1 ጢሞቴዎስ 1:1-7
1 ጢሞቴዎስ 1:1-7 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
መድኃኒታችን እግዚአብሔር ተስፋችንም ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳዘዘው ትእዛዝ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ የሆነ ጳውሎስ፥ በእምነት እውነተኛ ልጄ ለሆነ ለጢሞቴዎስ፤ ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከክርስቶስ ኢየሱስም ከጌታችን ጸጋና ምሕረት ሰላምም ይሁን። ወደ መቄዶንያ በሄድሁ ጊዜ፥ አንዳንዶች ልዩ ትምህርትን እንዳያስተምሩና ወደ ተረት መጨረሻም ወደሌለው ወደ ትውልዶች ታሪክ እንዳያደምጡ ልታዛቸው በኤፌሶን ትቀመጥ ዘንድ ለመንሁህ፤ እንደ እነዚህ ያሉ ነገሮች ክርክርን ያመጣሉና፤ በእምነት ግን ላለ ለእግዚአብሔር መጋቢነት አይጠቅሙም። የትእዛዝ ፍጻሜ ግን ከንጹሕ ልብና ከበጎ ሕሊና ግብዝነትም ከሌለበት እምነት የሚወጣ ፍቅር ነው፤ ከእነዚህም አንዳንዶች ስተው የሚሉትን ወይም ስለ እነርሱ አስረግጠው የሚናገሩትን ሳያስተውሉ፥ የሕግ አስተማሪዎች ሊሆኑ እየወደዱ ወደ ከንቱ ንግግር ፈቀቅ ብለዋል።
1 ጢሞቴዎስ 1:1-7 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በአዳኛችን በእግዚአብሔር፣ ተስፋችንም በሆነው በክርስቶስ ኢየሱስ ትእዛዝ የክርስቶስ ኢየሱስ ሐዋርያ ከሆነው ከጳውሎስ፤ በእምነት እውነተኛ ልጄ ለሆነው ለጢሞቴዎስ፤ ከአባታችን ከእግዚአብሔር፣ ከጌታችንም ከክርስቶስ ኢየሱስ ጸጋና ምሕረት፣ ሰላምም ይሁን። ወደ መቄዶንያ በሄድሁ ጊዜ ዐደራ እንዳልሁህ፣ አንዳንድ ሰዎች ከእንግዲህ የሐሰት ትምህርት እንዳያስተምሩ ታዝዛቸው ዘንድ በዚያው በኤፌሶን ተቀመጥ፤ ደግሞም ለተረትና መጨረሻ ለሌለው የትውልዶች ታሪክ ራሳቸውን አሳልፈው እንዳይሰጡ እዘዛቸው። እነዚህ ነገሮች በእምነት ከሆነው ከእግዚአብሔር ሥራ ይልቅ ክርክርን ያነሣሣሉ። የዚህ ትእዛዝ ዐላማ ግን ከንጹሕ ልብ፣ ከበጎ ኅሊና እንዲሁም ከእውነተኛ እምነት የሚገኝ ፍቅር ነው። አንዳንዶች ከእነዚህ ነገሮች ዘወር ብለው ወደ ከንቱ ንግግር ተመልሰዋል። የሕግ መምህራን ለመሆን ይፈልጋሉ፤ ሆኖም ስለሚናገሩት ወይም አስረግጠው ስለሚሟገቱለት ነገር አያውቁም።
1 ጢሞቴዎስ 1:1-7 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
መድኃኒታችን እግዚአብሔር ተስፋችንም ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳዘዘው ትእዛዝ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ የሆነ ጳውሎስ፥ በእምነት እውነተኛ ልጄ ለሆነ ለጢሞቴዎስ፦ ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከክርስቶስ ኢየሱስም ከጌታችን ጸጋና ምሕረት ሰላምም ይሁን። ወደ መቄዶንያ በሄድሁ ጊዜ፥ አንዳንዶች ልዩ ትምህርትን እንዳያስተምሩና ወደ ተረት መጨረሻም ወደሌለው ወደ ትውልዶች ታሪክ እንዳያደምጡ ልታዛቸው በኤፌሶን ትቀመጥ ዘንድ ለመንሁህ፤ እንደ እነዚህ ያሉ ነገሮች ክርክርን ያመጣሉና በእምነት ግን ላለ ለእግዚአብሔር መጋቢነት አይጠቅሙም። የትእዛዝ ፍጻሜ ግን ከንጹሕ ልብና ከበጎ ሕሊና ግብዝነትም ከሌለበት እምነት የሚወጣ ፍቅር ነው፤ ከእነዚህም አንዳንዶች ስተው፥ የሚሉትን ወይም ስለ እነርሱ አስረግጠው የሚናገሩትን ሳያስተውሉ፥ የሕግ አስተማሪዎች ሊሆኑ እየወደዱ፥ ወደ ከንቱ ንግግር ፈቀቅ ብለዋል።
1 ጢሞቴዎስ 1:1-7 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በአዳኛችን በእግዚአብሔር፥ በተስፋችን በኢየሱስ ክርስቶስ ትእዛዝ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ከሆነ ከጳውሎስ፦ በእምነት እውነተኛ ልጄ ለሆነው ለጢሞቴዎስ፥ ከአባታችን ከእግዚአብሔር፥ ከጌታችንም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ምሕረት ሰላምም ይሁንልህ። ወደ መቄዶንያ ስሄድ ሳለሁ ዐደራ እንዳልኩህ እዚያ ያሉ አንዳንድ ሰዎች የሐሰት ትምህርት እንዳያስተምሩ ታደርጋቸው ዘንድ በኤፌሶን ተቀመጥ። ወደ ተረትና መጨረሻ ወደሌለው ወደ ትውልዶች ቈጠራ እንዳይመለሱ እዘዛቸው፤ እነዚህ ነገሮች ክርክርን ያመጣሉ እንጂ በእምነት ለሚደረገው ለእግዚአብሔር ሥራ አይጠቅሙም። የዚህ ትእዛዝ ዓላማ ግን ከንጹሕ ልብ፥ ከመልካም ኅሊና፥ ከእውነተኛ እምነት የሚገኝ ፍቅር ነው። አንዳንድ ሰዎች ከእነዚህ ነገሮች ተለይተው ወደ ከንቱ ክርክር ተመልሰዋል። ይህንንም የሚያደርጉት የሕግ መምህራን ለመሆን ፈልገው ነው፤ ይሁን እንጂ የሚናገሩትን አያውቁም ወይም እርግጠኞች ነን የሚሉበትንም ነገር አያስተውሉም።
1 ጢሞቴዎስ 1:1-7 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በአዳኛችን በእግዚአብሔር በተስፋችንም በክርስቶስ ኢየሱስ ትእዛዝ የክርስቶስ ኢየሱስ ሐዋርያ የሆነ ጳውሎስ፥ በእምነት እውነተኛ ልጄ ለሆነ ለጢሞቴዎስ፤ ከእግዚአብሔር አብ ከጌታችንም ከክርስቶስ ኢየሱስ ጸጋና ምሕረት ሰላምም ይሁን። ወደ መቄዶንያ በምሄድ ጊዜ በኤፌሶን ተቀምጠህ አንዳንድ ሰዎች ልዩ ትምህርትን እንዳያስተምሩ፥ ራሳቸውንም በተረት፥ መጨረሻም በሌለው የትውልዶች ታሪክ እንዳይጠመዱ እንድታዝ ለመንሁህ፤ ሆኖም ግን እንደ እነዚህ ያሉ ነገሮች ከንቱ ምርምር ያመጣሉ እንጂ በእምነት የሚገኝውን የእግዚአብሔርን መጋቢነት አይጠቅሙም። የትእዛዙ ዓላማ ግን ከንጹሕ ልብና ከበጎ ኅሊና፤ ግብዝነትም ከሌለበት እምነት የሚመነጭ ፍቅር ነው፤ አንዳንድ ሰዎች ከእነዚህ ነገሮች ፈቀቅ ብለው ወደ ከንቱ ንግግር በመሄድ፥ ምን እንደሚናገሩ ወይም በምን ዓይነት ነገሮች ላይ በድፍረት ማረገጋገጫ እንደሚሰጡ ሳያስተውሉ የሕግ አስተማሪዎች መሆንን ይፈልጋሉ።