ሐዋርያት ሥራ 15:5-20 - Compare All Versions

ሐዋርያት ሥራ 15:5-20 አማ2000 (የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ))

ነገር ግን ካመ​ኑት ከፈ​ሪ​ሳ​ው​ያን ወገን አን​ዳ​ን​ዶች ተነ​ሥ​ተው፥ “ትገ​ዝ​ሩ​አ​ቸው ዘን​ድና የሙ​ሴን ሕግ እን​ዲ​ጠ​ብቁ ታዝ​ዙ​አ​ቸው ዘንድ ይገ​ባል” አሉ። ሐዋ​ር​ያ​ትና ቀሳ​ው​ስ​ትም ስለ​ዚህ ነገር የሚ​ያ​ደ​ር​ጉ​ትን ያዩ ዘንድ ተሰ​በ​ሰቡ። ብዙ ክር​ክ​ርም ከተ​ከ​ራ​ከሩ በኋላ ጴጥ​ሮስ ተነ​ሥቶ እን​ዲህ አላ​ቸው፥ “ወን​ድ​ሞች ሆይ፥ ስሙ፤ ለአ​ሕ​ዛብ ከአፌ የወ​ን​ጌ​ሉን ቃል እን​ዳ​ሰ​ማ​ቸ​ውና እን​ዲ​ያ​ምኑ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር አስ​ቀ​ድሞ እንደ መረ​ጠኝ እና​ንተ ራሳ​ችሁ ታው​ቃ​ላ​ችሁ። ልብን የሚ​ያ​ውቅ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ለእኛ እንደ ሰጠን መን​ፈስ ቅዱ​ስን በመ​ስ​ጠት መሰ​ከ​ረ​ላ​ቸው። ልባ​ቸ​ው​ንም በእ​ም​ነት አን​ጽቶ ከእኛ አል​ለ​ያ​ቸ​ውም። አሁ​ንም እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን አት​ፈ​ታ​ተ​ኑት፤ እኛም አባ​ቶ​ቻ​ች​ንም ልን​ሸ​ከ​መው ያል​ቻ​ል​ነ​ውን ቀን​በር በደቀ መዛ​ሙ​ርት ጫንቃ ላይ ለምን ትጭ​ና​ላ​ችሁ? ነገር ግን በጌ​ታ​ችን በኢ​የ​ሱስ ክር​ስ​ቶስ ጸጋ እን​ድን ዘንድ እን​ታ​መ​ና​ለን፤ እነ​ር​ሱም እንደ እኛ ይድ​ናሉ።” ያን​ጊ​ዜም ሕዝቡ ሁሉ ጸጥ ብለው እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር በአ​ሕ​ዛብ ዘንድ ያደ​ረ​ገ​ላ​ቸ​ውን ተአ​ም​ራ​ትና ድንቅ ሥራ ሁሉ ሲና​ገሩ ጳው​ሎ​ስ​ንና በር​ና​ባ​ስን አዳ​መ​ጡ​አ​ቸው። እነ​ር​ሱም ጸጥ ባሉ ጊዜ ያዕ​ቆብ መልሶ እን​ዲህ አለ፥ “ወን​ድ​ሞች ሆይ፥ ስሙኝ። ስም​ዖ​ንም፥ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር አስ​ቀ​ድሞ አሕ​ዛ​ብን ይቅር እን​ዳ​ላ​ቸ​ውና ከው​ስ​ጣ​ቸ​ውም ለስሙ ሕዝ​ብን እንደ መረጠ ተና​ግ​ሮ​አል። በዚ​ህም መጽ​ሐፍ እን​ዲህ ብሎ እንደ ተና​ገረ የነ​ቢ​ያት ቃል ይስ​ማ​ማል። ከዚ​ህም በኋላ የወ​ደ​ቀ​ች​ውን የዳ​ዊ​ትን ቤት መልሼ እሠ​ራ​ታ​ለሁ፤ ፍራ​ሽ​ዋ​ንም አድ​ሳ​ለሁ፤ የቀ​ሩት ሰዎ​ችና ስሜም የተ​ጠ​ራ​ባ​ቸው አሕ​ዛብ ሁሉ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ይፈ​ልጉ ዘንድ፥ ይላል ይህን የሚ​ያ​ደ​ርግ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር፤ ከጥ​ንት ጀምሮ ሥራው ሁሉ በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ዘንድ የታ​ወቀ ነው። “አሁ​ንም ወደ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር በተ​መ​ለሱ አሕ​ዛብ ላይ ሥር​ዐት አታ​ክ​ብዱ እላ​ች​ኋ​ለሁ። ነገር ግን ለጣ​ዖት ከሚ​ሠ​ዋው፥ ከዝ​ሙት፥ ሞቶ የተ​ገ​ኘ​ው​ንና ደም ከመ​ብ​ላት እን​ዲ​ርቁ፥ ለራ​ሳ​ቸው የሚ​ጠ​ሉ​ት​ንም በወ​ን​ድ​ሞ​ቻ​ቸው ላይ እን​ዳ​ያ​ደ​ርጉ እዘ​ዙ​አ​ቸው።

ሐዋርያት ሥራ 15:5-20 NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)

ከፈሪሳውያን ወገን ያመኑት አንዳንዶቹ ተነሥተው በመቆም፣ “አሕዛብ እንዲገረዙና የሙሴን ሕግ እንዲጠብቁ ማድረግ አስፈላጊ ነው” አሉ። ሐዋርያትና ሽማግሌዎችም ይህንኑ ጕዳይ ለማጤን ተሰበሰቡ። ከብዙ ክርክር በኋላ ጴጥሮስ ተነሥቶ እንዲህ አላቸው፤ “ወንድሞች ሆይ፤ እግዚአብሔር ከጥቂት ጊዜ በፊት በእናንተ መካከል እኔን መርጦ፣ አሕዛብ የወንጌልን ቃል ከእኔ አንደበት ሰምተው እንዲያምኑ ማድረጉን ታውቃላችሁ። ልብን የሚያውቅ አምላክ ለእኛ እንደ ሰጠን ሁሉ፣ ለእነርሱም መንፈስ ቅዱስን በመስጠት የተቀበላቸው መሆኑን መሰከረላቸው፤ ልባቸውንም በእምነት በማንጻት፣ በእኛና በእነርሱ መካከል ምንም ልዩነት አላደረገም። እንግዲህ፣ አባቶቻችንም እኛም ልንሸከመው ያልቻልነውን ቀንበር በደቀ መዛሙርት ጫንቃ ላይ በመጫን ለምን አሁን እግዚአብሔርን ትፈታተኑታላችሁ? እኛም የዳንነው ልክ እንደ እነርሱ በጌታ በኢየሱስ ጸጋ መሆኑን እናምናለን።” ጉባኤውም በሙሉ ዝም ብሎ፣ በርናባስና ጳውሎስ እግዚአብሔር በእነርሱ አማካይነት በአሕዛብ መካከል ስላደረጋቸው ታምራዊ ምልክቶችና ድንቅ ነገሮች ሲናገሩ ያዳምጣቸው ነበር። እነርሱም ተናግረው ሲጨርሱ፣ ያዕቆብ ተነሥቶ በመቆም እንዲህ አለ፤ “ወንድሞች ሆይ፤ ስሙኝ፤ እግዚአብሔር ከአሕዛብ ወገን ለርሱ የሚሆነውን ሕዝብ አስቀድሞ እንዴት እንደ ጐበኘ ስምዖን አስረድቶናል። እንዲህ ተብሎ የተጻፈው የነቢያቱም ቃል ከዚህ ጋራ ይስማማል፤ “ ‘ከዚህ በኋላ እመለሳለሁ፤ የወደቀውን የዳዊትን ቤት እገነባለሁ። ፍርስራሹን መልሼ አቆማለሁ፤ እንደ ገናም እሠራዋለሁ፤ ይኸውም የቀሩት ሰዎች ጌታን እንዲፈልጉ፣ ስሜን የተሸከሙ አሕዛብም ሁሉ እንዲሹኝ ነው፤ እነዚህን ያደረገ ጌታ እንዲህ ይላል፤’ እነርሱም ከጥንት ጀምሮ የታወቁ ናቸው። “ስለዚህ ወደ እግዚአብሔር የተመለሱትን አሕዛብ እንዳናስጨንቃቸው ይህ የእኔ ብያኔ ነው። ይልቁን በጣዖት ከረከሰ ነገር፣ ከዝሙት ርኩሰት፣ ታንቆ የሞተ እንስሳ ሥጋ ከመብላትና ደም ከመመገብ እንዲርቁ ልንጽፍላቸው ይገባል፤

ሐዋርያት ሥራ 15:5-20 አማ54 (መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት))

ከፈሪሳውያን ወገን ግን ያመኑት አንዳንዶቹ ተነሥተው፦ “ትገርዙአቸው ዘንድና የሙሴን ሕግ እንዲጠብቁ ታዙአቸው ዘንድ ይገባል” አሉ። ሐዋርያትና ሽማግሌዎችም ስለዚህ ነገር ለመማከር ተሰበሰቡ። ከብዙ ክርክርም በኋላ ጴጥሮስ ተነሥቶ እንዲህ አላቸው ወንድሞች ሆይ፥ አሕዛብ ከአፌ የወንጌልን ቃል ሰምተው ያምኑ ዘንድ እግዚአብሔር በመጀመሪያው ዘመን ከእናንተ እኔን እንደ መረጠኝ እናንተ ታውቃላችሁ። ልብንም የሚያውቅ አምላክ ለእኛ ደግሞ እንደ ሰጠን መንፈስ ቅዱስን በመስጠት መሰከረላቸው፤ ልባቸውንም በእምነት ሲያነጻ በእኛና በእነርሱ መካከል አንዳች አልለየም። እንግዲህ አባቶቻችንና እኛ ልንሸከመው ያልቻልነውን ቀንበር በደቀ መዛሙርት ጫንቃ ላይ በመጫን እግዚአብሔርን አሁን ስለ ምን ትፈታተናላችሁ? ነገር ግን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ እንደ እነርሱ ደግሞ እንድን ዘንድ እናምናለን።” ሕዝቡም ሁሉ ዝም አሉ፥ በርናባስና ጳውሎስም እግዚአብሔር በእጃቸው በአሕዛብ መካከል ያደረገውን ምልክትና ድንቅ ሁሉ ሲተርኩላቸው ይሰሙ ነበር። እነርሱም ዝም ካሉ በኋላ ያዕቆብ እንዲህ ብሎ መለሰ፦ “ወንድሞች ሆይ፥ ስሙኝ። እግዚአብሔር ለስሙ የሚሆንን ወገን ከአሕዛብ ይወስድ ዘንድ አስቀድሞ እንዴት እንደ ጐበኘ ስምዖን ተርኮአል። ከዚህም ጋር የነቢያት ቃል ይሰማማል፥ እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፦ ‘ከዚህ በኋላ የቀሩት ሰዎችና በስሜ የተጠሩት አሕዛብ ሁሉ ጌታን ይፈልጉ ዘንድ እመለሳለሁ፥ የወደቀችውንም የዳዊትን ድንኳን እንደ ገና እሠራታለሁ፥ ፍራሽዋንም እንደ ገና እሠራታለሁ እንደ ገናም አቆማታለሁ ይላል ይህን የሚያደርግ ጌታ። ከጥንት ጀምሮ ሥራው ሁሉ በእግዚአብሔር ዘንድ የታወቀ ነው።’ ስለዚህ ከአሕዛብ ወደ እግዚአብሔር የዞሩትን እንዳናስቸግራቸው፥ ነገር ግን ከጣዖት ርኵሰትና ከዝሙት ከታነቀም ከደምም ይርቁ ዘንድ እንድንጽፍላቸው እቈርጣለሁ።

ሐዋርያት ሥራ 15:5-20 አማ05 (አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም)

ነገር ግን ከፈሪሳውያን ወገን የሆኑ አንዳንድ አማኞች ተነሡና “አሕዛብ እንዲገረዙና የኦሪትን ሕግ እንዲጠብቁ ማድረግ ይገባል” አሉ። ሐዋርያትና ሽማግሌዎች ይህን ጉዳይ ለመመርመር ተሰበሰቡ፤ ብዙ ክርክር ከተደረገም በኋላ ጴጥሮስ ተነሥቶ እንዲህ አላቸው፤ “ወንድሞች ሆይ፥ አሕዛብ በእኔ አማካይነት የወንጌልን ቃል ሰምተው እንዲያምኑ ከዚህ በፊት እግዚአብሔር እኔን ከእናንተ መካከል እንደ መረጠኝ ታውቃላችሁ። የሰውን ልብ የሚያውቅ አምላክ፥ መንፈስ ቅዱስን ለእኛ እንደ ሰጠው ዐይነት ለእነርሱም በመስጠት መሰከረላቸው። ልባቸውን በእምነት ስላነጻ በእኛና በእነርሱ መካከል ምንም ልዩነት አላደረገም። ታዲያ፥ አባቶቻችንም ሆኑ እኛ ልንሸከመው ያልቻልነውን ቀንበር በአማኞች ጫንቃ ላይ በመጫን ለምን አሁን እግዚአብሔርን ትፈታተኑታላችሁ? እኛም የምንድነው ልክ እንደ እነርሱ በጌታ በኢየሱስ ጸጋ መሆኑን እናምናለን።” በዚህ ጊዜ ጉባኤው ጸጥ ብሎ በርናባስና ጳውሎስ በእነርሱ አማካይነት እግዚአብሔር በአሕዛብ መካከል ያደረገውን ተአምርና ድንቅ ነገር ሁሉ ሲናገሩ በመገረም አዳመጣቸው። እነርሱ ተናግረው ካበቁ በኋላ፥ ያዕቆብ እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ወንድሞች ሆይ! እስቲ ስሙኝ! እግዚአብሔር አንድ በስሙ የሚጠራ ሕዝብን ከመካከላቸው ለመምረጥ ለመጀመሪያ ጊዜ አሕዛብን እንዴት እንደ ጐበኘ ስምዖን አስረድቶአል። ከዚህም አሳብ ጋር የነቢያት ቃል ይስማማል፤ ይህም እንዲህ ተብሎ የተጻፈው ነው፦ ‘ከዚህ በኋላ እመለሳለሁ፤ የፈረሰውንም የዳዊትን ቤት እሠራለሁ፤ ፍርስራሹንም ጠግኜ እንደገና አቆማለሁ። ይህንንም የማደርገው የቀሩት ሰዎችና በስሜ የተጠሩት አሕዛብ ሁሉ እኔን እግዚአብሔርን እንዲፈልጉ ነው፤ ከጥንት ጀምሮ ይህን ሁሉ ያስታወቅኹ እኔ እግዚአብሔር እንዲህ እላለሁ፤’ “ስለዚህ የእኔ አሳብ ወደ እግዚአብሔር የሚመለሱትን አሕዛብ እንዳናስቸግራቸው ነው። ይልቅስ ‘ለጣዖት በመሠዋቱ ምክንያት የረከሰ ምግብን አትብሉ፤ ከዝሙት ራቁ፤ ሳይታረድና ደሙም ሳይፈስ ታንቆ የሞተ እንስሳ ሥጋን አትብሉ፤ ደምንም አትብሉ’ ብለን እንጻፍላቸው።

