ሐዋርያት ሥራ 21:1-40 - Compare All Versions

ሐዋርያት ሥራ 21:1-40 NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)

ከእነርሱ ከተለየን በኋላ ቀጥታ በመርከብ ወደ ቆስ ተጓዝን፤ በማግስቱም ወደ ሩድ፣ ከዚያም ወደ ጳጥራ አመራን። በዚያም ወደ ፊንቄ የሚሄድ መርከብ ስላገኘን፣ ተሳፍረን ጕዟችንን ቀጠልን። ቆጵሮስ በታየችን ጊዜ፣ ወደ ግራ ትተናት ዐለፍንና ወደ ሶርያ አመራን፤ መርከባችን ጭነቱን በጢሮስ ማራገፍ ስለ ነበረበት እኛም እዚያው ወረድን። ደቀ መዛሙርትንም በዚያ አግኝተን፣ ሰባት ቀን ከእነርሱ ጋራ ተቀመጥን። እነርሱም በመንፈስ ሆነው ጳውሎስ ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይሄድ ነገሩት። የቈይታ ጊዜያችን ባለቀ ጊዜ፣ ትተናቸው ጕዟችንን ቀጠልን፤ ደቀ መዛሙርቱም ሁሉ ከሚስቶቻቸውና ከልጆቻቸው ጋራ እስከ ከተማው ውጭ ድረስ ሸኙን፤ በባሕሩም ዳር ተንበርክከን ጸለይን፤ ከተሰነባበትንም በኋላ እኛ ወደ መርከቡ ገባን፤ እነርሱም ወደ ቤታቸው ተመለሱ። ከጢሮስ ተነሥተን ጕዟችንን በመቀጠል ጴጤሌማይስ ደረስን፤ ከመርከብ ወርደንም ለወንድሞች ሰላምታ ካቀረብን በኋላ፣ አንድ ቀን ከእነርሱ ጋራ ቈየን። በማግስቱም ከዚያ ተነሥተን ቂሳርያ ደረስን፤ ከሰባቱ ወንጌላውያን አንዱ በሆነው በፊልጶስ ቤትም ዐረፍን። እርሱም ትንቢት የሚናገሩ አራት ደናግል ሴቶች ልጆች ነበሩት። በዚያም ብዙ ቀን ከተቀመጥን በኋላ አጋቦስ የተባለ ነቢይ ከይሁዳ ወረደ፤ ወደ እኛም መጣና የጳውሎስን መታጠቂያ ወሰደ፤ የራሱንም እጅና እግር በማሰር፣ “መንፈስ ቅዱስ፣ ‘በኢየሩሳሌም ያሉ አይሁድ የዚህን መታጠቂያ ባለቤት እንዲህ አድርገው በማሰር ለአሕዛብ አሳልፈው ይሰጡታል’ ይላል” አለ። ይህን ስንሰማ እኛና በዚያም የሚኖሩት ጳውሎስ ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይሄድ ለመንነው። ጳውሎስ ግን፣ “ለምን እንዲህ እያለቀሳችሁ ልቤን ታባቡታላችሁ? እኔ መታሰር ቀርቶ ስለ ጌታ ኢየሱስ ስም በኢየሩሳሌም ለመሞት እንኳ ዝግጁ ነኝ” አላቸው። ምክራችንን አልቀበል ስላለን፣ “እንግዲህ የጌታ ፈቃድ ይሁን” ብለን ተውነው። ከዚህ በኋላ፣ ተዘጋጅተን ወደ ኢየሩሳሌም ወጣን። በቂሳርያ ከነበሩት ደቀ መዛሙርትም አንዳንዶቹ ወደ ምናሶን ቤት ይዘውን መጡ፤ እኛም በዚያው ተቀመጥን። ምናሶን የቆጵሮስ ሰው ሲሆን፣ ከመጀመሪያዎቹ ደቀ መዛሙርት አንዱ ነበረ። ኢየሩሳሌም በደረስን ጊዜ ወንድሞች በደስታ ተቀበሉን። በማግስቱም ጳውሎስና ሌሎቻችንም ያዕቆብን ለማየት ሄድን፤ ሽማግሌዎችም ሁሉ በዚያ ነበሩ። ጳውሎስም ሰላምታ ካቀረበላቸው በኋላ፣ እግዚአብሔር በርሱ አገልግሎት አማካይነት በአሕዛብ መካከል ያደረገውን ሁሉ በዝርዝር አስረዳቸው። እነርሱም ይህን ሲሰሙ፣ እግዚአብሔርን አመሰገኑ፤ ጳውሎስንም እንዲህ አሉት፤ “ወንድም ሆይ፤ በብዙ ሺሕ የሚቈጠሩ አይሁድ እንዳመኑ ተመልከት፤ ሁሉም ደግሞ ለሙሴ ሕግ የሚቀኑ ናቸው። በአሕዛብ መካከል የሚኖሩ አይሁድ ሁሉ ሙሴን እንዲተዉና ልጆቻቸውን እንዳይገርዙ፣ በቈየው ልማዳችን መሠረት እንዳይኖሩ እንደምታስተምር ስለ አንተ ተነግሯቸዋል። መምጣትህን መስማታቸው የማይቀር ነውና እንግዲህ ምን እናድርግ? ስለዚህ የምንልህን አድርግ። ስእለት ያለባቸው አራት ሰዎች በእኛ ዘንድ አሉ፤ እነዚህን ሰዎች ይዘህ ከእነርሱ ጋራ የመንጻቱን ሥርዐት ፈጽም፤ ራሳቸውንም እንዲላጩ የሚጠየቀውን ገንዘቡን ክፈልላቸው፤ በዚህም ስለ አንተ የተነገራቸው ሰዎች ሁሉ የሰሙት እውነት እንዳልሆነና አንተ ራስህ ሕጉን ጠብቀህ የምትኖር መሆንህን ያውቃሉ። ከአሕዛብ ወገን ያመኑትን በተመለከተ ግን ለጣዖት የተሠዋ ምግብ፣ ደምና ታንቆ የሞተ እንስሳ ሥጋ እንዳይበሉ፣ ደግሞም ከዝሙት ርኩሰት ራሳቸውን እንዲጠብቁ ወስነን ጽፈንላቸዋል።” ጳውሎስም በማግስቱም ሰዎቹን ይዞ ሄደ፤ ዐብሯቸውም የመንጻቱን ሥርዐት ፈጸመ። ከዚያም የመንጻቱ ሥርዐት መቼ እንደሚያበቃና የእያንዳንዳቸውም መሥዋዕት መቼ እንደሚቀርብ ለማስታወቅ ወደ ቤተ መቅደስ ገባ። ሰባቱ ቀንም ሊፈጸም ሲቃረብ፣ ከእስያ አውራጃ የመጡት አይሁድ ጳውሎስን በቤተ መቅደስ ባዩት ጊዜ፣ ሕዝቡን ሁሉ አነሣሥተው ያዙት፤ እንዲህም እያሉ ጮኹ፤ “የእስራኤል ሰዎች ሆይ፤ ርዱን! ሕዝባችንንና ሕጋችንን እንዲሁም ይህን ስፍራ በማጥላላት በደረሰበት ስፍራ የሚገኙትን ሰዎች ሁሉ የሚያስተምረው ሰው ይህ ነው፤ ከዚህም በላይ ግሪኮችን ወደ ቤተ መቅደስ እያስገባ ይህን የተቀደሰ ስፍራ የሚያረክሰው እርሱ ነው።” ይህንም ያሉት ቀደም ሲል፣ የኤፌሶኑን ሰው ጥሮፊሞስን ከጳውሎስ ጋራ በከተማው ውስጥ ስላዩት፣ ጳውሎስ እርሱንም ወደ ቤተ መቅደስ ይዞ የገባ ስለ መሰላቸው ነበር። ከተማው በሙሉ ታወከ፤ ሕዝቡም ከየአቅጣጫው እየተሯሯጡ መጡ፤ ጳውሎስንም ይዘው እየጐተቱት ከቤተ መቅደሱ ግቢ አወጡት፤ በሮቹም ወዲያውኑ ተዘጉ። ሊገድሉት ሲፈልጉም የኢየሩሳሌም ከተማ ፍጹም ታወከች፤ ወሬውም ለሮማ ጦር አዛዥ ደረሰው። እርሱም ወዲያው አንዳንድ የጦር መኰንኖችንና ወታደሮችን ይዞ እየሮጠ ወደ እነርሱ ወረደ፤ እነርሱም መኰንኖቹንና ወታደሮቹን ባዩ ጊዜ ጳውሎስን መደብደብ ተዉ። የጦር አዛዡም ቀርቦ ያዘው፤ በሁለት ሰንሰለትም እንዲታሰር ትእዛዝ ሰጠ፤ ከዚያም ማን መሆኑንና ምን እንዳደረገ ጠየቀ። ሕዝቡም ከፊሉ አንድ ነገር ሲናገር፣ ከፊሉ ደግሞ ሌላ ይናገር ነበር፤ ከጫጫታው የተነሣም አዛዡ ምንም ነገር ሊሰማ አልቻለም፤ ስለዚህ ጳውሎስ ወደ ጦር ሰፈር እንዲወሰድ አዘዘ። ከሕዝቡ ሁካታ የተነሣ፣ ጳውሎስ ወደ መውጫው ደረጃ ሲደርስ ወታደሮቹ ይሸከሙት ዘንድ ግድ ሆነባቸው። ከኋላ የተከተለውም ሕዝብ፣ “አስወግደው!” እያለ ይጮኽ ነበር። ወታደሮቹ ወደ ጦር ሰፈር ይዘውት ሊሄዱ ሲሉ፣ ጳውሎስ ጦር አዛዡን፣ “አንድ ነገር እንድነግርህ ፍቀድልኝ?” አለው። አዛዡም እንዲህ አለው፤ “የግሪክ ቋንቋ ታውቃለህ? አንተ ከዚህ ቀደም ዐመፅ አስነሥተህ፣ አራት ሺሕ ነፍሰ ገዳዮችን ወደ በረሓ ያሸፈትኸው ግብጻዊ አይደለህምን?” ጳውሎስም፣ “እኔስ በኪልቅያ ያለችው የታዋቂዋ የጠርሴስ ከተማ ነዋሪ የሆንሁ አይሁዳዊ ነኝ፤ ለሕዝቡ ንግግር እንዳደርግ ፍቀድልኝ” አለው። ጳውሎስም የጦር አዛዡን ካስፈቀደ በኋላ፣ በደረጃው ላይ ቆሞ ሕዝቡን በእጁ ጠቀሰ፤ ሁሉም ጸጥ ባሉ ጊዜ፣ በዕብራይስጥ ቋንቋ እንዲህ አለ፤

ሐዋርያት ሥራ 21:1-40 አማ05 (አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም)

ከእነርሱ ከተለየን በኋላ በመርከብ ተሳፈርንና በቀጥታ ቆስ ወደምትባል ደሴት ሄድን፤ በማግስቱም ወደ ሩድ ደሴት ደረስን፤ ከዚያም ወደ ጳጥራ ከተማ ሄድን። እዚያም ወደ ፊንቄ አገር የምትሄድ መርከብ አገኘንና በእርስዋ ተሳፍረን፤ ጒዞአችንን ቀጠልን። የቆጵሮስን ደሴት በስተግራችን ትተን ወደ ሶርያ አገር ተጓዝንና ወደ ጢሮስ ወደብ ሄድን፤ መርከቡ ጭነቱን እዚያ ማራገፍ ነበረበት። እዚያ ምእመናንን ፈልገን አገኘንና ከእነርሱ ጋር ሰባት ቀን ቈየን። እነርሱም በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው ጳውሎስን “ወደ ኢየሩሳሌም አትሂድ” ብለው ነገሩት። እዚያ የምንቈይበት ጊዜ ሲያልቅ ተለይተናቸው ጒዞአችንን ቀጠልን፤ ሁሉም ከሚስቶቻቸውና ከልጆቻቸው ጋር ሆነው እስከ ከተማው ውጪ ድረስ ሸኙን፤ በባሕሩም ዳር ተንበርክከን ከጸለይን በኋላ ተሰነባበትን። ከዚህ በኋላ እኛ በመርከብ ስንሳፈር እነርሱ ወደ ቤታቸው ተመለሱ። ከጢሮስ ተነሥተን ወደ ጴጤሌማይስ ደረስን፤ እዚያ ከአማኞች ጋር ተገናኝተን ሰላምታ ከተለዋወጥን በኋላ ከእነርሱ ጋር አንድ ቀን አሳለፍን። በማግስቱ ከዚያ ወጥተን ወደ ቂሳርያ ሄድን፤ እዚያ ከሰባቱ ዲያቆናት አንዱ ወደ ሆነው ወደ ወንጌላዊው ፊልጶስ ቤት ገባንና ከእርሱ ጋር ተቀመጥን። እርሱ ትንቢት የመናገር ስጦታ ያላቸው አራት ያላገቡ ሴቶች ልጆች ነበሩት። ለብዙ ቀኖች እዚያ በተቀመጥንበት ጊዜ አጋቦስ የሚባል ነቢይ ከይሁዳ ምድር መጣ። ይህ ነቢይ ወደ እኛ ቀረበ፤ የጳውሎስን መታጠቂያ ወስዶ የገዛ እጆቹንና እግሮቹን አሰረና “መንፈስ ቅዱስ የዚህን መታጠቂያ ባለቤት በኢየሩሳሌም ያሉ አይሁድ እንደዚህ አስረው ለአሕዛብ አሳልፈው ይሰጡታል ይላል” አለ። ይህንን በሰማን ጊዜ እኛም እዚያ የነበሩ ሰዎችም ጳውሎስ ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይሄድ ለመንነው። ጳውሎስ ግን “እንደዚህ እያለቀሳችሁ ስለምን ልቤን በሐዘን ትሰብሩታላችሁ? እኔ ስለ ጌታ ኢየሱስ ስም በኢየሩሳሌም ለመታሰር ብቻ ሳይሆን ለመሞትም ዝግጁ ነኝ” ሲል መለሰ። ምክራችንን አልቀበልም ባለን ጊዜ “እንግዲህ የጌታ ፈቃድ ይሁን” ብለን ተውነው። እዚያ ጥቂት ቀኖች ከቈየን በኋላ ዕቃችንን አዘጋጅተን ወደ ኢየሩሳሌም ሄድን። በቂሳርያ የነበሩ አንዳንድ ምእመናን አብረውን መጡ፤ እነርሱም በምናሶን ቤት እንድናርፍ ወደ እርሱ ቤት መሩን፤ ይህ ሰው ቀደም ብሎ ያመነ፥ የቆጵሮስ ተወላጅ ነበር። ኢየሩሳሌም በደረስን ጊዜ ምእመናን በደስታ ተቀበሉን። በማግስቱ ጳውሎስ ከእኛ ጋር ወደ ያዕቆብ ሄደ፤ የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ሁሉ እዚያ ነበሩ። ጳውሎስ ለሁሉም ሰላምታ ከሰጠ በኋላ በእርሱ አማካይነት እግዚአብሔር በአሕዛብ መካከል ያደረገውን ሁሉ አንድ በአንድ ተረከላቸው። ይህን በሰሙ ጊዜ ሁሉም ጌታን አመሰገኑ፤ ጳውሎስንም እንዲህ አሉት፦ “ወንድም ሆይ! በብዙ ሺህ የሚቈጠሩ ምእመናን በአይሁድ መካከል እንዳሉና ሁሉም ለሕግ ቀናተኞች እንደ ሆኑ ታውቃለህ፤ አንተ በአሕዛብ መካከል የሚኖሩትን አይሁድ ሁሉ ‘ልጆቻችሁን አትግረዙ ወይም ሥርዓቶችን አትፈጽሙ’ እያልክ በማስተማር የሙሴን ሕግ እንዲሽሩ ታደርጋለህ እየተባለ የሚወራውን ሰምተዋል። እንግዲህ ምን ማድረግ ይሻላል? መምጣትህን በእርግጥ ይሰማሉ፤ ስለዚህ እኛ የምንልህን አድርግ፤ በእኛ መካከል ስለት ያለባቸው አራት ሰዎች አሉ። እነርሱን ውሰድና ከእነርሱ ጋር ሆነህ ራስህን አንጻ፤ ጠጒራቸውንም እንዲላጩ ለቤተ መቅደስ የሚሰጠውን የመባ ገንዘብ ክፈልላቸው፤ ይህን ብታደርግ በአንተ ላይ የተወራው ሁሉ ከንቱ መሆኑንና አንተም ራስህ ለሕግ ታዛዥ መሆንክህን ሁሉም ያውቃሉ። ከአሕዛብ ወገን ያመኑት ግን ‘ለጣዖት በመሠዋቱ ምክንያት የረከሰ ምግብ አትብሉ፤ ደምም አትብሉ፤ ታንቆ የሞተ እንስሳ ሥጋ አትብሉ፤ ከዝሙት ራቁ’ የሚለውን ውሳኔ የያዘ ደብዳቤ ጽፈን ልከንላቸዋል።” ከዚህ በኋላ ጳውሎስ ሰዎቹን ወሰደና በማግስቱ ከእነርሱ ጋር ራሱን አነጻ፤ የሚነጹባቸው ቀኖች መቼ እንደሚሆንና ስለ እያንዳንዱም የሚሰጠው የመባ ገንዘብ የሚከፈልበት ጊዜ መቼ እንደሚሆን ለማስታወቅ ወደ ቤተ መቅደስ ገባ። ሰባቱ ቀን ሊፈጸም ሲቃረብ ከእስያ የመጡ አይሁድ ጳውሎስን በቤተ መቅደስ በማየታቸው ሕዝቡን ሁሉ አሳድመው ያዙት፤ “የእስራኤል ሰዎች ሆይ! እርዱን! ሕዝባችንንና ሕጋችንን፥ ይህንንም ስፍራ እየተሳደበ በየአገሩ ያለውን ሕዝብ ሁሉ የሚያስተምር ይህ ሰው ነው፤ ይህም አልበቃ ብሎት አሕዛብን ወደ ቤተ መቅደስ በማስገባት ይህን የተቀደሰ ስፍራ አርክሶአል!” እያሉ ጮኹ። ይህንንም ያሉበት ምክንያት ከዚህ ቀደም የኤፌሶኑን ተወላጅ ጥሮፊሞስን ከእርሱ ጋር በከተማ አይተውት ስለ ነበር እርሱን ጳውሎስ ወደ ቤተ መቅደስ ይዞት የገባ መስሎአቸው ነበር። ከተማዋ በሙሉ ታወከች፤ ሕዝቡም ሁሉ እየሮጡ በአንድነት መጡና ጳውሎስን ይዘው እየጐተቱ ከቤተ መቅደስ አወጡት፤ የቤተ መቅደሱ በሮችም ወዲያውኑ ተዘጉ። ሰዎቹ ጳውሎስን ሊገድሉት በፈለጉ ጊዜ “የኢየሩሳሌም ከተማ በሙሉ ታውካለች” የሚል መልእክት ለሮማውያኑ ጦር አዛዥ ደረሰ። ስለዚህ እርሱ ወታደሮችንና የመቶ አለቆችን አስከትሎ በፍጥነት እየሮጠ ወደ ሰዎቹ ሄደ። ሰዎቹም አዛዡንና ወታደሮቹን ባዩ ጊዜ ጳውሎስን መደብደብ ተዉ። አዛዡም ቀርቦ ጳውሎስን ያዘውና በሁለት ሰንሰለት እንዲታሰር አዘዘ፤ ከዚህ በኋላ ማን መሆኑንና ምን እንዳደረገ ለማወቅ ፈልጎ ጠየቀ። ሕዝቡም አንዳንዶቹ አንድ ነገር ሲሉ፥ ሌሎች ሌላ ነገር ይሉ ነበር፤ አዛዡ ከሕዝቡ ጩኸት የተነሣ እርግጠኛውን ነገር ለማወቅ ስላልቻለ ጳውሎስን