ሐዋርያት ሥራ 1:3-12
ሐዋርያት ሥራ 1:3-12 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ሕማማትን ከተቀበለ በኋላ ብዙ ተአምራት በማሳየት አርባ ቀን ሙሉ እየተገለጠላቸው፥ ስለ እግዚአብሔር መንግሥትም እየነገራቸውና እያስተማራቸው ሕያው ሆኖ ራሱንገለጠላቸው። ከእነርሱም ጋር አብሮ ሳለ፥ “ከእኔ የሰማችሁትን የአብን ተስፋ ጠብቁ” ብሎ ከኢየሩሳሌም እንዳይወጡ አዘዛቸው። “ዮሐንስ በውኃ አጠመቀ፤ እናንተ ግን እስከ ቅርብ ቀን ድረስ በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ” አላቸው። እነርሱም ተሰብስበው ሳሉ፥ “ጌታ ሆይ፥ በዚህ ወራት ለእስራኤል ልጆች መንግሥትን ትመልሳለህን?” ብለው ጠየቁት። እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው፥ “አብ በገዛ ሥልጣኑ የወሰነውን ቀኑንና ዘመኑን ልታውቁ አልተፈቀደላችሁም። ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኀይልን ትቀበላላችሁ፤ በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ሁሉ፥ በሰማርያና እስከ ምድር ዳርቻ ድረስም ምስክሮች ትሆኑኛላችሁ።” ይህንም እየነገራቸው ከፍ ከፍ አለ፤ ደመናም ተቀበለችው፤ እነርሱም ወደ እርሱ እያዩ ወደ ሰማይ ዐረገ፤ ከዐይናቸውም ተሰወረ። እነርሱም ወደ ሰማይ አተኵረው ሲመለከቱ እነሆ፥ ሁለት ሰዎች ነጫጭ ልብስ ለብሰው በአጠገባቸው ቆመው ታዩአቸው። እነርሱም፥ “እናንተ የገሊላ ሰዎች ሆይ፥ ወደ ሰማይ እየአያችሁ ለምን ቆማችኋል? ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ ያረገው ኢየሱስ፥ ከእናንተ ወደ ሰማይ ሲያርግ እንዳያችሁት እንዲሁ ዳግመኛ ይመጣል” አሏቸው። ከዚህም በኋላ ደብረ ዘይት ከሚባለው ተራራ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፤ እርሱም ለኢየሩሳሌም የሰንበት መንገድ ያህል የራቀ ነው።
ሐዋርያት ሥራ 1:3-12 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከሕማማቱም በኋላ ራሱ ቀርቦ ሕያው መሆኑን፣ ለእነዚሁ በብዙ ማስረጃ እያረጋገጠላቸው አርባ ቀንም ዐልፎ ዐልፎ እየታያቸው ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ነገራቸው። ከእነርሱም ጋራ በማእድ ተቀምጦ ሳለ እንዲህ ሲል አዘዛቸው፤ “ከኢየሩሳሌም አትውጡ፤ ነገር ግን እኔ ስናገር የሰማችሁትን፣ አብ የሰጠውን ተስፋ ጠብቁ፤ ዮሐንስ በውሃ አጥምቆ ነበርና፣ እናንተ ግን ከጥቂት ቀን በኋላ በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ።” እነርሱም ተሰብስበው ሳሉ፣ “ጌታ ሆይ፤ የእስራኤልን መንግሥት መልሰህ የምታቋቁምበት ጊዜው አሁን ነውን?” ብለው ጠየቁት። እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “አብ በገዛ ሥልጣኑ የወሰነውን ጊዜ ወይም ወቅት ማወቁ ለእናንተ አልተሰጣችሁም፤ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በሚወርድበት ጊዜ ኀይልን ትቀበላላችሁ፤ በኢየሩሳሌም፣ በይሁዳና በሰማርያ ሁሉ፣ እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ።” ይህን ካለ በኋላ እያዩት ወደ ላይ ዐረገ፤ ደመናም ከዐይናቸው ሰወረችው። እርሱም በሚሄድበት ጊዜ ትኵር ብለው ወደ ሰማይ ሲመለከቱ፣ እነሆ፤ ነጫጭ ልብስ የለበሱ ሁለት ሰዎች ድንገት አጠገባቸው ቆሙ፤ እንዲህም አሏቸው፤ “እናንተ የገሊላ ሰዎች ሆይ፤ ወደ ሰማይ እየተመለከታችሁ እዚህ የቆማችሁት ለምንድን ነው? ይህ ከእናንተ ዘንድ ወደ ሰማይ ሲያርግ ያያችሁት ኢየሱስ፣ ልክ ወደ ሰማይ ሲወጣ እንዳያችሁት በዚሁ ሁኔታ ይመለሳል።” ከዚያም ደብረ ዘይት ከተባለው ተራራ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፤ ይህም ተራራ ከኢየሩሳሌም የሰንበት መንገድ ያህል ይርቅ ነበር።
ሐዋርያት ሥራ 1:3-12 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ደግሞ አርባ ቀን እየታያቸው ስለ እግዚአብሔርም መንግሥት ነገር እየነገራቸው፥ በብዙ ማስረጃ ከሕማማቱ በኋላ ሕያው ሆኖ ለእነርሱ ራሱን አሳያቸው። ከእነርሱም ጋር አብሮ ሳለ ከኢየሩሳሌም እንዳይወጡ አዘዛቸው፥ ነገር ግን፦ “ከእኔ የሰማችሁትን አብ የሰጠውን የተስፋ ቃል ጠብቁ፤ ዮሐንስ በውኃ አጥምቆ ነበርና፥ እናንተ ግን ከጥቂት ቀን በኃላ በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ” አለ። እነርሱም በተሰበሰቡ ጊዜ፦ “ጌታ ሆይ፥ በዚህ ወራት ለእስራኤል መንግሥትን ትመልሳለህን?” ብለው ጠየቁት። እርሱም፦ “አብ በገዛ ሥልጣኑ ያደረገውን ወራትንና ዘመናትን ታውቁ ዘንድ ለእናንተ አልተሰጣችሁም፤ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ፥ በኢየሩሳሌምም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ” አለ። ይህንም ከተናገረ በኋላ እነርሱ እያዩት ከፍ ከፍ አለ፤ ደመናም ከዓይናቸው ሰውራ ተቀበለችው። እርሱም ሲሄድ ወደ ሰማይ ትኵር ብለው ሲመለከቱ ሳሉ፥ እነሆ፥ ነጫጭ ልብስ የለበሱ ሁለት ሰዎች በአጠገባቸው ቆሙ፤ ደግሞም፦ “የገሊላ ሰዎች ሆይ፥ ወደስማይ እየተመለከታችሁ ስለ ምን ቆማችኋል? ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ የወጣው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲሄድ እንዳያችሁት፥ እንዲሁ ይመጣል” አሉአቸው። በዚያን ጊዜ ደብረ ዘይት ከሚባለው ተራራ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፥ እርሱም ከኢየሩሳሌም የሰንበት መንገድ ያህል የራቀ ነው።
ሐዋርያት ሥራ 1:3-12 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ብዙ መከራ ተቀብሎ ከሞተ በኋላ በብዙ ግልጥ ማስረጃዎች ሕያው ሆኖ ታያቸው፤ አርባ ቀን ሙሉ እየተገለጠላቸውም ስለ እግዚአብሔር መንግሥት አስተማራቸው። አብሮአቸውም በነበረ ጊዜ እንዲህ ሲል አዘዛቸው፦ “እኔ የነገርኳችሁን ከአብ የተሰጠ ተስፋ ጠብቁ እንጂ ከኢየሩሳሌም አትውጡ፤ ዮሐንስ በውሃ አጠመቀ፤ እናንተ ግን ከጥቂት ቀን በኋላ በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ።” እነርሱ በአንድነት ተሰብስበው ሳሉ፥ “ጌታ ሆይ! መንግሥትን ለእስራኤል መልሰህ የምትሰጥበት ጊዜ አሁን ነውን?” ሲሉ ጠየቁት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “አብ በገዛ ሥልጣኑ የወሰነውን ጊዜና ዘመን እናንተ ልታውቁት አትችሉም። ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኀይልን ትቀበላላችሁ፤ በዚያን ጊዜ በኢየሩሳሌም፥ በይሁዳ ምድር ሁሉ፥ በሰማርያ፥ እስከ ምድርም ዳርቻ ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ።” ይህንንም ካለ በኋላ እነርሱ እያዩት ወደ ሰማይ ዐረገ፤ ደመናም ተቀብሎ ከዐይናቸው ሰወረው። እርሱ እያረገ ሳለ፥ እነርሱ ትኲር ብለው ወደ ሰማይ ሲመለከቱ ነጫጭ ልብስ የለበሱ ሁለት ሰዎች አጠገባቸው ቆመው፥ “እናንተ የገሊላ ሰዎች፥ ስለምን ወደ ሰማይ እየተመለከታችሁ ቆማችኋል? ይህ ወደ ሰማይ ሲያርግ ያያችሁት ኢየሱስ፥ ወደ ሰማይ ሲያርግ ባያችሁት ዐይነት ተመልሶ ይመጣል” አሉአቸው። ከዚህ በኋላ ደብረ ዘይት ከተባለው ተራራ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፤ የደብረ ዘይት ተራራ ከኢየሩሳሌም የሚርቀው የሰንበት መንገድ (አንድ ኪሎ ሜትር) ያኽል ነው።
ሐዋርያት ሥራ 1:3-12 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ደግሞ አርባ ቀን እየታያቸው ስለ እግዚአብሔርም መንግሥት ነገር እየነገራቸው፥ በብዙ ማስረጃ ከሕማማቱ በኋላ ሕያው ሆኖ ለእነርሱ ራሱን አሳያቸው። ከእነርሱም ጋር አብሮ ሳለ ከኢየሩሳሌም እንዳይወጡ አዘዛቸው፤ ነገር ግን “ከእኔ የሰማችሁትን አብ የሰጠውን የተስፋ ቃል ጠብቁ፤ ዮሐንስ በውሃ አጥምቆ ነበርና፤ እናንተ ግን ከጥቂት ቀን በኋላ በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ፤” አለ። እነርሱም በተሰበሰቡ ጊዜ “ጌታ ሆይ! በዚህ ወራት ለእስራኤል መንግሥትን ትመልሳለህን?” ብለው ጠየቁት። እርሱም “አብ በገዛ ሥልጣኑያደረገውን ወራትንና ዘመናትን ታውቁ ዘንድ ለእናንተ አልተሰጣችሁም፤ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ፤ በኢየሩሳሌምም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ፤” አለ። ይህንም ከተናገረ በኋላ እነርሱ እያዩት ከፍ ከፍ አለ፤ ደመናም ከዐይናቸው ሰውራ ተቀበለችው። እርሱም ሲሄድ ወደ ሰማይ ትኩር ብለው ሲመለከቱ ሳሉ፥ እነሆ፥ ነጫጭ ልብስ የለበሱ ሁለት ሰዎች በአጠገባቸው ቆሙ፤ ደግሞም “የገሊላ ሰዎች ሆይ! ወደስማይ እየተመለከታችሁ ስለምን ቆማችኋል? ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ የወጣው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲሄድ እንዳያችሁት፥ እንዲሁ ይመጣል፤” አሉአቸው። በዚያን ጊዜ ደብረዘይት ከሚባለው ተራራ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፤ እርሱም ከኢየሩሳሌም የሰንበት መንገድ ያህል የራቀ ነው።