ሐዋርያት ሥራ 14:14-18
ሐዋርያት ሥራ 14:14-18 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ሐዋርያት በርናባስና ጳውሎስም በሰሙ ጊዜ፥ ልብሳቸውን ቀደዱ፤ ፈጥነውም እየጮኹ ወደ ሕዝቡ ሄዱ። እንዲህም አሉአቸው፥ “እናንተ ሰዎች፥ ይህን ነገር ለምን ታደርጋላችሁ? እኛስ እንደ እናንተ የምንሞት ሰዎች አይደለንምን? ነገር ግን ይህን ከንቱ ነገር ትታችሁ ሰማይና ምድርን፥ ባሕርንም በውስጣቸውም ያለውን ሁሉ ወደ ፈጠረ ወደ ሕያው እግዚአብሔር ትመለሱ ዘንድ ወንጌልን እናስተምራችኋለን። አሕዛብን ሁሉ በቀድሞ ዘመን እንደ ነበሩበት እንደ ጠባያቸው ሊኖሩ ተዋአቸው። ከዚህም ሁሉ ጋር መልካም ሥራን እየሠራ ከሰማይ ዝናምን፥ ፍሬ የሚሆንበትንም ወራት ሲሰጠን፥ ልባችንንም በመብልና በደስታ ሲሞላው ራሱን ያለ ምስክር አልተወም።” ይህንም ብለው እንዳይሠዉላቸው ሕዝቡን በግድ አስተዉአቸው።
ሐዋርያት ሥራ 14:14-18 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ሐዋርያቱ በርናባስና ጳውሎስ ይህን በሰሙ ጊዜ ልብሳቸውን ቀድደው ወደ ሕዝቡ መካከል ሮጡ፤ ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው እንዲህ አሉ፤ “እናንተ ሰዎች፤ ለምን ይህን ታደርጋላችሁ? እኛም እኮ እንደ እናንተው ሰዎች ነን። እናንተም ደግሞ ከነዚህ ከንቱ ነገሮች ርቃችሁ ሰማይንና ምድርን፣ ባሕርንም በውስጣቸውም የሚኖሩትን ሁሉ ወደ ፈጠረ ወደ ሕያው እግዚአብሔር እንድትመለሱ ወንጌልን እንሰብክላችኋለን። እርሱ ባለፉት ትውልዶች፣ ሕዝቦች ሁሉ በገዛ መንገዳቸው እንዲሄዱ ተዋቸው፤ ይሁን እንጂ ዝናብን ከሰማይ እንዲሁም ፍሬያማ ወቅቶችን በመስጠቱ፣ ደግሞም ልባችሁን በመብልና በደስታ በማርካቱ መልካምን በማድረግ ራሱን ያለ ምስክር አልተወም።” ይህን ሁሉ ተናግረው እንኳ፣ ሕዝቡ እንዳይሠዋላቸው ያስተዉት በብዙ ችግር ነበር።
ሐዋርያት ሥራ 14:14-18 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ሐዋርያት በርናባስና ጳውሎስ ግን ይህን በሰሙ ጊዜ ልብሳቸውን ቀደው ወደ ሕዝቡ መካከል እየጮኹ ሮጡ፥ እንዲህም አሉ፦ “እናንተ ሰዎች ይህን ስለ ምን ታደርጋላችሁ? እኛ ደግሞ እንደ እናንተ የምንሰማ ሰዎች ነን፥ ከዚህም ከንቱ ነገር ሰማይንና ምድርን ባሕርንም በእርነርሱም ያለውን ሁሉ ወደ ፈጠረ ወደ ሕያው እግዚአብሔር ዘወር ትሉ ዘንድ ወንጌልን እንሰብካለን። እርሱ ባለፉት ትውልዶች አሕዛብን ሁሉ በገዛ ራሳቸው ጐዳና ይሄዱ ዘንድ ተዋቸው። ከዚህም ሁሉ ጋር መልካም ሥራ እየሠራ፥ ከሰማይ ዝናብን ፍሬ የሚሆንበትንም ወራት ሲሰጠን፥ ልባችንንም በመብልና በደስታ ሲሞላው ራሱን ያለ ምስክር አልተወም።” ይህንም ብለው እንዳይሠዉላቸው ሕዝቡን በጭንቅ አስተዉአቸው።
ሐዋርያት ሥራ 14:14-18 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ሐዋርያቱ ጳውሎስና በርናባስ ግን ይህን በሰሙ ጊዜ በሐዘን ልብሳቸውን ቀደዱ፤ ወደ ሕዝቡ ሮጡና እየጮኹ እንዲህ አሉ፦ “እናንተ ሰዎች ለምን ይህን ታደርጋላችሁ? እኛም እንደ እናንተ ሰዎች ነን፤ እኛ እዚህ የመጣነው እናንተ ከዚህ ከከንቱ ነገር ሁሉ ርቃችሁ ሰማይን፥ ምድርን፥ ባሕርንና በውስጣቸው የሚገኙትን ሁሉ ወደ ፈጠረው ወደ ሕያው አምላክ እንድትመለሱ መልካም ዜና ልናበሥርላችሁ ነው፤ ባለፉት ዘመኖች ሕዝቦች ሁሉ በገዛ ራሳቸው መንገድ እንዲሄዱ እግዚአብሔር ትቶአቸዋል፤ ይሁን እንጂ እርሱ እንዴት ያለ ቸር አምላክ መሆኑን የሚመሰክር መልካም ሥራ ማድረጉን አላቋረጠም፤ ከሰማይ ዝናብን አዘነበላችሁ፤ የመከር ወራትንም ሰጣችሁ፤ በምግብና በደስታ ልባችሁን አረካ።” ሐዋርያት ይህን ያኽል ቢናገሩም እንኳ ሕዝቡ ለእነርሱ መሥዋዕት እንዳያቀርብ ያስተዉት በብዙ ችግር ነው።
ሐዋርያት ሥራ 14:14-18 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ሐዋርያት በርናባስና ጳውሎስ ግን ይህን በሰሙ ጊዜ ልብሳቸውን ቀደው ወደ ሕዝቡ መካከል እየጮኹ ሮጡ፤ እንዲህም አሉ “እናንተ ሰዎች! ይህን ስለምን ታደርጋላችሁ? እኛ ደግሞ እንደ እናንተ የምንሰማ ሰዎች ነን፤ ከዚህም ከንቱ ነገር ሰማይንና ምድርን ባሕርንም በእርነርሱም ያለውን ሁሉ ወደ ፈጠረ ወደ ሕያው እግዚአብሔር ትመለሱ ዘንድ ወንጌልን እንሰብካለን። እርሱ ባለፉት ትውልዶች አሕዛብን ሁሉ በገዛ ራሳቸው ጐዳና ይሄዱ ዘንድ ተዋቸው። ከዚህም ሁሉ ጋር መልካም ሥራ እየሠራ፥ ከሰማይ ዝናብን ፍሬ የሚሆንበትንም ወራት ሲሰጠን፥ ልባችንንም በመብልና በደስታ ሲሞላው ራሱን ያለ ምስክር አልተወም።” ይህንም ብለው እንዳይሠዉላቸው ሕዝቡን በጭንቅ አስተዉአቸው።