2 ቆሮንቶስ 5:1-5
2 ቆሮንቶስ 5:1-5 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በምድር ያለው ማደሪያ ቤታችን ቢፈርስም፥ በሰማይ በእግዚአብሔር ዘንድ የሰው እጅ ያልሠራው ዘለዓለማዊ ቤት እንዳለን እናውቃለን። ስለ እርሱ የምንደክምለትን በሰማይ ያለውን ቤታችንን እንለብስ ዘንድ እርሱን ተስፋ እናደርጋለን። ከለበስነውም በኋላ ዕራቍታችንን የምንገኝ አይደለንም። በዚህ ቤት ውስጥ ሳለንም ከከባድነቱ የተነሣ እጅግ እናዝናለን፤ ነገር ግን ሟች በሕይወት ይዋጥ ዘንድ ሌላ ልንለብስ እንጂ ልንገፈፍ አንወድም። ለዚህም ያዘጋጀን እግዚአብሔር ነው፤ እርሱም የመንፈስ ቅዱስን ፈለማ ሰጠን።
2 ቆሮንቶስ 5:1-5 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
መኖሪያችን የሆነው ምድራዊ ድንኳን ቢፈርስም፣ በሰው እጅ ያልተሠራ ነገር ግን ከእግዚአብሔር የሆነ ዘላለማዊ ቤት በሰማይ እንዳለን እናውቃለን። እስከዚያው ግን የሰማዩን መኖሪያችንን ለመልበስ እየናፈቅን እንቃትታለን፤ በርግጥ ከለበስነው ዕራቍታችንን ሆነን አንገኝም። በዚህ ድንኳን እስካለን ድረስ ከብዶን እንቃትታለን፤ ምክንያቱም ሟች የሆነው በሕይወት እንዲዋጥ ሰማያዊውን መኖሪያችንን ልንለብስ እንጂ ልንገፈፍ አንፈልግም። ለዚህ ዐላማ ያዘጋጀን እግዚአብሔር ነው፤ ሊመጣ ላለው ዋስትና እንዲሆነን መንፈሱን መያዣ አድርጎ የሰጠንም እርሱ ነው።
2 ቆሮንቶስ 5:1-5 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ድንኳን የሚሆነው ምድራዊ መኖሪያችን ቢፈርስ፥ በሰማይ ያለ በእጅ ያልተሠራ የዘላለም ቤት የሚሆን ከእግዚአብሔር የተሠራ ሕንጻ እንዳለን እናውቃለንና። በዚህ ውስጥ በእውነት እንቃትታለንና፥ ከሰማይም የሚሆነውን መኖሪያችንን እንድንለብስ እንናፍቃለንና ለብሰን ራቁታችንን አንገኝም። በእውነትም የሚሞተው በሕይወት ይዋጥ ዘንድ ልንለብስ እንጂ ልንገፈፍ የማንወድ ስለ ሆነ፥ በድንኳኑ ያለን እኛ ከብዶን እንቃትታለን። ነገር ግን ለዚሁ የሠራን እግዚአብሔር ነው እርሱም የመንፈሱን መያዣ ሰጠን።
2 ቆሮንቶስ 5:1-5 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ይህ እንደ ድንኳን ጊዜያዊ የሆነው ምድራዊው ሥጋችን ሲፈርስ በሰው እጅ ሳይሆን በእግዚአብሔር የታነጸ ዘለዓለማዊ መኖሪያ በሰማይ እንዳለን እናውቃለን። ሰማያዊ አካልን ለመልበስ በመናፈቅ እንጥራለን። እርሱንም ስንለብስ ራቁታችንን ሆነን አንገኝም። በዚህ እንደ ምድራዊ ድንኳን በሆነው ሥጋችን ውስጥ ስንኖር ከብደን እንቃትታለን፤ የምንቃትተውም ሞት በሕይወት እንዲለወጥ ሰማያዊውን አካል በበለጠ እንድንለብስ ነው እንጂ ከዚህ ከምድራዊ ሥጋችን ለመለየት በመፈለግ አይደለም። ለዚህም ነገር ያዘጋጀን እግዚአብሔር ነው፤ ከዚያም በላይ ለሚሰጠን ነገር ሁሉ ዋስትና እንዲሆን መንፈሱን የሰጠንም እርሱ ነው።
2 ቆሮንቶስ 5:1-5 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
የምንኖርበት ምድራዊ ድንኳን የሆነው ሕይወት ቢፈርስ፥ በሰማይ ዘላለማዊ የሆነ በእጅ ያልተሠራ፥ በእግዚአብሔር የታነጸ መኖሪያ እንዳለን እናውቃለን። በዚህ ድንኳን ውስጥ እንቃትታለን፥ ከሰማይ የሆነ መኖሪያችንን ለመልበስ እንናፍቃለንና፤ ለብሰን ራቁታችንን አንገኝም። በእውነትም የሚሞተው በሕይወት እንዲዋጥ፥ ጨምረን ልንለብስ እንጂ ልንገፈፍ የማንወድ ስለሆነ፥ በዚህ ድንኳን ሳለን ከብዶን እንቃትታለን። ነገር ግን ለዚሁ የሠራን እግዚአብሔር ነው፤ እርሱም የመንፈሱን መያዣ ሰጠን።