2 ተሰሎንቄ 1:9-12 - Compare All Versions
2 ተሰሎንቄ 1:9-12 NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
እነርሱም ከጌታ ፊትና ከኀይሉ ክብር ተወግደው በዘላለም ጥፋት ይቀጣሉ፤ የሚቀጡትም በቅዱሳኑ ዘንድ ሊከብርና በሚያምኑበትም ሁሉ ሊገረም በሚመጣበት በዚያ ቀን ይሆናል፤ እናንተም ከሚያምኑት መካከል ናችሁ፤ ምስክርነታችንን ተቀብላችኋልና። ይህን እያሰብን አምላካችን ለጥሪው የበቃችሁ አድርጎ እንዲቈጥራችሁ፣ በጎ ለማድረግ ያላችሁን ምኞትና ከእምነት የሆነውን ሥራችሁን ሁሉ በኀይሉ እንዲፈጽምላችሁ ዘወትር ስለ እናንተ እንጸልያለን። ደግሞም እንደ አምላካችንና እንደ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ መጠን የጌታችን የኢየሱስ ስም በእናንተ ዘንድ እንዲከብርና እናንተም በርሱ እንድትከብሩ ይህን እንጸልያለን።
2 ተሰሎንቄ 1:9-12 አማ05 (አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም)
እነርሱ ከጌታ ፊትና ከኀያል ክብሩ ተለይተው በዘለዓለም ጥፋት ይቀጣሉ። የሚቀጡትም በዚያን ቀን በቅዱሳኑ ሊከበርና በሚያምኑትም ሁሉ ዘንድ ሊደነቅ በሚመጣበት ጊዜ ነው። እናንተም የእኛን ምስክርነት ተቀብላችሁ በማመናችሁ ከእነርሱ ጋር ትቈጠራላችሁ። ይህን በማሰብ ስለ እናንተ ሳናቋርጥ የምንጸልየው አምላካችን ለጥሪው ብቁዎች እንዲያደርጋችሁና መልካም ለማድረግ ያላችሁን ፈቃድና የእምነት ሥራችሁን ሁሉ በኀይሉ እንዲፈጽምላችሁ ነው። እንዲሁም የጌታችን የኢየሱስ ስም በእናንተ እንዲከበርና እናንተም በአምላካችንና በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ መሠረት በእርሱ እንድትከበሩ እንጸልያለን።
2 ተሰሎንቄ 1:9-12 አማ2000 (የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ))
በዚያም ቀን በቅዱሳኑ ሊከብር ምስክርነታችንንም አምናችኋልና በሚያምኑት ሁሉ ዘንድ ሊደነቅ ሲመጣ፥ ከጌታ ፊት ከኀይሉም ክብር ርቀው በዘላለም ጥፋት ይቀጣሉ። ስለዚህም ደግሞ እንደ አምላካችን እንደ ጌታም እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ፥ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ስም በእናንተ ዘንድ ሊከብር እናንተም በእርሱ ዘንድ ልትከብሩ፥ አምላካችን ለመጥራቱ የምትበቁ አድርጎ ይቈጥራችሁ ዘንድ፥ የበጎነትንም ፈቃድ ሁሉ የእምነትንም ሥራ በኀይል ይፈጽም ዘንድ ስለ እናንተ ሁልጊዜ እንጸልያለን።
2 ተሰሎንቄ 1:9-12 አማ54 (መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት))
በዚያም ቀን በቅዱሳኑ ሊከብር፥ ምስክርነታችንንም አምናችኋልና በሚያምኑት ሁሉ ዘንድ ሊገረም ሲመጣ፥ ከጌታ ፊት ከኃይሉም ክብር ርቀው በዘላለም ጥፋት ይቀጣሉ። ስለዚህም ደግሞ እንደ አምላካችን እንደ ጌታም እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ፥ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ስም በእናንተ ዘንድ ሊከብር እናንተም በእርሱ ዘንድ ልትከብሩ፥ አምላካችን ለመጥራቱ የምትበቁ አድርጎ ይቈጥራችሁ ዘንድ፥ የበጎነትንም ፈቃድ ሁሉ የእምነትንም ሥራ በኃይል ይፈጽም ዘንድ ስለ እናንተ ሁልጊዜ እንጸልያለን።
2 ተሰሎንቄ 1:9-12 መቅካእኤ (መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ))
ከጌታ ፊት ከኃይሉም ክብር ርቀው በዘለዓለም ጥፋት ይቀጣሉ። ይህም የሚሆነው ምስክርነታችን በእናንተ በመታመኑ የተነሣ ባመኑት ሁሉ ዘንድ ሊደነቅና፥ በቅዱሳኑም ሊከብር በሚመጣበት ጊዜ በዚያ ቀን ነው። አምላካችን ለጥሪው የተገባችሁ እንዲያደርጋችሁና በእርሱ ኃይል የመልካም ፈቃድ መሻትንና የእምነትን ሥራ እንዲፈጽም፥ ስለ እናንተ በዚህ ነገር ሁልጊዜ እንጸልያለን፤ በዚህም ምክንያት እንደ አምላካችን እንደ ጌታም እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ፥ የጌታችን የኢየሱስ ስም በእናንተ፥ እናንተም በእርሱ እንድትከብሩ ነው።