ሐዋርያት ሥራ 13:1-52 - Compare All Versions
ሐዋርያት ሥራ 13:1-52 NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
በአንጾኪያ ባለችው ቤተ ክርስቲያን ነቢያትና መምህራን ነበሩ፤ እነርሱም፦ በርናባስ፣ ኔጌር የተባለው ስምዖን፣ የቀሬናው ሉክዮስ፣ የአራተኛው ክፍል ገዥ የሄሮድስ ዐብሮ አደግ የነበረው ምናሔ እና ሳውል ነበሩ። እነዚህም ጌታን እያመለኩና እየጾሙ ሳሉ፣ መንፈስ ቅዱስ፣ “በርናባስንና ሳውልን እኔ ለጠራኋቸው ሥራ ለዩልኝ” አለ። እነርሱም ከጾሙና ከጸለዩ በኋላ እጃቸውን ጭነው አሰናበቷቸው። በርናባስና ሳውልም በመንፈስ ቅዱስ ተልከው ወደ ሴሌውቅያ ወረዱ፤ ከዚያም በመርከብ ወደ ቆጵሮስ ሄዱ። ስልማና በደረሱም ጊዜ በአይሁድ ምኵራቦች የእግዚአብሔርን ቃል ሰበኩ፤ ዮሐንስም እንደ አገልጋያቸው ዐብሯቸው ነበር። የቆጵሮስን ደሴት ከዳር እስከ ዳር አቋርጠው ጳፉ በደረሱ ጊዜ፣ በርያሱስ የተባለ አንድ አይሁዳዊ ጠንቋይና ሐሰተኛ ነቢይ አገኙ፤ እርሱም ሰርግዮስ ጳውሎስ ከተባለው አስተዋይ አገረ ገዥ ጋራ ነበረ። ይህ አገረ ገዥ፣ የእግዚአብሔርን ቃል ለመስማት ፈልጎ በርናባስንና ሳውልን አስጠራቸው። ጠንቋዩ ኤልማስ ግን፣ የስሙ ትርጕም እንዲህ ነበርና፣ አገረ ገዥው እንዳያምን ለማደናቀፍ ስለ ፈለገ ተቃወማቸው። ጳውሎስ የተባለውም ሳውል በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ፣ ትኵር ብሎ ተመለከተውና እንዲህ አለው፤ “አንተ የጽድቅ ሁሉ ጠላት፣ ተንኰልንና ክፋትን ሁሉ የተሞላህ የዲያብሎስ ልጅ፣ የጌታን ቀና መንገድ ከማጣመም አታርፍምን? አሁንም የጌታ እጅ በአንተ ላይ ነው፤ ዕውር ትሆናለህ፤ ከእንግዲህ የፀሓይን ብርሃን ለአንድ አፍታ እንኳ አታይም።” ወዲያውም ጭጋግና ጨለማ በላዩ ወረደ፤ እጁን ይዞ የሚመራውንም ሰው ለመፈለግ ወዲያ ወዲህ ይል ጀመር። አገረ ገዥውም የሆነውን ነገር ባየ ጊዜ፣ በጌታ ትምህርት በመደነቅ አመነ። ጳውሎስና ጓደኞቹ ከጳፉ ተነሥተው በጵንፍልያ ወደምትገኘው ወደ ጴርጌን ሄዱ፤ ዮሐንስም ከእነርሱ ተለይቶ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ። እነርሱ ግን ከጴርጌን ተነሥተው በጲስድያ ውስጥ ወዳለችው ወደ አንጾኪያ ሄዱ፤ በሰንበት ቀንም ወደ ምኵራብ ገብተው ተቀመጡ። የሕግና የነቢያት መጻሕፍት ከተነበቡ በኋላ፣ የምኵራብ አለቆች፣ “ወንድሞች ሆይ፤ ሕዝቡን የሚመክር ቃል ካላችሁ ተናገሩ” ሲሉ ላኩባቸው። ጳውሎስም ተነሥቶ በእጁ በመጥቀስ እንዲህ አለ፤ “የእስራኤል ሰዎች ሆይ፤ ደግሞም እናንተ እግዚአብሔርን የምትፈሩ ሁሉ፤ አድምጡ! የዚህ የእስራኤል ሕዝብ አምላክ፣ አባቶቻችንን መረጣቸው፤ በግብጽ ምድር እያሉም ከፍ ከፍ አደረጋቸው፤ በኀያል ክንዱም ከዚያ አወጣቸው። አርባ ዓመት ያህልም በበረሓ ታገሣቸው፤ በከነዓን ምድር የነበሩትንም ሰባት መንግሥታት አጥፍቶ፣ ምድራቸውን ለገዛ ሕዝቡ ርስት አድርጎ አወረሳቸው። ይህም ሁሉ የተፈጸመው በአራት መቶ ዐምሳ ዓመት ያህል ጊዜ ውስጥ ነበር። “ከዚህ በኋላ፣ እስከ ነቢዩ ሳሙኤል ዘመን ድረስ መሳፍንትን ሰጣቸው። ከዚያም ሕዝቡ ንጉሥ እንዲያነግሥላቸው ለመኑት፤ እግዚአብሔርም ከብንያም ወገን፣ የቂስን ልጅ ሳኦልን ሰጣቸው፤ እርሱም አርባ ዓመት ገዛቸው። ሳኦልንም ከሻረው በኋላ፣ ዳዊትን አነገሠላቸው፤ እግዚአብሔርም ስለ እርሱ፣ ‘እንደ ልቤ የሆነና እኔ የምሻውን ሁሉ የሚያደርግ የእሴይን ልጅ ዳዊትን አገኘሁ’ ሲል መሰከረለት። “እግዚአብሔርም በገባው ቃል መሠረት ከዚህ ሰው ዘር አዳኝ የሆነውን ኢየሱስን ለእስራኤል አመጣ። ኢየሱስ ከመምጣቱ በፊት፣ ዮሐንስ የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ ንስሓ ገብተው እንዲጠመቁ ሰብኮላቸው ነበር። ዮሐንስ ተልእኮውን በማጠናቀቅ ላይ ሳለ፣ ‘እኔ ማን መሰልኋችሁ? እኔ እኮ እርሱ አይደለሁም፤ ነገር ግን የእግሩን ጫማ መፍታት የማይገባኝ ከእኔ በኋላ ይመጣል’ ይል ነበር። “እናንተ ከአብርሃም ዘር የተወለዳችሁ ወንድሞች፤ ደግሞም በመካከላችሁ እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሁሉ፤ ይህ የድነት መልእክት የተላከው ለሁላችንም ነው። የኢየሩሳሌም ሰዎችና አለቆቻቸው ኢየሱስን አላወቁትም፤ ይሁን እንጂ በየሰንበቱ የሚነበበው የነቢያት ቃል እንዲፈጸም በርሱ ፈረዱበት። ለሞት የሚያበቃው አንድም ምክንያት ባያገኙበትም እንኳ ጲላጦስ የሞት ፍርድ እንዲፈርድበት ተማጸኑት። ስለ እርሱ የተጻፈውን ሁሉ ከፈጸሙ በኋላ ከተሰቀለበት ዕንጨት አውርደው በመቃብር ውስጥ አስገቡት። እግዚአብሔር ግን ከሙታን አስነሣው። ከገሊላ ጀምሮ እስከ ኢየሩሳሌም ከእነርሱ ጋራ ለነበሩትም ብዙ ቀን ታያቸው፤ እነርሱም አሁን ለሕዝቡ ምስክሮቹ ናቸው። “እኛም እግዚአብሔር ለአባቶች ቃል የገባውን የምሥራች ቃል ለእናንተ እንሰብካለን፤ ኢየሱስንም ከሙታን በማስነሣቱ ለእነርሱ የገባውን ቃል ለእኛ ለልጆቻቸው ፈጽሟል፤ ይኸውም እግዚአብሔር በሁለተኛው መዝሙር እንዲህ ብሎ ተጽፏል፤ “ ‘አንተ ልጄ ነህ፤ እኔ ዛሬ ወለድሁህ።’ ደግሞም፣ እርሱ እንዳልበሰበሰና እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው ለማረጋገጥ እንዲህ ብሏል፤ “ ‘የተቀደሰውንና የታመነውን፣ የዳዊትን በረከት እሰጣችኋለሁ።’ ስለዚህ በሌላም ስፍራ፣ “ ‘ቅዱስህ መበስበስን እንዲያይ አትፈቅድም’ ይላል። “ዳዊት በራሱ ዘመን የእግዚአብሔርን ፈቃድ ካገለገለ በኋላ አንቀላፍቷል፤ ከአባቶቹም ጋራ ተቀብሮ ሥጋው በስብሷል። እግዚአብሔር ከሙታን ያስነሣው እርሱ ግን መበስበስን አላየም። “እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፤ የኀጢአት ይቅርታ የሚገኘው በኢየሱስ በኩል መሆኑ እንደ ተሰበከላችሁ ዕወቁ፤ በርሱ የሚያምን ሁሉ በሙሴ ሕግ በኩል ማግኘት ያልተቻለውን ጽድቅ ያገኛል። ስለዚህ ነቢያት እንዲህ ብለው የተናገሩት እንዳይደርስባችሁ ተጠንቀቁ፤ “ ‘እናንተ ፌዘኞች፤ ተመልከቱ፤ ተደነቁ፤ ጥፉም፤ ማንም ቢነግራችሁ እንኳን፣ የማታምኑትን ነገር፣ እኔ በዘመናችሁ እሠራለሁና።’ ” ጳውሎስና በርናባስ ከምኵራብ ሲወጡ፣ ሰዎቹ ስለዚሁ ነገር በሚቀጥለው ሰንበት እንዲነግሯቸው ለመኗቸው። ጉባኤው ከተበተነ በኋላም፣ ብዙ አይሁድና ወደ ይሁዲ ሃይማኖት ገብተው በመንፈሳዊ ነገር የበረቱ ሰዎች፣ ጳውሎስንና በርናባስን ተከተሏቸው፤ እነርሱም አነጋገሯቸው፤ በእግዚአብሔርም ጸጋ ጸንተው እንዲኖሩ መከሯቸው። በሚቀጥለውም ሰንበት የከተማው ሕዝብ፣ ጥቂቱ ሰው ብቻ ሲቀር፣ በሙሉ የጌታን ቃል ለመስማት ተሰበሰቡ። አይሁድም ብዙ ሕዝብ ባዩ ጊዜ፣ በቅናት ተሞሉ፤ የጳውሎስንም ንግግር እየተቃወሙ ይሰድቡት ነበር። ጳውሎስና በርናባስም በድፍረት እንዲህ አሏቸው፤ “የእግዚአብሔር ቃል በመጀመሪያ ለእናንተ መነገር አለበት፤ እናንተ ግን ናቃችሁት፤ በዚህም የዘላለም ሕይወት እንደማይገባችሁ በራሳችሁ ላይ ስለ ፈረዳችሁ፣ እኛም ወደ አሕዛብ ዞር ለማለት እንገደዳለን። ደግሞም ጌታ እንዲህ ብሎ አዝዞናል፤ “ ‘ድነትን እስከ ምድር ዳርቻ ታደርስ ዘንድ፣ ለአሕዛብ ብርሃን አድርጌሃለሁ።’ ” አሕዛብ ይህን በሰሙ ጊዜ ደስ አላቸው፤ ለጌታም ቃል ክብርን ሰጡ፤ ለዘላለም ሕይወት የተዘጋጁትም ሁሉ አመኑ። የጌታም ቃል በአካባቢው ባለው አገር ሁሉ ተስፋፋ። አይሁድ ግን በመንፈሳዊ ነገር የተጉትንና የከበሩትን ሴቶች፣ እንዲሁም የከተማውን ታላላቅ ወንዶች ቀስቅሰው በጳውሎስና በበርናባስ ላይ ስደትን አስነሡ፤ ከአገራቸውም አስወጧቸው። ጳውሎስና በርናባስም ለማስጠንቀቂያ እንዲሆን የእግራቸውን ትቢያ አራግፈው ወደ ኢቆንዮን ሄዱ። ደቀ መዛሙርቱም በደስታና በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ።
ሐዋርያት ሥራ 13:1-52 አማ05 (አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም)
በአንጾኪያ ባለችው ቤተ ክርስቲያን ነቢያት ተብለው የሚጠሩ ሰባኪዎችና መምህራን ነበሩ፤ እነርሱም፦ በርናባስ፥ ጥቊር የተባለው ስምዖን፥ የቀሬናው ሉክዮስ፥ የአራተኛው ክፍል ገዢ የሄሮድስ አብሮ ዐደግ የነበረው ምናሔና ሳውል ነበሩ። እነርሱ ጌታን ሲያገለግሉና ሲጾሙ ሳሉ መንፈስ ቅዱስ “እኔ ለመረጥኳቸው ሥራ በርናባስንና ሳውልን ለዩልኝ!” አለ። እነርሱም ጾመውና ጸልየው እጆቻቸውን ከጫኑባቸው በኋላ ላኳቸው። በርናባስና ሳውል በመንፈስ ቅዱስ ተልከው ወደ ሴሌውቅያ ሄዱ፤ ከዚያም በመርከብ ወደ ቆጵሮስ ተጓዙ። ወደ ሰላሚስ ከተማ በደረሱ ጊዜ በአይሁድ ምኲራቦች የእግዚአብሔርን ቃል አስተማሩ፤ ዮሐንስ ማርቆስም ከእነርሱ ጋር ሆኖ ይረዳቸው ነበር። የቆጵሮስን ደሴት አቋርጠው ወደ ጳፉ በደረሱ ጊዜ ባርየሱስ የሚባለውን አንድ አይሁዳዊ ጠንቋይ አገኙ፤ እርሱ ሐሰተኛ ነቢይ ነበር። የሚኖረውም ሰርግዮስ ጳውሎስ ከሚባለው አስተዋይ አገረ ገዢ ጋር ነበረ፤ ይህ አገረ ገዢ በርናባስንና ሳውልን አስጠርቶ የእግዚአብሔርን ቃል ለመስማት ፈለገ። ነገር ግን በግሪክ ቋንቋ “ኤሊማስ” ተብሎ የሚጠራው ጠንቋይ ባርየሱስ አገረ ገዢው እንዳያምን ፈልጎ በርናባስንና ሳውልን ተቃወማቸው። ጳውሎስ የተባለው