ሐዋርያት ሥራ 14:1-22

ሐዋርያት ሥራ 14:1-22 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ኢቆ​ን​ዮን በም​ት​ባል ከተ​ማም እንደ ሁል​ጊ​ዜው ወደ አይ​ሁድ ምኵ​ራብ ገቡ፤ ከአ​ይ​ሁ​ድና ከአ​ረ​ማ​ው​ያ​ንም ብዙ ሰዎች እስ​ኪ​ያ​ምኑ ድረስ አስ​ተ​ማሩ። ማመ​ንን እንቢ ያሉት የአ​ይ​ሁድ ወገ​ኖች ግን የአ​ሕ​ዝ​ብን ልብ በወ​ን​ድ​ሞች ላይ አነ​ሣሡ፤ አስ​ከ​ፉም። በጌ​ታም ፊት ደፍ​ረው እያ​ስ​ተ​ማሩ፥ እር​ሱም የጸ​ጋ​ውን ቃል ምስ​ክር እያ​ሳ​የ​ላ​ቸው፥ በእ​ጃ​ቸ​ውም ድንቅ ሥራና ተአ​ም​ራ​ትን እያ​ደ​ረ​ገ​ላ​ቸው ብዙ ወራት ኖሩ። የከ​ተ​ማ​ውም ሕዝብ ሁሉ ተለ​ያዩ፤ እኩ​ሌ​ቶቹ ወደ አይ​ሁድ፥ እኩ​ሌ​ቶ​ቹም ወደ ሐዋ​ር​ያት ሆኑ። አሕ​ዛ​ብና አይ​ሁድ ግን ከአ​ለ​ቆ​ቻ​ቸው ጋር ሊያ​ን​ገ​ላ​ት​ዋ​ቸ​ውና በድ​ን​ጋይ ሊደ​በ​ድ​ቧ​ቸው ተነሡ። ሐዋ​ር​ያ​ትም ይህን ዐው​ቀው ወደ ሊቃ​ኦ​ንያ ከተ​ሞች ወደ ልስ​ጥ​ራ​ንና ወደ ደር​ቤን፥ ወደ​የ​አ​ው​ራ​ጃ​ውም ሸሹ። በዚ​ያም ወን​ጌ​ልን ሰበኩ። በል​ስ​ጥ​ራ​ንም እግሩ የሰ​ለለ፥ ከእ​ና​ቱም ማኅ​ፀን ጀምሮ ሽባ የሆነ፥ ከቶም ሂዶ የማ​ያ​ውቅ አንድ ሰው ተቀ​ምጦ ነበር። እር​ሱም ጳው​ሎ​ስን ሲያ​ስ​ተ​ምር ሰማው፤ ጳው​ሎ​ስም ትኩር ብሎ ተመ​ለ​ከ​ተው፤ እም​ነት እን​ዳ​ለ​ውና እን​ደ​ሚ​ድ​ንም ተረዳ። ድም​ፁ​ንም ከፍ አድ​ርጎ፥ “ተነ​ሥና ቀጥ ብለህ በእ​ግ​ርህ ቁም እል​ሃ​ለሁ” አለው፤ ወዲ​ያ​ው​ኑም ተነ​ሥቶ ተመ​ላ​ለሰ። ሕዝ​ቡም ጳው​ሎስ ያደ​ረ​ገ​ውን ባዩ ጊዜ፥ “አማ​ል​ክት ሰዎ​ችን መስ​ለው ወደ እኛ ወረዱ” እያሉ በሊ​ቃ​ኦ​ንያ ቋንቋ ጮኹ። በር​ና​ባ​ስን ድያ አሉት፤ ጳው​ሎ​ስ​ንም የት​ም​ህ​ርቱ መሪ እርሱ ነበ​ርና ሄር​ሜን ብለው ጠሩት። በከ​ተ​ማ​ውም ፊት ለፊት ቤተ መቅ​ደስ ያለው የድያ ካህን ኮር​ማ​ዎ​ች​ንና የአ​በባ አክ​ሊ​ሎ​ችን ወደ ደጃፍ አመጣ፤ ከሕ​ዝ​ቡም ጋር ሆኖ ሊሠ​ዋ​ላ​ቸው ወደደ። ሐዋ​ር​ያት በር​ና​ባ​ስና ጳው​ሎ​ስም በሰሙ ጊዜ፥ ልብ​ሳ​ቸ​ውን ቀደዱ፤ ፈጥ​ነ​ውም እየ​ጮኹ ወደ ሕዝቡ ሄዱ። እን​ዲ​ህም አሉ​አ​ቸው፥ “እና​ንተ ሰዎች፥ ይህን ነገር ለምን ታደ​ር​ጋ​ላ​ችሁ? እኛስ እንደ እና​ንተ የም​ን​ሞት ሰዎች አይ​ደ​ለ​ን​ምን? ነገር ግን ይህን ከንቱ ነገር ትታ​ችሁ ሰማ​ይና ምድ​ርን፥ ባሕ​ር​ንም በው​ስ​ጣ​ቸ​ውም ያለ​ውን ሁሉ ወደ ፈጠረ ወደ ሕያው እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ትመ​ለሱ ዘንድ ወን​ጌ​ልን እና​ስ​ተ​ም​ራ​ች​ኋ​ለን። አሕ​ዛ​ብን ሁሉ በቀ​ድሞ ዘመን እንደ ነበ​ሩ​በት እንደ ጠባ​ያ​ቸው ሊኖሩ ተዋ​አ​ቸው። ከዚ​ህም ሁሉ ጋር መል​ካም ሥራን እየ​ሠራ ከሰ​ማይ ዝና​ምን፥ ፍሬ የሚ​ሆ​ን​በ​ት​ንም ወራት ሲሰ​ጠን፥ ልባ​ች​ን​ንም በመ​ብ​ልና በደ​ስታ ሲሞ​ላው ራሱን ያለ ምስ​ክር አል​ተ​ወም።” ይህ​ንም ብለው እን​ዳ​ይ​ሠ​ዉ​ላ​ቸው ሕዝ​ቡን በግድ አስ​ተ​ዉ​አ​ቸው። አይ​ሁ​ድም ከአ​ን​ጾ​ኪ​ያና ከኢ​ቆ​ንያ መጡ፤ ልባ​ቸ​ው​ንም እን​ዲ​ያ​ጠ​ኑ​ባ​ቸው አሕ​ዛ​ብን አባ​በ​ሉ​አ​ቸው፤ ጳው​ሎ​ስ​ንም እየ​ጐ​ተቱ ከከ​ተማ ውጭ አው​ጥ​ተው በድ​ን​ጋይ ደበ​ደ​ቡት፤ የሞ​ተም መሰ​ላ​ቸው። ደቀ መዛ​ሙ​ር​ቱም ከበ​ቡት፤ ነገር ግን ተነ​ሥቶ አብ​ሮ​አ​ቸው ወደ ከተማ ገባ፤ በማ​ግ​ሥ​ቱም ከበ​ር​ና​ባስ ጋር ወደ ደር​ቤን ሄደ። በዚ​ያ​ችም ከተማ ወን​ጌ​ልን ሰበኩ፤ ብዙ ሰዎ​ች​ንም ደቀ መዛ​ሙ​ርት አድ​ር​ገው ወደ ልስ​ጥ​ራን፥ ወደ ኢቆ​ን​ዮ​ንና ወደ አን​ጾ​ኪያ ተመ​ለሱ። የደቀ መዛ​ሙ​ር​ት​ንም ልቡና አጽ​ናኑ፤ በሃ​ይ​ማ​ኖ​ትም እን​ዲ​ጸኑ፦“ በብዙ ድካ​ምና መከራ ወደ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር መን​ግ​ሥት እን​ገባ ዘንድ ይገ​ባ​ናል” እያሉ መከ​ሩ​አ​ቸው።

ሐዋርያት ሥራ 14:1-22 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

በኢቆንዮንም ጳውሎስና በርናባስ ዐብረው ወደ አይሁድ ምኵራብ ገቡ፤ በዚያም በሚገባ ስላስተማሩ፣ ከአይሁድም ከግሪክም እጅግ ብዙ ሰዎች አመኑ። ያላመኑት አይሁድ ግን፣ አሕዛብን አነሣሥተው ወንድሞችን እንዲጠሉ አደረጓቸው። ጳውሎስና በርናባስም ስለ ጌታ በድፍረት እየተናገሩ ብዙ ጊዜ እዚያው ቈዩ፤ ጌታም የሚናገሩትን የጸጋውን ቃል በታምራዊ ምልክትና በድንቅ ሥራ እየደገፈ ያረጋግጥላቸው ነበር። የከተማውም ሕዝብ ተከፋፈለ፤ ገሚሱ ከአይሁድ ጋራ፣ ገሚሱም ከሐዋርያት ጋራ ሆነ። በዚህ ጊዜ አሕዛብና አይሁድ ከመሪዎቻቸው ጋራ ተባብረው ሊያንገላቷቸውና በድንጋይ ሊያስወግሯቸው ሞከሩ። እነርሱ ግን ይህን እንዳወቁ ልስጥራንና ደርቤን ወደተባሉት ወደ ሊቃኦንያ ከተሞችና በዙሪያቸው ወዳለው አገር ሸሹ፤ በዚያም ወንጌልን መስበክ ቀጠሉ። በልስጥራንም፣ እግሩ ዐንካሳ የሆነና ከተወለደ ጀምሮ ፈጽሞ በእግሩ ሄዶ የማያውቅ ሽባ ሰው ተቀምጦ ነበር። ይህም ሰው ጳውሎስ ሲናገር ያደምጥ ነበር። ጳውሎስም ወደ እርሱ ትኵር ብሎ ተመለከተና ለመዳን እምነት እንዳለው ባየ ጊዜ በታላቅ ድምፅ፣ “ቀጥ ብለህ በእግርህ ቁም!” አለው፤ በዚህ ጊዜ ዘልሎ ተነሣና መራመድ ጀመረ። ሕዝቡም ጳውሎስ ያደረገውን ባዩ ጊዜ፣ በሊቃኦንያ ቋንቋ፣ “አማልክት በሰው ተመስለው ወደ እኛ ወርደዋል!” ብለው ጮኹ፤ በርናባስን “ድያ” አሉት፤ ጳውሎስም ዋና ተናጋሪ ስለ ነበር “ሄርሜን” አሉት። ከከተማው ወጣ ብሎ የነበረው የድያ ቤተ መቅደስ ካህንም፣ ኰርማዎችንና የአበባ ጕንጕኖችን ወደ ከተማው መግቢያ አምጥቶ፣ ከሕዝቡ ጋራ ሆኖ ሊሠዋላቸው ፈለገ። ሐዋርያቱ በርናባስና ጳውሎስ ይህን በሰሙ ጊዜ ልብሳቸውን ቀድደው ወደ ሕዝቡ መካከል ሮጡ፤ ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው እንዲህ አሉ፤ “እናንተ ሰዎች፤ ለምን ይህን ታደርጋላችሁ? እኛም እኮ እንደ እናንተው ሰዎች ነን። እናንተም ደግሞ ከነዚህ ከንቱ ነገሮች ርቃችሁ ሰማይንና ምድርን፣ ባሕርንም በውስጣቸውም የሚኖሩትን ሁሉ ወደ ፈጠረ ወደ ሕያው እግዚአብሔር እንድትመለሱ ወንጌልን እንሰብክላችኋለን። እርሱ ባለፉት ትውልዶች፣ ሕዝቦች ሁሉ በገዛ መንገዳቸው እንዲሄዱ ተዋቸው፤ ይሁን እንጂ ዝናብን ከሰማይ እንዲሁም ፍሬያማ ወቅቶችን በመስጠቱ፣ ደግሞም ልባችሁን በመብልና በደስታ በማርካቱ መልካምን በማድረግ ራሱን ያለ ምስክር አልተወም።” ይህን ሁሉ ተናግረው እንኳ፣ ሕዝቡ እንዳይሠዋላቸው ያስተዉት በብዙ ችግር ነበር። አይሁድ ግን ከአንጾኪያና ከኢቆንዮን መጥተው፣ ሕዝቡን አግባቡ፤ ጳውሎስንም በድንጋይ ከወገሩት በኋላ፣ የሞተ መስሏቸው ጐትተው ከከተማው ወደ ውጭ አወጡት። ሆኖም ደቀ መዛሙርት ከብበውት እንዳሉ ተነሣ፤ ወደ ከተማም ገባ። በማግስቱም ከበርናባስ ጋራ ወደ ደርቤን ሄዱ። ጳውሎስና በርናባስ በደርቤን የምሥራቹን ቃል ሰብከው፣ ብዙ ደቀ መዛሙርትም ካፈሩ በኋላ፣ ወደ ልስጥራን፣ ወደ ኢቆንዮንና ወደ አንጾኪያ ተመለሱ። የደቀ መዛሙርቱንም ልብ በማበረታታትና በእምነታቸው ጸንተው እንዲኖሩ በመምከር፣ “ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ለመግባት በብዙ መከራ ማለፍ አለብን” አሏቸው።

