2 ተሰሎንቄ 2:1-7

2 ተሰሎንቄ 2:1-7 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ወንድሞች ሆይ! ስለ ጌታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መምጣትና እኛም ከእርሱ ጋር ለመሆን ስለ መሰብሰባችን ጉዳይ የምንለምናችሁ ይህን ነው፤ በትንቢት ወይም በቃል እንደ ተነገረ ወይም ከእኛ በመልእክት እንደ ተጻፈ አድርጋችሁ “የጌታ ቀን ደርሶአል” በማለት በቶሎ አእምሮአችሁ አይናወጥ፤ አትታወኩም፤ ማንም ሰው በምንም ዐይነት አያታላችሁ፤ አስቀድሞ ክሕደት ሳይመጣ፥ ገሃነም የሚገባው የዐመፅ ሰው የሆነውም ሳይገለጥ፥ ያ ቀን አይመጣም። ይህ የዐመፅ ሰው አማልክት ተብለው ከሚመለኩት ሁሉ በላይ ራሱን ከፍ ያደርጋል፤ “እግዚአብሔር ነኝ” እያለም በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንኳ ለመቀመጥ ይደፍራል። ከእናንተ ጋር በነበርኩ ጊዜ ይህን ነገር ነግሬአችሁ እንደ ነበረ አታስታውሱምን? በተወሰነለት ጊዜ እስኪገለጥ ድረስ አሁን እንዳይገለጥ የሚከለክለው ምን እንደ ሆነ ታውቃላችሁ። ምሥጢራዊው የዐመፅ ኀይል አሁንም በመሥራት ላይ ነው፤ ሆኖም አሁን የሚከለከለው አለ፤ ይህም የሚሆነው ያ የሚከለክለው እስኪወገድ ድረስ ነው።

2 ተሰሎንቄ 2:1-7 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ነገር ግን ወንድሞች ሆይ! ስለ ጌታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መምጣትና ወደ እርሱ ስለ መሰብሰባችን ይህን እንለምናችኋለን፤ ከእኛ በሚመስል መልእክት ወይም በቃል ወይም በመንፈስ፦ “የጌታ ቀን መጥቷል፤” ብላችሁ አእምሮአችሁ በቀላሉ አይናወጥ አይደንግጥም። ማንም ሰው በማናቸውም መንገድ አያታልላችሁ፤ ከሐዲው አስቀድሞ ሳይመጣ የዓመፅም ሰው እርሱም የጥፋት ልጅ ሳይገለጥ ያ ቀን አይመጣምና። እርሱም ሰው የሚያመልከውን ነገር ወይም አማልክት ነን ከሚሉት ሁሉ በላይ ራሱን ከፍ ከፍ በማድረግና በመቃወም፦ “እኔ እግዚአብሔር ነኝ” ብሎ ያውጃል፤ በእግዚአብሔርም ቤተ መቅደስ ይቀመጣል። ከእናንተ ጋር በነበርሁ ጊዜ እነዚህን ነገሮች ነግሬአችሁ እንደ ነበረ አታስታውሱምን? አሁን ምን እንደከለከለው አውቃችኋልና በራሱ ጊዜ የተገለጠ ይሆናል። አስቀድሞም የዓመፅ ሚስጢር በሥራ ላይ ነው፤ አሁን ግን እርሱ ብቻ ይከለክለዋል፤ እርሱም እንዲህ የሚያደርገው ከመንገድ እስከሚወገድ ድረስ ነው።