2 ዜና መዋዕል 18:2-34 - Compare All Versions
2 ዜና መዋዕል 18:2-34 NASV (አዲሱ መደበኛ ትርጒም)
ከጥቂት ዓመታት በኋላም አክዓብን ሊጐበኝ ወደ ሰማርያ ወረደ። አክዓብም ለርሱና ዐብሮት ለነበረው ሕዝብ ብዙ በግና በሬ ዐረደ፤ ከዚያም በራሞት ገለዓድ ላይ አደጋ እንዲጥል አግባባው። የእስራኤል ንጉሥ አክዓብም የይሁዳን ንጉሥ ኢዮሣፍጥን፣ “ራሞት ገለዓድን ለመውጋት ዐብረኸኝ ትሄዳለህን?” ሲል ጠየቀው። ኢዮሣፍጥም፣ “እኔ እንደ አንተው ነኝ፤ ሕዝቤም እንደ ሕዝብህ ነው፤ በጦርነቱ ዐብረናችሁ እንሰለፋለን” አለው። ደግሞም ኢዮሣፍጥ የእስራኤልን ንጉሥ፣ “በመጀመሪያ ግን የእግዚአብሔርን ሐሳብ ጠይቅ” አለው። ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥ አራት መቶ ነቢያትን በአንድነት ሰብስቦ፣ “በገለዓድ በምትገኘው ራሞት ላይ እንዝመት ወይስ እንቅር?” ሲል ጠየቃቸው። እነርሱም፣ “እግዚአብሔር በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታልና ዝመትባት” አሉት። ኢዮሣፍጥ ግን፣ “እንጠይቀው ዘንድ ሌላ የእግዚአብሔር ነቢይ እዚህ የለምን?” አለ። የእስራኤልም ንጉሥ ለኢዮሣፍጥ፣ “መኖሩንማ በርሱ አማካይነት የእግዚአብሔርን ፈቃድ የምንጠይቀው አንድ ነቢይ አሁንም አለ፤ ነገር ግን ምን ጊዜም ስለ እኔ ክፉ እንጂ መልካም ትንቢት ተናግሮ ስለማያውቅ እጠላዋለሁ፤ እርሱም የይምላ ልጅ ሚክያስ ነው” አለ። ኢዮሣፍጥም፣ “ንጉሡ እንዲህ ማለት አይገባውም” አለው። ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥ ከሹማምቱ አንዱን ጠርቶ “የይምላን ልጅ ሚክያስን በፍጥነት አምጣው” አለው። የእስራኤል ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ አልባሰ መንግሥታቸውን ለብሰው፣ በሰማርያ ቅጥር በር መግቢያ አጠገብ ባለው ዐውድማ ላይ በየዙፋናቸው ተቀምጠው፣ ነቢያቱ ሁሉ በፊታቸው ትንቢት ይናገሩ ነበር። በዚህ ጊዜ፣ የክንዓና ልጅ ሴዴቅያስ የብረት ቀንዶች ሠርቶ፣ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ሶርያውያን እስኪጠፉ ድረስ በእነዚህ ትወጋቸዋለህ’ ” አለ። የቀሩትም ነቢያት ሁሉ፣ “እግዚአብሔር በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታልና፣ በገለዓድ በምትገኘው ራሞት ላይ ዝመትባት” በማለት ተመሳሳይ ትንቢት ይናገሩ ነበር። ሚክያስን ሊጠራ ሄዶ የነበረውም መልእክተኛ፣ “እነሆ፣ ሌሎቹ ነቢያት በአንድ አፍ ሆነው፣ ለንጉሡ መልካምን ነገር እየተነበዩ ነው፤ እባክህ የአንተም ቃል እንደ ቃላቸው ይሁን፤ ንጉሡን ደስ የሚያሠኘውን ተናገር” አለው። ሚክያስ ግን፣ “ሕያው እግዚአብሔርን! አምላኬ የሚለውን ብቻ እነግረዋለሁ” አለ። ወደ ንጉሡ በመጣ ጊዜ ንጉሡ፣ “ሚክያስ ሆይ፤ በገለዓድ በምትገኘው ራሞት ላይ እንዝመት ወይስ እንቅር?” ሲል ጠየቀው። እርሱም መልሶ፣ “ሂዱና ድል አድርጉ፤ በእጃችሁ ዐልፈው ይሰጣሉና” አለው። ንጉሡም፣ “ከእውነት በቀር ምንም ነገር በእግዚአብሔር ስም እንዳትነግረኝ የማምልህ ስንት ጊዜ ነው?” አለው። ከዚያም ሚክያስ፣ “እስራኤል ሁሉ እረኛ እንደሌላቸው በጎች በተራሮች ላይ ተበታትነው አየሁ፤ እግዚአብሔርም፣ ‘እነዚህ ሰዎች ጌታ የላቸውም፤ እያንዳንዱም በሰላም ወደየቤቱ ይመለስ’ ብሏል” ሲል መለሰ። የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮሣፍጥን፣ “ስለ እኔ ክፉ ብቻ እንጂ፣ መልካም ትንቢት አይናገርም አላልሁህምን?” አለው። ከዚያም ሚክያስ እንዲህ አለ፤ “እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቃል ስማ፤ እግዚአብሔር በዙፋኑ ላይ ተቀምጦ፣ የሰማይም ሰራዊት ሁሉ በቀኙና በግራው ቆመው አየሁ። እግዚአብሔርም፣ ‘የእስራኤል ንጉሥ አክዓብ በገለዓድ በምትገኘው ራሞት ላይ ዘምቶ እዚያው እንዲሞት ማን ያሳስተው?’ አለ። “አንዱ አንድ ሐሳብ፣ ሌላውም ሌላ ሐሳብ አቀረበ። ከዚያም አንድ መንፈስ መጥቶ፣ በእግዚአብሔር ፊት በመቆም፣ ‘እኔ አሳስተዋለሁ’ አለ። “እግዚአብሔርም፣ ‘እንዴት አድርገህ?’ ሲል ጠየቀው። “እርሱም፣ ‘እኔ እወጣና በገዛ ነቢያቱ ሁሉ አፍ የሐሰት መንፈስ እሆናለሁ’ አለ። “እግዚአብሔርም፣ ‘ታሳስተዋለህ፤ ይሳካልሃልም፤ እንግዲህ ውጣና አድርግ፤’ አለው። “ስለዚህ እነሆ፣ እግዚአብሔር በእነዚህ ነቢያትህ አፍ የሐሰት መንፈስ አኖረ፤ እግዚአብሔርም ጥፋት እንደሚያመጣብህ ተናግሯል”። ከዚያም የክንዓና ልጅ ሴዴቅያስ ወጥቶ ሚክያስን በጥፊ መታውና፣ “ለመሆኑ የእግዚአብሔር መንፈስ በየት በኩል ዐልፎኝ ነው አንተን ያናገረህ?” አለው። ሚክያስም፣ “ለመሸሸግ ወደ እልፍኝህ በምትሄድበት በዚያ ዕለት ታገኘዋለህ” አለው። ከዚያም የእስራኤል ንጉሥ እንዲህ ሲል አዘዘ፤ “ሚክያስን ይዛችሁ ወደ ከተማዪቱ ገዥ ወደ አሞንና ወደ ንጉሡ ልጅ ወደ ኢዮአስ መልሱት፤ ከዚያም፣ ‘ንጉሡ፣ ይህን ሰው እስር ቤት አስገቡት፤ በደኅና እስክመለስም ድረስ፣ ከደረቅ እንጀራና ከውሃ በቀር ሌላ እንዳትሰጡት’ ብሏል በሏቸው” አለ። ሚክያስም፣ “አንተ በደኅና ከተመለስክማ እግዚአብሔር በእኔ አልተናገረም ማለት ነው!” አለ፤ ቀጥሎም፣ “እናንተ ሰዎች ሁላችሁ ስሙኝ” አለ። ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ወደ ራሞት ገለዓድ ወጡ። የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮሣፍጥን፣ “እኔ ልብሴን ለውጬ ወደ ጦርነቱ እገባለሁ፤ አንተ ግን ልብሰ መንግሥትህን ልበስ” አለው። ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥ ልብሱን ለውጦ ሌላ ሰው መስሎ ወደ ጦርነቱ ገቡ። በዚህ ጊዜ የሶርያ ንጉሥ የሠረገላ አዛዦቹን፣ “ከእስራኤል ንጉሥ በቀር፣ ትንሽም ሆነ ትልቅ ከሌላ ከማንም ጋራ እንዳትዋጉ” ብሎ አዝዟቸው ነበር። የሠረገላው አዛዦችም ኢዮሣፍጥን ባዩ ጊዜ፣ “የእስራኤል ንጉሥ ይህ ነው” ብለው አሰቡ፤ ሊወጉትም ከበቡት፤ ኢዮሣፍጥ ግን ጮኸ፤ እግዚአብሔርም ረዳው፤ አምላክም ከርሱ መለሳቸው፤ የሠረገላ አዛዦቹም የእስራኤል ንጉሥ አለመሆኑን በተረዱ ጊዜ እርሱን ከማሳደድ ተመለሱ። ይሁን እንጂ አንዱ ቀስቱን በነሲብ ቢያስፈነጥረው፣ በጥሩሩ መጋጠሚያዎች መካከል ዐልፎ የእስራኤልን ንጉሥ ወጋው። ንጉሡም ሠረገላ ነጂውን “ተመለስና ከጦርነቱ አውጣኝ፤ ቈስያለሁና” አለው። ጦርነቱም ቀኑን ሙሉ ተፋፍሞ ዋለ፤ በዚህ ጊዜ የእስራኤል ንጉሥ በሶርያውያን ፊት ለፊት በሠረገላው ላይ እስከ ምሽት ድረስ ተደግፎ ነበር፤ ፀሓይ ስትጠልቅም ሞተ።
2 ዜና መዋዕል 18:2-34 አማ05 (አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም)
ከጥቂት ዓመቶች በኋላም ኢዮሣፍጥ አክዓብን ለመጐብኘት ወደ ሰማርያ ከተማ ሄደ፤ አክዓብም ለኢዮሣፍጥና ለአጃቢዎቹ ክብር ብዙ በጎችንና የቀንድ ከብቶችን ዐርዶ ታላቅ ግብዣ አደረገ፤ አክዓብ በገለዓድ በሚገኘው በራሞት ከተማ ላይ አደጋ ለመጣል ይተባበረው ዘንድ ኢዮሣፍጥን አግባባው፤ “በራሞት ላይ አደጋ ለመጣል ከእኔ ጋር ትዘምታለህን?” ሲል ጠየቀው። ኢዮሣፍጥም “እኔ እንደ አንተ ነኝ፤ ሕዝቤም እንደ ሕዝብህ ነው፤ በጦርነቱም እንተባበርሃለን አለው። ነገር ግን አስቀድመን የእግዚአብሔርን ፈቃድ እንጠይቅ” አለው። ስለዚህ አክዓብ ቊጥራቸው አራት መቶ የሆነውን ነቢያት ጠርቶ “ወደ ራሞት ሄጄ ጦርነት ልክፈትን? ወይስ ልተው?” ሲል ጠየቃቸው። እነርሱም “ሄደህ አደጋ ጣልባት፤ እግዚአብሔርም ድልን ያቀዳጅሃል” ሲሉ መለሱለት። ኢዮሣፍጥ ግን “በእርሱ አማካይነት የእግዚአብሔርን ፈቃድ የምንጠይቅበት ሌላ ነቢይ በዚህ የለምን?” ሲል ጠየቀ። አክዓብም “የይምላ ልጅ የሆነ ሚክያስ ተብሎ የሚጠራ ሌላም ነቢይ አለ፤ ነገር ግን እርሱ ምንጊዜም ቢሆን ስለ እኔ ክፉ እንጂ መልካም የትንቢት ቃል ስለማይናገር እርሱን አልወደውም” ሲል መለሰለት። ኢዮሣፍጥም “አንተ ይህን ማለት አይገባህም!” አለው። ከዚህ በኋላ ንጉሥ አክዓብ ባለሟሎቹ ከሆኑት ባለሥልጣኖች አንዱን ጠርቶ “ሚክያስን ፈልገህ በማግኘት በፍጥነት እንዲመጣ አድርግ” ሲል አዘዘው። በዚህ ጊዜ ሁለቱ ነገሥታት ልብሰ መንግሥታቸውን ለብሰው በሰማርያ ቅጽር በር አጠገብ በውጪ በኩል በሚገኘው አውድማ በየዙፋናቸው ላይ ተቀምጠው ነበር፤ ነቢያቱም ሁሉ በነገሥታቱ ፊት ሆነው የትንቢት ቃል ይናገሩ ነበር፤ ከእነርሱም አንዱ የከናዕና ልጅ ሴዴቅያስ ከብረት ቀንዶችን ሠርቶ አክዓብን “እግዚአብሔር ‘በእነዚህ ቀንዶች ሶርያውያንን ወግተህ ፍጹም የሆነ ድልን ትቀዳጃለህ’ ይልሃል” አለው። ሌሎቹም ነቢያት ይህንኑ ቃል በመደገፍ “በራሞት ላይ ዝመት፤ ታሸንፋለህ፤ እግዚአብሔር ድልን ይሰጥሃል” አሉት። ሚክያስን ለመጥራት ሄዶ የነበረው መልእክተኛ በዚሁ ጊዜ ሚክያስ “ሌሎች ነቢያት በሙሉ ንጉሥ አክዓብ ድል የሚያደርግ መሆኑን የሚያረጋግጥ የትንቢት ቃል ተናግረዋል፤ ስለዚህ አንተም እንደ እነርሱ ብታደርግ ይሻልሃል” አለው። ሚክያስ ግን “እግዚአብሔር የሚገልጥልኝን ቃል ብቻ የምናገር መሆኔን በሕያው እግዚአብሔር ስም እምላለሁ!” ሲል መለሰለት። ሚክያስም ወደ ንጉሥ አክዓብ ፊት በቀረበ ጊዜ ንጉሡ “ሚክያስ ሆይ፥ ንጉሥ ኢዮሣፍጥና እኔ ወደ ራሞት ሄደን ጦርነት እንክፈት? ወይስ እንተው?” ሲል ጠየቀው። ሚክያስም “ዝመትባት! በእርግጥም ታሸንፋለህ፤ እግዚአብሔርም ድልን ያቀዳጅሃል” ሲል መለሰለት። አክዓብም “በእግዚአብሔር ስም ከእውነት በቀር እንዳትነግረኝ ብዬ የማስምልህ ስንት ጊዜ ነው?” አለው። ሚክያስም “መላው የእስራኤል ሠራዊት ጠባቂ እንደሌላቸው በጎች በኰረብቶች ላይ ተበታትነው አያለሁ፤ እግዚአብሔርም ‘እነዚህ ሰዎች መሪ የላቸውም፤ ስለዚህ ወደየቤታቸው በሰላም ይመለሱ’ ብሎአል” ሲል መለሰለት። አክዓብም ኢዮሣፍጥን “እርሱ ዘወትር ስለ እኔ ክፉ እንጂ መልካም የትንቢት ቃል አይናገርም ብዬህ አልነበረምን?” አለው። ሚክያስም የሚናገረውን የትንቢት ቃል በመቀጠል እንዲህ አለ፤ “እንግዲህ እግዚአብሔር የሚለውን ስማ! እግዚአብሔር በሰማይ ባለው ዙፋኑ ላይ ተቀምጦ መላእክቱም ሁሉ በቀኝና በግራው ቆመው አየሁ፤ እግዚአብሔርም ‘አክዓብ ወደ ራሞት ሄዶ በዚያ እንዲገደል ሊያሳስተው የሚችል ማን ነው?’ ሲል ጠየቀ፤ ከመላእክቱም መካከል አንዱ አንድ ነገር፥ ሌላው ሌላ ነገር በመግለጥ የተለያየ ሐሳብ አቀረቡ፤ በመጨረሻ ግን አንድ መንፈስ ወደ እግዚአብሔር ፊት ቀርቦ ‘እኔ ላሳስተው እችላለሁ’ አለ፤ እግዚአብሔርም ‘እንዴት አድርገህ ልታሳስተው ትችላለህ?’ አለው፤ መልአኩም ‘ሄጄ የአክዓብ ነቢያት ሁሉ ሐሰት እንዲናገሩ አደርጋለሁ’ ሲል መለሰ፤ እግዚአብሔርም ‘እንግዲያውስ ሄደህ አሳስተው፤ ይከናወንልሃል’ አለው።” ሚክያስም “እግዚአብሔር እንዴት አድርጎ በእነዚህ በነቢያትህ አንደበት የሐሰት መንፈስ እንዳስቀመጠ ታያለህን? ይህንንም ያደረገው በአንተ ላይ ጥፋትን ስለ ወሰነብህ ነው!” አለው። የከናዕና ልጅ ሴዴቅያስ ወደ ሚክያስ ቀረብ ብሎ በጥፊ መታውና “ኧረ ከመቼ ወዲህ ነው የእግዚአብሔር መንፈስ ከእኔ አልፎ አንተን ያነጋገረህ?” አለው። ሚክያስም “ወደ ጓዳ ሄደህ በምትሸሸግበት ጊዜ ታገኘዋለህ” ሲል መለሰለት። በዚህን ጊዜ ንጉሥ አክዓብ ከጦር መኰንኖቹ አንዱን “ሚክያስን ያዘው፤ ወደ ከተማይቱ ገዢ ወደ አሞንና ወደ ልዑል ዮአሽ ውሰደው፤ እኔም ከዘመቻ በደኅና እስክመለስ ድረስ በእስር ቤት አስገብተው ደረቅ እንጀራና ውሃ ብቻ እየሰጡት እንዲቈይ ያደርጉ ዘንድ በእኔ ስም ንገራቸው” ሲል አዘዘው። ሚክያስም “አንተ ከዘመቻ በደኅና ከተመለስክማ እግዚአብሔር በእኔ አማካይነት አልተናገረም ማለት ነው!” አለው። ቀጥሎም ድምፁን ከፍ በማድረግ “በዚህ የምትገኙ ሁሉ እኔ የተናገርኩትን ሁሉ ልብ ብላችሁ አድምጡ!” አለ። ከዚህ በኋላ የእስራኤል ንጉሥ አክዓብና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ በገለዓድ ምድር ወደምትገኘው ወደ ራሞት ገለዓድ ወጡ፤ አክዓብም ኢዮሣፍጥን “ወደ ጦርነት ለመሄድ ስንነሣ እኔ ሌላ ሰው መስዬ ለመታየት ሌላ ልብስ እለብሳለሁ፤ አንተ ግን ልብሰ መንግሥትህን ልበስ” አለው፤ ስለዚህ የእስራኤል ንጉሥ አክዓብ ሌላ ልብስ ለብሶ ማንነቱን በመሰወር ዘመተ። የሶርያ ንጉሥም “የእስራኤል ንጉሥ አክዓብን ነጥላችሁ ግደሉ እንጂ በሌላ በማንም ላይ አደጋ አትጣሉ” ሲል ለሠረገላ ጦር አዛዦች ትእዛዝ አስተላለፈ። ስለዚህ ንጉሥ ኢዮሣፍጥን ባዩ ጊዜ የእስራኤል ንጉሥ ስለ መሰላቸው በእርሱ ላይ አደጋ ለመጣል ከበቡት፤ ነገር ግን ኢዮሣፍጥ ጮኸ፤ እግዚአብሔር አምላክም ከእነርሱ እጅ በመታደግ አዳነው፤ እነርሱም በእርሱ ላይ አደጋ ከመጣል ተገቱ። የሠረገላዎቹ አዛዦች ኢዮሣፍጥ የእስራኤል ንጉሥ አለመሆኑን በተገነዘቡ ጊዜ እርሱን ማሳደድ ተዉ፤ ይሁን እንጂ አንድ የሶርያ ወታደር በአጋጣሚ ያስፈነጠረው ፍላጻ በጥሩሩ መጋጠሚያ በኩል አልፎ አክዓብን መታው፤ ንጉሥ አክዓብም የሠረገላ ነጂውን “እኔ ቈስያለሁ! ስለዚህ ሠረገላውን መልሰህ ከጦር ሜዳው ውጣ!” ሲል አዘዘው። ጦርነቱም በተፋፋመ ጊዜ ንጉሥ አክዓብ በሶርያውያን ፊት ለፊት በሠረገላው ላይ ተደግፎ ይታይ ነበር፤ ፀሐይ ስትጠልቅም ሞተ።
2 ዜና መዋዕል 18:2-34 አማ2000 (የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ))
ከጥቂት ዓመታት በኋላም ወደ አክዓብ ወደ ሰማርያ ወረደ። አክዓብም ለእርሱና ከእርሱ ጋር ለነበሩት ሕዝብ ብዙ በጎችንና በሬዎችን አረደ፤ ወደደውም፤ ከእርሱም ጋር ወደ ሬማት ዘገለዓድ ይሄድ ዘንድ አባበለው። የእስራኤልም ንጉሥ አክዓብ የይሁዳን ንጉሥ ኢዮሣፍጥን፥ “ከእኔ ጋር ወደ ሬማት ዘገለዓድ ትሄዳለህን?” አለው። እርሱም፥ “እኔ እንደ አንተ ነኝ፤ ሕዝቤም ለሰልፍ እንደ ሕዝብህ ናቸው፤” ብሎ መለሰለት። ኢዮሣፍጥም የእስራኤልን ንጉሥ፥ “ዛሬ እግዚአብሔርን ጠይቅ” አለው። የእስራኤልም ንጉሥ ከነቢያቱ አራት መቶ ሰዎችን ሰብስቦ፥ “ወደ ሬማት ዘገለዓድ ለሰልፍ ልሂድን? ወይስ ልቅር?” አላቸው። እነርሱም፥ “እግዚአብሔር በንጉሥ እጅ አሳልፎ ይሰጣታልና ውጣ” አሉት። ኢዮሣፍጥ ግን፥ “እንጠይቀው ዘንድ የእግዚአብሔር ነቢይ የሆነ ሌላ ሰው በዚህ አይገኝምን?” አለ። የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮሣፍጥን፥ “እግዚአብሔርን የምንጠይቅበት አንድ ሰው አለ፤ ነገር ግን ሁልጊዜ ክፉ እንጂ ከቶ መልካም ትንቢት አይናገርልኝምና እጠላዋለሁ፤ እርሱም የይምላ ልጅ ሚክያስ ነው” አለው። ኢዮሣፍጥም፥ “ንጉሡ እንዲህ አይበል” አለው። የእስራኤልም ንጉሥ አንድ ጃንደረባ ጠርቶ፥ “የይምላን ልጅ ሚክያስን ፈጥነህ አምጣው” አለው። የእስራኤል ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ልብሰ መንግሥት ለብሰው በሰማርያ በር መግቢያ አጠገብ በአደባባይ በዙፋኖቻቸው ላይ ተቀምጠው ነበር፤ ነቢያትም ሁሉ በፊታቸው ትንቢት ይናገሩ ነበር። የካህናን ልጅ ሴዴቅያስም የብረት ቀንዶች ሠርቶ፦ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “ሶርያውያንን እስክታጠፋቸው ድረስ በእነዚህ ትወጋለህ” አለ። ነቢያትም ሁሉ፥ “እግዚአብሔር በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታልና ወደ ሬማት ዘገለዓድ ውጣና ተከናወን” እያሉ እንዲሁ ትንቢት ይናገሩ ነበር። ሚክያስንም ሊጠራ የሄደ መልእክተኛ፥ “እነሆ፥ ነቢያት በአንድ አፍ ሆነው ለንጉሡ መልካም ይናገራሉ፤ ቃልህም እንደ ቃላቸው እንዲሆን መልካም እንድትናገር እለምንሃለሁ” አለው። ሚክያስም፥ “ሕያው እግዚአብሔርን! አምላኬ የሚለውን እርሱን እናገራለሁ” አለ። ወደ ንጉሡም በመጣ ጊዜ ንጉሡ፥ “ሚክያስ ሆይ፥ ወደ ሬማት ዘገለዓድ ለሰልፍ ልሂድን? ወይስ ልቅር?” አለው። ነቢዩ ሚክያስም፥ “ውጣ፤ ተከናወን፤ በእጅህም አልፈው ይሰጣሉ” አለ። ንጉሡም፥ “በእግዚአብሔር ስም ከእውነት በቀር እንዳትነግረኝ ስንት ጊዜ አምልሃለሁ?” አለው። እርሱም፥ “እስራኤል ሁሉ ጠባቂ እንደሌላቸው በጎች በተራሮች ላይ ተበትነው አየሁ፤ እግዚአብሔርም፦ ለእነዚህ ጌታ የላቸውም፥ እያንዳንዱም በሰላም ወደ ቤቱ ይመለስ አለ” ብሎ ተናገረ። የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮሣፍጥን፥ “ክፉ እንጂ መልካም ትንቢት አይናገርልኝም አላልሁህምን?” አለው። ሚክያስም አለ፥ “እንዲህ አይደለም፤ እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ እግዚአብሔር በዙፋኑ ተቀምጦ፥ የሰማይ ሠራዊት ሁሉ በቀኙና በግራው፤ ቆመው አየሁ።” እግዚአብሔርም፥ “ወጥቶ በሬማት ዘገለዓድ ይወድቅ ዘንድ የእስራኤልን ንጉሥ አክዓብን የሚያታልል ማን ነው?” አለ። አንዱም እንደዚህ፥ ሌላውም እንደዚያ ያለ ነገር ተናገረ። መንፈስም መጣ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ቆሞ፥ “እኔ አታልለዋለሁ” አለ። እግዚአብሔርም፥ “በምን ታታልለዋለህ?” አለው። እርሱም፥ “ወጥቼ በነቢያት ሁሉ አፍ የሐሰት መንፈስ እሆናለሁ” አለ። እግዚአብሔርም፥ “ታታልለዋለህ፤ ይቀናሃል፥ ውጣ፤ እንዲህም አድርግ” አለው። “አሁንም እነሆ፥ እግዚአብሔር በእነዚህ በነቢያትህ አፍ የሐሰት መንፈስን አድርጎአል፤ እግዚአብሔርም በአንተ ላይ ክፉ ተናግሮብሃል።” የካህናንም ልጅ ሴዴቅያስ ቀረበ፤ ሚክያስንም በጥፊ መታውና፥ “የእግዚአብሔር መንፈስ ከአንተ ጋር ይናገር ዘንድ በምን መንገድ ከእኔ አለፈ?” አለው። ሚክያስም፥ “እነሆ፥ በዚያ ቀን ልትሸሸግ ከእልፍኝ ወደ እልፍኝ ስትሄድ ታያለህ” አለ። የእስራኤልም ንጉሥ እንዲህ አለ፥ “ሚክያስን ውሰዱ፤ ወደ ከተማዪቱም አለቃ ወደ ኤሜር፥ ወደ ንጉሡም ልጆች አለቃ ወደ ኢዮአስ መልሱት እንዲህም በሉአቸው፦ ንጉሡ እንዲህ ይላል፦ በደኅና እስክመለስ ድረስ ይህን ሰው በግዞት አኑሩት፤ የመከራም እንጀራ መግቡት፤ የመከራም ውኃ አጠጡት።” ሚክያስም፥ “በደኅና ብትመለስ እግዚአብሔር በእኔ አልተናገረም” አለ። “ደግሞም እናንተ ሕዝቡ ሁሉ ስሙኝ” አለ። የእስራኤል ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ወደ ሬማት ዘገለዓድ ወጡ። የእስራኤል ንጉሥም ኢዮሣፍጥን፥ “ልብሴን ለውጬ ወደ ጦርነት እገባለሁ፤ አንተ ግን የእኔን ልብስ ልበስ” አለው። የእስራኤልም ንጉሥ ልብሱን ለወጠ፤ ወደ ሰልፍም ገባ። የሶርያም ንጉሥ ከእርሱ ጋር የነበሩትን የሰረገሎቹን አለቆች፦ ከእስራኤልም ንጉሥ በቀር ትንሽ ቢሆን ወይም ትልቅ ከማናቸውም ጋር አትጋጠሙ ብሎ አዝዞ ነበር። የሰረገሎችም አለቆች ኢዮሣፍጥን ባዩ ጊዜ፥ “የእስራኤል ንጉሥ ነው” አሉ፤ ሊጋጠሙትም ከበቡት፤ ኢዮሣፍጥ ግን ጮኸ፤ እግዚአብሔርም አዳነው፤ አምላኩም ከእርሱ መለሳቸው። የሰረገሎቹም አለቆች የእስራኤል ንጉሥ እንዳልሆነ ባዩ ጊዜ ከእርሱ ተመለሱ። አንድ ሰውም ቀስቱን በድንገት ገትሮ የእስራኤልን ንጉሥ በጥሩሩ መጋጠሚያ በኩል ሳንባውን ወጋው። ሰረገለኛውንም፥ “ተወግቻለሁና እጅህን ግታ፤ ከጦርነት ውስጥ አውጣኝ” አለው። በዚያም ቀን ጦርነት በረታ፤ የእስራኤልም ንጉሥ በሶርያውያን ፊት እስከ ማታ ድረስ በሰረገላው ላይ ራሱን ይደግፍ ነበር፤ ፀሐይም በገባ ጊዜ ሞተ።
2 ዜና መዋዕል 18:2-34 አማ54 (መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት))
