2 ዜና መዋዕል 24:1-27
2 ዜና መዋዕል 24:1-27 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ኢዮአስም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሰባት ዓመት ልጅ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም አርባ ዓመት ነገሠ፤ እናቱ ሳብያ የተባለች የቤርሳቤህ ሴት ነበረች። ኢዮአስም በካህኑ በኢዮአዳ ዘመን ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገርን አደረገ። ኢዮአዳም ሁለት ሚስቶችን አጋባው፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ወለደ። ከዚህም በኋላ ኢዮአስ የእግዚአብሔርን ቤት ይጠግን ዘንድ አሰበ። ካህናትንና ሌዋውያንንም ሰብስቦ፥ “ወደ ይሁዳ ከተሞች ውጡ፤ የአምላካችሁንም ቤት በየዓመቱ ለማደስ የሚበቃ ከእስራኤል ሁሉ ገንዘብን ሰብስቡ፤ ነገሩንም ፈጥናችሁ አድርጉ” አላቸው። ሌዋውያን ግን አላፋጠኑም። ንጉሡ ኢዮአስም አለቃውን ኢዮአዳን ጠርቶ፥ “የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ እስራኤልን በምስክሩ ድንኳን በሰበሰበ ጊዜ እንዲያዋጣ ያዘዘውን ግብር ከይሁዳና ከኢየሩሳሌም ያመጡ ዘንድ ስለ ምን ሌዋውያንን አልተከታተልህም?” አለው። ጎቶልያ ከሐዲት ነበረችና ልጆችዋም የእግዚአብሔርን ቤት አፍርሰዋልና፤ በእግዚአብሔርም ቤት ተቀድሶ የነበረውን ሁሉ ለበኣሊም ሰጥተዋልና። ንጉሡም ሣጥን ሠርተው በእግዚአብሔር ቤት በር አጠገብ በስተውጭ ያኖሩት ዘንድ አዘዘ። የእግዚአብሔርም ባሪያ ሙሴ በምድረ በዳ በእስራኤል ላይ ያዘዘውን ግብር ለእግዚአብሔር ያመጡ ዘንድ፥ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ያስተምሩ ዘንድ አዘዘ። አለቆቹና ሕዝቡም ሁሉ ሰጡ፤ እስኪሞላም ድረስ በሣጥኑ ውስጥ አስገቡት። ሣጥኑም በሌዋውያን እጅ ወደ ንጉሡ ሹሞች በደረሰ ጊዜ፥ ብዙ ገንዘብም እንዳለበት ባዩ ጊዜ፥ የንጉሡ ጸሓፊና የሊቀ ካህናቱ ሹም እየመጡ ብሩን ከሣጥን ያወጡ ነበር፤ ሣጥኑንም ደግሞ ወደ ስፍራው ይመልሱት ነበር። እንዲሁም በየቀኑ ያደርጉ ነበር፤ ብዙም ገንዘብ ሰበሰቡ። ንጉሡና ኢዮአዳም በእግዚአብሔር ቤት ሥራ ላይ ለተሾሙት ሰጡአቸው፤ እነርሱም የእግዚአብሔርን ቤት የሚጠግኑትን ጠራቢዎችንና አናጢዎችን፥ የእግዚአብሔርንም ቤት የሚያድሱትን የብረትና የናስ ሠራተኞችን ይቀጥሩበት ነበር። ሠራተኞችም ሠሩ፤ ሥራውም ሁሉ በእጃቸው ተፈጸመ፤ የእግዚአብሔርንም ቤት እንደ ቀድሞው ሥራ መለሱ፤ አጽንተውም አቆሙት። በጨረሱም ጊዜ የተረፈውን ገንዘብ ወደ ንጉሡና ወደ ካህኑ ኢዮአዳ ፊት አመጡ፤ እነርሱም ለእግዚአብሔር ቤት ዕቃ፥ ለአገልግሎትና ለቍርባን ዕቃ፥ ለጭልፋዎችም፥ ለወርቅና ለብርም ዕቃ አደረጉት። በኢዮአዳም ዘመን ሁሉ ለእግዚአብሔር ቤት የሚቃጠል መሥዋዕት ሁልጊዜ ያቀርቡ ነበር። ኢዮአዳም ሸመገለ፤ ዕድሜም ጠግቦ ሞተ፤ በሞተም ጊዜ ዕድሜው መቶ ሠላሳ ዓመት ነበረ። ከእስራኤልም ጋር፥ ከእግዚአብሔርና ከቤቱም ጋር መልካም ሠርቶአልና በዳዊት ከተማ ከነገሥታቱ ጋር ቀበሩት። ካህኑ ኢዮአዳም ከሞተ በኋላ የይሁዳ አለቆች ገብተው ለንጉሡ ሰገዱ፤ ንጉሡም ሰማቸው። የአባቶቻቸውንም አምላክ የእግዚአብሔርን ቤት ትተው ባዕድ አምላክንና ጣዖታትን አመለኩ፤ በዚያም ወራት በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ ቍጣ ወረደ። ወደ እግዚአብሔርም ይመልሱአቸው ዘንድ ነቢያትን ይሰድድላቸው ነበር፤ መሰከሩባቸውም፤ እነርሱ ግን አላደመጡም። የእግዚአብሔርም መንፈስ በካህኑ በኢዮአዳ ልጅ በአዛርያስ ላይ መጣ፤ እርሱም በሕዝቡ ፊት ቆመና፥ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ለምን ትተላለፋላችሁ? መልካምም አይሆንላችሁም፤ እግዚአብሔርን ስለ ተዋችሁ እርሱ ትቶአችኋል” አላቸው። ወደ እርሱም ሮጡ በንጉሡም ትእዛዝ በእግዚአብሔር ቤት አደባባይ ውስጥ በድንጋይ ደበደቡት። እንዲሁም ንጉሡ ኢዮአስ አባቱ ኢዮአዳ ያደረገለትን ቸርነት አላሰበም፤ ልጁንም አዛርያስን አስገደለው፤ እርሱም ሲሞት፥ “እግዚአብሔር ይየው፤ ይፍረደውም” አለ። ዓመቱም ካለፈ በኋላ የሶርያውያን ሠራዊት መጡበት፤ ወደ ይሁዳና ወደ ኢየሩሳሌምም መጥተው ከሕዝቡ መካከል የሕዝቡን አለቆች ሁሉ አጠፉ፤ ምርኮአቸውንም ሁሉ ለደማስቆ ንጉሥ ላኩ። የሶርያውያንም ሠራዊት ቍጥር ጥቂት ነበር፤ እግዚአብሔር ግን ብዙውንና ጠንካራውን ሠራዊት አሳልፎ በእጃቸው ሰጣቸው፤ የአባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርን ዘንግተዋልና። በኢዮአስም ላይ ፈረደበት። ከእርሱም ዘንድ አልፈው ከሄዱ በኋላ እጅግ ታሞ ሳለ ተዉት፤ የገዛ ባሪያዎቹም ስለ ካህኑ ስለ ኢዮአዳ ልጅ ደም ተበቅለው በአልጋው ላይ ገደሉት፤ ሞተም፤ በዳዊትም ከተማ ቀበሩት፤ ነገር ግን በነገሥታት መቃብር አልቀበሩትም። የገደሉትም የአሞናዊቱ የሰማት ልጅ ዘቡድ፥ የሞዓባዊቱም የሰማሪት ልጅ ኢዮዛብድ ነበሩ። የልጆቹና በእርሱ ላይ የተደረገው ነገር፥ የእግዚአብሔርንም ቤት ማደሱ፥ እነሆ በነገሥታቱ የታሪክ መጽሐፍ ተጽፎአል። ልጁም አሜስያስ በእርሱ ፋንታ ነገሠ።
2 ዜና መዋዕል 24:1-27 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ኢዮአስ በነገሠ ጊዜ፣ ዕድሜው ሰባት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም አርባ ዓመት ገዛ። እናቱ ሳብያ የተባለች የቤርሳቤህ ሴት ነበረች። ካህኑ ዮዳሄ በሕይወት በነበረበት ዘመን ሁሉ፣ ኢዮአስ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ነገር አደረገ። ዮዳሄ ሁለት ሚስቶች መረጠለት፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆችም ወለደ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ኢዮአስ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ለማደስ ወሰነ። ካህናቱንና ሌዋውያኑን ሰብስቦም፣ “ወደ ይሁዳ ከተሞች ሄዳችሁ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ በየዓመቱ ለማደስ ገንዘብ ከእስራኤል ሁሉ ሰብስቡ፤ ይህንም አሁኑኑ አድርጉት” አላቸው። ሌዋውያኑ ግን ቸል አሉ። ስለዚህ ንጉሡ ሊቀ ካህኑን ዮዳሄን ጠርቶ፣ “የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴና የእስራኤል ጉባኤ ለምስክሩ ድንኳን እንዲወጣ የወሰኑትን ግብር ከይሁዳና ከኢየሩሳሌም እንዲያመጡ ሌዋውያኑን ያላተጋሃቸው ለምንድን ነው?” አለው። በዚህ ጊዜ የዚያች ክፉ የጎቶልያ ልጆች የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ሰብረው በመግባት የተቀደሱ ዕቃዎች እንኳ ሳይቀሩ፣ ለበኣል ጣዖታት አገልግሎት እንዲውሉ አድርገው ነበር። በንጉሡም ትእዛዝ የገንዘብ መሰብሰቢያ ሣጥን ሠርተው በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መግቢያ በር አጠገብ በውጭ በኩል አኖሩት። ከዚህ በኋላ እስራኤል በምድረ በዳ ሳሉ የእግዚአብሔር አገልጋይ ሙሴ ያዘዘውን ግብር ለእግዚአብሔር እንዲያመጡ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ዐዋጅ ተነገረ። ሹማምቱ ሁሉ፣ ሕዝቡም ሁሉ ግብሩን በደስታ አመጡ፤ እስኪሞላም ድረስ በሣጥኑ ውስጥ ጨመሩ። ሣጥኑ በሌዋውያኑ እጅ ወደ ንጉሡ ሹማምት በሚደርስበት ጊዜ፣ እነርሱም በውስጡ ብዙ ገንዘብ መኖሩን በሚያዩበት ጊዜ ሁሉ፣ የቤተ መንግሥቱ ጸሓፊና የሊቀ ካህናቱ ሹም ይመጡና ሣጥኑን አጋብተው ወደ ቦታው ይመልሱት ነበር። ይህን በየቀኑ በማድረግ እጅግ ብዙ ገንዘብ ሰበሰቡ። ንጉሡና ዮዳሄም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ሥራ እንዲያሠሩ ለተመደቡት ሰዎች ገንዘቡን አስረከቧቸው፤ እነርሱም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ለማደስ ድንጋይ የእጅ ጥበብ ባለሙያዎችና ዐናጺዎችን እንዲሁም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ለመጠገን የብረትና የናስ ሠራተኞችን ቀጠሩ። በሥራው ላይ የተሰማሩት ሰዎች ትጉሃን ስለ ነበሩ፣ ሥራው በእጃቸው ተከናወነ፤ የእግዚአብሔርንም ቤተ መቅደስ ቀደም ሲል በነበረው ዐይነት ዐደሱት፤ አጠናከሩትም። ከጨረሱም በኋላ ቀሪውን ገንዘብ ወደ ንጉሡና ወደ ዮዳሄ አመጡ፤ በገንዘቡም የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ዕቃዎች ማለትም ለአገልግሎትና ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚውሉ ዕቃዎች እንደዚሁም ጭልፋዎችና ሌሎች የወርቅና የብር ዕቃዎችም ተሠሩ። ዮዳሄ በሕይወት በነበረበት ዘመን ሁሉ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የሚቃጠል መሥዋዕት ዘወትር ይቀርብ ነበር። ዮዳሄ ሸምግሎ ዕድሜ ከጠገበ በኋላ፣ በመቶ ሠላሳ ዓመቱ ሞተ። እርሱም በእስራኤል ውስጥ ለእግዚአብሔርና ለቤተ መቅደሱ መልካም ሠርቷልና በዳዊት ከተማ በነገሥታቱ መቃብር ተቀበረ። ከዮዳሄ ሞት በኋላ የይሁዳ ሹማምት መጥተው ለንጉሡ ታማኝነታቸውን ገለጹ፤ ንጉሡም አደመጣቸው። እነርሱም የአባቶቻቸውን አምላክ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ትተው፣ የአሼራን ዐምዶችና ጣዖታትን አመለኩ፤ በበደላቸውም ምክንያት የእግዚአብሔር ቍጣ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ መጣ። ወደ እግዚአብሔር ይመልሷቸው ዘንድ እርሱ ነቢያቱን ወደ ሕዝቡ ሰደደ፤ ነቢያቱም መሰከሩባቸው፤ እነርሱ ግን አላዳመጡም። የእግዚአብሔርም መንፈስ በካህኑ በዮዳሄ ልጅ በዘካርያስ ላይ መጣ፤ እርሱም በሕዝቡ ፊት ቆሞ፣ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ለምን ትተላለፋላችሁ? አይሳካላችሁም፤ እናንተ እግዚአብሔርን ስለ ተዋችሁት እርሱም ትቷችኋል’ ” አላቸው። እነርሱ ግን አሤሩበት፤ በንጉሡም ትእዛዝ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አደባባይ ላይ በድንጋይ ወግረው ገደሉት። ንጉሥ ኢዮአስ የዘካርያስ አባት ዮዳሄ ያደረገለትን ቸርነት አላሰበም፤ በዚህ ፈንታ ልጁን ገደለው፤ በሚሞትበትም ጊዜ፣ “እግዚአብሔር ይየው፤ እርሱው ይበቀልህ” አለ። በዓመቱም መጨረሻ፣ የሶርያ ሰራዊት በኢዮአስ ላይ ዘመተ፤ ይሁዳንና ኢየሩሳሌምንም ወርሮ የሕዝቡን መሪዎች ሁሉ ደመሰሰ፤ ምርኮውንም ሁሉ ወደ ንጉሡ ወደ ደማስቆ ላከ። የሶርያ ሰራዊት ሰዎች ጥቂት ቢሆኑም እንኳ እግዚአብሔር በጣም የሚበልጠውን ሰራዊት በእጃቸው አሳልፎ ሰጠ፤ ይሁዳ የአባቶቹን አምላክ እግዚአብሔርን ስለ ተወ፣ በኢዮአስ ላይ ተፈረደበት። ሶርያውያንም በወጡ ጊዜ ኢዮአስን ክፉኛ አቍስለው፣ ጥለውት ሄዱ፤ የካህኑን የዮዳሄን ልጅ ስለ ገደለም፣ ሹማምቱ አሢረውበት በዐልጋው ላይ እንዳለ ገደሉት። በዚህ ሁኔታም ሞቶ በዳዊት ከተማ ተቀበረ እንጂ በነገሥታቱ መቃብር አልተቀበረም። በርሱ ላይ ያሤሩትም የአሞናዊቱ የሰምዓት ልጅ ዛባድና የሞዓባዊቱ የሰማሪት ልጅ ዮዛባት ነበሩ። የወንዶች ልጆቹ ታሪክ፣ ስለ እርሱ የተነገሩት ብዙ ትንቢቶችና የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መታደስ በነገሥታቱ የታሪክ መዛግብት ተጽፈዋል። ልጁ አሜስያስም በርሱ ፈንታ ነገሠ።
2 ዜና መዋዕል 24:1-27 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ኢዮአስም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሰባት ዓመት ልጅ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም አርባ ዓመት ነገሠ፤ እናቱም ሳብያ የተባለች የቤርሳቤህ ሴት ነበረች። በካህኑም በዮዳሄ ዘመን ሁሉ ኢዮአስ በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገር አደረገ። ዮዳሄም ሁለት ሚስቶች አጋባው፤ ወንዶችና ሴቶችም ልጆችንም ወለደ። ከዚህም በኋላ ኢዮአስ የእግዚአብሔርን ቤት ይጠግን ዘንድ አሰበ። ካህናትንና ሌዋውያንን ሰብስቦ “ወደ ይሁዳ ከተሞች ውጡ፤ የአምላካችሁንም ቤት በየዓመቱ ለማደስ ከእስራኤል ሁሉ ገንዘብን ሰብስቡ፤ ነገሩንም ፈጥናችሁ አድርጉ” አላቸው። ሌዋውያን ግን ቸል አሉ። ንጉሡም አለቃውን ዮዳሄን ጠርቶ “የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ ስለ ምስክሩ ድንኳን የእስራኤል ጉባኤ እንዲያወጣ ያዘዘውን ግብር ከይሁዳና ከኢየሩሳሌም ያመጡ ዘንድ ስለ ምን ሌዋውያንን አላተጋሃቸውም?” አለ። ጎቶሊያ ከሐዲት ነበረችና ልጆችዋም የእግዚአብሔርን ቤት አፍርሰዋልና፤ በእግዚአብሔርም ቤት ተቀድሶ የነበረውን ሁሉ ለበኣሊም ሰጥተዋልና። ንጉሡም አዘዘ፤ ሣጥንም ሠርተው በእግዚአብሔር ቤት በር አጠገብ በስተ ውጭ አኖሩት። የእግዚአብሔርም ባሪያ ሙሴ በምድረ በዳ በእስራኤል ላይ ያዘዘውን ግብር ለእግዚአብሔር ያመጡ ዘንድ በይሁዳና በኢየሩሳሌም አዋጅ ነገሩ። አለቆቹና ሕዝቡም ሁሉ ደስ ብሎአቸው አቀረቡት፤ እስኪሞላም ድረስ በሣጥኑ ውስጥ ጣሉት። ሣጥኑም በሌዋውያን እጅ ወደ ንጉሡ ሹማምት በደረሰ ጊዜ፥ ብዙ ገንዘብም እንዳለበት ባየ ጊዜ፥ የንጉሡ ጸሐፊና የዋነኛው ካህን ሹም እየመጡ ብሩን ከሣጥን ያወጡ ነበር፤ ሣጥኑንም ደግሞ ወደ ስፍራው ይመልሱት ነበር። እንዲሁም በየቀኑ ያደርጉ ነበር፤ ብዙም ገንዘብ አከማቹ። ንጉሡና ዮዳሄም በእግዚአብሔር ቤት ሥራ ላይ ለተሾሙት ሰጡአቸው፤ እነርሱም የእግዚአብሔርን