ሐዋርያት ሥራ 2:25-41 - Compare All Versions
ሐዋርያት ሥራ 2:25-41 አማ2000 (የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ))
ዳዊትም ስለ እርሱ እንዲህ አለ፦ እግዚአብሔርን ሁልጊዜ በፊቴ አየዋለሁ፤ እንዳልታወክ በቀኜ ነውና። ስለዚህ ልቤን ደስ አለው፤ አንደበቴም ሐሤት አደረገ፤ ሥጋዬም ደግሞ በተስፋው አደረ። ነፍሴን በሲኦል አትተዋትምና፥ ጻድቅህንም ጥፋትን ያይ ዘንድ አትሰጠውምና። የሕይወትን መንገድ አሳየኸኝ፤ ከፊትህ ጋራ ደስታን አጠገብኸኝ። “እናንተ ወንድሞች ሆይ፥ ስለ አባቶች አለቃ ስለ ዳዊት ነገር እንደ ሞተ እንደ ተቀበረም፥ መቃብሩም እስከ ዛሬ ድረስ በእኛ ዘንድ እንደ አለ ገልጬ እንድነግራችሁ ትፈቅዱልኛላችሁን? ነቢይ ስለ ነበረ፥ ከአብራኩም የተገኘውን በዙፋኑ እንዲያነግሥለት እግዚአብሔር መሐላን እንደ ማለለት ስለ ዐወቀ፥ ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ እንደሚነሣ፥ ሥጋዉም በመቃብር እንደማይቀር፥ ጥፋትንም እንደማያይ አስቀድሞ ዐውቆ ተናገረ። እርሱን ኢየሱስን እግዚአብሔር አስነሣው፤ ለዚህም እኛ ሁላችን ምስክሮቹ ነን። አሁን ግን በእግዚአብሔር ቀኝ ከፍ ከፍ ብሎና የመንፈስ ቅዱስን ተስፋ ከአብ ገንዘብ አድርጎ ይህን ዛሬ የምታዩትንና የምትሰሙትን አፈሰሰው። ዳዊት ወደ ሰማይ አልወጣም፥ ነገር ግን እርሱ አለ፦ ጌታ ጌታዬን አለው፦ በቀኜ ተቀመጥ። ጠላቶችህን ከእግርህ ጫማ በታች እስክጥላቸው ድረስ። እንግዲህ የእስራኤል ወገኖች ሁሉ እናንተ የሰቀላችሁትን ኢየሱስን እግዚአብሔር ጌታም መሢሕም እንዳደረገው በርግጥ ይወቁ።” ይህንም በሰሙ ጊዜ ልባቸው ተከፈተ፤ ጴጥሮስንና ወንድሞቹ ሐዋርያትንም፥ “ወንድሞቻችን ሆይ፥ ምን እናድርግ?” አሏቸው። ጴጥሮስም እንዲህ አላቸው፥ “ንስሓ ግቡ፤ ሁላችሁም በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ ኀጢአታችሁም ይሰረይላችኋል፤ የመንፈስ ቅዱስንም ጸጋ ትቀበላላችሁ። ተስፋዉ ለእናንተና ለልጆቻችሁ፥ እግዚአብሔር አምላካችንም ለሚጠራቸው ርቀው ለነበሩ ሁሉ ነውና።” ሌላም ብዙ ነገር ነገራቸው፤ “ከዚህ ከክፉ ዓለምም ነፍሳችሁን አድኑ” ብሎ መከራቸው። ቃሉንም ተቀብለው ተጠመቁ፤ በዚችም ዕለት ሦስት ሺህ ያህል ሰዎች ተጨመሩ።
ሐዋርያት ሥራ 2:25-41 NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
