ሐዋርያት ሥራ 21:1-26 - Compare All Versions
ሐዋርያት ሥራ 21:1-26 አማ2000 (የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ))
ከእነርሱም ከተለየን በኋላ እኛ በመርከብ ተሳፍረን፥ መንገዳችንንም አቅንተን ወደ ቆስ መጣን፤ በበነጋውም ወደ ሮዶስ፥ ከዚያም ወደ ጳጥራ ገባን። ወደ ፊንቄም የሚያልፍ መርከብ አግኝተን በዚያ ላይ ተሳፍረን ሄድን። ቆጵሮስንም አየናት፤ በስተ ግራችንም ትተናት ወደ ሶርያ ሄድን፤ ወደ ጢሮስም ወረድን፤ በመርከብ ያለውን ጭነት ሁሉ በዚያ ያራግፉ ነበርና። በዚያም ደቀ መዛሙርትን አገኘንና በእነርሱ ዘንድ ሰባት ቀን ተቀመጥን፤ እነርሱም በመንፈስ ቅዱስ ተገልጾላቸው ጳውሎስን ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይወጣ ነገሩት። ከዚህም በኋላ ለመሄድ ወጣን፤ ሁሉም ከሚስቶቻቸውና ከልጆቻቸው ጋር እስከ ከተማው ውጭ ሸኙን፤ በባሕሩም ዳር ተንበርክከን ጸለይን። እርስ በርሳችንም ተሳስመን ተሰነባበትን፤ ከዚህም በኋላ ወደ መርከብ ወጣን፤ እነርሱም ወደ ቤታቸው ተመለሱ። እኛም ከጢሮስ ወጥተን አካ ወደምትባል ሀገር መጣን፤ ወንድሞቻችንንም አግኝተን ሰላም አልናቸው፤ በእነርሱም ዘንድ አንድ ቀን አደርን። በማግሥቱም ወጥተን ወደ ቂሳርያ ሄድን፤ ወደ ወንጌላዊው ወደ ፊልጶስ ቤትም ገባን፤ እርሱም ከሰባቱ ወንድሞች ዲያቆናት አንዱ ነው። ለእርሱም ትንቢት የሚናገሩ አራት ደናግል ሴቶች ልጆች ነበሩት። በእርሱም ዘንድ ብዙ ቀን ኖርን፤ ከይሁዳም አጋቦስ የሚባል አንድ ነቢይ ወረደ። ወደ እኛም መጣና የጳውሎስን መታጠቂያ አንሥቶ እጁንና እግሩን በገዛ እጁ አስሮ እንዲህ አለ፥ “መንፈስ ቅዱስ እንዲህ ይላል፤ የዚህን መታጠቂያ ጌታ አይሁድ በኢየሩሳሌም እንዲህ ያስሩታል፤ ለአሕዛብም አሳልፈው ይሰጡታል።” ይህንም ሰምተን የሀገሪቱን ሰዎች ይዘን ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይወጣ ጳውሎስን ማለድነው። ጳውሎስ ግን መልሶ፥ “ለምን እንዲህ ታደርጋላችሁ? እያለቀሳችሁ ልቤን ትሰብሩታላችሁ፤ እኔ እኮ ተስፋ የማደርገው መከራንና እግር ብረትን ብቻ አይደለም፤ እኔ ግን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በኢየሩሳሌም ለመሞትም ቢሆን የቈረጥሁ ነኝ” አለ። እንቢ ባለ ጊዜም ዝም አልን፤ እኛም እግዚአብሔር የፈቀደው ይሁን ብለን ተውነው። ከእነዚያም ቀኖች በኋላ ተዘጋጅተን ወደ ኢየሩሳሌም ወጣን። ከደቀ መዛሙርትም ከቂሳርያ አብረውን የመጡ ነበሩ፤ ሄደንም ከመጀመሪያዎቹ ደቀ መዛሙርት ወገን ከሆነው በቆጵሮስ በሚኖረው በምናሶን ቤት አደርን። ኢየሩሳሌም በደረስን ጊዜም ወንድሞቻችን በደስታ ተቀበሉን። በማግሥቱም ጳውሎስ ከእኛ ጋር ወደ ያዕቆብ ገባ፤ ቀሳውስትም ሁሉ በዚያ ነበሩ። ጳውሎስም ሰላምታ ካቀረበላቸው በኋላ በእርሱ ሐዋርያነት እግዚአብሔር በአሕዛብ ያደረገውን ሁሉ ነገራቸው። እነርሱም ሰምተው እግዚአብሔርን አመሰገኑ፤ እንዲህም አሉ፥ “ወንድማችን ሆይ፥ ከአይሁድ መካከል ያመኑት ስንት አእላፋት እንደ ሆኑ ታያለህን? ሁሉም ለኦሪት የሚቀኑ ናቸው። ነገር ግን የማይሆነውን እንደምታስተምር፥ የሙሴንም ሕግ እንደምታስተዋቸው፥ በአሕዛብ መካከል ያሉ ያመኑ አይሁድንም ልጆቻቸውን እንዳይገርዙ፥ የኦሪትንም ሕግ እንዳይፈጽሙ እንደምትከለክላቸው ስለ አንተ ነግረዋቸዋል። አሁንሳ ምን ይሁን? ሕዝቡ ወደዚህ እንደ መጣህ ይሰሙና ይሰበሰቡ ይሆናል። ስለዚህም ይህን የምልህን አድርግ፦ ብፅዐት ያላቸው አራት ሰዎች በእኛ ዘንድ አሉ። ይዘሃቸው ሂድ፤ ከእነርሱም ጋር ራስህን አንጻ፤ ራሳቸውንም እንዲላጩ ስለ እነርሱ ገንዘብ ክፈልላቸው፤ የሚያሙህም በሐሰት እንደ ሆነ፥ አንተም የኦሪትን ሕግ እንደምትጠብቅ ሁሉም ያውቃሉ። ስለሚአምኑት አሕዛብ ግን እርም ከሆነውና ለጣዖታት ከሚሠዉት፥ ከዝሙት፥ ሞቶ የተገኘውንና ደምን ከመብላት እንዲከለከሉ እኛ አዝዘናል።” ያንጊዜም ጳውሎስ ሰዎችን ይዞ በማግሥቱ ከእነርሱ ጋር ነጻ። የመንጻታቸውንም ወራት መድረሱን ከነገራቸው በኋላ ሁሉም እየአንዳንዳቸው መሥዋዕት ያቀርቡ ዘንድ ወደ ቤተ መቅደስ ይዞአቸው ገባ።
ሐዋርያት ሥራ 21:1-26 NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
ከእነርሱ ከተለየን በኋላ ቀጥታ በመርከብ ወደ ቆስ ተጓዝን፤ በማግስቱም ወደ ሩድ፣ ከዚያም ወደ ጳጥራ አመራን። በዚያም ወደ ፊንቄ የሚሄድ መርከብ ስላገኘን፣ ተሳፍረን ጕዟችንን ቀጠልን። ቆጵሮስ በታየችን ጊዜ፣ ወደ ግራ ትተናት ዐለፍንና ወደ ሶርያ አመራን፤ መርከባችን ጭነቱን በጢሮስ ማራገፍ ስለ ነበረበት እኛም እዚያው ወረድን። ደቀ መዛሙርትንም በዚያ አግኝተን፣ ሰባት ቀን ከእነርሱ ጋራ ተቀመጥን። እነርሱም በመንፈስ ሆነው ጳውሎስ ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይሄድ ነገሩት። የቈይታ ጊዜያችን ባለቀ ጊዜ፣ ትተናቸው ጕዟችንን ቀጠልን፤ ደቀ መዛሙርቱም ሁሉ ከሚስቶቻቸውና