2 ሳሙኤል 13:1-39
2 ሳሙኤል 13:1-39 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ከዚህም በኋላ እንዲህ ሆነ፤ ለዳዊት ልጅ ለአቤሴሎም አንዲት የተዋበች እኅት ነበረችው፤ ስምዋም ትዕማር ነበረ፤ የዳዊትም ልጅ አምኖን ወደዳት። አምኖንም ከእኅቱ ከትዕማር የተነሣ እስከሚታመም ድረስ እጅግ ተከዘ፤ ድንግልም ነበረችና አንዳች ነገር ያደርግባት ዘንድ በዐይኑ ፊት ጭንቅ ሆኖበት ነበር። ለአምኖንም የዳዊት ወንድም የሳምዓ ልጅ ኢዮናዳብ የሚባል ወዳጅ ነበረው፤ ኢዮናዳብም እጅግ ብልህ ሰው ነበረ። እርሱም፥ “የንጉሥ ልጅ ሆይ፥ ስለምን በየቀኑ እንዲህ ከሳህ? አትነግረኝምን?” አለው። አምኖንም፥ “የወንድሜን የአቤሴሎምን እኅት ትዕማርን እወድዳታለሁ” አለው። ኢዮናዳብም አለው፦“ ታምሜአለሁ ብለህ በአልጋህ ላይ ተኛ፤ አባትህም ሊያይህ ይመጣል፦ እኅቴ ትዕማር እንድትመጣና እኔ የምበላውን እንጀራ እንድትሰጠኝ፥ መብሉንም እኔ እያየሁ እንድታበስልልኝ፥ ከእጅዋም እንድበላው እለምንሃለሁ በለው።” እንዲሁም አምኖን፥ ታምሜአለሁ ብሎ ተኛ፤ ንጉሡም ሊያየው መጣ፤ አምኖንም ንጉሡን፥ “እኅቴ ትዕማር እንድትመጣና እኔ እያየሁ ሁለት እንጎቻ እንድታበስልልኝ፥ ከእጅዋም እንድበላ እለምንሃለሁ” አለው። ዳዊትም፥ “ወደ ወንድምሽ ወደ አምኖን ቤት ሂጂ፤ መብልንም አዘጋጂለት” ብሎ ወደ ትዕማር ቤት ላከ። ትዕማርም ወደ ወንድምዋ ወደ አምኖን ቤት ሄደች፤ ተኝቶም ነበር፤ ዱቄትም ወስዳ ለወሰች፤ በፊቱም እንጎቻ አደረገች፤ ጋገረችም። ምጣዱንም ወስዳ በፊቱ ገለበጠች፤ እርሱ ግን ይበላ ዘንድ እንቢ አለ። አምኖንም፥ “ሰውን ሁሉ ከእኔ ዘንድ አስወጡ” አለ፤ ሰውም ሁሉ ከእርሱ ዘንድ ወጣ። አምኖንም ትዕማርን፥ “በእጅሽ እበላ ዘንድ መብሉን ወደ እልፍኙ አግቢው” አላት፤ ትዕማርም የሠራችውን እንጎቻ ወስዳ ወንድምዋ አምኖን ወዳለበት እልፍኝ አገባችው። ይበላም ዘንድ መብሉን አቀረበችለት። እርሱም ያዛትና፥ “እኅቴ ሆይ፥ ነዪ ከእኔ ጋር ተኚ” አላት። እርስዋም አለችው፥ “ወንድሜ ሆይ፥ አታዋርደኝ፤ እንዲህ ያለ ነገር በእስራኤል ዘንድ አይገባምና ይህን ነውረኛ ሥራ አታድርግ። እኔም ነውሬን ወዴት እጥላታለሁ? አንተም በእስራኤል ዘንድ ከሰነፎች እንደ አንዱ ትሆናለህ፤ እንግዲያስ ለንጉሡ ንገረው፥ እኔንም አይነሣህም” አለችው። አምኖንም ቃልዋን አልሰማም፤ ይዞም አደከማት፤ ከእርስዋም ጋር ተኛ። ከዚያም በኋላ አምኖን ፈጽሞ ጠላት፤ አስቀድሞ ከአፈቀራት ፍቅር ይልቅ በኋላ የጠላት ጥል በለጠ። አምኖንም፥ “ተነሥተሽ ሂጂ” አላት። ትዕማርም፥ “ቀድሞ ከሠራኸው ክፋት ይልቅ እኔን በማውጣትህ የበለጠ ክፋት ትሠራለህ” አለችው፤ አምኖን ግን ቃልዋን አልሰማትም። በበር ቁሞ የሚያገለግለውንም ብላቴና ጠርቶ፥ “ይህችን ሴት ከፊቴ አስወጥተህ በሩን ዝጋባት” አለው። ብዙ ኅብር ያለውንም ልብስ ለብሳ ነበር፤ የንጉሡ ልጆች ደናግሉ እንዲህ ያለውን ልብስ ይለብሱ ነበርና፤ አገልጋዩም አስወጥቶ በሩን ዘጋባት። ትዕማርም አመድ ወስዳ በራስዋ ላይ ነሰነሰች፤ በላይዋ የነበረውንም ብዙ ኅብር ያለውን ልብስዋን ቀደደችው፤ እጅዋንም በራስዋ ላይ ጭና እየጮኸች ሄደች። ወንድምዋም አቤሴሎም፥ “ወንድምሽ አምኖን ከአንቺ ጋር ነበርን? እኅቴ ሆይ፥ አሁን ግን ዝም በዪ፤ ወንድምሽ ነውና፤ ይህን ነገር ትናገሪ ዘንድ በልብሽ አታስቢ” አላት። ትዕማርም በወንድምዋ በአቤሴሎም ቤት መበለት ሆና ተቀመጠች። ንጉሡም ዳዊት ይህን ነገር ሁሉ ሰማ፤ እጅግም ተቈጣ፥ ነገር ግን የበኵር ልጁ ነበረና ስለ ወደደው የልጁን የአምኖንን ነፍስ አላሳዘነም። አቤሴሎምም አምኖንን ክፉም ሆነ መልካም አልተናገረውም። እኅቱን ትዕማርን ስላስነወራት አቤሴሎም አምኖንን ጠልቶታልና። ከሁለት ዓመትም በኋላ አቤሴሎም በኤፍሬም አቅራቢያ ባለችው በቤላሶር በጎቹን በሚያሸልትበት ጊዜ አቤሴሎም የንጉሡን ልጆች ሁሉ ጠራ። አቤሴሎምም ወደ ንጉሡ መጥቶ፥ “እነሆ፥ አገልጋይህ በጎቹን ያሸልታል፤ ንጉሡ ከአገልጋይህ ጋር ይሂድ፤ አገልጋዮቹም ይሂዱ” አለው። ንጉሡም አቤሴሎምን፥ “ልጄ ሆይ፥ አይሆንም፤ እንከብድብሃለንና ሁላችን አንሄድም” አለው። የግድም አለው፤ እርሱ ግን መረቀው እንጂ ለመሄድ እንቢ አለ። አቤሴሎምም፥ “አንተ እንቢ ካልህ ወንድሜ አምኖን ከእኛ ጋር እንዲሄድ እለምንሃለሁ” አለ። ንጉሡም፥ “ከአንተ ጋር ለምን ይሄዳል?” አለው። አቤሴሎምም የግድ አለው፤ አምኖንንና የንጉሡንም ልጆች ከእርሱ ጋር ላከ። አቤሴሎምም እንደ ንጉሥ ግብዣ ያለ ግብዣ አደረገ፤ አቤሴሎምም አገልጋዮቹን፥ “አምኖን የወይን ጠጅ ጠጥቶ ልቡን ደስ ባለው ጊዜ እዩ፦ አምኖንን ግደሉ ባልኋችሁ ጊዜ ግደሉት። አትፍሩም፤ ያዘዝኋችሁም እኔ ነኝና በርቱ፤ ጽኑም” ብሎ አዘዛቸው። የአቤሴሎምም አገልጋዮች አቤሴሎም እንዳዘዛቸው በአምኖን ላይ አደረጉበት። የንጉሡም ልጆች ሁሉ ተነሥተው በየበቅሎዎቻቸው ተቀምጠው ሸሹ። ገናም በመንገድ ሲሄዱ ለዳዊት፥ “አቤሴሎም የንጉሡን ልጆች ሁሉ ገደላቸው፤ ከእነርሱም አንድ አልቀረም” የሚል ወሬ መጣ። ንጉሡም ተነሥቶ ልብሱን ቀደደ፤ በምድር ላይም ወደቀ፤ በዙሪያውም ቁመው የነበሩ ብላቴኖቹ ሁሉ ልብሳቸውን ቀደዱ። የዳዊትም ወንድም የሳምዓ ልጅ ኢዮናዳብ መልሶ እንዲህ አለው፥ “ጌታዬ ጐልማሶቹ የንጉሡ ልጆች ሁሉ እንደ ሞቱ አያስብ፤ እኅቱን ትዕማርን በግድ ካስነወራት ጀምሮ በአቤሴሎም ዘንድ የተቈረጠ ነገር ነበረና የሞተ አምኖን ብቻ ነው። አሁንም የሞተ አምኖን ብቻ ነው እንጂ የንጉሥ ልጆች ሁሉ ሞቱ ብሎ ጌታዬ ንጉሡ ይህን ነገር በልቡ አያስብ።” አቤሴሎምም ኰበለለ። ጕበኛውም ጐልማሳ ዐይኑን ከፍ አደረገ፤ እነሆም፥ ብዙ ሰዎች በኋላው በተራራው አጠገብ በመንገድ ሲመጡ አየ። ጕበኛውም መጥቶ ለንጉሡ እንዲህ ብሎ ነገረው፥ “ብዙ ሰዎች በተራራው ጎን ባለው በአርኖን መንገድ ሲመጡ አየሁ።” ኢዮናዳብም ንጉሡን፥ “እነሆ፥ የንጉሡ ልጆች መጥተዋል፤ አገልጋይህ እንዳለው እንዲሁ ሆኖአል” አለው። ተናግሮም በጨረሰ ጊዜ እነሆ፥ ወዲያው የንጉሥ ልጆች ገቡ፤ ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው አለቀሱ፤ ደግሞም ንጉሡና ብላቴኖቹ ሁሉ እጅግ ታላቅ ልቅሶ አለቀሱ። አቤሴሎም ግን ኰብልሎ ወደ መአክ ሀገር ወደ ጌድሶር ንጉሥ ወደ አሚሁድ ልጅ ወደ ቶልማይዮ ሄደ። ዳዊትም ሁል ጊዜ ለልጁ ያለቅስ ነበር። አቤሴሎምም ኰብልሎ ወደ ጌድሶር ሄደ፤ በዚያም ሦስት ዓመት ያህል ተቀመጠ። ንጉሡም ዳዊት አቤሴሎምን መከታተልን ተወ፤ ስለ ሞተው ልጁ ስለ አምኖን ተጽናንቶ ነበርና።
2 ሳሙኤል 13:1-39 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
የዳዊት ልጅ አቤሴሎም ትዕማር የምትባል ቈንጆ እኅት ነበረችው፤ እርሷንም የዳዊት ልጅ አምኖን ወደዳት። አምኖን እኅቱን ትዕማርን ከማፍቀሩ የተነሣ እስኪታመም ድረስ ተጨነቀ፤ ድንግል ስለ ሆነች እርሷን ማግኘት የማይቻል ሆኖ አግኝቶታልና። አምኖን ኢዮናዳብ የተባለ ወዳጅ ነበረው፤ እርሱም የዳዊት ወንድም የሳምዓ ልጅ ነው። ኢዮናዳብ እጅግ ተንኰለኛ ሰው ነበር። አምኖንንም፣ “የንጉሥ ልጅ ሆይ፤ ሰውነትህ ቀን በቀን የሚከሳበትን ምክንያት ለምን አትነግረኝም?” ሲል ጠየቀው። አምኖንም፣ “የወንድሜን የአቤሴሎምን እኅት ትዕማርን አፍቅሬ ነው” አለው። ኢዮናዳብም፣ “እንግዲያው ‘ታምሜአለሁ’ ብለህ ዐልጋ ላይ ተኛ፤ አባትህ ሊጠይቅህ ሲመጣም፣ ‘እኅቴ ትዕማር መጥታ የምበላውን ነገር ብትሰጠኝ ደስ ይለኛል፤ መብሉንም እዚሁ አጠገቤ ሆና እያየሁ አዘጋጅታ በእጇ እንድታጐርሰኝ እባክህ ፍቀድልኝ ብለህ ንገረው፣’ ” አለው። ስለዚህ አምኖን የታመመ ሰው መስሎ ተኛ፤ ንጉሡም ሊጠይቀው መጣ፤ አምኖንም፣ “እኅቴ ትዕማር መጥታ፣ እያየሁ ሁለት እንጀራ ጋግራ በእጇ እንድታጐርሰኝ እለምንሃለሁ” ብሎ ጠየቀው። ዳዊትም፣ “ወንድምሽ አምኖን ቤት ሄደሽ ምግብ እንድታዘጋጂለት” በማለት ለትዕማር እንዲነግሯት ወደ ቤተ መንግሥቱ ላከ። ስለዚህም ትዕማር ወንድሟ አምኖን ወደ ተኛበት ቤት ሄደች፤ ጥቂት ሊጥ ወስዳ ካቦካች በኋላ እያየ አዘጋጅታ ጋገረችው፤ ከዚያም መጋገሪያውን አውጥታ እንጀራውን አቀረበችለት፤ እርሱ ግን መብላት