1 ሳሙኤል 8:4-22
1 ሳሙኤል 8:4-22 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
የእስራኤልም ሰዎች ሁሉ በአንድነት ተሰብስበው ወደ ሳሙኤል ወደ አርማቴም መጡ፤ እንዲህም አሉት፥ “እነሆ፥ አንተ ሸምግለሃል፤ ልጆችህም በመንገድህ አይሄዱም፤ አሁንም እንደ ሌሎች አሕዛብ ሁሉ የሚፈርድልን ንጉሥ አንግሥልን።” “የሚፈርድልን ንጉሥ ስጠን” ባሉት ጊዜም ነገሩ ሳሙኤልን አስከፋው፤ ሳሙኤልም ወደ እግዚአብሔር ጸለየ። እግዚአብሔርም ሳሙኤልን አለው፥ “በእነርሱ ላይ እንዳልነግሥ እኔን ናቁ እንጂ አንተን አልናቁምና በሚሉህ ነገር ሁሉ የሕዝቡን ቃል ስማ። ከግብፅ ካወጣኋቸው ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ እኔን ትተው እንግዶች አማልክትን በማምለካቸው እንደ ሠሩት ሥራ ሁሉ እንዲሁ በአንተ ደግሞ ያደርጉብሃል። አሁንም ቃላቸውን ስማ፤ ነገር ግን ጽኑ ምስክር መስክርባቸው፤ በእነርሱም ላይ የሚነግሠውን የንጉሡን ሥርዐት ንገራቸው።” ሳሙኤልም የእግዚአብሔርን ቃል ሁሉ ንጉሥን ለፈለጉ ሕዝብ ነገራቸው። እንዲህም አለ፥ “በእናንተ ላይ የሚነግሠው የንጉሡ ሥርዐት ይህ ነው፤ ወንዶች ልጆቻችሁን ወስዶ ሰረገላ ነጂዎችና ፈረሰኞች ያደርጋቸዋል፤ በሰረገሎችም ፊት ይሮጣሉ፤ ለራሱም የሻለቆችና የመቶ አለቆች የአምሳ አለቆችም ያደርጋቸዋል፤ እርሻውንም የሚያርሱ፥ እህሉንም የሚያጭዱ፥ ፍሬውንም የሚለቅሙ፥ የጦር መሣሪያውንና የሰረገሎቹንም ዕቃ የሚሠሩ ያደርጋቸዋል። ሴቶች ልጆቻችሁንም ወስዶ ሽቱ ቀማሚዎችና ወጥ ቤቶች፥ አበዛዎችም ያደርጋቸዋል። እርሻችሁንና ወይናችሁንም፥ መልካም መልካሙንም የዘይት ቦታችሁን ወስዶ ለሎሌዎቹ ይሰጣቸዋል። ከዘራችሁና ከወይናችሁም ዐሥራት ወስዶ ለጃንደረቦቹና ለሎሌዎቹ ይሰጣቸዋል። ሎሌዎቻችሁንና ገረዶቻችሁን፥ ከከብቶቻችሁና ከአህዮቻችሁም መልካም መልካሙን ወስዶ ያሠራቸዋል። ከላሞቻችሁ፥ ከበጎቻችሁና ከፍየሎችቻችሁም ዐሥራት ይወስዳል፤ እናንተም ባሪያዎች ትሆኑታላችሁ። በዚያም ቀን ለእናንተ ከመረጣችሁት ከንጉሣችሁ የተነሣ ትጮኻላችሁ፤ በእነዚያም ወራት እግዚአብሔር አይሰማችሁም። ለራሳችሁ ንጉሥ መርጣችኋልና።” ሕዝቡ ግን የሳሙኤልን ነገር ይሰሙ ዘንድ እንቢ አሉ፥ “እንዲህ አይሁን፤ ነገር ግን ንጉሥ አንግሥልን፤ እኛም ደግሞ እንደ አሕዛብ ሁሉ እንሆናለን፤ ንጉሣችንም ይፈርድልናል፤ በፊታችንም ወጥቶ ስለ እኛ ጠላታችንን ይዋጋል” አሉት። ሳሙኤልም የሕዝቡን ቃል ሁሉ ሰማ፤ ለእግዚአብሔርም ተናገረ። እግዚአብሔርም ሳሙኤልን፥ “ቃላቸውን ስማ፤ ንጉሥም አንግሥላቸው” አለው። ሳሙኤልም የእስራኤልን ሰዎች፥ “እያንዳንዳችሁ ወደ ከተማችሁ ሂዱ” አላቸው።
1 ሳሙኤል 8:4-22 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ስለዚህ የእስራኤል ሽማግሌዎች ሁሉ በአንድነት ተሰብስበው ሳሙኤል ወዳለበት ወደ አርማቴም መጡ። እነርሱም፣ “አንተ አርጅተሃል፤ ልጆችህ ያንተን ፈለግ አይከተሉም፤ ስለዚህ ሌሎች ሕዝቦች እንደሚያደርጉት ሁሉ የሚመራን ንጉሥ አንግሥልን” አሉት። ነገር ግን፣ “የሚመራን ንጉሥ አንግሥልን” ማለታቸው ሳሙኤልን አላስደሰተውም፤ ስለዚህ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፤ እግዚአብሔርም ሳሙኤልን እንዲህ አለው፤ “ንጉሣቸው እንዳልሆን የናቁት እኔን እንጂ አንተን አይደለምና ሕዝቡ የሚሉህን ሁሉ ስማ። ከግብጽ ምድር ካወጣኋቸው ዕለት አንሥቶ እስከ ዛሬ ድረስ እኔን ትተው ሌሎች አማልክትን በማምለክ ያደረጉትን ሁሉ በአንተም ላይ እያደረጉ ነው። አሁን የሚሉህን ስማቸው፤ በላያቸው የሚነግሠው ንጉሥ ምን እንደሚፈጽምባቸውም አሳውቃቸው፤ በሚገባም አስጠንቅቃቸው።” ሳሙኤልም የእግዚአብሔርን ቃል ሁሉ፣ ንጉሥ እንዲነግሥላቸው ለጠየቁት ሕዝብ ተናገረ። እንዲህም አለ፤ “በላያችሁ የሚነግሠው ንጉሥ የሚያደርግባችሁ ይህ ነው፤ ወንዶች ልጆቻችሁን ወስዶ ሠረገለኞችና ፈረሰኞች ያደርጋቸዋል፤ በሠረገሎቹም ፊት ይሮጣሉ። አንዳንዶቹን ሻለቆችና ዐምሳ አለቆች ያደርጋቸዋል፤ ሌሎቹን መሬቱን እንዲያርሱና እህሉን እንዲያጭዱ፣ የቀሩትን ደግሞ የጦር መሣሪያና ለሠረገላ የሚሆኑትን ዕቃዎች እንዲሠሩ ያደርጋቸዋል፤ ሴቶች ልጆቻችሁን ወስዶ ሽቱ ቀማሚ፣ ወጥ ሠሪዎችና እንጀራ ጋጋሪዎች ያደርጋቸዋል። ከዕርሻችሁ፣ ከወይንና ከወይራ ተክል ቦታዎቻችሁ ምርጥ ምርጡን ወስዶ ለባለሟሎቹ ይሰጣቸዋል። ከእህላችሁና ከወይናችሁ ከዐሥር አንዱን ወስዶ ለሹማምቱና ለባለሟሎቹ ይሰጣቸዋል። ወንድና ሴት አሽከሮቻችሁን እንዲሁም ምርጥ ከብቶቻችሁንና አህዮቻችሁን ለራሱ ያደርጋቸዋል። ከበግና ከፍየል መንጎቻችሁ አንድ ዐሥረኛውን ለራሱ ይወስዳል፤ እናንተ ራሳችሁም ባሪያዎቹ ትሆናላችሁ። ያም ቀን በደረሰ ጊዜ፣ ወዳችሁ ከመረጣችሁት ንጉሥ የተነሣ ትጮኻላችሁ፤ ነገር ግን በዚያ ቀን እግዚአብሔር አይመልስላችሁም።” ሕዝቡ ግን ሳሙኤልን መስማት እንቢ በማለት፤ እንዲህ አሉ፤ “አይሆንም፤ ንጉሥ እንዲነግሥልን እንፈልጋለን፤ እኛም እንደ ሌሎቹ ሕዝቦች የሚመራንና ከፊታችን የሚሄድ፣ ጦርነታችንንም የሚዋጋልን ንጉሥ ያለን ሕዝቦች እንሆናለን።” ሳሙኤልም ሕዝቡ ያለውን ሁሉ ሰማ፤ ያንኑ በእግዚአብሔር ፊት ተናገረው። እግዚአብሔርም፣ “የሚሉህን ስማቸው፤ ንጉሥም አንግሥላቸው” አለው። ከዚያም ሳሙኤል የእስራኤልን ሰዎች፣ “እያንዳንዳችሁ ወደ ከተማችሁ ተመለሱ” አላቸው።
