2 ጴጥሮስ 3:3-16
2 ጴጥሮስ 3:3-16 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በመጨረሻው ዘመን እንደ ራሳቸው ምኞት የሚመላለሱ ዘባቾች በመዘበት እንዲመጡ ይህን በፊት እወቁ፤ እነርሱም “የመምጣቱ የተስፋ ቃል ወዴት ነው? አባቶች ከሞቱባት ጊዜ ከፍጥረት መጀመሪያ ይዞ ሁሉ እንዳለ ይኖራልና፤” ይላሉ። ሰማያት ከጥንት ጀምረው ምድርም በእግዚአብሔር ቃል ከውሃ ተጋጥማ በውሃ መካከል እንደ ነበሩ ወደው አያስተውሉምና፤ በዚህም ምክንያት ያን ጊዜ የነበረ ዓለም በውሃ ሰጥሞ ጠፋ፤ አሁን ያሉ ሰማያትና ምድር ግን እግዚአብሔርን የማያመልኩት ሰዎች እስከሚጠፉበት እስከ ፍርድ ቀን ድረስ ተጠብቀው በዚያ ቃል ለእሳት ቀርተዋል። እናንተ ግን ወዳጆች ሆይ! በጌታ ዘንድ አንድ ቀን እንደ ሺህ ዓመት፥ ሺህ ዓመትም እንደ አንድ ቀን እንደ ሆነ ይህን አንድ ነገር አትርሱ። ለአንዳንዶች የሚዘገይ እንደሚመስላቸው ጌታ ስለ ተስፋ ቃሉ አይዘገይም፤ ነገር ግን ሁሉ ወደ ንስሓ እንዲደርሱ እንጂ ማንም እንዳይጠፋ ወዶ ስለ እናንተ ይታገሣል። የጌታው ቀን ግን እንደ ሌባ ሆኖ ይመጣል፤ በዚያም ቀን ሰማያት በታላቅ ድምፅ ያልፋሉ፤ የሰማይም ፍጥረት በትልቅ ትኵሳት ይቀልጣል፤ ምድርም በእርስዋም ላይ የተደረገው ሁሉ ይቃጠላል። ይህ ሁሉ እንዲህ የሚቀልጥ ከሆነ፥ የእግዚአብሔርን ቀን መምጣት እየጠበቃችሁና እያስቸኰላችሁ በቅዱስ ኑሮ እግዚአብሔርንም በመምሰል እንደ ምን ልትሆኑ ይገባችኋል? ስለዚያ ቀን ሰማያት ተቃጥለው ይቀልጣሉ፤ የሰማይም ፍጥረት በትልቅ ትኵሳት ይፈታል፤ ነገር ግን ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደ ተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን። ስለዚህ ወዳጆች ሆይ! ይህን እየጠበቃችሁ ያለ ነውርና ያለ ነቀፋ ሆናችሁ በሰላም በእርሱ እንድትገኙ ትጉ፤ የጌታችንም ትዕግሥት መዳናችሁ እንደ ሆነ ቍጠሩ። እንዲህም የተወደደው ወንድማችን ጳውሎስ ደግሞ እንደ ተሰጠው ጥበብ መጠን ጻፈላችሁ፤ በመልእክቱም ሁሉ ደግሞ እንደ ነገረ ስለዚህ ነገር ተናገረ። በእነዚያ ዘንድ ለማስተዋል የሚያስቸግር ነገር አለ፤ ያልተማሩትና የማይጸኑትም ሰዎች ሌሎችን መጻሕፍት እንደሚያጣምሙ እነዚህን ደግሞ ለገዛ ጥፋታቸው ያጣምማሉ።
2 ጴጥሮስ 3:3-16 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከሁሉ አስቀድሞ ይህን ዕወቁ፤ በመጨረሻው ዘመን የራሳቸውን ክፉ ምኞቶቻቸውን የሚከተሉ ዘባቾች እየዘበቱ ይመጣሉ። እነርሱም፣ “ ‘እመጣለሁ’ ያለው ታዲያ የት አለ? አባቶች ከሞቱበት ከፍጥረት መጀመሪያ አንሥቶ እስካሁን ድረስ ሁሉም ነገር እንዳለ ይኖራል” ይላሉ። ነገር ግን እነዚህ ሰዎች ሰማያት ከጥንት ጀምሮ በእግዚአብሔር ቃል ተፈጥረው እንደሚኖሩ፣ መሬትም በውሃ መካከልና በውሃም እንደ ተሠራች ሆነ ብለው ይክዳሉ፤ በዚያ ጊዜ የነበረው ዓለም በውሃ ተጥለቅልቆ ጠፋ። በዚያው ቃል ደግሞ አሁን ያሉት ሰማያትና ምድር፣ ኀጢአተኞች እስከሚጠፉበት እስከ ፍርድ ቀን ድረስ ለእሳት