ከልጆቻቸው ጋራ እስከ ከተማው ውጭ ድረስ ሸኙን፤ በባሕሩም ዳር ተንበርክከን ጸለይን፤ ከተሰነባበትንም በኋላ እኛ ወደ መርከቡ ገባን፤ እነርሱም ወደ ቤታቸው ተመለሱ። ከጢሮስ ተነሥተን ጕዟችንን በመቀጠል ጴጤሌማይስ ደረስን፤ ከመርከብ ወርደንም ለወንድሞች ሰላምታ ካቀረብን በኋላ፣ አንድ ቀን ከእነርሱ ጋራ ቈየን። በማግስቱም ከዚያ ተነሥተን ቂሳርያ ደረስን፤ ከሰባቱ ወንጌላውያን አንዱ በሆነው በፊልጶስ ቤትም ዐረፍን። እርሱም ትንቢት የሚናገሩ አራት ደናግል ሴቶች ልጆች ነበሩት። በዚያም ብዙ ቀን ከተቀመጥን በኋላ አጋቦስ የተባለ ነቢይ ከይሁዳ ወረደ፤ ወደ እኛም መጣና የጳውሎስን መታጠቂያ ወሰደ፤ የራሱንም እጅና እግር በማሰር፣ “መንፈስ ቅዱስ፣ ‘በኢየሩሳሌም ያሉ አይሁድ የዚህን መታጠቂያ ባለቤት እንዲህ አድርገው በማሰር ለአሕዛብ አሳልፈው ይሰጡታል’ ይላል” አለ። ይህን ስንሰማ እኛና በዚያም የሚኖሩት ጳውሎስ ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይሄድ ለመንነው። ጳውሎስ ግን፣ “ለምን እንዲህ እያለቀሳችሁ ልቤን ታባቡታላችሁ? እኔ መታሰር ቀርቶ ስለ ጌታ ኢየሱስ ስም በኢየሩሳሌም ለመሞት እንኳ ዝግጁ ነኝ” አላቸው። ምክራችንን አልቀበል ስላለን፣ “እንግዲህ የጌታ ፈቃድ ይሁን” ብለን ተውነው። ከዚህ በኋላ፣ ተዘጋጅተን ወደ ኢየሩሳሌም ወጣን። በቂሳርያ ከነበሩት ደቀ መዛሙርትም አንዳንዶቹ ወደ ምናሶን ቤት ይዘውን መጡ፤ እኛም በዚያው ተቀመጥን። ምናሶን የቆጵሮስ ሰው ሲሆን፣ ከመጀመሪያዎቹ ደቀ መዛሙርት አንዱ ነበረ። ኢየሩሳሌም በደረስን ጊዜ ወንድሞች በደስታ ተቀበሉን። በማግስቱም ጳውሎስና ሌሎቻችንም ያዕቆብን ለማየት ሄድን፤ ሽማግሌዎችም ሁሉ በዚያ ነበሩ። ጳውሎስም ሰላምታ ካቀረበላቸው በኋላ፣ እግዚአብሔር በርሱ አገልግሎት አማካይነት በአሕዛብ መካከል ያደረገውን ሁሉ በዝርዝር አስረዳቸው። እነርሱም ይህን ሲሰሙ፣ እግዚአብሔርን አመሰገኑ፤ ጳውሎስንም እንዲህ አሉት፤ “ወንድም ሆይ፤ በብዙ ሺሕ የሚቈጠሩ አይሁድ እንዳመኑ ተመልከት፤ ሁሉም ደግሞ ለሙሴ ሕግ የሚቀኑ ናቸው። በአሕዛብ መካከል የሚኖሩ አይሁድ ሁሉ ሙሴን እንዲተዉና ልጆቻቸውን እንዳይገርዙ፣ በቈየው ልማዳችን መሠረት እንዳይኖሩ እንደምታስተምር ስለ አንተ ተነግሯቸዋል። መምጣትህን መስማታቸው የማይቀር ነውና እንግዲህ ምን እናድርግ? ስለዚህ የምንልህን አድርግ። ስእለት ያለባቸው አራት ሰዎች በእኛ ዘንድ አሉ፤ እነዚህን ሰዎች ይዘህ ከእነርሱ ጋራ የመንጻቱን ሥርዐት ፈጽም፤ ራሳቸውንም እንዲላጩ የሚጠየቀውን ገንዘቡን ክፈልላቸው፤ በዚህም ስለ አንተ የተነገራቸው ሰዎች ሁሉ የሰሙት እውነት እንዳልሆነና አንተ ራስህ ሕጉን ጠብቀህ የምትኖር መሆንህን ያውቃሉ። ከአሕዛብ ወገን ያመኑትን በተመለከተ ግን ለጣዖት የተሠዋ ምግብ፣ ደምና ታንቆ የሞተ እንስሳ ሥጋ እንዳይበሉ፣ ደግሞም ከዝሙት ርኩሰት ራሳቸውን እንዲጠብቁ ወስነን ጽፈንላቸዋል።” ጳውሎስም በማግስቱም ሰዎቹን ይዞ ሄደ፤ ዐብሯቸውም የመንጻቱን ሥርዐት ፈጸመ። ከዚያም የመንጻቱ ሥርዐት መቼ እንደሚያበቃና የእያንዳንዳቸውም መሥዋዕት መቼ እንደሚቀርብ ለማስታወቅ ወደ ቤተ መቅደስ ገባ።
ሐዋርያት ሥራ 21:1-26 አማ54 (መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት))
ከእነርሱም ተለይተን ተነሣን፤ በቀጥታም ሄደን ወደ ቆስ በነገውም ወደ ሩድ ከዚያም ወደ ጳጥራ መጣን፤ ወደ ፊንቄም የሚሻገር መርከብ አግኝተን ገባንና ተነሣን። ቆጵሮስንም ባየናት ጊዜ በስተ ግራችን ተውናት ወደ ሶርያም ሄደን ወደ ጢሮስ ደረስን፥ መርከቡ ሸክሙን በዚያ የሚያራግፍ ነበርና። ደቀ መዛሙርትንም ባገኘን ጊዜ በዚያ ሰባት ቀን ተቀመጥን፤ እነርሱም ጳውሎስን ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይወጣ በመንፈስ አሉት። ጊዜውንም በፈጸምን ጊዜ ወጥተን ሄድን፤ ሁላቸውም ከሚስቶቻቸውና ከልጆቻቸው ጋር እስከ ከተማው ውጭ ድረስ ሸኙን፥ በባሕሩም ዳር ተንበርክከን ጸለይን፤ እርስ በርሳችንም ተሰነባብተን ወደ መርከብ ወጣን፥ እነዚያም ወደ ቤታቸው ተመለሱ። እኛም የባሕሩን መንገድ ጨርሰን ከጢሮስ ወደ አካ ደረስን፥ ለወንድሞችም ሰላምታ ሰጥተን ከእነርሱ ዘንድ አንድ ቀን ተቀመጥን። በነገውም ወጥተን ወደ ቂሣርያ መጣን፥ ከሰባቱም አንድ በሚሆን በወንጌላዊው ፊልጶስ ቤት ገብተን በእርሱ ዘንድ ተቀመጥን። ለእርሱም ትንቢት የሚናገሩ አራት ደናግል ሴቶች ልጆች ነበሩት። አያሌ ቀንም ተቀምጠን ሳለን ነቢይ የነበረ አጋቦስ የሚሉት አንድ ሰው ከይሁዳ ወረደ። ወደ እኛም መጣና የጳውሎስን መታጠቂያ ወስዶ የገዛ እጁንና እግሩን አስሮ፦ እንዲሁ መንፈስ ቅዱስ፦ ይህ መታጠቂያ ያለውን ሰው አይሁድ በኢየሩሳሌም እንደዚህ ያስሩታል በአሕዛብም እጅ አሳልፈው ይሰጡታል ይላል አለ። ይህንም በሰማን ጊዜ እኛም በዚያ የሚኖሩትም ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይወጣ ለመንነው። ጳውሎስ ግን መልሶ፦ እያለቀሳችሁ ልቤንም እየሰበራችሁ ምን ማድረጋችሁ ነው? እኔ ስለ ጌታ ስለ ኢየሱስ ስም በኢየሩሳሌም ለመሞት እንኳ ተሰናድቼአለሁ እንጂ ለእስራት ብቻ አይደለም አለ። ምክርንም ሊቀበል እምቢ ባለ ጊዜ፦ የጌታ ፈቃድ ይሁን ብለን ዝም አልን። ከዚህም ቀን በኋላ ተዘጋጅተን ወደ ኢየሩሳሌም ወጣን። በቂሣርያም ከነበሩ ደቀ መዛሙርት አንዳንዶች ደግሞ ከእኛ ጋር መጡ፥ እነርሱም ወደምናድርበት ወደ ቀደመው ደቀ መዝሙር ወደ ቆጵሮሱ ምናሶን ወደሚሉት ቤት መሩን። ወደ ኢየሩሳሌም በደረስን ጊዜ ወንድሞች በደስታ ተቀበሉን። በነገውም ጳውሎስ ከእኛ ጋር ወደ ያዕቆብ ዘንድ ገባ ሽማግሌዎችም ሁሉ መጡ። ሰላምታም ካቀረበላቸው በኋላ በእርሱ ማገልገል እግዚአብሔር በአሕዛብ መካከል ያደረገውን በእያንዳንዱ ተረከላቸው። እነርሱም በሰሙ ጊዜ እግዚአብሔርን አመሰገኑ አሉትም፦ ወንድም ሆይ፥ በአይሁድ መካከል አምነው የነበሩት ስንት አእላፋት እንደ ሆኑ ታያለህ፤ ሁላቸውም ለሕግ የሚቀኑ ናቸው። ልጆቻቸውንም እንዳይገርዙ በሥርዓትም እንዳይሄዱ ብለህ በአሕዛብ መካከል ያሉት አይሁድ ሁሉ ሙሴን ይክዱ ዘንድ እንድታስተምር ስለ አንተ ነግረዋቸዋል። እንግዲህ ምን ይሁን? የአንተን መምጣት ይሰማሉና ብዙዎች የግድ ሳይሰበሰቡ አይቀሩም። እንግዲህ ይህን የምንልህን አድርግ፤ ስለት ያለባቸው አራት ሰዎች በእኛ ዘንድ አሉ። እነዚህንም ይዘህ ከእነርሱ ጋር ንጻ፥ ራሳቸውንም እንዲላጩ ገንዘብ ክፈልላቸው፤ ሁሉም ስለ አንተ የተማሩት ከንቱ እንደ ሆነና አንተ ራስህ ደግሞ ሕጉን እየጠበቅህ በሥርዓት እንድትመላለስ ያውቃሉ። አምነው ስለ ነበሩ አሕዛብ ግን ለጣዖት ከተሠዋ ከደምም ከታነቀም ከዝሙትም ነፍሳቸውን እንዲጠብቁ ፈርደን እኛ ጽፈንላቸዋል። በዚያን ጊዜ ጳውሎስ ሰዎችን ይዞ በማግሥቱ ከእነርሱ ጋር እየነጻ፥ መንጻታቸውን የሚፈጽሙበትን ቀን አስታውቆ ወደ መቅደስ ገባ። በዚያም ቀን ስለ እያንዳንዳቸው መሥዋዕትን አቀረቡ።
ሐዋርያት ሥራ 21:1-26 አማ05 (አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም)
ከእነርሱ ከተለየን በኋላ በመርከብ ተሳፈርንና በቀጥታ ቆስ ወደምትባል ደሴት ሄድን፤ በማግስቱም ወደ ሩድ ደሴት ደረስን፤ ከዚያም ወደ ጳጥራ ከተማ ሄድን። እዚያም ወደ ፊንቄ አገር የምትሄድ መርከብ አገኘንና በእርስዋ ተሳፍረን፤ ጒዞአችንን ቀጠልን። የቆጵሮስን ደሴት በስተግራችን ትተን ወደ ሶርያ አገር ተጓዝንና ወደ ጢሮስ ወደብ ሄድን፤ መርከቡ ጭነቱን እዚያ ማራገፍ ነበረበት። እዚያ ምእመናንን ፈልገን አገኘንና