1 ተሰሎንቄ 3:1-13

1 ተሰሎንቄ 3:1-13 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ስለዚህ ወደ ፊት እንታገሥ ዘንድ ባልተቻለን ጊዜ፥ በአቴና ብቻችንን ልንቀር በጎ ፈቃዳችን ሆነ። ስለ እምነታችሁም እንዲያጸናችሁና እንዲመክራችሁ ወንድማችንን የእግዚአብሔርንም አገልጋይ ከእኛ ጋርም አብሮ በክርስቶስ ወንጌል የሚሠራውን ጢሞቴዎስን ላክነው፤ በዚህ መከራ ማንም እንዳይናወጥ፥ ለዚህ እንደ ተመረጥን ራሳችሁ ታውቃላችሁና። በእውነት ከእናንተ ጋር ሳለን፥ መከራ እንቀበል ዘንድ እንዳለን አስቀድመን እንነግራችሁ ነበር፤ እንዲሁም ደግሞ ሆነ፤ ይህንም ታውቃላችሁ። ስለዚህ እኔ ደግሞ ወደ ፊት እታገሥ ዘንድ ባልተቻለኝ ጊዜ “ፈታኝ ምናልባት ፈትኖአቸዋል፤ ድካማችንም ከንቱ ሆኖአል፤” ብዬ እምነታችሁን ለማወቅ ላክሁ። አሁን ግን ጢሞቴዎስ ከእናንተ ዘንድ ወደ እኛ መጥቶ ስለ እምነታችሁና ስለ ፍቅራችሁ የምሥራች ብሎ በነገረን ጊዜ፥ እኛም እናያችሁ ዘንድ እንደምንናፍቅ ታዩን ዘንድ እየናፈቃችሁ ሁልጊዜ በመልካም እንደምታስቡን በነገረን ጊዜ፥ ስለዚህ ወንድሞች ሆይ! በእምነታችሁ በኩል በችግራችንና በመከራችን ሁሉ ስለ እናንተ ተጽናናን፤ እናንተ በጌታ ጸንታችሁ ብትቆሙ፥ አሁን በሕይወት እንኖራለንና። ፊታችሁን ልናይ በእምነታችሁም የጎደለውን ልንሞላበት ሌሊትና ቀን ከመጠን ይልቅ እየጸለይን በአምላካችን ፊት ከእናንተ የተነሣ ስለምንደሰተው ደስታ ሁሉ ለእግዚአብሔር በእናንተ ምክንያት ምን ያህል ምስጋና እናስረክብ ዘንድ እንችላለን? አምላካችንና አባታችን ራሱ ጌታችንም ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ እናንተ መንገዳችንን ያቅና፤ ጌታችንም ኢየሱስ ክርስቶስ ከቅዱሳኑ ሁሉ ጋር ሲመጣ፥ በአምላካችንና በአባታችን ፊት በቅድስና ነቀፋ የሌለበት አድርጎ ልባችሁን ያጸና ዘንድ፥ እኛ ደግሞ ለእናንተ እንደምንሆን ጌታ እርስ በእርሳችሁ ያላችሁን ለሁሉም የሚሆን ፍቅራችሁን ያብዛ፤ ይጨምርም።

1 ተሰሎንቄ 3:1-13 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ስለዚህ መታገሥ ስላልቻልን ለጊዜው በአቴና ብቻችንን መቅረት መልካም መስሎ ታየን። በእምነታችሁ እንዲያጸናችሁና እንዲያበረታችሁ ወንድማችንንና በክርስቶስ ወንጌል ሥራ ከእኛ ጋራ የእግዚአብሔር አገልጋይ የሆነውን ጢሞቴዎስን ልከንላችኋል፤ ይኸውም በዚህ ፈተና ማንም እንዳይናወጥ ነው። እኛም ለዚህ ነገር እንደ ተመደብን እናንተ ራሳችሁ ታውቃላችሁ። በርግጥ ከእናንተ ጋራ በነበርንበት ጊዜ መከራ እንደሚደርስብን በየጊዜው እንነግራችሁ ነበር፤ እንደምታውቁትም እንዲሁ ደግሞ ሆኗል። ስለዚህ ምንም መታገሥ ባልቻልሁ ጊዜ ስለ እምነታችሁ ለማወቅ ላክሁ፤ ይህንም ያደረግሁት ምናልባት ፈታኙ ፈትኗችሁ ድካማችን ሁሉ ከንቱ ሆኗል ብዬ ስለ ፈራሁ ነው። አሁን ግን ጢሞቴዎስ ከእናንተ ዘንድ ወደ እኛ መጥቶ ስለ እምነታችሁና ስለ ፍቅራችሁ መልካም ዜና አሰምቶናል። ደግሞም እኛን ሁልጊዜ በመልካም እንደምታስታውሱንና እኛ እናንተን ለማየት የምንናፍቃችሁን ያህል እናንተም እኛን ለማየት እንደምትናፍቁ ነግሮናል። ስለዚህ ወንድሞች ሆይ፤ በጭንቀታችንና በመከራችን ሁሉ በእምነታችሁ ምክንያት በእናንተ ተጽናናን። በጌታ ጸንታችሁ ስለ ቆማችሁ በርግጥ አሁን በሕይወት እንኖራለን። በእናንተ ምክንያት በአምላካችን ፊት ስላገኘነው ደስታ ሁሉ ለእግዚአብሔር ምን ያህል ምስጋና ልናቀርብ እንችላለን? እንደ ገና ልናያችሁና በእምነታችሁ የጐደለውን ለማሟላት ሌሊትና ቀን እጅግ ተግተን እንጸልያለን። አሁንም ራሱ አምላካችንና አባታችን፣ ጌታችንም ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ እናንተ እንድንመጣ መንገዳችንን ያቅናልን። እኛ ለእናንተ ፍቅር እንዳለን ሁሉ እርስ በርስ ያላችሁን ፍቅርና ለሌሎችም ያላችሁን ፍቅር ጌታ ያብዛላችሁ፤ ያትረፍርፍላችሁም። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከቅዱሳኑ ሁሉ ጋራ በሚመጣበት ጊዜ በአምላካችንና በአባታችን ፊት ነቀፋ የሌለባችሁና ቅዱሳን ሆናችሁ እንድትገኙ ልባችሁን ያጽና።

1 ተሰሎንቄ 3:1-13 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ስለዚህ ወደ ፊት እንታገሥ ዘንድ ባልተቻለን ጊዜ፥ በአቴና ብቻችንን ልንቀር በጎ ፈቃዳችን ሆነ። ስለ እምነታችሁም እንዲያጸናችሁና እንዲመክራችሁ ወንድማችንን የእግዚአብሔርንም አገልጋይ ከእኛ ጋርም አብሮ በክርስቶስ ወንጌል የሚሠራውን ጢሞቴዎስን ላክነው፤ በዚህ መከራ ማንም እንዳይናውጥ፥ ለዚህ እንደ ተመረጥን ራሳችሁ ታውቃላችሁና። በእውነት ከእናንተ ጋር ሳለን፥ መከራ እንቀበል ዘንድ እንዳለን አስቀድመን እንነግራችሁ ነበር፤ እንዲሁም ደግሞ ሆነ፥ ይህንም ታውቃላችሁ። ስለዚህ እኔ ደግሞ ወደ ፊት እታገሥ ዘንድ ባልተቻለኝ ጊዜ፦ ፈታኝ ምናልባት ፈትኖአቸዋል ድካማችንም ከንቱ ሆኖአል ብዬ እምነታችሁን ለማወቅ ላክሁ። አሁን ግን ጢሞቴዎስ ከእናንተ ዘንድ ወደ እኛ መጥቶ ስለ እምነታችሁና ስለ ፍቅራችሁ የምስራች ብሎ በነገረን ጊዜ፥ እኛም እናያችሁ ዘንድ እንደምንናፍቅ ታዩን ዘንድ እየናፈቃችሁ ሁልጊዜ በመልካም እንደምታስቡን በነገረን ጊዜ፥ ስለዚህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ በእምነታችሁ በኩል በችግራችንና በመከራችን ሁሉ ስለ እናንተ ተጽናናን፤ እናንተ በጌታ ጸንታችሁ ብትቆሙ፥ አሁን በሕይወት እንኖራለንና። ፊታችሁን ልናይ በእምነታችሁም የጎደለውን ልንሞላበት ሌሊትና ቀን ከመጠን ይልቅ እየጸለይን በአምላካችን ፊት ከእናንተ የተነሣ ስለምንደሰተው ደስታ ሁሉ ለእግዚአብሔር በእናንተ ምክንያት ምን ያህል ምስጋና እናስረክብ ዘንድ እንችላለን? አምላካችንና አባታችን ራሱ ጌታችንም ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ እናንተ መንገዳችንን ያቅና፤ ጌታችንም ኢየሱስ ክርስቶስ ከቅዱሳኑ ሁሉ ጋር ሲመጣ፥ በአምላካችንና በአባታችን ፊት በቅድስና ነቀፋ የሌለበት አድርጎ ልባችሁን ያጸና ዘንድ፥ እኛ ደግሞ ለእናንተ እንደምንሆን ጌታ እርስ በእርሳችሁ ያላችሁን ለሁሉም የሚሆን ፍቅራችሁን ያብዛ ይጨምርም።

1 ተሰሎንቄ 3:1-13 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ስለዚህ ከእንግዲህ ወዲህ መታገሥ ባለመቻላችን በአቴና ብቻችንን መቅረት መልካም ሆኖ ታየን። ወንድማችንንና የእግዚአብሔር አገልጋይ የሆነውን፥ የክርስቶስን መልካም ዜና በማብሠር የሥራ ጓደኛችንን ጢሞቴዎስን ልከንላችኋል፤ የላክንላችሁም እንዲያጸናችሁና በእምነት እንድትበረቱ እንዲመክራችሁ ነው፤ ይህም በደረሰባችሁ መከራ እንዳትናወጡ ያደርጋችኋል፤ ይህ መከራ ለእኛ የተወሰነልን ዕጣ መሆኑን እናንተ ራሳችሁ ታውቃላችሁ። እንዲያውም ከእናንተ ጋር በነበርንበት ጊዜ መከራ እንደሚደርስብን አስቀድመን እንነግራችሁ ነበር፤ እንደምታውቁትም መከራው ደርሶብናል፤ በዚህ ምክንያት ከእንግዲህ ወዲህ በትዕግሥት መጠበቅ ባለመቻሌ ስለ እምነታችሁ ማወቅ ፈልጌ ጢሞቴዎስን ወደ እናንተ ላክሁት፤ እርሱን የላክሁትም ምናልባት ፈታኙ በአንድ መንገድ ፈትኖአችሁ ይሆናል፤ ሥራችንም ከንቱ ሆኖ ቀርቶአል በማለት ፈርቼ ነው። አሁን ግን ጢሞቴዎስ ከእናንተ ዘንድ ወደ እኛ መጥቶ ስለ እምነታችሁና ስለ ፍቅራችሁ ደስ የሚያሰኝ ዜና ነገረን፤ እንዲሁም እናንተ ዘወትር በመልካም እንደምታስታውሱንና እኛ እናንተን ለማየት የምንናፍቃችሁን ያኽል እናንተም እኛን ለማየት እንደምትናፍቁ ነገረን። ስለዚህ ወንድሞች ሆይ፥ እኛ የምንገኘው በችግርና በመከራ ውስጥ ቢሆንም እንኳ በእምነታችሁ ምክንያት በእናንተ ተጽናንተናል። የእናንተ በጌታ ኢየሱስ ጸንቶ መኖር ለእኛ ሕይወታችን ነው። እነሆ፥ አሁን