2 ሳሙኤል 6:1-23
2 ሳሙኤል 6:1-23 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ዳዊትም ደግሞ ከእስራኤል የተመረጡትን ሰባ ሺህ ያህል ሰው ሰበሰበ። ዳዊትና ከእርሱ ጋር የነበሩት ሕዝብ ሁሉ ከይሁዳ አለቆች ጋር ተነሥተው በኪሩቤል ላይ የተቀመጠ የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር ስም የተጠራባትን የእግዚአብሔርን ታቦት ከዚያ ያመጡ ዘንድ ሄዱ። የእግዚአብሔርንም ታቦት በአዲስ ሰረገላ ላይ ጫኑአት፥ በኮረብታውም ላይ ከነበረው ከአሚናዳብ ቤት አመጡአት፤ የአሚናዳብ ልጆችም ዖዛና ወንድሞቹ ታቦቷ ያለችበትን ሰረገላ ይነዱ ነበር። ወንድሞቹም በታቦቷ ፊት ይሄዱ ነበር። ዳዊትና የእስራኤልም ልጆች ሁሉ በዜማ መሣሪያዎች በበገናና በመሰንቆ፥ በከበሮና በነጋሪት፥ በጸናጽልና በዕንዚራ በእግዚአብሔር ፊት በሙሉ ኀይላቸው ይጫወቱ ነበር። ወደ ናኮንም አውድማ ደረሱ፤ ዖዛም በሬዎቹ አነቃንቀዋት ነበርና ይይዛት ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ታቦት እጁን ዘረጋ፤ አስተካከላትም። ሲይዛትም በሬው ወጋው። እግዚአብሔርም በዖዛ ላይ ተቈጣ፤ እግዚአብሔርም በዚያው ቀሠፈው። በእግዚአብሔርም ታቦት አጠገብ በእግዚአብሔር ፊት በዚያው ሞተ። እግዚአብሔርም ዖዛን ስለ ገደለው ዳዊት አዘነ፤ እስከ ዛሬም ድረስ የዚያ ስፍራ ስም “ዖዛ የሞተበት” ተባለ። በዚያም ቀን ዳዊት እግዚአብሔርን ፈራና፥ “የእግዚአብሔር ታቦት ወደ እኔ እንዴት ትገባለች?” አለ። ዳዊትም የእግዚአብሔርን ታቦተ ሕግ ወደ እርሱ ወደ ዳዊት ከተማ ያመጣት ዘንድ አልወደደም፤ ዳዊትም በጌት ሰው በአቢዳራ ቤት አገባት። የእግዚአብሔርም ታቦት በጌት ሰው በአቢዳራ ቤት ሦስት ወር ተቀመጠች፤ እግዚአብሔርም አቢዳራንና ቤቱን ሁሉ ባረከ። ለንጉሡ ዳዊትም “እግዚአብሔር የአቢዳራን ቤትና የነበረውን ሁሉ ስለ እግዚአብሔር ታቦት ባረከ” ብለው ነገሩት። ዳዊትም ሄዶ የእግዚአብሔርን ታቦት ከአቢዳራ ቤት ወደ ዳዊት ከተማ በደስታ አመጣት። ከእርሱም ጋር የእግዚአብሔርን ታቦት የተሸከሙ ሰባት መሰንቆ የሚመቱ ክፍሎች ነበሩ። በሬዎችንና በጎችን ይሠዉ ነበር። ዳዊትም በእግዚአብሔር ፊት በገና ይደረድር ነበር፤ ዳዊትም ለዐይን የሚያንጸባርቅ የሐር ቀሚስ ለብሶ ነበር። ዳዊትና የእስራኤልም ቤት ሁሉ በእልልታ ቀንደ መለከት እየነፉ የእግዚአብሔርን ታቦት አመጡአት። የእግዚአብሔርም ታቦት ወደ ዳዊት