ሐዋርያት ሥራ 28:1-31 - Compare All Versions
ሐዋርያት ሥራ 28:1-31 አማ2000 (የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ))
ከዚህም በኋላ በደኅና በደረስን ጊዜ ደሴቲቱ መላጥያ እንደምትባል ዐወቅን። በዚያ የሚኖሩት አረማውያንም አዘኑልን፤ መልካም ነገርንም አደረጉልን፤ ከቍሩም ጽናትና ከዝናሙ ብዛት የተነሣ እሳት አንድደው እንድንሞቅ ሁላችንንም ሰበሰቡን። ጳውሎስም ብዙ ጭራሮ ሰብስቦ በእሳቱ ላይ ጨመረው፤ እፉኝትም ከእሳቱ ወላፈን የተነሣ ወጥታ ጳውሎስን እጁን ነደፈችው። አረማውያንም እፉኝቱ በጳውሎስ እጅ ላይ ተንጠልጥላ ባዩ ጊዜ እርስ በርሳቸው፥ “ይህ ሰው ነፍሰ ገዳይ ይመስላል፤ ከባሕር እንኳ በደኅና ቢወጣም በሕይወት ይኖር ዘንድ የእግዚአብሔር ፍርድ አልተወውም” አሉ። ጳውሎስ ግን እጁን አራግፎ እፉኝቱን በእሳት ውስጥ ጣላት፤ ጕዳትም አላገኘውም። እነርሱ ግን ወዲያውኑ የሚያብጥ ወይም ሞቶ የሚወድቅ መስሎአቸው ነበር። እያዩትም ብዙ ሰዓት ቆሙ፤ አንዳችም እንደ አልጐዳው በአዩ ጊዜም፥ “ይህስ አምላክ ነው” ብለው ቃላቸውን ለወጡ። በዚያ ቦታም አጠገብ ስሙን ፑፕልዮስ የሚሉት የደሴቲቱ አለቃ መሬት ነበር፤ እርሱም ሦስት ቀን ሙሉ በደስታ በቤቱ ተቀብሎ አስተናገደን። የፑፕልዮስም አባት በንዳድና በተቅማጥ ታሞ ተኝቶ ይኖር ነበር፤ ጳውሎስም እርሱ ወዳለበት ገብቶ ጸለየለት፤ እጁንም በላዩ ጭኖ ፈወሰው። ያደረገውንም ይህን ተአምር ባዩ ጊዜ በዚያች ደሴት ያሉትን ድውያን ሁሉ አመጡለት፤ ፈወሳቸውም። እጅግ ታላቅ ክብርም አከበሩን፤ ከእነርሱም ዘንድ ለመሄድ በተነሣን ጊዜ የሚያስፈልገንን ስንቅ ሰጡን። ከሦስት ወር በኋላም በዚያች ደሴት ወደ ከረመችው ወደ እስክንድርያ መርከብ ወጣን፤ በዚያች መርከብ ላይም የዲዮስቆሮስ ምልክት ነበረባት፤ ይኸውም “የመርከበኞች አምላክ” የሚሉት ነው። ከዚያም ሄደን ወደ ሰራኩስ ደረስን፤ በዚያም ሦስት ቀን ተቀመጥን። ከዚያም ሄደን ሬቅዩን ወደምትባል ሀገር ደረስን፤ በማግሥቱም ወጣን፤ ከአንድ ቀንም በኋላ ከጐንዋ ነፋስ በነፈሰ ጊዜ በሁለተኛው ቀን ወደ ፑቲዮሉስ ደረስን። በዚያም ወንድሞችን አግኝተን ተቀበሉን፤ በእነርሱ ዘንድም ሰባት ቀን እንድንቀመጥ ለመኑን፤ ከዚያም በኋላ ሄደን ወደ ሮሜ ደረስን። በዚያም ያሉት ወንድሞች ስለ እኛ በሰሙ ጊዜ፤ አፍዩስ ፋሩስ እስከሚባለው ገበያና እስከ ሦስተኛው ማረፊያ ድረስ ወጥተው ተቀበሉን፤ ጳውሎስም ባያቸው ጊዜ እግዚአብሔርን አመሰገነ፤ ልቡም ተጽናና። ወደ ሮሜም በገባን ጊዜ የመቶ አለቃው እስረኞችን ለሠራዊቱ አለቃ አስረከበ፤ ጳውሎስ ግን ከሚጠብቀው አንድ ወታደር ጋር ለብቻው ይቀመጥ ዘንድ ፈቀደለት። ከሦስት ቀንም በኋላ ጳውሎስ የአይሁድን ታላላቅ ሰዎች ሰበሰባቸው፤ በተሰበሰቡም ጊዜ እንዲህ አላቸው፥ “ወንድሞቻችን ሆይ፥ እኔ በሕዝቡም ላይ ቢሆን፥ በአባቶቻችንም ሕግ ላይ ቢሆን ያደረግሁት ክፉ ነገር የለም፤ ነገር ግን በኢየሩሳሌም እንደ ታሰርሁ ለሮም ሰዎች አሳልፈው ሰጡኝ። እነርሱም መርምረው ለሞት የሚያበቃ በደል