ሐዋርያት ሥራ 15:5-20 መቅካእኤ (መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ))

ከፈሪሳውያን ወገን ግን ያመኑት አንዳንዶቹ ተነሥተው “ትገርዙአቸው ዘንድና የሙሴን ሕግ እንዲጠብቁ ታዙአቸው ዘንድ ይገባል፤” አሉ። ሐዋርያትና ሽማግሌዎችም ስለዚህ ነገር ለመማከር ተሰበሰቡ። ከብዙ ክርክርም በኋላ ጴጥሮስ ተነሥቶ እንዲህ አላቸው “ወንድሞች ሆይ! አሕዛብ ከአፌ የወንጌልን ቃል ሰምተው ያምኑ ዘንድ እግዚአብሔር በመጀመሪያው ዘመን ከእናንተ እኔን እንደ መረጠኝ እናንተ ታውቃላችሁ። ልብንም የሚያውቅ አምላክ ለእኛ ደግሞ እንደ ሰጠን መንፈስ ቅዱስን በመስጠት መሰከረላቸው፤ ልባቸውንም በእምነት ሲያነጻ በእኛና በእነርሱ መካከል አንዳች አልለየም። እንግዲህ አባቶቻችንና እኛ ልንሸከመው ያልቻልነውን ቀንበር በደቀ መዛሙርት ጫንቃ ላይ በመጫን እግዚአብሔርን አሁን ስለምን ትፈታተናላችሁ? ነገር ግን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ እንደ እነርሱ ደግሞ እንድን ዘንድ እናምናለን።” ሕዝቡም ሁሉ ዝም አሉ፤ በርናባስና ጳውሎስም እግዚአብሔር በእጃቸው በአሕዛብ መካከል ያደረገውን ምልክትና ድንቅ ሁሉ ሲተርኩላቸው ይሰሙ ነበር። እነርሱም ዝም ካሉ በኋላ ያዕቆብ እንዲህ ብሎ መለሰ “ወንድሞች ሆይ! ስሙኝ። እግዚአብሔር ለስሙ የሚሆንን ወገን ከአሕዛብ ይወስድ ዘንድ አስቀድሞ እንዴት እንደ ጐበኘ ስምዖን ተርኮአል። ከዚህም ጋር የነቢያት ቃል ይስማማል፤ እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ “‘ከዚህ በኋላ እመለሳለሁ፤ የፈረሰውን የዳዊትን ቤት እገነባለሁ። ፍርስራሹን መልሼ አቆማለሁ፤ እንደገናም እሠራዋለሁ፤ የቀሩት ሰዎችና በስሜ የተጠሩት አሕዛብ ሁሉ ጌታን እንዲፈልጉ፥ ይላል ይህን የሚያደርግ ጌታ። ከጥንት ጀምሮ ሥራቸው ሁሉ በእግዚአብሔር ዘንድ የታወቀ ነው።’ ስለዚህ ከአሕዛብ ወደ እግዚአብሔር የዞሩትን እንዳናስቸግራቸው፥ ነገር ግን ከጣዖት ርኩሰትና ከዝሙት ከታነቀም ከደምም ይርቁ ዘንድ እንድንጽፍላቸው እቆርጣለሁ።