1 ጢሞቴዎስ 5:17-25
1 ጢሞቴዎስ 5:17-25 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በመልካም የሚያስተዳድሩ ሽማግሌዎች፥ ይልቁንም በመስበክና በማስተማር የሚደክሙት፥ እጥፍ ክብር ይገባቸዋል። መጽሐፍ “የሚያበራየውን በሬ አፉን አትሰር፤” ደግሞ “ለሠራተኛ ደመወዙ ይገባዋል፤” ይላልና። ከሁለት ወይም ከሦስት ምስክር በቀር በሽማግሌ ላይ ክስ አትቀበል። ሌሎቹ ደግሞ እንዲፈሩ፥ ኀጢአት የሚሠሩትን በሁሉ ፊት ገሥጻቸው። አንድን እንኳ በአድልዎ ሳታደርግ፥ እነዚህን ያለ ማዘንበል እንድትጠብቅ በእግዚአብሔርና በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ በተመረጡትም መላእክት ፊት እመክርሃለሁ። በማንም ላይ ፈጥነህ እጆችህን አትጫን፤ በሌሎችም ኀጢአት አትተባበር፤ ራስህን በንጽህና ጠብቅ። ስለ ሆድህና ስለ በሽታህ ብዛት ጥቂት የወይን ጠጅ ጠጣ እንጂ፥ ወደ ፊት ውሃ ብቻ አትጠጣ። የአንዳንዶች ሰዎች ኀጢአት የተገለጠ ነው፤ ፍርድንም ያመለክታል፤ ሌሎችን ግን ይከተላቸዋል፤ እንዲሁ መልካም ሥራ ደግሞ የተገለጠ ነው፤ ያልተገለጠም ከሆነ ሊሰወር አይችልም።
1 ጢሞቴዎስ 5:17-25 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ቤተ ክርስቲያንን በሚገባ የሚያስተዳድሩ፣ ይልቁንም በመስበክና በማስተማር የሚተጉ ሽማግሌዎች ዕጥፍ ክብር ይገባቸዋል፤ መጽሐፍም፣ “እህል እያበራየ ያለውን በሬ አፉን አትሰር፤” ደግሞም፣ “ለሠራተኛ ደመወዙ ይገባዋል” ይላልና። በሁለት ወይም በሦስት ምስክሮች ካልተደገፈ በቀር በሽማግሌ ላይ የሚቀርብ ክስ አትቀበል። ሌሎች አይተው እንዲጠነቀቁ ኀጢአት የሚሠሩትን በጉባኤ ፊት ገሥጻቸው። በእግዚአብሔርና በክርስቶስ ኢየሱስ፣ በተመረጡትም መላእክት ፊት እነዚህን ትእዛዞች ያለ አድልዎ እንድትጠብቅና አንዳችም ነገር በማበላለጥ እንዳታደርግ ዐደራ እልሃለሁ። በማንም ላይ እጅ ለመጫን አትቸኵል፤ ከሌሎችም ጋራ በኀጢአት አትተባበር፤ ራስህን በንጽሕና ጠብቅ። ለሆድህና ደጋግሞ ለሚነሣብህ ሕመም፣ ጥቂት የወይን ጠጅ ጠጣበት እንጂ ከእንግዲህ ውሃ ብቻ አትጠጣ። የአንዳንድ ሰዎች ኀጢአት ግልጽ ነው፤ ከእነርሱም ቀድሞ ፍርድ ቦታ ይደርሳል፤ ሌሎችን ግን ኀጢአታቸው ይከተላቸዋል። መልካም ሥራም እንደዚሁ ግልጽ ነው፤ ግልጽ ያልሆነ ቢኖርም እንኳ ተሰውሮ አይቀርም።
1 ጢሞቴዎስ 5:17-25 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በመልካም የሚያስተዳድሩ ሽማግሌዎች፥ ይልቁንም በመስበክና በማስተማር የሚደክሙት፥ እጥፍ ክብር ይገባቸዋል። መጽሐፍ፦ የሚያበራየውን በሬ አፉን አትሰር፥ ደግሞ፦ ለሠራተኛ ደመወዙ ይገባዋል ይላልና። ከሁለት ወይም ከሦስት ምስክር በቀር በሽማግሌ ላይ ክስ አትቀበል። ሌሎቹ ደግሞ እንዲፈሩ፥ ኃጢአት የሚሰሩትን በሁሉ ፊት ገሥጻቸው። አንድን እንኳ በአድልዎ ሳታደርግ፥ እነዚህን ያለ መዘንበል እንድትጠብቅ በእግዚአብሔርና በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ በተመረጡትም መላእክት ፊት እመክርሃለሁ። በማንም ላይ ፈጥነህ እጆችህን አትጫን፥ በሌሎችም ኃጢአት አትተባበር፤ ራስህን በንጽህና ጠብቅ። ስለ ሆድህና ስለ በሽታህ ብዛት ጥቂት የወይን ጠጅ ጠጣ እንጂ፥ ወደ ፊት ውኃ ብቻ አትጠጣ። የአንዳንዶች ሰዎች ኃጢአት የተገለጠ ነው ፍርድንም ያመለክታል፥ ሌሎችን ግን ይከተላቸዋል፤ እንዲሁ መልካም ሥራ ደግሞ የተገለጠ ነው፥ ያልተገለጠም ከሆነ ሊሰወር አይችልም።
1 ጢሞቴዎስ 5:17-25 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ቤተ ክርስቲያንን በደንብ የሚያስተዳድሩ፥ ይልቁንም በመስበክና በማስተማር የሚደክሙ ሽማግሌዎች እጥፍ ክብር ይገባቸዋል፤ ቅዱስ መጽሐፍ “እህል የሚያበራየውን በሬ አፉን አትሰር፤” እንዲሁም “ለሠራተኛው ደመወዝ ይገባዋል” ይላል። ሁለት ወይም ሦስት ሰዎች ካልመሰከሩበት በቀር በቤተ ክርስቲያን ሽማግሌ ላይ የሚቀርበውን ክስ አትቀበል። ሌሎች እንዲፈሩ ኃጢአት የሚሠሩትን በሰዎች ሁሉ ፊት ገሥጽ። በምታደርገው ነገር ሁሉ አንዱን ከሌላው ሳታበላልጥ ወይም ለማንም ሳታዳላ ይህን ምክሬን ሁሉ እንድትፈጽም በእግዚአብሔርና በኢየሱስ ክርስቶስ በተመረጡትም መላእክት ፊት ዐደራ እልሃለሁ። እጆችህን በመጫን ማንንም ለመሾም አትቸኲል፤ ራስህን በንጽሕና ጠብቅ እንጂ ከሌሎች ሰዎች ጋር በኃጢአት አትተባበር። ስለ ሆድህ ሕመምና ስለ ዘወትር ደዌህ ጥቂት የወይን ጠጅ ጠጣ እንጂ ከእንግዲህ ወዲህ ውሃ ብቻ አትጠጣ። የአንዳንድ ሰዎች ኃጢአት ግልጥ በመሆኑ አስቀድሞ ፍርዱን ያመለክታል፤ የሌሎች ሰዎች ኃጢአት ግን የሚገለጠው ዘግየት ብሎ ነው። እንዲሁም መልካም ሥራ ግልጥ ነው፤ ግልጥ ያልሆነውም እንኳ ተሰውሮ አይቀርም።
1 ጢሞቴዎስ 5:17-25 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በመልካም የሚያስተዳድሩ፥ በተለይም በመስበክና በማስተማር የሚደክሙ ሽማግሌዎች፥ እጥፍ ክብር ይገባቸዋል። ቅዱስ መጽሐፍ፦ “የሚያበራየውን በሬ አፉን አትሰር፤” ደግሞ “ለሠራተኛ ደመወዙ ይገባዋል፤” ይላል። በሁለት ወይም በሦስት ምስክር ካልተደገፈ በቀር በሽማግሌ ላይ ክስ አትቀበል። ሌሎቹ ደግሞ እንዲፈሩ፥ ኃጢአት የሚሠሩትን በሁሉ ፊት ገሥጽ። አንዱን ከሌላው በማበላለጥ ምንም ዓይነት ነገር ሳታደርግ፥ ያለ አድልዎ እነዚህን ትዛዛቶች እንድትጠብቅ በእግዚአብሔርና በጌታ በክርስቶስ ኢየሱስ በተመረጡትም መላእክት ፊት አደራ እልሃለሁ። በማንም ላይ ፈጥነህ እጆችህን አትጫን፤ በሌሎችም ኃጢአት አትተባበር፤ ራስህን በንጽህና ጠብቅ። ስለ ሆድህና በተደጋጋሚ ስለሚያጠቃህ በሽታ ስትል ጥቂት የወይን ጠጅ ጠጣ እንጂ፥ ከእንግዲህ ውሃ ብቻ አትጠጣ። የአንዳንድ ሰዎች ኃጢአት የተገለጠ በመሆኑ አስቀድሞ ፍርድን ያመለክታል፤ የሌሎች ግን የሚገለጠው ዘግየት ብሎ ነው፤ እንዲሁ መልካም ሥራ ደግሞ የተገለጠ ነው፤ ያልተገለጠም ከሆነ እንኳ ተሰውሮ መቅረት አይችልም።