ስለአላገኙብኝ ሊፈቱኝ ወደዱ። አይሁድ ግን ሊቃወሙኝ በተነሡ ጊዜ ወደ ቄሣር ይግባኝ ለማለት ግድ ሆነብኝ፤ ነገር ግን ወገኖችን የምከስበት ነገር ኖሮኝ አይደለም። ስለዚህም ላያችሁ፥ ልነግራችሁና ላስረዳችሁ ወደ እኔ እንድትመጡ ማለድኋችሁ፤ ስለ እስራኤል ተስፋ በዚህ ሰንሰለት ታስሬአለሁና።” የአይሁድ ታላላቅ ሰዎችም እንዲህ አሉት፥ “ለእኛስ ከይሁዳ ሀገር ስለ አንተ መልእክት አልደረሰንም፤ ከኢየሩሳሌም ከመጡት ወንድሞችም ቢሆን አንድ ስንኳ ከዚህ አስቀድሞ ስለ አንተ ክፉ ነገር ያወራን፥ የነገረንም የለም። ነገር ግን በዚህ ነገር በየስፍራው ሁሉ እንዲጣሉ በእኛ ዘንድ ታውቋልና የአንተን ዐሳብ ደግሞ ከአንተ እንሰማ ዘንድ እንወድዳለን።” ከዚህም በኋላ ወደ እርሱ የሚመጡበትን ቀን ቀጠሩትና ብዙዎች ወዳረፈበት ወደ እርሱ መጡ፤ ከጥዋትም ጀምሮ እስከ ማታ ድረስ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት እየመሰከረ ስለ ጌታችን ስለ ኢየሱስም ከሙሴ ኦሪትና ከነቢያት እየጠቀሰ ነገራቸው። ከእነርሱም እኩሌቶቹ የተናገረውን አመኑ፤ እኩሌቶቹ ግን አልተቀበሉትም። እርስ በርሳቸውም ባልተስማሙ ጊዜ ጳውሎስ አንዲት ቃል ከተናገረ በኋላ ከእርሱ ተመለሱ፤ እንዲህም አላቸው፥ “መንፈስ ቅዱስ በነቢዩ በኢሳይያስ አንደበት ለአባቶቻችን በእውነት እንዲህ ብሎ መልካም ነገር ተናግሮአል። ‘ወደዚህ ሕዝብ ሂድና እንዲህ በላቸው፦ መስማትን ትሰማላችሁ፤ ግን አታስተውሉም፤ ማየትንም ታያላችሁ፤ ግን አትመለከቱም። በዐይናቸው እንዳያዩ፥ በጆሮአቸውም እንዳይሰሙ፥ በልባቸውም እንዳያስተውሉ፥ ወደ እኔም እንዳይመለሱና ይቅር እንዳልላቸው የዚህ ሕዝብ ልባቸው ደንድኖአልና፥ ጆሮአቸውም ደንቁሮአልና፥ ዐይናቸውንም ጨፍነዋልና’። እንግዲህ ከእግዚአብሔር የተገኘች ይህቺ ድኅነት ለአሕዛብ እንደምትሆን ዕወቁ፤ እነርሱም ይሰሙታል።” ይህንም በተናገራቸው ጊዜ አይሁድ እርስ በርሳቸው እጅግ እየተከራከሩ ወጥተው ሄዱ። ጳውሎስም በገንዘቡ በተከራየው ቤት ሁለት ዓመት ተቀመጠ፤ ወደ እርሱ የሚመጣውንም ሁሉ ይቀበል ነበር። ማንም ሳይከለክለው የእግዚአብሔርን መንግሥት ይሰብክ ነበር፤ ስለ ጌታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስም እጅግ ገልጦ ያስተምር ነበር።
ሐዋርያት ሥራ 28:1-31 NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
በደኅና ወደ ምድር ከደረስን በኋላ፣ ደሴቲቱ መላጥያ ተብላ እንደምትጠራ ተረዳን። የደሴቲቱ ነዋሪዎችም የሚያስገርም ደግነት አሳዩን፤ ዝናብና ብርድ ነበርና እሳት አንድደው ሁላችንን ተቀበሉን። ጳውሎስም ጭራሮ ሰብስቦ ወደ እሳቱ ሲጨምር፣ ከሙቀቱ የተነሣ እፉኝት ወጥታ እጁ ላይ ተጣበቀች። የደሴቲቱ ነዋሪዎች እባብ በእጁ ላይ ተንጠልጥላ ባዩ ጊዜ፣ “ይህ ሰው በርግጥ ነፍስ ገዳይ ነው፤ ከባሕር ቢያመልጥ እንኳ የፍርድ አምላክ በሕይወት እንዲኖር አልፈቀደለትም” ተባባሉ። ጳውሎስ ግን እባቢቱን ወደ እሳቱ አራገፋት፤ አንዳችም ጕዳት አልደረሰበትም። ሰዎቹ ከአሁን አሁን