አልፈለገም። አምኖንም፣ “ሰውን ሁሉ ከዚህ አስወጡልኝ” አለ፤ ያለውም ሰው ሁሉ ትቶት ወጣ። ከዚያም አምኖን ትዕማርን፣ “እንድታጐርሺኝ ምግቡን እዚሁ መኝታ ክፍሌ አምጪልኝ” አላት። ትዕማርም ያዘጋጀችውን እንጀራ ይዛ ወንድሟ አምኖን ወዳለበት መኝታ ክፍል ገባች። ነገር ግን ምግቡን ስታቀርብለት አፈፍ አድርጎ ያዛትና፣ “እኅቴ ነዪ ዐብረን እንተኛ” አላት። እርሷም እንዲህ አለችው፤ “እባክህ ወንድሜ ተው አይሆንም! አታስገድደኝ፤ እንዲህ ያለው ነገር በእስራኤል ተደርጎ አያውቅም፤ ይህን አሳፋሪ ድርጊት አታድርግ። እኔስ እንዴት እሆናለሁ? ነውሬንስ ተሸክሜ የት እገባለሁ? አንተስ ብትሆን በእስራኤል ሞኞች እንደ አንዱ መቈጠርህ አይደለምን? እባክህ ለንጉሡ ንገረው፤ እንዳላገባህም አይከለክለኝም።” እርሱ ግን ሊሰማት አልፈለገም፤ ከርሷ ይልቅ ብርቱ ስለ ነበር፣ በግድ አስነወራት፤ ከርሷም ጋራ ተኛ። ከዚያም አምኖን እጅግ ጠላት፤ እንዲያውም ቀድሞ ካፈቀራት የበለጠ ጠላት። አምኖንም፣ “ተነሽ ውጭልኝ!” አላት። እርሷም፣ “ይህ አይሆንም! እኔን አስወጥቶ መስደድ፣ አስቀድመህ ካደረስህብኝ በደል የባሰ መፈጸምህ ነው” አለችው። እርሱ ግን አልተቀበላትም፤ በግል የሚያገለግለውን ወጣት ጠርቶ፣ “ይህችን ሴት ከዚህ አስወጣና በሩን ዝጋባት” አለው። ስለዚህም አገልጋዩ አስወጥቶ በሩን ዘጋባት፤ ጌጠኛ የሆነና በዚያ ጊዜ ድንግል የሆኑት የንጉሥ ልጆች የሚለብሱትን ዐይነት ልብስ ለብሳ ነበር። ትዕማርም በራሷ ላይ ዐመድ ነሰነሰች፤ ጌጠኛ ልብሷን ቀደደች፤ ከዚያም እጇን በራሷ ላይ አድርጋ እያለቀሰች ሄደች። ወንድሟ አቤሴሎምም፣ “ያ ወንድምሽ አምኖን ካንቺ ጋራ ነበርን? እኅቴ ሆይ፣ አሁን ዝም በዪ፤ ወንድምሽ ስለ ሆነ፤ ነገሩን በልብሽ አትያዢው” አላት። ትዕማርም በወንድሟ በአቤሴሎም ቤት ብቸኛ ሴት ሆና ኖረች። ንጉሥ ዳዊት ይህን ሁሉ በሰማ ጊዜ እጅግ ተቈጣ፤ አቤሴሎም አምኖንን ክፉም ሆነ ደግ አንዳች ቃል አልተናገረውም፤ ምክንያቱም አምኖን እኅቱን ትዕማርን ስላስነወራት ጠልቶት ነበር። ከሁለት ዓመት በኋላ አቤሴሎም በኤፍሬም ድንበር አቅራቢያ ባለችው በቤላሶር ከተማ በጎቹን ይሸልት ነበር፤ በዚህ ጊዜ የንጉሡን ወንዶች ልጆች ሁሉ በዚያ እንዲገኙለት ጋበዛቸው። አቤሴሎምም ወደ ንጉሡ ሄዶ፣ “እነሆ፤ ባሪያህ በጎቹን እየሸለተ ነው፤ ታዲያ ንጉሡና ሹማምቱ ፈቃዳቸው ሆኖ እባክህ ይገኙልኝ?” ሲል ጠየቀው። ንጉሡም፣ “ልጄ ሆይ፣ ሁላችንም መሄድ የለብንም፤ ሸክም እንሆንብሃለን” ሲል መለሰለት። አቤሴሎም አጥብቆ ቢለምነውም ንጉሡ መሄድ አልፈለገም፤ ነገር ግን መርቆ አሰናበተው። አቤሴሎምም፣ “እንግዲያውስ ወንድሜ አምኖን ዐብሮን ይሂድ” አለው። ንጉሡም፣ “ዐብሯችሁ የሚሄደው ስለ ምንድን ነው?” ሲል ጠየቀው። ነገር ግን አቤሴሎም አጥብቆ ስለ ለመነው፣ አምኖንና ሌሎቹ የንጉሡ ወንዶች ልጆች ሁሉ ዐብረውት እንዲሄዱ አደረገ። አቤሴሎምም አገልጋዮቹን፣ “አምኖን የወይን ጠጅ ጠጥቶ መንፈሱ መለወጡን ተጠባበቁ፤ ከዚያም እኔ አምኖንን፣ ‘ምቱት’ ስላችሁ ግደሉት፤ ያዘዝኋችሁ እኔ ነኝ አትፍሩ፤ በርቱ፤ ጠንክሩ” ብሎ አዘዛቸው። የአቤሴሎምም አገልጋዮች ጌታቸው ያዘዛቸውን በአምኖን ላይ ፈጸሙ። ከዚያም የንጉሡ ልጆች በሙሉ ተነሥተው በየበቅሎዎቻቸው ላይ ተቀምጠው ሸሹ። እነርሱ በመንገድ ላይ ሳሉም፣ “አቤሴሎም የንጉሡን ልጆች በሙሉ ፈጃቸው፤ አንድም የተረፈ የለም” የሚል ወሬ ለዳዊት ደረሰው። ንጉሡም ተነሥቶ ቆመ፤ ልብሱን ቀደደ፤ በመሬትም ላይ ተዘረረ፤ በአጠገቡ ቆመው የነበሩት አገልጋዮቹም ሁሉ ልብሳቸውን ቀደዱ። የዳዊት ወንድም የሳምዓ ልጅ ኢዮናዳብ ግን እንዲህ አለ፤ “የንጉሡን ልጆች በሙሉ እንደ ፈጇቸው አድርጎ ጌታዬ አያስብ፤ እኅቱን ትዕማርን በግድ ካስነወራት ጊዜ አንሥቶ አቤሴሎም ቈርጦ የተነሣበት ጕዳይ ስለ ሆነ፣ የሞተው አምኖን ብቻ ነው። እንግዲህ የሞተው አምኖን ብቻ ስለ ሆነ፣ ‘የንጉሡ ልጆች በሙሉ ተገደሉ’ ተብሎ የተነገረውን ንጉሥ ጌታዬ ማመን የለበትም።” አቤሴሎምም ፈጥኖ ሸሸ። ለዘብ ጥበቃ የቆመውም ሰው ቀና ብሎ ሲመለከት፣ ከርሱ በስተ ምዕራብ ካለው