ሐዋርያት ሥራ 14:1-22 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

በኢቆንዮንም እንደ ቀድሞ ወደ አይሁድ ምኵራብ ገብተው ከአይሁድና ከግሪክ ሰዎች ብዙ እስኪያምኑ ድረስ ተናገሩ። ያላመኑት አይሁድ ግን የአሕዛብን ልብ በወንድሞች ላይ አነሣሡ አስከፉም። ምልክትና ድንቅ በእጃቸው ይደረግ ዘንድ እየሰጠ ለጸጋው ቃል ስለ መሰከረው ስለ ጌታ ገልጠው እየተናገሩ ረጅም ወራት ተቀመጡ። የከተማውም ሕዝብ ተከፍለው እኵሌቶቹ ከአይሁድ እኵሌቶቹም ከሐዋርያት ጋር ሆኑ። አሕዛብና አይሁድ ግን ከአለቆቻቸው ጋር ሊያንገላቱአቸውና ሊወግሩአቸው ባሰቡ ጊዜ፥ አውቀው ልስጥራንና ደርቤን ወደሚባሉት ወደ ሊቃኦንያ ከተማዎች በእነርሱም ዙሪያ ወዳለው አገር ሸሹ፤ በዚያም ወንጌልን ይሰብኩ ነበር። በልስጥራንም እግሩ የሰለለ፥ ከእናቱም ማኅፀን ጀምሮ አንካሳ የሆነ፥ ከቶም ሄዶ የማያውቅ አንድ ሰው ተቀምጦ ነበር። ይህም ሰው ጳውሎስ ሲናገር ይሰማ ነበር፤ እርሱም ትኵር ብሎ ተመለከተውና ይድን ዘንድ እምነት እንዳለው ባየ ጊዜ፥ በታላቅ ድምፅ፦ “ቀጥ ብለህ በእግርህ ቁም” አለው። ብድግ ብሎም ተንሥቶ ይመላለስ ነበር። ሕዝቡም ጳውሎስ ያደረገውን ባዩ ጊዜ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው በሊቃኦንያ ቋንቋ፦ “አማልክት ሰዎችን መስለው ወደ እኛ ወርደዋል” አሉ፤ በርናባስንም ድያ አሉት፤ ጳውሎስንም እርሱ በመናገር ዋና ስለ ነበረ ሄርሜን አሉት። በከተማውም ፊት ቤተ መቅደስ ያለው የድያ ካህን ኮርማዎችንና የአበባን አክሊሎች ወደ ደጃፍ አምጥቶ ከሕዝቡ ጋር ሆኖ ሊሠዋላቸው ወደደ። ሐዋርያት በርናባስና ጳውሎስ ግን ይህን በሰሙ ጊዜ ልብሳቸውን ቀደው ወደ ሕዝቡ መካከል እየጮኹ ሮጡ፥ እንዲህም አሉ፦ “እናንተ ሰዎች ይህን ስለ ምን ታደርጋላችሁ? እኛ ደግሞ እንደ እናንተ የምንሰማ ሰዎች ነን፥ ከዚህም ከንቱ ነገር ሰማይንና ምድርን ባሕርንም በእርነርሱም ያለውን ሁሉ ወደ ፈጠረ ወደ ሕያው እግዚአብሔር ዘወር ትሉ ዘንድ ወንጌልን እንሰብካለን። እርሱ ባለፉት ትውልዶች አሕዛብን ሁሉ በገዛ ራሳቸው ጐዳና ይሄዱ ዘንድ ተዋቸው። ከዚህም ሁሉ ጋር መልካም ሥራ እየሠራ፥ ከሰማይ ዝናብን ፍሬ የሚሆንበትንም ወራት ሲሰጠን፥ ልባችንንም በመብልና በደስታ ሲሞላው ራሱን ያለ ምስክር አልተወም።” ይህንም ብለው እንዳይሠዉላቸው ሕዝቡን በጭንቅ አስተዉአቸው። አይሁድ ግን ከአንጾኪያና ከኢቆንዮን መጡ፤ ሕዝቡንም አባብለው ጳውሎስን ወገሩ የሞተም መስሎአቸው ከከተማ ወደ ውጭ ጐተቱት። ደቀ መዛሙርት ግን ከበውት ሳሉ፥ ተነስቶ ወደ ከተማ ገባ። በነገውም ከበርናባስ ጋር ወደ ደርቤን ወጣ። በዚያችም ከተማ ወንጌልን ሰብከው እጅግ ደቀ መዛሙርትን ካደረጉ በኋላ፥ የደቀ መዛሙርትን ልብ እያጸኑ በሃይማኖትም ጸንተው እንዲኖሩ እየመከሩና፦ “ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በብዙ መከራ እንገባ ዘንድ ያስፈልገናል” እያሉ፥ ወደ ልስጥራን ወደ ኢቆንዮንም ወደ አንጾኪያም ተመለሱ።

ሐዋርያት ሥራ 14:1-22 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

በኢቆንዮን ጳውሎስና በርናባስ አብረው ወደ አይሁድ ምኲራብ ገቡ፤ በዚያም ብዙ አይሁድና ከአሕዛብ እጅግ ብዙ ሰዎች እስኪያምኑ ድረስ አስተማሩ። ያላመኑት አይሁድ ግን አሕዛብን አነሣሥተው በወንድሞች ላይ ጥላቻ እንዲፈጠር አደረጉ። ስለዚህ ጳውሎስና በርናባስ የጌታን ነገር በድፍረት እየተናገሩ እዚያ ብዙ ጊዜ ቈዩ፤ ጌታም ተአምራትና ድንቅ ነገሮች በእነርሱ እጅ እንዲደረጉ ሥልጣን በመስጠት፥ የእርሱ የጸጋ ቃል እውነተኛ መሆኑን ያረጋግጥ ነበር። የከተማው ነዋሪዎች ግን፥ በሁለት ተከፍለው ግማሹ ከአይሁድ ጋር ግማሹም ከሐዋርያት ጋር ሆኑ። አሕዛብና አይሁድ ከአለቆቻቸው ጋር ሆነው ጳውሎስንና በርናባስን ሊያንገላቱአቸውና በድንጋይ ሊወግሩአቸው ፈለጉ፤ ጳውሎስና በርናባስ ይህን ባወቁ ጊዜ ልስጥራና ደርቤ ወደሚባሉት ወደ ሊቃኦንያ ከተሞችና በዙሪያቸው ወዳለው አገር ሸሽተው ሄዱ። እዚያም ወንጌልን ሰበኩ። በልስጥራ እግሩ የሰለለ አንድ ሰው ነበረ፤ ይህ ሰው ከተወለደ ጀምሮ ሽባ ስለ ነበር በእግሩ ሄዶ አያውቅም፤ ይህ ሰው ጳውሎስ በሚናገርበት ጊዜ ተቀምጦ ያዳምጥ ነበር፤ ጳውሎስ ሰውየውን ትኲር ብሎ ተመለከተና ለመዳን የሚያበቃው እምነት እንዳለው ባየ ጊዜ፥ “ቀጥ ብለህ በእግርህ ቁም!” ሲል በታላቅ ድምፅ ተናገረ፤ ሰውየውም ብድግ አለና መራመድ ጀመረ። ሰዎቹም ጳውሎስ ያደረገውን ባዩ ጊዜ፥ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው “አማልክት በሰው አምሳል ሆነው ወደ እኛ ወርደዋል!” በማለት በሊቃኦንያ ቋንቋ ተናገሩ። በርናባስንም “ድያ” አሉት፤ ዋናው ተናጋሪ ጳውሎስ ስለ ነበረ እርሱን “ሄርሜን” አሉት። ከከተማው ውጪ ያለው የድያ ቤተ መቅደስ ካህን ኮርማዎችንና የአበባ ጒንጒኖችን ወደ ከተማው በር አምጥቶ ከሕዝቡ ጋር በመተባበር ለጳውሎስና ለበርናባስ መሥዋዕት ሊያቀርብላቸው ፈለገ። ሐዋርያቱ ጳውሎስና በርናባስ ግን ይህን በሰሙ ጊዜ በሐዘን ልብሳቸውን ቀደዱ፤ ወደ ሕዝቡ ሮጡና እየጮኹ እንዲህ አሉ፦ “እናንተ ሰዎች ለምን ይህን ታደርጋላችሁ? እኛም እንደ እናንተ ሰዎች ነን፤ እኛ እዚህ የመጣነው እናንተ ከዚህ ከከንቱ ነገር ሁሉ ርቃችሁ ሰማይን፥ ምድርን፥ ባሕርንና በውስጣቸው የሚገኙትን ሁሉ ወደ ፈጠረው ወደ ሕያው አምላክ እንድትመለሱ መልካም ዜና ልናበሥርላችሁ ነው፤ ባለፉት ዘመኖች ሕዝቦች ሁሉ በገዛ ራሳቸው መንገድ እንዲሄዱ እግዚአብሔር ትቶአቸዋል፤ ይሁን እንጂ እርሱ እንዴት ያለ ቸር አምላክ መሆኑን የሚመሰክር መልካም ሥራ ማድረጉን አላቋረጠም፤ ከሰማይ ዝናብን አዘነበላችሁ፤ የመከር ወራትንም ሰጣችሁ፤ በምግብና በደስታ ልባችሁን አረካ።” ሐዋርያት ይህን ያኽል ቢናገሩም እንኳ ሕዝቡ ለእነርሱ መሥዋዕት እንዳያቀርብ ያስተዉት በብዙ ችግር ነው። አይሁድ ግን ከአንጾኪያና ከኢቆንዮን ወደዚያ መጥተው ሕዝቡን አሳደሙና ጳውሎስን በድንጋይ እንዲወግሩት አደረጉ፤ የሞተ መስሎአቸውም ጐትተው ከከተማ አወጡት። ነገር ግን ደቀ መዛሙርቱ መጥተው በዙሪያው በቆሙ ጊዜ ጳውሎስ ተነሣና ወደ ከተማ ገባ፤ በማግስቱም ከበርናባስ ጋር ወደ ደርቤ ሄደ። ጳውሎስና በርናባስ በደርቤ ወንጌልን አስተምረው ብዙ ሰዎችን አማኞች ካደረጉ በኋላ በልስጥራና በኢቆንዮን አልፈው በጵስድያ ወደምትገኘው አንጾኪያ ሄዱ። በእነዚያም አገሮች ሁሉ አማኞች በእምነታቸው እንዲጸኑ በማበረታታትና በመምከር “ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ለመግባት ብዙ መከራ መቀበል አለብን” እያሉ አስተማሩአቸው።

ሐዋርያት ሥራ 14:1-22 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

በኢቆንዮንም እንደ ቀድሞ ወደ አይሁድ ምኵራብ ገብተው ከአይሁድና ከግሪክ ሰዎች ብዙ እስኪያምኑ ድረስ ተናገሩ። ያላመኑት አይሁድ ግን የአሕዛብን ልብ በወንድሞች ላይ አነሣሡ፤ አስከፉም። ምልክትና ድንቅ በእጃቸው ይደረግ ዘንድ እየሰጠ ለጸጋው ቃል ስለ መሰከረው ስለ ጌታ ገልጠው እየተናገሩ ረጅም ወራት ተቀመጡ። የከተማውም ሕዝብ ተከፍለው እኩሌቶቹ ከአይሁድ እኩሌቶቹም ከሐዋርያት ጋር ሆኑ። አሕዛብና አይሁድ ግን ከአለቆቻቸው ጋር