ሳውል ግን በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ ሰውየውን ትኲር ብሎ ተመለከተውና እንዲህ አለው፦ “አንተ የዲያብሎስ ልጅ! የእውነት ሁሉ ጠላት! ማታለልና ክፋት ሁሉ የሞላብህ፥ ቀጥተኛውን የጌታን መንገድ ማጣመም አትተውምን! አሁንም እነሆ፥ የጌታ እጅ ይመታሃል፤ ዕውርም ትሆናለህ፤ ለጥቂት ጊዜም የፀሐይን ብርሃን አታይም።” ወዲያውኑ ዐይኖቹን ጭጋግና ጨለማ ሸፈናቸው፤ እጁን ይዞ የሚመራውንም ሰው ዙሪያውን መፈለግ ጀመረ። አገረ ገዢውም የሆነውን ነገር ባየ ጊዜ አመነ፤ ስለ ጌታ በሰማውም ትምህርት ተደነቀ። ከዚህ በኋላ ጳውሎስና ጓደኞቹ በመርከብ ተሳፍረው ከጳፉ በጵንፍልያ ወደምትገኘው ወደ ጴርጌ ሄዱ፤ ማርቆስ የተባለው ዮሐንስ ግን ከእነርሱ ተለይቶ ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሶ ሄደ። እነርሱ ግን ከጴርጌ ተነሥተው በጲስድያ ወደምትገኘው ወደ አንጾኪያ ሄዱ፤ በሰንበት ቀን ወደ አንድ ምኲራብ ገብተው ተቀመጡ። የሕግና የነቢያት መጻሕፍት ከተነበቡ በኋላ የምኲራቡ አለቆች “ወንድሞች ሆይ፥ ሕዝቡን የሚያጽናና የምክር ቃል ካላችሁ ተናገሩ” ብለው ወደነጳውሎስ ሰው ላኩ። ስለዚህ ጳውሎስ ተነሣና ሕዝቡን በእጁ ጠቀሰ፤ እንዲህም ሲል ተናገረ፤ “የእስራኤል ሰዎችና እግዚአብሔርን የምትፈሩ እናንተ አሕዛብ! ስሙ! የዚህ የእስራኤል ሕዝብ አምላክ የቀድሞ አባቶቻችንን መረጠ፤ በግብጽ አገር በነበሩበት ጊዜም ትልቅ ሕዝብ አደረጋቸው፤ በታላቅ ኀይሉም ከዚያ አገር አወጣቸው። ለአርባ ዓመትም ያኽል በበረሓ ታገሣቸው ከዚያም በኋላ በከነዓን አገር ሰባት መንግሥታትን አጥፍቶ የእነርሱን ምድር አወረሳቸው፤ ከዚህም በኋላ ለአራት መቶ ኀምሳ ዓመት ያኽል እስከ ነቢዩ ሳሙኤል ድረስ መሳፍንትን ሰጣቸው። “ከዚያም ቀጥሎ ንጉሥ እንዲያነግሥላቸው እግዚአብሔርን ለመኑ፤ እግዚአብሔርም ከብንያም ወገን የሆነውን የቂስን ልጅ ሳኦልን ለአርባ ዓመት አነገሠላቸው። ሳኦልንም ከሻረው በኋላ ዳዊትን አነገሠላቸው፤ እግዚአብሔር ስለ ዳዊት ሲመሰክር፦ ‘እንደ ፍላጎቴ የሚሆንልኝን፤ ፈቃዴንም የሚፈጽመውን፥ የእሴይን ልጅ ዳዊትን አገኘሁ’ ብሎአል። ከዚህ ሰው ዘር እግዚአብሔር በገባው የተስፋ ቃል መሠረት የእስራኤልን አዳኝ ኢየሱስን አስነሣላቸው። ኢየሱስ ከመምጣቱ በፊት ዮሐንስ ለእስራኤል ሰዎች ሁሉ የንስሓን ጥምቀት ሰብኮ ነበር። ዮሐንስ ሥራውን በጨረሰ ጊዜ ‘እኔ ማን መሰልኳችሁ? እኔ መሲሕ አይደለሁም፤ ነገር ግን የጫማውን ማሰሪያ ለመፍታት እንኳ የማልበቃ ከእኔ በኋላ ሌላ ይመጣል’ ይል ነበር። “እናንተ ከአብርሃም ዘር የተወለዳችሁ ወንድሞችና እናንተም እግዚአብሔርን የምትፈሩ አሕዛብ! ይህ የመዳን ቃል የተላከው ለእኛ ነው። በኢየሩሳሌም የሚኖሩ ሰዎችና አለቆቻቸው ኢየሱስ አዳኝ መሆኑን አላወቁም፤ በየሰንበቱም የሚነበቡትን የነቢያት መጻሕፍት ባለማስተዋላቸው በእርሱ ላይ በፈረዱበት ጊዜ ትንቢቱ ተፈጻሚ እንዲሆን አድርገዋል። ምንም እንኳ ለሞት የሚያበቃ ምክንያት ባያገኙበት እርሱን እንዲገድልላቸው ጲላጦስን ለመኑት። ስለ እርሱ የተጻፈውን ሁሉ ከፈጸሙበት በኋላ ከመስቀል አውርደው ቀበሩት፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ከሞት አስነሣው። ከገሊላ ወደ ኢየሩሳሌም ከእርሱ ጋር ለመጡትም ብዙ ቀን ታያቸው፤ እነርሱም አሁን በሕዝብ ፊት ምስክሮቹ ናቸው። እኛም ይዘንላችሁ የመጣነው እግዚአብሔር ለአባቶቻችን በተስፋ የሰጠውን መልካም ዜና ነው። እግዚአብሔር ኢየሱስን ከሞት በማስነሣቱ ይህንኑ ተስፋ ለእኛ ለልጆቻቸው ፈጽሞታል፤ ይህም በሁለተኛው መዝሙር፥ ‘አንተ ልጄ ነህ፥ እኔ ዛሬ ወልጄሃለሁ፤’ ተብሎ እንደ ተጻፈው ነው። መበስበስ እንዳይደርስበት እግዚአብሔር ከሞት እንዳስነሣው ለማስረዳት፥ ‘ቅዱሱን የታመነ በረከትን ለዳዊት የተሰጠውን ተስፋ እሰጣችኋለሁ’ ብሎ ተናግሮአል። ደግሞም በሌላ መዝሙር፥ ‘ቅዱሱ ልጅህ መበስበስ እንዲደርስበት አታደርገውም’ ይላል። ነገር ግን ዳዊት በሕይወቱ ዘመን አገልግሎቱን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ከፈጸመ በኋላ ሞቶአል፤ ከአባቶቹም ጋር ተቀብሮአል፤ መበስበስም ደርሶበታል። እግዚአብሔር ከሞት ያስነሣው ግን መበስበስ አልደረሰበትም። እንግዲህ ወንድሞች ሆይ! የኃጢአት ይቅርታ የሚገኘው በኢየሱስ መሆኑ እንደ ተሰበከላችሁ ዕወቁ፤ በእርሱ የሚያምን ሁሉ በሙሴ አማካይነት የተሰጠው ሕግ ነጻ ሊያወጣው ከማይችለው ኃጢአት ሁሉ ነጻ ይወጣል። ስለዚህ በነቢያት እንዲህ ተብሎ የተነገረው እንዳይደርስባችሁ ተጠንቀቁ፤ ‘እናንተ ፌዘኞች እዩ! ተደነቁ! ጥፉም! ማንም ሰው ቢያወራላችሁ የማታምኑትን ሥራ በዘመናችሁ እሠራለሁ።’ ” ጳውሎስና በርናባስ ከምኲራብ ሲወጡ ይህንኑ ነገር በሚመጣው ሰንበት እንደገና እንዲነግሩአቸው ሰዎቹ ለመኑአቸው። የምኲራቡ ጉባኤ በተበተነ ጊዜ ብዙ የአይሁድ ወገኖችና ወደ አይሁድ እምነት ገብተው እግዚአብሔርን የሚያመልኩ ሰዎች ጳውሎስንና በርናባስን ተከተሉአቸው፤ ጳውሎስና በርናባስም ሰዎቹን በማስተማር በእግዚአብሔር ጸጋ ጸንተው እንዲኖሩ አሳሰቡአቸው። በሚቀጥለው ሰንበት ከከተማው ነዋሪዎች አብዛኞቻቸው የእግዚአብሔርን ቃል ለመስማት ተሰበሰቡ፤ አይሁድ የሕዝቡን ብዛት ባዩ ጊዜ በቅናት ተሞሉ፤ ንግግሩንም እየተቃወሙ ጳውሎስን ሰደቡት፤ ጳውሎስና በርናባስ ግን እንዲህ ሲሉ በድፍረት ተናገሩ፤ “የእግዚአብሔር ቃል አስቀድሞ ለእናንተ እንዲነገር አስፈላጊ ነው፤ እናንተ አንቀበልም ካላችሁና የዘለዓለም ሕይወት እንደማይገባችሁ በራሳችሁ ከፈረዳችሁ ግን እነሆ፥ እኛ ዞር ብለን ወደ አሕዛብ እንሄዳለን። ይህንንም የምናደርገው ጌታ፦ ‘መዳንን እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ እንድታመጣ ለአሕዛብ ብርሃን አድርጌሃለሁ’ በማለት ስላዘዘን ነው።” አሕዛብ ይህን በሰሙ ጊዜ ደስ አላቸው፤ የጌታንም ቃል አከበሩ፤ ለዘለዓለም ሕይወት የተመረጡትም ሁሉ አመኑ። የጌታም ቃል በዚያ አገር ሁሉ ተስፋፋ። የአይሁድ መሪዎች ግን የአይሁድ እምነት ተከታዮች የሆኑትን ሀብታሞች ሴቶችና የከተማውን ታላላቅ ሰዎች አሳድመው በጳውሎስና በበርናባስ ላይ ስደት እንዲነሣ አደረጉ፤ ከአገራቸውም አስወጡአቸው። ጳውሎስና በርናባስም በእነርሱ ላይ የእግራቸውን አቧራ አራግፈው ወደ ኢቆንዮን ሄዱ። ደቀ መዛሙርቱም በደስታና በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ።
ሐዋርያት ሥራ 13:1-52 አማ2000 (የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ))
በአንጾኪያ በነበረችው ቤተ ክርስቲያንም ነቢያትና መምህራን ነበሩ፤ እነርሱም በርናባስ፥ ኔጌር የተባለው ስምዖን፥ የቀሬናው ሉቅዮስ፥ ከአራተኛው ክፍል ገዢ ከሄሮድስ ጋር ያደገው ምናሔ፥ ሳውልም ነበሩ። የእግዚአብሔርን ሥራ ሲሠሩ፥ ሲጾሙም መንፈስ ቅዱስ፥ “በርናባስንና ሳውልን እኔ ለፈለግኋቸው ሥራ ለዩልኝ” አላቸው። ያንጊዜም ከጾሙና ከጸለዩ፥ እጃቸውንም በራሳቸው ላይ ከጫኑባቸው በኋላ ላኩአቸው። ከመንፈስ ቅዱስም ተልከው ወደ ሴሌውቅያ ወረዱ፤ ከዚያም በመርከብ ወደ ቆጵሮስ ሄዱ። ወደ ሰልሚና ሀገርም ገብተው በአይሁድ ምኵራቦች የእግዚአብሔርን ቃል አስተማሩ፤ ዮሐንስም እየአገለገላቸው ከእነርሱ ጋር ነበር። በደሴቲቱም ሁሉ ሲዘዋወሩ ጳፉ ወደምትባል ሀገር ደረሱ፤ በዚያም አንድ አይሁዳዊ የሆነ ሐሰተኛ ነቢይና አስማተኛ ሰው አገኙ፤ ስሙም በርያሱስ ይባላል። እርሱም ብልህ ሰው በሆነ ሰርግዮስ ጳውሎስ በሚባል አገረ ገዢ ዘንድ ይኖር ነበረ። የእግዚአብሔርንም ቃል ሊሰማ ወድዶ በርናባስንና ሳውልን ወደ እርሱ ጠራቸው። አስማተኛው ኤልማስም የስሙ ትርጓሜ እንዲህ ነበረና፥ ገዥውን ከማመን ሊከለክለው ፈልጎ ተቃወማቸው። ጳውሎስ በተባለው በሳውል ላይም ቅዱስ መንፈስ ሞላበት፤ አተኵሮም ተመለከተው። እንዲህም አለው፥ “ሽንገላንና ክፋትን ሁሉ የተመላህ፥ የሰይጣን ልጅ፥ የጽድቅ ሁሉ ጠላት ሆይ፥ የቀናውን የእግዚአብሔርን መንገድ ማጣመምህን ትተው ዘንድ እንቢ አልህን? እነሆ፥ አሁን የእግዚአብሔር እጅ በአንተ ላይ ነው፤ ዕውርም ትሆናለህ፤ እስከ ጊዜውም ፀሐይን አታይም፤” ወዲያውኑም ታወረ፤ ጨለማም ዋጠው፤ የሚመራውም ፈለገ። አገረ ገዢውም የሆነውን በአየ ጊዜ ተገረመ፤ በጌታችን ትምህርትም አመነ። ከዚህም በኋላ እነ ጳውሎስ ከጳፉ ከተማ ወጥተው ሄዱና የጵንፍልያ አውራጃ ወደምትሆን ወደ ጰርጌን ገቡ፤ ዮሐንስ ግን ትቶአቸው ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ። እነርሱም ከጰርጌን አልፈው የጲስድያ አውራጃ ወደምትሆን ወደ አንጾኪያ ደረሱ፤ በሰንበት ቀንም ወደ ምኵራብ ገብተው ተቀመጡ። ኦሪትንና ነቢያትን ካነበቡ በኋላም የምኵራቡ አለቆች፥ “እናንተ ወንድሞቻችን ሆይ፥ ለሕዝብ ሊነገር የሚገባው የምክር ቃል እንደ አላችሁ ተናገሩ” ብለው ላኩባቸው። ጳውሎስም ተነሥቶ ዝም እንዲሉ አዘዘና እንዲህ አላቸው፥ “እናንት የእስራኤል ሰዎችና እግዚአብሔርንም የምትፈሩ ሁሉ፥ ስሙ። የእስራኤል ሕዝብ አምላክ አባቶቻችንን መረጣቸው፤ ወገኖቹንም በተሰደዱበት በምድረ ግብፅ ከፍ ከፍ አደረጋቸው፤ ከዚያም ከፍ ባለ ክንዱ አወጣቸው። አርባ ዘመንም በምድረ በዳ መገባቸው። ሰባቱን የከነዓንን አሕዛብ አጥፍቶ ምድራቸውን አወረሳቸው። ከዚህም በኋላ አራት መቶ አምሳ ዓመት እስከ ነቢዩ እስከ ሳሙኤል ዘመን ድረስ መሳፍንትን ሾመላቸው። ከዚያም ወዲያ ንጉሥ ያነግሥላቸው ዘንድ ለመኑ፤ እግዚአብሔርም ከብንያም ነገድ የተወለደውን ሰው የቂስን ልጅ ሳኦልን አርባ ዓመት አነገሠላቸው። እርሱንም ሻረው፤ ከእርሱም በኋላ ዳዊትን አነገሠላቸው፤ ‘የእሴይን ልጅ ዳዊትን ፈቃዴን ሁሉ የሚፈጽም እንደ ልቤም የታመነ ሰው ሆኖ አገኘሁት’ ብሎ መሰከረለት። እግዚአብሔር ተስፋ እንደ ሰጣቸው ከዳዊት ዘር ለእስራኤል መድኀኒት አድርጎ ኢየሱስን አመጣላቸው። እርሱ ከመምጣቱ አስቀድሞ ዮሐንስ ለእስራኤል ሕዝብ ሁሉ የንስሓ ጥምቀትን ሰበከላቸው። ዮሐንስም መልእክቱን ሲፈጽም እንዲህ አላቸው፦ ‘እኔን ለምን ትጠራጠሩኛላችሁ? እርሱን አይደለሁም፤ የጫማውን ማዘቢያ ከእግሩ ልፈታ የማይገባኝ ከእኔ በኋላ እነሆ፥ ይመጣል።’ “እናንተ ከአብርሃም ወገን የተወለዳችሁ ወንድሞቻችን እግዚአብሔርንም የምትፈሩ፥ ይህ የሕይወት ቃል ለእናንተ ተልኮአል። በኢየሩሳሌም የሚኖሩና አለቆቻቸው ግን እርሱን አላወቁም፤ የነቢያት መጻሕፍትንም በየሰንበቱ ሁሉ ሲያነቡ አላስተዋሉትም፤ ነገር ግን ይሙት በቃ ፈረዱበት፥ ስለ እርሱ የተጻፈውንም ሁሉ ፈጸሙበት። ለሞትም የሚያበቃ ምንም በደል ባላገኙበት ጊዜ እንዲገድለው ጲላጦስን ለመኑት። ስለ እርሱም የተጻፈውን ሁሉ ከፈጸሙ በኋላ ከመስቀል አውርደው በመቃብር ቀበሩት። እግዚአብሔር ግን ከሙታን ለይቶ አስነሣው። ከተነሣም በኋላ ከገሊላ ወደ ኢየሩሳሌም አብረውት ለወጡት ብዙ ቀን ተገለጠላቸው። እነርሱም በሕዝብ ዘንድ ምስክሮች ሆኑት። “እኛም እግዚአብሔር ለአባቶቻችን ያናገረላቸውን ተስፋ እንነግራችኋለን። በሁለተኛው መዝሙር፦ ‘አንተ ልጄ ነህ፤ እኔ ዛሬ ወለድሁህ’ እንዳለ ኢየሱስን አስነሥቶ ተስፋውን ለእኛ ለልጆቻቸው ፈጽሞአል። መፍረስ መበስበስንም እንዳያይ እግዚአብሔር ከሙታን ለይቶ እንዳስነሣው እንዲህ አለ፦ ‘የታመነውን የዳዊትን ቅዱስ ተስፋ እሰጣችኋለሁ። በሌላ ስፍራም እንዲህ ይላል፦ ‘ጻድቅህን መፍረስ መበስበስን ያይ ዘንድ አትሰጠውም።’ ዳዊት ግን በዘመኑ ለእግዚአብሔር ትእዛዝ አገልግሎአል፤ እንደ አባቶቹ ሞተ፥ ተቀበረም፤ መፍረስ መበስበስንም አይቶአል። ይህ እግዚአብሔር ያስነሣው ግን መፍረስ መበስበስን አላየም። እንግዲህ ወንድሞቻችን፥ በእርሱ ኀጢአታችሁ እንደሚሰረይላችሁ ተስፋ የሰጣችሁን ዕወቁ። ከሁሉም ይልቅ በሙሴ ሕግ መጽደቅ የተሳናችሁ ናችሁ። በእርሱ ግን ያመነ ሁሉ ይጸድቃል። እንግዲህ እንዲህ የሚለው የነቢያት ቃል እንዳይደርስባችሁ ተጠንቀቁ። ‘እነሆ፥ እናንተ የምታቃልሉ፥ እዩ፤ ተደነቁም፤ ያለዚያ ግን ትጠፋላችሁ፤ ማንም ቢነግራችሁ የማታምኑትን ሥራ እኔ በዘመናችሁ እሠራለሁና።’ ” ከምኵራብም ከወጡ በኋላ ይህን ነገር በሁለተኛው ሰንበት እንዲነግሩአቸው ማለዱአቸው። ጉባኤውም በተፈታ ጊዜ ከአይሁድና ወደ ይሁዲነት ከተመለሱት ከደጋጉ ሰዎች ብዙዎች ጳውሎስንና በርናባስን ተከተሉአቸው፤ እነርሱም በእግዚአብሔር ጸጋ ይድኑ ዘንድ እያስረዱ ነገሯቸው። በሁለተኛው ሰንበትም የከተማው ሰዎች ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃል ይሰሙ ዘንድ ተሰበሰቡ። አይሁድም የተሰበሰበውን ብዙ ሕዝብ ባዩ ጊዜ ቀኑባቸው፤ እየተሳደቡም ጳውሎስ የተናገረውን ቃል ተቃወሙ። ጳውሎስና በርናባስም ደፍረው እንዲህ ብለው ተናገሩአቸው፥ “የእግዚአብሔርን ቃል ለእናንተ አስቀድሞ ልንነግራችሁ ይገባል፤ እንቢ ብትሉና ራሳችሁን ለዘለዓለም ሕይወት የተዘጋጀ ባታደርጉ ግን እነሆ፥ ወደ አሕዛብ እንመለሳለን። እግዚአብሔር፦ እስከ ምድር ዳርቻ ላሉት ሁሉ መድኀኒት ትሆን ዘንድ ለአሕዛብ ብርሃን አድርጌሃለሁ” ብሎ አዝዞናልና። አሕዛብም ይህን ሰምተው ደስ አላቸው፤ የእግዚአብሔርንም ቃል አከበሩ፤ ለዘለዓለም ሕይወትም የተዘጋጁ ሁሉ አመኑ። የእግዚአብሔርም ቃል በሀገሩ ሁሉ ተዳረሰ። አይሁድ ግን እግዚአብሔርን የሚፈሩ የከበሩ ሴቶችንና የከተማውን ሽማግሌዎች አነሳሡአቸው፤ በጳውሎስና በበርናባስ ላይም ስደትን አስነሡ፤ ከሀገራቸውም አባረሩአቸው። እነርሱ ግን የእግራቸውን ትቢያ አራግፈውባቸው ወደ ኢቆንዮን ሄዱ። መንፈስ ቅዱስም በደቀ መዛሙርት ላይ ሞላ፤ ደስም አላቸው።
ሐዋርያት ሥራ 13:1-52 አማ54 (መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት))
