2 ቆሮንቶስ 7:10-11
2 ቆሮንቶስ 7:10-11 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ስለ እግዚአብሔር ተብሎ የሚደረግ ኀዘን የዘለዓለም ሕይወትን የሚያሰጥ ንስሓ ነው። ስለ ዓለም የሚደረግ ኀዘን ግን ሞትን ያመጣል። እነሆ፥ ያ ስለ እግዚአብሔር ብላችሁ ያደረጋችሁት ኀዘን ምንም የማታውቁ እስከ መሆን ደርሳችሁ፥ ራሳችሁን በበጎ ሥራና በንጽሕና እስክታጸኑ ድረስ፥ ትጋትንና ክርክርን፥ ቍጣንና ፍርሀትን፥ ናፍቆትንና ቅንዐትን፥ በቀልንም አደረገላችሁ፤
2 ቆሮንቶስ 7:10-11 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሆነ ሐዘን ወደ ድነት ለሚያደርስ ንስሓ ያበቃል፤ ጸጸትም የለበትም። ዓለማዊ ሐዘን ግን ለሞት ያበቃል። ይህ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሆነው ሐዘን እንዴት ያለ ትጋት፣ እንዴት ያለ መልስ የመስጠት ችሎታ፣ እንዴት ያለ ቍጣ፣ እንዴት ያለ ፍርሀት፣ እንዴት ያለ ናፍቆት፣ እንዴት ያለ በጎ ቅናት፣ እንዴት ያለ በቀል እንዳስገኘላችሁ ተመልከቱ። በዚህም ጕዳይ ንጹሓን መሆናችሁን በሁሉ ረገድ አስመስክራችኋል።
2 ቆሮንቶስ 7:10-11 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሆነ ኀዘን ጸጸት የሌለበትን፥ ወደ መዳንም የሚያደርሰውን ንስሐ ያደርጋልና፤ የዓለም ኀዘን ግን ሞትን ያመጣል። እነሆ፥ ይህ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሆነ ኀዘን እንዴት ያለ ትጋት፥ እንዴት ያለ መልስ፥ እንዴት ያለ ቁጣ፥ እንዴት ያለ ፍርሃት፥ እንዴት ያለ ናፍቆት፥ እንዴት ያለ ቅንዓት፥ እንዴት ያለ በቀል በመካከላችሁ አደረገ። በዚህ ነገር ንጹሐን እንደ ሆናችሁ በሁሉ አስረድታችኋል።
2 ቆሮንቶስ 7:10-11 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሚሆን ሐዘን ወደ መዳን የሚመራ በንስሓ የሚገኘውን ለውጥ ስለሚያስገኝ ጸጸትን አያስከትልም፤ ዓለማዊ ሐዘን ግን ሞትን ያመጣል። ይህ ሐዘናችሁ በእግዚአብሔር ፈቃድ መሆኑ እንዴት ያለ የመከላከያ መልስ መስጠትን፥ እንዴት ያለ ቶሎ መቈጣትን፥ እንዴት ያለ ፍርሀትን፥ እንዴት ያለ ናፍቆትን፥ እንዴት ያለ ቅናትን፥ እንዴት ያለ ቅጣትንም እንዳስከተለ ልብ ብላችሁ አስተውሉ። እናንተ ደግሞ በሁሉም ነገር ከጉዳዩ ነጻ መሆናችሁን አስመስክራችኋል።
2 ቆሮንቶስ 7:10-11 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሆነ ኀዘን ወደ መዳን ለሚያደርስ ንስሓ ያበቃል፤ ጸጸትም የለበትም፤ ዓለማዊው ኀዘን ግን ሞትን ያመጣል። እነሆ፥ ይህ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሆነ ኀዘን ለእንዴት ዓይነት ትጋት፥ ለእንዴት ዓይነት ራስን የማንጻት ጉጉት፥ ለእንዴት ዓይነት ቊጣ፥ ለእንዴት ዓይነት ፍርሃት፥ ለእንዴት ዓይነት ናፍቆት፥ ለእንዴት ዓይነት ቅንዓት፥ ለእንዴት ዓይነት ቅጣት እንዳደረሳችሁ ተመልከቱ! በዚህም ጉዳይ ንጹሓን መሆናችሁን በሁሉ ረገድ አስመስክራችኋል።

