ሐዋርያት ሥራ 6:1-15

ሐዋርያት ሥራ 6:1-15 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

በዚ​ያም ወራት ደቀ መዛ​ሙ​ርት በበዙ ጊዜ ከግ​ሪክ የመጡ ደቀ መዛ​ሙ​ርት በአ​ይ​ሁድ ምእ​መ​ናን ላይ አን​ጐ​ራ​ጐ​ሩ​ባ​ቸው፤ የዕ​ለት የዕ​ለ​ቱን ምግብ ሲያ​ካ​ፍሉ ባል​ቴ​ቶ​ቻ​ቸ​ውን ቸል ይሉ​ባ​ቸው ነበ​ርና። ዐሥራ ሁለ​ቱም ሐዋ​ር​ያት ሕዝ​ቡን ሁሉ ጠር​ተው እን​ዲህ አሉ​አ​ቸው፥ “የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ቃል ትተን ማዕ​ድን እና​ገ​ለ​ግል ዘንድ የሚ​ገባ አይ​ደ​ለም። ወን​ድ​ሞ​ቻ​ችን ሆይ፥ ከእ​ና​ንተ ወገን በመ​ል​ካም የተ​መ​ሰ​ከ​ረ​ላ​ቸ​ውን መን​ፈስ ቅዱ​ስና ጥበብ የሞ​ላ​ባ​ቸ​ውን ሰባት ሰዎ​ችን ምረጡ፤ ለዚህ ሥራም እን​ሾ​ማ​ቸ​ዋ​ለን። እኛ ግን ለጸ​ሎ​ትና ቃሉን ለማ​ስ​ተ​ማር እን​ተ​ጋ​ለን።” ይህም ነገር በእ​ነ​ርሱ ዘንድ የተ​ወ​ደደ ሆነ፤ ሃይ​ማ​ኖቱ የቀ​ናና መን​ፈስ ቅዱስ ያደ​ረ​በ​ትን ሰው እስ​ጢ​ፋ​ኖ​ስን፥ ፊል​ጶ​ስን፥ ጵሮ​ኮ​ሮ​ስን፥ ኒቃ​ሮ​ናን፥ ጢሞ​ናን፥ ጰር​ሜ​ናን፥ ወደ ይሁ​ዲ​ነት የተ​መ​ለ​ሰ​ውን የአ​ን​ጾ​ኪ​ያ​ውን ኒቆ​ላ​ዎ​ስ​ንም መረጡ። በሐ​ዋ​ር​ያ​ትም ፊት አቆ​ሙ​አ​ቸው፤ ጸል​የ​ውም እጃ​ቸ​ውን በራ​ሳ​ቸው ላይ ጫኑ። የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ቃል ከፍ ከፍ አለ፤ በኢ​የ​ሩ​ሳ​ሌ​ምም ምእ​መ​ናን እጅግ በዙ፤ ከካ​ህ​ና​ትም መካ​ከል ያመኑ ብዙ​ዎች ነበሩ። እስ​ጢ​ፋ​ኖ​ስም የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ጸጋና ኀይል የመ​ላ​በት ሰው ነበር፤ በሕ​ዝ​ቡም መካ​ከል ታላ​ላቅ ተአ​ም​ራ​ት​ንና ድንቅ ሥራን ይሠራ ነበር። የነጻ ወጭ​ዎች ከም​ት​ባ​ለው ምኵ​ራ​ብም ከቀ​ሬ​ናና ከእ​ስ​ክ​ን​ድ​ርያ፥ ከቂ​ል​ቅ​ያና ከእ​ስያ የሆኑ ሰዎ​ችም ተነ​ሥ​ተው እስ​ጢ​ፋ​ኖ​ስን ይከ​ራ​ከ​ሩት ነበር። ነገር ግን ይቃ​ወ​ሙት ዘንድ አል​ቻ​ሉም፤ በጥ​በ​ብና በመ​ን​ፈስ ቅዱስ ይከ​ራ​ከ​ራ​ቸው ነበ​ርና። ከዚ​ህም በኋላ “ይህን ሰው በሙ​ሴና በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ላይ የስ​ድ​ብን ቃል ሲና​ገር ሰም​ተ​ነ​ዋል” የሚሉ የሐ​ሰት ምስ​ክ​ሮ​ችን አስ​ነ​ሡ​በት፤ ሕዝ​ቡን፥ ሽማ​ግ​ሌ​ዎ​ች​ንና ጸሓ​ፊ​ዎ​ች​ንም አነ​ሳ​ሡ​አ​ቸው፤ ከበ​ውም እየ​ጐ​ተቱ ወደ ሸንጎ አቀ​ረ​ቡት። የሐ​ሰት ምስ​ክ​ሮ​ች​ንም አቆ​ሙ​በት፤ እነ​ር​ሱም እን​ዲህ አሉ፥ “ይህ ሰው በዚህ ቤተ መቅ​ደስ ላይና በኦ​ሪት ላይ የስ​ድብ ቃል እየ​ተ​ና​ገረ ዝም በል ቢሉት እንቢ አለ፤ የና​ዝ​ሬቱ ኢየ​ሱስ ይህን ቤተ መቅ​ደስ ያፈ​ር​ሰ​ዋል፤ ሙሴም የሰ​ጠ​ንን ኦሪ​ታ​ች​ንን ይሽ​ራል ሲል ሰም​ተ​ነ​ዋል።” በሸ​ን​ጎም ተቀ​ም​ጠው የነ​በ​ሩት ሁሉ ትኩር ብለው ተመ​ለ​ከ​ቱት፤ ፊቱ​ንም እንደ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር መል​አክ ፊት ሆኖ አዩት።