በአንጾኪያም ባለችው ቤተ ክርሲቲያን ነቢያትና መምህራን ነበሩ፤ እነርሱም በርናባስ፥ ኔጌር የተባለው ስምዖንም፥ የቀሬናው ሉክዮስም፥ የአራተኛው ክፍል ገዥ የሄሮድስም ባለምዋል ምናሔ፥ ሳውልም ነበሩ። እነዚህም ጌታን ሲያመልኩና ሲጦሙ መንፈስ ቅዱስ፦ “በርናባስንና ሳውልን ለጠራኋቸው ሥራ ለዩልኝ” አለ። በዚያን ጊዜም ከጦሙ ከጸለዩም እጃቸውንም ከጫኑ በኋላ አሰናበቱአቸው። እነርሱም በመንፈስ ቅዱስ ተልከው ወደ ሴሌውቅያ ወረዱ፤ ከዚያም በመርከብ ወደ ቆጵሮስ ሄዱ። በስልማናም በነበሩ ጊዜ በአይሁድ ምኵራቦች የእግዚአብሔርን ቃል ሰበኩ፤ አገልጋይም ዮሐንስ ነበራቸው። ደሴቲቱንም ሁሉ እስከ ጳፉ በዞሩ ጊዜ፥ በርያሱስ የሚሉትን ጠንቋይና ሐሰተኛ ነቢይ የሆነውን አንድ አይሁዳዊ ሰው አገኙ፤ እርሱም አስተዋይ ሰው ከሆነው ሰርግዮስ ጳውሎስ ከሚባለው አገረ ገዥ ጋር ነበረ። ይህም በርናባስንና ሳውልን ወደ እርሱ ጠርቶ የእግዚአብሔርን ቃል ሊሰማ ፈለገ። ጠንቋዩ ግን ኤልማስ፥ ስሙ እንዲሁ ይተረጐማልና፥ አገረ ገዡን ከማመን ሊያጣምም ፈልጎ ተቃወማቸው። ጳውሎስ የተባለው ሳውል ግን መንፈስ ቅዱስን ተሞልቶ ትኵር ብሎ ሲመለከተው፦ “አንተ ተንኰል ሁሉ ክፋትም ሁሉ የሞላብህ፥ የዲያብሎስ ልጅ፥ የጽድቅም ሁሉ ጠላት፥ የቀናውን የጌታን መንገድ ከማጣመም አታርፍምን? አሁንም፥ እነሆ፥ የጌታ እጅ በአንተ ላይ ናት፥ ዕውርም ትሆናለህ እስከ ጊዜውም ፀሐይን አታይም” አለው። ያን ጊዜም ጭጋግና ጨለማ ወደቀበት፥ በእጁም የሚመራውን እየዞረ ፈለገ። በዚያን ጊዜ አገረ ገዡ የተደረገውን ባየ ጊዜ ከጌታ ትምህርት የተነሣ ተገርሞ አመነ። ጳውሎስም ከጓደኞቹ ጋር ከጳፉ ተነሥቶ የጵንፍልያ ወደምትሆን ወደ ጴርጌን መጣ፤ ዮሐንስም ከእነርሱ ተለይቶ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ። እነርሱ ግን ከጴርጌን አልፈው የጲስድያ ወደምትሆን ወደ አንጾኪያ ደረሱ፤ በሰንበትም ቀን ወደ ምኵራብ ገብተው ተቀመጡ። ሕግና ነቢያትም ከተነበቡ በኋላ የምኵራቡ አለቆች፦ “ወንድሞች ሆይ፥ ሕዝብን የሚመክር ቃል እንዳላችሁ ተናገሩ” ብለው ላኩባቸው። ጳውሎስም ተነሣና በእጁ ጠቅሶ እንዲህ አለ፦ “የእስራኤል ሰዎችና እግዚአብሔርን የምትፈሩት ሆይ፥ ስሙ። የዚህ የእስራኤል ሕዝብ አምላክ አባቶቻችንን መርጦ በግብፅ አገር በእንግድነት ሳሉ ሕዝቡን ከፍ ከፍ አደረጋቸው፥ ከፍ ባለችውም ክንዱ ከዚያ አወጣቸው። በበረሀም አርባ ዓመት ያህል መገባቸው። በከነዓንም አገር ሰባት አሕዛብን አጥፍቶ ምድራቸውን አወረሳቸው። ከዚህም በኋላ እስከ ነቢዩ እስከ ሳሙኤል ድረስ አራት መቶ አምሳ ዓመት ያህል መሳፍንትን ሰጣቸው። ከዚያም ወዲያ ንጉሥን ያነግሥላቸው ዘንድ ለመኑ፥ እግዚአብሔርም ከብንያም ወገን የሚሆን ሰው የቂስን ልጅ ሳኦልን አርባ ዓመት ሰጣቸው፤ እርሱንም ከሻረው በኋላ ዳዊትን በእነርሱ ላይ እንዲነግሥ አስነሣው፥ ሲመሰክርለትም፦ እንደ ልቤ የሆነ ሰው ፈቃዴንም ሁሉ የሚያደርግ የእሴይን ልጅ ዳዊትን አገኘሁ አለ። ከዚህም ሰው ዘር እግዚአብሔር እንደ ተስፋው ቃል ለእስራኤል መድኃኒትን እርሱም ኢየሱስን አመጣ። ከመምጣቱ በፊት ዮሐንስ አስቀድሞ ለእስራኤል ሕዝብ ሁሉ የንስሐን ጥምቀት ሰብኮ ነበር። ዮሐንስም ሩጫውን ሲፈጽም ሳለ፦ ‘እኔ ማን እንደ ሆንሁ ታስባላችሁ? እኔስ እርሱን አይደለሁም፤ ነገር ግን እነሆ፥ የእግሩን ጫማ እፈታ ዘንድ ከማይገባኝ ከእኔ በኋላ ይመጣል’ ይል ነበር። እናንተ ወንድሞቻችን፥ የአብርሃም ዘር ልጆች ከእናንተ መካከልም እግዚአብሔርን የምትፈሩ ሆይ፥ ለእናንተ የዚህ የመዳን ቃል ተላከ። በኢየሩሳሌም የሚኖሩ ሰዎችና አለቆቻቸው እርሱንና በየሰንበቱ የሚነበቡትን የነቢያትን ድምፆች ስላላወቁ በፍርዳቸው ፈጽመዋልና፤ ለሞትም የሚያደርስ ምክንያት አንድ ስንኳ ባያገኙበት፥ ይገድለው ዘንድ ጲላጦስን ለመኑት፤ ስለ እርሱም የተጻፈውን ሁሉ በፈጸሙ ጊዜ ከእንጨት አውርደው በመቃብር አኖሩት። እግዚአብሔር ግን ከሙታን አስነሣው፤ በሕዝብም ዘንድ ምስክሮቹ ለሆኑት ከእርሱ ጋር ከገሊላ ወደ ኢየሩሳሌም ለወጡት ብዙ ቀን ታያቸው። እኛም ለአባቶች የተሰጠውን ተስፋ የምስራቹን ለእናንተ እንሰብካለን፤ ይህን ተስፋ እግዚአብሔር በሁለተኛው መዝሙር ደግሞ፦ ‘አንተ ልጄ ነህ እኔ ዛሬ ወለድሁህ’ ተብሎ እንደ ተጻፈ፥ ኢየሱስን አስነሥቶ ለእኛ ለልጆቻቸው ፈጽሞአልና። እንደገናም ወደ መበስበስ እንዳይመለስ ከሙታን እንደ አስነሣው፥ እንዲህ፦ ‘የታመነውን የዳዊትን ቅዱስ ተስፋ እሰጣችኋለሁ ብሎአል።’ ደግሞ በሌላ ስፍራ፦ ‘ቅዱስህን መበስበስን ያይ ዘንድ አትሰጠውም’ ይላልና። ዳዊትም በራሱ ዘመን የእግዚአብሔርን አሳብ ካገለገለ በኋላ አንቀላፋ፥ ከአባቶቹም ጋር ተጨምሮ መበስበስን አየ፤ ይህ እግዚአብሔር ያስነሣው ግን መበስበስን አላየም። እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፥ በእርሱ በኩል የኃጢአት ስርየት እንዲነገርላችሁ፥ በሙሴም ሕግ ትጸድቁበት ዘንድ ከማይቻላችሁ ሁሉ ያመነ ሁሉ በእርሱ እንዲጸድቅ በእናንተ ዘንድ የታወቀ ይሁን። እንግዲህ፦ እናንተ የምትንቁ፥ እዩ ተደነቁም ጥፉም አንድ ስንኳ ቢተርክላችሁ የማታምኑትን ሥራ በዘመናችሁ እኔ እሠራለሁና ተብሎ በነቢያት የተነገረው እንዳይደርስባችሁ ተጠንቀቁ።” በወጡም ጊዜ ይህን ነገር በሚመጣው ሰንበት ይነግሩአቸው ዘንድ ለመኑአቸው። ጉባኤውም ከተፈታ በኋላ ከአይሁድና ወደ ይሁዲነት ገብተው ከሚያመልኩ ብዙዎች ጳውሎስንና በርናባስን ተከተሉአቸው፥ እነርሱም ሲነግሩአቸው በእግዚአብሔር ጸጋ ጸንተው እንዲኖሩ አስረዱአቸው። በሁለተኛውም ሰንበት ከጥቂቶቹ በቀር የከተማው ሰው ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃል ይሰሙ ዘንድ ተሰበሰቡ። አይሁድም ብዙ ሕዝብ ባዩ ጊዜ ቅንዓት ሞላባቸው፥ እየተሳደቡም ጳውሎስ የተናገረውን ቃል ተቃወሙ። ጳውሎስና በርናባስም ገልጠው፦ “የእግዚአብሔር ቃል አስቀድሞ ለእናንተ ይነገር ዘንድ ያስፈልጋል፤ ከገፋችሁትና የዘላለም ሕይወት እንዳይገባችሁ በራሳችሁ ከፈረዳችሁ ግን፥ እነሆ፥ ወደ አሕዛብ ዘወር እንላለን። እንዲሁ ጌታ፦ ‘እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ለማዳን ትሆን ዘንድ ለአሕዛብ ብርሃን አድርጌሃለሁ’ ብሎ አዞናልና” አሉ። አሕዛብም ሰምተው ደስ አላቸው የእግዚአብሔርንም ቃል አከበሩ፥ ለዘላለም ሕይወትም የተዘጋጁ ሁሉ አመኑ፤ የጌታም ቃል በአገሩ ሁሉ ተስፋፋ። አይሁድ ግን የሚያመልኩትን የከበሩትንም ሴቶችና የከተማውን መኳንንት አወኩ፥ በጳውሎስና በበርናባስም ላይ ስደትን አስነሥተው ከአገራቸው አወጡአቸው። እነርሱ ግን የእግራቸውን ትቢያ አራግፈውባቸው ወደ ኢቆንዮን መጡ። በደቀ መዛሙርትም ደስታና መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው።
ሐዋርያት ሥራ 13:1-52 መቅካእኤ (መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ))
በአንጾኪያም ባለችው ቤተ ክርሲቲያን ነቢያትና መምህራን ነበሩ፤ እነርሱም በርናባስ፥ ኔጌር የተባለው ስምዖንም፥ የቀሬናው ሉክዮስም፥ የአራተኛው ክፍል ገዥ የሄሮድስም ባለምዋል ምናሔ፥ ሳውልም ነበሩ። እነዚህም ጌታን ሲያመልኩና ሲጦሙ መንፈስ ቅዱስ “በርናባስንና ሳውልን ለጠራኋቸው ሥራ ለዩልኝ፤” አለ። በዚያን ጊዜም ከጦሙ ከጸለዩም እጃቸውንም ከጫኑ በኋላ አሰናበቱአቸው። እነርሱም በመንፈስ ቅዱስ ተልከው ወደ ሴሌውቅያ ወረዱ፤ ከዚያም በመርከብ ወደ ቆጵሮስ ሄዱ። በስልማናም በነበሩ ጊዜ በአይሁድ ምኵራቦች የእግዚአብሔርን ቃል ሰበኩ፤ አገልጋይም ዮሐንስ ነበራቸው። ደሴቲቱንም ሁሉ እስከ ጳፉ በዞሩ ጊዜ፥ በርያሱስ የሚሉትን ጠንቋይና ሐሰተኛ ነቢይ የሆነውን አንድ አይሁዳዊ ሰው አገኙ፤ እርሱም አስተዋይ ሰው ከሆነው ሰርግዮስ ጳውሎስ ከሚባለው አገረ ገዥ ጋር ነበረ። ይህም በርናባስንና ሳውልን ወደ እርሱ ጠርቶ የእግዚአብሔርን ቃል ሊሰማ ፈለገ። ጠንቋዩ ግን ኤልማስ፥ ስሙ እንዲሁ ይተረጐማልና፥ አገረ ገዡን ከማመን ሊያጣምም ፈልጎ ተቃወማቸው። ጳውሎስ የተባለው ሳውል ግን መንፈስ ቅዱስን ተሞልቶ ትኩር ብሎ ሲመለከተው “አንተ ተንኰል ሁሉ ክፋትም ሁሉ የሞላብህ፥ የዲያብሎስ ልጅ፥ የጽድቅም ሁሉ ጠላት፥ የቀናውን የጌታን መንገድ ከማጣመም አታርፍምን? አሁንም፥ እነሆ፥ የጌታ እጅ በአንተ ላይ ናት፤ ዕውርም ትሆናለህ እስከ ጊዜውም ፀሐይን አታይም፤” አለው። ያን ጊዜም ጭጋግና ጨለማ ወደቀበት፤ በእጁም የሚመራውን እየዞረ ፈለገ። በዚያን ጊዜ አገረ ገዢው የተደረገውን ባየ ጊዜ ከጌታ ትምህርት የተነሣ ተገርሞ አመነ። ጳውሎስም ከጓደኞቹ ጋር ከጳፉ ተነሥቶ የጵንፍልያ ወደምትሆን ወደ ጴርጌን መጣ፤ ዮሐንስም ከእነርሱ ተለይቶ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ። እነርሱ ግን ከጴርጌን አልፈው የጲስድያ ወደምትሆን ወደ አንጾኪያ ደረሱ፤ በሰንበትም ቀን ወደ ምኵራብ ገብተው ተቀመጡ። ሕግና ነቢያትም ከተነበቡ በኋላ የምኵራቡ አለቆች “ወንድሞች ሆይ! ሕዝብን የሚመክር ቃል እንዳላችሁ ተናገሩ፤” ብለው ላኩባቸው። ጳውሎስም ተነሣና በእጁ ጠቅሶ እንዲህ አለ “የእስራኤል ሰዎችና እግዚአብሔርን የምትፈሩት ሆይ! ስሙ። የዚህ የእስራኤል ሕዝብ አምላክ አባቶቻችንን