ከተማ በደረሰች ጊዜ የሳኦል ልጅ ሜልኮል በመስኮት ሆና ተመለከተች፤ ንጉሡም ዳዊት በእግዚአብሔር ፊት ሲዘልልና ሲዘምር አየችው፥ በልብዋም ናቀችው። የእግዚአብሔርንም ታቦት አምጥተው ዳዊት በተከለላት ድንኳን ውስጥ በስፍራዋ አኖሩአት፤ ዳዊትም የሚቃጠልና የሰላም መሥዋዕትን በእግዚአብሔር ፊት አሳረገ። ዳዊትም የሚቃጠልና የሰላም መሥዋዕት ማሳረግን ከፈጸመ በኋላ ሕዝቡን በሰራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ስም መረቀ። ለሕዝቡም ሁሉ ለእስራኤል ወገን ከዳን እስከ ቤርሳቤህ ለወንዱም፥ ለሴቱም ለእያንዳንዱ አንዳንድ እንጀራ፥ አንዳንድም የሥጋ ቍራጭ፥ አንዳንድም ጽዋዕ ወይን አከፋፈለ። ሕዝቡም ሁሉ እያንዳንዱ ወደ ቤቱ ሄደ። ዳዊትም ቤተ ሰቡን ሊመርቅ ተመለሰ። የሳኦል ልጅ ሜልኮልም ዳዊትን ለመቀበል ወጣችና ሰላምታ ሰጠችው፥ “ከሚዘፍኑት አንዱ እንደሚገለጥ የእስራኤል ንጉሥ በአገልጋዮቹ ሚስቶች ፊት በመገለጡ ምንኛ የተከበረ ነው!” አለች። ዳዊትም ሜልኮልን፥ “በእግዚአብሔር ፊት ዘምሬአለሁ፤ በእግዚአብሔር ሕዝብ በእስራኤል ላይ አለቃ እሆን ዘንድ ከአባትሽና ከቤቱ ሁሉ ይልቅ የመረጠኝ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን፤ ስለዚህም በእግዚአብሔር ፊት እጫወታለሁ፤ እዘምራለሁም፤ አሁንም እገለጣለሁ፤ በዐይንሽ ፊትና እንዴት ከበርህ ባልሽባቸው ሴቶች ልጆች ፊት የተናቅሁ እሆናለሁ” አላት። የሳኦልም ልጅ ሜልኮል እስከ ሞተችበት ቀን ድረስ ልጅ አልወለደችም።
2 ሳሙኤል 6:1-23 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ዳዊት እንደ ገና ከእስራኤል የተመረጡ በአጠቃላይ ሠላሳ ሺሕ ሰዎች ሰበሰበ። እርሱና ዐብረውት ያሉት ሰዎች ሁሉ በታቦቱ ላይ ባለው ኪሩቤል ላይ በተቀመጠው በሰራዊት ጌታ በእግዚአብሔርም ስም የተጠራውን የእግዚአብሔርን ታቦት ከዚያ ለማምጣት በይሁዳ ወዳለችው ወደ ባኣላ ሄዱ። የእግዚአብሔርንም ታቦት በአዲስ ሠረገላ ላይ አኑረው፣ በኰረብታ ላይ ካለው ከአሚናዳብ ቤት አውጥተው አመጡ፤ ሠረገላውን ይነዱ የነበሩትም የአሚናዳብ ልጆች ዖዛና አሒዮ ሲሆኑ፣ የእግዚአብሔርም ታቦት በሠረገላው ላይ ሆኖ፣ አሒዮ ፊት ፊት ይሄድ ነበር። ዳዊትና የእስራኤል ቤት በሙሉ በዝማሬ፣ በበገና፣ በመሰንቆ፣ በከበሮ፣ በጸናጽልና በቃጭል ባለ ኀይላቸው ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ያሸበሽቡ ነበር። ወደ ናኮን ዐውድማ ሲደርሱም በሬዎቹ ስለ ተደናቀፉ፣ ዖዛ እጁን ዘርግቶ የእግዚአብሔርን ታቦት ያዘ። ዖዛ በድፍረት ይህን ስላደረገ፣ የእግዚአብሔር ቍጣ በላዩ ላይ ነደደ፤ ስለዚህም እግዚአብሔር ቀሠፈው፤ እርሱም በእግዚአብሔር ታቦት አጠገብ እዚያው ሞተ። የእግዚአብሔር ቍጣ ዖዛንን ስለ ሰበረው፣ ዳዊት ተከፋ፤ ያም ቦታ እስከ ዛሬ ድረስ ፔሬዝ ዖዛ ተብሎ ይጠራል። ዳዊት በዚያ ቀን እግዚአብሔርን ስለ ፈራ “የእግዚአብሔር ታቦት እንዴት ወደ እኔ ይመጣል?” አለ። ስለዚህ ዳዊት የእግዚአብሔር ታቦት ዐብሮት እንዲሆን ወደ ዳዊት ከተማ ይዞት ለመሄድ አልፈለገም፤ በዚህ ፈንታ አቅጣጫ ለውጦ የጋት ሰው ወደ ሆነው ወደ አቢዳራ ቤት ወሰደው። የእግዚአብሔርም ታቦት የጋት ሰው በሆነው በአቢዳራ ቤት ሦስት ወር ተቀመጠ፤ እግዚአብሔርም አቢዳራንና ቤተ ሰቡን ሁሉ ባረከ። በዚህ ጊዜ፣ “በእግዚአብሔር ታቦት ምክንያት የአቢዳራን ቤተ ሰውና ያለውን ሁሉ እግዚአብሔር ባረከለት” ብለው ለንጉሥ ዳዊት ነገሩት። ስለዚህ ዳዊት ወደዚያው ወርዶ፣ የእግዚአብሔርን ታቦት ከአቢዳራ ቤት ወደ ዳዊት ከተማ በታላቅ ደስታ አመጣው። እነዚያ የእግዚአብሔርን ታቦት ተሸክመው የነበሩት ሰዎች ስድስት ርምጃ በሄዱ ቍጥር፣ አንድ በሬና አንድ የሠባ ጥጃ ይሠዋ ነበር። ዳዊትም የበፍታ ኤፉድ በወገቡ ታጥቆ በሙሉ ኀይሉ በእግዚአብሔር ፊት ይጨፍር ነበር። እንዲህ ባለ ሁኔታም ዳዊትና መላው የእስራኤል ቤት ሆይ እያሉና ቀንደ መለከቱን እየነፉ የእግዚአብሔርን ታቦት አመጡ። የእግዚአብሔር ታቦት ወደ ዳዊት ከተማ ሲገባ፣ የሳኦል ልጅ ሜልኮል በመስኮት ሆና ትመለከት ነበር፤ ንጉሥ ዳዊት በእግዚአብሔር ፊት ሲዘልልና ሲያሸበሽብ ባየችው ጊዜ በልቧ ናቀችው። ከዚያም የእግዚአብሔርን ታቦት አምጥተው፣ ዳዊት በተከለለት ድንኳን ውስጥ አኖሩት፤ ዳዊትም የሚቃጠል መሥዋዕትና የኅብረት መሥዋዕት በእግዚአብሔር ፊት አቀረበ። ዳዊት የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የኅብረቱን መሥዋዕት ካቀረበ በኋላ ሕዝቡን በሰራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ስም ባረከ። የእስራኤል ወገን ለሆነው ለሕዝቡ ሁሉ፣ ለወንዱም ለሴቱም ለእያንዳንዱ ሰው አንዳንድ ሙልሙል ዳቦ፣ አንዳንድ ሙዳ ሥጋና አንዳንድ የዘቢብ ጥፍጥፍ ሰጠ፤ ከዚህ በኋላ ሁሉም ወደየቤቱ ሄደ። ዳዊት ቤተ ሰቡን ለመመረቅ ወደ ቤቱ በተመለሰ ጊዜ፣ የሳኦል ልጅ ሜልኮል