ከጥቂት ዓመት በኋላም ወደ አክዓብ ወደ ሰማርያ ወረደ። አክዓብም ለእርሱና ከእርሱ ጋር ለነበሩት ሕዝብ ብዙ በጎችና በሬዎችን አረደ፤ ከእርሱም ጋር ወደ ሬማት ዘገለዓድ ይሄድ ዘንድ አባበለው። የእስራኤልም ንጉሥ አክዓብ የይሁዳን ንጉሥ ኢዮሣፍጥን “ከእኔ ጋር ወደ ሬማት ዘገለዓድ ትሄዳለህን?” አለው። እርሱም“እኔ እንደ አንተ ነኝ፤ ሕዝቤም እንደ ሕዝብህ ናቸው፤ በሰልፍም ከአንተ ጋር እንሆናለን” ብሎ መለሰለት። ኢዮሳፍጥም የእስራኤልን ንጉሥ“የእግዚአብሔርን ቃል አስቀድመህ ትጠይቅ ዘንድ እለምንሃለሁ” አለው። የእስራኤልም ንጉሥ ነቢያቱን አራት መቶ ሰዎች ሰብስቦ“ወደ ሬማት ዘገለዓድ ለሰልፍ ልሂድን? ወይስ ልቅር?” አላቸው። እነርሱም “እግዚአብሔር በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታልና ውጣ” አሉት። ኢዮሳፍጥ ግን “እንጠይቀው ዘንድ የእግዚአብሔር ነብይ የሆነ ሌላ ሰው በዚህ አይገኝምን?” አለ። የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮሳፍጥን “እግዚአብሔርን የምንጠይቅበት አንድ ሰው አለ፤ ነገር ግን ሁል ግዜ ክፉ እንጅ ከቶ መልካም ትንቢት አይናገርልኝምና እጠላዋለሁ፤ እርሱም የይምላ ልጅ ሚክያስ ነው” አለው። ኢዮሳፍጥም “ንጉሥ እንዲህ አይበል” አለው። የእስራኤልም ንጉሥ አንድ ጃንደረባ ጠርቶ “የይምላን ልጅ ሚክያስን ፈጥነህ አምጣው” አለው። የእስራኤል ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሳፍጥ ልብሰ መንግሥት ለብሰው በሰማርያ በር መግቢያ አጠገብ በአደባባይ በዙፋኖቻቸው ላይ ተቀምጠው ነበር፤ ነቢያትም ሁሉ በፊታቸው ትንቢትን ይናገሩ ነበር። የክንዓና ልጅ ሰዴቅያስም የብረት ቀንዶች ሠርቶ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ‘ሶሪያውያንን እስኪጠፉ ድረስ በእነዚህ ትወጋለህ’” አለ። ነቢያትም ሁሉ “እግዚአብሔር በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታልና ወደ ሬማት ዘገለዓድ ሂድና ተከናወን” እያሉ እንዲሁ ትንቢት ይናገሩ ነበር። ሚክያስንም ሊጠራ የሄደ መልክተኛ “እነሆ፥ ነቢያት በአንድ አፍ ሆነው ለንጉሡ መልካም ይናገራሉ፤ ቃልህም እንደ ቃላቸው እንዲሆን መልካም እንድትናገር እለምንሃለሁ” አለው። ሚክያስም “ሕያው እግዚአብሔርን! አምላኬ የሚለውን እርሱን እናገራለሁ” አለ። ወደ ንጉሡም በመጣ ጊዜ ንጉሡ “ሚክያስ ሆይ! ወደ ሬማት ዘገለዓድ ለሰልፍ እንሂድን? ወይስ እንቅር?” አለው። እርሱም “ውጣ፤ ተከናወን፤ በእጅህም አልፈው ይሰጣሉ” አለ። ንጉሡም “በእግዚአብሔር ስም ከእውነት በቀር እንዳትነግረኝ ስንት ጊዜ አምልሃለሁ?” አለው። እርሱም “እስራኤል ሁሉ ጠባቂ እንደሌላቸው በጎች በተራሮች ላይ ተበትነው አየሁ፤ እግዚአብሔርም ‘ለእነዚህ ጌታ የላቸውም፤ እያንዳንዱም በሰላም ወደ ቤቱ ይመለስ’ አለ” ብሎ ተናገረ። የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮሳፍጥን “ክፉ እንጂ መልካም ትንቢት አይናገርልኝም አላልሁህምን?” አለው። ሚክያስም አለ “እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ እግዚአብሔር በዙፋኑ ተቀምጦ፥ የሰማይም ሠራዊት ሁሉ በቀኙና በግራው ቆመው አየሁ። እግዚአብሔርም ‘ወጥቶ በሬማት ዘገለዓድ ይወድቅ ዘንድ የእስራኤልን ንጉሥ አክዓብን የሚያታልል ማን ነው?’ አለ። አንዱም እንደዚህ፥ ሌላውም እንደዚያ ያለ ነገር ተናገረ። መንፈስም መጣ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ቆሞ ‘እኔ አታልልዋለሁ’ አለ። እግዚአብሔርም ‘በምን?’ አለው። እርሱም ‘ወጥቼ በነቢያቱ ሁሉ አፍ ሐሰተኛ መንፈስ እሆናለሁ’ አለ። እግዚአብሔርም ‘ታታልለዋለህ፤ ይቀናሃል፤ ውጣ፥ እንዲህም አድርግ’ አለ። አሁንም፥ እነሆ፥ እግዚአብሔር በእነዚህ በነቢያትህ አፍ ሐሰተኛ መንፈስን አድርጎአል፤ እግዚአብሔርም በአንተ ላይ ክፉ ተናግሮብሃል።” የክንዓናም ልጅ ሴዴቅያስ ቀረበ፤ ሚክያስንም በጥፊ መታውና “የእግዚአብሔር መንፈስ ከአንተ ጋር ይናገር ዘንድ በምን መንገድ ከእኔ አለፈ?” አለ። ሚክያስም “እነሆ፥ በዚያን ቀን ልትሸሸግ ወደ እልፍኝህ ስትሄድ ታያለህ” አለ። የእስራኤልም ንጉሥ “ሚክያስን ውሰዱ፤ ወደ ከተማይቱም አለቃ ወደ አሞን፥ ወደ ንጉሡም ልጅ ወደ ኢዮአስ መልሳችሁ፤ ንጉሡ እንዲህ ይላል ‘በደኅና እስክመለስ ድረስ ይህን ሰው በግዞቱ አኑሩት፤ የመከራም እንጀራ መግቡት፤ የመከራም ውኃ አጠጡት በሉ’ አለ።” ሚክያስም “በደህና ብትመለስ እግዚአብሔር በእኔ የተናገረ አይደለም” አለ። ደግሞም “እናንተ ሕዝብ ሁሉ፥ ስሙኝ” አለ። የእስራኤል ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ወደ ሬማት ዘገለዓድ ወጡ። የእስራኤል ንጉሥም ኢዮሣፍጥን “ልብሴን ለውጬ ወደ ሰልፍ እገባለሁ፤ አንተ ግን ልብስህን ልበስ” አለው። የእስራኤልም ንጉሥ ልብሱን ለወጠ፤ ወደ ሰልፍም ገቡ። የሶርያም ንጉሥ የሰረገሎቹን አለቆች “ከእስራኤል ንጉሥ በቀር ትንሽ ቢሆን ወይም ትልቅ ከማናቸውም ጋር አትጋጠሙ” ብሎ አዝዞ ነበር። የሰረገሎችም አለቆች ኢዮሣፍጥን ባዩ ጊዜ “የእስራኤል ንጉሥ ነው” አሉ፤ ሊጋጠሙትም ከበቡት፤ ኢዮሣፍጥ ግን ጮኸ፤ እግዚአብሔርም ረዳው፤ አምላኩም ከእርሱ መለሳቸው። የሰረገሎቹም አለቆች የእስራኤል ንጉሥ እንዳልሆነ ባዩ ጊዜ እርሱን ከማሳደድ ተመለሱ። አንድ ሰውም ቀስቱን በድንገት ገትሮ የእስራኤልን ንጉሥ በጥሩሩ መጋጠሚያ በኩል ሳንባውን ወጋው። ሰረጋለኛውንም “ተወግቻለሁና እጅህን ግታ፤ ከሰልፍም ውስጥ አውጣኝ” አለው። በዚያም ቀን ሰልፍ በረታ፤ የእስራኤልም ንጉሥ በሶርያውያን ፊት እስከ ማታ ድረስ በሰረገላው ላይ ራሱን ይደግፍ ነበር፤ ፀሐይም በገባ ጊዜ ሞተ።
2 ዜና መዋዕል 18:2-34 መቅካእኤ (መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ))
ከጥቂት ዓመት በኋላም ወደ አክዓብ ወደ ሰማርያ ወረደ። አክዓብም ለእርሱና ከእርሱ ጋር ለነበሩት ሕዝብ ብዙ በጎችና በሬዎችን አረደ፥ ከእርሱም ጋር ወደ ሬማት ዘገለዓድ እንዲሄድ አባበለው። የእስራኤልም ንጉሥ አክዓብ የይሁዳን ንጉሥ ኢዮሣፍጥን፦ “ከእኔ ጋር ወደ ሬማት ዘገለዓድ ትሄዳለህን?” አለው። እርሱም፦ “እኔ እንደ አንተ ነኝ፥ ሕዝቤም እንደ ሕዝብህ ናቸው፤ በጦርነቱም ላይ ከአንተ ጋር እንሆናለን” ብሎ መለሰለት። ኢዮሣፍጥም የእስራኤልን ንጉሥ፦ “የጌታን ቃል አስቀድመህ እንድትጠይቅ እለምንሃለሁ” አለው። የእስራኤልም ንጉሥ አራት መቶ ነቢያትን ሰብስቦ፦ “ወደ ሬማት ዘገለዓድ ለጦርነት እንሂድን? ወይስ ልቅር?” አላቸው። እነርሱም፦ “ጌታ በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታልና ውጣ” አሉት። ኢዮሣፍጥ ግን፦ “እንድንጠይቀው የጌታ ነቢይ የሆነ ሌላ ሰው በዚህ አይገኝምን?” አለ። የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮሣፍጥን እንዲህ አለው፦ “ጌታን የምንጠይቅበት አንድ ሰው አለ፤ ነገር ግን ሁልጊዜ ስለ እኔ ክፉ እንጂ ከቶ መልካም ትንቢት አይናገርምና እጠላዋለሁ፤ እርሱም የይምላ ልጅ ሚክያስ ነው።” ኢዮሣፍጥም፦ “ንጉሡ እንዲህ አይበል” አለው። የእስራኤልም ንጉሥ አንድ ጃንደረባ ጠርቶ፦ “የይምላን ልጅ ሚክያስን ፈጥነህ አምጣው” አለው። የእስራኤል ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ልብሰ መንግሥት ለብሰው በሰማርያ በር መግቢያ አጠገብ በአደባባይ በዙፋኖቻቸው ላይ ተቀምጠው ነበር፤ ነቢያትም ሁሉ በፊታቸው ትንቢትን ይናገሩ ነበር። የክንዓና ልጅ ሰዴቅያስም የብረት ቀንዶች ሠርቶ፦ “ጌታ እንዲህ ይላል፦ ‘ሶሪያውያንን እስኪጠፉ ድረስ በእነዚህ ትወጋቸዋለህ’ ” አለ። ነቢያትም ሁሉ፦ “ጌታ በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታልና ወደ ሬማት ዘገለዓድ ሂድ፥ ለአንተም ይከናወንልሃል” እያሉ ተመሳሳይ የሆነን ትንቢት ይናገሩ ነበር። ሚክያስንም ሊጠራ የሄደ መልክተኛ ሚክያስን እንዲህ አለው፦ “እነሆ፥ ነቢያት በአንድ ድምፅ ሆነው ለንጉሡ መልካም ነገር ይናገራሉ፤ ቃልህም እንደ ቃላቸው እንዲሆን መልካም እንድትናገር እለምንሃለሁ።” ሚክያስም፦ “በሕያው ጌታ እምላለሁ! አምላኬ የሚለውን እርሱን እናገራለሁ” አለ። ወደ ንጉሡም በመጣ ጊዜ ንጉሡ፦ “ሚክያስ ሆይ! ወደ ሬማት ዘገለዓድ ለጦርነት እንሂድን? ወይስ ልቅር?” አለው። እርሱም መለልሶ እንዲህ አለው፦ “ውጣ፥ ይከናወንልህ፤ በእጅህም ተላልፈው ይሰጣሉ።” ንጉሡም፦ “በጌታ ስም ከእውነት በቀር ምንም ዓይነት ነገር እንዳትነግረኝ ስንት ጊዜ አምልሃለሁ?” አለው። ሚክያስም እንዲህ አለ፦ “እስራኤል ሁሉ ጠባቂ እንደሌላቸው በጎች በተራሮች ላይ ተበትነው አየሁ፤ ጌታም እንዲህ አለ፦ ‘ለእነዚህ ጌታ የላቸውም፥ እያንዳንዱም በሰላም ወደ ቤቱ ይመለስ።’ ” የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮሣፍጥን፦ “ስለ እኔ ክፉ እንጂ መልካም ትንቢት አይናገርም አላልሁህምን?” አለው። ሚክያስም እንዲህ አለ፦ “እንግዲህ የጌታን ቃል ስሙ፤ ጌታ በዙፋኑ ተቀምጦ፥ የሰማይም ሠራዊት ሁሉ በቀኙና በግራው ቆመው አየሁ። ጌታም እንዲህ አለ፦ ‘ወጥቶ በሬማት ዘገለዓድ እንዲወድቅ የእስራኤልን ንጉሥ አክዓብን ያታለለው ማን ነው?’ አንዱም እንደዚህ፥ ሌላውም እንደዚያ ያለ ነገር ተናገረ። መንፈስም መጣ፥ በጌታም ፊት ቆሞ፦ ‘እኔ አታልልዋለሁ’ አለ። ጌታም፦ ‘በምን ዓይነት መንገድ?’ አለው። እርሱም መልሶ እንዲህ አለ፦ ‘ወጥቼ በነቢያቱ ሁሉ አፍ ሐሰተኛ መንፈስ እሆናለሁ።’ ጌታም እንዲህ አለው፦ ‘ታታልለዋለህ፤ ይከናወንልሃል፤ ውጣ፥ እንዲህም አድርግ። እንግዲህ አሁን፥ እነሆ፥ ጌታ በእነዚህ በነቢያትህ አፍ ሐሰተኛ መንፈስን አኑሮአል፤ ጌታም በአንተ ላይ ክፉ ተናግሮብሃል።’” የክንዓናም ልጅ ሴዴቅያስ ቀረበ፥ ሚክያስንም በጥፊ መታውና እንዲህ አለ፦ “የጌታ መንፈስ ከአንተ ጋር ለመነጋገር በምን ዓይነት መንገድ ከእኔ አለፈ?” ሚክያስም፦ “እነሆ፥ በዚያን ቀን ልትሸሸግ ወደ እልፍኝህ ስትሄድ ይታይሃል” አለው። የእስራኤልም ንጉሥ እንዲህ አለ፦ “ሚክያስን ውሰዱ፥ ወደ ከተማይቱም አለቃ ወደ አሞን፥ ወደ ንጉሡም ልጅ ወደ ኢዮአስ መልሱት፤ እናንተም እንዲህ በሉ፦ ‘ንጉሡ እንዲህ ይላል፦ በደኅና እስክመለስ ድረስ ይህን ሰው በወህኒ ቤት አኑሩት፥ የመከራም እንጀራ መግቡት፥ የመከራም ውኃ አጠጡት።’ ” ሚክያስም እንዲህ አለ፦ “በደህና የተመለስህ እንደሆነ ጌታ በእኔ አልተናረም።” ዳግመኛም እርሱ፦ “እናንተ ሕዝቦች ሆይ! ሁላችሁም ስሙኝ!” አለ። የእስራኤል ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ወደ ሬማት ዘገለዓድ ወጡ። የእስራኤል ንጉሥም ኢዮሣፍጥን፦ “ልብሴን ለውጬ ወደ ጦርነቱ እገባለሁ፤ አንተ ግን ልብስህን ልበስ” አለው። የእስራኤልም ንጉሥ ልብሱን ለወጠ፥ ወደ ጦርነቱም ገቡ። የሶርያም ንጉሥ የሰረገሎቹን አለቆች እንዲህ ብሎ አዝዞ ነበር፦ “ከእስራኤል ንጉሥ በቀር ትንሽ ቢሆን ወይም ትልቅ ከማናቸውም ጋር አትዋጉ።” የሰረገሎችም አለቆች ኢዮሣፍጥን ባዩ ጊዜ፦ “የእስራኤል ንጉሥ ነው” አሉ፥ ሊወጉትም ከበቡት፤ ኢዮሣፍጥ ግን ጮኸ፥ ጌታም ረዳው፥ አምላኩም ከእርሱ መለሳቸው። የሰረገሎቹም አለቆች የእስራኤል ንጉሥ እንዳልሆነ ባዩ ጊዜ እርሱን ከማሳደድ ተመለሱ። አንድ ሰውም ቀስቱን በድንገት ገትሮ የእስራኤልን ንጉሥ በጥሩሩ መጋጠሚያ በኩል ሳንባውን ወጋው። ሰረጋለኛውንም፦ “ተወግቻለሁና ሠረገላውን አዙር ከጦርነቱም ውስጥ አውጣኝ” አለው። በዚያም ቀን ጦርነቱ በረታ፤ የእስራኤልም ንጉሥ በሶርያውያን ፊት እስከ ማታ ድረስ በሠረገላው ላይ ራሱን አስደግፎ ተንጋለለ፤ ፀሐይም በጠለቀች ጊዜ ሞተ።