ሐዋርያት ሥራ 6:1-15 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

የደቀ መዛሙርት ቍጥር እየጨመረ በሄደበት በዚህ ወቅት፣ ከግሪክ አገር የመጡ አይሁድ በይሁዳ ይኖሩ በነበሩት አይሁድ ላይ አጕረመረሙ፤ ምክንያቱም በየዕለቱ በሚከናወነው ምግብ የማደል አሠራር ላይ ከእነርሱ ወገን የሆኑት መበለቶች ችላ ተብለው ነበር። ስለዚህ ዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ሌሎችን ደቀ መዛሙርት በአንድነት ሰብስበው እንዲህ አሉ፤ “እኛ የማእዱን አገልግሎት ለማስተናገድ ስንል የእግዚአብሔርን ቃል አገልግሎት መተው አይገባንም። ስለዚህ ወንድሞች ሆይ፤ ከእናንተ መካከል በመንፈስ ቅዱስና በጥበብ የተሞሉ ለመሆናቸው የተመሰከረላቸውን ሰባት ሰዎች ምረጡ፤ ይህን ኀላፊነት ለእነርሱ እንሰጣለን፤ እኛ ግን በጸሎትና በቃሉ አገልግሎት እንተጋለን።” አባባሉ ሁላቸውን ደስ አሠኘ፤ በእምነትና በመንፈስ ቅዱስ የተሞላውን እስጢፋኖስን እንዲሁም ፊልጶስን፣ ጵሮኮሮስን፣ ኒቃሮናን፣ ጢሞናን፣ ጰርሜናንና ወደ ይሁዲነት ገብቶ የነበረውን አንጾኪያዊውን ኒቆላዎስን መረጡ። እነዚህንም አምጥተው ሐዋርያት ፊት አቀረቧቸው፤ እነርሱም ከጸለዩ በኋላ እጃቸውን ጫኑባቸው። የእግዚአብሔርም ቃል እየሰፋ ሄደ፤ የደቀ መዛሙርቱም ቍጥር በኢየሩሳሌም እጅግ እየበዛ ሄደ፤ ከካህናትም ብዙዎቹ ለእምነት የታዘዙ ሆኑ። በዚህ ጊዜ እስጢፋኖስ ጸጋንና ኀይልን ተሞልቶ በሕዝቡ መካከል ድንቅ ነገሮችንና ታምራዊ ምልክቶችን ያደርግ ነበር። “የነጻ ወጪዎች ምኵራብ” ተብሎ የሚጠራው ምኵራብ አባላት የሆኑ ከቀሬናና ከእስክንድርያ፣ እንዲሁም ከኪልቅያና ከእስያ አውራጃዎች የመጡ ሰዎችም ተቃውሞ አስነሥተው እስጢፋኖስን ይከራከሩት ጀመር፤ ይሁን እንጂ ይናገርበት የነበረውን ጥበብና መንፈስ መቋቋም አልቻሉም። ስለዚህ፣ “እስጢፋኖስ በሙሴና በእግዚአብሔር ላይ የስድብ ቃል ሲሰነዝር ሰምተናል” የሚሉ ሰዎችን በስውር አዘጋጁ። በዚህ ሁኔታ ሕዝቡን፣ የአገር ሽማግሌዎቹንና የሕግ መምህራኑን በማነሣሣት፣ እስጢፋኖስን አስይዘው በአይሁድ ሸንጎ ፊት አቀረቡት፤ እንዲህ ብለው የሚመሰክሩ የሐሰት ምስክሮችንም አቆሙበት፤ “ይህ ሰው በዚህ በተቀደሰው ስፍራና በሕጉ ላይ የስድብ ቃል መናገሩን በፍጹም አልተወም፤ ምክንያቱም ይህ የናዝሬቱ ኢየሱስ ይህን ስፍራ እንደሚያጠፋና ከሙሴ የተቀበልነውን ወግ እንደሚለውጥ ሲናገር ሰምተነዋል።” በሸንጎው ተቀምጠው የነበሩትም ሁሉ እስጢፋኖስን ትኵር ብለው ሲመለከቱት ፊቱ የመልአክ ፊት መስሎ ታያቸው።