ስለ እናንተ ምስጋና እናቀርባለን፤ በእናንተም ምክንያት በእርሱ ፊት ስላለን ደስታ እግዚአብሔርን እናመሰግናለን። ሌሊትና ቀን በብርቱ የምንጸልየው በዐይነ ሥጋ እንድናያችሁና በእምነታችሁ የጐደለውን ለመሙላት እንድንችል ነው። አሁንም አምላካችንና አባታችን ራሱ ጌታችን ኢየሱስም ወደ እናንተ እንድንመጣ መንገዳችንን ያቅናልን። እኛ እንደምናፈቅራችሁ ጌታ እርስ በርስና ለሌሎችም ሁሉ ያላችሁ ፍቅር እንዲያድግና እንዲበዛ ያድርግላችሁ፤ በዚህ ዐይነት ጌታችን ኢየሱስ ከቅዱሳኑ ሁሉ ጋር በሚመጣበት ጊዜ በአምላካችንና በአባታችን ፊት ልባችሁ ነቀፋ የሌለበትና ቅዱስ እንዲሆን ያበረታችኋል።

1 ተሰሎንቄ 3:1-13 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ስለዚህ ወደ ፊት ለመታገስ ባልተቻለን ጊዜ፥ በአቴና ብቻችንን ልንቀር በጎ ፈቃዳችን ሆነ። ስለ እምነታችሁም እንዲያጸናችሁና እንዲመክራችሁ ወንድማችንን፥ የእግዚአብሔርንም አገልጋይ ከእኛ ጋርም አብሮ በክርስቶስ ወንጌል የሚሠራውን ጢሞቴዎስን ላክነው፤ በዚህ መከራ ማንም እንዳይናወጥ፥ ለዚህ እንደ ተሾምን ራሳችሁ ታውቃላችሁና። በእውነት ከእናንተ ጋር ሳለን፥ መከራ እንደምንቀበል አስቀድመን እንነግራችሁ ነበር፤ እንዲሁም ደግሞ ሆነ፤ ይህንንም ታውቃላችሁ። ስለዚህ እኔ ደግሞ ወደ ፊት ለመታገስ ባልተቻለኝ ጊዜ፦ “ፈታኙ ምናልባት ፈትኖአቸዋል፤ ድካማችንም ከንቱ ሆኖአል፤” ብዬ በመፍራት እምነታችሁን ለማወቅ ጢሞቴዎስን ላክሁ። አሁን ግን ጢሞቴዎስ ከእናንተ ዘንድ ወደ እኛ መጥቶ ስለ እምነታችሁና ስለ ፍቅራችሁ መልካም ዜና አመጣልን፤ እኛ እናንተን ለማየት እንደምንናፍቅ እናንተም እኛን ለማየት እንደምትናፍቁና ሁልጊዜ በመልካም እንደምታስታውሱን ደግሞ ነገረን፤ ስለዚህ ወንድሞች ሆይ! በእምነታችሁ በኩል በችግራችንና በመከራችን ሁሉ ስለ እናንተ ተጽናናን፤ እናንተ በጌታ ጸንታችሁ ብትቆሙ፥ አሁን በሕይወት እንኖራለንና። በእናንተ የተነሣ በአምላካችን ፊት ለተደሰትነው ደስታ ሁሉ ስለ እናንተ ለእግዚአብሔር ምን ያህል ምስጋና ልናቀርብ እንችላለን? ፊታችሁን ለማየትና በእምነታችሁ የጎደለውንም ለማሟላት ሌሊትና ቀን እጅግ አብዝተን እንጸልይ የለምን? አምላካችንና አባታችን ራሱ ጌታችንም ኢየሱስ ወደ እናንተ መንገዳችንን ይምራ፤ ጌታ እንድትበዙ ያድርጋችሁ፤ እኛም ለእናንተ ፍቅርን እንዳበዛንላችሁ እንዲሁም የእርስ በርሳችሁንና ለሁሉ ሰው ያላችሁን ፍቅር ያብዛ። ከቅዱሳኑ ሁሉ ጋር ጌታችን ኢየሱስ በሚመጣበት ጊዜ በአባታችንና በአምላካችን ፊት ያለ ነቀፋ እንድትሆኑ በቅድስና ልባችሁን ያጽና።