መንገድ ብዙ ሰዎች በተራራው ጥግ ቍልቍል ሲወርዱ አየ፤ ዘብ ጠባቂውም ሄዶ ለንጉሡ፣ “ከበስተ ሖሮናይም አቅጣጫ በኰረብታው ጥግ ላይ ሰዎች ቍልቍል ሲወርዱ አያለሁ” ብሎ ነገረው። ኢዮናዳብም ዳዊትን፣ “እነሆ፣ የንጉሡ ልጆች መጥተዋል፤ አገልጋይህም እንዳለው ሆኗል” አለው። ገና ተናግሮ ሳይጨርስ፣ የንጉሡ ልጆች ጮኸው እየተላቀሱ ገቡ፤ እንደዚሁም ንጉሡና አገልጋዮቹ ሁሉ እጅግ አለቀሱ። አቤሴሎም ኰብልሎ የጌሹር ንጉሥ ወደ ሆነው ወደ ዓሚሁድ ልጅ ወደ ተልማይ ሄደ፤ ነገር ግን ዳዊት ስለ ሞተው ልጁ ዘወትር ያለቅስ ነበር። አቤሴሎም ሸሽቶ ወደ ጌሹር ከሄደ በኋላ፣ በዚያ ሦስት ዓመት ተቀመጠ። ንጉሥ ዳዊት በልጁ በአምኖን ሞት ከደረሰበት ሐዘን ከተጽናና በኋላ፣ ወደ አቤሴሎም ለመሄድ መንፈሱ ተነሣሣ።
2 ሳሙኤል 13:1-39 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ከዚህም በኋላ እንዲህ ሆነ፥ ለዳዊት ልጅ ለአቤሴሎም አንዲት የተዋበች እኅት ነበረችው፥ ስምዋም ትዕማር ነበረ፥ የዳዊት ልጅ አምኖን ወደዳት። አምኖንም ከእኅቱ ከትዕማር የተነሣ እጅግ ስለ ተከዘ ታመመ፥ ድንግልም ነበረችና አንዳች ያደርጋት ዘንድ በዓይኑ ፊት ጭንቅ ሆኖበት ነበር። ለአምኖንም የዳዊት ወንድም የሳምዓ ልጅ ኢዮናዳብ የሚባል ወዳጅ ነበረው፥ ኢዮናዳብም እጅግ ብልህ ሰው ነበረ። እርሱም፦ የንጉሥ ልጅ ሆይ፥ ስለ ምን ቀን በቀን እንዲህ ከሳህ? አትነግረኝምን? አለው። አምኖንም፦ የወንድሜን የአቤሴሎምን እኅት ትዕማርን እወድዳታለሁ አለው። ኢዮናዳብም፦ ታምሜአለሁ ብለህ በአልጋህ ላይ ተኛ፥ አባትህም ሊያይህ በመጣ ጊዜ፦ እኅቴ ትዕማር እንድትመጣና እኔ የምበላውን እንጀራ እንድትሰጠኝ፥ መብሉንም እኔ እያየሁ እንድታዘጋጅልኝ፥ ከእጅዋም እንድበላው እለምንሃለሁ በል አለው። እንዲሁም አምኖን፦ ታምሜአለሁ ብሎ ተኛ፥ ንጉሡም ሊያየው በመጣ ጊዜ አምኖን ንጉሡን፦ እኅቴ ትዕማር እንድትመጣና እኔ እያየሁ ሁለት እንጎቻ እንድታደርግልኝ፥ ከእጅዋም እንድበላ እለምንሃለሁ አለው። ዳዊትም፦ መብልን ታዘጋጂለት ዘንድ ወደ ወንድምሽ ወደ አምኖን ቤት ሂጂ ብሎ መልእክተኞችን ወደ ትዕማር ቤት ላከ። ትዕማርም ወደ ወንድምዋ ወደ አምኖን ቤት ሄደች፥ ተኝቶም ነበር፥ ዱቄትም ወስዳ ለወሰች፥ እያየም እንጎቻ አደረገች፥ ጋገረችም። ምጣዱንም ወስዳ በፊቱ ገለበጠች እርሱ ግን ይበላ ዘንድ እንቢ አለ። አምኖንም፦ ሰውን ሁሉ ከእኔ ዘንድ አስወጡ አለ፥ ሰውም ሁሉ ከእርሱ ዘንድ ወጣ። አምኖንም ትዕማርን፦ ከእጅሽ እበላ ዘንድ መብሉን ወደ እልፍኙ አግቢው አላት፥ ትዕማርም የሠራችውን እንጎቻ ወስዳ ወንድምዋ አምኖን ወዳለበት እልፍኝ አገባችው። መብሉንም ባቀረበች ጊዜ ያዛትና፦ እኅቴ ሆይ፥ ነዪ ከእኔም ጋር ተኚ አላት። እርስዋ መልሳ፦ ወንድሜ ሆይ፥ አይሆንም፥ እንዲህ ያለ ነገር በእስራኤል ዘንድ አይገባምና አታሳፍረኝ፥ ይህንም ነውረኛ ሥራ አታድርግ። እኔም ነውሬን ወዴት ልሸከም? አንተም በእስራኤል ዘንድ ከምናምንቴዎች እንደ አንዱ ትሆናለህ፥ እንግዲህስ ለንጉሡ ንገረው፥ እኔንም አይነሣህም አለችው። ቃልዋን ግን አልሰማም፥ ከእርስዋ ይልቅ ብርቱ ነበረና በግድ አስነወራት፥ ከእርስዋም ጋር ተኛ። ከዚያም በኋላ አምኖን ፈጽሞ ጠላት፥ አስቀድሞም ከወደዳት ውድ ይልቅ በኋላ የጠላት ጥል በለጠ። አምኖንም፦ ተነሥተሽ ሂጂ አላት። እርስዋም፦ አይሆንም፥ ቀድሞ ከሠራኸው ክፋት ይልቅ እኔን በማውጣትህ የበለጠ ክፋት ትሠራለህ አለችው፥ እርሱ ግን አልሰማትም። የሚያገለግለውንም ብላቴና ጠርቶ፦ ይህችን ሴት ከፊቴ አስወጥተህ በሩን ዝጋባት አለው። ብዙ ኅብር ያለውንም ልብስ ለብሳ ነበር፥ እንዲህ ያለውን ልብስ የንጉሡ ልጆች ደናግሉ ይለብሱ ነበርና፥ አገልጋዩም አስወጥቶ በሩን ዘጋባት። ትዕማርም በራስዋ ላይ አመድ ነስንሳ፥ ብዙ ኅብርም ያለውን ልብስዋን ተርትራ፥ እጅዋንም በራስዋ ላይ ጭና እየጮኸች ሄደች። ወንድምዋም አቤሴሎም፦ ወንድምሽ አምኖን ከአንቺ ጋር ነበረን? እኅቴ ሆይ፥ አሁን ግን ዝም በዪ፥ ወንድምሽ ነው፥ ይህን ነገር በልብሽ አትያዢው አላት። ትዕማርም