1 ሳሙኤል 8:4-22 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
የእስራኤልም ሽማግሌዎች ሁሉ ተሰብስበው ወደ ሳሙኤል ወደ አርማቴም መጡና፦ እነሆ፥ አንተ ሸምግለሃል፥ ልጆችህም በመንገድህ አይሄዱም፥ አሁንም እንደ አሕዛብ ሁሉ የሚፈርድልን ንጉሥ አድርግልን አሉት። የሚፈርድልንም ንጉሥ ስጠን ባሉት ጊዜ ነገሩ ሳሙኤልን አስከፋው፥ ሳሙኤልም ወደ እግዚአብሔር ጸለየ። እግዚአብሔርም ሳሙኤልን አለው፦ በእነርሱ ላይ እንዳልነግሥ እኔን እንጂ አንተን አልናቁምና በሚሉህ ነገር ሁሉ የሕዝቡን ቃል ስማ። ከግብጽ ካወጣኋቸው ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ እኔን ትተው እንግዶች አማልክት በማምለካቸው እንደ ሠሩት ሥራ ሁሉ እንዲሁ በአንተ ደግሞ ያደርጉብሃል። አሁንም ቃላቸውን ስማ፥ ነገር ግን ጽኑ ምስክር መስክርባቸው፥ በእነርሱም ላይ የሚነግሠውን የንጉሡን ወግ ንገራቸው። ሳሙኤልም የእግዚአብሔርን ቃል ሁሉ ንጉሥን ለፈለጉ ሕዝብ ነገራቸው። እንዲህም አለ፦ በእናንተ ላይ የሚነግሠው የንጉሡ ወግ ይህ ነው፥ ወንዶች ልጆቻችሁን ወስዶ ሰረገለኞችና ፈረሰኞች ያደርጋቸዋል፥ በሰረገሎቹም ፊት ይሮጣሉ፥ ለራሱም የሻለቆችና የመቶ አለቆች ያደርጋቸዋል፥ እርሻውንም የሚያርሱ እህሉንም የሚያጭዱ የጦር መሣሪያውንና የሰረገሎቹንም ዕቃ የሚሠሩ ይሆናሉ። ሴቶች ልጆቻችሁንም ወስዶ ሽቶ ቀሚሚዎችና ወጥቤቶች አበዛዎችም ያደርጋቸዋል። ከእርሻችሁና ከወይናችሁም መልካም መልካሙን ወስዶ ለሎሌዎቹ ይሰጣቸዋል። ከዘራችሁና ከወይናችሁም አሥራት ወስዶ ለጃንደረቦቹና ለሎሌዎቹ ይሰጣቸዋል። ሎሌዎቻችሁንና ገረዶቻችሁን፥ ከከብቶቻችሁና ከአህዮቻችሁም መልካም መልካሞቹን ወስዶ ያሠራቸዋል። ከበጎቻችሁና ከፍየሎቻችሁ አሥራት ይወስዳል፥ እናንተም ባሪያዎች ትሆኑታላችሁ። በዚያም ቀን ለእናንተ ከመረጣችሁት ከንጉሣችሁ የተነሣ ትጮኻላችሁ፥ በዚያም ቀን እግዚአብሔር አልሰማችሁም። ሕዝቡ ግን የሳሙኤልን ነገር ይሰማ ዘንድ እንቢ አለ፦ እንዲህ አይሁን፥ ነገር ግን ንጉሥ ይሁንልን፥ እኛም ደግሞ እንደ አሕዛብ ሁሉ እንሆናለን፥ ንጉሣችንም ይፈርድልናል፥ በፊታችንም ወጥቶ ስለ እኛ ይዋጋል አሉት። ሳሙኤልም የሕዝቡን ቃል ሁሉ ሰማ፥ ለእግዚአብሔርም ተናገረ። እግዚአብሔርም ሳሙኤልን፦ ቃላቸውን ስማ፥ ንጉሥም አንግሥላቸው አለው። ሳሙኤልም የእስራኤልን ሰዎች፦ እያንዳንዳችሁ ወደ ከተማችሁ ሂዱ አላቸው።
1 ሳሙኤል 8:4-22 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከዚህ በኋላ የእስራኤል ማኅበር መሪዎች በአንድነት በመሰብሰብ ሳሙኤል ወደሚገኝበት ወደ ራማ መጥተው እንዲህ አሉ፦ “እነሆ! አንተ በእርጅና ላይ ነህ፤ ልጆችህም የአንተን መልካም አርአያነት አልተከተሉም፤ ስለዚህ በሌሎች አገሮች እንደሚደረገው እኛን የሚመራን ንጉሥ አንግሥልን።” ንጉሥ ያነግሥላቸው ዘንድ በመጠየቃቸውም ሳሙኤል አዝኖ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፤ እግዚአብሔርም ሳሙኤልን እንዲህ አለው፦ “ሕዝቡ የሚሉህን ነገር ሁሉ ተቀበል፤ እነርሱ የናቁት አንተን አይደለም፤ በእነርሱ ላይ ነግሼ እንዳልኖር፥ እነርሱ የናቁት እኔን ነው። እኔ እነርሱን ከግብጽ ካወጣሁበት ጊዜ ጀምሮ ፊታቸውን መልሰው ከእኔ በመራቅ ባዕዳን አማልክትን ሲያመልኩ ኖረዋል፤ እንግዲህ በእኔ ላይ ሲያደርጉት የነበረውን ሁሉ እነሆ በአንተም ላይ መፈጸም ጀምረዋል፤ ስለዚህ ከእንግዲህ ወዲህ የሚሉህን ተቀበል፤ ነገር ግን ንጉሦቻቸው ወደ ፊት በእነርሱ ላይ የሚፈጽሙባቸውን ነገር ሁሉ በመግለጥ በብርቱ አስጠንቅቃቸው።” ሳሙኤልም ንጉሥ እንዲያነግሥላቸው ለጠየቁት ሕዝብ እግዚአብሔር የነገረውን ሁሉ አስረዳቸው፤ እንዲህም ሲል ገለጠላቸው፤ “ንጉሣችሁ የሚያደርግባችሁ ነገር ይህ ነው፦ ልጆቻችሁን ወስዶ ሠረገለኞችና ፈረሰኞች ያደርጋቸዋል፤ አንዳንዶቹም በሠረገሎቹም ፊት የሚሮጡ ያደርጋቸዋል፤ ከእነርሱም አንዳንዶቹን የሺህ አለቆችና የኀምሳ አለቆች አድርጎ ይሾማል፤ ወንዶቹ ልጆቻችሁ የንጉሡ ሁዳድ አራሾችና መከር ሰብሳቢዎች ይሆናሉ፤ ሌሎችም የጦር መሣሪያና የሠረገላ ዕቃ ሠራተኞች ይሆናሉ። ሴቶች ልጆቻችሁም ለእርሱ ሽቶ አዘጋጀች፥ ወጥ ሠሪዎችና እንጀራ ጋጋሪዎች ይሆናሉ። ምርጥ የሆነውን የእርሻ መሬታችሁን፥ የወይን ተክል ቦታችሁንና የወይራ ተክላችሁን ሁሉ ወስዶ ለባለሟሎቹ ይሰጥባችኋል። ከእህላችሁና ከወይናችሁም ከዐሥር አንዱን እጅ ወስዶ ለቤተ መንግሥቱ ባለሟሎችና አጃቢዎች ይሰጥባችኋል። የወንድና የሴት አገልጋዮቻችሁን፥ ምርጥ ከብቶቻችሁንና አህዮቻችሁን ወስዶ ለራሱ መጠቀሚያ ያደርጋቸዋል። ከበግና ከፍየል መንጋዎቻችሁ ከዐሥር አንዱን ይወስዳል፤ እናንተም የእርሱ ባሪያዎች ትሆናላችሁ፤ ያ ዘመን በደረሰ ጊዜ የመረጣችሁት ንጉሥ ስለሚፈጽምባችሁ በደል በመረረ ሁኔታ ማጒረምረም ትጀምራላችሁ፤ እግዚአብሔር ግን አቤቱታችሁን አያዳምጥም።” ይሁን እንጂ ሕዝቡ ሳሙኤል ለነገራቸው ቃል ሁሉ ዋጋ አልሰጡትም፤ ይልቁንም “እንደዚህ አይደለም! እኛ ንጉሥ እንዲኖረን እንፈልጋለን፤ በዚህም ዐይነት ሌሎች ሕዝቦች እንደሚያደርጉት እኛን የሚያስተዳድርና ከጠላቶቻችንም ጋር በምንዋጋበት ጊዜ ወደ ጦር ሜዳ የሚመራን ንጉሥ ይኖረናል።” ሳሙኤልም እነርሱ ያሉትን ሁሉ አዳመጠ፤ ከዚያም ሄዶ ለእግዚአብሔር ነገረ፤ እግዚአብሔርም “እነርሱ በጠየቁህ መሠረት፥ ንጉሥ አንግሥላቸው” አለው፤ ከዚያም በኋላ ወደየቤታቸው እንዲሄዱ ሳሙኤል ሕዝቡን አሰናበተ።
1 ሳሙኤል 8:4-22 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ስለዚህ የእስራኤል ሽማግሌዎች ሁሉ በአንድነት ተሰብስበው ሳሙኤል ወዳለበት ወደ ራማ መጡ። እነርሱም፥ “አንተ አርጅተሃል፤ ልጆችህም በመንገድህ አይሄዱም፤ ስለዚህ ሌሎች ሕዝቦች እንደሚያደርጉት ሁሉ የሚመራን ንጉሥ አንግሥልን” አሉት። ነገር ግን፥ “የሚመራን ንጉሥ አንግሥልን” ማለታቸው ሳሙኤልን አላስደሰተውም፤ ስለዚህ ወደ ጌታ ጸለየ። ጌታም ሳሙኤልን እንዲህ አለው፤ “ንጉሣቸው እንዳልሆን የናቁት እኔን እንጂ አንተን አይደለምና ሕዝቡ የሚሉህን ሁሉ አድምጥ። ከግብጽ ምድር ካወጣኋቸው ቀን አንሥቶ እስከ ዛሬ ድረስ እኔን ትተው ሌሎች አማልክትን በማምለክ ያደረጉትን ሁሉ በአንተም ላይ እያደረጉ ነው። አሁንም የሚሉህን ስማ፤ ግን በላያቸው የሚነግሠው ንጉሥ ምን እንደሚፈጽምባቸውም አሳውቃቸው፤ በብርቱም አስጠንቅቃቸው።” ሳሙኤልም የጌታን ቃል ሁሉ፥ ንጉሥ እንዲነግሥላቸው ለጠየቁት ሕዝብ ተናገረ። እንዲም አለ፤ “በላያችሁ የሚነግሠው ንጉሥ የሚያደርግባችሁ ይህ ነው፤ ወንዶች ልጆቻችሁን ወስዶ ሠረገለኞችና ፈረሰኞች ያደርጋቸዋል፤ በሠረገሎቹም ፊት ይሮጣሉ። አንዳንዶቹን ሻለቆችና አምሳ አለቆች ያደርጋቸዋል፤ ሌሎቹን መሬቱን እንዲያርሱና እህሉን እንዲያጭዱ፥ ሌሎቹን ደግሞ የጦር መሣሪያና ለሠረገላ የሚሆኑትን ዕቃዎች እንዲሠሩ ያደርጋቸዋል። ሴቶች ልጆቻችሁን ወስዶ ሽቶ ቀማሚ፥ ወጥ ሠሪዎችና እንጀራ ጋጋሪዎች ያደርጋቸዋል። ከእርሻችሁ፥ ከወይንና ከወይራ ተክል ቦታዎቻችሁ ምርጥ ምርጡን ወስዶ ለባለሟሎቹ ይሰጣቸዋል። ከእህላችሁና ከወይናችሁ ከዐሥር አንዱን ወስዶ ለሹማምቱና ለባለሟሎቹ ይሰጣቸዋል። ወንድና ሴት አሽከሮቻችሁን እንዲሁም ምርጥ ከብቶቻችሁንና አህዮቻችሁን ለራሱ ወስዶ ያሠራቸዋል። ከበግና ከፍየል መንጎቻችሁ አንድ ዐሥረኛውን ለራሱ ይወስዳል፤ እናንተም ባርያዎቹ ትሆናላችሁ። ያም ቀን በደረሰ ጊዜ፥ ከመረጣችሁት ንጉሥ የተነሣ ትጮኻላችሁ፤ ነገር ግን በዚያ ቀን ጌታ አይመልስላችሁም።” ሕዝቡ ግን ሳሙኤልን መስማት እምቢ በማለት፥ እንዲህ አሉ፦ “አይሆንም፤ ንጉሥ እንዲነግሥልን እንፈልጋለን። እኛም እንደ ሌሎቹ ሕዝቦች የሚመራንና ከፊታችን የሚሄድ፥ ጦርነታችንንም የሚዋጋልን ንጉሥ ያለን ሕዝቦች እንሆናለን።” ሳሙኤልም ሕዝቡ ያለውን ሁሉ ሰማ፤ ያንኑ ለጌታ ተናገረ። ጌታም፥ “አድምጣቸው፤ ንጉሥም አንግሥላቸው” አለው። ከዚያም ሳሙኤል የእስራኤልን ሰዎች፥ “እያንዳንዳችሁ ወደ ከተማችሁ ተመለሱ” አላቸው።