1 ተሰሎንቄ 2:1-9
1 ተሰሎንቄ 2:1-9 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ወንድሞች ሆይ! ራሳችሁ ወደ እናንተ መግባታችን ከንቱ እንዳልሆነ ታውቃላችሁ። ነገር ግን እንደምታውቁት በፊልጵስዩስ አስቀድመን መከራ ተቀብለን ተንገላትተንም፥ በብዙ ገድል የእግዚአብሔርን ወንጌል ለእናንተ እንናገር ዘንድ በአምላካችን ደፈርን። ልመናችን ከስሕተት ወይም ከርኵሰት ወይም ከተንኰል አልነበረምና፤ ነገር ግን ወንጌልን አደራ ይሰጠን ዘንድ እግዚአብሔር የታመንን ሆነን እንዳገኘን መጠን፥ እንዲሁ እንናገራለን፤ ልባችንን የሚመረምር እግዚአብሔርን እንጂ ሰውን ደስ እንደምናሰኝ አይደለም። እንደምታውቁ፥ እያቈላመጥን ከቶ አልተናገርንም፤ እግዚአብሔርም እንደሚመሰክር እያመካኘን በመጐምጀት አልሠራንም፤ የክርስቶስም ሐዋርያት እንደ መሆናችን ልንከብድባችሁ ስንችል፥ ከእናንተ ቢሆን ወይም ከሌሎች ክብርን ከሰው አልፈለግንም። ነገር ግን ሞግዚት የራስዋን ልጆች እንደምትከባከብ፥ በመካከላችሁ የዋሆች ሆንን፤ እንዲሁም እያፈቀርናችሁ የእግዚአብሔርን ወንጌል ለማካፈል ብቻ ሳይሆን የገዛ ነፍሳችንን ደግሞ እናካፍላችሁ ዘንድ በጎ ፈቃዳችን ነበረ፤ ለእኛ የተወደዳችሁ ሆናችሁ ነበርና። ወንድሞች ሆይ! ድካማችንና ጥረታችን ትዝ ይላችኋል፤ ከእናንተ በአንዱ ስንኳ እንዳንከብድበት ሌሊትና ቀን እየሠራን፥ የእግዚአብሔርን ወንጌል ለእናንተ ሰበክን።
1 ተሰሎንቄ 2:1-9 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ወንድሞች ሆይ፤ ወደ እናንተ የመጣነው ለከንቱ እንዳልሆነ እናንተ ራሳችሁ ታውቃላችሁ። እንደምታውቁት ከዚህ ቀደም በፊልጵስዩስ መከራ ተቀብለን ተንገላታን፤ ነገር ግን ብርቱ ተቃውሞ ቢደርስብንም እንኳ፣ የእግዚአብሔርን ወንጌል ለእናንተ እንደምናበሥር በአምላካችን ድፍረት አገኘን። የምናቀርበው ልመና ከስሕተት ወይም ከክፉ ዐላማ ወይም እናንተን ለማታለል ከመፈለግ የመነጨ አይደለም። ነገር ግን ወንጌልን በዐደራ ለመቀበል እግዚአብሔር ብቁ አድርጎ እንደ ቈጠራቸው ሰዎች ሆነን እንናገራለን። ይህንም የምናደርገው ልባችንን የሚመረምረውን እግዚአብሔርን እንጂ ሰዎችን ደስ ለማሠኘት ብለን አይደለም። የሽንገላ ቃል ከቶ እንዳልተናገርን ወይም ሥሥትን ለመሸፈን ብለን አስመሳዮች እንዳልሆንን ታውቃላችሁ፤ ለዚህም እግዚአብሔር ምስክራችን ነው። ከእናንተም ሆነ ከሌሎች ከማንም፣ ከሰው የሚገኝ ክብር አልፈለግንም። የክርስቶስ ሐዋርያት እንደ መሆናችን መጠን