ሐዋርያት ሥራ 19:11-20
ሐዋርያት ሥራ 19:11-20 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እግዚአብሔርም በጳውሎስ እጅ ታላላቅ ሥራን ይሠራ ነበር። ከልብሱ ዘርፍና ከመጠምጠሚያዉ ጫፍ ቈርጠው እየወሰዱ በድውያኑ ላይ ያኖሩት ነበር፤ እነርሱም ይፈወሱ ነበር፤ ክፉዎች መናፍስትም ይወጡ ነበር። ከአይሁድም አስማት እያደረጉ የሚዞሩ ሰዎች ክፉዎች መናፍስት ባሉባቸው ላይ “ጳውሎስ በሚያስተምርበት በኢየሱስ ስም እናምላችኋለን” እያሉ የጌታችን የኢየሱስን ስም ይጠሩባቸው ነበር። እኒህ እንዲህ ያደርጉ የነበሩትም የካህናቱ አለቃ የአይሁዳዊው የአስቂዋ ልጆች ናቸው፤ እነርሱም ሰባት ነበሩ። ያም ክፉ መንፈስ፥ “በኢየሱስ አምናለሁ፥ ጳውሎስንም አውቀዋለሁ፤ እንግዲህ እናንተ እነማን ናችሁ?” ብሎ መለሰላቸው። ያም ክፉ መንፈስ የያዘው ሰው ተነሣባቸው፤ አየለባቸውም፤ አሸነፋቸውም፤ አቍስሎም ከዚያ ቤት አስወጥቶ አባረራቸው። ይህም ነገር በኤፌሶን በሚኖሩ በአይሁድና በአረማውያን ሁሉ ዘንድ ተሰማ፤ ሁሉም ፈሩ፤ የጌታችን የኢየሱስንም ስም ከፍ ከፍ አደረጉ። ያመኑትም ሁሉ እየመጡ ስለ ሠሩት ንስሓ ይገቡ ነበር። ብዙዎች አስማተኞችም መጽሐፎቻቸውን እየሰበሰቡ እያመጡ በሕዝቡ ሁሉ ፊት በእሳት ያቃጥሉ ነበር፤ ያቃጠሏቸው የመጽሐፎች ዋጋም አምሳ ሺህ ብር ነበር። እንዲህም እያለ የእግዚአብሔር ቃል በኀይል ያድግና ይበረታ ነበር።
ሐዋርያት ሥራ 19:11-20 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እግዚአብሔርም በጳውሎስ እጅ እጅግ የሚያስደንቅ ታምራትን ያደርግ ነበር፤ መሐረብ ወይም ሰውነቱን የነካ ጨርቅ እንኳ ወደ ሕመምተኞች ሲወስዱ በሽታቸው ይለቅቃቸው ነበር፤ ርኩሳን መናፍስትም ይወጡ ነበር። እየዞሩ አጋንንትን ያስወጡ ከነበሩት አይሁድ አንዳንዶቹ፣ “ጳውሎስ በሚሰብከው በኢየሱስ ስም እንድትወጡ አዝዛችኋለሁ” እያሉ የጌታን የኢየሱስን ስም ርኩሳን መናፍስት በያዟቸው ሰዎች ላይ ለመጥራት ሞከሩ፤ የአይሁዳዊው የካህናቱ አለቃ የአስቄዋ ሰባት ወንዶች ልጆችም ይህንኑ ያደርጉ ነበር። ርኩስ መንፈሱም፣ “ኢየሱስን ዐውቀዋለሁ፤ ጳውሎስንም ዐውቀዋለሁ፤ እናንተ ግን እነማን ናችሁ?” አላቸው። ከዚያም ርኩስ መንፈስ ያደረበት ሰው ዘልሎ ያዛቸው፤ በረታባቸውም፤ እጅግ ስላየለባቸውም ቤቱን ጥለው ዕራቍታቸውን ሸሹ። ይህም በኤፌሶን በሚኖሩት፣ በአይሁድና በግሪክ ሰዎች ሁሉ ዘንድ በታወቀ ጊዜ፣ ሁሉም ፍርሀት ያዛቸው፤ በዚህም የጌታ የኢየሱስ ስም ተከበረ። ካመኑትም ሰዎች ብዙዎቹ እየቀረቡ ክፉ ሥራቸውን በግልጽ ተናዘዙ፤ ሲጠነቍሉ ከነበሩትም መካከል ብዙዎች መጽሐፋቸውን ሰብስበው በማምጣት በሕዝብ ፊት አቃጠሉ፤ ዋጋቸውም ሲሰላ ዐምሳ ሺሕ ብር ያህል ሆኖ ተገኘ። በዚህ ሁኔታ የጌታ ቃል በኀይል እያደገና እያሸነፈ ሄደ።
ሐዋርያት ሥራ 19:11-20 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እግዚአብሔርም በጳውሎስ እጅ የሚያስገርም ተአምራት ያደርግ ነበር፤ ስለዚህም ከአካሉ ጨርቅ ወይም ልብስ ወደ ድውዮች ይወስዱ ነበር፥ ደዌያቸውም ይለቃቸው ነበር ክፉዎች መናፍስትም ይወጡ ነበር። አጋንንትንም እያወጡ ይዞሩ ከነበሩት አይሁድ አንዳንዶች፦ ጳውሎስ በሚሰብከው በኢየሱስ እናምላችኋለን እያሉ ክፉዎች መናፍስት ባሉባቸው ላይ የጌታን የኢየሱስን ስም ይጠሩባቸው ዘንድ ሞከሩ። የካህናትም አለቃ ለሆነ አስቄዋ ለሚሉት ለአንድ አይሁዳዊ ይህን ያደረጉ ሰባት ልጆች