ቤት የሚጠግኑትን ጠራቢዎችንና አናጢዎችን፥ የእግዚአብሔርንም ቤት የሚያድሱትን የብረትና የናስ ሠራተኞችን ይገዙበት ነበር። ሠራተኞችም ሠሩ፤ የፈረሰውም በእጃቸው ተጠገነ፤ የእግዚአብሔርንም ቤት እንደ ቀድሞው ሥራ መለሱ፤ አጽንተውም አቆሙት። በጨረሱም ጊዜ የተረፈውን ገንዘብ በንጉሡና በዮዳሄ ፊት አመጡ፤ እነርሱም ለእግዚአብሔር ቤት ዕቃ፥ ለአገልግሎትና ለቍርባን ዕቃ፥ ለጭልፋዎችም፥ ለወርቅና ለብርም ዕቃ አደረጉት። በዮዳሄም ዘመን ሁሉ ለእግዚአብሔር ቤት የሚቃጠል መሥዋዕት ሁልጊዜ ያቀርቡ ነበር። ዮዳሄም ሸመገለ፤ ዕድሜም ጠግቦ ሞተ፤ በሞተ ጊዜ ዕድሜው መቶ ሠላሣ ዓመት ነበረ። ከእስራኤልም ጋር፥ ከእግዚአብሔርና ከቤቱም ጋር ቸርነትን ሠርቶአልና በዳዊት ከተማ ከነገሥታቱ ጋር ቀበሩት። ዮዳሄም ከሞተ በኋላ የይሁዳ አለቆች ገብተው ለንጉሡ እጅ ነሡ፤ ንጉሡም እሺ አላቸው። የአባቶቻቸውንም አምላክ እግዚአብሔርን ትተው የማምለኪያ ዐጸዶችንና ጣዖታትን አመለኩ፤ በዚህ በደላቸውም ምክንያት በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ ቍጣ ወረደ። ወደ እግዚአብሔርም ይመልሱአቸው ዘንድ ነቢያትን ይሰድድላቸው ነበር፤ መሰከሩባቸውም፤ እነርሱ ግን አላደመጡም። የእግዚአብሔርም መንፈስ በካህኑ በዮዳሄ ልጅ በዘካርያስ ላይ መጣ፤ እርሱም በሕዝቡ ፊት ቆመና “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ‘የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ለምን ትተላለፋላችሁ? መልካምም አይሆንላችሁም፤ እግዚአብሔርን ስለ ተዋችሁ እርሱ ትቶአችኋል’” አላቸው። ተማማሉበትም በንጉሡም ትእዛዝ በእግዚአብሔር ቤት አደባባይ ውስጥ በድንጋይ ወገሩት። እንዲሁም ንጉሡ ኢዮአስ ዮዳሄ ያደረገለትን ቸርነት አላሰበም፤ ልጁንም ዘካርያስን አስገደለው፤ እርሱም ሲሞት “እግዚአብሔር ይየው፤ ይፈልገውም” አለ። ዓመቱም ካለፈ በኋላ የሶርያውያን ሠራዊት መጡበት፤ ወደ ይሁዳና ወደ ኢየሩሳሌምም መጥተው ከሕዝቡ መካከል የሕዝቡን አለቆች ሁሉ አጠፉ፤ ምርኮአቸውንም ሁሉ ወደ ንጉሡ ወደ ደማስቆ ላኩ። የሶርያውያንም ሠራዊት ቍጥር ጥቂት ሆኖ ሳለ እግዚአብሔር ታላቅን ሠራዊት አሳልፎ በእጃቸው ሰጣቸው፤ ይህም የሆነው የአባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርን ትተው ስለ ነበረ ነው። እነርሱም በኢዮአስ ላይ ፍርድ ፈረዱበት። ከእርሱም ዘንድ አልፈው ከሄዱ በኋላ እጅግ ታምሞ ነበር፤ የገዛ ባሪያዎቹም ስለ ካህኑ ስለ ዮዳሄ ልጅ ተበቅለው ተማማሉበት፤ በአልጋውም ላይ ገደሉት፤ ሞተም፤ በዳዊት ከተማ እንጂ በነገሥታት መቃብር አልቀበሩትም። የተማማሉበትም የአሞናዊቱ የሰምዓት ልጅ ዛባድ፥ የሞዓባዊቱም የሰማሪት ልጅ ዮዛባት ነበሩ። የልጆቹና በእርሱ ላይ የተደረገው ነገር የእግዚአብሔርንም ቤት ማደሱ፥ እነሆ፥ በነገሥታቱ መጽሐፍ ተጽፎአል። ልጁም አሜስያስ በእርሱ ፋንታ ነገሠ።
2 ዜና መዋዕል 24:1-27 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ኢዮአስ በሰባት ዓመቱ የይሁዳ ንጉሥ ሆነ፤ መኖሪያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ አርባ ዓመት ገዛ፤ እናቱም ጺቢያ ተብላ የምትጠራ የቤርሳቤህ ከተማ ተወላጅ ነበረች፤ ካህኑ ዮዳሄ በሕይወት በነበረበት ዘመን ሁሉ ኢዮአስ፥ እግዚአብሔርን ደስ የሚያስኝ ነገር ያደርግ ነበር፤ ዮዳሄ ለንጉሥ ኢዮአስ ሁለት ሚስቶችን መርጦለት ነበር፤ እነርሱም ወንዶችንና ሴቶች ልጆችን ወልደውለታል። ኢዮአስ ከነገሠ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ቤተ መቅደሱን ለማደስ ወሰነ፤ ስለዚህ ካህናቱንና ሌዋውያኑን በአንድነት ሰብስቦ “ወደ ይሁዳ ከተሞች ሄዳችሁ ለአምላካችሁ ቤት ዓመታዊ እድሳት የሚሆን በቂ ገንዘብ ከእስራኤል ሕዝብ ሁሉ በፍጥነት ሰብስቡ” ሲል አዘዛቸው፤ ሌዋውያኑ ግን ቸል በማለት ዘገዩ፤ ስለዚህ ንጉሥ ኢዮአስ የሌዋውያኑን መሪ ዮዳሄን ጠርቶ፦ “የእግዚአብሔር አገልጋይ ሙሴ፥ እግዚአብሔር ለሚመለክበት ድንኳን አገልግሎት የሚሆን ግብር የእስራኤል ሕዝብ እንዲያዋጣ ያዘዘውን ሌዋውያኑ ከይሁዳና ከኢየሩሳሌም ሕዝብ ሰብስበው ያመጡ ዘንድ ስለምን አላተጋሃቸውም?” አለ። የዚያች ዐታልያ ተብላ የምትጠራ ክፉይቱ ሴት ተከታዮች ቤተ መቅደሱን አበላሽተውት ነበር፤ ንዋያተ ቅድሳቱን እንኳ ሳይቀር ባዓል ተብሎ ለሚጠራው ጣዖት በሚደረገው የአምልኮ ሥነ ሥርዓት ይጠቀሙባቸው ነበር። ንጉሥ ኢዮአስ “የገንዘብ መሰብሰቢያ ሣጥን ሠርታችሁ በቤተ መቅደሱ ቅጽር በር በስተውጭ በኩል አኑሩት” ሲል ሌዋውያኑን አዘዘ፤ ከዚህ በኋላ ሌዋውያኑ በመላው ኢየሩሳሌምና በይሁዳ የሚገኙ ነዋሪዎች ሁሉ የእግዚአብሔር አገልጋይ ሙሴ በምድረ በዳ ለመጀመሪያ ጊዜ ከእስራኤል ሕዝብ እንዲሰበሰብ ያዘዘውን ግብር ለእግዚአብሔር እንዲያመጡ ትእዛዝ አስተላለፉ፤ ይህም ሕዝቡንና መሪዎቹን ሁሉ ደስ ስላሰኛቸው ገንዘብ በማምጣት ሣጥኑን ሞሉት። ሌዋውያኑም ሣጥኑን ወስደው ኀላፊዎች ለሆኑት ለመንግሥት ባለሥልጣኖች በየቀኑ ያስረክቡት ነበር። ሣጥኑ በገንዘብ በሞላ ቊጥር የቤተ መንግሥቱ ጸሐፊና የካህናት አለቃው እንደ ራሴ ገንዘቡን ከሣጥኑ አውጥተው ከወሰዱ በኋላ፥ ሣጥኑን መልሰው በቦታው ያኖሩት ነበር፤ በዚህ ዐይነት ብዙ ገንዘብ ሰበሰቡ። ንጉሡና ካህኑ ዮዳሄ ገንዘቡን የቤተ መቅደሱ እድሳት ኀላፊዎች ለሆኑት ሰዎች ይሰጡአቸው ነበር፤ እነዚህም ኀላፊዎች ገንዘቡን ቤተ መቅደሱን የሚጠግኑ ግንበኞችን፥ አናጢዎችንና ብረታ ብረት ሠራተኞችን ይቀጥሩበት ነበር፤ ሠራተኞቹም በብርቱ ትጋት በመሥራት ቤተ መቅደሱን ቀድሞ በነበረው ሁኔታ በጥሩ አኳኋን አደሱት። የእድሳቱ ሥራ ባለቀ ጊዜም ቀሪው ገንዘብ ለንጉሥ ኢዮአስና ለካህኑ ዮዳሄ ተሰጠ፤ እነርሱም በዚህ ወርቅ ለቤተ መቅደሱ አገልግሎትና ለመሥዋዕት የሚውሉ ሳሕኖችንና ሌሎች ልዩ ልዩ ዕቃዎችን ገዙ። ዮዳሄ በሕይወት በነበረበት ዘመን ሁሉ ዘወትር በቤተ መቅደስ መሥዋዕት ይቀርብ ነበር፤ ዮዳሄ በዕድሜ እጅግ ከሸመገለ በኋላ በአንድ መቶ ሠላሳ ዓመቱ ሞተ፤ እርሱ ለእስራኤል ሕዝብ፥ ለእግዚአብሔርና ለቤተ መቅደሱ ስለ ሰጠው አገልግሎት ውለታ በዳዊት ከተማ በሚገኘው በነገሥታት መካነ መቃብር ቀበሩት። ዮዳሄ ከሞተ በኋላ ግን የይሁዳ መሪዎች ወደ ንጉሥ ኢዮአስ መጥተው እጅ በመንሣት ፍላጎታቸውን ገለጡለት፤ እርሱም በሐሳቡ ተስማማ፤ ስለዚህ ሰዎቹም በቀድሞ አባቶቻቸው አምላክ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ መስገድ ትተው፥ አሼራ ተብላ ለምትጠራ ሴት አምላክ ጣዖቶችና ምስሎች መስገድ ጀመሩ። ይህንንም ኃጢአት በመሥራታቸው የእግዚአብሔር ቊጣ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ ወረደ። እግዚአብሔር ወደ እርሱ እንዲመለሱ አጥብቀው ያሳስቡአቸው ዘንድ ነቢያትን ላከ፤ መሰከሩባቸውም፤ እነርሱ ግን አላዳመጡም፤ ከዚህ በኋላ የእግዚአብሔር መንፈስ በካህኑ በዮዳሄ ልጅ በዘካርያስ ላይ ወረደ፤ እርሱም ሕዝቡ ሊያዩት በሚችሉበት ከፍ ያለ ስፍራ ላይ ቆሞ “እግዚአብሔር ‘ትእዛዞቼን ስለምን ትተላለፋላችሁ? በገዛ ራሳችሁስ ላይ ስለምን ጥፋትን ታመጣላችሁ?’ ሲል ይጠይቃችኋል፤ እንግዲህ እናንተ ስለ ተዋችሁት እርሱም ትቶአችኋል” አላቸው። ንጉሥ ኢዮአስ በዘካርያስ ላይ በተደረገው ሤራ ተባባሪ ሆነ፤ ሕዝቡም በንጉሡ ትእዛዝ ዘካርያስን በቤተ መቅደሱ አደባባይ ውስጥ በድንጋይ ወግረው ገደሉት። ንጉሥ ኢዮአስ የዘካርያስ አባት ዮዳሄ ያደረገለትን ቅን አገልግሎት በመዘንጋት ዘካርያስን ገደለ፤ ዘካርያስም ሊሞት ሲያጣጥር ሳለ “እግዚአብሔር ይህን ግፍ ተመልክቶ ይቅጣህ” አለ። በዚያን ዓመት በመከር ወራት የሶርያ ወታደሮች በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ አደጋ በመጣል መሪዎቹን ሁሉ ገደሉ፤ እጅግ ብዙ የሆነ ምርኮም ይዘው ወደ ደማስቆ ተመለሱ፤ የሶርያ ሠራዊት ቊጥር ጥቂት ነበር፤ ነገር ግን እጅግ ብዙ የሆነውን የይሁዳን ሠራዊት ድል እንዲያደርግ እግዚአብሔር ፈቀደ፤ ይህም የሆነው እነርሱ የቀድሞ አባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርን ስለ ተዉ ነው፤ በዚህ ዐይነት በኢዮአስ ላይ ትክክለኛ ፍርድ ተፈጸመበት። በብርቱም ቈስሎ ነበር፤ የጠላት ሠራዊት ከዚያ ተነሥቶ ከሄደ በኋላ ባለሟሎቹ ከሆኑት ባለሥልጣኖች የካህኑን የዮዳሄን ልጅ ደም ለመበቀል በንጉሡ ላይ አሢረው በአልጋው ላይ እንዳለ ገደሉት፤ ንጉሡም በዳዊት ከተማ ተቀበረ፤ ይሁን እንጂ በነገሥታት መካነ መቃብር አልተቀበረም። በንጉሡ ላይ ያሤሩትም ሺምዓት ተብላ የምትጠራ የዐሞን ተወላጅ ልጅ የሆነው ዛባድና ሺምሪት ተብላ የምትጠራ የሞአብ ተወላጅ ልጅ የሆነው ይሆዛባድ ናቸው። የኢዮአስ ልጆች ታሪክ፥ በኢዮአስ ላይ ተነግረው የነበሩት የትንቢት ቃላትና ኢዮአስ ቤተ መቅደሱን እንዴት እንዳደሰ በነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ መግለጫ ውስጥ ተመዝግቦ ይገኛል፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ልጁ አሜስያስ ነገሠ።
2 ዜና መዋዕል 24:1-27 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ኢዮአስም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሰባት ዓመት ልጅ ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም አርባ ዓመት ነገሠ፤ እናቱም ሳብያ የተባለች የቤርሳቤህ ሴት ነበረች። በካህኑም በዮዳሄ ዘመን ሁሉ ኢዮአስ በጌታ ፊት ቅን ነገር አደረገ። ዮዳሄም ሁለት ሚስቶች አጋባው፤ ወንዶችና ሴቶችም ልጆች ወለደ። ከዚህም በኋላ ኢዮአስ የጌታን ቤት ለማደስ አሰበ። ካህናትንና ሌዋውያንንም ሰብስቦ እንዲህ አላቸው፦ “ወደ ይሁዳ ከተሞች ውጡ፥ የአምላካችሁንም ቤት በየዓመቱ ለማደስ ከእስራኤል ሁሉ ገንዘብን ሰብስቡ፤ ነገሩንም ፈጥናችሁ አድርጉ።” ሌዋውያን ግን ቸል አሉ። ንጉሡም አለቃውን ዮዳሄን ጠርቶ እንዲህ አለው፦ “የጌታ ባርያ ሙሴ ስለ ምስክሩ ድንኳን የእስራኤል ጉባኤ እንዲያወጣ ያዘዘውን ግብር ከይሁዳና ከኢየሩሳሌም ላይ ሌዋውያን እንዲሰበስቡ ለምን አላተጋሃቸውም?” ጎቶሊያ ከሐዲት ነበረችና ልጆችዋም የጌታን ቤት