ወደ ወታደሮቹ ሰፈር እንዲወስዱት አዘዘ። ጳውሎስ ወደ ደረጃው በደረሰ ጊዜ ሕዝብ ሁሉ በብርቱ ቊጣ ተነሣሥቶ አደጋ ሊያደርስበት በመፈለጉ ወታደሮቹ ተሸክመውት ሄዱ። ሕዝቡም “ይገደል!” እያሉ በመጮኽ ይከተሉት ነበር። ወታደሮች ወደ ጦር ሰፈራቸው ሊያስገቡት በቀረቡ ጊዜ ጳውሎስ የጦር አዛዡን “አንድ ነገር እንድነግርህ ትፈቅድልኛለህን?” አለው። አዛዡም “የግሪክ ቋንቋ ታውቃለህን? ታዲያ፥ አሁን በቅርቡ ብጥብጥ አስነሥቶና አራት ሺህ ነፍሰ ገዳዮች ይዞ ወደ በረሓ የሸሸው ግብጻዊው አንተ አይደለህምን?” አለ። ጳውሎስም “እኔ በኪልቅያ በምትገኘውና ዝነኛ በሆነችው በጠርሴስ ከተማ የተወለድኩ አይሁዳዊ ነኝ፤ እባክህ ለሕዝቡ እንድናገር ፍቀድልኝ” አለው። እንዲናገር በፈቀደለት ጊዜ ጳውሎስ በደረጃ ላይ ቆሞ ሕዝቡ ዝም እንዲል በእጁ ጠቀሰ፤ ሕዝቡ ጸጥ ባለ ጊዜ በዕብራይስጥ ቋንቋ እንዲህ ሲል መናገር ጀመረ፤

ሐዋርያት ሥራ 21:1-40 አማ2000 (የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ))

ከእ​ነ​ር​ሱም ከተ​ለ​የን በኋላ እኛ በመ​ር​ከብ ተሳ​ፍ​ረን፥ መን​ገ​ዳ​ች​ን​ንም አቅ​ን​ተን ወደ ቆስ መጣን፤ በበ​ነ​ጋ​ውም ወደ ሮዶስ፥ ከዚ​ያም ወደ ጳጥራ ገባን። ወደ ፊን​ቄም የሚ​ያ​ልፍ መር​ከብ አግ​ኝ​ተን በዚያ ላይ ተሳ​ፍ​ረን ሄድን። ቆጵ​ሮ​ስ​ንም አየ​ናት፤ በስተ ግራ​ች​ንም ትተ​ናት ወደ ሶርያ ሄድን፤ ወደ ጢሮ​ስም ወረ​ድን፤ በመ​ር​ከብ ያለ​ውን ጭነት ሁሉ በዚያ ያራ​ግፉ ነበ​ርና። በዚ​ያም ደቀ መዛ​ሙ​ር​ትን አገ​ኘ​ንና በእ​ነ​ርሱ ዘንድ ሰባት ቀን ተቀ​መ​ጥን፤ እነ​ር​ሱም በመ​ን​ፈስ ቅዱስ ተገ​ል​ጾ​ላ​ቸው ጳው​ሎ​ስን ወደ ኢየ​ሩ​ሳ​ሌም እን​ዳ​ይ​ወጣ ነገ​ሩት። ከዚ​ህም በኋላ ለመ​ሄድ ወጣን፤ ሁሉም ከሚ​ስ​ቶ​ቻ​ቸ​ውና ከል​ጆ​ቻ​ቸው ጋር እስከ ከተ​ማው ውጭ ሸኙን፤ በባ​ሕ​ሩም ዳር ተን​በ​ር​ክ​ከን ጸለ​ይን። እርስ በር​ሳ​ች​ንም ተሳ​ስ​መን ተሰ​ነ​ባ​በ​ትን፤ ከዚ​ህም በኋላ ወደ መር​ከብ ወጣን፤ እነ​ር​ሱም ወደ ቤታ​ቸው ተመ​ለሱ። እኛም ከጢ​ሮስ ወጥ​ተን አካ ወደ​ም​ት​ባል ሀገር መጣን፤ ወን​ድ​ሞ​ቻ​ች​ን​ንም አግ​ኝ​ተን ሰላም አል​ና​ቸው፤ በእ​ነ​ር​ሱም ዘንድ አንድ ቀን አደ​ርን። በማ​ግ​ሥ​ቱም ወጥ​ተን ወደ ቂሳ​ርያ ሄድን፤ ወደ ወን​ጌ​ላ​ዊው ወደ ፊል​ጶስ ቤትም ገባን፤ እር​ሱም ከሰ​ባቱ ወን​ድ​ሞች ዲያ​ቆ​ናት አንዱ ነው። ለእ​ር​ሱም ትን​ቢት የሚ​ና​ገሩ አራት ደና​ግል ሴቶች ልጆች ነበ​ሩት። በእ​ር​ሱም ዘንድ ብዙ ቀን ኖርን፤ ከይ​ሁ​ዳም አጋ​ቦስ የሚ​ባል አንድ ነቢይ ወረደ። ወደ እኛም መጣና የጳ​ው​ሎ​ስን መታ​ጠ​ቂያ አን​ሥቶ እጁ​ንና እግ​ሩን በገዛ እጁ አስሮ እን​ዲህ አለ፥ “መን​ፈስ ቅዱስ እን​ዲህ ይላል፤ የዚ​ህን መታ​ጠ​ቂያ ጌታ አይ​ሁድ በኢ​የ​ሩ​ሳ​ሌም እን​ዲህ ያስ​ሩ​ታል፤ ለአ​ሕ​ዛ​ብም አሳ​ል​ፈው ይሰ​ጡ​ታል።” ይህ​ንም ሰም​ተን የሀ​ገ​ሪ​ቱን ሰዎች ይዘን ወደ ኢየ​ሩ​ሳ​ሌም እን​ዳ​ይ​ወጣ ጳው​ሎ​ስን ማለ​ድ​ነው። ጳው​ሎስ ግን መልሶ፥ “ለምን እን​ዲህ ታደ​ር​ጋ​ላ​ችሁ? እያ​ለ​ቀ​ሳ​ችሁ ልቤን ትሰ​ብ​ሩ​ታ​ላ​ችሁ፤ እኔ እኮ ተስፋ የማ​ደ​ር​ገው መከ​ራ​ንና እግር ብረ​ትን ብቻ አይ​ደ​ለም፤ እኔ ግን በጌ​ታ​ችን በኢ​የ​ሱስ ክር​ስ​ቶስ ስም በኢ​የ​ሩ​ሳ​ሌም ለመ​ሞ​ትም ቢሆን የቈ​ረ​ጥሁ ነኝ” አለ። እንቢ ባለ ጊዜም ዝም አልን፤ እኛም እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር የፈ​ቀ​ደው ይሁን ብለን ተው​ነው። ከእ​ነ​ዚ​ያም ቀኖች በኋላ ተዘ​ጋ​ጅ​ተን ወደ ኢየ​ሩ​ሳ​ሌም ወጣን። ከደቀ መዛ​ሙ​ር​ትም ከቂ​ሳ​ርያ አብ​ረ​ውን የመጡ ነበሩ፤ ሄደ​ንም ከመ​ጀ​መ​ሪ​ያ​ዎቹ ደቀ መዛ​ሙ​ርት ወገን ከሆ​ነው በቆ​ጵ​ሮስ በሚ​ኖ​ረው በም​ና​ሶን ቤት አደ​ርን። ኢየ​ሩ​ሳ​ሌም በደ​ረ​ስን ጊዜም ወን​ድ​ሞ​ቻ​ችን በደ​ስታ ተቀ​በ​ሉን። በማ​ግ​ሥ​ቱም ጳው​ሎስ ከእኛ ጋር ወደ ያዕ​ቆብ ገባ፤ ቀሳ​ው​ስ​ትም ሁሉ በዚያ ነበሩ። ጳው​ሎ​ስም ሰላ​ምታ ካቀ​ረ​በ​ላ​ቸው በኋላ በእ​ርሱ ሐዋ​ር​ያ​ነት እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር በአ​ሕ​ዛብ ያደ​ረ​ገ​ውን ሁሉ ነገ​ራ​ቸው። እነ​ር​ሱም ሰም​ተው እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን አመ​ሰ​ገኑ፤ እን​ዲ​ህም አሉ፥ “ወን​ድ​ማ​ችን ሆይ፥ ከአ​ይ​ሁድ መካ​ከል ያመ​ኑት ስንት አእ​ላ​ፋት እንደ ሆኑ ታያ​ለ​ህን? ሁሉም ለኦ​ሪት የሚ​ቀኑ ናቸው። ነገር ግን የማ​ይ​ሆ​ነ​ውን እን​ደ​ም​ታ​ስ​ተ​ምር፥ የሙ​ሴ​ንም ሕግ እን​ደ​ም​ታ​ስ​ተ​ዋ​ቸው፥ በአ​ሕ​ዛብ መካ​ከል ያሉ ያመኑ አይ​ሁ​ድ​ንም ልጆ​ቻ​ቸ​ውን እን​ዳ​ይ​ገ​ርዙ፥ የኦ​ሪ​ት​ንም ሕግ እን​ዳ​ይ​ፈ​ጽሙ እን​ደ​ም​ት​ከ​ለ​ክ​ላ​ቸው ስለ አንተ ነግ​ረ​ዋ​ቸ​ዋል። አሁ​ንሳ ምን ይሁን? ሕዝቡ ወደ​ዚህ እንደ መጣህ ይሰ​ሙና ይሰ​በ​ሰቡ ይሆ​ናል። ስለ​ዚ​ህም ይህን የም​ል​ህን አድ​ርግ፦ ብፅ​ዐት ያላ​ቸው አራት ሰዎች በእኛ ዘንድ አሉ። ይዘ​ሃ​ቸው ሂድ፤ ከእ​ነ​ር​ሱም ጋር ራስ​ህን አንጻ፤ ራሳ​ቸ​ው​ንም እን​ዲ​ላጩ ስለ እነ​ርሱ ገን​ዘብ ክፈ​ል​ላ​ቸው፤ የሚ​ያ​ሙ​ህም በሐ​ሰት እንደ ሆነ፥ አን​ተም የኦ​ሪ​ትን ሕግ እን​ደ​ም​ት​ጠ​ብቅ ሁሉም ያው​ቃሉ። ስለ​ሚ​አ​ም​ኑት አሕ​ዛብ ግን እርም ከሆ​ነ​ውና ለጣ​ዖ​ታት ከሚ​ሠ​ዉት፥ ከዝ​ሙት፥ ሞቶ የተ​ገ​ኘ​ው​ንና ደምን ከመ​ብ​ላት እን​ዲ​ከ​ለ​ከሉ እኛ አዝ​ዘ​ናል።” ያን​ጊ​ዜም ጳው​ሎስ ሰዎ​ችን ይዞ በማ​ግ​ሥቱ ከእ​ነ​ርሱ ጋር ነጻ። የመ​ን​ጻ​ታ​ቸ​ው​ንም ወራት መድ​ረ​ሱን ከነ​ገ​ራ​ቸው በኋላ ሁሉም እየ​አ​ን​ዳ​ን​ዳ​ቸው መሥ​ዋ​ዕት ያቀ​ርቡ ዘንድ ወደ ቤተ መቅ​ደስ ይዞ​አ​ቸው ገባ። በሰ​ባ​ተ​ኛ​ውም ቀን ከእ​ስያ የመጡ አይ​ሁድ ጳው​ሎ​ስን በመ​ቅ​ደስ አዩት፤ ሕዝ​ቡ​ንም ሁሉ በእ​ርሱ ላይ አነ​ሳ​ሥ​ተው ያዙት። እየ​ጮ​ሁም እን​ዲህ አሉ፥ “እና​ንተ የእ​ስ​ራ​ኤል ወገ​ኖች ሆይ፥ ርዱን፤ በየ​ስ​ፍ​ራው ሕዝ​ባ​ች​ንን፥ ኦሪ​ት​ንም፥ ይህ​ንም ስፍራ የሚ​ቃ​ወም ትም​ህ​ርት ለሰው ሁሉ የሚ​ያ​ስ​ተ​ምር እነሆ፥ ይህ ሰው ነው፤ አሁ​ንም አረ​ማ​ው​ያ​ንን ወደ መቅ​ደስ አስ​ገባ፤ ቤተ መቅ​ደ​ስ​ንም አረ​ከሰ። የኤ​ፌ​ሶን ሀገር ሰው የሆነ ጥሮ​ፊ​ሞ​ስን ከጳ​ው​ሎስ ጋር በከ​ተማ አይ​ተ​ውት ነበ​ርና፤ ጳው​ሎ​ስም ወደ ቤተ መቅ​ደስ ያስ​ገ​ባው መስ​ሎ​አ​ቸው ነበ​ርና። ከተ​ማ​ውም ሁሉ ታወከ፤ ሕዝ​ቡም ሁሉ እየ​ሮጡ ሄደው ጳው​ሎ​ስን ጐት​ተው ከቤተ መቅ​ደስ አወ​ጡት፤ በሩ​ንም ሁሉ ዘጉ። ሊገ​ድ​ሉ​ትም ፈል​ገው ብዙ ደበ​ደ​ቡት፤ ወዲ​ያ​ውም ኢየ​ሩ​ሳ​ሌም በመ​ላዋ እንደ ታወ​ከች የሚ​ገ​ልጥ መል​እ​ክት ወደ ሻለ​ቃው ደረ​ሰ​ለት። በዚያ ጊዜም ጭፍ​ሮ​ቹን ከአ​ለ​ቆ​ቻ​ቸው ጋር ይዞ ወደ እነ​ርሱ ሄደ፤ እነ​ር​ሱም የሻ​ለ​ቃ​ውን ጭፍ​ሮች ባዩ ጊዜ ጳው​ሎ​ስን መም​ታ​ታ​ቸ​ውን ተዉ። የሻ​ለ​ቃ​ውም ቀረብ ብሎ ያዘው፤ በሁ​ለት ሰን​ሰ​ለ​ትም እን​ዲ​ታ​ሰር አዘዘ፤ “ምን​ድ​ነው? ምንስ አደ​ረገ?” ብሎም ጠየቀ። ሕዝ​ቡም እኩ​ሌ​ቶቹ እን​ዲህ ነው፤ እኩ​ሌ​ቶ​ቹም እን​ዲህ አይ​ደ​ለም እያሉ ይጮሁ ነበር፤ ሻለ​ቃ​ውም ሕዝቡ የሚ​ታ​ወ​ክ​በ​ትን ርግ​ጡን ማወቅ ተሣ​ነው፤ ወደ ወታ​ደ​ሮ​ቹም ሰፈር እን​ዲ​ወ​ስ​ዱት አዘዘ። ደረ​ጃ​ው​ንም በሚ​ወ​ጣ​በት ጊዜ ወታ​ደ​ሮች ተሸ​ክ​መው አወ​ጡት፤ ሰው ይጋፋ ነበ​ርና። ብዙ​ዎ​ችም ይከ​ተ​ሉት ነበር፤ ሕዝ​ቡም፥ “አስ​ወ​ግ​ዱት” እያሉ ይጮሁ ነበር። ወደ ሰፈ​ርም በደ​ረሰ ጊዜ ጳው​ሎስ ሻለ​ቃ​ውን፥ “ላነ​ጋ​ግ​ርህ ትፈ​ቅ​ድ​ል​ኛ​ለ​ህን?” አለው፤ ሻለ​ቃ​ውም፥ “የጽ​ርዕ ቋንቋ ታው​ቃ​ለ​ህን?” አለው። “ምና​ል​ባት ከዚህ በፊት ወን​ጀል የሠ​ራ​ህና ከነ​ፍሰ ገዳ​ዮች አራት ሺህ ሰዎ​ችን ይዘህ ወደ ምድረ በዳ የወ​ጣህ ያ ግብ​ፃዊ አንተ አይ​ደ​ለ​ህ​ምን?” አለው። ጳው​ሎ​ስም፥ “እኔስ አይ​ሁ​ዳዊ ሰው ነኝ፤ የተ​ወ​ለ​ድ​ሁ​ባ​ትም ሀገር ጠር​ሴስ የታ​ወ​ቀች የቂ​ል​ቅያ ከተማ ናት፤ ለሕ​ዝ​ቡም እን​ድ​ነ​ግ​ራ​ቸው ትፈ​ቅ​ድ​ልኝ ዘንድ እለ​ም​ን​ሃ​ለሁ” አለው። በፈ​ቀ​ደ​ለ​ትም ጊዜ ጳው​ሎስ በደ​ረ​ጃው ላይ ቆሞ እጁን ወደ ሕዝቡ ዘረጋ፤ እጅ​ግም ጸጥታ በሆነ ጊዜ ጳው​ሎስ በዕ​ብ​ራ​ይ​ስጥ ቋንቋ ተና​ገረ፤ እን​ዲ​ህም አለ።