ልትቀበለው ወጥታ፣ “ዛሬ የእስራኤል ንጉሥ በመኳንንቱ ገረዶች ፊት እንደ አንድ ተራ ሰው ዕራቍቱን መታየቱ ክብሩ ሆኖ ነው!” አለችው። ዳዊትም ሜልኮልን እንዲህ አላት፤ “አዎን ከአባትሽና በቤቱ ካሉት ሁሉ አስበልጦ በእግዚአብሔር ሕዝብ በእስራኤል ላይ ገዥ አድርጎ በመረጠኝ በእግዚአብሔር ፊት አሸብሽቤአለሁ፤ አሁንም አሸበሽባለሁ። እንዲያውም ከዚህ ይልቅ ራሴን በፊቱ ዝቅ አደርጋለሁ፤ ከዚህም የባሰ የተናቅሁ እሆናለሁ፤ ነገር ግን በጠቀስሻቸው ገረዶች ፊት እከብራለሁ።” የሳኦልም ልጅ ሜልኮል እስከሞተችበት ጊዜ ድረስ ልጅ አልወለደችም ነበር።
2 ሳሙኤል 6:1-23 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ዳዊትም ዳግም ከእስራኤል የተመረጡትን ሠላሳ ሺህ ያህል ሰው ሰበሰበ። ዳዊትና ከእርሱ ጋር የነበሩት ሕዝብ ሁሉ በይሁዳ ካለች ከበኣል ተነሥተው በኪሩቤል ላይ በተቀመጠ በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ስም የተጠራውን የእግዚአብሔርን ታቦት ከዚያ ያመጡ ዘንድ ሄዱ። የእግዚአብሔርንም ታቦት በአዲስ ሰረገላ ላይ ጫኑ፥ በኮረብታውም ላይ ከነበረው ከአሚናዳብ ቤት አመጡት፥ የአሚናዳብ ልጆችም ዖዛ እና አሒዮ አዲሱን ሰረገላ ይነዱ ነበር። በኮረብታውም ላይ ከነበረው ከአሚናዳብ ቤት የእግዚአብሔርን ታቦት ባመጡ ጊዜ አሒዮ በታቦቱ ፊት ይሄድ ነበር። ዳዊትና የእስራኤልም ቤት ሁሉ በቅኔና በበገና በመሰንቆም በከበሮም በነጋሪትና በጸናጽል በእግዚአብሔር ፊት በሙሉ ኃይላቸው ይጫወቱ ነበር። ወደ ናኮንም አውድማ በደረሱ ጊዜ በሬዎቹ ይፋንኑ ነበርና ዖዛ እጁን ዘርግቶ የእግዚአብሔርን ታቦት ያዘ። የእግዚአብሔርም ቁጣ በዖዛ ላይ ነደደ፥ እግዚአብሔርም ስለ ድፍረቱ በዚያው ቀሠፈው፥ በእግዚአብሔርም ታቦት አጠገብ በዚያው ሞተ። እግዚአብሔርም ዖዛን ስለ ሰበረው ዳዊት አዘነ፥ እስከ ዛሬም ድረስ የዚያ ስፍራ ስም የዖዛ ስብራት ተብሎ ተጠራ። በዚያም ቀን ዳዊት እግዚአብሔርን ፈራና፦ የእግዚአብሔር ታቦትም ወደ እኔ እንዴት ይመጣል? አለ። ዳዊትም የእግዚአብሔርን ታቦት ወደ እርሱ ወደ ዳዊት ከተማ ያመጣው ዘንድ አልወደደም፥ ዳዊትም በጌት ሰው በአቢዳራ ቤት አገባው። የእግዚአብሔርም ታቦት በጌት ሰው በአቢዳራ ቤት ሦስት ወር ያህል ተቀመጠ፥ እግዚአብሔርም አቢዳራንና ቤቱን ሁሉ ባረከ። ንጉሡ ዳዊትም እግዚአብሔር የአቢዳራን ቤትና የነበረውን ሁሉ ስለ እግዚአብሔር ታቦት እንደ ባረከ ሰማ። ዳዊትም ሄዶ የእግዚአብሔርን ታቦት ከአቢዳራ ቤት ወደ ዳዊት ከተማ በደስታ አመጣው። የእግዚአብሔርንም ታቦት የተሸከሙ ስድስት እርምጃ በሄዱ ጊዜ አንድ በሬና አንድ ፍሪዳ ሠዋ። ዳዊትም በሙሉ ኃይሉ በእግዚአብሔር ፊት ይዘፍን ነበር፥ ዳዊትም የበፍታ ኤፉድ ለብሶ ነበር። ዳዊትና የእስራኤልም ቤት ሁሉ ሆ እያሉ ቀንደ መለከትም እየነፋ የእግዚአብሔርን ታቦት አመጡ። የእግዚአብሔርም ታቦት ወደ ዳዊት ከተማ በገባ ጊዜ የሳኦል ልጅ ሜልኮል በመስኮት ሆና ተመለከተች፥ ንጉሡም ዳዊት በእግዚአብሔር ፊት ሲዘልልና ሲዘፍን አየች፥ በልብዋም ናቀችው። የእግዚአብሔርንም ታቦት አገቡ፥ ዳዊትም በተከለለት ድንኳን ውስጥ በስፍራው አኖሩት፥ ዳዊትም የሚቃጠልና የደኅንነት መሥዋዕትን በእግዚአብሔር ፊት አሳረገ። ዳዊትም የሚቃጠልና የደኅንነት መሥዋዕት ማሳረግ ከፈጸመ በኋላ ሕዝቡን በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ስም መረቀ። ለሕዝቡም ሁሉ ለእስራኤል ወገን ለወንዱም ለሴቱም ለእያንዳንዱ አንዳንድ እንጀራ አንዳንድም የሥጋ ቁራጭ አንዳንድም የዘቢብ ጥፍጥፍ አከፋፈለ። ሕዝቡም ሁሉ እያንዳንዱ ወደ ቤቱ ሄደ። ዳዊትም ቤተ ሰቡን ሊመርቅ ተመለሰ። የሳኦልም ልጅ ሜልኮል ዳዊትን ለመቀበል ወጣችና፦ ምናምንቴዎች እርቃናቸውን እንደሚገልጡ የእስራኤል ንጉሥ በባሪያዎቹ ቈነጃጅት ፊት እርቃኑን በመግለጡ ምንኛ የተከበረ ነው! አለችው። ዳዊትም ሜልኮልን፦ በእግዚአብሔር ፊት ዘፍኛለሁ፥ በእግዚአብሔር ሕዝብ በእስራኤል ላይ አለቃ እሆን ዘንድ ከአባትሽና ከቤቱ ሁሉ ይልቅ የመረጠኝ እግዚአብሔር የተባረከ ይሁን ስለዚህም በእግዚአብሔር ፊት እጫወታለሁ። አሁንም ከሆንሁት ይልቅ የተናቅሁ እሆናለሁ፥ በዓይንሽም እዋረዳለሁ፥ ነገር ግን በተናገርሽው ቈነጃጅት ዘንድ እከብራለሁ አላት። የሳኦልም ልጅ ሜልኮል እስከ ሞተችበት ቀን ድረስ ልጅ አልወለደችም።
2 ሳሙኤል 6:1-23 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ዳዊት እንደገና ከመላው እስራኤል የተመረጡ በድምሩ ሠላሳ ሺህ የሚሆኑ ምርጥ ወታደሮች በአንድነት አሰባሰበ፤ ዳዊትና አብረውት የነበሩት ሰዎች ሁሉ በኪሩቤል ላይ ዙፋኑን የዘረጋውን በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ስም የተጠራውን የቃል ኪዳኑን ታቦት ለማምጣት ወደ በዓለ ይሁዳ ሄዱ። እነርሱም የቃል ኪዳኑን ታቦት በኮረብታ ላይ ከሚገኘው ከአቢናዳብ ቤት