2 ሳሙኤል 14:1-4
2 ሳሙኤል 14:1-4 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
የሶርህያ ልጅ ኢዮአብም የንጉሡ ልብ ወደ አቤሴሎም እንዳዘነበለ ዐወቀ። ኢዮአብም ወደ ቴቁሔ ልኮ ከዚያ ብልሃተኛ ሴት አስመጣና፥ “አልቅሺ፤ የኀዘንም ልብስ ልበሺ፤ ዘይትም አትቀቢ፤ ስለ ሞተ ሰውም ብዙ ዘመን እንደምታለቅስ ሴት ሁኚ፤ ወደ ንጉሡም ገብተሽ እንዲህ ያለውን ቃል ንገሪው” አላት፤ ኢዮአብም ቃሉን በእርስዋ አፍ አደረገ። እንዲሁም የቴቁሔዪቱ ሴት ወደ ንጉሥ ገብታ በግንባርዋ በምድር ላይ ወደቀች፤ ሰግዳም “ንጉሥ ሆይ፥ አድነኝ፤ አድነኝ” አለች።
2 ሳሙኤል 14:1-4 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
የጽሩያ ልጅ ኢዮአብ የንጉሡ ልብ አቤሴሎምን እንደ ናፈቀ ተረዳ። ስለዚህም ኢዮአብ ወደ ቴቁሔ፤ ሰው ልኮ አንዲት ብልኅ የሆነች ሴት አስመጣ፤ እንዲህም አላት፤ “ሐዘንተኛ በመምሰል የሐዘን ልብስ ልበሺ፤ ዘይት አትቀቢ፤ ለሞተ ሰው ብዙ ጊዜ እንዳዘነች ሴት መስለሽም ታዪ። ከዚያም ወደ ንጉሡ ሄደሽ እንዲህ በዪው።” ከዚያም ኢዮአብ የምትናገራቸውን ቃላት ነገራት። የቴቁሔዪቱም ሴት ወደ ንጉሡ ገብታ፣ በንጉሡ ፊት ወደ መሬት በግምባሯ ተደፍታ እጅ በመንሣት አክብሮቷን ከገለጠች በኋላ፣ “ንጉሥ ሆይ! እርዳኝ” አለች።
2 ሳሙኤል 14:1-4 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
የጽሩያም ልጅ ኢዮአብ የንጉሡ ልብ ወደ አቤሴሎም እንዳዘነበለ አወቀ። ኢዮአብም ወደ ቴቁሔ ልኮ ከዚያ ብልሃተኛ ሴት አስመጣና፦ አልቅሺ፥ የኅዘንም ልብስ ልበሺ፥ ዘይትም አትቀቢ፥ ስለ ሞተ ሰውም ብዙ ዘመን እንደምታለቅሺ ሁኚ፥ ወደ ንጉሡም ገብተሽ እንዲህ ያለውን ቃል ንገሪው አላት፥ ኢዮአብም ቃሉን በእርስዋ አፍ አደረገ። እንዲሁም የቴቁሔይቱ ሴት ወደ ንጉሥ ገብታ በግምባርዋ በምድር ላይ ወደቀች፥ እጅ ነሥታም፦ ንጉሥ ሆይ፥ አድነኝ አለች።
2 ሳሙኤል 14:1-4 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ንጉሡ ዳዊት አቤሴሎምን እንደ ናፈቀ የጽሩያ ልጅ ኢዮአብ ተረዳ፤ ስለዚህም በተቆዓ የምትኖረውን አንዲት ብልኅ ሴት አስጠራ፤ እርስዋም በደረሰች ጊዜ “ሐዘንተኛ ለመምሰል ሞክሪ፤ የሐዘን ልብስሽን ልበሺ፤ ቅቤም አትቀቢ፤ ለብዙ ጊዜ በሐዘን ላይ የቈየሽ ሴት ለመምሰል ተዘጋጂ፤ ከዚያም በኋላ ወደ ንጉሡ ቀርበሽ እኔ የምነግርሽን ንገሪው” አላት፤ ከዚህ በኋላ እርስዋ ልትናገረው የሚገባትን ሁሉ ኢዮአብ ነገራት። ሴቲቱም ወደ ንጉሡ ቀርባ ወደ መሬት ለጥ ብላ እጅ ነሣችና “ንጉሥ ሆይ! እባክህ እርዳኝ!” አለችው።
2 ሳሙኤል 14:1-4 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
የንጉሡ ልብ አቤሴሎምን እንደናፈቀ የጽሩያ ልጅ ኢዮአብ ተረዳ። ስለዚህም ኢዮአብ ወደ ተቆዓ ሰው ልኮ አንዲት ብልኅ የሆነች ሴት አስመጣ፤ እንዲህም አላት፤ “ኀዘንተኛ በመምሰል የኀዘን ልብስ ልበሺ፤ ዘይት አትቀቢ፤ ለሞተ ሰው ብዙ ጊዜ እንዳዘነች ሴት ትሆኛለሽ፤ ከዚያም ወደ ንጉሡ ሂጂ፤ እንዲህም በዪው።” ከዚያም ኢዮአብ መናገር ያለባትን ነገር ነገራት። የተቆዓዪቱም ሴት ወደ ንጉሡ ገብታ፥ በንጉሡ ፊት በግምባሯ በምድር ላይ ተደፍታ እጅ በመንሣት፥ “ንጉሥ ሆይ! እርዳኝ” አለች።