ከእነርሱ ጋር ሰባት ቀን ቈየን። እነርሱም በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው ጳውሎስን “ወደ ኢየሩሳሌም አትሂድ” ብለው ነገሩት። እዚያ የምንቈይበት ጊዜ ሲያልቅ ተለይተናቸው ጒዞአችንን ቀጠልን፤ ሁሉም ከሚስቶቻቸውና ከልጆቻቸው ጋር ሆነው እስከ ከተማው ውጪ ድረስ ሸኙን፤ በባሕሩም ዳር ተንበርክከን ከጸለይን በኋላ ተሰነባበትን። ከዚህ በኋላ እኛ በመርከብ ስንሳፈር እነርሱ ወደ ቤታቸው ተመለሱ። ከጢሮስ ተነሥተን ወደ ጴጤሌማይስ ደረስን፤ እዚያ ከአማኞች ጋር ተገናኝተን ሰላምታ ከተለዋወጥን በኋላ ከእነርሱ ጋር አንድ ቀን አሳለፍን። በማግስቱ ከዚያ ወጥተን ወደ ቂሳርያ ሄድን፤ እዚያ ከሰባቱ ዲያቆናት አንዱ ወደ ሆነው ወደ ወንጌላዊው ፊልጶስ ቤት ገባንና ከእርሱ ጋር ተቀመጥን። እርሱ ትንቢት የመናገር ስጦታ ያላቸው አራት ያላገቡ ሴቶች ልጆች ነበሩት። ለብዙ ቀኖች እዚያ በተቀመጥንበት ጊዜ አጋቦስ የሚባል ነቢይ ከይሁዳ ምድር መጣ። ይህ ነቢይ ወደ እኛ ቀረበ፤ የጳውሎስን መታጠቂያ ወስዶ የገዛ እጆቹንና እግሮቹን አሰረና “መንፈስ ቅዱስ የዚህን መታጠቂያ ባለቤት በኢየሩሳሌም ያሉ አይሁድ እንደዚህ አስረው ለአሕዛብ አሳልፈው ይሰጡታል ይላል” አለ። ይህንን በሰማን ጊዜ እኛም እዚያ የነበሩ ሰዎችም ጳውሎስ ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይሄድ ለመንነው። ጳውሎስ ግን “እንደዚህ እያለቀሳችሁ ስለምን ልቤን በሐዘን ትሰብሩታላችሁ? እኔ ስለ ጌታ ኢየሱስ ስም በኢየሩሳሌም ለመታሰር ብቻ ሳይሆን ለመሞትም ዝግጁ ነኝ” ሲል መለሰ። ምክራችንን አልቀበልም ባለን ጊዜ “እንግዲህ የጌታ ፈቃድ ይሁን” ብለን ተውነው። እዚያ ጥቂት ቀኖች ከቈየን በኋላ ዕቃችንን አዘጋጅተን ወደ ኢየሩሳሌም ሄድን። በቂሳርያ የነበሩ አንዳንድ ምእመናን አብረውን መጡ፤ እነርሱም በምናሶን ቤት እንድናርፍ ወደ እርሱ ቤት መሩን፤ ይህ ሰው ቀደም ብሎ ያመነ፥ የቆጵሮስ ተወላጅ ነበር። ኢየሩሳሌም በደረስን ጊዜ ምእመናን በደስታ ተቀበሉን። በማግስቱ ጳውሎስ ከእኛ ጋር ወደ ያዕቆብ ሄደ፤ የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ሁሉ እዚያ ነበሩ። ጳውሎስ ለሁሉም ሰላምታ ከሰጠ በኋላ በእርሱ አማካይነት እግዚአብሔር በአሕዛብ መካከል ያደረገውን ሁሉ አንድ በአንድ ተረከላቸው። ይህን በሰሙ ጊዜ ሁሉም ጌታን አመሰገኑ፤ ጳውሎስንም እንዲህ አሉት፦ “ወንድም ሆይ! በብዙ ሺህ የሚቈጠሩ ምእመናን በአይሁድ መካከል እንዳሉና ሁሉም ለሕግ ቀናተኞች እንደ ሆኑ ታውቃለህ፤ አንተ በአሕዛብ መካከል የሚኖሩትን አይሁድ ሁሉ ‘ልጆቻችሁን አትግረዙ ወይም ሥርዓቶችን አትፈጽሙ’ እያልክ በማስተማር የሙሴን ሕግ እንዲሽሩ ታደርጋለህ እየተባለ የሚወራውን ሰምተዋል። እንግዲህ ምን ማድረግ ይሻላል? መምጣትህን በእርግጥ ይሰማሉ፤ ስለዚህ እኛ የምንልህን አድርግ፤ በእኛ መካከል ስለት ያለባቸው አራት ሰዎች አሉ። እነርሱን ውሰድና ከእነርሱ ጋር ሆነህ ራስህን አንጻ፤ ጠጒራቸውንም እንዲላጩ ለቤተ መቅደስ የሚሰጠውን የመባ ገንዘብ ክፈልላቸው፤ ይህን ብታደርግ በአንተ ላይ የተወራው ሁሉ ከንቱ መሆኑንና አንተም ራስህ ለሕግ ታዛዥ መሆንክህን ሁሉም ያውቃሉ። ከአሕዛብ ወገን ያመኑት ግን ‘ለጣዖት በመሠዋቱ ምክንያት የረከሰ ምግብ አትብሉ፤ ደምም አትብሉ፤ ታንቆ የሞተ እንስሳ ሥጋ አትብሉ፤ ከዝሙት ራቁ’ የሚለውን ውሳኔ የያዘ ደብዳቤ ጽፈን ልከንላቸዋል።” ከዚህ በኋላ ጳውሎስ ሰዎቹን ወሰደና በማግስቱ ከእነርሱ ጋር ራሱን አነጻ፤ የሚነጹባቸው ቀኖች መቼ እንደሚሆንና ስለ እያንዳንዱም የሚሰጠው የመባ ገንዘብ የሚከፈልበት ጊዜ መቼ እንደሚሆን ለማስታወቅ ወደ ቤተ መቅደስ ገባ።
ሐዋርያት ሥራ 21:1-26 መቅካእኤ (መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ))
ከእነርሱም ተለይተን ተነሣን፤ በቀጥታም ሄደን ወደ ቆስ በነገውም ወደ ሩድ ከዚያም ወደ ጳጥራ መጣን፤ ወደ ፊንቄም የሚሻገር መርከብ አግኝተን ገባንና ተነሣን። ቆጵሮስንም ባየናት ጊዜ በስተ ግራችን ተውናት፤ ወደ ሶርያም ሄደን ወደ ጢሮስ ደረስን፤ መርከቡ ሸክሙን በዚያ የሚያራግፍ ነበርና። ደቀ መዛሙርትንም ባገኘን ጊዜ በዚያ ሰባት ቀን ተቀመጥን፤ እነርሱም ጳውሎስን ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይወጣ በመንፈስ ተመርተው ነገሩት። ጊዜውንም በፈጸምን ጊዜ ወጥተን ሄድን፤ ሁላቸውም ከሚስቶቻቸውና ከልጆቻቸው ጋር እስከ ከተማው ውጭ ድረስ ሸኙን፤ በባሕሩም ዳር ተንበርክከን ጸለይን፤ እርስ በርሳችንምተሰነባብተን ወደ መርከብ ወጣን፤ እነዚያም ወደ ቤታቸው ተመለሱ። እኛም የባሕሩን መንገድ ጨርሰን ከጢሮስ ወደ አካ ደረስን፤ ለወንድሞችም ሰላምታ ሰጥተን ከእነርሱ ዘንድ አንድ ቀን ተቀመጥን። በነገውም ወጥተን ወደ ቂሣርያ መጣን፤ ከሰባቱም አንድ በሚሆን በወንጌላዊው ፊልጶስ ቤት ገብተን በእርሱ ዘንድ ተቀመጥን። ለእርሱም ትንቢት የሚናገሩ አራት