ሰውነቱ ያብጣል ወይም ድንገት ሞቶ ይወድቃል ብለው ይጠባበቁ ነበር፤ ነገር ግን ብዙ ጊዜ ጠብቀው ምንም የተለየ ነገር እንዳልደረሰበት ባዩ ጊዜ፣ ሐሳባቸውን ለውጠው፣ “ይህስ አምላክ ነው” አሉ። በዚያም ስፍራ አጠገብ ፑፕልዮስ የተባለ የደሴቲቱ አለቃ ርስት የሆነ መሬት ነበረ፤ እርሱም በቤቱ ተቀብሎን ሦስት ቀን በቸርነት አስተናገደን። የፑፕልዮስም አባት በትኵሳትና በተቅማጥ ሕመም ተይዞ ተኝቶ ነበር፤ ጳውሎስም ሊጠይቀው ገብቶ ከጸለየለት በኋላ፣ እጁን ጭኖ ፈወሰው። ይህም በሆነ ጊዜ፣ በደሴቲቱ የነበሩ ሌሎች ሕመምተኞችም እየመጡ ተፈወሱ። እኛንም በብዙ መንገድ አከበሩን፤ በመርከብም ለመሄድ በተዘጋጀን ጊዜ፣ የሚያስፈልገንን ሁሉ ጫኑልን። ከሦስት ወር በኋላም፣ በደሴቲቱ ክረምቱን ቆሞ በሰነበተ በአንድ መርከብ ተነሥተን ጕዞ ጀመርን። ይህም መርከብ የእስክንድርያ ሲሆን፣ በላዩ ላይ የመንታ አማልክቱ የዲዮስቆሮስ አርማ ነበረበት። ወደ ሰራኩስ ከተማ ገብተን ሦስት ቀን በዚያ ተቀመጥን። ከዚያም በመርከብ ተጕዘን ሬጊዩም ደረስን፤ በማግስቱም የደቡብ ነፋስ ስለ ተነሣ ፑቲዮሉስ የደረስነው በሚቀጥለው ቀን ነበር። በዚያም ወንድሞችን አገኘን፤ እነርሱም ሰባት ቀን ዐብረናቸው እንድንቀመጥ ለመኑን፤ ከዚያም በኋላ ወደ ሮም ሄድን። በዚያ የነበሩ ወንድሞችም መምጣታችንን ስለ ሰሙ፣ እስከ አፍዩስ ፋሩስ እንዲሁም “ሦስት ማደሪያ” እስከሚባለው ቦታ ድረስ ሊቀበሉን ወጡ፤ ጳውሎስም ባያቸው ጊዜ እግዚአብሔርን አመሰገነ፤ ተጽናናም። ሮም በደረስን ጊዜም፣ ጳውሎስ ይጠብቀው ከነበረው ወታደር ጋራ ለብቻው በዚያ እንዲቈይ ተፈቀደለት። ከሦስት ቀንም በኋላ፣ ጳውሎስ የአይሁድን መሪዎች በአንድነት ጠራ፤ በተሰበሰቡም ጊዜ እንዲህ አላቸው፤ “ወንድሞች ሆይ፤ እኔ፣ ሕዝባችንን ወይም የአባቶቻችንን ሥርዐት የሚቃረን ምንም ሳላደርግ፣ በኢየሩሳሌም አስረው ለሮማውያን አሳልፈው ሰጥተውኛል። እነርሱም መርምረው ለሞት የሚያበቃ በደል ስላላገኙብኝ፣ ሊፈቱኝ ፈልገው ነበር፤ አይሁድ በተቃወሙ ጊዜ ግን፣ ለቄሳር ይግባኝ ማለት ግድ ሆነብኝ እንጂ ሕዝቤን የምከስስበት ምክንያት ኖሮኝ አይደለም። እናንተንም ለማየትና ለማነጋገር የጠራኋችሁ በዚሁ ምክንያት ነው፤ በዚህ ሰንሰለት የታሰርሁትም ለእስራኤል በተሰጠው ተስፋ ምክንያት ነው።” እነርሱም እንዲህ አሉት፤ “ስለ አንተ ከይሁዳ ምድር የተጻፈ አንድም ደብዳቤ አልደረሰንም፤ ከዚያ የመጡ ወንድሞችም ስለ አንተ ያቀረቡት ወይም የተናገሩት አንዳች መጥፎ ነገር የለም። ይሁን እንጂ፣ ሰዎች ስለዚህ የእምነት ክፍል በየቦታው ክፉ እንደሚያወሩበት እናውቃለን፤ የአንተ አስተሳሰብ ደግሞ ምን እንደ ሆነ መስማት እንፈልጋለን።” ቀን ከቀጠሩለትም በኋላ፣ ብዙ ሆነው ወደ ማረፊያ ስፍራው መጡ፤ እርሱም ከጧት ጀምሮ እስከ ማታ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት እየመሰከረ ያብራራላቸው ነበር፤ ከሙሴ ሕግና ከነቢያትም በመጥቀስ ስለ ኢየሱስ ሊያሳምናቸው ሞከረ። አንዳንዶቹ እርሱ የሚለውን አምነው ተቀበሉ፤ ሌሎቹ ግን አላመኑበትም፤ እርስ በርሳቸውም አልተስማሙም፤ ጳውሎስም እንዲህ የሚል የመጨረሻ ቃል ከተናገራቸው በኋላ ሄዱ፤ “መንፈስ ቅዱስ በነቢዩ በኢሳይያስ አማካይነት ለአባቶቻችሁ በትክክል እንዲህ ብሎ ተናግሯል፤ “ ‘ወደዚህ ሕዝብ ሂድ፤ እንዲህም በላቸው፤ “መስማትን ትሰማላችሁ፤ ነገር ግን አታስተውሉም፤ ማየትን ታያላችሁ፤ ነገር ግን አትመለከቱም።” የዚህ ሕዝብ ልብ ደንድኗልና፤ ጆሯቸውም ተደፍኗል፤ ዐይናቸውንም ጨፍነዋል። አለዚያማ፣ በዐይናቸው አይተው፣ በጆሯቸው ሰምተው፣ በልባቸውም አስተውለው፣ ወደ እኔ በተመለሱና በፈወስኋቸው ነበር።’ “ስለዚህ የእግዚአብሔር ማዳን ለአሕዛብ እንደ ተላከ እንድታውቁ እፈልጋለሁ፤ እነርሱም ይሰሙታል!” [ይህንም ከተናገረ በኋላ፣ አይሁድ እርስ በርሳቸው እጅግ እየተከራከሩ ሄዱ።] ጳውሎስም ራሱ በተከራየው ቤት ሁለት ዓመት ሙሉ ተቀመጠ፤ ወደ እርሱ የሚመጡትንም ሁሉ በደስታ ይቀበል ነበር፤ ማንም ሳይከለክለው የእግዚአብሔርን መንግሥት እየሰበከ፣ ስለ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በፍጹም ግልጽነት ያስተምር ነበር።
ሐዋርያት ሥራ 28:1-31 አማ54 (መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት))
በደኅና ከደረስን በኋላ በዚያን ጊዜ ደሴቲቱ መላጥያ እንድትባል አወቅን። አረማውያንም የሚያስገርም ቸርነት አደረጉልን፤ ዝናብ ስለ ሆነም ስለ ብርዱም እሳት አንድደው ሁላችንን ተቀበሉን። ጳውሎስ ግን ብዙ ጭራሮ አከማችቶ ወደ እሳት ሲጨምር እፉኝት ከሙቀት የተነሣ ወጥታ እጁን ነደፈችው። አረማውያንም እባብ በእጁ ተንጠልጥላ ባዩ ጊዜ፥ እርስ በርሳቸው፦ “ይህ ሰው በእርግጥ ነፍሰ ገዳይ ነው፥ ከባሕርም ስንኳ በደኅና ቢወጣ የእግዚአብሔር ፍርድ በሕይወት ይኖር ዘንድ አልተወውም” አሉ። እርሱ ግን እባቢቱን ወደ እሳት አራገፋት አንዳችም አልጐዳችውም፤ እነርሱም፦ “ሊያብጥ ወይም ወዲያው ሞቶ ሊወድቅ ነው” ብለው ይጠባበቁት ነበር ብዙ ጊዜ ግን ሲጠባበቁ በእርሱ ላይ የሚያስገርም ነገር ምንም ባላዩ ጊዜ፦ “ይህስ አምላክ ነው” ብለው አሳባቸውን ለወጡ። በዚያም ስፍራ አጠገብ ፑፕልዮስ የሚሉት የደሴት አለቃ መሬት ነበረ፥ እርሱም እንግድነት ተቀብሎን ሦስት ቀን በፍቅር አሳደረን። የፑፕልዮስም አባት በንዳድና በተቅማጥ ታሞ ተኝቶ ነበር፤ ጳውሎስም ወደ እርሱ ገብቶ ጸለየለት እጁንም በላዩ ጭኖ ፈወሰው። ይህም በሆነ ጊዜ የቀሩት ደግሞ በደሴቲቱ ደዌ የነበረባቸው እየመጡ ተፈወሱ፤ በብዙ ክብርም ደግሞ አከበሩን፥ በተነሣንም ጊዜ በመርከብ ላይ የሚያስፈልገንን ነገር አኖሩልን። ከሦስት ወርም በኋላ በደሴቲቱ ከርሞ በነበረው በእስክንድርያው መርከብ ተነሣን፥ በእርሱም የዲዮስቆሮስ አላማ ነበረበት። ወደ ሰራኩስም በገባን ጊዜ ሦስት ቀን ተቀመጥን፤ ከዚያም እየተዛወርን ወደ ሬጊዩም ደረስን። ከአንድ ቀን በኋላም የደቡብ ነፋስ በነፈሰ ጊዜ በሁለተኛው ቀን ወደ ፑቲዮሉስ መጣን። በዚያም ወንድሞችን አግኝተን በእነርሱ ዘንድ ሰባት ቀን እንድንቀመጥ ለመኑን፤ እንዲሁም ወደ ሮሜ መጣን። ከዚያም ወንድሞች ስለ እኛ ሰምተው እስከ አፍዩስ ፋሩስና ሦስት ማደሪያ እስከሚባለው ሊቀበሉን ወጡ፥ ጳውሎስም ባያቸው ጊዜ እግዚአብሔርን አመሰገነ ልቡም ተጽናና። ወደ ሮሜም በገባን ጊዜ ጳውሎስ ከሚጠብቀው ወታደር ጋር ለብቻው ይቀመጥ ዘንድ ተፈቀደለት። ከሦስት ቀንም በኋላ ጳውሎስ የአይሁድን ታላላቆች ወደ እርሱ ጠራ፤ በተሰበሰቡም ጊዜ እንዲህ አላቸው፦ “ወንድሞች ሆይ፥ እኔ ሕዝቡን ወይም የአባቶችን ሥርዓት የሚቃወም አንዳች ሳላደርግ፥ ከኢየሩሳሌም እንደ ታሰርሁ በሮማውያን እጅ አሳልፈው ሰጡኝ። እነርሱም መርምረው ለሞት የሚገባ ምክንያት ስላልነበረብኝ ሊፈቱኝ አሰቡ፤ አይሁድ ግን በተቃወሙ ጊዜ፥ ወደ ቄሣር ይግባኝ እንድል ግድ ሆነብኝ እንጂ ሕዝቤን የምከስበት ነገር ኖሮኝ አይደለም። ስለዚህም ምክንያት አያችሁና እነግራችሁ ዘንድ ጠራኋችሁ፤ ስለ እስራኤል ተስፋ ይህን ሰንሰለት ለብሻለሁና።” እነርሱም፦ “እኛ ከይሁዳ ስለ አንተ ደብዳቤ አልተቀበልንም፥ ከወንድሞችም አንድ ስንኳ መጥቶ ስለ አንተ ክፉ ነገር አላወራልንም ወይም አልተናገረብህም። ነገር ግን ስለዚህ ወገን በየስፍራው ሁሉ እንዲቃወሙ በእኛ ዘንድ ታውቆአልና የምታስበውን ከአንተ እንሰማ ዘንድ እንፈቅዳለን” አሉት። ቀንም ቀጥረውለት ብዙ ሆነው ወደ መኖሪያው ወደ እርሱ መጡ፤ ስለ እግዚአብሔር መንግሥትም እየመሰከረ ስለ ኢየሱስም ከሙሴ ሕግና ከነቢያት ጠቅሶ እያስረዳቸው፥ ከጥዋት ጀምሮ እስከ ማታ ድረስ ይገልጥላቸው ነበር። እኵሌቶቹም የተናገረውን አመኑ፥ እኵሌቶቹ ግን አላመኑም፤ እርስ በርሳቸውም ባልተስማሙ ጊዜ፥ ጳውሎስ አንዲት ቃል ከተናገረ በኋላ ሄዱ፤ እንዲህም አለ፦ “መንፈስ ቅዱስ በነቢዩ በኢሳይያስ ለአባቶቻችን፦ ‘ወደዚህ ሕዝብ ሂድና፦ መስማትን ትሰማላችሁና አታስተውሉም፥ ማየትንም ታያላችሁና አትመለከቱም፤ በዓይናቸው እንዳያዩ በጆሮአቸው እንዳይሰሙ በልባቸውም እንዳያስተውሉ ተመልሰውም እንዳልፈውሳቸው፥ የዚህ ሕዝብ ልብ ደንድኖአል ጆሮአቸውም ደንቁሮአል ዓይናቸውንም ጨፍነዋል በላቸው’ ሲል መልካም ተናገረ። እንግዲህ ይህ የእግዚአብሔር ደኅንነት ለአሕዛብ እንደ ተላከ በእናንተ ዘንድ የታወቀ ይሁን፤ እነርሱ ደግሞ ይሰሙታል። ይህንም በተናገረ ጊዜ አይሁድ እርስ በርሳቸው እጅግ እየተከራከሩ ሄዱ።” ጳውሎስም በተከራየው ቤት ሁለት ዓመት ሙሉ ተቀመጠ፥ ወደ እርሱም የሚመጡትን ሁሉ ይቀበል ነበር፤ ማንም ሳይከለክለው የእግዚአብሔርን መንግሥት እየሰበከ ስለ ጌታ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እጅግ ገልጦ ያስተምር ነበር።
ሐዋርያት ሥራ 28:1-31 አማ05 (አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም)
ወደ ምድር በደኅና ከደረስን በኋላ የደረስንባት ደሴት ማልታ የምትባል መሆንዋን ዐወቅን። የዚያች ደሴት ነዋሪዎች የሚያስደንቅ ደግነት አደረጉልን፤ በዚያን ጊዜም ዝናብ ስለ ዘነበና ብርድ ስለ ሆነ እሳት አንድደው ተቀበሉን፤ ጳውሎስ ጭራሮ ሰብስቦ ወደ እሳቱ ሲጥል፥ ከሙቀቱ የተነሣ አንድ እባብ ወጣና በእጁ ላይ ተጣብቆ ተንጠለጠለ፤ የማልታ ሰዎች እባብ በጳውሎስ እጅ ላይ ተንጠልጥሎ ባዩ ጊዜ “ይህ ሰው በእርግጥ ነፍሰ ገዳይ ነው! ከባሕሩ ማዕበል በደኅና ቢወጣም ከአምላክ ፍርድ አምልጦ በሕይወት ለመኖር አልቻለም” ተባባሉ። ጳውሎስ ግን እባቡን ወደ እሳቱ አራግፎ ጣለውና ምንም ጒዳት ሳያገኘው ቀረ። ሰዎቹም “ከአሁን አሁን ሰውነቱ ያብጣል፤ ወይም በድንገት ሞቶ ይወድቃል” በማለት ይጠባበቁ ነበር። ነገር ግን ብዙ ጊዜ ተጠባብቀውት ምንም ጒዳት እንዳልደረሰበት ባዩ ጊዜ አሳባቸውን ለወጡና “ይህስ አምላክ ነው!” አሉ። በዚያ በነበርንበት ስፍራ አጠገብ የደሴቲቱ ገዢ የፑፕልዮስ መሬት ነበር፤ ይህ ሰው በቤቱ ተቀብሎን ሦስት ቀን በጥሩ ሁኔታ አስተናገደን። በዚያን ጊዜ የፑፕልዮስ አባት ትኩሳትና ተቅማጥ ይዞት ታሞ ተኝቶ ነበር፤ ጳውሎስ ወደ እርሱ ገብቶ ጸለየለት፤ እጁንም ጫነበትና ፈወሰው። ይህ ከሆነ በኋላ በደሴቲቱ የሚኖሩት ሌሎች በሽተኞች መጡና ተፈወሱ። ሰዎቹ ብዙ ስጦታ አመጡልን፤ አክብሮታቸውንም ገለጡልን፤ በመርከብ ለመሄድ በተነሣንም ጊዜ የሚያስፈልገንን ሁሉ በመርከብ ላይ ጫኑልን። ሦስት ወር በማልታ ከቈየን በኋላ ክረምቱን በደሴቲቱ ባሳለፈው በእስክንድርያው መርከብ ተሳፍረን ተነሣን፤ መርከቡ ዲዮስቆሮስ የተባሉ የመንታ አማልክት አርማ ነበረበት። ወደ ስራኩስ ከተማ በደረስን ጊዜ እዚያ ሦስት ቀን ተቀመጥን። ከዚያም በባሕሩ ዞረን ወደ ሬጊዩም ከተማ ደረስን፤ እዚያ አንድ ቀን ካሳለፍን በኋላ የደቡብ ነፋስ ስለ ነፈሰ በሁለተኛው ቀን ወደ ፑቲዮሉስ ሄድን። እዚያ ወንድሞችን አገኘንና ከእነርሱ ጋር ሰባት ቀን እንድንቀመጥ ለመኑን፤ ከዚህ በኋላ ወደ ሮም ሄድን። በሮም ያሉ ምእመናን ስለ እኛ በሰሙ ጊዜ እስከ አፍዮስ ገበያና “ሦስት ማደሪያዎች” እስከሚባለው ቦታ ድረስ ሊቀበሉን መጡ፤ ጳውሎስ እነርሱን ባየ ጊዜ እግዚአብሔርን አመሰገነና ተጽናና። ወደ ሮም በገባን ጊዜ ጳውሎስ አንድ የሚጠብቀው ወታደር ተሰጠውና ብቻውን እንዲኖር ተፈቀደለት። ከሦስት ቀን በኋላ ጳውሎስ በሮም የሚኖሩትን የአይሁድን ታላላቅ ሰዎች አስጠራ፤ በተሰበሰቡም ጊዜ እንዲህ አላቸው፦ “ወንድሞቼ ሆይ፥ በእስራኤል ሕዝብ ላይና በአባቶች ሥርዓት ላይ ያደረግኹት ምንም በደል የለም፤ ይሁን እንጂ በኢየሩሳሌም ታስሬ ለሮማውያን ተላልፌ ተሰጠሁ። ሮማውያን ከመረመሩኝ በኋላ በሞት የሚያስቀጣ ምክንያት ስላላገኙብኝ በነጻ ሊለቁኝ አስበው ነበር። አይሁድ ግን የእኔን በነጻ መለቀቅ በተቃወሙ ጊዜ ወደ ሮም ንጉሠ ነገሥት ይግባኝ ለማለት ተገደድኩ፤ ሆኖም ሕዝቤን የምከስበት ነገር አልነበረኝም። አሁንም ያስጠራኋችሁ እንዳያችሁና ይህንንም እንድነግራችሁ ነው፤ እኔ በዚህ በሰንሰለት የታሰርኩት ለእስራኤል በተሰጠው ተስፋ ምክንያት ነው።” እነርሱም እንዲህ ሲሉ መለሱለት፦ “ከይሁዳ ምድር ስለ አንተ ጉዳይ የተጻፈ ደብዳቤ አልደረሰንም፤ ወደዚህ ከመጡ ሰዎች ማንም ስለ አንተ ክፉ ያወራ ወይም የተናገረ የለም። ይህን አንተ የምትከተለውን የሃይማኖት ክፍል በየቦታው ሰዎች እንደሚቃወሙት እናውቃለን፤ ስለዚህ የአንተ አሳብ ምን እንደ ሆነ መስማት እንፈልጋለን።” ቀን ከቀጠሩለትም በኋላ ብዙ ሆነው ወደ መኖሪያ ቤቱ መጡ፤ እርሱም ከጧት እስከ ማታ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት በመመስከር አሳቡን ገለጠላቸው፤ እነርሱንም ለማሳመን ከሙሴ ሕግና ከነቢያት መጻሕፍት እየጠቀሰም ስለ ኢየሱስ አስረዳቸው። አንዳንዶቹ የተናገረውን ቃል አመኑ፤ ሌሎች ግን አላመኑም። እነርሱም እርስ በርሳቸው ሳይስማሙ ተለያዩ። ሆኖም ከመለያየታቸው በፊት ጳውሎስ ለመጨረሻ ጊዜ ሲናገር እንዲህ አለ፦ “መንፈስ ቅዱስ በነቢዩ በኢሳይያስ አማካይነት ለአባቶቻችሁ የተናገረው ልክ ነበር! የተናገረውም ቃል ይህ ነው፦ ‘ወደዚህ ሕዝብ ሂድና መስማትስ ትሰማላችሁ፤ ግን አታስተውሉም፤ ማየትስ ታያላችሁ፤ ግን ልብ አታደርጉም በላቸው፤ የእነዚህ ሰዎች ልብ ደንድኖአል፤ ጆሮአቸውም ተጨፍኖአል፤ ዐይናቸውም ተዘግቶአል፤ እንዲህስ ባይሆን ኖሮ፥ በዐይናቸው አይተው፥ በጆሮአቸው ሰምተው፥ በልባቸውም አስተውለው፥ ወደ እኔ በተመለሱና እኔም በፈወስኩአቸው ነበር።’ “እንግዲህ የእግዚአብሔር አዳኝነት መልእክት ለአሕዛብ እንደ ተላከ ዕወቁ፤ እነርሱም እሺ ብለው ይቀበሉታል።” [“ጳውሎስ ይህን ከተናገረ በኋላ አይሁድ በብርቱ እየተከራከሩ ከዚያ ወጥተው ሄዱ።”] ጳውሎስ በተከራየው ቤት ሁለት ዓመት ሙሉ ተቀመጠ፤ ወደ እርሱ የሚመጡትንም ሰዎች ሁሉ ይቀበል ነበር፤ የእግዚአብሔርንም መንግሥት በመስበክ ስለ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ማንም ሳይከለክለው በድፍረት ያስተምር ነበር።
ሐዋርያት ሥራ 28:1-31 መቅካእኤ (መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ))
በደኅና ከደረስን በኋላ በዚያን ጊዜ ደሴቲቱ መላጥያ እንደምትባለ አወቅን። አረማውያንም የሚያስገርም ቸርነት አደረጉልን፤ ዝናብ ስለ ሆነም ስለ ብርዱም እሳት አንድደው ሁላችንን ተቀበሉን። ጳውሎስ ግን ብዙ ጭራሮ አከማችቶ ወደ እሳት ሲጨምር እፉኝት ከሙቀት የተነሣ ወጥታ እጁን ነደፈችው። አረማውያንም እባብ በእጁ ተንጠልጥላ ባዩ ጊዜ፥ እርስ በርሳቸው “ይህ ሰው በእርግጥ ነፍሰ ገዳይ ነው፤ ከባሕርም ስንኳ በደኅና ቢወጣ የእግዚአብሔር ፍርድ በሕይወት ይኖር ዘንድ አልተወውም፤” አሉ። እርሱ ግን እባቢቱን ወደ እሳት አራገፋት፤ አንዳችም አልጐዳችውም፤ እነርሱም “ሊያብጥ ወይም ወዲያው ሞቶ ሊወድቅ ነው፤” ብለው ይጠባበቁት ነበር ብዙ ጊዜ ግን ሲጠባበቁ በእርሱ ላይ የሚያስገርም ነገር ምንም ባላዩ ጊዜ “ይህስ አምላክ ነው፤” ብለው አሳባቸውን ለወጡ። በዚያም ስፍራ አጠገብ ፑፕልዮስ የሚሉት የደሴት አለቃ መሬት ነበረ፤ እርሱም በእንግድነት ተቀብሎን ሦስት ቀን በፍቅር አሳደረን። የፑፕልዮስም አባት በንዳድና በተቅማጥ ታሞ ተኝቶ ነበር፤ ጳውሎስም ወደ እርሱ ገብቶ ጸለየለት፤ እጁንም በላዩ ጭኖ ፈወሰው። ይህም በሆነ ጊዜ የቀሩት ደግሞ በደሴቲቱ ደዌ የነበረባቸው እየመጡ ተፈወሱ፤ በብዙ ክብርም ደግሞ አከበሩን፤ በተነሣንም ጊዜ በመርከብ ላይ የሚያስፈልገንን