2 ቆሮንቶስ 5:15-21

2 ቆሮንቶስ 5:15-21 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

በሕ​ይ​ወት የሚ​ኖ​ሩ​ትም ስለ እነ​ርሱ ቤዛ ሆኖ ለሞ​ተ​ውና ለተ​ነ​ሣ​ውም እንጂ ወደ​ፊት ለራ​ሳ​ቸው የሚ​ኖሩ እን​ዳ​ይ​ሆኑ እርሱ ስለ ሁሉ ቤዛ ሆኖ ሞተ። ስለ​ዚህ ከአ​ሁን ጀምሮ በሥጋ የም​ና​ው​ቀው የለም፤ ክር​ስ​ቶ​ስ​ንም በሥጋ ብና​ው​ቀው አሁን ግን ከእ​ን​ግ​ዲህ ወዲህ የም​ና​ው​ቀው አይ​ደ​ለም። አሁ​ንም በክ​ር​ስ​ቶስ የሆ​ነው ሁሉ አዲስ ፍጥ​ረት ነው፤ የቀ​ደ​መ​ውም አለፈ፤ እነሆ ሁሉም አዲስ ሆነ። ነገር ግን ሁሉ በክ​ር​ስ​ቶስ ከራሱ ጋር ከአ​ስ​ታ​ረ​ቀን፥ የማ​ስ​ታ​ረቅ መል​እ​ክ​ት​ንም ከሰ​ጠን ከእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ዘንድ ነው። ኀጢ​አ​ታ​ቸ​ውን ይቅር ብሎ በደ​ላ​ቸ​ው​ንም ሳያ​ስብ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር በክ​ር​ስ​ቶስ ዓለ​ሙን ከራሱ ጋር አስ​ታ​ር​ቆ​አ​ልና፤ የዕ​ርቅ ቃሉ​ንም በእኛ ላይ አደ​ረገ፤ የይ​ቅ​ር​ታ​ው​ንም መል​እ​ክት ሰጠን። እኛስ በክ​ር​ስ​ቶስ አም​ሳል እን​ለ​ም​ና​ለን፤ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም በእኛ መጽ​ና​ና​ትን ይሰ​ጣ​ች​ኋል፤ ከእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ጋር ትታ​ረቁ ዘንድ በክ​ር​ስ​ቶስ እን​ለ​ም​ና​ች​ኋ​ለን። ኀጢ​አት የሌ​ለ​በት እርሱ እኛን ለእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ያጸ​ድ​ቀን ዘንድ ስለ እኛ ራሱን እንደ ኃጥእ አድ​ር​ጓ​ልና።

2 ቆሮንቶስ 5:15-21 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

በሕይወት ያሉትም ለሞተላቸውና ከሙታን ለተነሣላቸው እንጂ ከእንግዲህ ለራሳቸው እንዳይኖሩ እርሱ ስለ ሁሉ ሞተ። ስለዚህ ከአሁን ጀምሮ ማንንም በውጫዊ ነገር አንመዝንም፤ ከዚህ ቀደም ክርስቶስን በዚህ መልክ መዝነነው ነበር፤ ከእንግዲህ ግን እንደዚህ አናደርግም። ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር ዐልፏል፤ እነሆ፤ አዲስ ሆኗል። ይህ ሁሉ ከእግዚአብሔር ነው፤ እርሱ በክርስቶስ አማካይነት ከራሱ ጋራ አስታረቀን፤ የማስታረቅንም አገልግሎት ሰጠን፤ እግዚአብሔር በክርስቶስ ዓለምን ከራሱ ጋራ ሲያስታርቅ የሰዎችን በደል አይቈጥርባቸውም ነበር፤ ለእኛም ደግሞ የማስታረቅ ቃል ሰጠን። ስለዚህ እኛ የክርስቶስ እንደራሴዎች ነን፤ እግዚአብሔርም በእኛ አማካይነት ጥሪውን ያቀርባል፤ እኛም ከእግዚአብሔር ጋራ ታረቁ ብለን በክርስቶስ እንለምናችኋለን። እኛ በርሱ ሆነን የእግዚአብሔር ጽድቅ እንድንሆን፣ ኀጢአት የሌለበትን እርሱን እግዚአብሔር ስለ እኛ ኀጢአት አደረገው።