ደናግል ሴቶች ልጆች ነበሩት። አያሌ ቀንም ተቀምጠን ሳለን ነቢይ የነበረ አጋቦስ የሚሉት አንድ ሰው ከይሁዳ ወረደ። ወደ እኛም መጣና የጳውሎስን መታጠቂያ ወስዶ የገዛ እጁንና እግሩን አስሮ “እንዲሁ መንፈስ ቅዱስ ‘ይህ መታጠቂያ ያለውን ሰው አይሁድ በኢየሩሳሌም እንደዚህ ያስሩታል፤ በአሕዛብም እጅ አሳልፈው ይሰጡታል፤’ ይላል፤” አለ። ይህንም በሰማን ጊዜ እኛም በዚያ የሚኖሩትም ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይወጣ ለመንነው። ጳውሎስ ግን መልሶ “እያለቀሳችሁ ልቤንም እየሰበራችሁ ምን ማድረጋችሁ ነው? እኔ ስለ ጌታ ስለ ኢየሱስ ስም በኢየሩሳሌም ለመሞት እንኳ ተሰናድቼአለሁ እንጂ ለእስራት ብቻ አይደለም፤” አለ። ምክርንም ሊቀበል እምቢ ባለ ጊዜ “የጌታ ፈቃድ ይሁን፤” ብለን ዝም አልን። ከዚህም ቀን በኋላ ተዘጋጅተን ወደ ኢየሩሳሌም ወጣን። በቂሣርያም ከነበሩ ደቀ መዛሙርት አንዳንዶች ደግሞ ከእኛ ጋር መጡ፤ እነርሱም ወደምናድርበት ወደ ቀደመው ደቀመዝሙር ወደ ቆጵሮሱ ምናሶን ወደሚሉት ቤት መሩን። ወደ ኢየሩሳሌም በደረስን ጊዜ ወንድሞች በደስታ ተቀበሉን። በነገውም ጳውሎስ ከእኛ ጋር ወደ ያዕቆብ ዘንድ ገባ፤ ሽማግሌዎችም ሁሉ መጡ። ሰላምታም ካቀረበላቸው በኋላ በእርሱ ማገልገል እግዚአብሔር በአሕዛብ መካከል ያደረገውን በእያንዳንዱ ተረከላቸው። እነርሱም በሰሙ ጊዜ እግዚአብሔርን አመሰገኑ፤ አሉትም “ወንድም ሆይ! በአይሁድ መካከል አምነው የነበሩት ስንት አእላፋት እንደ ሆኑ ታያለህ፤ ሁላቸውም ለሕግ የሚቀኑ ናቸው። ልጆቻቸውንም እንዳይገርዙ በሥርዓትም እንዳይሄዱ ብለህ በአሕዛብ መካከል ያሉት አይሁድ ሁሉ ሙሴን ይክዱ ዘንድ እንድታስተምር ስለ አንተ ነግረዋቸዋል። እንግዲህ ምን ይሁን? የአንተን መምጣት ይሰማሉና ብዙዎች የግድ ሳይሰበሰቡ አይቀሩም። እንግዲህ ይህን የምንልህን አድርግ፤ ስለት ያለባቸው አራት ሰዎች በእኛ ዘንድ አሉ። እነዚህንም ይዘህ ከእነርሱ ጋር ንጻ፤ ራሳቸውንም እንዲላጩ ገንዘብ ክፈልላቸው፤ ሁሉም ስለ አንተ የተማሩት ከንቱ እንደ ሆነና አንተ ራስህ ደግሞ ሕጉን እየጠበቅህ በሥርዓት እንድትመላለስ ያውቃሉ። አምነው ስለ ነበሩ አሕዛብ ግን ለጣዖት ከተሠዋ ከደምም ከታነቀም ከዝሙትም ነፍሳቸውን እንዲጠብቁ ፈርደን እኛ ጽፈንላቸዋል።” በዚያን ጊዜ ጳውሎስ ሰዎችን ይዞ በማግሥቱ ከእነርሱ ጋር እየነጻ፥ መንጻታቸውን የሚፈጽሙበትን ቀን አስታውቆ ወደ መቅደስ ገባ። በዚያም ቀን ስለ እያንዳንዳቸው መሥዋዕትን አቀረቡ።