ሐዋርያት ሥራ 20:1-16

ሐዋርያት ሥራ 20:1-16 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ክር​ክ​ሩም ከተ​ፈ​ጸመ በኋላ ጳው​ሎስ ደቀ መዛ​ሙ​ር​ቱን ጠራና አጽ​ና​ና​ቸው፤ ተሰ​ና​በ​ታ​ቸ​ውም፤ ወጥ​ቶም ወደ መቄ​ዶ​ንያ ሄደ። በዚያ አው​ራ​ጃም አልፎ ሄደ፤ በቃ​ሉም ብዙ አስ​ተ​ማ​ራ​ቸው፤ ከዚ​ያም በኋላ ወደ ግሪክ ሀገር ሄደ። በዚ​ያም ሦስት ወር ተቀ​መጠ፤ ወደ ሶር​ያም በመ​ር​ከብ ለመ​ሄድ ዐስቦ ሳለ አይ​ሁድ ስለ ተማ​ከ​ሩ​በት ወደ መቄ​ዶ​ንያ ሊመ​ለስ ቈረጠ። ከእ​ር​ሱም ጋር የቤ​ርያ ሀገር ሰው የሚ​ሆን ሱሲ​ጳ​ጥ​ሮስ፥ የተ​ሰ​ሎ​ን​ቄም ሰዎች አር​ስ​ጥ​ሮ​ኮ​ስና ሲኮ​ን​ዱስ፥ የደ​ር​ቤኑ ሰው ጋይ​ዮ​ስና ጢሞ​ቴ​ዎ​ስም፥ የእ​ስያ ሰዎች የሚ​ሆኑ ቲኪ​ቆ​ስና ጥሮ​ፊ​ሞ​ስም አብ​ረ​ውት ሄዱ። እነ​ር​ሱም ቀድ​መ​ውን ሄደው በጢ​ሮ​አስ ቆዩን። እኛ ግን ከፋ​ሲካ በኋላ ከፊ​ል​ጵ​ስ​ዩስ ተነ​ሥ​ተን በባ​ሕር ላይ ተጕ​ዘን በአ​ም​ስት ቀን ወደ ጢሮ​አስ ደረ​ስን፤ በዚ​ያም ሰባት ቀን ተቀ​መ​ጥን። ከሳ​ም​ን​ቱም በመ​ጀ​መ​ሪ​ያው ቀን እሑድ ማዕድ ለመ​ባ​ረክ ተሰ​ብ​ስ​በን ሳለን ጳው​ሎስ በማ​ግ​ሥቱ የሚ​ሄድ ነውና ያስ​ተ​ም​ራ​ቸው ጀመረ፤ እስከ መን​ፈቀ ሌሊ​ትም ድረስ ትም​ህ​ር​ቱን አስ​ረ​ዘመ። ተሰ​ብ​ስ​በን በነ​በ​ር​ን​በት ሰገ​ነ​ትም ብዙ መብ​ራት ነበር። ስሙ አው​ጤ​ክስ የሚ​ባል አንድ ጐል​ማሳ ልጅም በመ​ስ​ኮት በኩል ተቀ​ምጦ ሳለ ከባድ እን​ቅ​ልፍ አን​ቀ​ላ​ፍቶ ነበር፤ ጳው​ሎ​ስም ትም​ህ​ር​ቱን ባስ​ረ​ዘመ ጊዜ ያ ጐል​ማሳ ከእ​ን​ቅ​ልፉ ብዛት የተ​ነሣ ከተ​ኛ​በት ከሦ​ስ​ተ​ኛው ፎቅ ወደ ታች ወደቀ፤ ሬሳ​ው​ንም አነ​ሡት። ጳው​ሎ​ስም ወርዶ በላዩ ወደቀ፤ አቅ​ፎም ያዘው፤ እነ​ር​ሱ​ንም፥ “ነፍሱ አለ​ችና አት​ደ​ን​ግጡ” አላ​ቸው። ከዚ​ህም በኋላ ወደ ሰገ​ነት ወጣ፤ ማዕ​ዱ​ንም ባርኮ በላ፤ እስ​ኪ​ነ​ጋም ድረስ ብዙ ትም​ህ​ርት አስ​ተ​ማ​ራ​ቸው፤ ከዚያ በኋ​ላም ተነ​ሥቶ ሄደ። ብላ​ቴ​ና​ው​ንም ደኅና ሆኖ ወሰ​ዱት፤ እጅ​ግም ደስ አላ​ቸው። እኛ ግን በመ​ር​ከብ ሆነን ወደ አሶስ ሄድን፤ ከዚያ ጳው​ሎ​ስን ልን​ቀ​በ​ለው እንሻ ነበ​ርና፤ እን​ደ​ዚሁ በእ​ግር እን​ደ​ሚ​መጣ ነግ​ሮን ነበ​ርና ተቀ​በ​ል​ነው። አሶ​ስም ደረ​ስን፤ በመ​ር​ከ​ብም ይዘ​ነው ወደ ሚጢ​ሊኒ ሄድን። በማ​ግ​ሥ​ቱም ከዚያ ወጥ​ተን በኪ​ዮስ ፊት ለፊት ደረ​ስን፤ በማ​ግ​ሥ​ቱም ወደ ሳሞስ አለ​ፍን፤ በት​ሮ​ጊ​ሊ​ዮም ተቀ​መ​ጥን፤ ከዚህ ቀን በኋ​ላም ወደ መሊጡ ደረ​ስን። ጳው​ሎ​ስም በእ​ስያ እን​ዳ​ይ​ዘ​ገይ በኤ​ፌ​ሶን በኩል ሊሄድ ቈርጦ ነበር፤ የሚ​ቻ​ለ​ውም ቢሆን ለበ​ዓለ ኀምሳ ኢየ​ሩ​ሳ​ሌም ለመ​ድ​ረስ ቸኵሎ ነበ​ርና።

ሐዋርያት ሥራ 20:1-16 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ሁከቱም እንደ በረደ፣ ጳውሎስ ደቀ መዛሙርትን አስጠርቶ መከራቸው፤ ተሰናብቷቸውም ወደ መቄዶንያ ለመሄድ ተነሣ። ባለፈባቸውም ስፍራዎች ሕዝቡን በብዙ ቃል እየመከረ ግሪክ አገር ደረሰ፤ በዚያም ሦስት ወር ተቀመጠ። ወደ ሶርያ በመርከብ ለመሄድ ሲዘጋጅም አይሁድ አሢረውበት ስለ ነበር፣ በመቄዶንያ በኩል አድርጎ ለመመለስ ወሰነ። የጳይሮስ ልጅ የቤርያው ሱሲጴጥሮስ፣ የተሰሎንቄዎቹ አርስጥሮኮስና ሲኮንዱስ፣ የደርቤኑ ጋይዮስ፣ ከእስያ አውራጃ የመጡት ቲኪቆስና ጥሮፊሞስ እንዲሁም ጢሞቴዎስ ዐብረውት ሄዱ። እነዚህም ሰዎች ወደ ፊት ቀድመውን በጢሮአዳ ጠበቁን። እኛ ግን የቂጣ በዓል ካለፈ በኋላ፣ ከፊልጵስዩስ በመርከብ ተነሣን፤ ከዐምስት ቀንም በኋላ ከሌሎቹ ጋራ በጢሮአዳ ተገናኘን፤ በዚያም ሰባት ቀን ተቀመጥን። በሳምንቱ መጀመሪያ ቀን እንጀራ ለመቍረስ ተሰብስበን ሳለን፣ ጳውሎስ በማግስቱም ለመሄድ ስላሰበ፣ ከእነርሱ ጋራ ይነጋገር ነበር፤ ንግግሩንም እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ አራዘመ። በተሰበሰብንበትም ሰገነት ላይ ብዙ መብራት ነበር። አውጤኪስ የተባለ አንድ ጐበዝም በመስኮት ላይ ተቀምጦ ነበር፤ ጳውሎስ ንግግሩን ባስረዘመ ጊዜ፣ እንቅልፍ እንቅልፍ አለውና ጭልጥ ብሎ ተኛ፤ ከሦስተኛውም ፎቅ ቍልቍል ወደቀ፤ ሞቶም አነሡት። ጳውሎስም ወርዶ በላዩ ተጋድሞ ዐቀፈውና፣ “ሕይወቱ በውስጡ ስላለች ሁከት አትፍጠሩ!” አላቸው። ተመልሶም እንደ ገና ወደ ፎቁ ወጣ፤ እንጀራውንም ቈርሶ በላ፤ እስኪነጋም ድረስ ብዙ ከተናገረ በኋላ ተነሥቶ ሄደ። ሰዎችም ያን ጐበዝ ሕያው ሆኖ ወሰዱት፤ በዚህም እጅግ ተጽናኑ። እኛ ግን ጳውሎስን ለመቀበል ቀድመን ወደ መርከቡ ሄድን፤ ከዚያም በመርከብ ወደ አሶን ተጓዝን፤ ይህን ያደረግነውም ጳውሎስ በየብስ በእግሩ ሊሄድ ስላሰበ ነበር። በአሶን ከተገናኘንም በኋላ፣ ተቀብለነው ዐብረን በመርከብ ወደ ሚጢሊኒ ሄድን። በማግስቱም በመርከብ ተጕዘን ከኪዩ ደሴት ትይዩ ደረስን። በሚቀጥለውም ቀን ወደ ሳሞን ተሻገርን፤ በማግስቱም ሚሊጢን ደረስን። ጳውሎስም በእስያ አውራጃ ብዙ መቈየት ስላልፈለገ፣ ወደ ኤፌሶን ሳይገባ ዐልፎ ለመሄድ ወሰነ፤ ቢቻል በዓለ ዐምሳን በኢየሩሳሌም ለመዋል ቸኵሎ ነበርና።

ሐዋርያት ሥራ 20:1-16 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ሁከቱም ከቀረ በኋላ ጳውሎስ ደቀ መዛሙርቱን አስመጥቶ መከራቸው፥ ተሰናብቶአቸውም ወደ መቄዶንያ ይሄድ ዘንድ ወጣ። ያንም አገር እያለፈ በብዙ ቃል ከመከራቸው በኋላ ወደ ግሪክ አገር መጣ። በዚያም ሦስት ወር ተቀምጦ ወደ ሶርያ በመርከብ ሊሄድ ባሰበ ጊዜ፥ አይሁድ ሴራ ስላደረጉበት በመቄዶንያ አልፎ ይመለስ ዘንድ ቆረጠ። የሸኙትም የቤርያው ሱሲጳጥሮስ ከተሰሎንቄ ሰዎችም አርስጥሮኮስና ሲኮንዱስ የደርቤኑም ጋይዮስና ጢሞቴዎስ የእስያ ሰዎችም ቲኪቆስ ጥሮፊሞስም ነበሩ፤ እነዚህም ወደ ፊታችን አልፈው በጢሮአዳ ቆዩን። እኛ ግን ከቂጣ በዓል ቀን በኋላ ከፊልጵስዩስ በመርከብ ተነሥተን በአምስት ቀን ወደ ጢሮአዳ ወደ እነርሱ ደረስንና በዚያ ሰባት ቀን ተቀመጥን። ከሳምንቱም በመጀመሪያ ቀን እንጀራ ለመቁረስ ተሰብስበን ሳለን፥ ጳውሎስ በነገው ሊሄድ ስላሰበ ከእነርሱ ጋር ይነጋገር ነበር፥ እስከ መንፈቀ ሌሊትም ነገሩን አስረዘመ። ተሰብስበንም በነበርንበት ሰገነት እጅግ መብራት ነበረ። አውጤኪስ የሚሉትም አንድ ጎበዝ በመስኮት ተቀምጦ ታላቅ እንቅልፍ አንቀላፍቶ ነበር፤ ጳውሎስም ነገርን ባስረዘመ ጊዜ እንቅልፍ ከብዶት ከሦስተኛው ደርብ ወደ ታች ወደቀ፥ ሞቶም አነሡት። ጳውሎስም ወርዶ በላዩ ወደቀ፥ አቅፎም፦ ነፍሱ አለችበትና አትንጫጩ አላቸው። ወጥቶም እንጀራ ቆርሶም በላ፤ ብዙ ጊዜም እስኪነጋ ድረስ ተነጋገረ እንዲህም ሄደ። ብላቴናውንም ደኅና ሆኖ ወሰዱት እጅግም ተጽናኑ። እኛ ግን ጳውሎስን ከዚያ እንቀበለው ዘንድ ስላለን ወደ መርከብ ቀድመን ሄድንና ወደ አሶን ተነሣን፤ እርሱ በመሬት ይሄድ ዘንድ ስላሰበ እንደዚህ አዞ ነበርና። በአሶንም ባገኘን ጊዜ ተቀብለነው ወደ ሚጢሊኒ መጣን፤ በማግሥቱም ከዚያ በባሕር ተነሥተን በኪዩ ፊት ለፊት ደረስን፥ በነገውም ወደ ሳሞን ተሻገርን በትሮጊሊዮም አድረን በማግሥቱ ወደ ሚሊጢን መጣን። ጳውሎስ በእስያ እጅግ እንዳይቀመጥ ኤፌሶንን ይተው ዘንድ ቆርጦ ነበርና ቢቻለውም በዓለ ኀምሳን በኢየሩሳሌም ይውል ዘንድ ይቸኩል ነበርና።

