ሐዋርያት ሥራ 2:1-40
ሐዋርያት ሥራ 2:1-40 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ኀምሳው ቀንም በተፈጸመ ጊዜ፥ ሁሉም በአንድነት በአንድ ቦታ ተሰብስበው ነበር። ድንገትም እንደ ዐውሎ ነፋስ ድምፅ ያለ ከሰማይ ድምፅ መጣ፤ የነበሩበትንም ቤት ሞላው። እንደ እሳት የተከፋፈሉ የእሳት ላንቃዎችም ታዩአቸው፤ በሁሉም ላይ ተቀመጡባቸው። ሁሉም መንፈስ ቅዱስን ተሞሉ፤ ይናገሩ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እንደ አደላቸው መጠንም እየራሳቸው በሀገሩ ሁሉ ቋንቋ ይናገሩ ጀመሩ። ከሰማይ በታች ካሉ አሕዛብ ሁሉ በኢየሩሳሌም የሚኖሩ ደጋግ የአይሁድ ሰዎች ነበሩ። ይህንም ቃል ሲናገሩ ሰምተው ሁሉም ደንግጠው ተሰበሰቡ፤ ሁሉም በየሀገራቸው ቋንቋ ሲናገሩ ሰምተዋቸዋልና የሚሉትን አጡ። ተገረሙ፤ አደነቁም፥ እንዲህም አሉ፥ “እነዚህ የሚናገሩት ሁሉ የገሊላ ሰዎች አይደሉምን? እንግዲህ በየሀገራችን ቋንቋ ሲናገሩ እንዴት እንሰማቸዋለን? እኛ በተወለድንበት በጳርቴ፥ በሜድ፥ በኢላሜጤ፥ በሁለቱ ወንዞች መካከል፥ በይሁዳ፥ በቀጰዶቅያ፥ በጳንጦስና በእስያ፥ በፍርግያ፥ በጵንፍልያ፥ በግብፅ፥ በሊብያ አውራጃ፥ በቀርኔን የምንኖር፥ ከሮሜም የመጣን አይሁድ፥ መጻተኞችም፥ ከቀርጤስና ከዐረብም የመጣን፥ እነሆ፥ የእግዚአብሔርን ጌትነት በየሀገራችን ቋንቋ ሲናገሩ እንሰማቸዋለን።” ሁሉም ተገረሙ፤ የሚሉትንም አጡ፥ እርስ በርሳቸውም፥ “እንጃ! ይህ ነገር ምን ይሆን?” ተባባሉ። እኩሌቶቹ ግን “እነዚህስ ጉሽ ጠጅ ጠግበው ሰክረዋል” ብለው ሳቁባቸው። ጴጥሮስም ከዐሥራ አንዱ ጋር ቆሞ ድምፁን ከፍ አድርጎ እንዲህ አለ፥ “እናንተ የአይሁድ ሰዎች፥ በኢየሩሳሌምም የምትኖሩ ሁሉ፥ ይህን ዕወቁ፤ ቃሌንም ስሙ። ለእናንተ እንደ መሰላችሁ እነዚህ የሰከሩ አይደሉም፤ ከቀኑ ገና ሦስተኛ ሰዓት ነውና። ነገር ግን ይህ በነቢዩ በኢዩኤል የተባለው ነው። በኋለኛዪቱ ቀን እንዲህ ይሆናል ይላል እግዚአብሔር፦ ሥጋን በለበሰ ሁሉ ላይ ከመንፈሴ አፈስሳለሁ፤ ወንዶች ልጆቻችሁና ሴቶች ልጆቻችሁ ትንቢት ይናገራሉ፤ ጐልማሶቻችሁ ራእይን ያያሉ፤ ሽማግሌዎቻችሁም ሕልምን ያልማሉ። በወንዶችና በሴቶች ባሮች ላይም ያንጊዜ መንፈሴን አፈስሳለሁ፤ ትንቢትም ይናገራሉ። በላይ በሰማይ ተአምራትን፥ በታች በምድርም ምልክቶችን፥ ደምን እሳትንና ጢስንም እሰጣለሁ። የምትገለጠው ታላቅዋ የእግዚአብሔር ቀን ሳትመጣ ፀሐይ ወደ ጨለማ፥ ጨረቃም ወደ ደም ይለወጣል። የእግዚአብሔርንም ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል። “እናንተ የእስራኤል ሰዎች ሆይ፥ ይህን ነገር ስሙ፤ እንደምታውቁት በመካከላችሁ እግዚአብሔር በእጁ ባደረገው በከሃሊነቱ በተአምራቱና በድንቅ ሥራዎቹ እግዚአብሔር የገለጠላችሁን ሰው የናዝሬቱን ኢየሱስን ስሙ። እርሱንም በተወሰነው በእግዚአብሔር ምክርና በቀደመው ዕውቀቱ እናንተ አሳልፋችሁ በኃጥኣን እጅ ሰጣችሁት፤ ሰቅላችሁም ገደላችሁት። እግዚአብሔር ግን የሞትን ማሰሪያ ፈቶ ከሙታን ለይቶ አስነሣው፤ ሞት እርሱን ሊይዘው አይችልምና። ዳዊትም ስለ እርሱ እንዲህ አለ፦ እግዚአብሔርን ሁልጊዜ በፊቴ አየዋለሁ፤ እንዳልታወክ በቀኜ ነውና። ስለዚህ ልቤን ደስ አለው፤ አንደበቴም ሐሤት አደረገ፤ ሥጋዬም ደግሞ በተስፋው አደረ። ነፍሴን በሲኦል አትተዋትምና፥ ጻድቅህንም ጥፋትን ያይ ዘንድ አትሰጠውምና። የሕይወትን መንገድ አሳየኸኝ፤ ከፊትህ ጋራ ደስታን አጠገብኸኝ። “እናንተ ወንድሞች ሆይ፥ ስለ አባቶች አለቃ ስለ ዳዊት ነገር እንደ ሞተ እንደ ተቀበረም፥ መቃብሩም እስከ ዛሬ ድረስ በእኛ ዘንድ እንደ አለ ገልጬ እንድነግራችሁ ትፈቅዱልኛላችሁን? ነቢይ ስለ ነበረ፥ ከአብራኩም የተገኘውን በዙፋኑ እንዲያነግሥለት እግዚአብሔር መሐላን እንደ ማለለት ስለ ዐወቀ፥ ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ እንደሚነሣ፥ ሥጋዉም በመቃብር እንደማይቀር፥ ጥፋትንም እንደማያይ አስቀድሞ ዐውቆ ተናገረ። እርሱን ኢየሱስን እግዚአብሔር አስነሣው፤ ለዚህም እኛ ሁላችን ምስክሮቹ ነን። አሁን ግን በእግዚአብሔር ቀኝ ከፍ ከፍ ብሎና የመንፈስ ቅዱስን ተስፋ ከአብ ገንዘብ አድርጎ ይህን ዛሬ የምታዩትንና የምትሰሙትን አፈሰሰው። ዳዊት ወደ ሰማይ አልወጣም፥ ነገር ግን እርሱ አለ፦ ጌታ ጌታዬን አለው፦ በቀኜ ተቀመጥ። ጠላቶችህን ከእግርህ ጫማ በታች እስክጥላቸው ድረስ። እንግዲህ የእስራኤል ወገኖች ሁሉ እናንተ የሰቀላችሁትን ኢየሱስን እግዚአብሔር ጌታም መሢሕም እንዳደረገው በርግጥ ይወቁ።” ይህንም በሰሙ ጊዜ ልባቸው ተከፈተ፤ ጴጥሮስንና ወንድሞቹ ሐዋርያትንም፥ “ወንድሞቻችን ሆይ፥ ምን እናድርግ?” አሏቸው። ጴጥሮስም እንዲህ አላቸው፥ “ንስሓ ግቡ፤ ሁላችሁም በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ ኀጢአታችሁም ይሰረይላችኋል፤ የመንፈስ ቅዱስንም ጸጋ ትቀበላላችሁ። ተስፋዉ ለእናንተና ለልጆቻችሁ፥ እግዚአብሔር አምላካችንም ለሚጠራቸው ርቀው ለነበሩ ሁሉ ነውና።” ሌላም ብዙ ነገር ነገራቸው፤ “ከዚህ ከክፉ ዓለምም ነፍሳችሁን አድኑ” ብሎ መከራቸው።
ሐዋርያት ሥራ 2:1-40 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
የበዓለ ዐምሳ ቀን በደረሰ ጊዜ ሁሉም በአንድነት፣ በአንድ ስፍራ ተሰብስበው ነበር። ድንገትም እንደ ብርቱ ዐውሎ ነፋስ ያለ ድምፅ ከሰማይ መጥቶ ተቀምጠው የነበሩበትን ቤት እንዳለ ሞላው። የእሳት ምላሶች የሚመስሉም ታዩአቸው፤ ተከፋፍለውም በእያንዳንዳቸው ላይ ዐረፉ። ሁሉም በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ፤ መንፈስም እንዲናገሩ በሰጣቸው መጠን በሌሎች ቋንቋዎች ይናገሩ ጀመር። በዚህ ጊዜ ከሰማይ በታች ካለው ሕዝብ ሁሉ የመጡና እግዚአብሔርን የሚፈሩ አይሁድ በኢየሩሳሌም ነበሩ። ይህን ድምፅ ሲሰሙ፣ ብዙ ሕዝብ በአንድነት ተሰበሰቡ፤ እያንዳንዱም ሰው፣ ሰዎቹ በገዛ ቋንቋው ሲናገሩ በመስማቱ ግራ ተጋባ፤ በመገረምና በመደነቅም እንዲህ አሉ፤ “እነዚህ የሚነጋገሩት ሁሉ የገሊላ ሰዎች አይደሉምን? ታዲያ፣ እያንዳንዳችን በተወለድንበት፣ በራሳችን ቋንቋ ሲናገሩ የምንሰማቸው እንዴት ቢሆን ነው? እኛ የጳርቴና፣ የሜድ፣ የኢላሜጤም ሰዎች፣ በመስጴጦምያ፣ በይሁዳ፣ በቀጰዶቅያ፣ በጳንጦስ፣ በእስያ፣ በፍርግያ፣ በጵንፍልያ፣ በግብጽ፣ በቀሬና አጠገብ ባሉት በሊቢያ አውራጃዎች የምንኖር፣ ከሮም የመጣን አይሁድና ወደ ይሁዲነት የገባን፣ የቀርጤስና የዐረብ ሰዎች ስንሆን፣ ሰዎቹ የእግዚአብሔርን ታላቅ ሥራ በየቋንቋችን ሲናገሩ እንሰማቸዋለን!” ሁሉም በአድናቆትና ግራ በመጋባት፣ “ይህ ነገር ምን ይሆን?” ተባባሉ። አንዳንዶቹ ደግሞ “ያልፈላ ብዙ የወይን ጠጅ ጠጥተዋል” በማለት አፌዙባቸው። በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ ከዐሥራ አንዱ ጋራ ተነሥቶ ቆመ፤ ድምፁንም ከፍ አድርጎ እንዲህ ሲል ለሕዝቡ ተናገረ፤ “እናንተ የይሁዳ ሰዎች፤ በኢየሩሳሌምም የምትኖሩ ሁሉ፤ ይህን አንድ ነገር ዕወቁ፤ በጥሞናም አድምጡ። ጊዜው ገና ከጧቱ ሦስት ሰዓት ስለ ሆነ፣ እናንተ እንደምታስቡት እነዚህ ሰዎች አልሰከሩም! ነገር ግን ይህ በነቢዩ በኢዩኤል እንዲህ ተብሎ የተነገረ ነው፤ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘በመጨረሻው ቀን፣ መንፈሴን በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ አፈስሳለሁ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁ ትንቢት ይናገራሉ፤ ጕልማሶቻችሁም ራእይ ያያሉ፤ ሽማግሌዎቻችሁም ሕልም ያልማሉ። በእነዚያ ቀናት በወንዶችና በሴቶች ባሮቼም ላይ፣ መንፈሴን አፈስሳለሁ፤ እነርሱም ትንቢት ይናገራሉ። በላይ በሰማያት ድንቅ ነገሮችን፣ አሳያለሁ፤ በታች በምድርም ምልክቶችን እሰጣለሁ፤ ደምና እሳት፣ የጢስም ዐምድ ይሆናል። ታላቁና ክቡር የሆነው የጌታ ቀን ከመምጣቱ በፊት፣ ፀሓይ ወደ ጨለማ፣ ጨረቃም ወደ ደም ይለወጣሉ። የጌታን ስም፣ የሚጠራ ሁሉ ይድናል።’ “የእስራኤል ሰዎች ሆይ፤ ይህን ቃል ስሙ፤ እናንተ ራሳችሁ እንደምታውቁት፣ እግዚአብሔር በመካከላችሁ ታምራትን፣ ድንቅ ነገሮችንና ምልክቶችን በርሱ በኩል በማድረግ ለናዝሬቱ ኢየሱስ መስክሮለታል። እግዚአብሔር በጥንት ውሳኔውና በቀደመው ዕውቀቱ ይህን ሰው አሳልፎ በእጃችሁ ሰጣችሁ፤ እናንተም በክፉ ሰዎች እጅ ሰቅላችሁ ገደላችሁት። እግዚአብሔር ግን የሞትን ጣር አስወግዶ አስነሣው፤ ሞት ይዞ ሊያስቀረው አልቻለምና። ዳዊትም ስለ እርሱ እንዲህ ይላል፤ “ ‘ጌታን ሁልጊዜ በፊቴ አየዋለሁ፤ እርሱ በቀኜ ነውና፣ ከቶ አልታወክም። ስለዚህ ልቤ ደስ አለው፤ አንደበቴም ሐሤት አደረገ፤ ሥጋዬም በተስፋ ይኖራል። ነፍሴን በሲኦል አትተዋትምና፤ ቅዱስህም መበስበስን እንዲያይ አትፈቅድም። የሕይወትን መንገድ እንዳውቅ አደረግኸኝ፤ በፊትህም በሐሤት ትሞላኛለህ።’ “ወንድሞች ሆይ፤ ከቀደምት አባቶች ዳዊት ሞቶ እንደ ተቀበረ፣ መቃብሩም እስከ ዛሬ ድረስ በመካከላችን እንደሚገኝ በድፍረት መናገር እችላለሁ። ነቢይ በመሆኑም፣ እግዚአብሔር ከዘሮቹ አንዱን በዙፋኑ ላይ እንደሚያስቀምጥ በመሐላ ቃል የገባለት መሆኑን ዐወቀ። ይህን አስቀድሞ በማየቱ እርሱ በሲኦል እንዳልቀረና ሥጋውም መበስበስን እንዳላየ ስለ ክርስቶስ ትንሣኤ ተናገረ። ይህን ኢየሱስ፣ እግዚአብሔር ከሞት አስነሣው፤ እኛም ሁላችን ለዚህ ነገር ምስክሮች ነን። ስለዚህ በእግዚአብሔር ቀኝ ከፍ ከፍ ካለ በኋላ፣ የመንፈስ ቅዱስን ተስፋ ከአብ ተቀብሎ አሁን የምታዩትንና የምትሰሙትን አፈሰሰው። ዳዊት ወደ ሰማያት አልወጣምና፤ እርሱ ራሱ ግን እንዲህ ብሏል፤ “ ‘ጌታ ጌታዬን፣ “ጠላቶችህን ለእግርህ መረገጫ፣ እስከማደርግልህ ድረስ፣ በቀኜ ተቀመጥ” አለው።’ “እንግዲህ፣ እግዚአብሔር ይህን እናንተ የሰቀላችሁትን ኢየሱስን፣ ጌታም ክርስቶስም እንዳደረገው የእስራኤል ወገን ሁሉ ይረዳ!” ሕዝቡም ይህን በሰሙ ጊዜ ልባቸው እጅግ ተነካ፤ ጴጥሮስንና ሌሎቹንም ሐዋርያት፣ “ወንድሞች ሆይ፤ ታዲያ ምን እናድርግ?” አሏቸው። ጴጥሮስም እንዲህ አላቸው፤ “ንስሓ ግቡ፤ ኀጢአታችሁም እንዲሰረይላችሁ፣ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ። የተስፋው ቃል ለእናንተና ለልጆቻችሁ እንዲሁም ጌታ አምላካችን ወደ ራሱ ለሚጠራቸው፣ በሩቅ ላሉትም ሁሉ ነውና።” በሌላ ብዙ ቃል እየመሰከረላቸው፣ “ከዚህ ጠማማ ትውልድ ራሳችሁን አድኑ” በማለት አስጠነቀቃቸው።
ሐዋርያት ሥራ 2:1-40 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በዓለ ኀምሳ የተባለውም ቀን በደረሰ ጊዜ፥ ሁሉም በአንድ ልብ ሆነው አብረው ሳሉ፥ ድንገት እንደሚነጥቅ ዓውሎ ነፋስ ከሰማይ ድምፅ መጣ፥ ተቀምጠው የነበሩበትንም ቤት ሁሉ ሞላው። እንደ እሳትም የተከፋፈሉ ልሳኖች ታዩአቸው፤ በያንዳንዳቸውም ላይ ተቀመጡባቸው። በሁሉም መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው፥ መንፈስም ይናገሩ ዘንድ እንደ ሰጣቸው በሌላ ልሳኖች ይናገሩ ጀመር። ከሰማይም በታች ካሉ ሕዝብ ሁሉ በጸሎት የተጉ አይሁድ በኢየሩሳሌም ይኖሩ ነበር፤ ይህም ድምፅ በሆነ ጊዜ ሕዝብ ሁሉ ተሰበሰቡ፥ እያንዳንዱም በገዛ ቋንቋው ሲናገሩ ይሰማ ስለ ነበር የሚሉትን አጡ። ተገርመውም ተደንቀውም እንዲህ አሉ፦ “እነሆ፥ እነዚህ የሚናገሩት ሁሉ የገሊላ ሰዎች አይደሉምን? እኛም እያንዳንዳችን የተወለድንበትን የገዛ ቋንቋ ችንን እንዴት እንሰማለን? የጳርቴና የሜድ የኢላሜጤም ሰዎች፥ በሁለት ወንዝም መካከል በይሁዳም በቀጰዶቅያም በጳንጦስም በእስያም፥ በፍርግያም በጵንፍልያም በግብፅም በቀሬናም በኩል ባሉት በሊቢያ ወረዳዎች የምንኖር፥ በሮሜም የምንቀመጥ፥ አይሁድም ወደ ይሁዲነትም የገባን፥ የቀርጤስና የዓረብ ሰዎች፥ የእግዚአብሔርን ታላቅ ሥራ በልሳኖቻችን ሲናገሩ እንሰማቸዋለን።” ሁሉም ተገረሙና አመንትተው እርስ በርሳቸው፦ “እንጃ ይህ ምን ይሆን?” አሉ። ሌሎች ግን እያፌዙባቸው፦ “ጉሽ የወይን ጠጅ ጠግበዋል” አሉ። ነገር ግን ጴጥሮስ ከአሥራ አንዱ ጋር ቆመ፥ ድምፁንም ከፍ አድርጎ እንዲህ ሲል ተናገራቸው፦ “አይሁድ በኢየሩሳሌምም የምትኖሩ ሁላችሁ፥ ይህ በእናንተ ዘንድ የታወቀ ይሁን፥ ቃሎቼንም አድምጡ። ለእናንተ እንደ መሰላችሁ እነዚህ የሰከሩ አይደሉም፥ ከቀኑ ሦስተኛ ሰዓት ነውና፤ ነገር ግን ይህ በነቢዩ በኢዩኤል የተባለው ነው፦ እግዚአብሔር ይላል፦ ‘በመጨረሻው ቀን እንዲህ ይሆናል፤ ሥጋ በለበሰ ሁሉ ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁም ትንቢት ይናገራሉ፥ ጎበዞቻችሁም ራእይ ያያሉ፥ ሽማግሌዎቻችሁም ሕልም ያልማሉ፤ ደግሞም በዚያች ወራት በወንዶችና በሴቶች ባሪያዎቼ ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ ትንቢትም ይናገራሉ። ድንቆችን በላይ በሰማይ፥ ምልክቶችንም በታች በምድር እሰጣለሁ፤ ደምም እሳትም የጢስ ጭጋግም ይሆናል፤ ታላቅ የሆነ የተሰማም የጌታ ቀን ሳይመጣ ፀሐይ ወደ ጨለማ ጨረቃም ወደ ደም ይለወጣሉ። የጌታን ስም የሚጠራም ሁሉ ይድናል።’ የእስራኤል ሰዎች ሆይ፥ ይህን ቃል ስሙ፤ ራሳችሁ እንደምታውቁ፥ የናዝሬቱ ኢየሱስ እግዚአብሔር በመካከላችሁ በእርሱ በኩል ባደረገው ተአምራትና በድንቆች በምልክቶችም ከእግዚአብሔር ዘንድ ለእናንተ የተገለጠ ሰው ነበረ፤ እርሱንም በእግዚአብሔር በተወሰነው አሳቡና በቀደመው እውቀቱ ተሰጥቶ በዓመፀኞች እጅ ሰቅላችሁ ገደላችሁት። እግዚአብሔር ግን የሞትን ጣር አጥፍቶ አስነሣው፥ ሞት ይይዘው ዘንድ አልቻለምና። ዳዊት ስለ እርሱ እንዲህ ይላልና፦ ‘ጌታን ሁልጊዜ በፊቴ አየሁት፥ እንዳልታወክ በቀኜ ነውና። ስለዚህ ልቤን ደስ አለው፥ ልሳኔም ሐሤት አደረገ፥ ደግሞም ሥጋዬ በተስፋ ያድራል፤ ነፍሴን በሲኦል አትተዋትምና፥ ቅዱስህንም መበስበስን ያይ ዘንድ አትሰጠውም። የሕይወትን መንገድ አስታወቅኸኝ፤ ከፊትህ ጋር ደስታን ትሞላብኛለህ።’ ወንድሞች ሆይ፥ ስለ አባቶች አለቃ ስለ ዳዊት እንደ ሞተም እንደ ተቀበረም ለእናንተ በግልጥ እናገር ዘንድ ፍቀዱልኝ፤ መቃብሩም እስከ ዛሬ በእኛ ዘንድ ነው። ነቢይ ስለ ሆነ፥ ከወገቡም ፍሬ በዙፋኑ ያስቀምጥ ዘንድ እግዚአብሔር መሐላ እንደ ማለለት ስለ አወቀ፥ ስለ ክርስቶስ ትንሣኤ አስቀድሞ አይቶ፥ ነፍሱ በሲኦል እንዳልቀረች ሥጋውም መበስበስን እንዳላየ ተናገረ። ይህን ኢየሱስን እግዚአብሔር አስነሣው ለዚህም ነገር እኛ ሁላችን ምስክሮች ነን፤ ስለዚህ በእግዚአብሔር ቀኝ ከፍ ከፍ ብሎና የመንፈስ ቅዱስን የተስፋ ቃል ከአብ ተቀብሎ ይህን እናንተ አሁን የምታዩትንና የምትሰሙትን አፈሰሰው። ዳዊት ወደ ሰማያት አልወጣምና፥ ነገር ግን እርሱ፦ ‘ጌታ ጌታዬን፦ ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው።’ አለ። እንግዲህ ይህን እናንተ የሰቀላችሁትን ኢየሱስን እግዚአብሔር ጌታም ክርስቶስም እንዳደረገው የእእራኤል ወገን ሁሉ በእርግጥ ይወቅ።” ይህንም በሰሙ ጊዜ ልባቸው ተነካ፥ ጴጥሮስንና ሌሎችንም ሐዋርያት፦ “ወንድሞች ሆይ፥ ምን እናድርግ?” አሉአቸው። ጴጥሮስም፦ “ንስሐ ግቡ፥ ኃጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ። የተስፋው ቃል ለእናንተና ለልጆቻችሁ ጌታ አምላካችንም ወደ እርሱ ለሚጠራቸው በሩቅ ላሉ ሁሉ ነውና” አላቸው። በብዙ ሌላ ቃልም መሰከረና፦ “ከዚህ ጠማማ ትውልድ ዳኑ” ብሎ መከራቸው።
ሐዋርያት ሥራ 2:1-40 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
የጰንጠቆስጤ በዓል በደረሰ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ሁሉ በአንድነት በአንድ ቦታ ተሰብስበው ነበር፤ በድንገት ብርቱ ዐውሎ ነፋስ የመሰለ ድምፅ ከሰማይ መጣ፤ የነበሩበትንም ቤት ሞላው። የእሳት ነበልባሎች የሚመስሉ ልሳኖች ታዩአቸው፤ ተከፋፍለውም በእያንዳንዳቸው ላይ ዐረፉባቸው። ሁሉም በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ፤ መንፈስ ቅዱስ እንዲናገሩ በሰጣቸው ችሎታ መጠን በሌሎች ቋንቋዎች መናገር ጀመሩ። በዓለም ካሉት አገሮች ሁሉ የመጡ፥ በጸሎት የተጉ አይሁድ በኢየሩሳሌም ይኖሩ ነበር። ይህንንም ድምፅ በሰሙ ጊዜ ብዙ ሰዎች ተሰበሰቡ፤ በየቋንቋቸውም ሲናገሩ ስለ ሰሙአቸው ተደነቁ። በመገረምና በመደነቅም እንዲህ አሉ፤ “እነዚህ እንዲህ የሚናገሩት ሁሉ የገሊላ ሰዎች አይደሉምን? ታዲያ፥ እኛ በየትውልድ አገራችን ቋንቋ ሲናገሩ የምንሰማቸው እንዴት ነው? እኛ በጳርቴ፥ በሜድ፥ በዔላም፥ በመስጴጦምያ፥ በይሁዳ፥ በቀጰዶቅያ፥ በጳንጦስ፥ በእስያ፥ በፍርግያ፥ በጵንፍልያ፥ በግብጽ፥ በቀሬና አጠገብ ባሉት በሊቢያ አውራጃዎች የምንኖር ነን፤ ከሮምም የመጣን አይሁድና ወደ አይሁድነትም የገባን እንገኛለን፤ እንዲሁም የቀርጤስና የዐረብ ሰዎች ይገኛሉ፤ እነሆ፥ እነዚህ ሁሉ የእግዚአብሔርን ታላቅ ሥራ በየቋንቋችን ሲናገሩ እንሰማለን!” ስለዚህ ሁሉም ተገርመውና የሚሉትን አጥተው “ይህ ነገር ምን ይሆን!” ተባባሉ። አንዳንዶቹ ግን “አዲስ የወይን ጠጅ ጠጥተው ሰክረዋል!” እያሉ አፌዙባቸው። በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ ከዐሥራ አንዱ ጋር ቆመና ድምፁን ከፍ አድርጎ ለሕዝቡ እንዲህ ሲል ተናገረ፦ “እናንተ የይሁዳ ምድር ሰዎችና የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ሁሉ፥ ይህን የሆነውን ነገር ለማወቅ ንግግሬን አዳምጡ፤ ከጠዋቱ ገና ሦስት ሰዓት ስለ ሆነ እናንተ እንዳሰባችሁት እነዚህ ሰዎች አልሰከሩም። ነገር ግን ይህ የሆነው ነቢዩ ኢዩኤል እንዲህ ሲል የተናገረው ቃል እንዲፈጸም ነው፤ ‘እግዚአብሔር በመጨረሻው ቀን እንዲህ ይሆናል ይላል፤ መንፈሴን በሰው ሁሉ ላይ አፈሳለሁ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁ ትንቢት ይናገራሉ፤ ጐልማሶቻችሁም ራእይ ያያሉ፤ ሽማግሌዎቻችሁም ሕልም ያልማሉ። እንዲሁም በእነዚያ ቀኖች በወንዶችና በሴቶች አገልጋዮቼ ላይ መንፈሴን አፈሳለሁ፤ እነርሱም ትንቢት ይናገራሉ። በላይ በሰማይ ድንቅ ነገሮችን፥ በታች በምድር ተአምራትን አሳያለሁ፤ ደም፥ እሳት፥ የጢስ ጭጋግም ይታያል። ታላቁና አስገራሚው የጌታ ቀን ከመምጣቱ በፊት፥ ፀሐይ ይጨልማል፤ ጨረቃም ደም ትመስላለች። የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል።’ “የእስራኤል ሰዎች ሆይ! ይህን ቃል አዳምጡ፤ እናንተ ራሳችሁ እንደምታውቁት የናዝሬቱ የኢየሱስ ማንነት እግዚአብሔር በእናንተ መካከል በእርሱ አማካይነት በፈጸማቸው ታላላቅ ሥራዎች፥ ተአምራትና ምልክቶች ተረጋግጦአል። እርሱም ራሱ እግዚአብሔር አስቀድሞ ባቀደውና ባወቀው አሠራር መሠረት ለእናንተ ተላልፎ ተሰጠ፤ እናንተም በዐመፀኞች እጅ እንዲሰቀልና እንዲሞት አደረጋችሁት። እግዚአብሔር ግን የሞትን ኀይል አስወግዶ ከሞት አስነሣው፤ ስለዚህም ሞት ይዞ ሊያስቀረው አልቻለም። ዳዊትም ስለ እርሱ እንዲህ ይላል፦ ‘ጌታን ሁልጊዜ በፊቴ አየዋለሁ፤ እንዳልናወጥም እርሱ በቀኜ ነው ስለዚህ ልቤን ደስ አለው፤ አንደበቴም በደስታ ተሞላ፤ እንዲሁም ሟች የሆነው ሥጋዬ በተስፋ ይኖራል፤ ነፍሴን በሲኦል አትተዋትም፤ ቅዱስህንም በመቃብር በስብሶ እንዲቀር አታደርገውም። የሕይወትን መንገድ አስታወቅኸኝ፤ ከእኔም ጋር በመሆንህ ደስታዬ ፍጹም ይሆናል።’ “ወንድሞቼ ሆይ! ከቀድሞ አባቶች አንዱ የሆነው ዳዊት እንደ ሞተና እንደ ተቀበረ፥ መቃብሩም እስከ ዛሬ በእኛ ዘንድ እንዳለ በግልጥ ልንገራችሁ። ነገር ግን ዳዊት ይህን የተናገረው ነቢይ ስለ ነበረና እግዚአብሔር ‘ከዘርህ አንዱን በዙፋንህ ላይ አስቀምጥልሃለሁ’ ሲል በመሐላ የሰጠውን የተስፋ ቃል ያውቅ ስለ ነበር ነው፤ በዚህም ምክንያት መሲሕ በሲኦል እንደማይቀርና ሥጋውም በመቃብር በስብሶ እንደማይቀር አስቀድሞ አይቶ ስለ ትንሣኤው ተናገረ። ይህን ኢየሱስን እግዚአብሔር ከሞት አስነሣው፤ እኛም ሁላችን ለዚህ ነገር ምስክሮች ነን። በእግዚአብሔር ቀኝ ለመቀመጥ ከፍ ባለ ጊዜና የመንፈስ ቅዱስን ተስፋ ከአብ በተቀበለ ጊዜ ይህን የምታዩትንና የምትሰሙትን አፈሰሰው። እንግዲህ ወደ ሰማይ የወጣው ዳዊት ባለመሆኑ ዳዊት ራሱ እንዲህ ሲል ተናግሮአል፤ ‘ጌታ ለጌታዬ (ለመሲሑ) ጠላቶችህን በሥልጣንህ ሥር እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ’ ብሎታል። “እንግዲህ ይህን እናንተ የሰቀላችሁትን ኢየሱስን እግዚአብሔር ጌታና መሲሕ እንዳደረገው የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ በእርግጥ ይወቅ!” ሰዎቹም ይህን በሰሙ ጊዜ ልባቸው በሐዘን ተነክቶ ጴጥሮስንና ሌሎቹን ሐዋርያት፥ “ወንድሞች ሆይ! እንግዲህ ምን እናድርግ?” አሉአቸው። ጴጥሮስም እንዲህ አላቸው፤ “ንስሓ ግቡ፤ ኃጢአታችሁም ይቅር እንዲባልላችሁ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የእግዚአብሔር ስጦታ የሆነውን መንፈስ ቅዱስንም ትቀበላላችሁ፤ የተስፋው ቃል ለእናንተና ለልጆቻችሁ፥ ጌታ አምላካችን ወደ እርሱ ለሚጠራቸው፥ በሩቅ ላሉትም ሁሉ ነው።” በሌላም በብዙ ቃል እየመሰከረ፥ “በዚህ ጠማማ ትውልድ ላይ ከሚመጣው ቅጣት ራሳችሁን አድኑ!” በማለት መከራቸው።
ሐዋርያት ሥራ 2:1-40 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በዓለ ኀምሳ የተባለውም ቀን በደረሰ ጊዜ፥ ሁሉም በአንድ ልብ ሆነው አብረው ሳሉ፥ ድንገት እንደሚነጥቅ ዓውሎ ነፋስ ከሰማይ ድምፅ መጣ፤ ተቀምጠው የነበሩበትንም ቤት ሁሉ ሞላው። እንደ እሳትም የተከፋፈሉ ልሳኖች ታዩአቸው፤ በያንዳንዳቸውም ላይ ተቀመጡባቸው። በሁሉም መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው፤ መንፈስም ይናገሩ ዘንድ እንደሰጣቸው በሌላ ልሳኖች ይናገሩ ጀመር። ከሰማይም በታች ካሉ ሕዝብ ሁሉ በጸሎት የተጉ አይሁድ በኢየሩሳሌም ይኖሩ ነበር፤ ይህም ድምፅ በሆነ ጊዜ ሕዝብ ሁሉ ተሰበሰቡ፤ እያንዳንዱም በገዛ ቋንቋው ሲናገሩ ይሰማ ስለ ነበር የሚሉትን አጡ። ተገርመውም ተደንቀውም እንዲህ አሉ “እነሆ፥ እነዚህ የሚናገሩት ሁሉ የገሊላ ሰዎች አይደሉምን? እኛም እያንዳንዳችን የተወለድንበትን የገዛ ቋንቋ ችንን እንዴት እንሰማለን? የጳርቴና የሜድ የኢላሜጤም ሰዎች፥ በመስጴጦምያም በይሁዳም በቀጰዶቅያም በጳንጦስም በእስያም፥ በፍርግያም በጵንፍልያም በግብጽም በቀሬናም በኩል ባሉት በሊቢያ ወረዳዎች የምንኖር፥ በሮሜም የምንቀመጥ፥ አይሁድም ወደ ይሁዲነትም የገባን፥ የቀርጤስና የዓረብ ሰዎች፥ የእግዚአብሔርን ታላቅ ሥራ በልሳኖቻችን ሲናገሩ እንሰማቸዋለን።” ሁሉም ተገረሙና አመንትተው እርስ በርሳቸው “እንጃ ይህ ምን ይሆን?” አሉ። ሌሎች ግን እያፌዙባቸው “ጉሽ የወይን ጠጅ ጠግበዋል፤” አሉ። ነገር ግን ጴጥሮስ ከዐሥራ አንዱ ጋር ቆመ፤ ድምፁንም ከፍ አድርጎ እንዲህ ሲል ተናገራቸው “የይሁዳ ሰዎችና በኢየሩሳሌም የምትኖሩ ሁላችሁ፥ ይህ በእናንተ ዘንድ የታወቀ ይሁን፤ ቃሎቼንም አድምጡ። ለእናንተ እንደ መሰላችሁ እነዚህ የሰከሩ አይደሉም፤ ከቀኑ ሦስተኛ ሰዓት ነውና፤ ነገር ግን ይህ በነቢዩ በኢዩኤል የተባለው ነው፤ “እግዚአብሔር ይላል ‘በመጨረሻው ቀን እንዲህ ይሆናል፤ ሥጋ በለበሰ ሁሉ ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁም ትንቢት ይናገራሉ፤ ጎበዞቻችሁም ራእይ ያያሉ፤ ሽማግሌዎቻችሁም ሕልም ያልማሉ፤ ደግሞም በዚያች ወራት በወንዶችና በሴቶች ባርያዎቼ ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ፤ ትንቢትም ይናገራሉ። ድንቆችን በላይ በሰማይ፥ ምልክቶችንም በታች በምድር እሰጣለሁ፤ ደምም እሳትም የጢስ ጭጋግም ይሆናል፤ ታላቅ የሆነ የተሰማም የጌታ ቀን ሳይመጣ ፀሐይ ወደ ጨለማ ጨረቃም ወደ ደም ይለወጣሉ። የጌታን ስም የሚጠራም ሁሉ ይድናል።’ “የእስራኤል ሰዎች ሆይ! ይህን ቃል ስሙ፤ ራሳችሁ እንደምታውቁት፥ የናዝሬቱ ኢየሱስ እግዚአብሔር በመካከላችሁ በእርሱ በኩል ባደረገው ተአምራትና በድንቆች በምልክቶችም ከእግዚአብሔር ዘንድ ለእናንተ የተገለጠ ሰው ነበረ፤ እርሱንም በእግዚአብሔር በተወሰነው አሳቡና በቀደመው እውቀቱ ተሰጥቶ በዐመፀኞች እጅ ሰቅላችሁ ገደላችሁት። እግዚአብሔር ግን የሞትን ጣር አጥፍቶ አስነሣው፤ ሞት ይይዘው ዘንድ አልቻለምና። ዳዊት ስለ እርሱ እንዲህ ይላልና “ጌታን ሁልጊዜ በፊቴ አየሁት፤ እንዳልታወክ በቀኜ ነውና። ስለዚህ ልቤን ደስ አለው፤ ልሳኔም ሐሤት አደረገ፤ ደግሞም ሥጋዬ በተስፋ ያድራል፤ ነፍሴን በሲኦል አትተዋትምና፤ ቅዱስህንም መበስበስን ያይ ዘንድ አትሰጠውም። የሕይወትን መንገድ አስታወቅኸኝ፤ ከፊትህ ጋር ደስታን ትሞላብኛለህ።” ወንድሞች ሆይ! ስለ አባቶች አለቃ ስለ ዳዊት እንደ ሞተም እንደ ተቀበረም ለእናንተ በግልጥ እናገር ዘንድ ፍቀዱልኝ፤ መቃብሩም እስከ ዛሬ በእኛ ዘንድ ነው። ነቢይ ስለ ሆነ፥ ከወገቡም ፍሬ በዙፋኑ ያስቀምጥ ዘንድ እግዚአብሔር መሐላ እንደማለለት ስለ አወቀ፥ ስለ ክርስቶስ ትንሣኤ አስቀድሞ አይቶ፥ ነፍሱ በሲኦል እንዳልቀረች ሥጋውም መበስበስን እንዳላየ ተናገረ። ይህን ኢየሱስን እግዚአብሔር አስነሣው፤ ለዚህም ነገር እኛ ሁላችን ምስክሮች ነን፤ ስለዚህ በእግዚአብሔር ቀኝ ከፍ ከፍ ብሎና የመንፈስ ቅዱስን የተስፋ ቃል ከአብ ተቀብሎ ይህን እናንተ አሁን የምታዩትንና የምትሰሙትን አፈሰሰው። ዳዊት ወደ ሰማያት አልወጣምና፤ ነገር ግን እርሱ እንዳለው፦ ጌታ ጌታዬን በቀኜ ተቀመጥ፤ “ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስካደርግልህ ድረስ!” “እንግዲህ ይህን እናንተ የሰቀላችሁትን ኢየሱስን እግዚአብሔር ጌታም ክርስቶስም እንዳደረገው የእእራኤል ወገን ሁሉ በእርግጥ ይወቅ።” ይህንም በሰሙ ጊዜ ልባቸው ተሰበረ፤ ጴጥሮስንና ሌሎችንም ሐዋርያት “ወንድሞች ሆይ! ምን እናድርግ?” አሉአቸው። ጴጥሮስም “ንስሐ ግቡ፤ ኀጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ። የተስፋው ቃል ለእናንተና ለልጆቻችሁ ጌታ አምላካችንም ወደ እርሱ ለሚጠራቸው በሩቅ ላሉ ሁሉ ነውና፤” አላቸው። በብዙ ሌላ ቃልም መሰከረና “ከዚህ ጠማማ ትውልድ ዳኑ፤” ብሎ መከራቸው።