ሐዋርያት ሥራ 19:1-41 - Compare All Versions

ሐዋርያት ሥራ 19:1-41 NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)

አጵሎስ በቆሮንቶስ በነበረበት ጊዜ፣ ጳውሎስ በላይኛው አገር ዐልፎ ወደ ኤፌሶን መጣ፤ በዚያም አንዳንድ ደቀ መዛሙርትን አግኝቶ፣ “ባመናችሁ ጊዜ መንፈስ ቅዱስን ተቀበላችሁን?” አላቸው። እነርሱም፣ “አልተቀበልንም፤ እንዲያውም መንፈስ ቅዱስ መኖሩን እንኳ አልሰማንም” አሉት። ጳውሎስም፣ “ታዲያ፣ በምን ተጠመቃችሁ?” አላቸው። እነርሱም፣ “የዮሐንስን ጥምቀት” አሉት። ጳውሎስም፣ “የዮሐንስ ጥምቀትማ የንስሓ ጥምቀት ነበር፤ ዮሐንስም ራሱ ሰዎች ከርሱ በኋላ በሚመጣው በኢየሱስ እንዲያምኑ ተናግሯል” አላቸው። እነርሱም ይህን በሰሙ ጊዜ በጌታ በኢየሱስ ስም ተጠመቁ። ጳውሎስም እጁን በላያቸው በጫነ ጊዜ፣ መንፈስ ቅዱስ ወረደባቸው፤ በሌሎች ቋንቋዎች ተናገሩ፤ ትንቢትም ተናገሩ። ሰዎቹም በአጠቃላይ ዐሥራ ሁለት ያህል ነበሩ። ጳውሎስም ወደ ምኵራብ እየገባ፣ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት እየተነጋገረና እያሳመናቸው ሦስት ወር ሙሉ ምንም ሳይፈራ ፊት ለፊት ይናገር ነበር። አንዳንዶቹ ግን ግትር በመሆን፣ ለማመን ፈቃደኞች አልነበሩም፤ የጌታንም መንገድ በገሃድ ያጥላሉ ነበር። ስለዚህ ጳውሎስ ትቷቸው ሄደ፤ ደቀ መዛሙርትንም ለብቻቸው ወስዶ በጢራኖስ የትምህርት አዳራሽ ውስጥ በየዕለቱ ያነጋግራቸው ነበር። ይህን ማድረጉንም ሁለት ዓመት ስለ ቀጠለ፣ በእስያ አውራጃ ይኖሩ የነበሩት የአይሁድና የግሪክ ሰዎች ሁሉ የጌታን ቃል ለመስማት ቻሉ። እግዚአብሔርም በጳውሎስ እጅ እጅግ የሚያስደንቅ ታምራትን ያደርግ ነበር፤ መሐረብ ወይም ሰውነቱን የነካ ጨርቅ እንኳ ወደ ሕመምተኞች ሲወስዱ በሽታቸው ይለቅቃቸው ነበር፤ ርኩሳን መናፍስትም ይወጡ ነበር። እየዞሩ አጋንንትን ያስወጡ ከነበሩት አይሁድ አንዳንዶቹ፣ “ጳውሎስ በሚሰብከው በኢየሱስ ስም እንድትወጡ አዝዛችኋለሁ” እያሉ የጌታን የኢየሱስን ስም ርኩሳን መናፍስት በያዟቸው ሰዎች ላይ ለመጥራት ሞከሩ፤ የአይሁዳዊው የካህናቱ አለቃ የአስቄዋ ሰባት ወንዶች ልጆችም ይህንኑ ያደርጉ ነበር። ርኩስ መንፈሱም፣ “ኢየሱስን