2 ተሰሎንቄ 3:7-15

2 ተሰሎንቄ 3:7-15 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

እኛን ልትመስሉ እንዴት እንደሚገባችሁ ራሳችሁ ታውቃላችሁና፤ በእናንተ ዘንድ ያለ ሥርዐት አልሄድንምና፤ ከእናንተ ዘንድ በአንዱ ስንኳ እንዳንከብድበት ሌሊትና ቀን በድካምና በጥረት እየሠራን እንኖር ነበር እንጂ፥ ከማንም እንጀራን እንዲያው አልበላንም። ይህም እኛን ልትመስሉ ራሳችንን እንደ ምሳሌ እንሰጣችሁ ዘንድ ነበር እንጂ፥ ያለ ሥልጣን ስለ ሆንን አይደለም። ደግሞ ከእናንተ ጋር ሳለን “ሊሠራ የማይወድ አይብላ፤” ብለን አዘናችሁ ነበርና። ሥራ ከቶ ሳይሠሩ በሰው ነገር እየገቡ ያለ ሥርዐት ከእናንተ ዘንድ ስለሚሄዱ ስለ አንዳንዶች ሰምተናልና። እንደነዚህ ያሉትንም በጸጥታ እየሠሩ የገዛ እንጀራቸውን ይበሉ ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እናዛቸዋለን፤ እንመክራቸውማለን። እናንተ ግን ወንድሞች ሆይ! መልካም ሥራን ለመሥራት አትታክቱ። በዚህ መልእክት ለተላከ ቃላችን የማይታዘዝ ማንም ቢኖር፥ ይህን ተመልከቱት፤ ያፍርም ዘንድ ከእርሱ ጋር አትተባበሩ። ነገር ግን እንደ ወንድም ገሥጹት እንጂ እንደ ጠላት አትቍጠሩት።

2 ተሰሎንቄ 3:7-15 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

የእኛን ምሳሌ እንዴት መከተል እንደሚገባችሁ እናንተ ራሳችሁ ታውቃላችሁና። ከእናንተ ጋራ በነበርንበት ጊዜ ሥራ ፈቶች አልነበርንም፤ ደግሞም የማንንም እንጀራ በነጻ አልበላንም፤ ነገር ግን ከእናንተ በአንዳችሁም ላይ ሸክም እንዳንሆን ሌሊትና ቀን እንደክምና እንሠራ ነበር፤ ይህን ያደረግነው ምሳሌነታችንን እንድትከተሉ ብለን እንጂ የሚያስፈልገንን ነገር ከእናንተ ለማግኘት ሥልጣን ሳይኖረን ቀርቶ አይደለም። ከእናንተ ጋራ በነበርንበት ጊዜ፣ “ሊሠራ የማይወድድ አይብላ” ብለን ይህን ትእዛዝ ሰጥተናችሁ ነበርና። ከእናንተ አንዳንዶች ያለ ሥርዐት የሚመላለሱ እንደ ሆኑ ሰምተናል፤ እነርሱም ያለ ሥራ እየዞሩ በሰው ጕዳይ ጣልቃ የሚገቡ ናቸው። እንደዚህ ያሉ ሰዎች ተግተው ሥራቸውን እንዲሠሩና እንጀራቸውን እንዲበሉ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እናዝዛቸዋለን፤ እንመክራቸዋለንም። እናንተ ግን ወንድሞች ሆይ፤ መልካም ሥራን ከመሥራት ከቶ አትታክቱ። በዚህ መልእክት ላይ ላለው ቃላችን የማይታዘዝ ማንም ቢኖር፣ እንደዚህ ያለውን ሰው በጥንቃቄ ተከታተሉት፤ በሥራውም እንዲያፍር ከርሱ ጋራ አትተባበሩ። ሆኖም እንደ ወንድም ገሥጹት እንጂ እንደ ጠላት አትቍጠሩት።

2 ተሰሎንቄ 3:7-15 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

እኛን ልትመስሉ እንዴት እንደሚገባችሁ ራሳችሁ ታውቃላችሁና፤ በእናንተ ዘንድ ያለ ሥርዓት አልሄድንምና፤ ከእናንተ ዘንድ በአንዱ ስንኳ እንዳንከብድበት፥ ሌሊትና ቀን በድካምና በጥረት እየሠራን እንኖር ነበር እንጂ፥ ከማንም እንጀራን እንዲያው አልበላንም። ይህም እኛን ልትመስሉ ራሳችንን እንደ ምሳሌ እንሰጣችሁ ዘንድ ነበር እንጂ፥ ያለ ሥልጣን ስለ ሆንን አይደለም። ደግሞ ከእናንተ ጋር ሳለን፦ ሊሠራ የማይወድ አይብላ ብለን አዘናችሁ ነበርና። ሥራ ከቶ ሳይሠሩ፥ በሰው ነገር እየገቡ፥ ያለ ሥርዓት ከእናንተ ዘንድ ስለሚሄዱ ስለ አንዳንዶች ሰምተናልና። እንደነዚህ ያሉትንም በጸጥታ እየሠሩ የገዛ እንጀራቸውን ይበሉ ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እናዛቸዋለን እንመክራቸውማለን። እናንተ ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ መልካም ሥራን ለመሥራት አትታክቱ። በዚህ መልእክት ለተላከ ቃላችን የማይታዘዝ ማንም ቢኖር፥ ይህን ተመልከቱት፥ ያፍርም ዘንድ ከእርሱ ጋር አትተባበሩ። ነገር ግን እንደ ወንድም ገሥጹት እንጂ እንደ ጠላት አትቍጠሩት።