አውጥተው በአዲስ ሠረገላ ላይ አኖሩት፤ ዑዛና አሕዮ ተብለው የሚጠሩት የአቢናዳብ ልጆች ሠረገላውን እየመሩ በሚጓዙበት ጊዜ፥ አሕዮ ከታቦቱ ፊት ቀድሞ ይሄድ ነበር። ዳዊትና እስራኤላውያን ሁሉ የበገና፥ የመሰንቆ፥ የከበሮ፥ የጸናጽልና የቃጭል ድምፅ እያሰሙ ለእግዚአብሔር ክብር በመዘመር በሙሉ ኀይላቸው ያሸበሽቡ ነበር። ናኮን ተብሎ ወደሚጠራውም አውድማ በደረሱ ጊዜ ሠረገላውን የሚስቡት በሬዎች ስለ ነቀነቁት ዑዛ እጁን ዘርግቶ የቃል ኪዳኑ ታቦት እንዳይወድቅ ደገፈ፤ እግዚአብሔር አምላክም ወዲያውኑ ተቈጥቶ ስለ ድፍረቱ ዑዛን ገደለው፤ ስለዚህም ዑዛ በዚያው በቃል ኪዳን ታቦት አጠገብ ሞተ፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮም የዚያ ስፍራ ስም “ፌሬጽዑዛ” እየተባለ ሲጠራ ይኖራል፤ እግዚአብሔር በቊጣ ተነሣሥቶ ዑዛን በመግደሉ ዳዊት እጅግ ተበሳጨ። ከዚያም በኋላ ዳዊት እግዚአብሔርን ስለ ፈራ “እንዲህ ከሆነማ የቃል ኪዳኑን ታቦት እንዴት ልወስደው እችላለሁ?” አለ። ስለዚህም ታቦቱን ወደ ኢየሩሳሌም ላለመውሰድ ወሰነ፤ ይህንንም በማድረግ ፈንታ ከመንገድ መልሶ የጋት ከተማ ነዋሪ ወደ ሆነው ዖቤድኤዶም ተብሎ ወደሚጠራው ሰው ቤት አስገባው፤ እዚያም ሦስት ወር ተቀመጠ፤ እግዚአብሔርም ዖቤድኤዶምንና ቤተሰቡን ባረከ። በቃል ኪዳኑ ታቦት ምክንያት እግዚአብሔር የዖቤድኤዶምን ቤተሰብና ያለውን ነገር ሁሉ እግዚአብሔር የባረከለት መሆኑን ንጉሥ ዳዊት ሰማ፤ ስለዚህም የቃል ኪዳኑን ታቦት በታላቅ ደስታ ወደ ኢየሩሳሌም ሊወስደው በማሰብ ወደ ዖቤድኤዶም ቤት ሄዶ አወጣው። የቃል ኪዳኑን ታቦት የተሸከሙት ሰዎች ስድስት እርምጃ በተራመዱ ቊጥር ዳዊት እንደገና እያስቆመ አንድ ወይፈንና አንድ የሰባ ፍሪዳ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት ያቀርብ ነበር። ዳዊት ከበፍታ የተሠራ ሽርጥ በወገቡ ዙሪያ ታጥቆ እግዚአብሔርን በማክበር በሙሉ ኀይሉ ያሸበሽብ ነበር፤ በዚህም ዐይነት ዳዊትና መላው እስራኤል በደስታ እልል እያሉና የእምቢልታ ድምፅ እያሰሙ፥ የቃል ኪዳኑን ታቦት ወደ ኢየሩሳሌም ይዘው ሄዱ። ታቦቱን ይዘው ወደ ከተማ በሚገቡበት ጊዜ የሳኦል ልጅ ሜልኮል በመስኮት ተመለከተች፤ ንጉሡ ዳዊት እየዘለለ ሲያሸበሽብ አይታም በልብዋ ናቀችው፤ ታቦቱንም አምጥተው ዳዊት ባዘጋጀለት ድንኳን ውስጥ በተመደበለት ስፍራ አኖሩት፤ ከዚህም በኋላ ዳዊት የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የአንድነት መሥዋዕት ሁሉ ለእግዚአብሔር አቀረበ። መሥዋዕት ማቅረቡንም በፈጸመ ጊዜ በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ስም ሕዝቡን መረቀ፤ ለሁሉም ምግብ አደላቸው፤ በእስራኤል ለሚገኘው ለእያንዳንዱ ወንድና ሴት አንዳንድ ኅብስት፥ አንዳንድ ቊራጭ የተጠበሰ ሥጋና አንዳንድ የዘቢብ ጥፍጥፍ ሰጠ፤ ከዚያም በኋላ ሁሉም ወደየቤታቸው ሄዱ። ከዚያም በኋላ ዳዊት ቤተሰቡን ሰላም ለማለት ወደ ቤት ገባ፤ የሳኦል ልጅ ሜልኮል ልትቀበለው ወጣችና “የእስራኤል ንጉሥ ዛሬ ትልቅ ስም አግኝቶአል! በመኳንንቱ ገረዶች ፊት እንደ ቅሌታም ሽማግሌ እርቃኑን ገልጦአል!” አለችው። ዳዊትም እንዲህ ሲል መለሰላት፦ “እኔ ያሸበሸብኩት የሕዝቡ የእስራኤል መሪ ያደርገኝ ዘንድ በአባትሽና በቤተሰቡ ፈንታ ለመረጠኝ እግዚአብሔር ክብር ነው፤ አሁንም ቢሆን እርሱን ለማክበር ከመጨፈር አልገታም፤ ከዚህም የባሰ ራሴን አዋርዳለሁ፤ ለአንቺ እንደሚመስልሽ በዐይንሽ ፊት የተናቅሁ ብሆንም በእነርሱ ፊት ራስህን አዋረድክ ብለሽ በተናገርሽባቸው ልጃገረዶች ዘንድ እጅግ የተከበርኩ እሆናለሁ!” ከዚህም የተነሣ የሳኦል ልጅ ሜልኮል እስከ ሞተችበት ቀን ድረስ ልጅ አልወለደችም።
2 ሳሙኤል 6:1-23 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ዳዊት እንደገና ከእስራኤል የተመረጡትን ሠላሳ ሺህ ሰዎች ሰበሰበ። ዳዊትና ከእርሱ ጋር የነበሩት ሰዎች ሁሉ፥ በኪሩቤል ላይ በተቀመጠ በሠራዊት ጌታ ስም የተጠራውን የእግዚአብሔርን ታቦት ከዚያ ለማምጣት በይሁዳ ወዳለችው በዓል ሄዱ። የእግዚአብሔርንም ታቦት በአዲስ ሠረገላ ላይ አኑረው፥ በኰረብታ ላይ ካሚገኘው ከአቢናዳብ ቤት አውጥተው አመጡ፤ ሠረገላውን ይነዱ የነበሩትም የአቢናዳብ ልጆች ዖዛና አሒዮ ነበሩ፤ የእግዚአብሔርም ታቦት በሠረገላው ላይ ሆኖ፥ አሒዮ ፊት ፊት ይሄድ ነበር። ዳዊትና የእስራኤል ቤት በሙሉ በዝማሬ፥ በበገና፥ በመሰንቆ፥ በከበሮ፥ በጽናጽልና በቃጭል ድምፅ በጌታ ፊት ያሸበሽቡ ነበር። ወደ ናኮን አውድማ ሲደርሱም በሬዎቹ ስለተደናቀፉ፥ ዖዛ እጁን ዘርግቶ የእግዚአብሔርን ታቦት ያዘ። ዖዛ በድፍረት ይህን ስላደረገ፥ የጌታ ቁጣ በላዩ ላይ ነደደ፤ ስለዚህም እግዚአብሔር ቀሠፈው፤ እርሱም በእግዚአብሔር ታቦት አጠገብ እዚያው ሞተ። የጌታ ቁጣ ዖዛን ስለሰበረው ዳዊት አዘነ፤ ያም ቦታ እስከ ዛሬ ድረስ ፌሬጽ ዑዛ ተብሎ ይጠራል። ዳዊት