ዳዊትም ስለ እርሱ እንዲህ ይላል፤ “ ‘ጌታን ሁልጊዜ በፊቴ አየዋለሁ፤ እርሱ በቀኜ ነውና፣ ከቶ አልታወክም። ስለዚህ ልቤ ደስ አለው፤ አንደበቴም ሐሤት አደረገ፤ ሥጋዬም በተስፋ ይኖራል። ነፍሴን በሲኦል አትተዋትምና፤ ቅዱስህም መበስበስን እንዲያይ አትፈቅድም። የሕይወትን መንገድ እንዳውቅ አደረግኸኝ፤ በፊትህም በሐሤት ትሞላኛለህ።’ “ወንድሞች ሆይ፤ ከቀደምት አባቶች ዳዊት ሞቶ እንደ ተቀበረ፣ መቃብሩም እስከ ዛሬ ድረስ በመካከላችን እንደሚገኝ በድፍረት መናገር እችላለሁ። ነቢይ በመሆኑም፣ እግዚአብሔር ከዘሮቹ አንዱን በዙፋኑ ላይ እንደሚያስቀምጥ በመሐላ ቃል የገባለት መሆኑን ዐወቀ። ይህን አስቀድሞ በማየቱ እርሱ በሲኦል እንዳልቀረና ሥጋውም መበስበስን እንዳላየ ስለ ክርስቶስ ትንሣኤ ተናገረ። ይህን ኢየሱስ፣ እግዚአብሔር ከሞት አስነሣው፤ እኛም ሁላችን ለዚህ ነገር ምስክሮች ነን። ስለዚህ በእግዚአብሔር ቀኝ ከፍ ከፍ ካለ በኋላ፣ የመንፈስ ቅዱስን ተስፋ ከአብ ተቀብሎ አሁን የምታዩትንና የምትሰሙትን አፈሰሰው። ዳዊት ወደ ሰማያት አልወጣምና፤ እርሱ ራሱ ግን እንዲህ ብሏል፤ “ ‘ጌታ ጌታዬን፣ “ጠላቶችህን ለእግርህ መረገጫ፣ እስከማደርግልህ ድረስ፣ በቀኜ ተቀመጥ” አለው።’ “እንግዲህ፣ እግዚአብሔር ይህን እናንተ የሰቀላችሁትን ኢየሱስን፣ ጌታም ክርስቶስም እንዳደረገው የእስራኤል ወገን ሁሉ ይረዳ!” ሕዝቡም ይህን በሰሙ ጊዜ ልባቸው እጅግ ተነካ፤ ጴጥሮስንና ሌሎቹንም ሐዋርያት፣ “ወንድሞች ሆይ፤ ታዲያ ምን እናድርግ?” አሏቸው። ጴጥሮስም እንዲህ አላቸው፤ “ንስሓ ግቡ፤ ኀጢአታችሁም እንዲሰረይላችሁ፣ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ። የተስፋው ቃል ለእናንተና ለልጆቻችሁ እንዲሁም ጌታ አምላካችን ወደ ራሱ ለሚጠራቸው፣ በሩቅ ላሉትም ሁሉ ነውና።” በሌላ ብዙ ቃል እየመሰከረላቸው፣ “ከዚህ ጠማማ ትውልድ ራሳችሁን አድኑ” በማለት አስጠነቀቃቸው። ቃሉን የተቀበሉትም ተጠመቁ፤ በዚያ ቀን ሦስት ሺሕ ያህል ሰዎች በቍጥራቸው ላይ ተጨመሩ።
ሐዋርያት ሥራ 2:25-41 አማ54 (መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት))
ዳዊት ስለ እርሱ እንዲህ ይላልና፦ ‘ጌታን ሁልጊዜ በፊቴ አየሁት፥ እንዳልታወክ በቀኜ ነውና። ስለዚህ ልቤን ደስ አለው፥ ልሳኔም ሐሤት አደረገ፥ ደግሞም ሥጋዬ በተስፋ ያድራል፤ ነፍሴን በሲኦል አትተዋትምና፥ ቅዱስህንም መበስበስን ያይ ዘንድ አትሰጠውም። የሕይወትን መንገድ አስታወቅኸኝ፤ ከፊትህ ጋር ደስታን ትሞላብኛለህ።’ ወንድሞች ሆይ፥ ስለ አባቶች አለቃ ስለ ዳዊት እንደ ሞተም እንደ ተቀበረም ለእናንተ በግልጥ እናገር ዘንድ ፍቀዱልኝ፤ መቃብሩም እስከ ዛሬ በእኛ ዘንድ ነው። ነቢይ ስለ ሆነ፥ ከወገቡም ፍሬ በዙፋኑ ያስቀምጥ ዘንድ እግዚአብሔር መሐላ እንደ ማለለት ስለ አወቀ፥ ስለ ክርስቶስ ትንሣኤ አስቀድሞ አይቶ፥ ነፍሱ በሲኦል እንዳልቀረች ሥጋውም መበስበስን እንዳላየ ተናገረ። ይህን ኢየሱስን እግዚአብሔር አስነሣው ለዚህም ነገር እኛ ሁላችን ምስክሮች ነን፤ ስለዚህ በእግዚአብሔር ቀኝ ከፍ ከፍ ብሎና የመንፈስ ቅዱስን የተስፋ ቃል ከአብ ተቀብሎ ይህን እናንተ አሁን የምታዩትንና የምትሰሙትን አፈሰሰው። ዳዊት ወደ ሰማያት አልወጣምና፥ ነገር ግን እርሱ፦ ‘ጌታ ጌታዬን፦ ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው።’ አለ። እንግዲህ ይህን እናንተ የሰቀላችሁትን ኢየሱስን እግዚአብሔር ጌታም ክርስቶስም እንዳደረገው የእእራኤል ወገን ሁሉ በእርግጥ ይወቅ።” ይህንም በሰሙ ጊዜ ልባቸው ተነካ፥ ጴጥሮስንና ሌሎችንም ሐዋርያት፦ “ወንድሞች ሆይ፥ ምን እናድርግ?” አሉአቸው። ጴጥሮስም፦ “ንስሐ ግቡ፥ ኃጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ። የተስፋው ቃል ለእናንተና ለልጆቻችሁ ጌታ አምላካችንም ወደ እርሱ ለሚጠራቸው በሩቅ ላሉ ሁሉ ነውና” አላቸው። በብዙ ሌላ ቃልም መሰከረና፦ “ከዚህ ጠማማ ትውልድ ዳኑ” ብሎ መከራቸው። ቃሉንም የተቀበሉ ተጠመቁ፥ በዚያም ቀን ሦስት ሺህ የሚያህል ነፍስ ተጨመሩ፤
ሐዋርያት ሥራ 2:25-41 አማ05 (አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም)
ዳዊትም ስለ እርሱ እንዲህ ይላል፦ ‘ጌታን ሁልጊዜ በፊቴ አየዋለሁ፤ እንዳልናወጥም እርሱ በቀኜ ነው ስለዚህ ልቤን ደስ አለው፤ አንደበቴም በደስታ ተሞላ፤ እንዲሁም ሟች የሆነው ሥጋዬ በተስፋ ይኖራል፤ ነፍሴን በሲኦል አትተዋትም፤ ቅዱስህንም በመቃብር በስብሶ እንዲቀር አታደርገውም። የሕይወትን መንገድ አስታወቅኸኝ፤ ከእኔም ጋር በመሆንህ ደስታዬ ፍጹም ይሆናል።’ “ወንድሞቼ ሆይ! ከቀድሞ አባቶች አንዱ የሆነው ዳዊት እንደ ሞተና እንደ ተቀበረ፥ መቃብሩም እስከ ዛሬ በእኛ ዘንድ እንዳለ በግልጥ ልንገራችሁ። ነገር ግን ዳዊት ይህን የተናገረው ነቢይ ስለ ነበረና እግዚአብሔር ‘ከዘርህ አንዱን በዙፋንህ ላይ አስቀምጥልሃለሁ’ ሲል በመሐላ የሰጠውን የተስፋ ቃል ያውቅ ስለ ነበር ነው፤ በዚህም ምክንያት መሲሕ በሲኦል እንደማይቀርና ሥጋውም በመቃብር በስብሶ እንደማይቀር አስቀድሞ አይቶ ስለ ትንሣኤው ተናገረ። ይህን ኢየሱስን እግዚአብሔር ከሞት አስነሣው፤ እኛም ሁላችን ለዚህ ነገር ምስክሮች ነን። በእግዚአብሔር ቀኝ ለመቀመጥ ከፍ ባለ ጊዜና የመንፈስ ቅዱስን ተስፋ ከአብ በተቀበለ ጊዜ ይህን የምታዩትንና የምትሰሙትን አፈሰሰው። እንግዲህ ወደ ሰማይ የወጣው ዳዊት ባለመሆኑ ዳዊት ራሱ እንዲህ ሲል ተናግሮአል፤ ‘ጌታ ለጌታዬ (ለመሲሑ) ጠላቶችህን በሥልጣንህ ሥር እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ’ ብሎታል። “እንግዲህ ይህን እናንተ የሰቀላችሁትን ኢየሱስን እግዚአብሔር ጌታና መሲሕ እንዳደረገው የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ በእርግጥ ይወቅ!” ሰዎቹም ይህን በሰሙ ጊዜ ልባቸው በሐዘን ተነክቶ ጴጥሮስንና ሌሎቹን ሐዋርያት፥ “ወንድሞች ሆይ! እንግዲህ ምን እናድርግ?” አሉአቸው። ጴጥሮስም እንዲህ አላቸው፤ “ንስሓ ግቡ፤ ኃጢአታችሁም ይቅር እንዲባልላችሁ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የእግዚአብሔር ስጦታ የሆነውን መንፈስ ቅዱስንም ትቀበላላችሁ፤ የተስፋው ቃል ለእናንተና ለልጆቻችሁ፥ ጌታ አምላካችን ወደ እርሱ ለሚጠራቸው፥ በሩቅ ላሉትም ሁሉ ነው።” በሌላም በብዙ ቃል እየመሰከረ፥ “በዚህ ጠማማ ትውልድ ላይ ከሚመጣው ቅጣት ራሳችሁን አድኑ!” በማለት መከራቸው። ከእነርሱ ብዙዎቹ ቃሉን ተቀብለው ተጠመቁ፤ በዚያን ቀን ሦስት ሺህ የሚያኽሉ አማኞች ተጨመሩ።
ሐዋርያት ሥራ 2:25-41 መቅካእኤ (መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ))
ዳዊት ስለ እርሱ እንዲህ ይላልና “ጌታን ሁልጊዜ በፊቴ አየሁት፤ እንዳልታወክ በቀኜ ነውና። ስለዚህ ልቤን ደስ አለው፤ ልሳኔም ሐሤት አደረገ፤ ደግሞም ሥጋዬ በተስፋ ያድራል፤ ነፍሴን በሲኦል አትተዋትምና፤ ቅዱስህንም መበስበስን ያይ ዘንድ አትሰጠውም። የሕይወትን መንገድ አስታወቅኸኝ፤ ከፊትህ ጋር ደስታን ትሞላብኛለህ።” ወንድሞች ሆይ! ስለ አባቶች አለቃ ስለ ዳዊት እንደ ሞተም እንደ ተቀበረም ለእናንተ በግልጥ እናገር ዘንድ ፍቀዱልኝ፤ መቃብሩም እስከ ዛሬ በእኛ ዘንድ ነው። ነቢይ ስለ ሆነ፥ ከወገቡም ፍሬ በዙፋኑ ያስቀምጥ ዘንድ እግዚአብሔር መሐላ እንደማለለት ስለ አወቀ፥ ስለ ክርስቶስ ትንሣኤ አስቀድሞ አይቶ፥ ነፍሱ በሲኦል እንዳልቀረች ሥጋውም መበስበስን እንዳላየ ተናገረ። ይህን ኢየሱስን እግዚአብሔር አስነሣው፤ ለዚህም ነገር እኛ ሁላችን ምስክሮች ነን፤ ስለዚህ በእግዚአብሔር ቀኝ ከፍ ከፍ ብሎና የመንፈስ ቅዱስን የተስፋ ቃል ከአብ ተቀብሎ ይህን እናንተ አሁን የምታዩትንና የምትሰሙትን አፈሰሰው። ዳዊት ወደ ሰማያት አልወጣምና፤ ነገር ግን እርሱ እንዳለው፦ ጌታ ጌታዬን በቀኜ ተቀመጥ፤ “ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስካደርግልህ ድረስ!” “እንግዲህ ይህን እናንተ የሰቀላችሁትን ኢየሱስን እግዚአብሔር ጌታም ክርስቶስም እንዳደረገው የእእራኤል ወገን ሁሉ በእርግጥ ይወቅ።” ይህንም በሰሙ ጊዜ ልባቸው ተሰበረ፤ ጴጥሮስንና ሌሎችንም ሐዋርያት “ወንድሞች ሆይ! ምን እናድርግ?” አሉአቸው። ጴጥሮስም “ንስሐ ግቡ፤ ኀጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ። የተስፋው ቃል ለእናንተና ለልጆቻችሁ ጌታ አምላካችንም ወደ እርሱ ለሚጠራቸው በሩቅ ላሉ ሁሉ ነውና፤” አላቸው። በብዙ ሌላ ቃልም መሰከረና “ከዚህ ጠማማ ትውልድ ዳኑ፤” ብሎ መከራቸው። ቃሉንም የተቀበሉ ተጠመቁ፤ በዚያም ቀን ሦስት ሺህ የሚያህል ነፍስ ተጨመሩ፤