ነገር አኖሩልን። ከሦስት ወርም በኋላ በደሴቲቱ ከርሞ በነበረው በእስክንድርያው መርከብ ተነሣን፤ በእርሱም የዲዮስቆሮስ ዓላማ ነበረበት። ወደ ሰራኩስም በገባን ጊዜ ሦስት ቀን ተቀመጥን፤ ከዚያም እየተዛወርን ወደ ሬጊዩም ደረስን። ከአንድ ቀን በኋላም የደቡብ ነፋስ በነፈሰ ጊዜ በሁለተኛው ቀን ወደ ፑቲዮሉስ መጣን። በዚያም ወንድሞችን አግኝተን በእነርሱ ዘንድ ሰባት ቀን እንድንቀመጥ ለመኑን፤ እንዲሁም ወደ ሮሜ መጣን። ከዚያም ወንድሞች ስለ እኛ ሰምተው እስከ አፍዩስ ፋሩስና ሦስት ማደሪያ እስከሚባለው ሊቀበሉን ወጡ፤ ጳውሎስም ባያቸው ጊዜ እግዚአብሔርን አመሰገነ፤ ልቡም ተጽናና። ወደ ሮሜም በገባን ጊዜ ጳውሎስ ከሚጠብቀው ወታደር ጋር ለብቻው ይቀመጥ ዘንድ ተፈቀደለት። ከሦስት ቀንም በኋላ ጳውሎስ የአይሁድን ታላላቆች ወደ እርሱ ጠራ፤ በተሰበሰቡም ጊዜ እንዲህ አላቸው “ወንድሞች ሆይ! እኔ ሕዝቡን ወይም የአባቶችን ሥርዓት የሚቃወም አንዳች ሳላደርግ፥ ከኢየሩሳሌም እንደ ታሰርሁ በሮማውያን እጅ አሳልፈው ሰጡኝ። እነርሱም መርምረው ለሞት የሚገባ ምክንያት ስላልነበረብኝ ሊፈቱኝ አሰቡ፤ አይሁድ ግን በተቃወሙ ጊዜ፥ ወደ ቄሣር ይግባኝ እንድል ግድ ሆነብኝ እንጂ ሕዝቤን የምከስበት ነገር ኖሮኝ አይደለም። ስለዚህም ምክንያት አያችሁና እነግራችሁ ዘንድ ጠራኋችሁ፤ ስለ እስራኤል ተስፋ ይህን ሰንሰለት ለብሻለሁና።” እነርሱም “እኛ ከይሁዳ ስለ አንተ ደብዳቤ አልተቀበልንም፤ ከወንድሞችም አንድ ስንኳ መጥቶ ስለ አንተ ክፉ ነገር አላወራልንም፤ ወይም አልተናገረብህም። ነገር ግን ስለዚህ ወገን በየስፍራው ሁሉ እንዲቃወሙ በእኛ ዘንድ ታውቆአልና የምታስበውን ከአንተ እንሰማ ዘንድ እንፈቅዳለን፤” አሉት። ቀንም ቀጥረውለት ብዙ ሆነው ወደ መኖሪያው ወደ እርሱ መጡ፤ ስለ እግዚአብሔር መንግሥትም እየመሰከረ ስለ ኢየሱስም ከሙሴ ሕግና ከነቢያት ጠቅሶ እያስረዳቸው፥ ከጥዋት ጀምሮ እስከ ማታ ድረስ ይገልጥላቸው ነበር። እኩሌቶቹም የተናገረውን አመኑ፤ እኩሌቶቹ ግን አላመኑም፤ እርስ በርሳቸውም ባልተስማሙ ጊዜ፥ ጳውሎስ አንዲት ቃል ከተናገረ በኋላ ሄዱ፤ እንዲህም አለ፦ መንፈስ ቅዱስ በነቢዩ በኢሳይያስ ለአባቶቻችን ወደዚህ ሕዝብ ሂድና፥ መስማትን ትሰማላችሁና አታስተውሉም፤ ማየትንም ታያላችሁና አትመለከቱም፤ በዐይናቸው እንዳያዩ በጆሮአቸውም እንዳይሰሙ በልባቸውም እንዳያስተውሉ ተመልሰውም እንዳልፈውሳቸው፥ የዚህ ሕዝብ ልብ ደንድኖአል፤ ጆሮአቸውም ደንቁሮአል ዐይናቸውንም ጨፍነዋል፤ በላቸው። ሲል መልካም ተናገረ። እንግዲህ ይህ የእግዚአብሔር ማዳን ለአሕዛብ እንደ ተላከ በእናንተ ዘንድ የታወቀ ይሁን፤ እነርሱ ደግሞ ይሰሙታል። ይህንም በተናገረ ጊዜ አይሁድ እርስ በርሳቸው እጅግ እየተከራከሩ ሄዱ። ጳውሎስም በተከራየው ቤት ሁለት ዓመት ሙሉ ተቀመጠ፤ ወደ እርሱም የሚመጡትን ሁሉ ይቀበል ነበር፤ ማንም ሳይከለክለው የእግዚአብሔርን መንግሥት እየሰበከ ስለ ጌታ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ በግልጽነትና በልበ ሙሉነት ያስተምር ነበር።