በዚያን ቀን ጌታን ስለ ፈራ “የጌታ ታቦት እንዴት ወደ እኔ ይመጣል?” አለ። ስለዚህ ዳዊት የጌታን ታቦት አብሮት እንዲሆን ወደ ዳዊት ከተማ ይዞት ለመሄድ አልፈለገም፤ በዚህ ፈንታ አቅጣጫ ለውጦ የጌት ሰው ወደ ሆነው ወደ ዖቤድ ኤዶም ቤት ወሰደው። የጌታም ታቦት የጌት ሰው በሆነው በዖቤድ ኤዶም ቤት ሦስት ወር ተቀመጠ፤ ጌታም ዖቤድ ኤዶምና ቤተሰቡን ሁሉ ባረከ። በዚህ ጊዜ፥ “በእግዚአብሔር ታቦት ምክንያት የዖቤድ ኤዶም ቤተሰቡና ያለውን ሁሉ ጌታ ባረከለት” ብለው ለዳዊት ነገሩት። ስለዚህ ዳዊት ወደዚያው ወርዶ፥ የእግዚአብሔርን ታቦት ከዖቤድኤዶም ቤት ወደ ዳዊት ከተማ በታላቅ ደስታ አመጣው። እነዚያ የጌታን ታቦት ተሸክመው የነበሩት ሰዎች ስድስት ርምጃ በሄዱ ቍጥር፥ በሬና የሰባ ፍሪዳ ይሠዋ ነበር። ዳዊትም የበፍታ ኤፉድ በወገቡ ታጥቆ በሙሉ ኀይሉ በጌታ ፊት ይጨፍር ነበር። እንዲህ ባለ ሁኔታም ዳዊትና መላው የእስራኤል ቤት እየጨፈሩና ቀንደ መለከቱን እየነፉ የጌታን ታቦት አመጡ። የጌታ ታቦት ወደ ዳዊት ከተማ ሲገባ፥ የሳኦል ልጅ ሜልኮል በመስኮት ሆና ትመለከት ነበር፤ ንጉሥ ዳዊት በጌታ ፊት ሲዘልና ሲያሸበሽብ ባየችው ጊዜ በልቧ ናቀችው። ከዚያም የጌታን ታቦት አምጥተው፥ ዳዊት በተከለለት ድንኳን ውስጥ በተዘጋጀለት ስፍራ አኖሩት፤ ዳዊትም የሚቃጠል መሥዋዕትና የሰላም መሥዋዕት በጌታ ፊት አቀረበ። ዳዊት የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የሰላም መሥዋዕት ካቀረበ በኋላ ሕዝቡን በሠራዊት ጌታ ስም ባረከ። የእስራኤል ወገን ለሆነው ለሕዝቡ ሁሉ፥ ለወንዱም ለሴቱም ለእያንዳንዱ ሰው አንዳንድ እንጀራ፥ አንዳንድ ቁራጭ ሥጋና አንዳንድ የዘቢብ ጥፍጥፍ ሰጠ፤ ከዚህ በኋላ ሁሉም ወደየቤቱ ሄደ። ዳዊትም ቤተሰቡን ለመመረቅ ወደ ቤቱ ተመለሰ፤ የሳኦል ልጅ ሜልኮል ግን ልትቀበለው ወጣችና፥ “ዛሬ የእስራኤል ንጉሥ በመኳንንቱ ገረዶች ፊት እንደ አንድ ተራ ሰው ራቁቱን መታየቱ ክብሩ ሆኖ ነው!” አለችው። ዳዊትም ሜልኮልን እንዲህ አላት፤ “አዎን ያሸበሸብኩት በጌታ ፊት ነው፤ በአባትሽና በቤቱ ካሉት ሁሉ አስበልጦ በጌታ ሕዝብ በእስራኤል ላይ ገዥ አድርጎ በመረጠኝ በጌታ ፊት አሁንም እጨፍራለሁ። እንዲያውም ከዚህ ይልቅ ራሴን በፊቱ ዝቅ አደርጋለሁ፤ ከዚህም የባሰ በፊትሽ የተናቅሁ እሆናለሁ፤ ነገር ግን በጠቀስሻቸው ገረዶች ፊት እከብራለሁ።” የሳኦልም ልጅ ሜልኮል እሰከሞተችበት ጊዜ ድረስ ልጅ አልወለደችም ነበር።