መርጦ በግብጽ አገር በእንግድነት ሳሉ ሕዝቡን ከፍ ከፍ አደረጋቸው፤ ከፍ ባለችውም ክንዱ ከዚያ አወጣቸው። በበረሃም አርባ ዓመት ያህል መገባቸው። በከነዓንም አገር ሰባት አሕዛብን አጥፍቶ ምድራቸውን አወረሳቸው። ከዚህም በኋላ እስከ ነቢዩ እስከ ሳሙኤል ድረስ አራት መቶ አምሳ ዓመት ያህል መሳፍንትን ሰጣቸው። ከዚያም ወዲያ ንጉሥን ያነግሥላቸው ዘንድ ለመኑ፤ እግዚአብሔርም ከብንያም ወገን የሚሆን ሰው የቂስን ልጅ ሳኦልን አርባ ዓመት ሰጣቸው፤ እርሱንም ከሻረው በኋላ ዳዊትን በእነርሱ ላይ እንዲነግሥ አስነሣው፤ ሲመሰክርለትም ‘እንደ ልቤ የሆነ ሰው ፈቃዴንም ሁሉ የሚያደርግ የእሴይን ልጅ ዳዊትን አገኘሁ፤’ አለ። ከዚህም ሰው ዘር እግዚአብሔር እንደ ተስፋው ቃል ለእስራኤል መድኃኒትን እርሱም ኢየሱስን አመጣ። ከመምጣቱ በፊት ዮሐንስ አስቀድሞ ለእስራኤል ሕዝብ ሁሉ የንስሐን ጥምቀት ሰብኮ ነበር። ዮሐንስም ሩጫውን ሲፈጽም ሳለ ‘እኔ ማን እንደሆንሁ ታስባላችሁ? እኔስ እርሱን አይደለሁም፤ ነገር ግን እነሆ፥ የእግሩን ጫማ እፈታ ዘንድ ከማይገባኝ ከእኔ በኋላ ይመጣል፤’ ይል ነበር።” እናንተ ወንድሞቻችን፥ የአብርሃም ዘር ልጆች ከእናንተ መካከልም እግዚአብሔርን የምትፈሩ ሆይ! ለእናንተ የዚህ የመዳን ቃል ተላከ። በኢየሩሳሌም የሚኖሩ ሰዎችና አለቆቻቸው እርሱንና በየሰንበቱ የሚነበቡትን የነቢያትን ድምፆች ስላላወቁ በፍርዳቸው ፈጽመዋልና፤ ለሞትም የሚያደርስ ምክንያት አንድ ስንኳ ባያገኙበት፥ ይገድለው ዘንድ ጲላጦስን ለመኑት፤ ስለ እርሱም የተጻፈውን ሁሉ በፈጸሙ ጊዜ ከእንጨት አውርደው በመቃብር አኖሩት። እግዚአብሔር ግን ከሙታን አስነሣው፤ በሕዝብም ዘንድ ምስክሮቹ ለሆኑት ከእርሱ ጋር ከገሊላ ወደ ኢየሩሳሌም ለወጡት ብዙ ቀን ታያቸው። እኛም ለአባቶች የተሰጠውን ተስፋ የምስራቹን ለእናንተ እንሰብካለን፤ ይህን ተስፋ እግዚአብሔር በሁለተኛው መዝሙር ደግሞ “አንተ ልጄ ነህ፤ እኔ ዛሬ ወለድሁህ፤” ተብሎ እንደ ተጻፈ፥ ኢየሱስን አስነሥቶ ለእኛ ለልጆቻቸው ፈጽሞአልና። እንደገናም ወደ መበስበስ እንዳይመለስ ከሙታን እንደ አስነሣው፥ እንዲህ “የታመነውን የዳዊትን ቅዱስ ተስፋ እሰጣችኋለሁ፤” ብሏል። ደግሞ በሌላ ስፍራ “ቅዱስህን መበስበስን ያይ ዘንድ አትሰጠውም፤” ይላልና። ዳዊትም በራሱ ዘመን የእግዚአብሔርን አሳብ ካገለገለ በኋላ አንቀላፋ፤ ከአባቶቹም ጋር ተጨምሮ መበስበስን አየ፤ ይህ እግዚአብሔር ያስነሣው ግን መበስበስን አላየም። እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፤ የኀጢአት ይቅርታ የሚገኘው በኢየሱስ በኩል መሆኑ እንደ ተሰበከላችሁ ዕወቁ፤ በእርሱ የሚያምን ሁሉ በሙሴ ሕግ በኩል ማግኘት ያልተቻለውን ጽድቅ ያገኛል። ስለዚህ ነቢያት እንዲህ ብለው የተናገሩት እንዳይደርስባችሁ ተጠንቀቁ፤ “እናንተ የምትንቁ፥ ተመልከቱ፤ ተደነቁም፤ ጥፉም፤ ማንም ቢተርክላችሁ የማታምኑትን ሥራ በዘመናችሁ እኔ እሠራለሁና፤” ተብሎ በነቢያት የተነገረው እንዳይደርስባችሁ ተጠንቀቁ። በወጡም ጊዜ ይህን ነገር በሚመጣው ሰንበት ይነግሩአቸው ዘንድ ለመኑአቸው። ጉባኤውም ከተፈታ በኋላ ከአይሁድና ወደ ይሁዲነት ገብተው ከሚያመልኩ ብዙዎች ጳውሎስንና በርናባስን ተከተሉአቸው፤ እነርሱም ሲነግሩአቸው በእግዚአብሔር ጸጋ ጸንተው እንዲኖሩ አስረዱአቸው። በሁለተኛውም ሰንበት ከጥቂቶቹ በቀር የከተማው ሰው ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃል ይሰሙ ዘንድ ተሰበሰቡ። አይሁድም ብዙ ሕዝብ ባዩ ጊዜ ቅንዓት ሞላባቸው፤ እየተሳደቡም ጳውሎስ የተናገረውን ቃል ተቃወሙ። ጳውሎስና በርናባስም ገልጠው “የእግዚአብሔር ቃል አስቀድሞ ለእናንተ ይነገር ዘንድ ያስፈልጋል፤ ከገፋችሁትና የዘለዓለም ሕይወት እንዳይገባችሁ በራሳችሁ ከፈረዳችሁ ግን፥ እነሆ፥ ወደ አሕዛብ ዘወር እንላለን። እንዲሁ ጌታ “እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ለማዳን ትሆን ዘንድ ለአሕዛብ ብርሃን አድርጌሃለሁ፤” ብሎ አዞናልና፤ አሉ። አሕዛብም ሰምተው ደስ አላቸው፤ የእግዚአብሔርንም ቃል አከበሩ፤ ለዘለዓለም ሕይወትም የተዘጋጁ ሁሉ አመኑ፤ የጌታም ቃል በአገሩ ሁሉ ተስፋፋ። አይሁድ ግን የሚያመልኩትን የከበሩትንም ሴቶችና የከተማውን መኳንንት አወኩ፤ በጳውሎስና በበርናባስም ላይ ስደትን አስነሥተው ከአገራቸው አወጡአቸው። እነርሱ ግን የእግራቸውን ትቢያ አራግፈውባቸው ወደ ኢቆንዮን መጡ። በደቀ መዛሙርትም ደስታና መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው።