2 ቆሮንቶስ 4:8-11
2 ቆሮንቶስ 4:8-11 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በሁሉ መከራን እንቀበላለን፤ ነገር ግን አንጨነቅም፤ እንናቃለን፥ ነገር ግን ተስፋ አንቈርጥም። እንሰደዳለን፤ ነገር ግን አንጣልም፤ እንወድቃለን፤ ነገር ግን አንጠፋም። የክርስቶስ ሕይወቱ በዚህ በሟች ሰውነታችን ላይ ይገለጥ ዘንድ፥ ዘወትር የክርስቶስን ሞት በሥጋችን እንሸከማለን። በሕይወት የምንኖር እኛም በሟች ሰውነታችን ላይ የኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወቱ ይገለጥ ዘንድ፥ ዘወትር ስለ ኢየሱስ ክስርቶስ ብለን ተላልፈን ለሞት እንሰጣለን።
2 ቆሮንቶስ 4:8-11 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከየአቅጣጫው ብንገፋም አንንኰታኰትም፤ ግራ ብንጋባም ተስፋ አንቈርጥም፤ ብንሰደድም ተጥለን አንቀርም፤ መትተው ቢጥሉንም አንጠፋም። የኢየሱስ ሕይወት በሰውነታችን እንዲገለጥ፣ የኢየሱስን ሞት ዘወትር በሰውነታችን ተሸክመን እንዞራለን። የኢየሱስ ሕይወት ሟች በሆነው ሥጋችን እንዲገለጥ፣ እኛ ሕያዋን የሆንን ሁልጊዜ ስለ ኢየሱስ ለሞት ዐልፈን እንሰጣለንና።
2 ቆሮንቶስ 4:8-11 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በሁሉ እንገፋለን እንጂ አንጨነቅም፤ እናመነታለን እንጂ ተስፋ አንቆርጥም፤ እንሰደዳለን እንጂ አንጣልም፤ እንወድቃለን እንጂ አንጠፋም፤ የኢየሱስ ሕይወት ደግሞ በሥጋችን ይገለጥ ዘንድ ሁልጊዜ የኢየሱስን መሞት በሥጋችን ተሸክመን እንዞራለን። የኢየሱስ ሕይወት ደግሞ በሚሞት ሥጋችን ይገለጥ ዘንድ እኛ ሕያዋን የሆንን ከኢየሱስ የተነሣ ዘወትር ለሞት አልፈን እንሰጣለንና።
2 ቆሮንቶስ 4:8-11 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በየአቅጣጫው መከራ ይደርስብናል፤ ግን አንሸነፍም፤ ብዙ ጊዜ ግራ ይገባናል፤ ግን ተስፋ አንቈርጥም፤ ጠላቶች ያሳድዱናል፤ ግን ወዳጆች አጥተን አናውቅም፤ ተመተን እንወድቃለን፤ ግን አንሞትም፤ የኢየሱስ ሕይወት በእኛ ሰውነት እንዲገለጥ በኢየሱስ ላይ የደረሰው ሞት በእኛም ሰውነት ላይ ዘወትር ተሸክመን እንዞራለን። የኢየሱስ ሕይወት በሟች ሰውነታችን ይገለጥ ዘንድ እኛ ሕያዋኑ ስለ ኢየሱስ ሁልጊዜ ለሞት ተላልፈን እንሰጣለን።