ሐዋርያት ሥራ 20:1-16 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ሁከቱ ጸጥ ካለ በኋላ ጳውሎስ ምእመናኑን በአንድነት አስጠርቶ በምክር ቃል አጽናናቸው፤ ተሰናብቶአቸውም ወደ መቄዶንያ ሄደ። በእነዚያ በሚያልፍባቸው ስፍራዎች ምእመናንን በብዙ ምክር እያበረታታ ወደ ግሪክ አገር ሄደ። እዚያም ሦስት ወር ቈየ፤ ከዚህ በኋላ በመርከብ ወደ ሶርያ ለመሄድ አሰበ፤ ግን አይሁድ በእርሱ ላይ ሤራ ማድረጋቸውን ባወቀ ጊዜ በመቄዶንያ በኩል ለመመለስ ወሰነ። የጲርሁስ ልጅ ሶጳጥሮስ ከቤርያ፥ አርስጥሮኮስና ሲኮንዱስ ከተሰሎንቄ፥ ጋይዮስ ከደርቤ፥ ጢሞቴዎስ፥ ቲኪቆስና ጥሮፊሞስ ከእስያ አብረውት ሄዱ። እነርሱ ቀድመውን ሄደው በጢሮአዳ ቈዩን። እኛ ግን ከቂጣ በዓል በኋላ ከፊልጵስዩስ በመርከብ ተሳፍረን በአምስት ቀን እነርሱ ወዳሉበት ወደ ጢሮአዳ ደረስንና እዚያ ሰባት ቀን አሳለፍን። ከሳምንቱ በመጀመሪያው ቀን እንጀራ ቈርሶ በአንድነት ለመብላት ተሰበሰብን፤ ጳውሎስ በማግስቱ መሄድ ስለ ነበረበት ለተሰበሰቡት ሰዎች ይናገር ነበር፤ ንግግሩንም እስከ እኩለ ሌሊት አስረዘመ። እኛ በተሰበሰብንበት ፎቅ ብዙ መብራት ነበር። ኤውጤኪስ የተባለ አንድ ወጣት በመስኮት ላይ ተቀምጦ ነበር፤ ጳውሎስ ንግግሩን በማስረዘሙ ወጣቱ ከባድ እንቅልፍ ያዘው፤ እንቅልፍ ስላሸነፈውም ከሦስተኛው ፎቅ ወደ ታች ወደቀ፤ ሰዎች ባነሡት ጊዜ ሞቶ አገኙት። ነገር ግን ጳውሎስ ወርዶ በልጁ ላይ ጐንበስ በማለት አቀፈውና “ገና በሕይወት አለ፤ አትደንግጡ!” አለ። ጳውሎስ ወደ ፎቅ ተመልሶ ወጣና እንጀራ ቈርሶ ከአማኞች ጋር በላ፤ እስኪነጋም ድረስ ከሰዎቹ ጋር ሲነጋገር ከቈየ በኋላ ሄደ። ሰዎቹም የዳነውን ወጣት ወደ ቤት ወሰዱት፤ በዚህም እጅግ ተጽናኑ። ጳውሎስን ለማሳፈር ስለ አሰብን እኛ ቀድመን በመርከብ ወደ አሶስ ሄድን፤ ይህንንም ያደረግነው ጳውሎስ እስከ አሶስ ድረስ በእግሩ ለመሄድ ስለ ወሰነና እንዲህ እንድናደርግ ስለ አዘዘን ነው። ከእርሱ ጋር በአሶስ በተገናኘን ጊዜ በመርከብ አሳፍረነው ወደ ሚጢሊኒ አብረን ሄድን። በማግስቱ ከዚያ ተነሥተን በኪዮስ ፊት ለፊት ወዳለው ስፍራ በመርከብ ደረስን፤ በሚቀጥለውም ቀን ወደ ሳሞስ ተሻገርንና በማግስቱ ወደ ሚሊጢ ደረስን። ጳውሎስ በእስያ ጊዜ እንዳያባክን ብሎ ኤፌሶንን አልፎ ለመሄድ ፈለገ፤ ይህንንም ያደረገው ለጰንጠቆስጤ በዓል በኢየሩሳሌም ለመገኘት አስቦ ስለ ነበር ነው።