በወንድምዋ በአቤሴሎም ቤት ብቻዋን ተቀመጠች። ንጉሡም ዳዊት ይህን ነገር ሁሉ በሰማ ጊዜ እጅግ ተቆጣ፥ ነገር ግን የበኵር ልጁ ነበረና ስለ ወደደው የልጁን የአምኖን ነፍስ አላሳዘነም። አቤሴሎምም እኅቱን ትዕማርን ስላሳፈራት አምኖንን ጠልቶታልና አቤሴሎም አምኖንን ክፉም ሆነ መልካምም አልተናገረውም። ከሁለት ዓመትም በኋላ አቤሴሎም በኤፍሬም አቅራቢያ ባለችው በቤላሶር በጎቹን አሸለተ፥ አቤሴሎምም የንጉሡን ልጆች ሁሉ ጠራ። አቤሴሎምም ወደ ንጉሡ መጥቶ፦ እነሆ፥ ባሪያህ በጎቹን ያሸልታል፥ ንጉሡና ሎሌዎቹ ከባሪያህ ጋር ይሂዱ አለው። ንጉሡም አቤሴሎምን፥ ልጄ ሆይ፥ እንከብድብሃለንና ሁላችን እንመጣ ዘንድ አይሆንም አለው። የግድም አለው፥ እርሱ ግን መረቀው እንጂ ለመሄድ እንቢ አለ። አቤሴሎምም አንተ እንቢ ካልህ ወንድሜ አምኖን ከእኛ ጋር እንዲሄድ እለምንሃለሁ አለ። ንጉሡም፦ ከአንተ ጋር ለምን ይሄዳል? አለው። አቤሴሎምም የግድ አለው፥ አምኖንንና የንጉሡንም ልጆች ሁሉ ከእርሱ ጋር ሰደደ። አቤሴሎምም እንደ ንጉሥ ግብዣ ያለ ግብዣ አደረገ፥ አቤሴሎምም አገልጋዮቹን፦ አምኖን የወይን ጠጅ ጠጥቶ ልቡን ደስ ባለው ጊዜ እዩ፦ አምኖንን ግደሉ ባልኋችሁም ጊዜ ግደሉት፥ አትፍሩም፥ ያዘዝኋችሁም እኔ ነኝና በርቱ ጽኑም ብሎ አዘዛቸው። የአቤሴሎምም አገልጋዮች አቤሴሎም እንዳዘዛቸው በአምኖን ላይ አደረጉበት። የንጉሡም ልጆች ሁሉ ተነሥተው በየበቅሎቻቸው ተቀምጠው ሸሹ። ገናም በመንገድ ሲሄዱ ለዳዊት፦ አቤሴሎም የንጉሡን ልጆች ሁሉ ገድሎአል፥ ከእነርሱም አንድ አልቀረም የሚል ወሬ መጣለት። ንጉሡም ተነሥቶ ልብሱን ቀደደ፥ በምድር ላይም ወደቀ፥ ባሪያዎቹም ሁሉ ልብሳቸውን ቀድደው በአጠገቡ ቆሙ። የዳዊትም ወንድም የሳምዓ ልጅ ኢዮናዳብ፦ ጌታዬ ጕልማሶቹ የንጉሡ ልጆች ሁሉ እንደ ሞቱ አያስብ፥ እኅቱን ትዕማርን በግድ ካስነወራት ጀምሮ በአቤሴሎም ዘንድ የተቆረጠ ነገር ነበረና የሞተ አምኖን ብቻ ነው። አሁንም የሞተ ብቻ ነው እንጂ የንጉሥ ልጆች ሁሉ ሞቱ ብሎ ጌታዬ ንጉሡ ይህን ነገር በልቡ አያኑር አለው። አቤሴሎምም ኮበለለ። ጕበኛውም ጕልማሳ ዓይኑን ከፍ አደረገ፥ እነሆም፥ ብዙ ሰዎች በኋላው በተራራው አጠገብ በመንገድ ሲመጡ አየ። ኢዮናዳብም ንጉሡን፦ እነሆ፥ የንጉሡ ልጆች መጥተዋል፥ ባሪያህ እንዳለው እንዲሁ ሆኖአል አለው። ተናግሮም በጨረሰ ጊዜ፥ እነሆ፥ ወዲያው የንጉሥ ልጆች ገቡ፥ ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው አለቀሱ፥ ደግሞ ንጉሡና ባሪያዎቹ ሁሉ እጅግ ታላቅ ልቅሶ አለቀሱ። አቤሴሎም ግን ኮብልሎ ወደ ጌሹር ንጉሥ ወደ ዓሚሁድ ልጅ ወደ ተልማይ ሄደ። ዳዊትም ሁልጊዜ ለልጁ ያለቅስ ነበር። አቤሴሎም ኮብልሎ ወደ ጌሹር ሄደ፥ በዚያም ሦስት ዓመት ያህል ተቀመጠ። ንጉሡም ዳዊት ስለ አምኖን ሞት ተጽናንቶ ወደ አቤሴሎም ይሄድ ዘንድ እጅግ ናፈቀ።
2 ሳሙኤል 13:1-39 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
የዳዊት ልጅ አቤሴሎም ውብ የሆነች ትዕማር ተብላ የምትጠራ፥ ገና ባል ያላገባች እኅት ነበረችው፤ አምኖን ተብሎ የሚጠራው ከዳዊት ልጆች አንዱ ትዕማርን ወደዳት፤ እርስዋንም እጅግ ከማፍቀሩ የተነሣ ታመመ፤ ድንግል ስለ ነበረች እርስዋን መገናኘት ከቶ አልተቻለውም። ነገር ግን በጣም ዘዴኛ የሆነ፥ ዮናዳብ ተብሎ የሚጠራ ወዳጅ ነበረው፤ እርሱም የዳዊት ወንድም የሻማ ልጅ ነበር፤ ዮናዳብ አምኖንን “አንተ የንጉሥ ልጅ ሆነህ ሳለ በየቀኑ ሰውነትህ ጠውልጎ የማይህ ስለምንድን ነው? እስቲ ንገረኝ” ሲል ጠየቀው። አምኖንም “የወንድሜን የአቤሴሎምን እኅት ትዕማርን ስለ ወደድኩ ነው” ሲል መለሰለት። ዮናዳብም እንዲህ አለው፤ “ይህ ከሆነ እንግዲህ የታመምህ መስለህ አልጋህ ላይ ተኛ፤ አባትህ ሊጠይቅህ ሲመጣ፥ ‘እኅቴ ትዕማርን መጥታ እንድታስታምመኝ እባክህ ንገራት፤ እዚህ በአጠገቤ እያየኋት ምግብ አዘጋጅታ እርስዋ ራስዋ እንድታጐርሰኝ እፈልጋለሁ’ በለው።” ስለዚህም አምኖን የታመመ በመምሰል በአልጋው ላይ ተኛ። ንጉሥ ዳዊትም ሊጠይቀው