ሐዋርያት ሥራ 21:1-40 አማ54 (መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት))

ከእነርሱም ተለይተን ተነሣን፤ በቀጥታም ሄደን ወደ ቆስ በነገውም ወደ ሩድ ከዚያም ወደ ጳጥራ መጣን፤ ወደ ፊንቄም የሚሻገር መርከብ አግኝተን ገባንና ተነሣን። ቆጵሮስንም ባየናት ጊዜ በስተ ግራችን ተውናት ወደ ሶርያም ሄደን ወደ ጢሮስ ደረስን፥ መርከቡ ሸክሙን በዚያ የሚያራግፍ ነበርና። ደቀ መዛሙርትንም ባገኘን ጊዜ በዚያ ሰባት ቀን ተቀመጥን፤ እነርሱም ጳውሎስን ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይወጣ በመንፈስ አሉት። ጊዜውንም በፈጸምን ጊዜ ወጥተን ሄድን፤ ሁላቸውም ከሚስቶቻቸውና ከልጆቻቸው ጋር እስከ ከተማው ውጭ ድረስ ሸኙን፥ በባሕሩም ዳር ተንበርክከን ጸለይን፤ እርስ በርሳችንም ተሰነባብተን ወደ መርከብ ወጣን፥ እነዚያም ወደ ቤታቸው ተመለሱ። እኛም የባሕሩን መንገድ ጨርሰን ከጢሮስ ወደ አካ ደረስን፥ ለወንድሞችም ሰላምታ ሰጥተን ከእነርሱ ዘንድ አንድ ቀን ተቀመጥን። በነገውም ወጥተን ወደ ቂሣርያ መጣን፥ ከሰባቱም አንድ በሚሆን በወንጌላዊው ፊልጶስ ቤት ገብተን በእርሱ ዘንድ ተቀመጥን። ለእርሱም ትንቢት የሚናገሩ አራት ደናግል ሴቶች ልጆች ነበሩት። አያሌ ቀንም ተቀምጠን ሳለን ነቢይ የነበረ አጋቦስ የሚሉት አንድ ሰው ከይሁዳ ወረደ። ወደ እኛም መጣና የጳውሎስን መታጠቂያ ወስዶ የገዛ እጁንና እግሩን አስሮ፦ እንዲሁ መንፈስ ቅዱስ፦ ይህ መታጠቂያ ያለውን ሰው አይሁድ በኢየሩሳሌም እንደዚህ ያስሩታል በአሕዛብም እጅ አሳልፈው ይሰጡታል ይላል አለ። ይህንም በሰማን ጊዜ እኛም በዚያ የሚኖሩትም ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይወጣ ለመንነው። ጳውሎስ ግን መልሶ፦ እያለቀሳችሁ ልቤንም እየሰበራችሁ ምን ማድረጋችሁ ነው? እኔ ስለ ጌታ ስለ ኢየሱስ ስም በኢየሩሳሌም ለመሞት እንኳ ተሰናድቼአለሁ እንጂ ለእስራት ብቻ አይደለም አለ። ምክርንም ሊቀበል እምቢ ባለ ጊዜ፦ የጌታ ፈቃድ ይሁን ብለን ዝም አልን። ከዚህም ቀን በኋላ ተዘጋጅተን ወደ ኢየሩሳሌም ወጣን። በቂሣርያም ከነበሩ ደቀ መዛሙርት አንዳንዶች ደግሞ ከእኛ ጋር መጡ፥ እነርሱም ወደምናድርበት ወደ ቀደመው ደቀ መዝሙር ወደ ቆጵሮሱ ምናሶን ወደሚሉት ቤት መሩን። ወደ ኢየሩሳሌም በደረስን ጊዜ ወንድሞች በደስታ ተቀበሉን። በነገውም ጳውሎስ ከእኛ ጋር ወደ ያዕቆብ ዘንድ ገባ ሽማግሌዎችም ሁሉ መጡ። ሰላምታም ካቀረበላቸው በኋላ በእርሱ ማገልገል እግዚአብሔር በአሕዛብ መካከል ያደረገውን በእያንዳንዱ ተረከላቸው። እነርሱም በሰሙ ጊዜ እግዚአብሔርን አመሰገኑ አሉትም፦ ወንድም ሆይ፥ በአይሁድ መካከል አምነው የነበሩት ስንት አእላፋት እንደ ሆኑ ታያለህ፤ ሁላቸውም ለሕግ የሚቀኑ ናቸው። ልጆቻቸውንም እንዳይገርዙ በሥርዓትም እንዳይሄዱ ብለህ በአሕዛብ መካከል ያሉት አይሁድ ሁሉ ሙሴን ይክዱ ዘንድ እንድታስተምር ስለ አንተ ነግረዋቸዋል። እንግዲህ ምን ይሁን? የአንተን መምጣት ይሰማሉና ብዙዎች የግድ ሳይሰበሰቡ አይቀሩም። እንግዲህ ይህን የምንልህን አድርግ፤ ስለት ያለባቸው አራት ሰዎች በእኛ ዘንድ አሉ። እነዚህንም ይዘህ ከእነርሱ ጋር ንጻ፥ ራሳቸውንም እንዲላጩ ገንዘብ ክፈልላቸው፤ ሁሉም ስለ አንተ የተማሩት ከንቱ እንደ ሆነና አንተ ራስህ ደግሞ ሕጉን እየጠበቅህ በሥርዓት እንድትመላለስ ያውቃሉ። አምነው ስለ ነበሩ አሕዛብ ግን ለጣዖት ከተሠዋ ከደምም ከታነቀም ከዝሙትም ነፍሳቸውን እንዲጠብቁ ፈርደን እኛ ጽፈንላቸዋል። በዚያን ጊዜ ጳውሎስ ሰዎችን ይዞ በማግሥቱ ከእነርሱ ጋር እየነጻ፥ መንጻታቸውን የሚፈጽሙበትን ቀን አስታውቆ ወደ መቅደስ ገባ። በዚያም ቀን ስለ እያንዳንዳቸው መሥዋዕትን አቀረቡ። ሰባቱ ቀንም ይፈጸም ዘንድ ሲቀርብ ከእስያ የመጡ አይሁድ በመቅደስ አይተውት ሕዝብን ሁሉ አወኩና፦ የእስራኤል ሰዎች ሆይ፥ እርዱን ሕዝብን ሕግንም ይህንም ስፍራ ሲቃወም ሰውን ሁሉ በየስፍራው የሚያስተምረው ሰው ይህ ነው፤ ጨምሮም የግሪክን ሰዎች ደግሞ ወደ መቅደስ አግብቶ ይህን የተቀደሰ ስፍራ አርክሶአል ብለው እየጮኹ እጃቸውን ጫኑበት። በፊት የኤፌሶኑን ጥሮፊሞስን ከእርሱ ጋር በከተማ አይተውት ነበርና ጳውሎስም ወደ መቅደስ ያገባው መስሎአቸው ነው። ከተማውም ሁሉ ታወከ ሕዝቡም ሁሉ ተሰበሰቡ ጳውሎስንም ይዘው ከመቅደስ ውጭ ጎተቱት፥ ወዲያውም ደጆች ተዘጉ። ሊገድሉትም ሲፈልጉ፦ ኢየሩሳሌም ፈጽማ ታወከች የሚል ወሬ ወደ ጭፍራው ሻለቃ ወጣ፤ እርሱም ያን ጊዜ ወታደሮችን ከመቶ አለቆች ጋር ይዞ እየሮጠ ወረደባቸው፤ እነርሱም የሻለቃውንና ወታደሮችን ባዩ ጊዜ ጳውሎስን መምታት ተዉ። በዚያን ጊዜም የሻለቃው ቀርቦ ያዘውና በሁለት ሰንሰለት ይታሰር ዘንድ አዞ ማን እንደ ሆነና ምን እንዳደረገ ጠየቀ። ሕዝቡም እኵሌቶቹ እንዲህ እኵሌቶቹም እንዲያ እያሉ ይጮኹ ነበር፤ ስለ ጫጫታውም እርግጡን ማወቅ ባልተቻለ ጊዜ፥ ወደ ወታደሮች ሰፈር ይወስዱት ዘንድ አዘዘ። ወደ ደረጃውም በደረሰ ጊዜ ስለ ሕዝቡ ግፊያ ወታደሮች እንዲሸከሙት ሆነ፤ ብዙ ሕዝብ፦ አስወግደው እያሉና እየጮኹ ይከተሉ ነበርና። ወደ ሰፈርም ሊያገቡት በቀረቡ ጊዜ፥ ጳውሎስ የሻለቃውን፦ አንድ ነገር ብነግርህ ትፈቅዳለህን? አለው። እርሱም፦ የግሪክ ቋንቋ ታውቃለህን? አንተ ከዚህ ዘመን አስቀድሞ ከነፍሰ ገዳዮቹ አራቱን ሺህ ሰዎች አሸፍተህ ወደ ምድረ በዳ ያወጣህ የግብፅ ሰው አይደለህምን? አለ። ጳውሎስ ግን፦ እኔስ አይሁዳዊ በኪልቅያ ያለው የጠርሴስ ሰው ሆኜ ስመ ጥር በሆነ ከተማ የምኖር ነኝ፤ ለሕዝቡ እናገር ዘንድ እንድትፈቅድልኝ እለምንሃለሁ አለ። በፈቀደለትም ጊዜ ጳውሎስ በደረጃው ላይ ቆሞ በእጁ ወደ ሕዝቡ ጠቀሰ እጅግም ጸጥታ በሆነ ጊዜ በዕብራይስጥ ቋንቋ እየተናገረ እንዲህ አለ።

ሐዋርያት ሥራ 21:1-40 መቅካእኤ (መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ))

ከእነርሱም ተለይተን ተነሣን፤ በቀጥታም ሄደን ወደ ቆስ በነገውም ወደ ሩድ ከዚያም ወደ ጳጥራ መጣን፤ ወደ ፊንቄም የሚሻገር መርከብ አግኝተን ገባንና ተነሣን። ቆጵሮስንም ባየናት ጊዜ በስተ ግራችን ተውናት፤ ወደ ሶርያም ሄደን ወደ ጢሮስ ደረስን፤ መርከቡ ሸክሙን በዚያ የሚያራግፍ ነበርና። ደቀ መዛሙርትንም ባገኘን ጊዜ በዚያ ሰባት ቀን ተቀመጥን፤ እነርሱም ጳውሎስን ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይወጣ በመንፈስ ተመርተው ነገሩት። ጊዜውንም በፈጸምን ጊዜ ወጥተን ሄድን፤ ሁላቸውም ከሚስቶቻቸውና ከልጆቻቸው ጋር እስከ ከተማው ውጭ ድረስ ሸኙን፤ በባሕሩም ዳር ተንበርክከን ጸለይን፤ እርስ በርሳችንምተሰነባብተን ወደ መርከብ ወጣን፤ እነዚያም ወደ ቤታቸው ተመለሱ። እኛም የባሕሩን መንገድ ጨርሰን ከጢሮስ ወደ አካ ደረስን፤ ለወንድሞችም ሰላምታ ሰጥተን ከእነርሱ ዘንድ አንድ ቀን ተቀመጥን። በነገውም ወጥተን ወደ ቂሣርያ መጣን፤ ከሰባቱም አንድ በሚሆን በወንጌላዊው ፊልጶስ ቤት ገብተን በእርሱ ዘንድ ተቀመጥን። ለእርሱም ትንቢት የሚናገሩ አራት ደናግል ሴቶች ልጆች ነበሩት። አያሌ ቀንም ተቀምጠን ሳለን ነቢይ የነበረ አጋቦስ የሚሉት አንድ ሰው ከይሁዳ ወረደ። ወደ እኛም መጣና የጳውሎስን መታጠቂያ ወስዶ የገዛ እጁንና እግሩን አስሮ “እንዲሁ መንፈስ ቅዱስ ‘ይህ መታጠቂያ ያለውን ሰው አይሁድ በኢየሩሳሌም እንደዚህ ያስሩታል፤ በአሕዛብም እጅ አሳልፈው ይሰጡታል፤’ ይላል፤” አለ። ይህንም በሰማን ጊዜ እኛም በዚያ የሚኖሩትም ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይወጣ ለመንነው። ጳውሎስ ግን መልሶ “እያለቀሳችሁ ልቤንም እየሰበራችሁ ምን ማድረጋችሁ ነው? እኔ ስለ ጌታ ስለ ኢየሱስ ስም በኢየሩሳሌም ለመሞት እንኳ ተሰናድቼአለሁ እንጂ ለእስራት ብቻ አይደለም፤” አለ። ምክርንም ሊቀበል እምቢ ባለ ጊዜ “የጌታ ፈቃድ ይሁን፤” ብለን ዝም አልን። ከዚህም ቀን በኋላ ተዘጋጅተን ወደ ኢየሩሳሌም ወጣን። በቂሣርያም ከነበሩ ደቀ መዛሙርት አንዳንዶች ደግሞ ከእኛ ጋር መጡ፤ እነርሱም ወደምናድርበት ወደ ቀደመው ደቀመዝሙር ወደ ቆጵሮሱ ምናሶን ወደሚሉት ቤት መሩን። ወደ ኢየሩሳሌም በደረስን ጊዜ ወንድሞች በደስታ ተቀበሉን። በነገውም ጳውሎስ ከእኛ ጋር ወደ ያዕቆብ ዘንድ ገባ፤ ሽማግሌዎችም ሁሉ መጡ። ሰላምታም ካቀረበላቸው በኋላ በእርሱ ማገልገል እግዚአብሔር በአሕዛብ መካከል ያደረገውን በእያንዳንዱ ተረከላቸው። እነርሱም በሰሙ ጊዜ እግዚአብሔርን አመሰገኑ፤ አሉትም “ወንድም ሆይ! በአይሁድ መካከል አምነው የነበሩት ስንት አእላፋት እንደ ሆኑ ታያለህ፤ ሁላቸውም ለሕግ የሚቀኑ ናቸው። ልጆቻቸውንም እንዳይገርዙ በሥርዓትም እንዳይሄዱ ብለህ በአሕዛብ መካከል ያሉት አይሁድ ሁሉ ሙሴን ይክዱ ዘንድ እንድታስተምር ስለ አንተ ነግረዋቸዋል። እንግዲህ ምን ይሁን? የአንተን መምጣት ይሰማሉና ብዙዎች የግድ ሳይሰበሰቡ አይቀሩም። እንግዲህ ይህን የምንልህን አድርግ፤ ስለት ያለባቸው አራት ሰዎች በእኛ ዘንድ አሉ። እነዚህንም ይዘህ ከእነርሱ ጋር ንጻ፤ ራሳቸውንም እንዲላጩ ገንዘብ ክፈልላቸው፤ ሁሉም ስለ አንተ የተማሩት ከንቱ እንደ ሆነና አንተ ራስህ ደግሞ ሕጉን እየጠበቅህ በሥርዓት እንድትመላለስ ያውቃሉ። አምነው ስለ ነበሩ አሕዛብ ግን ለጣዖት ከተሠዋ ከደምም ከታነቀም ከዝሙትም ነፍሳቸውን እንዲጠብቁ ፈርደን እኛ ጽፈንላቸዋል።” በዚያን ጊዜ ጳውሎስ ሰዎችን ይዞ በማግሥቱ ከእነርሱ ጋር እየነጻ፥ መንጻታቸውን የሚፈጽሙበትን ቀን አስታውቆ ወደ መቅደስ ገባ። በዚያም ቀን ስለ እያንዳንዳቸው መሥዋዕትን አቀረቡ። ሰባቱ ቀንም ይፈጸም ዘንድ ሲቀርብ ከእስያ የመጡ አይሁድ በመቅደስ አይተውት ሕዝብን ሁሉ አወኩና “የእስራኤል ሰዎች ሆይ! እርዱን፤ ሕዝብን ሕግንም ይህንም ስፍራ ሲቃወም ሰውን ሁሉ በየስፍራው የሚያስተምረው ሰው ይህ ነው፤ ጨምሮም የግሪክን ሰዎች ደግሞ ወደ መቅደስ አግብቶ ይህን የተቀደሰ ስፍራ አርክሶአል፤” ብለው እየጮኹ እጃቸውን ጫኑበት። በፊት የኤፌሶኑን ጥሮፊሞስን ከእርሱ ጋር በከተማ አይተውት ነበርና ጳውሎስም ወደ መቅደስ ያገባው መስሎአቸው ነው። ከተማውም ሁሉ ታወከ፤ ሕዝቡም ሁሉ ተሰበሰቡ ጳውሎስንም ይዘው ከመቅደስ ውጭ ጎተቱት፤ ወዲያውም ደጆች ተዘጉ። ሊገድሉትም ሲፈልጉ “ኢየሩሳሌም ፈጽማ ታወከች፤” የሚል ወሬ ወደ ጭፍራው ሻለቃ ወጣ፤ እርሱም ያንጊዜ ወታደሮችን ከመቶ አለቆች ጋር ይዞ እየሮጠ ወደ እነርሱ ወረደ፤ እነርሱም የሻለቃውንና ወታደሮችን ባዩ ጊዜ ጳውሎስን መምታት ተዉ። በዚያን ጊዜም የሻለቃው ቀርቦ ያዘውና በሁለት ሰንሰለት ይታሰር ዘንድ አዞ ማን እንደ ሆነና ምን እንዳደረገ ጠየቀ። ሕዝቡም እኩሌቶቹ እንዲህ እኩሌቶቹም እንዲያ እያሉ ይጮኹ ነበር፤ ስለ ጫጫታውም እርግጡን ማወቅ ባልተቻለ ጊዜ፥ ወደ ወታደሮች ሰፈር ይወስዱት ዘንድ አዘዘ። ወደ ደረጃውም በደረሰ ጊዜ ስለ ሕዝቡ ግፊያ ወታደሮች እንዲሸከሙት ሆነ፤ ብዙ ሕዝብ “አስወግደው!” እያሉና እየጮኹ ይከተሉ ነበርና። ወደ ሰፈርም ሊያገቡት በቀረቡ ጊዜ፥ ጳውሎስ የሻለቃውን “አንድ ነገር ብነግርህ ትፈቅዳለህን?” አለው። እርሱም “የግሪክ ቋንቋ ታውቃለህን? አንተ ከዚህ ዘመን አስቀድሞ ከነፍሰ ገዳዮቹ አራቱን ሺህ ሰዎች አሸፍተህ ወደ ምድረ በዳ ያወጣህ የግብጽ ሰው አይደለህምን?” አለ። ጳውሎስ ግን “እኔስ አይሁዳዊ በኪልቅያ ያለው የጠርሴስ ሰው ሆኜ ስመ ጥር በሆነ ከተማ የምኖር ነኝ፤ ለሕዝቡ እናገር ዘንድ እንድትፈቅድልኝ እለምንሃለሁ፤” አለ። በፈቀደለትም ጊዜ ጳውሎስ በደረጃው ላይ ቆሞ በእጁ ወደ ሕዝቡ ጠቀሰ፤ እጅግም ጸጥታ በሆነ ጊዜ በዕብራይስጥ ቋንቋ እየተናገረ እንዲህ አለ።