ሸክም በሆንንባችሁ ነበር፤ ነገር ግን እናት ልጇን እንደምትንከባከብ እኛም በመካከላችሁ በየዋህነት ተመላለስን። የእግዚአብሔርን ወንጌል ብቻ ሳይሆን ሕይወታችንን ጭምር ልናካፍላችሁ ደስ እስከሚለን ድረስ ወደድናችሁ፤ ምክንያቱም እናንተ በእኛ ዘንድ ተወዳጆች ነበራችሁ። ወንድሞች ሆይ፤ ጥረታችንንና ድካማችንን ታስታውሳላችሁ፤ በማንም ላይ ሸክም እንዳንሆን ሌሊትና ቀን እየሠራን የእግዚአብሔርን ወንጌል ሰበክንላችሁ።
1 ተሰሎንቄ 2:1-9 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ወንድሞች ሆይ፥ ራሳችሁ ወደ እናንተ መግባታችን ከንቱ እንዳልሆነ ታውቃላችሁና። ነገር ግን እንደምታውቁት በፊልጵስዩስ አስቀድመን መከራ ተቀብለን ተንገላትተንም፥ በብዙ ገድል የእግዚአብሔርን ወንጌል ለእናንተ እንናገር ዘንድ በአምላካችን ደፈርን። ልመናችን ከስሕተት ወይም ከርኵሰት ወይም ከተንኵኦል አልነበረምና፤ ነገር ግን ወንጌልን አደራ ይሰጠን ዘንድ እግዚአብሔር የታመንን ሆነን እንዳገኘን መጠን፥ እንዲሁ እንናገራለን፥ ልባችንን የሚመረምር እግዚአብሔርን እንጂ ሰውን ደስ እንደምናሰኝ አይደለም። እንደምታውቁ፥ እያቍኦላመጥን ከቶ አልተናገርንም፥ እግዚአብሔርም እንደሚመሰክር እያመካኘን በመጕኦምጀት አልሠራንም፤ የክርስቶስም ሐዋርያት እንደ መሆናችን ልንከብድባችሁ ስንችል፥ ከእናንተ ቢሆን ወይም ከሌሎች ክብርን ከሰው አልፈለግንም። ነገር ግን ሞግዚት የራስዋን ልጆች እንደምትከባከብ፥ በመካከላችሁ የዋሆች ሆንን፤ እንዲሁም እያፈቀርናችሁ የእግዚአብሔርን ወንጌል ለማካፈል ብቻ ሳይሆን የገዛ ነፍሳችንን ደግሞ እናካፍላችሁ ዘንድ በጎ ፈቃዳችን ነበረ፥ ለእኛ የተወደዳችሁ ሆናችሁ ነበርና። ወንድሞች ሆይ፥ ድካማችንና ጥረታችን ትዝ ይላችኋልና፤ ከእናንተ በአንዱ ስንኳ እንዳንከብድበት ሌሊትና ቀን እየሠራን፥ የእግዚአብሔርን ወንጌል ለእናንተ ሰበክን።
1 ተሰሎንቄ 2:1-9 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ወንድሞች ሆይ! የእኛ ወደ እናንተ መምጣት ፍሬቢስ እንዳልሆነ እናንተ ራሳችሁ ታውቃላችሁ። እናንተ እንደምታውቁት ከዚህ ቀደም በፊልጵስዩስ በነበርንበት ጊዜ መከራና ስድብ ደርሶብናል፤ ነገር ግን ታላቅ ተቃውሞ ቢደርስብንም እንኳ ወንጌሉን ለእናንተ እንድናስተምር አምላካችን ድፍረትን ሰጥቶናል። እኛ የመከርናችሁ በስሕተት ወይም በርኩስ ዓላማ ተመርተን አይደለም፤ እናንተን ለማታለል ያደረግነው ምንም ነገር የለም። ይልቅስ እግዚአብሔር ወንጌሉን ለእኛ በዐደራ የሰጠን በእኛ ተማምኖ ስለ ሆነ እንናገራለን፤ ይህንንም የምናደርገው ልባችንን የሚመረምረውን እግዚአብሔርን ደስ ለማሰኘት ብለን ነው እንጂ ሰውን ለማስደሰት ብለን አይደለም። አንድም ጊዜ በቃላት በማቈላመጥ ወይም የገንዘብ ፍላጎት ኖሮን ከቶ እንዳልተናገርን እናንተ ራሳችሁ ታውቃላችሁ፤ እግዚአብሔርም ምስክራችን ነው። ከእናንተም ሆነ ከሌሎች ከማንም ሰው ክብርን አልፈለግንም። የክርስቶስ ሐዋርያት እንደ መሆናችን አስፈላጊውን ከእናንተ ለመጠየቅ እንችል ነበር፤ ነገር ግን ለልጆችዋ እንደምትጠነቀቅ እናት በገርነት በመካከላችሁ ተመላለስን። እንዲሁም በጣም ስለምንወዳችሁ የእግዚአብሔርን ወንጌል ለእናንተ ማብሠር ብቻ ሳይሆን ሕይወታችንንም እንኳ ልንሰጣችሁ ዝግጁዎች ነበርን። ወንድሞች ሆይ! እንዴት እንደ ሠራንና እንደ ደከምን ታውቃላችሁ፤ የእግዚአብሔርን ወንጌል ለእናንተ በምናበሥርበት ጊዜ በአንዳችሁም ላይ ሸክም እንዳንሆን ሌሊትና ቀን በመሥራት እንደክም ነበር።
1 ተሰሎንቄ 2:1-9 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ወንድሞች ሆይ! እናንተን መጎብኘታችን በከንቱ አልነበረም፥ እናንተም ራሳችሁ ታውቁታላችሁ። ነገር ግን እንደምታውቁት በፊልጵስዩስ አስቀድመን መከራንና እንግልትን ብንቀበልም እንኳ፥ በታላቅም ተቃውሞ ፊት የእግዚአብሔርን የምሥራች ቃል ለእናንተ ለመናገር በአምላካችን ድፍረትን አገኘን። ምክራችን ከስሕተት ወይም ከርኩሰት ከተንኰልም የመነጨ አልነበረምና፤ ነገር ግን ወንጌል በአደራ እንዲሰጠን እግዚአብሔር የታመንን እንዳደረገን፥ እንዲሁ ሰውን ደስ ለማሰኘት ሳይሆን ልባችንን የሚመረምረውን እግዚአብሔርን ደስ ለማሰኘት ብለን እንናገራለን። እንደምታውቁት፥ የቁልምጫን ቃል ለስግብግብነትም ማመካኛ የሚሆን ነገር ከቶ አልተገኘብንም፥ እግዚአብሔርም ምስክር ነው። እንዲሁም ከእናንተም ሆነ ከሌሎች ክብርን አልፈለግንም፥ ዳሩ ግን የክርስቶስ ሐዋርያት እንደ መሆናችን መጠን ልንጫናችሁ በቻልን ነበር፤ ነገር ግን ሞግዚት የራስዋን ልጆች እንደምትንከባከብ፥ በመካከላችሁ የዋሆች ሆንን፤ ስለዚህም እናንተን በፍቅር በመሻት የእግዚአብሔርን ወንጌል ብቻ ሳይሆን የገዛ ነፍሳችንን ደግሞ ለማካፈል በጎ ፈቃዳችን ነበረ፤ ምክንያቱም ለእኛ እጅግ የተወደዳችሁ ሆናችሁ ስለ ነበር ነው። ወንድሞች ሆይ! ድካማችንንና ጥረታችንን ታስታውሱታላችሁ፤ የእግዚአብሔርን ወንጌል ለእናንተ እየሰበክን በአንዳችሁም ላይ እንኳ ሸክም ላለመሆን ስንል ሌሊትና ቀን እንሠራ ነበር።