀ። ይገድሉትም ዘንድ በሌሊትና በቀን የከተማይቱን በር ሁሉ ይጠቀብቁ ነበር፤ ደቀ መዛሙርት ግን በሌሊት ወስደው በቅጥር ላይ አሳልፈው በቅርጫት አወረዱት።