ዐውቀዋለሁ፤ ጳውሎስንም ዐውቀዋለሁ፤ እናንተ ግን እነማን ናችሁ?” አላቸው። ከዚያም ርኩስ መንፈስ ያደረበት ሰው ዘልሎ ያዛቸው፤ በረታባቸውም፤ እጅግ ስላየለባቸውም ቤቱን ጥለው ዕራቍታቸውን ሸሹ። ይህም በኤፌሶን በሚኖሩት፣ በአይሁድና በግሪክ ሰዎች ሁሉ ዘንድ በታወቀ ጊዜ፣ ሁሉም ፍርሀት ያዛቸው፤ በዚህም የጌታ የኢየሱስ ስም ተከበረ። ካመኑትም ሰዎች ብዙዎቹ እየቀረቡ ክፉ ሥራቸውን በግልጽ ተናዘዙ፤ ሲጠነቍሉ ከነበሩትም መካከል ብዙዎች መጽሐፋቸውን ሰብስበው በማምጣት በሕዝብ ፊት አቃጠሉ፤ ዋጋቸውም ሲሰላ ዐምሳ ሺሕ ብር ያህል ሆኖ ተገኘ። በዚህ ሁኔታ የጌታ ቃል በኀይል እያደገና እያሸነፈ ሄደ። ይህ ሁሉ ከሆነ በኋላ፣ ጳውሎስ በመቄዶንያና በአካይያ በኩል ዐልፎ ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ በመንፈሱ ወስኖ፣ “እዚያ ከደረስሁ በኋላ ሮምን ደግሞ ማየት አለብኝ” አለ። ከረዳቶቹም ሁለቱን፣ ጢሞቴዎስንና ኤርስጦንን፣ ወደ መቄዶንያ ልኮ እርሱ ራሱ ግን በእስያ አውራጃ ጥቂት ቀን ተቀመጠ። በዚህ ጊዜ፣ ስለ ጌታ መንገድ ታላቅ ሁከት ተፈጠረ። ድሜጥሮስ የተባለ አንድ የብር አንጥረኛ የአርጤምስን ቤተ መቅደስ ምስሎች ከብር ቀጥቅጦ እየሠራ ለሠራተኞቹ የሚያስገኘው ገቢ ቀላል አልነበረም። እርሱም እነዚህን ሠራተኞችና በተመሳሳይ ሙያ የሚተዳደሩትን ሌሎቹን ሰዎች በአንድነት ሰብስቦ እንዲህ አላቸው፤ “ሰዎች ሆይ፤ ይህ ሥራ ጥሩ ገቢ እንደሚያስገኝልን ታውቃላችሁ። ይህ ጳውሎስ የተባለ ሰው በኤፌሶን ብቻ ሳይሆን፣ በመላው የእስያ አውራጃ የሚገኘውን በርካታ ሕዝብ እያሳመነ እንዳሳታቸው ይኸው የምታዩትና የምትሰሙት ነገር ነው፤ በሰው እጅ የተሠሩ አማልክት በፍጹም አማልክት እንዳልሆኑ ይናገራልና። የዚህ የሥራችን መልካም ስም ከመጕደፉም በላይ፣ መላው እስያና ዓለም የሚያመልካት የታላቋ አርጤምስ ቤተ መቅደስም ዋጋ ቢስ ይሆናል፤ ደግሞም ገናናው ክብሯ ይዋረዳል።” ሰዎቹም ይህን በሰሙ ጊዜ ክፉኛ ተቈጥተው፣ “የኤፌሶኗ አርጤምስ ታላቅ ናት!” እያሉ ይጮኹ ጀመር። ወዲያውም በከተማው ሁሉ ሁከት ተነሣ፤ ሕዝቡም አንድ ላይ በማበር የመቄዶንያ ተወላጅ የሆኑትንና ከጳውሎስ ጋራ ይጓዙ የነበሩትን ጓደኞቹን፣ ጋይዮስንና አርስጥሮኮስን ይዘው ወደ ጨዋታ ማሳያው ስፍራ እየሮጡ ገቡ። ጳውሎስም ወጥቶ ሕዝቡ ፊት ለመቅረብ ፈልጎ ነበር፤ ደቀ መዛሙርት ግን ከለከሉት። ከአውራጃው ባለሥልጣናት አንዳንድ ወዳጆቹ እንኳ፣ ጳውሎስ ወደ ጨዋታ ማሳያው ስፍራ ደፍሮ እንዳይገባ ሰው ልከው ለመኑት። ጉባኤውም ተበጣብጦ፣ አንዱ አንድ ነገር ሲናገር ሌላውም ሌላ እየተናገረ ይጯጯኽ ነበር፤ አብዛኛውም ሰው ለምን እዚያ እንደ ተሰበሰበ እንኳ አያውቅም ነበር። አይሁድም እስክንድሮስን ከሕዝቡ መካከል ገፍተው ወደ ፊት ባወጡት ጊዜ፤ አንዳንዶቹ እንዲናገርላቸው ጮኹ፤ እርሱም ሊከራከርላቸው ፈልጎ ዝም እንዲሉ በምልክት ጠቀሳቸው። ነገር ግን እርሱ አይሁዳዊ መሆኑን ባወቁ ጊዜ ሁሉም በአንድ ድምፅ፣ “የኤፌሶኗ አርጤምስ ታላቅ ናት!” እያሉ ሁለት ሰዓት ያህል ጮኹ። የከተማዪቱም ዋና ጸሓፊ ሕዝቡን ጸጥ አሠኝቶ እንዲህ አለ፤ “የኤፌሶን ሰዎች ሆይ፤ የታላቋ የአርጤምስ ቤተ መቅደስና ከሰማይ የወረደው ምስሏ ጠባቂ የኤፌሶን ከተማ ሕዝብ መሆኑን የማያውቅ ማን አለ? ስለዚህ፣ ይህ ሐቅ የማይካድ እንደ መሆኑ መጠን፣ ልትረጋጉና አንዳች ነገር በጥድፊያ ከመፈጸም ልትቈጠቡ ይገባችኋል። እነዚህን ሰዎች ቤተ መቅደስን ሳይዘርፉ ወይም አምላካችን በሆነችው ላይ የስድብ ቃል ሳይሰነዝሩ ይዛችሁ እዚህ ድረስ እንዲያው አምጥታችኋቸዋል። እንግዲህ፣ ድሜጥሮስና ከርሱ ጋራ ያሉት አንጥረኞች በማንም ላይ አቤቱታ ካላቸው፣ ፍርድ ቤቱ ክፍት ነው፤ ዳኞችም አሉ፤ ክስ ማቅረብ ይችላሉ። ከዚህ ሌላ ልታቀርቡ የፈለጋችሁት ነገር ካለ በሕጋዊ ጉባኤ ይታያል። አለዚያ ዛሬ ስለ ሆነው ነገር፣ በሁከት አነሣሽነት እንዳንከሰስ ያሠጋናል፤ አጥጋቢ ምክንያት ስለሌለንም፣ ስለ ሁከቱ ብንጠየቅበት መልስ መስጠት አንችልም።” ይህን ከተናገረ በኋላም ጉባኤው እንዲበተን አደረገ።

ሐዋርያት ሥራ 19:1-41 አማ05 (አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም)

አጵሎስ በቆሮንቶስ በነበረበት ጊዜ ጳውሎስ በላይኛው አገር አልፎ ወደ ኤፌሶን ደረሰ፤ እዚያ ጥቂት ክርስቲያኖችን አገኘና “ባመናችሁ ጊዜ መንፈስ ቅዱስን ተቀብላችሁ ነበርን?” ሲል ጠየቃቸው። እነርሱም “አልተቀበልንም፤ መንፈስ ቅዱስ መኖሩን እንኳ ሰምተን አናውቅም” ሲሉ መለሱለት። ጳውሎስም “ታዲያ፥ ምን ዐይነት ጥምቀት ነው የተጠመቃችሁት?” አላቸው። እነርሱም “የዮሐንስን ጥምቀት ነው” አሉት። ጳውሎስም “የዮሐንስ ጥምቀትማ ንስሓ ስለ መግባት የተፈጸመ ነው፤ ለሕዝቡም የተናገረው ‘ከእኔ በኋላ በሚመጣው እመኑ’ እያለ ነበር፤ እርሱም ኢየሱስ ነው” አላቸው። ይህን በሰሙ ጊዜ በጌታ በኢየሱስ ስም ተጠመቁ። ጳውሎስ እጁን በጫነባቸውም ጊዜ መንፈስ ቅዱስ በእነርሱ ላይ ወረደና በሌላ ቋንቋዎች ተናገሩ፤ ትንቢትንም መናገር ጀመሩ። ሰዎቹም በአጠቃላይ ዐሥራ ሁለት ያኽል ነበሩ። ጳውሎስ ወደ ምኲራብ ሄዶ ለሦስት ወር ያኽል ስለ እግዚአብሔር መንግሥት እየተከራከረና ሕዝቡን እያስረዳ በድፍረት ያስተምር ነበር። አንዳንዶች ግን እልኸኞች በመሆን የጌታን መንገድ በሕዝቡ ፊት እየተሳደቡ አናምንም ባሉ ጊዜ ከእነርሱ ራቀ፤ አማኞችንም ለብቻቸው ወስዶ በጢራኖስ አዳራሽ በየቀኑ ያስተምር ነበር። ጳውሎስ ይህን ያደረገው ለሁለት ዓመት ያኽል ነው፤ በዚያም ጊዜ በእስያ የሚኖሩ አይሁድና አሕዛብ ሁሉ የጌታን ቃል ለመስማት ቻሉ። እግዚአብሔር በጣም አስደናቂ የሆኑ ተአምራትን በጳውሎስ እጅ ያደርግ ነበር። በዚህም ምክንያት የጳውሎስን አካል የነካውን ልብስና መሐረብ እየወሰዱ በሽተኞቹን ሲያስነኩአቸው ከበሽታቸው ይፈወሱ ነበር፤ ርኩሳን መናፍስትም ይወጡላቸው ነበር። አጋንንትን ከሰዎች እያስወጡ በየቦታው የሚዞሩ አንዳንድ አይሁድ “ጳውሎስ በሚሰብከው በጌታ ኢየሱስ ስም እንድትወጡ እናዛችኋለን” በማለት አጋንንትን ከሰዎች ለማስወጣት ይሞክሩ ነበር። የአይሁድ ሊቀ ካህናት የሆነ የአስቄዋ ሰባት ልጆችም እንዲሁ ያደርጉ ነበር። ነገር ግን ርኩሱ መንፈስ “ኢየሱስን ዐውቃለሁ! ጳውሎስንም ዐውቃለሁ! ኧረ እናንተ እነማን ናችሁ?” አላቸው። አንድ ርኩስ መንፈስ ያደረበትም ሰው ዘሎ በማነቅ በረታባቸው፤ አሸነፋቸውም፤ ቈስለውና ራቊታቸውን ሆነው ከቤት ሸሽተው ወጡ። ይህም ነገር በኤፌሶን በሚኖሩት አይሁድና አሕዛብ ዘንድ ስለ ተሰማ ሁሉም ፈሩ፤ የጌታ የኢየሱስም ስም እጅግ ገናና ሆነ። ከአማኞችም ብዙዎቹ ክፉ ሥራቸውን በግልጥ እየተናዘዙ ይመጡ ነበር። ብዙ አስማተኞችም የአስማት መጽሐፎቻቸውን ሰብስበው በሕዝቡ ሁሉ ፊት አቃጠሉአቸው፤ የመጽሐፎቹ ዋጋ ሲተመን ኀምሳ ሺህ ጥሬ ብር ሆኖ ተገኘ። በዚህ ዐይነት የጌታ ቃል በጣም እየተስፋፋና ድል እያደረገ ይሄድ ነበር። ይህ ሁሉ ከሆነ በኋላ ጳውሎስ በመቄዶንያና በአካይያ አድርጎ ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ በመንፈሱ አስቦ “እዚያ ከደረስኩ በኋላ ወደ ሮም መሄድ አለብኝ” አለ። ስለዚህ ከሚያገለግሉት ሰዎች ሁለቱን፥ ጢሞቴዎስንና ኤራስጦስን ወደ መቄዶንያ ልኮ እርሱ ራሱ በእስያ ለጥቂት ቀኖች ቈየ። በዚያን ጊዜ በጌታ መንገድ ምክንያት በኤፌሶን ታላቅ ሁከት ተነሣ። አንድ ድሜጥሮስ የሚባል ብር አንጥረኛ የአርጤሚስን ቤተ መቅደስ ምስል ከብር እየሠራ ለአንጥረኞች ብዙ ትርፍ ያስገኝ ነበር። ስለዚህ ይህ ሰው አንጥረኞችንና የእነርሱ ዐይነት ሥራ ያላቸውን ሌሎችንም ሰዎች ሰብስቦ እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ ሰዎች! እኛ ሀብት የምናገኘው በዚህ ሥራ እንደ ሆነ ታውቃላችሁ፤ ይህ ጳውሎስ ‘በሰው እጅ የተሠሩ ምስሎች አማልክት አይደሉም’ እያለ በኤፌሶን ብቻ ሳይሆን ከጥቂት አገሮች በቀር በመላዋ እስያ ምን ያኽል ብዙ ሕዝብ እንዳግባባና እንዳሳመነ እናንተ ራሳችሁ ያያችሁትና የሰማችሁት ነው። በዚህ ዐይነት ይህ የእኛ ሥራ መናቁ ነው፤ ይህም ብቻ ሳይሆን በእስያና በመላው ዓለም ሰው ሁሉ የሚያመልካት የታላቂቱ አምላክ የአርጤሚስ ቤተ መቅደስ ከንቱ ሆኖ መቅረቱ ነው፤ የእርስዋም ታላቅነት መሻሩ ነው።” ሰዎቹም ይህን በሰሙ ጊዜ ተቈጥተው፥ “የኤፌሶን አርጤሚስ ታላቅ ናት!” እያሉ ጮኹ። ከተማዋም በሙሉ ተሸበረች፤ ሕዝቡም የመቄዶንያ ተወላጆች የሆኑትን ሁለቱን የጳውሎስን የጒዞ ጓደኞች፥ ጋይዮስንና አርስጥሮኮስን ይዘው እየጐተቱ ወደ ሕዝብ መሰብሰቢያ ቦታ ሮጡ። ጳውሎስ ወደ ሕዝቡ ለመሄድ ፈልጎ ነበር፤ ደቀ መዛሙርት ግን እንዳይሄድ ከለከሉት። ከእስያ አገር ባለሥልጣኖችም ወዳጆቹ የሆኑ አንዳንዶቹ ወደ ጳውሎስ ሰው ልከው “ወደ ሕዝብ መሰብሰቢያው ቦታ ሄደህ እንዳትታይ” ሲሉ ለመኑት። በሕዝቡ መካከል ታላቅ ሁከት ስለ ነበር አብዛኞቹ ለምን እንደ ተሰበሰቡ እንኳ አያውቁም ነበር፤ በዚህ ምክንያት አንዱ አንድ ነገር እያለ ሲጮኽ ሌላው ደግሞ ሌላ ነገር እያለ ይጮኽ ነበር። አንዳንድ የአይሁድ ወገኖች እስክንድር የተባለውን ሰው ከሕዝቡ ገፋፍተው ወደ ፊት አቀረቡት፤ ከሕዝቡም መካከል አንዳንዶቹ በደንብ እንዲከራከርላቸው መከሩት፤ እስክንድርም ሕዝቡ ጸጥ እንዲል በእጁ ጠቀሰና የመከላከያ ንግግር ለማድረግ ተዘጋጀ። ነገር ግን እስክንድር አይሁዳዊ መሆኑን ሰዎቹ ሁሉ ባወቁ ጊዜ “የኤፌሶን አርጤሚስ ታላቅ ናት!” እያሉ ሁለት ሰዓት ያኽል ሁሉም በአንድ ድምፅ ጮኹ። በመጨረሻ የከተማይቱ ዋና ጸሐፊ፥ ሕዝቡን ዝም አሰኘና እንዲህ አለ፦ “የኤፌሶን ሰዎች ሆይ! የኤፌሶን ከተማ ነዋሪዎች፥ የታላቂቱን አርጤሚስን ቤተ መቅደስና ከሰማይ የወረደውን ምስልዋን እንደሚጠብቁ በሁሉም ዘንድ የታወቀ ነው። ይህን የሚክድ ማንም ስለሌለ ጸጥ እንድትሉና በችኰላ ክፉ ነገር ከማድረግ እንድትጠነቀቁ ይገባል። ቤተ መቅደስን ያልዘረፉትንና በአምላካችን ላይ የስድብ ቃል ያልተናገሩትን ሰዎች ወደዚህ ይዛችሁ መጥታችኋል። ድሜጥሮስና ከእርሱ ጋር ያሉት አንጥረኞች የሚከሱት ሰው ካለ ፍርድ የሚሰጥባቸው ቀኖች አሉ፤ ባለሥልጣኖችም አሉ፤ እዚያ ይሟገቱ። ሌላ የምትፈልጉት ነገር ካለ ግን በሕጋዊ ሸንጎ ይታያል። አለበለዚያ ዛሬ በተደረገው ነገር ‘ሁከት አስነሥተዋል’ ተብለን እንዳንከሰስ ያስፈራል፤ ‘ይህ ብጥብጥ በምን ምክንያት ተነሣ’ ተብለን ብንጠየቅ የምንሰጠው መልስ የለንም” ይህንንም ብሎ የተሰበሰቡት ሰዎች እንዲበተኑ አደረገ።

ሐዋርያት ሥራ 19:1-41 አማ54 (መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት))

አጵሎስም በቆሮንቶስ ሳለ ጳውሎስ በላይኛው አገር አልፎ ወደ ኤፌሶን መጣ፥ አንዳንድ ደቀ መዛሙርትንም አገኘ። ባመናችሁ ጊዜ መንፈስ ቅዱስን ተቀበላችሁን? አላቸው። እነርሱም፦ አልተቀበልንም መንፈስ ቅዱስ እንዳለ ስንኳ አልሰማንም አሉት። እንኪያ በምን ተጠመቃችሁ? አላቸው። እነርሱም፦ በዮሐንስ ጥምቀት አሉት። ጳውሎስም፦ ዮሐንስስ ከእርሱ በኋላ በሚመጣው በኢየሱስ ክርስቶስ ያምኑ ዘንድ ለሕዝብ እየተናገረ በንስሐ ጥምቀት አጠመቀ አላቸው። ይህንም በሰሙ ጊዜ በጌታ በኢየሱስ ስም ተጠመቁ፤ ጳውሎስም እጁን በጫነባቸው ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ወረደባቸው በልሳኖችም ተናገሩ፥ ትንቢትም ተናገሩ። ሰዎቹም ሁሉ አሥራ ሁለት ያህሉ ነበር። ወደ ምኵራብም ገብቶ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት እየተነጋገረና እያስረዳቸው ሦስት ወር ያህል በግልጥ ይናገር ነበር። አንዳንዶች ግን እልከኞች ሆነው በሕዝብ ፊት መንገዱን እየሰደቡ ባላመኑ ጊዜ፥ ከእነርሱ ርቆ ደቀ መዛሙርትን ለየ፥ ጢራኖስም በሚሉት በትምህርት ቤት ዕለት ዕለት ይነጋገር ነበር። በእስያም የኖሩት ሁሉ አይሁድም የግሪክ ሰዎችም የጌታን ቃል እስኪሰሙ ድረስ ሁለት ዓመት ያህል እንዲህ ሆነ። እግዚአብሔርም በጳውሎስ እጅ የሚያስገርም ተአምራት ያደርግ ነበር፤ ስለዚህም ከአካሉ ጨርቅ ወይም ልብስ ወደ ድውዮች ይወስዱ ነበር፥ ደዌያቸውም ይለቃቸው ነበር ክፉዎች መናፍስትም ይወጡ ነበር። አጋንንትንም እያወጡ ይዞሩ ከነበሩት አይሁድ አንዳንዶች፦ ጳውሎስ በሚሰብከው በኢየሱስ እናምላችኋለን እያሉ ክፉዎች መናፍስት ባሉባቸው ላይ የጌታን የኢየሱስን ስም ይጠሩባቸው ዘንድ ሞከሩ። የካህናትም አለቃ ለሆነ አስቄዋ ለሚሉት ለአንድ አይሁዳዊ ይህን ያደረጉ ሰባት ልጆች ነበሩት። ክፉው መንፈስ ግን መልሶ፦ ኢየሱስንስ አውቀዋለሁ ጳውሎስንም አውቀዋለሁ፤ እናንተሳ እነማን ናችሁ? አላቸው። ክፉው መንፈስም ያለበት ሰው ዘለለባቸው ቆስለውም ከዚያ ቤት ዕራቁታቸውን እስኪሸሹ ድረስ በረታባቸው አሸነፋቸውም። ይህም በኤፌሶን በሚኖሩት ሁሉ በአይሁድና በግሪክ ሰዎች ዘንድ የታወቀ ሆነ፥ በሁላቸውም ላይ ፍርሃት ወደቀባቸው፥ የጌታም የኢየሱስ ስም ተከበረ፤ አምነውም ከነበሩት እጅግ ሰዎች ያደረጉትን እየተናዘዙና እየተናገሩ ይመጡ ነበር። ከአስማተኞችም ብዙዎቹ መጽሐፋቸውን ሰብስበው በሰው ሁሉ ፊት አቃጠሉት፤ ዋጋውም ቢታሰብ አምሳ ሺህ ብር ሆኖ ተገኘ። እንዲህም የጌታ ቃል በኃይል ያድግና ያሸንፍ ነበር። ይህም በተፈጸመ ጊዜ ጳውሎስ፦ ወደዚያ ደርሼ ሮሜን ደግሞ አይ ዘንድ ይገባኛል ብሎ በመቄዶንያና በአካይያ አልፎ ወደ ኢየሩሳሌም እንዲሄድ በመንፈስ አሰበ። ከሚያገለግሉትም ሁለቱን ጢሞቴዎስንና ኤርስጦንን ወደ መቄዶንያ ልኮ ራሱ በእስያ ጥቂት ቀን ቆየ። በዚያም ጊዜ ስለዚህ መንገድ ብዙ ሁከት ሆነ። ብር ሠሪ የሆነ ድሜጥሮስ የሚሉት አንድ ሰው የአርጤምስን ቤተ መቅደስ ምስሎች በብር እየሠራ ለአንጥረኞች እጅግ ትርፍ ያገኝ ነበርና፤ እነዚህንም ይህንም