ነበሩት። ክፉው መንፈስ ግን መልሶ፦ ኢየሱስንስ አውቀዋለሁ ጳውሎስንም አውቀዋለሁ፤ እናንተሳ እነማን ናችሁ? አላቸው። ክፉው መንፈስም ያለበት ሰው ዘለለባቸው ቆስለውም ከዚያ ቤት ዕራቁታቸውን እስኪሸሹ ድረስ በረታባቸው አሸነፋቸውም። ይህም በኤፌሶን በሚኖሩት ሁሉ በአይሁድና በግሪክ ሰዎች ዘንድ የታወቀ ሆነ፥ በሁላቸውም ላይ ፍርሃት ወደቀባቸው፥ የጌታም የኢየሱስ ስም ተከበረ፤ አምነውም ከነበሩት እጅግ ሰዎች ያደረጉትን እየተናዘዙና እየተናገሩ ይመጡ ነበር። ከአስማተኞችም ብዙዎቹ መጽሐፋቸውን ሰብስበው በሰው ሁሉ ፊት አቃጠሉት፤ ዋጋውም ቢታሰብ አምሳ ሺህ ብር ሆኖ ተገኘ። እንዲህም የጌታ ቃል በኃይል ያድግና ያሸንፍ ነበር።
ሐዋርያት ሥራ 19:11-20 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔር በጣም አስደናቂ የሆኑ ተአምራትን በጳውሎስ እጅ ያደርግ ነበር። በዚህም ምክንያት የጳውሎስን አካል የነካውን ልብስና መሐረብ እየወሰዱ በሽተኞቹን ሲያስነኩአቸው ከበሽታቸው ይፈወሱ ነበር፤ ርኩሳን መናፍስትም ይወጡላቸው ነበር። አጋንንትን ከሰዎች እያስወጡ በየቦታው የሚዞሩ አንዳንድ አይሁድ “ጳውሎስ በሚሰብከው በጌታ ኢየሱስ ስም እንድትወጡ እናዛችኋለን” በማለት አጋንንትን ከሰዎች ለማስወጣት ይሞክሩ ነበር። የአይሁድ ሊቀ ካህናት የሆነ የአስቄዋ ሰባት ልጆችም እንዲሁ ያደርጉ ነበር። ነገር ግን ርኩሱ መንፈስ “ኢየሱስን ዐውቃለሁ! ጳውሎስንም ዐውቃለሁ! ኧረ እናንተ እነማን ናችሁ?” አላቸው። አንድ ርኩስ መንፈስ ያደረበትም ሰው ዘሎ በማነቅ በረታባቸው፤ አሸነፋቸውም፤ ቈስለውና ራቊታቸውን ሆነው ከቤት ሸሽተው ወጡ። ይህም ነገር በኤፌሶን በሚኖሩት አይሁድና አሕዛብ ዘንድ ስለ ተሰማ ሁሉም ፈሩ፤ የጌታ የኢየሱስም ስም እጅግ ገናና ሆነ። ከአማኞችም ብዙዎቹ ክፉ ሥራቸውን በግልጥ እየተናዘዙ ይመጡ ነበር። ብዙ አስማተኞችም የአስማት መጽሐፎቻቸውን ሰብስበው በሕዝቡ ሁሉ ፊት አቃጠሉአቸው፤ የመጽሐፎቹ ዋጋ ሲተመን ኀምሳ ሺህ ጥሬ ብር ሆኖ ተገኘ። በዚህ ዐይነት የጌታ ቃል በጣም እየተስፋፋና ድል እያደረገ ይሄድ ነበር።
ሐዋርያት ሥራ 19:11-20 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እግዚአብሔርም በጳውሎስ እጅ የሚያስገርም ተአምራት ያደርግ ነበር፤ ስለዚህም ከአካሉ ጨርቅ ወይም ልብስ ወደ ድውዮችይወስዱ ነበር፤ ደዌያቸውም ይለቃቸው ነበር ክፉዎች መናፍስትም ይወጡ ነበር። አጋንንትንም እያወጡ ይዞሩ ከነበሩት አይሁድ አንዳንዶች “ጳውሎስ በሚሰብከው በኢየሱስ እናምላችኋለን፤” እያሉ ክፉዎች መናፍስት ባሉባቸው ላይ የጌታን የኢየሱስን ስም ይጠሩባቸው ዘንድ ሞከሩ። የካህናትም አለቃ ለሆነ አስቄዋ ለሚሉት ለአንድ አይሁዳዊ ይህን ያደረጉ ሰባት ልጆች ነበሩት። ክፉው መንፈስ ግን መልሶ “ኢየሱስንስ አውቀዋለሁ፤ ጳውሎስንም አውቀዋለሁ፤ እናንተሳ እነማን ናችሁ?” አላቸው። ክፉው መንፈስም ያለበት ሰው ዘለለባቸው፤ ቆስለውም ከዚያ ቤት ዕራቁታቸውን እስኪሸሹ ድረስ በረታባቸው፤ አሸነፋቸውም። ይህም በኤፌሶን በሚኖሩት ሁሉ በአይሁድና በግሪክ ሰዎች ዘንድ የታወቀ ሆነ፤ በሁላቸውም ላይ ፍርሃት ወደቀባቸው፤ የጌታም የኢየሱስ ስም ተከበረ፤ አምነውም ከነበሩት እጅግ ሰዎች ያደረጉትን እየተናዘዙና እየተናገሩ ይመጡ ነበር። ከአስማተኞችም ብዙዎቹ መጽሐፋቸውን ሰብስበው በሰው ሁሉ ፊት አቃጠሉት፤ ዋጋውም ቢታሰብ አምሳ ሺህ ብር ሆኖ ተገኘ። እንዲህም የጌታ ቃል በኃይል ያድግና ያሸንፍ ነበር።