ወደ እርሱ በሄደ ጊዜ አምኖን “እኅቴ ትዕማር እዚህ በአጠገቤ እያየኋት ሁለት እንጀራ ጋግራ እርስዋ ራስዋ እንድታቀርብልኝ ፍቀድላት” አለው። ስለዚህም ዳዊት በቤተ መንግሥት ለምትገኘው ለትዕማር “ወደ ወንድምሽ ወደ አምኖን ቤት ሄደሽ ምግብ አዘጋጂለት” የሚል ትእዛዝ ላከ። እርስዋም ወደ ወንድምዋ ወደ አምኖን ቤት በሄደች ጊዜ አልጋ ላይ ተኝቶ አገኘችው፤ ጥቂት ሊጥ ወስዳ በማቅጠንም አምኖን እያያት እንጀራ ጋገረች፤ የጋገረችውንም እንጀራ ከምጣዱ አውጥታ እንዲበላ አቀረበችለት፤ እርሱ ግን መመገቡን እምቢ ብሎ “ሰዎቹን ሁሉ አስወጡልኝ” አለ፤ ሁሉም ወጡ፤ ከዚያም በኋላ አምኖን ትዕማርን “ታጐርሺኝ ዘንድ ምግቡን ይዘሽ ወደ አልጋዬ አምጪው” አላት፤ ስለዚህም ትዕማር ምግቡን ወደ ወንድምዋ ወደ አምኖን አመጣችው። በምታቀርብለትም ጊዜ አፈፍ በማድረግ ይዞ “እኅቴ ሆይ! አብረን እንተኛ!” አላት። እርስዋም “አይሆንም ወንድሜ ሆይ! እባክህ አታዋርደኝ! የዚህ ዐይነቱ አሳፋሪ ተግባር በእስራኤል ተፈጽሞ አያውቅም! ስለዚህ ይህን ትልቅ ብልግና አትፈጽም፤ እንደዚህ ካዋረድከኝ በኋላ በሕዝብ ፊት ራሴን ቀና አድርጌ ለመሄድ እንዴት እችላለሁ? አንተም ብትሆን በእስራኤል እጅግ የተዋረድክ ትሆናለህ፤ ይልቅስ ለንጉሡ ብትነግረው እኔን ለአንተ በሚስትነት እንደሚሰጥህ እርግጠኛ ነኝ” አለችው። እርሱ ግን ሊያዳምጣት አልፈቀደም፤ እርሱም ከእርስዋ ይልቅ ብርቱ ስለ ነበረ በኀይል አስገድዶ ክብረ ንጽሕናዋን ደፈረ። ከዚያም በኋላ አምኖን እጅግ አድርጎ ጠላት፤ እንዲያውም ቀድሞ ካፈቀራት ይበልጥ አሁን በእርስዋ ላይ ያለው ጥላቻ ስለ ባሰ “ከዚህ ውጪልኝ!” አላት። እርስዋም “አይሆንም! እኔን እንደዚህ አድርገህ ብታባርረኝ አሁን ከፈጸምከው በደል ይልቅ የከፋ ኃጢአት ትፈጽማለህ!” አለችው። አምኖን ግን ሊያዳምጣት አልፈቀደም፤ የግል አገልጋዩንም ጠርቶ “ይህችን ሴት ከፊቴ ወዲያ አስወግድልኝ! እርስዋንም ወደ ውጪ አስወጥተህ በሩን ዝጋ!” አለው። ትዕማርም የአምኖን አሽከር ከቤት አስወጥቶ በሩን ዘጋባት፤ በዚያን ዘመን ያላገቡ የነገሥታት ልጆች ይለብሱት የነበረውን እጅጌ ረዥም የነበረ መጐናጸፊያ ለብሳ ነበር፤ እርስዋም በራስዋ ላይ አመድ ነስንሳ ለብሳው የነበረውን መጐናጸፊያ ቀዳ እጅዋን በራስዋ ላይ በመጫን ድምፅዋን ከፍ አድርጋ እያለቀሰች ሄደች። ወንድምዋ አቤሴሎም ባያት ጊዜ “እኅቴ ሆይ! ወንድምሽ አምኖን አስነወረሽን? እባክሽ እንደዚህ አትበሳጪ፤ እርሱ ወንድምሽ ስለ ሆነ ለማንም አትናገሪ” አላት። ስለዚህ ትዕማር በወንድሟ በአቤሴሎም ቤት ከሰው የተለየች ብቸኛ ሆና ተቀመጠች። ንጉሥ ዳዊት የሆነውን ነገር በሰማ ጊዜ በብርቱ ተቈጣ፤ [ነገር ግን ይወደው ስለ ነበርና የበኲር ልጁም ስለ ነበረ ልጁን አምኖንን ሊያሳዝነው አልፈለገም።] የእኅቱን የትዕማርን ክብረ ንጽሕና በመድፈሩም ምክንያት አቤሴሎም አምኖንን እጅግ ጠላው፤ ዳግመኛም ክፉም ሆነ ደግ ሊያነጋግረው አልፈለገም። ከሁለት ዓመት በኋላ አቤሴሎም በኤፍሬም ከተማ አጠገብ በዓለ ሐጾር ተብሎ በሚጠራው ስፍራ በጎቹን ይሸልት ነበር፤ ስለዚህም የንጉሡን ወንዶች ልጆች ሁሉ ለግብዣ ወደዚያ ጠራ። ወደ ንጉሥ ዳዊትም ሄዶ “ንጉሥ ሆይ! በጎቼን እየሸለትሁ ነው፤ ስለዚህ አንተና መኳንንትህ መጥታችሁ የግብዣው ተካፋዮች እንድትሆኑልኝ ትፈቅዳለህን?” አለው። ንጉሡም “ልጄ ሆይ! መምጣት አያስፈልገንም፤ እኛ ሁላችን ከመጣን መስተንግዶው ይከብድብሃል” ሲል መለሰለት፤ አቤሴሎምም አጥብቆ ጠየቀ፤ ንጉሡ ግን አሳቡን መለወጥ ስላልፈቀደ አቤሴሎምን መርቆ አሰናበተው። አቤሴሎም ግን “መልካም ነው! አንተ መምጣት ካልፈቀድህ ወንድሜ አምኖን እንዲመጣ አትፈቅድለትምን?” ሲል ጠየቀ። ንጉሡም “እርሱስ ቢሆን ለምን ይመጣል?” ሲል ጠየቀው። አቤሴሎም አጥብቆ ስለ ጠየቀ ዳዊት፥ አምኖንና የቀሩትም ወንዶች ልጆቹ ሁሉ እንዲሄዱ ፈቀደ። አቤሴሎም ለንጉሥ የሚገባ ግብዣ አዘጋጅቶ ነበር፤ አገልጋዮቹንም “አምኖን ብዙ ጠጥቶ መስከሩን ተመልከቱ፤ እኔም ትእዛዝ በምሰጣችሁ ጊዜ ግደሉት፤ ይህን ትእዛዝ የሰጠኋችሁ እኔ ስለ ሆንኩ ከቶ አትፍሩ! ደፋሮች ሁኑ፤ ምንም አታመንቱ!” አላቸው። ስለዚህ አገልጋዮቹ አቤሴሎም በነገራቸው መመሪያ መሠረት አምኖንን ገደሉ፤ የቀሩትም የዳዊት ወንዶች ልጆች በበቅሎዎቻቸው ተቀምጠው እየጋለቡ ሸሹ። ወደ ቤታቸው ለመድረስ ገና በመንገድ ላይ ሳሉ “አቤሴሎም ልጆችህን ሁሉ ገደላቸው! አንድ እንኳ የቀረ የለም!” የሚል ወሬ ለዳዊት ደረሰው። ንጉሡ ከተቀመጠበት በመነሣት በሐዘን ልብሱን ቀዶ በመሬት ላይ ተዘረረ፤ በዚያ ከእርሱ ጋር የነበሩ አገልጋዮቹም በሐዘን ልብሳቸውን ቀደው በአጠገቡ በአክብሮት ቆሙ። የዳዊት ወንድም የሻማ ልጅ ዮናዳብ ግን እንዲህ አለ፤ “ጌታዬ ሆይ! የተገደሉት ልዑላኑ በሙሉ አይደሉም፤ የተገደለው አምኖን ብቻ ነው፤ አቤሴሎም ይህን ለማድረግ ያቀደው አምኖን የእኅቱን የትዕማርን ክብረ ንጽሕና ከደፈረበት ጊዜ አንሥቶ እንደ ነበር ፊቱን አይተህ መረዳት ትችላለህ። አሁንም ልዑላን በሙሉ እንደ ተገደሉ ሆኖ የተነገረህን ወሬ አትመን። የተገደለው አምኖን ብቻ ነው።” በዚህም ጊዜ አቤሴሎም ሸሽቶ አምልጦ ነበር፤ ለዘብ ጥበቃ ተረኛ የነበረውም ወታደር ልክ በዚያን ሰዓት ከሖርናይም ወደዚህ በሚመጣው መንገድ ላይ ካለው ኮረብታ ብዙ ሕዝብ ወደ ታች ሲወርድ አየ፤ ወደ ንጉሡም ቀርቦ ያየውን ሁሉ ተናገረ፤ ዮናዳብም ዳዊትን “ልክ እኔ አገልጋይህ እንዳልኩት እነሆ፥ የንጉሡ ልጆች መጥተዋል፤” አለው። እርሱ ይህን ተናግሮ እንዳበቃ የዳዊት ልጆች ገብተው መላቀስ ጀመሩ፤ ዳዊትና መኳንንቱም በመረረ ሁኔታ አለቀሱ። አቤሴሎምም ሸሽቶ የገሹር ንጉሥ ወደ ሆነው ወደ ዓሚሁድ ልጅ ወደ ታልማይ ሄደ፤ በዚያም ሦስት ዓመት ቈየ፤ ዳዊት ስለ ልጁ ስለ አምኖን ሞት ለረዥም ጊዜ በማዘን አለቀሰ፤ ነገር ግን ስለ አምኖን ሞት የነበረበት ሐዘን እየተረሳ በሄደ ቊጥር ልጁን አቤሴሎምን መናፈቅ ጀመረ።
2 ሳሙኤል 13:1-39 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
የዳዊት ልጅ አቤሴሎም ትዕማር የምትባል ቆንጆ እኅት ነበረችው፤ የዳዊት ልጅ አምኖንም ወደዳት። እኅቱን ትዕማርን ያፈቀረው አምኖን እስኪታመም ድረስ እጅግ ተሰቃየ፤ ድንግል ነበረችና አንዳች ነገር እንዳያደርግባት የማይታሰብ ሆኖበት አስጨነቀው። ነገር ግን አምኖን በጣም ዘዴኛ የሆነ፥ ዮናዳብ ተብሎ የሚጠራ ወዳጅ ነበረው፤ እርሱም የዳዊት ወንድም የሻማ ልጅ ነበር፤ እርሱም አምኖንን፥ “የንጉሥ ልጅ ሆይ፤ ሰውነትህ ቀን በቀን የሚከሳው ለምንድነው? ለምን አትነግረኝም?” ሲል ጠየቀው። አምኖንም፥ “የወንድሜን የአቤሴሎምን እኅት ትዕማርን አፍቅሬ ነው” አለው። ዮናዳብም፥ “እንግዲያው የታመምህ መስለህ አልጋ ላይ ተኛ፤ አባትህ ሊጠይቅህ ሲመጣም፥ ‘እኅቴ ትዕማር መጥታ የምበላውን ነገር ትስጠኝ፤ እዚህ በአጠገቤ እያየኋት ምግብ አዘጋጅታ እርሷ ራስዋ እንድታጐርሰኝ እፈልጋለሁ’ በለው” አለው። ስለዚህ አምኖን የታመመ ሰው መስሎ ተኛ፤ ንጉሡም ሊጠይቀው መጣ፤ አምኖንም፥ “እኅቴ ትዕማር መጥታ፥ እያየሁ ሁለት እንጀራ ጋግራ በእጇ እንድታጐርሰኝ እለምንሃለሁ” ብሎ ጠየቀው። ከዚያም ዳዊት፥ “ወንድምሽ አምኖን ቤት ሄደሽ ምግብ እንድታዘጋጂለት” የሚል ትእዛዝ ለትዕማር ላከ። ስለዚህም ትዕማር ወንድሟ አምኖን ወደ ተኛበት ቤት ሄደች፤ ጥቂት ሊጥ ወስዳ ካቦካች በኋላ እያየ ጋገረችው፤ ከዚያም መጋገሪያውን አውጥታ እንጀራውን አቀረበችለት፤ እርሱ ግን መብላት አልፈለገም። አምኖንም፥ “ሰውን ሁሉ ከዚህ አስወጡልኝ” አለ፤ ሰውም ሁሉ ትቶት ወጣ። ከዚያም አምኖን ትዕማርን፥ “እንድታጐርሺኝ ምግቡን እዚሁ መኝታ ክፍሌ አምጪልኝ” አላት። ትዕማርም ያዘጋጀችውን እንጀራ ይዛ ወንድሟ አምኖን ወዳለበት መኝታ ክፍል ገባች። ነገር ግን ምግቡን ስታቀርብለት አፈፍ አድርጎ ያዛትና፥ “እህቴ ነዪ አብረን እንተኛ” አላት። እርሷም እንዲህ አለችው፤ “አይሆንም፥ ወንድሜ፥ ተው አታስገድደኝ፤ እንዲህ ያለው ነገር በእስራኤል ተደርጎ አያውቅም፤ ይህን አስነዋሪ ድርጊት አትፈጽም። እኔስ እንዴት እሆናለሁ? ነውሬንስ ተሸክሜ የት እገባለሁ? አንተም ብትሆን በእስራኤል