ሐዋርያት ሥራ 6:1-15 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

በዚህም ወራት ደቀ መዛሙርት እየበዙ ሲሄዱ ከግሪክ አገር መጥተው የነበሩት አይሁድ በይሁዳ ኖረው በነበሩት አይሁድ አንጐራጐሩባቸው፥ በየቀኑ በተሠራው አገልግሎት መበለቶቻቸውን ችላ ይሉባቸው ነበርና። አሥራ ሁለቱም ደቀ መዛሙርት ሁሉን ጠርተው እንዲህ አሉአቸው፦ “የእግዚአብሔር ቃል ትተን ማዕድን እናገለግል ዘንድ የሚገባ ነገር አይደለም። ወንድሞች ሆይ፥ በመልካም የተመሰከረላቸውን መንፈስ ቅዱስና ጥበብም የሞላባቸውን ሰባት ሰዎች ከእናንተ ምረጡ፥ ለዚህም ጉዳይ እንሾማቸዋለን፤ እኛ ግን ለጸሎትና ቃሉን ለማገልገል እንተጋለን።” ይህም ቃል ሕዝብን ሁሉ ደስ አሰኛቸው፤ እምነትና መንፈስ ቅዱስም የሞላበትን ሰው እስጢፋኖስን ፊልጶስንም ጵሮኮሮስንም ኒቃሮናንም ጢሞናንም ጳርሜናንም ወደ ይሁዲነት ገብቶ የነበረውን የአንጾኪያውን ኒቆላዎስንም መረጡ። በሐዋርያትም ፊት አቆሙአቸው፥ ከጸለዩም በኋላ እጃቸውን ጫኑባቸው። የእግዚአብሔርም ቃል እየሰፋ ሄደ፥ በኢየሩሳሌምም የደቀ መዛሙርት ቍጥር እጅግ እየበዛ ሄደ፤ ከካህናትም ብዙ ሰዎች ለሃይማኖት የታዘዙ ሆኑ። እስጢፋኖስም ጸጋንና ኃይልን ተሞልቶ በሕዝቡ መካከል ድንቅንና ታላቅ ምልክትን ያደርግ ነበር። የነፃ ወጪዎች ከተባለችው ምኵራብም ከቀሬናና ከእስክንድርያም ሰዎች ከኪልቅያና ከእስያም ከነበሩት አንዳንዶቹ ተነሥተው እስጢፋኖስን ይከራከሩት ነበር፤ ይናገርበት የነበረውንም ጥበብና መንፈስ ይቃወሙ ዘንድ አልቻሉም። በዚያን ጊዜ፦ “በሙሴ ላይ በእግዚአብሔርም ላይ የስድብን ነገር ሲናገር ሰምተነዋል” የሚሉ ሰዎችን አስነሡ። ሕዝቡንና ሽማግሌዎችንም ጻፎችንም አናደዱ፥ ቀርበውም ያዙት ወደ ሸንጎም አመጡትና፦ “ይህ ሰው በዚህ በተቀደሰው ስፍራ በሕግም ላይ የስድብን ነገር ለመናገር አይተውም፤ ይህ የናዝሬቱ ኢየሱስ ይህን ስፍራ ያፈርሰዋል ሙሴም ያስተላለፈልንን ሥርዓት ይለውጣል ሲል ሰምተነዋልና” የሚሉ የሐሰት ምስክሮችን አቆሙ። በሸንጎም የተቀመጡት ሁሉ ትኵር ብለው ሲመለከቱት እንደ መልአክ ፊት ሆኖ ፊቱን አዩት።