አፍርሰዋልና፤ በጌታም ቤት ተቀድሶ የነበረውን ሁሉ ለባዓል ተጠቅመውበታልና። ንጉሡም አዘዘ፥ ሣጥንም ሠርተው በጌታ ቤት በር አጠገብ በስተ ውጭ አኖሩት። የጌታም ባርያ ሙሴ በምድረ በዳ በእስራኤል ላይ ያዘዘውን ግብር ለጌታ እንዲያመጡ በይሁዳና በኢየሩሳሌም አዋጅ ነገሩ። አለቆቹና ሕዝቡም ሁሉ ደስ ብሎአቸው ግብሩን አመጡ፥ እስኪሞላም ድረስ በሣጥኑ ውስጥ ጣሉት። ሣጥኑም በሌዋውያን እጅ ወደ ንጉሡ ሹማምንት በመጣ ጊዜ፥ ብዙ ገንዘብም እንዳለበት ባየ ጊዜ፥ የንጉሡ ጸሐፊና የታላቁ ካህን ሹም እየመጡ ብሩን ከሣጥኑ ውስጥ ያወጡ ነበር፥ ሣጥኑንም ደግሞ ወደ ስፍራው ይመልሱት ነበር። እንዲህም በየቀኑ ያደርጉ ነበር፥ ብዙም ገንዘብ አከማቹ። ንጉሡና ዮዳሄም በጌታ ቤት ሥራ ላይ ለተሾሙት ሰጡአቸው፤ እነርሱም የጌታን ቤት የሚጠግኑትን ጠራቢዎችንና አናጢዎችን፥ የጌታንም ቤት የሚያድሱትን የብረትና የናስ ሠራተኞችን ይቀጥሩበት ነበር። ሠራተኞችም ሠሩ፥ የፈረሰውም በእጃቸው ተጠገነ፤ የጌታንም ቤት ቀድሞ ወደ ነበረበት ሁኔታ መለሱት፥ አጽንተውም አቆሙት። በጨረሱም ጊዜ የተረፈውን ገንዘብ በንጉሡና በዮዳሄ ፊት አመጡ፤ በእርሱም ለጌታ የቤት ዕቃ፥ የአገልግሎትና የቁርባን ዕቃ፥ ሙዳዮቹም፥ የወርቅና የብርም ዕቃ ተሠራበት። በዮዳሄም ዘመን ሁሉ በጌታ ቤት የሚቃጠል መሥዋዕት ሁልጊዜ ያቀርቡ ነበር። ዮዳሄም ሸመገለ፥ ዕድሜም ጠግቦ ሞተ፤ በሞተ ጊዜ ዕድሜው መቶ ሠላሣ ዓመት ነበረ። በእስራኤልም፥ ለጌታና ለቤቱም ቸርነትን ሠርቶአልና በዳዊት ከተማ ከነገሥታቱ ጋር ቀበሩት። ዮዳሄም ከሞተ በኋላ የይሁዳ አለቆች ገብተው ለንጉሡ እጅ ነሡ፤ በዚያን ጊዜ ንጉሡ ሰማቸው። የአባቶቻቸውንም አምላክ ጌታን ትተው የማምለኪያ ዐፀዶችንና ጣዖታትን አመለኩ፤ በዚህ በደላቸውም ምክንያት በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ ቁጣ ወረደ። ወደ ጌታም እንዲመልሱአቸው ነቢያትን ይልክላቸው ነበር፤ መሰከሩባቸውም፥ እነርሱ ግን አላደመጡም። የጌታም መንፈስ በካህኑ በዮዳሄ ልጅ በዘካርያስ ላይ መጣ፤ እርሱም በሕዝቡ ፊት ቆሞ እንዲህ አላቸው፦ “ጌታ እንዲህ ይላል፦ ‘የጌታን ትእዛዝ ለምን ትተላለፋላችሁ? ለእናተም አሳካላችሁም፤ ጌታን ስለ ተዋችሁ እርሱ ትቶአችኋል።’ ” ተማማሉበትም በንጉሡም ትእዛዝ በጌታ ቤት አደባባይ ውስጥ በድንጋይ ወገሩት። እንዲሁም ንጉሡ ኢዮአስ ዮዳሄ ያደረገለትን ቸርነት አላሰበም፥ ልጁንም ዘካርያስን አስገደለው፤ እርሱም ሲሞት፦ “ጌታ ይየው፥ ይበቀለውም” አለ። በዓመቱ መጨረሻ በኢዮአስ ላይ የሶርያውያን ሠራዊት መጡበት፤ ወደ ይሁዳና ወደ ኢየሩሳሌምም መጥተው ከሕዝቡ መካከል የሕዝቡን አለቆች ሁሉ አጠፉ፥ ምርኮአቸውንም ሁሉ ወደ ንጉሡ ወደ ደማስቆ ላኩ። የሶርያውያንም ሠራዊት ቍጥር ጥቂት ሆኖ ሳለ ጌታ ታላቅን ሠራዊት አሳልፎ በእጃቸው ሰጣቸው፤ ይህም የሆነው የአባቶቻቸውን አምላክ ጌታን ትተው ስለ ነበረ ነው። እነርሱም በኢዮአስ ላይ ፍርድ ፈረዱበት። እርሱንም ትተውት በሄዱ ጊዜ በጽኑ አቊስለውት ነበር፤ የገዛ ባርያዎቹም የካህኑ የዮዳሄን ልጅ ደም ለመበቀል ሲሉ አሴሩበት፥ በአልጋውም ላይ ገደሉት፥ ሞተም፤ በዳዊት ከተማ እንጂ በነገሥታት መቃብር አልቀበሩትም። ያሴሩበትም የአሞናዊቱ የሰምዓት ልጅ ዛባድ፥ የሞዓባዊቱም የሰማሪት ልጅ ዮዛባት ነበሩ። የልጆቹና በእርሱ ላይ የተደረገው ነገር የጌታንም ቤት ማደሱ፥ እነሆ፥ በነገሥታቱ መጽሐፍ ተጽፎአል። ልጁም አሜስያስ በእርሱ ፋንታ ነገሠ።