የሚመስለውን ሥራ የሠሩትን ሰብስቦ እንዲህ አላቸው፦ ሰዎች ሆይ፥ ትርፋችን በዚህ ሥራ እንደ ሆነ ታውቃላችሁ። ይህም ጳውሎስ፦ በእጅ የተሠሩቱ አማልክት አይደሉም ብሎ፥ በኤፌሶን ብቻ ሳይሆን ከጥቂት ክፍል በቀር በእስያ ሁሉ ብዙ ሕዝብን እንደ አስረዳና እንደ አሳተ አይታችኋል ሰምታችሁማል። ሥራችንም እንዲናቅ ብቻ አይደለም፥ እስያ ሁሉ ዓለሙም የሚያመልካት የታላቂቱ አምላክ የአርጤምስ መቅደስ ምናምን ሆኖ እንዲቆጠር እንጂ፥ ታላቅነትዋም ደግሞ እንዳይሻር ያስፈራል። ይህንም በሰሙ ጊዜ ቍጣ ሞላባቸው፦ የኤፌሶን አርጤምስ ታላቅ ናት እያሉም ጮኹ። ከተማውም በሙሉው ተደባለቀ፥ የመቄዶንያም ሰዎች የጳውሎስን ጓደኞች ጋይዮስንና አርስጥሮኮስን ከእነርሱ ጋር ነጥቀው በአንድ ልብ ሆነው ወደ ጨዋታ ስፍራ ሮጡ። ጳውሎስም ወደ ሕዝቡ ይገባ ዘንድ በፈቀደ ጊዜ ደቀ መዛሙርት ከለከሉት። ከእስያም አለቆች ወዳጆቹ የሆኑት አንዳንዶች ደግሞ ወደ እርሱ ልከው ወደ ጨዋታ ስፍራ ራሱን እንዳይሰጥ ለመኑት። ወዲያና ወዲህም እያሉ ይጮኹ ነበር፤ በጉባኤው ድብልቅልቅ ሆኖ የሚበልጡት ስንኳ ስለ ምን እንደተሰበሰቡ አላወቁም ነበርና። አይሁድም ሲያቀርቡት፥ እስክንድሮስን ከሕዝቡ መካከል ወደ ፊት ገፉት፤ እስክንድሮስም በእጁ ጠቅሶ በሕዝብ ፊት እንዲምዋገትላቸው ወደደ። አይሁዳዊ ግን እንደ ሆነ ባወቁ ጊዜ፥ ሁሉ በአንድ ድምፅ፦ የኤፌሶን አርጤምስ ታላቅ ናት እያሉ ሁለት ሰዓት ያህል ጮኹ። የከተማይቱም ጸሐፊ ሕዝቡን ጸጥ አሰኝቶ እንዲህ አለ፦ የኤፌሶን ሰዎች ሆይ፥ የኤፌሶን ከተማ ለታላቂቱ አርጤምስ ከሰማይም ለወረደው ጣዖትዋ የመቅደስ ጠባቂ መሆንዋን የማያውቅ ሰው ማን ነው? ይህንም የሚክደው ከሌለ፥ ጸጥ እንድትሉና አንዳች በችኮላ እንዳታደርጉ ይገባል። የመቅደስን ዕቃ ያልሰረቁ አምላካችንንም ያልሰደቡ እነዚህን ሰዎች አምጥታችኋቸዋልና። ድሜጥሮስና ከእርሱ ጋር ያሉት አንጥረኞች ግን በሰው ላይ ነገር እንዳላቸው፥ የመጋቢያ ቀንና አገረ ገዢዎች አሉ፤ እርስ በርሳቸው ይምዋገቱ። ስለ ሌላ ነገር እንደ ሆነ ግን አንዳች ብትፈልጉ፥ በተደነገገው ጉባኤ ይፈታል። ዛሬ ስለ ተደረገው፦ ሁከት ነው ሲሉ እንዳይከሱን ያስፈራልና፤ ስለዚህም ስብሰባ ምላሽ መስጠት አንችልም፥ ምክንያት የለምና። ይህንም ብሎ ጉባኤውን ፈታው።