ሐዋርያት ሥራ 6:1-15 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ከጥቂት ጊዜ በኋላ የአማኞች ቊጥር እየበዛ ሲሄድ የግሪክ ቋንቋ የሚናገሩ አይሁድ የይሁዳ አገር ተወላጆች በሆኑት አይሁድ ላይ ማጒረምረም ጀመሩ፤ ያጒረመረሙትም በየቀኑ ይታደል በነበረው ርዳታ ባሎቻቸው የሞቱባቸውን ሴቶች ችላ ይሉባቸው ስለ ነበር ነው። ስለዚህ ዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት አማኞችን ሁሉ ሰብስበው እንዲህ አሉአቸው፦ “ምግብ ለማደል ብለን የእግዚአብሔርን ቃል የማስተማር ሥራችንን መተው አይገባንም። እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፥ በመልካም ጠባያቸው የተመሰገኑ፥ በመንፈስ ቅዱስና በጥበብ የተሞሉ ሰባት ሰዎችን ከመካከላችሁ ምረጡ፤ እነርሱን ለዚህ ኀላፊነት እንሾማቸዋለን። እኛ ግን በመጸለይና የእግዚአብሔርን ቃል በማስተማር እንተጋለን።” ይህ አባባል ሁሉንም አስደሰተ ቀጥሎ ያሉትም ሰዎች ተመረጡ፤ እነርሱም በእምነትና በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ እስጢፋኖስን፥ ፊልጶስ፥ ጵሮኮሮስ፥ ኒቃሮና፥ ጢሞና፥ ጰርሜና የአይሁድን እምነት ተቀብሎ የነበረው የአንጾኪያው ኒቆላዎስ ናቸው። እነዚህን በሐዋርያት ፊት አቆሙአቸው፤ ሐዋርያትም ከጸለዩ በኋላ እጃቸውን ጫኑባቸው። በዚህ ሁኔታ የእግዚአብሔር ቃል እየተስፋፋ ስለ ሄደ፥ በኢየሩሳሌም የአማኞች ቊጥር በጣም እየበዛ ሄደ፤ ከካህናትም እጅግ ብዙዎቹ አመኑ። እስጢፋኖስ በጸጋና በኀይል ተሞልቶ ድንቅ ነገሮችንና ታላላቅ ተአምራትን በሕዝቡ መካከል ያደርግ ነበር፤ በዚያን ጊዜ “የነጻ ወጪዎች ምኵራብ” ከተባለው የአይሁድ ጸሎት ቤት ሰዎች፥ ከቀሬናና ከእስክንድርያ ሰዎች፥ ከኪልቅያና ከእስያ አንዳንድ ሰዎች ተነሥተው እስጢፋኖስን በመቃወም ይከራከሩት ነበር። ነገር ግን እስጢፋኖስ ይናገርበት የነበረውን ጥበብና መንፈስ መቋቋም አልቻሉም። በዚያን ጊዜ “ይህ ሰው በሙሴና በእግዚአብሔር ላይ የስድብ ቃል ሲናገር ሰምተነዋል” የሚሉ ሰዎችን በስውር አነሣሡበት። በዚሁ ዐይነት ሕዝቡንና ሽማግሌዎቹን የሕግ መምህራንንም በእርሱ ላይ አነሣሡ፤ ወደ እስጢፋኖስም ሄዱና ይዘው በሸንጎው ፊት አቀረቡት። በእርሱ ላይ በሐሰት የሚመሰክሩ አንዳንድ ሰዎችንም አመጡ፤ የሐሰት ምስክሮችም እንዲህ አሉ፦ “ይህ ሰው በዚህ ቤተ መቅደስና በሕግ ላይ የስድብ ቃል ከመናገር አይቈጠብም። ደግሞም ‘ይህ የናዝሬቱ ኢየሱስ ይህን ቤተ መቅደስ ያፈርሳል፤ ሙሴም ያስተላለፈልንን ሥርዓት ይለውጣል’ ብሎ ሲናገር ሰምተነዋል።” በዚህ ጊዜ በሸንጎው የተገኙት ሁሉ እስጢፋኖስን ትኲር ብለው ሲመለከቱት ፊቱ እንደ መልአክ ፊት ሆኖ ታያቸው።

ሐዋርያት ሥራ 6:1-15 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

በዚህም ወራት ደቀ መዛሙርት እየበዙ ሲሄዱ ከግሪክ አገር መጥተው የነበሩት አይሁድ በይሁዳ ኖረው በነበሩት አይሁድ አንጐራጐሩባቸው፤ በየቀኑ በተሠራው አገልግሎት መበለቶቻቸውን ችላ ይሉባቸው ነበርና። ዐሥራ ሁለቱም ደቀ መዛሙርት ሁሉን ጠርተው እንዲህ አሉአቸው “የእግዚአብሔር ቃል ትተን ማዕድን እናገለግል ዘንድ የሚገባ ነገር አይደለም። ወንድሞች ሆይ! በመልካም የተመሰከረላቸውን መንፈስ ቅዱስና ጥበብም የሞላባቸውን ሰባት ሰዎች ከእናንተ ምረጡ፤ ለዚህም ጉዳይ እንሾማቸዋለን፤ እኛ ግን ለጸሎትና ቃሉን ለማገልገል እንተጋለን።” ይህም ቃል ሕዝቡን ሁሉ ደስ አሰኛቸው፤ እምነትና መንፈስ ቅዱስም የሞላበትን ሰው እስጢፋኖስን ፊልጶስንም ጵሮኮሮስንም ኒቃሮናንም ጢሞናንም ጳርሜናንም ወደ ይሁዲነት ገብቶ የነበረውን የአንጾኪያውን ኒቆላዎስንም መረጡ። በሐዋርያትም ፊት አቆሙአቸው፤ ከጸለዩም በኋላ እጃቸውን ጫኑባቸው። የእግዚአብሔርም ቃል እየሰፋ ሄደ፤ በኢየሩሳሌምም የደቀ መዛሙርት ቍጥር እጅግ እየበዛ ሄደ፤ ከካህናትም ብዙ ሰዎች ለሃይማኖት የታዘዙ ሆኑ። እስጢፋኖስም ጸጋንና ኃይልን ተሞልቶ በሕዝቡ መካከል ድንቅንና ታላቅ ምልክትን ያደርግ ነበር። የነፃ ወጪዎች ከተባለችው ምኵራብም ከቀሬናና ከእስክንድርያም ሰዎች ከኪልቅያና በእስያም ከነበሩት አንዳንዶቹ ተነሥተው እስጢፋኖስን ይከራከሩት ነበር፤ ይናገርበት የነበረውንም ጥበብና መንፈስ ይቃወሙ ዘንድ አልቻሉም። በዚያን ጊዜ “በሙሴ ላይ በእግዚአብሔርም ላይ የስድብን ነገር ሲናገር ሰምተነዋል፤” የሚሉ ሰዎችን አስነሡ። ሕዝቡንና ሽማግሌዎችንም ጻፎችንም አነሣሡ፤ ቀርበውም ያዙት፤ ወደ ሸንጎም አመጡትና “ይህ ሰው በዚህ በተቀደሰው ስፍራ በሕግም ላይ የስድብን ነገር ለመናገር አይተውም፤ ‘ይህ የናዝሬቱ ኢየሱስ ይህን ስፍራ ያፈርሰዋል፤ ሙሴም ያስተላለፈልንን ሥርዓት ይለውጣል፤’ ሲል ሰምተነዋልና፤” የሚሉ የሐሰት ምስክሮችን አቆሙ። በሸንጎም የተቀመጡት ሁሉ ትኩር ብለው ሲመለከቱት እንደ መልአክ ፊት ሆኖ ፊቱን አዩት።