ከወራዳዎቹ እንደ አንዱ ትቆጠራለህ፤ እባክህ ለንጉሡ ጠይቀው፤ እኔንም አይከለክልህም።” እርሱ ግን ሊሰማት አልፈለገም፤ ከእርሷ ይልቅ ብርቱ ስለ ነበር፥ በግድ አስገድዶ ደፈራት። ከዚያም በኋላ አምኖን ፈጽሞ ጠላት፥ አስቀድሞም ሲወዳት ከነበረው ፍቅሩ ይልቅ በኋላ የጠላት ጥላቻ አየለ። አምኖንም፥ “ተነሽ ውጭልኝ!” አላት። እርሷም፥ “ይህ አይሆንም! እኔን አስወጥቶ መስደድ፥ አስቀድመህ ካደረስህብኝ በደል የባሰ መፈጸምህ ነው” አለችው። እርሱ ግን ሊሰማት አልፈቀደም፤ ወጣት አገልጋዩንም ጠርቶ፥ “ይህቺን ሴት ከፊቴ አስወጣና በሩን ዝጋባት” አለው። ስለዚህም አገልጋዩ አስወጥቶ በሩን ዘጋባት፤ በዚያን ጊዜ ድንግል የሆኑት የንጉሥ ልጆች የሚለብሱትን እጅጌ ረዥም የነበረ መጐናጸፊያ ለብሳ ነበር። ትዕማርም በራሷ ላይ ዐመድ ነስንሳ፤ ለብሳው የነበረውን መጐናጸፊያ ቀዳደደች፤ እጇንም በራሷ ላይ አድርጋ እያለቀሰች ሄደች። ወንድሟ አቤሴሎምም፥ “ወንድምሽ አምኖን ከአንቺ ጋር ነበርን? እኅቴ ሆይ፥ በይ አሁን ዝም በዪ፤ ወንድምሽ ስለሆነ፥ ነገሩን በልብሽ አትያዠው” አላት። ትዕማርም በወንድሟ በአቤሴሎም ቤት ብቸኛ ሴት ሆና ኖረች። ንጉሥ ዳዊት ይህን ሁሉ በሰማ ጊዜ እጅግ ተቆጣ፤ አቤሴሎም ግን አምኖን እኅቱን ትዕማርን ስለደፈራት፥ ከጥላቻው የተነሣ አምኖንን ክፉም ሆነ ደግ አንዳች ቃል አልተናገረውም። ከሁለት ዓመት በኋላ አቤሴሎም በኤፍሬም አቅራቢያ ባለችው በበዓለ ሐጾር ከተማ በጎቹን ይሸልት ነበር፤ ከዚያም የንጉሡን ወንዶች ልጆች ሁሉ በዚያ እንዲገኙለት አቤሴሎም ጋበዛቸው። ወደ ንጉሡም ሄዶ፥ “እነሆ፤ አገልጋይህ በጎቹን ይሸልታል፤ ንጉሡና ሹማምንቱ ፈቃዳቸው ሆኖ እባክህ ይገኙልኝ?” ሲል ጠየቀው። ንጉሡም አቤሴሎምን፥ “ልጄ ሆይ፥ ሸክም ስለምናበዛብህ ሁላችንም መሄድ የለብንም” ሲል መለሰለት። አቤሴሎም አጥብቆ ቢለምነውም ንጉሡ መሄድ አልፈለገም፤ ነገር ግን መርቆ አሰናበተው። ከዚያም አቤሴሎም፥ “እምቢ ካልህ እሽ ወንድሜ አምኖን አብሮን ይሂድ” አለው። ንጉሡም፥ “አብሮህ የሚሄደው ለምንድን ነው?” ሲል ጠየቀው። ነገር ግን አቤሴሎም አጥብቆ ስለ ለመነው፥ አምኖንና የንጉሡ ወንዶች ልጆች ሁሉ አብረውት እንዲሄዱ አደረገ። ከዚያም አቤሴሎም አገልጋዮቹን፥ “አምኖን የወይን ጠጅ ጠጥቶ መንፈሱ መለወጡን ተጠባበቁ፤ እኔ ‘አምኖንን፥ ምቱት’ በምላችሁ ጊዜ ግደሉት፤ ያዘዝኋችሁ እኔው ስለሆንኩ አትፍሩ፤ ብርቱዎች ሁኑ፥ ጨከን በሉም” ብሎ አዘዛቸው። የአቤሴሎምም አገልጋዮች በአምኖን ላይ አቤሴሎም ያዘዛቸውን ፈጸሙ። ከዚያም የንጉሡ ልጆች በሙሉ ተነሥተው በየበቅሎዎቻቸው ላይ ተቀምጠው ሸሹ። እነርሱ በመንገድ ላይ ሳሉም፥ “አቤሴሎም የንጉሡን ልጆች በሙሉ ፈጃቸው፤ አንድም የተረፈ የለም” የሚል ወሬ ለዳዊት ደረሰው። ንጉሡም ከተቀመጠበት ተነሥቶ ልብሱን ቀደደ፤ በመሬትም ላይ ተዘረረ፤ በአጠገቡ ቆመው የነበሩት አገልጋዮቹም ሁሉ ልብሳቸውን ቀደዱ። የዳዊት ወንድም የሻምዓ ልጅ ዮናዳብ ግን እንዲህ አለ፤ “የተገደሉት የንጉሡ ልጆች በሙሉ እንደ ሆኑ አድርጎ ጌታዬ አያስብ፤ የሞተው አምኖን ብቻ ነው። አምኖን እኅቱን ትዕማርን በግድ ከደፈራት ጊዜ አንሥቶ አቤሴሎም ይህን ጉዳይ ቆርጦ የተነሣበት ነበር። አሁንም የሞተው አምኖን ብቻ ስለሆነ፥ የንጉሡ ልጆች በሙሉ እንደተገደሉ አድርጎ ንጉሥ ጌታዬ በልቡ ማሰብ የለበትም።” አቤሴሎምም ፈጥኖ ሸሸ። ለዘብ ጥበቃ የቆመውም ሰው ቀና ብሎ ተመለከተ፤ እነሆም፥ በኋላው ብዙ ሰዎች በተራራው ጥግ ሲመጡ አየ። ዮናዳብም ለንጉሡ፥ “እነሆ፥ የንጉሡ ልጆች መጥተዋል፤ አገልጋይህም እንዳለው ሆኖአል” አለው። እርሱም ተናግሮ እንዳበቃ፥ የንጉሡ ልጆች ጮኸው እየተላቀሱ ገቡ፤ እንደዚሁም ንጉሡና አገልጋዮቹ ሁሉ አምርረው አለቀሱ። አቤሴሎም ግን ኰብልሎ የገሹር ንጉሥ ወደ ሆነው ወደ ዓሚሁድ ልጅ ወደ ታልማይ ሄደ፤ ዳዊትም ዘወትር ስለ ልጁ ያለቅስ ነበር። አቤሴሎም ሸሽቶ ወደ ገሹር ከሄደ በኋላ፥ በዚያ ሦስት ዓመት ተቀመጠ። ንጉሥ ዳዊትም በልጁ ሞት ከደረሰበት ኀዘን ተጽናና፤ ከዚያም መንፈሱ ወደ አቤሴሎም ለመሄድ ናፈቀ።