1 ሳሙኤል 3:8-11
1 ሳሙኤል 3:8-11 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እግዚአብሔርም ሳሙኤልን እንደ ገና ሦስተኛ ጊዜ ጠራው። እርሱም ተነሥቶ ወደ ዔሊ ሄደና፥ “እነሆኝ ስለ ጠራኸኝ መጣሁ” አለ። ዔሊም እግዚአብሔር ልጁን እንደ ጠራው አስተዋለ። ዔሊም ሳሙኤልን፥ “ልጄ፥ ሄደህ ተኛ፤ ቢጠራህም፦ አቤቱ፥ ባሪያህ ይሰማልና ተናገር በለው፥” አለው። ሳሙኤልም ሄዶ በስፍራው ተኛ። እግዚአብሔርም መጥቶ ቆመ፤ እንደ ቀድሞውም ጠራው። ሳሙኤልም፥ “ባሪያህ ይሰማልና ተናገር” አለ። እግዚአብሔርም ሳሙኤልን አለው፥ “እነሆ የሰማውን ሁሉ ሁለቱን ጆሮዎቹን ጭው የሚያደርግ ነገሬን በእስራኤል ላይ አደርጋለሁ።
1 ሳሙኤል 3:8-11 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እግዚአብሔር ሳሙኤልን ለሦስተኛ ጊዜ ጠራው፤ አሁንም ሳሙኤል ተነሥቶ ወደ ዔሊ በመሄድ፣ “እነሆኝ የጠራኸኝ” አለው። ዔሊ በዚህ ጊዜ ብላቴናውን ይጠራ የነበረው እግዚአብሔር መሆኑን ተረዳ። በዚያ ጊዜ ዔሊ ሳሙኤልን፣ “ሂድና ተኛ፤ ከእንግዲህ ቢጠራህ ግን፣ ‘እግዚአብሔር ሆይ፤ ባሪያህ ይሰማልና ተናገር’ በል” አለው። ስለዚህም ሳሙኤል ወደ ስፍራው ተመልሶ ተኛ። እግዚአብሔርም መጥቶ በዚያ ቆመ፤ ቀደም ሲል እንዳደረገው ሁሉ “ሳሙኤል! ሳሙኤል!” ብሎ ጠራው። ሳሙኤልም፣ “ባሪያህ ይሰማልና ተናገር” አለ። እግዚአብሔርም ሳሙኤልን እንዲህ አለው፤ “እነሆ፤ የሰሚውን ሁሉ ጆሮ ጭው የሚያደርግ አንድ ነገር በእስራኤል ላይ አደርጋለሁ።
1 ሳሙኤል 3:8-11 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እግዚአብሔርም ሳሙኤልን እንደ ገና ሦስተኛ ጊዜ ጠራው። እርሱም ተነሥቶ ወደ ዔሊ ሄደና፦ እነሆኝ የጠራኽኝ አለ። ዔሊም እግዚአብሔር ብላቴናውን እንደ ጠራው አስተዋለ። ዔሊም ሳሙኤልን፦ ሄደህ ተኛ፥ ቢጠራህም፦ አቤቱ፥ ባሪያህ ይሰማልና ተናገር በለው አለው። ሳሙኤልም ሄዶ በስፍራው ተኛ። እግዚአብሔርም መጥቶ ቆመ፥ እንደ ቀድሞውም፦ ሳሙኤል ሳሙኤል ብሎ ጠራው። ሳሙኤልም፦ ባሪያህ ይሰማልና ተናገር አለ። እግዚአብሔርም ሳሙኤልን አለው፦ እነሆ፥ የሰማውን ሁሉ ሁለቱ ጆሮቹ ጭው የሚያደርግ አንድ ነገርን በእስራኤል አደርጋለሁ።
1 ሳሙኤል 3:8-11 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔርም እንደገና ለሦስተኛ ጊዜ ሳሙኤልን ጠራው፤ ሳሙኤልም ተነሥቶ ወደ ዔሊ በመሄድ “እነሆ! ስለጠራኸኝ መጥቻለሁ” አለው። ከዚህም በኋላ ሳሙኤልን ይጠራው የነበረው እግዚአብሔር መሆኑን ዔሊ ተገነዘበ፤ ስለዚህም “ወደ መኝታህ ተመልሰህ ሂድ፤ እንደገናም የጠራህ እንደ ሆነ ‘ጌታ ሆይ፥ እነሆ እኔ አገልጋይህ እሰማለሁና ተናገር’ በለው” ሲል ሳሙኤልን መከረው። ሳሙኤልም ተመልሶ ወደ መኝታው ሄደ። እግዚአብሔርም መጥቶ በዚያ ቆመ፤ ከዚያም በፊት ያደርግ በነበረው ዐይነት “ሳሙኤል! ሳሙኤል!” ብሎ ጠራው። ሳሙኤልም “ጌታ ሆይ! እነሆ አገልጋይህ እሰማለሁና ተናገር” አለው። እግዚአብሔር እንዲህ አለው፦ “እነሆ እኔ በእስራኤል ላይ አንድ ነገር የማደርግበት ቀን ተቃርቦአል፤ ያን ነገር በጆሮው የሚሰማው ሁሉ ይዘገንነዋል።
1 ሳሙኤል 3:8-11 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ጌታም ሳሙኤልን ለሦስተኛ ጊዜ ጠራው፤ አሁንም ሳሙኤል ተነሥቶ ወደ ዔሊ በመሄድ፥ “ስለ ጠራኸኝ እነሆ! መጥቻለሁ” አለው። ዔሊም በዚህ ጊዜ ሳሙኤልን ይጠራ የነበረው ጌታ መሆኑን ተረዳ። ስለዚህም ዔሊ ሳሙኤልን፥ “ሂድና ተኛ፤ ከእንግዲህ ቢጠራህ ግን፥ ‘ጌታ ሆይ፤ አገልጋይህ ይሰማልና ተናገር’ በል” አለው። ሳሙኤልም ወደ ስፍራው ተመልሶ ተኛ። ጌታም መጥቶ በዚያ ቆመ፤ ቀደም ሲል እንዳደረገው ሁሉ “ሳሙኤል! ሳሙኤል!” ብሎ ጠራው። ሳሙኤልም፥ “አገልጋይህ ይሰማልና ተናገር” አለ። ጌታም ሳሙኤልን እንዲህ አለው፤ “እነሆ፤ የሰሚውን ጆሮ ሁሉ ዝግንን የሚያደርግ አንድ ነገር በእስራኤል ላይ አደርጋለሁ።