ሐዋርያት ሥራ 20:1-16 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ሁከቱም ከቀረ በኋላ ጳውሎስ ደቀ መዛሙርቱን አስመጥቶ መከራቸው፤ ተሰናብቶአቸውም ወደ መቄዶንያ ይሄድ ዘንድ ወጣ። ያንም አገር እያለፈ በብዙ ቃል ከመከራቸው በኋላ ወደ ግሪክ አገር መጣ። በዚያም ሦስት ወር ተቀምጦ ወደ ሶርያ በመርከብ ሊሄድ ባሰበ ጊዜ፥ አይሁድ ሤራ ስላደረጉበት በመቄዶንያ አልፎ ይመለስ ዘንድ ቆረጠ። የሸኙትም የቤርያው ሶጳጥሮስ ከተሰሎንቄ ሰዎችም አርስጥሮኮስና ሲኮንዱስ የደርቤኑም ጋይዮስና ጢሞቴዎስ የእስያ ሰዎችም ቲኪቆስ ጥሮፊሞስም ነበሩ፤ እነዚህም ወደ ፊታችን አልፈው በጢሮአዳ ቆዩን። እኛ ግን ከቂጣ በዓል ቀን በኋላ ከፊልጵስዩስ በመርከብ ተነሥተን በአምስት ቀን ወደ ጢሮአዳ ወደ እነርሱ ደረስንና በዚያ ሰባት ቀን ተቀመጥን። ከሳምንቱም በመጀመሪያ ቀን እንጀራ ለመቁረስ ተሰብስበን ሳለን፥ ጳውሎስ በነገው ሊሄድ ስላሰበ ከእነርሱ ጋር ይነጋገር ነበር፤ እስከ መንፈቀ ሌሊትም ነገሩን አስረዘመ። ተሰብስበንም በነበርንበት ሰገነት እጅግ መብራት ነበረ። አውጤኪስ የሚሉትም አንድ ጎበዝ በመስኮት ተቀምጦ ታላቅ እንቅልፍ አንቀላፍቶ ነበር፤ ጳውሎስም ነገርን ባስረዘመ ጊዜ እንቅልፍ ከብዶት ከሦስተኛው ደርብ ወደ ታች ወደቀ፤ ሞቶም አነሡት። ጳውሎስም ወርዶ በላዩ ወደቀ፤ አቅፎም “ነፍሱ አለችበትና አትንጫጩ፤” አላቸው። ወጥቶም እንጀራ ቆርሶም በላ፤ ብዙ ጊዜም እስኪ ነጋ ድረስ ተነጋገረ እንዲህም ሄደ። ብላቴናውንም ደኅና ሆኖ ወሰዱት፤ እጅግም ተጽናኑ። እኛ ግን ጳውሎስን ከዚያ እንቀበለው ዘንድ ስላለን ወደ መርከብ ቀድመን ሄድንና ወደ አሶን ተነሣን፤ እርሱ በመሬት ይሄድ ዘንድ ስላሰበ እንደዚህ አዞ ነበርና። በአሶንም ባገኘን ጊዜ ተቀብለነው ወደ ሚጢሊኒ መጣን፤ በማግሥቱም ከዚያ በባሕር ተነሥተን በኪዩ ፊት ለፊት ደረስን፤ በነገውም ወደ ሳሞን ተሻገርን፤ በትሮጊሊዮም አድረን በማግሥቱ ወደ ሚሊጢን መጣን። ጳውሎስ በእስያ እጅግ እንዳይቀመጥ ኤፌሶንን ይተው ዘንድ ቆርጦ ነበርና፤ ቢቻለውም በዓለ ኀምሳን በኢየሩሳሌም ይውል ዘንድ ይቸኩል ነበርና።