2 ተሰሎንቄ 1:1-10
2 ተሰሎንቄ 1:1-10 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ጳውሎስና ስልዋኖስ ጢሞቴዎስም፥ በእግዚአብሔር በአባታችን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስም ወደምትሆን ወደ ተሰሎንቄ ሰዎች ቤተ ክርስቲያን፤ ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታ ከኢየሱስ ክርስቶስም ጸጋ ሰላምም ለእናንተ ይሁን። ወንድሞች ሆይ! እምነታችሁ እጅግ ስለሚያድግ፥ የሁላችሁም የእያንዳንዳችሁ ፍቅር እርስ በርሳችሁ ስለሚበዛ፥ ሁልጊዜ ስለ እናንተ እግዚአብሔርን እንደሚገባ ልናመሰግን ግድ አለብን፤ ስለዚህ በምትታገሱበት በስደታችሁና በመከራችሁ ሁሉ ከመጽናታችሁና ከእምነታችሁ የተነሣ በእግዚአብሔር አብያተ ክርስቲያናት ስለ እናንተ ራሳችን እንመካለን። ስለ እርሱ ደግሞ መከራ ለምትቀበሉለት ለእግዚአብሔር መንግሥት የምትበቁ ሆናችሁ ትቈጠሩ ዘንድ ይህ የእግዚአብሔር ቅን ፍርድ ምልክት ነው። ጌታ ኢየሱስ ከኀያላን መላእክቱ ጋር ከሰማይ በእሳት ነበልባል ሲገለጥ፥ መከራን ለሚያሳዩአችሁ መከራን፥ መከራንም ለምትቀበሉ ከእኛ ጋር ዕረፍትን ብድራት አድርጎ እንዲመልስ በእግዚአብሔር ፊት በእርግጥ ጽድቅ ነውና። እግዚአብሔርን የማያውቁትን፥ ለጌታችንም ለኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል የማይታዘዙትን ይበቀላል፤ በዚያም ቀን በቅዱሳኑ ሊከብር ምስክርነታችንንም አምናችኋልና በሚያምኑት ሁሉ ዘንድ ሊደነቅ ሲመጣ፥ ከጌታ ፊት ከኀይሉም ክብር ርቀው በዘላለም ጥፋት ይቀጣሉ።
2 ተሰሎንቄ 1:1-10 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ጳውሎስ፣ ሲላስና ጢሞቴዎስ፤ በእግዚአብሔር በአባታችን በጌታም በኢየሱስ ክርስቶስ ለሆኑት፣ ለተሰሎንቄ ሰዎች ቤተ ክርስቲያን፤ ከአባታችን ከእግዚአብሔር፣ ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን። ወንድሞች ሆይ፤ እምነታችሁ በየጊዜው እያደገ በመሄዱና የእርስ በርስ ፍቅራችሁም እየጨመረ በመምጣቱ፣ ስለ እናንተ እግዚአብሔርን ሁልጊዜ በሚገባ ማመስገን አለብን። ስለዚህ በደረሰባችሁ ስደትና መከራ ሁሉ በመጽናታችሁ፣ እኛ ራሳችን ስለ ትዕግሥታችሁና ስለ እምነታችሁ በእግዚአብሔር አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ እንመካለን። ይህ ሁሉ የእግዚአብሔር ፍርድ ቅን መሆኑን የሚያመለክት ነው፤ ከዚህም የተነሣ መከራን ለምትቀበሉለት ለእግዚአብሔር መንግሥት የበቃችሁ ሆናችሁ ትቈጠራላችሁ። እግዚአብሔር ጻድቅ በመሆኑ መከራን ለሚያመጡባችሁ መከራን ይከፍላቸዋል፤ መከራን ለተቀበላችሁት ለእናንተም ሆነ ለእኛ ደግሞ ዕረፍት ይሰጠናል። ይህም የሚሆነው ጌታ ኢየሱስ በሚንበለበል እሳት ከኀያላን መላእክት ጋራ ከሰማይ በሚገለጥበት ጊዜ ነው። በዚያ ጊዜ እግዚአብሔርን የማያውቁትንና ለጌታችንም ለኢየሱስ ወንጌል የማይታዘዙትን ይበቀላል። እነርሱም ከጌታ ፊትና ከኀይሉ ክብር ተወግደው በዘላለም ጥፋት ይቀጣሉ፤ የሚቀጡትም በቅዱሳኑ ዘንድ ሊከብርና በሚያምኑበትም ሁሉ ሊገረም በሚመጣበት በዚያ ቀን ይሆናል፤ እናንተም ከሚያምኑት መካከል ናችሁ፤ ምስክርነታችንን ተቀብላችኋልና።
2 ተሰሎንቄ 1:1-10 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ጳውሎስና ስልዋኖስ ጢሞቴዎስም፥ በእግዚአብሔር በአባታችን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስም ወደምትሆን ወደ ተሰሎንቄ ሰዎች ቤተ ክርስቲያን፦ ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታ ከኢየሱስ ክርስቶስም ጸጋ ሰላምም ለእናንተ ይሁን። ወንድሞች ሆይ፥ እምነታችሁ እጅግ ስለሚያድግ የሁላችሁም የእያንዳንዳችሁ ፍቅር እርስ በርሳችሁ ስለሚበዛ፥ ሁልጊዜ ስለ እናንተ እግዚአብሔርን እንደሚገባ ልናመሰግን ግድ አለብን፤ ስለዚህ በምትታገሱበት በስደታችሁና በመከራችሁ ሁሉ ከመጽናታችሁና ከእምነታችሁ የተነሣ በእግዚአብሔር አብያተ ክርስቲያናት ስለ እናንተ ራሳችን እንመካለን። ስለ እርሱ ደግሞ መከራ ለምትቀበሉለት ለእግዚአብሔር መንግሥት የምትበቁ ሆናችሁ ትቍኦጠሩ ዘንድ፥ ይህ የእግዚአብሔር ቅን ፍርድ ምልክት ነው። ጌታ ኢየሱስ ከሥልጣኑ መላእክት ጋር ከሰማይ በእሳት ነበልባል ሲገለጥ፥ መከራን ለሚያሳዩአችሁ መከራን፥ መከራንም ለምትቀበሉ ከእኛ ጋር ዕረፍትን ብድራት አድርጎ እንዲመልስ በእግዚአብሔር ፊት በእርግጥ ጽድቅ ነውና። እግዚአብሔርን የማያውቁትን፥ ለጌታችንም ለኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል የማይታዘዙትን ይበቀላል፤ በዚያም ቀን በቅዱሳኑ ሊከብር፥ ምስክርነታችንንም አምናችኋልና በሚያምኑት ሁሉ ዘንድ ሊገረም ሲመጣ፥ ከጌታ ፊት ከኃይሉም ክብር ርቀው በዘላለም ጥፋት ይቀጣሉ።
2 ተሰሎንቄ 1:1-10 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
የእግዚአብሔር የአባታችንና የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ለሆነችው ለተሰሎንቄ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ከጳውሎስ፥ ከሲላስና ከጢሞቴዎስ የተላከ፦ ከእግዚአብሔር አብና ከጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን። ወንድሞች ሆይ! በእናንተ ምክንያት እግዚአብሔርን ሁልጊዜ እናመሰግናለን፤ ማመስገንም ተገቢያችን ነው፤ የምናመሰግነውም እምነታችሁ ይበልጥ እያደገና የእያንዳንዳችሁ የእርስ በርስ ፍቅር እየጨመረ በመሄዱ ነው። ስለዚህም ምንም እንኳ ብዙ ችግርና ሥቃይ ቢደርስባችሁ እናንተ እንዴት ታጋሾችና በእምነታችሁ የጸናችሁ መሆናችሁን በመናገር እኛ በሌሎች አብያተ ክርስቲያን መካከል ሆነን በእናንተ እንመካለን። ይህ ሁሉ ነገር የሚያሳየው የእግዚአብሔር ፍርድ ትክክል መሆኑንና እናንተንም መከራ ለተቀበላችሁለት መንግሥቱ ብቁ የሚያደርጋችሁ መሆኑን ነው። እግዚአብሔር ቅን ፈራጅ በመሆኑ መከራን በሚያመጡባችሁ ላይ መከራን በማምጣት ዋጋቸውን ይከፍላቸዋል። አሁን መከራን ለምትቀበሉትም ከእኛ ጋር ዕረፍትን ይሰጣችኋል። ይህም የሚሆነው ጌታ ኢየሱስ ከኀያላን መላእክቱ ጋር ከሰማይ በሚወርድበት ጊዜ ነው፤ ከሰማይ የሚገለጠውም በሚንበለበል እሳት ነው፤ በዚያን ጊዜ እግዚአብሔርን የማያውቁትንና ለጌታችን ለኢየሱስ ወንጌል የማይታዘዙትን ይቀጣቸዋል። እነርሱ ከጌታ ፊትና ከኀያል ክብሩ ተለይተው በዘለዓለም ጥፋት ይቀጣሉ። የሚቀጡትም በዚያን ቀን በቅዱሳኑ ሊከበርና በሚያምኑትም ሁሉ ዘንድ ሊደነቅ በሚመጣበት ጊዜ ነው። እናንተም የእኛን ምስክርነት ተቀብላችሁ በማመናችሁ ከእነርሱ ጋር ትቈጠራላችሁ።
2 ተሰሎንቄ 1:1-10 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ጳውሎስና ስልዋኖስ ጢሞቴዎስም፥ በእግዚአብሔር በአባታችን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስም ወደምትሆን ወደ ተሰሎንቄ ሰዎች ቤተ ክርስቲያን፤ ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታ ከኢየሱስ ክርስቶስም ጸጋ ሰላምም ለእናንተ ይሁን። ወንድሞች ሆይ! እምነታችሁ እጅግ አድጎአልና፥ የእናንተም የእያንዳንዳችሁ ሁሉ ፍቅር ለእርስ በርሳችሁ በዝቶአልና፥ ሁልጊዜ ስለ እናንተ እግዚአብሔርን እንደሚገባ ልናመሰግን ግዴታ አለብን፤ ስለዚህ በምትታገሱት መከራችሁና በስደታችሁ ሁሉ ስለ እናንተ መጽናትና እምነት እኛ ራሳችን በእግዚአብሔር አብያተ ክርስቲያናት በእናንተ እንመካለን። ስለ እርሱ ደግሞ መከራ ለምትቀበሉለት ለእግዚአብሔር መንግሥት የምትበቁ ሆናችሁ እንድትቆጠሩ ይህ የእግዚአብሔር ቅን ፍርድ ምልክት ነው። በእርግጥ በእግዚአብሔር ዘንድ ጽድቅ ነውና፥ መከራን የሚያደርሱባችሁን በመከራ ብድራታቸውን ይከፍላል። እንዲሁም እርሱ ጌታ ኢየሱስ ከኃያላን መላእክቱ ጋር ከሰማይ በእሳት ነበልባል በሚመጣበት ጊዜ መከራን ለተቀበላችሁት ከእኛ ጋር ዕረፍትን ይሰጣችኋል፤ ነገር ግን እግዚአብሔርን የማያውቁትን፥ ለጌታችንም ለኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል የማይታዘዙትን ይበቀላል፤ ከጌታ ፊት ከኃይሉም ክብር ርቀው በዘለዓለም ጥፋት ይቀጣሉ። ይህም የሚሆነው ምስክርነታችን በእናንተ በመታመኑ የተነሣ ባመኑት ሁሉ ዘንድ ሊደነቅና፥ በቅዱሳኑም ሊከብር በሚመጣበት ጊዜ በዚያ ቀን ነው።