ተጠብቀዋል። ወዳጆች ሆይ፤ በጌታ ዘንድ አንድ ቀን እንደ ሺሕ ዓመት፣ ሺሕ ዓመትም እንደ አንድ ቀን መሆኑን ይህን አንድ ነገር አትርሱ። አንዳንድ ሰዎች የዘገየ እንደሚመስላቸው ጌታ የተስፋ ቃሉን ለመፈጸም አይዘገይም፤ ነገር ግን ማንም እንዳይጠፋ ፈልጎ፣ ሁሉ ለንስሓ እንዲበቃ ስለ እናንተ ይታገሣል። የጌታ ቀን ግን እንደ ሌባ ይመጣል፤ በዚያች ቀን ሰማያት በታላቅ ድምፅ ያልፋሉ፤ ፍጥረትም በታላቅ ግለት ይጠፋል፤ ምድርና በርሷም ላይ ያለ ነገር ሁሉ ወና ይሆናል። እንግዲህ ሁሉም ነገር በዚህ ሁኔታ የሚጠፋ ከሆነ፣ እናንተ እንዴት ዐይነት ሰዎች ልትሆኑ ይገባችኋል? አዎን፣ በቅድስናና በእውነተኛ መንፈሳዊነት ልትኖሩ ይገባችኋል፤ ደግሞም የእግዚአብሔርን ቀን እየተጠባበቃችሁ መምጫውን ልታፋጥኑ ይገባል። በዚያ ቀን ሰማያት በእሳት ተቃጥለው ይጠፋሉ፤ የሰማይም ፍጥረት በታላቅ ትኵሳት ይቀልጣል። እኛ ግን ጽድቅ የሚኖርበትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር በተስፋ ቃሉ መሠረት እንጠባበቃለን። ስለዚህ ወዳጆች ሆይ፤ እነዚህን ሁሉ ነገሮች የምትጠባበቁ ስለ ሆናችሁ፣ ያለ ነውርና ያለ ነቀፋ ከርሱ ጋራ በሰላም እንድትገኙ ትጉ። የጌታችን ትዕግሥት እናንተ እንድትድኑ እንደ ሆነ አስቡ፤ እንዲሁም የተወደደው ወንድማችን ጳውሎስ እንደ ተሰጠው ጥበብ መጠን ጻፈላችሁ። እርሱ ስለ እነዚህ ነገሮች በመልእክቶቹ ሁሉ ጽፏል፤ በመልእክቶቹም ውስጥ በቀላሉ ለመረዳት የሚያዳግቱ ነገሮች አሉ። ዕውቀት የጐደላቸውና ጽናት የሌላቸው ሰዎች ሌሎችን ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሚያጣምሙ፣ እነዚህንም ደግሞ ለገዛ ጥፋታቸው ያጣምማሉ።
2 ጴጥሮስ 3:3-16 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በመጨረሻው ዘመን እንደ ራሳቸው ምኞት የሚመላለሱ ዘባቾች በመዘበት እንዲመጡ ይህን በፊት እወቁ፤ እነርሱም፦ የመምጣቱ የተስፋ ቃል ወዴት ነው? አባቶች ከሞቱባት ጊዜ፥ ከፍጥረት መጀመሪያ ይዞ ሁሉ እንዳለ ይኖራልና ይላሉ። ሰማያት ከጥንት ጀምረው ምድርም በእግዚአብሔር ቃል ከውኃ ተጋጥማ በውኃ መካከል እንደ ነበሩ ወደው አያስተውሉምና፤ በዚህም ምክንያት ያን ጊዜ የነበረ ዓለም በውኃ ሰጥሞ ጠፋ፤ አሁን ያሉ ሰማያትና ምድር ግን እግዚአብሔርን የማያመልኩት ሰዎች እስከሚጠፉበት እስከ ፍርድ ቀን ድረስ ተጠብቀው በዚያ ቃል ለእሳት ቀርተዋል። እናንተ ግን ወዳጆች ሆይ፥ በጌታ ዘንድ አንድ ቀን እንደ ሺህ ዓመት፥ ሺህ ዓመትም እንደ አንድ ቀን እንደ ሆነ ይህን አንድ ነገር አትርሱ። ለአንዳንዶች የሚዘገይ እንደሚመስላቸው ጌታ ስለ ተስፋ ቃሉ አይዘገይም፥ ነገር ግን ሁሉ ወደ ንስሐ እንዲደርሱ እንጂ ማንም እንዳይጠፋ ወዶ ስለ እናንተ ይታገሣል። የጌታው ቀን ግን እንደ ሌባ ሆኖ ይመጣል፤ በዚያም ቀን ሰማያት በታላቅ ድምፅ ያልፋሉ፥ የሰማይም ፍጥረት በትልቅ ትኵሳት ይቀልጣል፥ ምድርም በእርስዋም ላይ የተደረገው ሁሉ ይቃጠላል። ይህ ሁሉ እንዲህ የሚቀልጥ ከሆነ፥ የእግዚአብሔርን ቀን መምጣት እየጠበቃችሁና እያስቸኰላችሁ፥ በቅዱስ ኑሮ እግዚአብሔርንም በመምሰል እንደ ምን ልትሆኑ ይገባችኋል? ስለዚያ ቀን ሰማያት ተቃጥለው ይቀልጣሉ የሰማይም ፍጥረት በትልቅ ትኵሳት ይፈታል፤ ነገር ግን ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደ ተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን። ስለዚህ፥ ወዳጆች ሆይ፥ ይህን እየጠበቃችሁ ያለ ነውርና ያለ ነቀፋ ሆናችሁ በሰላም በእርሱ እንድትገኙ ትጉ፥ የጌታችንም ትዕግሥት መዳናችሁ እንደ ሆነ ቍጠሩ። እንዲህም የተወደደው ወንድማችን ጳውሎስ ደግሞ እንደ ተሰጠው ጥበብ መጠን ጻፈላችሁ፥ በመልእክቱም ሁሉ ደግሞ እንደ ነገረ ስለዚህ ነገር ተናገረ። በእነዚያ ዘንድ ለማስተዋል የሚያስቸግር ነገር አለ፥ ያልተማሩትና የማይጸኑትም ሰዎች ሌሎችን መጻሕፍት እንደሚያጣምሙ እነዚህን ደግሞ ለገዛ ጥፋታቸው ያጣምማሉ።
2 ጴጥሮስ 3:3-16 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከሁሉ በፊት ይህን አስተውሉ፤ በመጨረሻዎቹ ቀኖች የሚያፌዙና ክፉ ምኞታቸውን የሚከተሉ ዘባቾች ይመጣሉ፤ እነርሱ “ጌታ ኢየሱስ ይመጣል ተብሎ ተስፋ ተሰጥቶ አልነበረምን? ታዲያ፥ የት አለ? የቀድሞ አባቶቻችን ከሞቱበት ጊዜ አንሥቶ ሁሉ ነገር ከፍጥረት መጀመሪያ ጀምሮ እንደ ነበረው ነው” ይላሉ። እነዚህ ሰዎች ከብዙ ዘመን በፊት ሰማይ በእግዚአብሔር ቃል መፈጠሩን ምድርም የተሠራችው ከውሃና በውሃ መሆኑን ሆን ብለው ይክዳሉ። በዚያን ጊዜ የነበረውም ዓለም በውሃ ተጥለቅልቆ ጠፋ። እግዚአብሔርን የማያመልኩ ሰዎች አሁን ያሉት ሰማይና ምድር እስከሚጠፉበት እስከ ፍርድ ቀን ድረስ ለእሳት ተጠብቀው ይቈያሉ። ወዳጆቼ ሆይ! እናንተ ግን በጌታ ዘንድ አንድ ቀን እንደ ሺህ ዓመት፥ ሺህ ዓመት እንደ አንድ ቀን መሆኑን ይህን አንድ ነገር አትርሱ። አንዳንድ ሰዎች እንደሚመስላቸው ጌታ የተናገረውን የተስፋ ቃል ለመፈጸም አይዘገይም፤ ነገር ግን ሰው ሁሉ ለንስሓ እንዲበቃና ማንም ሰው እንዳይጠፋ ፈልጎ ስለ እናንተ ይታገሣል። የጌታ ቀን ግን እንደ ሌባ በድንገት ይመጣል፤ በዚያን ቀን ሰማያት በታላቅ ድምፅ ያልፋሉ፤ ፍጥረት ሁሉ በእሳት ተቃጥሎ ይጠፋል። ምድርና በእርስዋም ላይ ያለው ነገር ሁሉ ይቃጠላል፤ እንግዲህ እነዚህ ሁሉ ነገሮች በዚህ ሁኔታ የሚጠፉ ከሆነ፥ ታዲያ፥ እናንተ በቅድስናና እግዚአብሔርን በማምለክ መኖር እንዴት አይገባችሁም? እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቀን መምጣት በናፍቆት የምትጠባበቁና በቶሎም እንዲመጣ የምትሠሩ ሁኑ፤ በዚያን ቀን ሰማይ በእሳት ተቃጥሎ ይጠፋል፤ ፍጥረቶችም በእሳት ግለት ይቀልጣሉ፤ ነገር ግን እኛ በሰጠን ተስፋ መሠረት የጽድቅ ሥራ የሚመሠረትበትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንጠባበቃለን። ስለዚህ ወዳጆች ሆይ! ይህ ሁሉ የሚሆንበትን ቀን በመጠባበቅ ላይ ካላችሁ፥ ጌታ ያለ ነውር ወይም ያለ ነቀፋ ሆናችሁ በሰላም እንዲያገኛችሁ በትጋት ኑሩ፤ የጌታችንም መታገሥ ለእናንተ መዳን መሆኑን ዕወቁ፤ የተወደደው ወንድማችን ጳውሎስም በተሰጠው ጥበብ መጠን የጻፈላችሁ ይህንኑ ነው። እርሱ ስለዚህ ጉዳይ በመልእክቶቹ ሁሉ በዚሁ ዐይነት ጽፎአል፤ በመልእክቶቹ ውስጥ አንዳንድ ለመረዳት የሚያስቸግሩ ነገሮች አሉ። ዕውቀት የጐደላቸውና ወላዋዮች ሌሎችን ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሚያጣምሙ እነዚህንም ነገሮች ያጣምማሉ፤ ይህንንም የሚያደርጉት ለጥፋታቸው ነው።
2 ጴጥሮስ 3:3-16 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ከሁሉ በፊት ይህን አስተውሉ፤ በመጨረሻው ዘመን እንደራሳቸው ምኞት የሚመላለሱ ዘባቾች በመዘበት እንደሚመጡ እወቁ፤ እነርሱም “የመምጣቱ የተስፋ ቃል ወዴት ነው? ከፍጥረት መጀመሪያ ጀምሮ፥ የቀድሞ አባቶቻችን ከሞቱበት ጊዜ አንሥቶ፥ ሁሉ እንዳለ ይኖራል” ይላሉ። እነዚህ ሰዎች ከብዙ ዘመን በፊት ሰማያት በእግዚአብሔር ቃል መፈጠራቸውን ምድርም የተሠራችው ከውሃና በውሃ መሆኑን ሆን ብለው አያስተውሉም። በዚህም ምክንያት ያንጊዜ የነበረው ዓለም በውሃ ተጥለቅልቆ ጠፋ፤ ነገር ግን አሁን ያሉት ሰማያትና ምድር በዚሁ ቃል፥ እግዚአብሔርን የማያመልኩት ሰዎች እስከሚጠፉበት እስከ ፍርድ ቀን ድረስ ለእሳት ተጠብቀው ይቆያሉ። ወዳጆች ሆይ! እናንተ ግን በጌታ ዘንድ አንድ ቀን እንደ ሺህ ዓመት፥ ሺህ ዓመትም እንደ አንድ ቀን እንደሆነ ይህን አንድ ነገር አትርሱ። አንዳንዶች የሚዘገይ እንደሚመስላቸው፥ ጌታ ስለ ተስፋ ቃሉ አይዘገይም፤ ነገር ግን ሰው ሁሉ ለንስሓ እንዲበቃና ማንም እንዳይጠፋ ወዶ ስለ እናንተ ይታገሣል። የጌታ ቀን ግን እንደ ሌባ በድንገት ይመጣል፤ በዚያም ቀን ሰማያት በታላቅ ድምፅ ያልፋሉ፤ ምድርም በእርሷም ላይ የተደረገው ሁሉ ይቃጠላል። እንግዲህ እነዚህ ሁሉ ነገሮች በዚህ ሁኔታ የሚጠፉ ከሆነ፥ በቅዱስ ኑሮ እግዚአብሔርንም በመምሰል መኖር አይገባችሁም? እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቀን መምጣት የምትጠባበቁ የምታፋጥኑ ሁኑ፤ ምክንያቱም ስለዚያ ቀን ሰማያት ተቃጥለው ይጠፋሉ፤ የፍጥረት መሰረተ ነገር በእሳት ግለት ይቀልጣሉ! ነገር ግን እኛ ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማያትና አዲስ ምድር እንደ ተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን። ስለዚህ ወዳጆች ሆይ! ይህን ሁሉ እየተጠባበቃችሁ፥ ጌታ ያለ ነውር ወይም ያለ ነቀፋ ሆናችሁ በሰላም እንዲያገኛችሁ በትጋት ኑሩ፤ የጌታችንም ትዕግሥት ለእናንተ መዳን እንደሆነ ቁጠሩ። እንደዚሁ የተወደደው ወንድማችን ጳውሎስ እንደተሰጠው ጥበብ መጠን ጻፈላችሁ፤ በመልእክቶቹም ሁሉ እንዳደረገው ስለዚህ ነገር ተናግሯል። በመልእክቶቹ ውስጥ አንዳንድ ለመረዳት የሚያስቸግሩ ነገሮች አሉ፤ ዕውቀት የጐደላቸውና ጽናት የሌላቸው ሰዎች ሌሎችን ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሚያጣምሙ ሁሉ እነዚህን ደግሞ ለገዛ ጥፋታቸው ያጣምማሉ።