2 ተሰሎንቄ 3:7-15 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

የእኛን ምሳሌነት መከተል እንደሚገባችሁ እናንተ ራሳችሁ ታውቃላችሁ፤ እኛ ከእናንተ ጋር በነበርንበት ጊዜ ሥራ ፈቶች አልነበርንም፤ የማንንም እንጀራ በብላሽ አልበላንም፤ ይልቅስ ከእናንተ በማንም ላይ ሸክም እንዳንሆንበት በማለት ሌሊትና ቀን በመድከምና በመልፋት እንሠራ ነበር። እንዲህም ያደረግነው እናንተ የእኛን ምሳሌነት እንድትከተሉ ብለን ነው እንጂ ከእናንተ ርዳታ ለማግኘት መብት ሳይኖረን ቀርቶ አይደለም። ከእናንተ ጋር በነበርንበት ጊዜ “ሊሠራ የማይፈልግ አይብላ” የሚል ደንብ ሰጥተናችሁ ነበር። ይህን ያልንበት ምክንያት በመካከላችሁ አንዳንድ ሥራ ፈቶች እንዳሉ በመስማታችን ነው፤ እነዚህ ሰዎች በማያገባቸው ነገር እየገቡ ሌሎችን ከማወክ በቀር ምንም አይሠሩም። እንደእነዚህ ያሉ ሰዎች ተረጋግተው እንዲሠሩና መተዳደሪያቸውን እንዲያገኙ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እናዛቸዋለን፤ እንመክራቸዋለንም። እናንተ ግን ወንድሞች ሆይ! ደከምን ብላችሁ መልካም ከመሥራት አትቦዝኑ። በዚህ መልእክት ያስተላለፍንላችሁን ምክር የማይቀበል ሰው ቢኖር እንዲህ ያለውን ሰው ልብ በሉት፤ እንዲያፍርም ከእርሱ ጋር ግንኙነት አታድርጉ። ሆኖም እንደ ወንድም ምከሩት እንጂ እንደ ጠላት አትቊጠሩት።

2 ተሰሎንቄ 3:7-15 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ስለዚህም እኛን ልትመስሉ እንዴት እንደሚገባችሁ እናንተው ራሳችሁ ታውቃላችሁ፤ በእናንተ ዘንድ በነበርንበት ጊዜ ሥራ ፈቶች አልነበርንም፤ ከእናንተ ዘንድ በማንም ላይ ሸክም እንዳንሆንበት ሌሊትና ቀን በድካምና በጥረት እየሠራን እንኖር ነበር እንጂ የማንንም ሰው እንጀራ እንዲያው በነፃ አልበላንም። ይህም እኛን እንድትመስሉ ራሳችንን እንደ ምሳሌ አድርገን ሰጠናችሁ እንጂ ሥልጣን ስላልነበረን አይደለም። እንዲሁም ከእናንተ ጋር በነበርንበት ጊዜ “ማንም ሊሠራ የማይወድ አይብላ፤” ብለን አዘናችሁ ነበር። ይህም የሆነው ሥራ ፈትተው ሥራን ከቶ የማይሰሩ ይልቁንም በሰው ነገር ጣልቃ የሚገቡ አንዳንዶች በእናንተ መካከል እንደሚኖሩ ስለ ሰማን ነው። እንደነዚህ ያሉትንም ሥራቸውን በጸጥታ እየሠሩ የገዛ እንጀራቸውን እንዲበሉ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እናዛቸዋለን፤ እንመክራቸዋለንም። እናንተ ግን ወንድሞች ሆይ! መልካም ሥራን ለመሥራት አትታክቱ። በዚህ መልእክት በኩል ለተላከው ቃላችን የማይታዘዝ ማንም ቢኖር፥ ይህን ሰው በምልክት ለዩት፤ እንዲያፍርም ከእርሱ ጋር አትተባበሩ። ነገር ግን እንደ ወንድም ገሥጹት እንጂ እንደ ጠላት አትቁጠሩት።