2 ቆሮንቶስ 11:1-4
2 ቆሮንቶስ 11:1-4 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በስንፍናዬ እናገር ዘንድ ጥቂት ልትታገሡኝ ይገባ ነበር፤ ቢሆንም በርግጥ ታገሡኝ፤ ለእግዚአብሔር የሚገባ ቅንዐት እቀናላችኋለሁና፤ ወደ እርሱ አቀርባችሁ ዘንድ ለአንዱ ንጹሕ ድንግል ሙሽራ ለክርስቶስ አጭቻችኋለሁና። ነገር ግን እባብ ሔዋንን በተንኰሉ እንዳሳታት፥ አሳባችሁ ከክርስቶስ የዋህነትና ንጽሕና ምናልባት እንዳይለወጥ ብዬ እፈራለሁ። ወደ እናንተ የመጣና እኛ ወደ አላስተማርናችሁ ወደ ሌላ ኢየሱስ የጠራችሁ ቢኖር፥ ወይም ያልተቀበላችሁት ሌላ መንፈስ ቢኖር፥ ወይም ያልተማራችሁት ሌላ ወንጌል ቢኖር ልትጠብቁን ይገባል።
2 ቆሮንቶስ 11:1-4 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ጥቂቱን ሞኝነቴን እንደምትታገሡኝ ተስፋ አደርጋለሁ፤ በርግጥም እየታገሣችሁኝ ነው። በእግዚአብሔር ቅናት እቀናላችኋለሁ፤ እናንተን እንደ ንጽሕት ድንግል ለክርስቶስ ለማቅረብ ለአንድ ባል ዐጭቻችኋለሁና። ነገር ግን እባብ ሔዋንን በተንኰል እንዳሳታት ምናልባት የእናንተም ልቡና ተበላሽቶ ለክርስቶስ ካላችሁ ቅንነትና ንጽሕና እንዳትወሰዱ እሠጋለሁ። ምክንያቱም አንድ ሰው ወደ እናንተ መጥቶ እኛ ከሰበክንላችሁ ኢየሱስ ሌላ ኢየሱስ ቢሰብክላችሁ፣ ወይም ከተቀበላችሁት መንፈስ የተለየ መንፈስ ብትቀበሉ፣ ወይም ከተቀበላችሁት ወንጌል የተለየ ወንጌል ብትቀበሉ፣ ነገሩን በዝምታ ታልፉታላችሁ ማለት ነው።
2 ቆሮንቶስ 11:1-4 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በጥቂቱ ሞኝነቴ ብትታገሡኝ መልካም ይሆን ነበር፤ ቢሆንም በእርግጥ ታገሡኝ። በእግዚአብሔር ቅንዓት እቀናላችኋለሁና፥ እንደ ንጽሕት ድንግል እናንተን ለክርስቶስ ላቀርብ ለአንድ ወንድ አጭቻችኋለሁና፤ ነገር ግን እባብ በተንኮሉ ሔዋንን እንዳሳታት፥ አሳባችሁ ተበላሽቶ ለክርስቶስ ከሚሆን ቅንነትና ንጽሕና ምናልባት እንዳይለወጥ ብዬ እፈራለሁ። የሚመጣውም ያልሰበክነውን ሌላ ኢየሱስ ቢሰብክ፥ ወይም ያላገኛችሁትን ልዩ መንፈስ ወይም ያልተቀበላችሁትን ልዩ ወንጌል ብታገኙ፥ በመልካም ትታገሡታላችሁ።
2 ቆሮንቶስ 11:1-4 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ጥቂቱን ሞኝነቴን እንደምትታገሡኝ ተስፋ አደርጋለሁ፤ እባካችሁ ታገሡኝ። እንደ አንዲት ንጽሕት ልጃገረድ በድንግልናዋ ለአንድ ባል እንደምትታጭ እኔም እናንተን ለክርስቶስ ስላአጨኋችሁ ስለ እናንተ መንፈሳዊ ቅናት እቀናለሁ። እባብ ሔዋንን በተንኰሉ እንዳሳታት ምናልባት የእናንተም ሐሳብ ተበላሽቶ ለክርስቶስ ያላችሁን ቅንና ንጹሕ የሆነ ታማኝነት ትተዋላችሁ ብዬ እፈራለሁ። አንድ ሰው ወደ እናንተ መጥቶ እኛ የሰበክነውን ሳይሆን ሌላ ኢየሱስ ቢሰብክላችሁ ወይም እናንተ የተቀበላችሁትን መንፈስ ሳይሆን ሌላ መንፈስ ብትቀበሉ፥ ወይም የተቀበላችሁትን ወንጌል ሳይሆን ሌላ ወንጌል ብትቀበሉ፥ ዝም ብላችሁ ተሸነፋችሁ ማለት ነው።
2 ቆሮንቶስ 11:1-4 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ሞኝነቴን በጥቂቱ ብትታገሡኝ በወደድኩ ነበር፤ ስለሆነም በእርግጥ ታገሡኝ። እንደ አንዲት ንጽሕት ድንግል እናንተን ለክርስቶስ ለማቅረብ ለአንድ ወንድ አጭቻችኋለሁና፥ በእግዚአብሔር ቅንዐት እቀናላችኋለሁና። ነገር ግን እባብ በተንኮሉ ሔዋንን እንዳሳታት፥ አሳባችሁ ተበላሽቶ ለክርስቶስ ሊኖራችሁ ከሚገባ ቅንነትና ንጽሕና እንዳትርቁ ብዬ እፈራለሁ። ምክንያቱም አንዱ መጥቶ እኛ ያልሰበክነውን ሌላ ኢየሱስ ቢሰብክ፥ ወይም ያላገኛችሁትን ልዩ መንፈስ ወይም ያልተቀበላችሁትን ልዩ ወንጌል ሆኖ ብታገኙት፥ በመልካምነታችሁ ትታገሡታላችሁ።