2 ቆሮንቶስ 5:15-21 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

በሕይወትም ያሉት ስለ እነርሱ ለሞተውና ለተነሣው እንጂ ወደ ፊት ለራሳቸው እንዳይኖሩ ስለ ሁሉ ሞተ። ስለዚህ እኛ ከአሁን ጀምሮ ማንንም በሥጋ እንደሚሆን አናውቅም ክርስቶስንም በሥጋ እንደ ሆነ ያወቅነው ብንሆን እንኳ፥ አሁን ግን ከእንግዲህ ወዲህ እንደዚህ አናውቀውም። ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፎአል፤ እነሆ፥ ሁሉም አዲስ ሆኖአል። ነገር ግን የሆነው ሁሉ፥ በክርስቶስ ከራሱ ጋር ካስታረቀን የማስታረቅም አገልግሎት ከሰጠን፥ ከእግዚአብሔር ነው፤ እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበርና፥ በደላቸውን አይቆጥርባቸውም ነበር፤ በእኛም የማስታረቅ ቃል አኖረ። እንግዲህ እግዚአብሔር በእኛ እንደሚማልድ ስለ ክርስቶስ መልክተኞች ነን፤ ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለን ስለ ክርስቶስ እንለምናለን። እኛ በእርሱ ሆነን የእግዚአብሔር ጽድቅ እንሆን ዘንድ ኃጢአት ያላወቀውን እርሱን ስለ እኛ ኃጢአት አደረገው።

2 ቆሮንቶስ 5:15-21 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

በሕይወት ያሉት ሁሉ ለእነርሱ ለሞተውና ከሞትም ለተነሣው እንዲኖሩ እንጂ ከእንግዲህ ወዲህ ለራሳቸው ሲሉ እንዳይኖሩ ክርስቶስ ለሁሉም ሞተ። ከእንግዲህ ወዲህ እኛ ማንንም ሰው በሥጋዊ አመለካከት አንመለከትም፤ ከዚህ በፊት ክርስቶስንም የተመለከትነው እንደ ማንኛውም ሰው በሥጋዊ አመለካከት ከሆነ ለወደፊቱ ግን ይህን አናደርግም። ስለዚህ ማንም ሰው የክርስቶስ ወገን ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ፍጥረት አልፎአል፤ በእርሱም ስፍራ አዲስ ፍጥረት ተተክቶአል። ይህም ሁሉ የሆነው እኛን ከራሱ ጋር በክርስቶስ አማካይነት ባስታረቀንና የማስታረቅንም አገልግሎት በሰጠን በእግዚአብሔር ነው። ይህም እግዚአብሔር በክርስቶስ የዓለምን ሰዎች ሁሉ ከራሱ ጋር አስታረቀ ማለት ነው፤ በደላቸውንም አልቈጠረባቸውም፤ ለእኛም ሰውን ከጌታ ጋር የምናስታርቅበትን ቃል ሰጠን። እግዚአብሔር ሰዎችን በእኛ አማካይነት ስለሚጠራ እኛ የክርስቶስ እንደራሴዎች ነን፤ ስለዚህ “ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ!” ብለን በክርስቶስ ስም እንለምናችኋለን። እኛ በክርስቶስ የእግዚአብሔር ጽድቅ ተካፋዮች እንድንሆን እግዚአብሔር ኃጢአት የሌለበትን ክርስቶስን የእኛን ኃጢአት እንዲሸከም አደረገው።

2 ቆሮንቶስ 5:15-21 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

በሕይወትም ያሉት፥ ስለ እነርሱ ለሞተውና ለተነሣው እንጂ፥ ወደ ፊት ለራሳቸው እንዳይኖሩ እርሱ ስለ ሁሉ ሞተ። ስለዚህ ከአሁን ጀምሮ ማንንም በሰብአዊ አመለካከት እንደምናየው አድርገን አንመለክትም፤ ክርስቶስንም በዚህ መልክ ተመልክተነው የነበርን ብንሆን እንኳን፥ ከእንግዲህ ወዲህ ግን በዚህ መልክ አይደለም የምናውቀው። ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፎአል፤ እነሆ፥ ሁሉም አዲስ ሆኖአል! ይህ ሁሉ የሆነው፥ በክርስቶስ ከራሱ ጋር ካስታረቀን፥ የማስታረቅም አገልግሎት ከሰጠን ከእግዚአብሔር ነው፤ ይህ እግዚአብሔር የሰዎችን በደል ሳይቆጥርባቸው በክርስቶስ ዓለምን ከራሱ ጋር አስታርቋል፤ በእኛም የማስታረቅ ቃል አኑሯል። ስለዚህ እግዚአብሔር ጥሪውን የሚያቀርበው በእኛ በኩል በመሆኑ፥ እኛ ለክርስቶስ መልክተኞች ነን፤ ስለ ክርስቶስ ሆነን “ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ” ብለን እንለምናለን። እኛ በእርሱ ሆነን የእግዚአብሔር ጽድቅ እንድንሆን ስለ እኛ ኃጢአት የሌለበትን እርሱን ኃጢአት አደረገው።