ሊያንገላቱአቸውና ሊወግሩአቸው ባሰቡ ጊዜ፥ አውቀው ልስጥራንና ደርቤን ወደሚባሉት ወደ ሊቃኦንያ ከተማዎች በእነርሱም ዙሪያ ወዳለው አገር ሸሹ፤ በዚያም ወንጌልን ይሰብኩ ነበር። በልስጥራንም እግሩ የሰለለ፥ ከእናቱም ማኅፀን ጀምሮ አንካሳ የሆነ፥ ከቶም ሄዶ የማያውቅ አንድ ሰው ተቀምጦ ነበር። ይህም ሰው ጳውሎስ ሲናገር ይሰማ ነበር፤ እርሱም ትኩር ብሎ ተመለከተውና ይድን ዘንድ እምነት እንዳለው ባየ ጊዜ፥ በታላቅ ድምፅ “ቀጥ ብለህ በእግርህ ቁም፤” አለው። ብድግ ብሎም ተንሥቶ ይመላለስ ነበር። ሕዝቡም ጳውሎስ ያደረገውን ባዩ ጊዜ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው በሊቃኦንያ ቋንቋ “አማልክት ሰዎችን መስለው ወደ እኛ ወርደዋል፤” አሉ። በርናባስንም “ድያ” አሉት፤ ጳውሎስንም እርሱ በመናገር ዋና ስለ ነበረ “ሄርሜን” አሉት። በከተማውም ፊት ቤተ መቅደስ ያለው የድያ ካህን ኮርማዎችንና የአበባን አክሊሎች ወደ ደጃፍ አምጥቶ ከሕዝቡ ጋር ሆኖ ሊሠዋላቸው ወደደ። ሐዋርያት በርናባስና ጳውሎስ ግን ይህን በሰሙ ጊዜ ልብሳቸውን ቀደው ወደ ሕዝቡ መካከል እየጮኹ ሮጡ፤ እንዲህም አሉ “እናንተ ሰዎች! ይህን ስለምን ታደርጋላችሁ? እኛ ደግሞ እንደ እናንተ የምንሰማ ሰዎች ነን፤ ከዚህም ከንቱ ነገር ሰማይንና ምድርን ባሕርንም በእርነርሱም ያለውን ሁሉ ወደ ፈጠረ ወደ ሕያው እግዚአብሔር ትመለሱ ዘንድ ወንጌልን እንሰብካለን። እርሱ ባለፉት ትውልዶች አሕዛብን ሁሉ በገዛ ራሳቸው ጐዳና ይሄዱ ዘንድ ተዋቸው። ከዚህም ሁሉ ጋር መልካም ሥራ እየሠራ፥ ከሰማይ ዝናብን ፍሬ የሚሆንበትንም ወራት ሲሰጠን፥ ልባችንንም በመብልና በደስታ ሲሞላው ራሱን ያለ ምስክር አልተወም።” ይህንም ብለው እንዳይሠዉላቸው ሕዝቡን በጭንቅ አስተዉአቸው። አይሁድ ግን ከአንጾኪያና ከኢቆንዮን መጡ፤ ሕዝቡንም አባብለው ጳውሎስን ወገሩ፤ የሞተም መስሎአቸው ከከተማ ወደ ውጭ ጐተቱት። ደቀ መዛሙርት ግን ከበውት ሳሉ፥ ተነሥቶ ወደ ከተማ ገባ። በነገውም ከበርናባስ ጋር ወደ ደርቤን ወጣ። በዚያችም ከተማ ወንጌልን ሰብከው እጅግ ደቀ መዛሙርትን ካደረጉ በኋላ፥ የደቀ መዛሙርትን ልብ እያጸኑ በሃይማኖትም ጸንተው እንዲኖሩ እየመከሩና “ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በብዙ መከራ እንገባ ዘንድ ያስፈልገናል፤” እያሉ፥ ወደ ልስጥራን ወደ ኢቆንዮንም ወደ አንጾኪያም ተመለሱ።